ሆሣዕና በአርያም!

ከመምህር ጌራ ሞገስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን። በባሕርዩ ሞት በመንግሥቱ ሽረት የሌለበት፤ አንድነቱን ሦስትነቱ የማይከፋፍለው ሦስትነቱን አንድነቱ የማይጠቀልለው ለዘለዓለም አንድ ሲሆን ሦስት ሦስት ሲሆን አንድ እየተባለ የሚመሰገን እግዚአብሔር አምላክ ወዶና ፈቅዶ እንኳንም ለ ፳፻፲፰ ዓ.ም በዓለ ሆሣዕና በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ።

ሆሣዕና

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከዘለዓለማዊ ሞት የማዳን ሥራውን ለመፈጸም ጥቂት ቀናት ሲቀሩት በነቢያት የተነገረው ትንቢትና በብሉይ ኪዳን የነበረው ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ በአህያይቱና በውርንጫው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱና ብዛት ያለው ሕዝብ ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ በመዘመር ሰማያዊ አዳኝ መሆኑን መስክረው ተቀብለውታል። ሆሣዕና ቃሉ የአረማይክ ሲሆን ትርጉሙም አሁን አድን ማለት ነው፡፡

የሆሣዕና በዓል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትሕትና ንጉሥነት እና የድል ጉዞ የምናስብበት ታላቅ ዕለት ነው። ይህ በዓል በታሪክ ውስጥ የተከናወነ ድርጊት ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ላለንበት ዘመንና ሕይወት ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉም አለው።

ሆሣዕናን እና ያለንበትን ዘመን በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ማየት እንችላለን፦

. ትሕትና እንደ መሪነት መገለጫ

በዓለ ሆሣዕና የዓለምን የሥልጣንና የክብር ትርጉም የለወጠ ዕለት ነው። በወቅቱ የነበሩ ነገሥታት በፈረስና በሰረገላ፣ በጦር መሣሪያ ታጅበው ለጦርነትና ለግርማ ሞገስ ሲወጡ፣ የሰላሙ ንጉሥ ግን በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ መጣ።

 “ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሏት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።” (ማቴዎስ ፳፩፥፬-፭) ፤ ዘካርያስ ፱-፱)

በዘመነ ብሉይ የነቢያቱ ትርኢት ትርጓሜ ወንገል እነደሚነግረን ዘመኑ ሰላም ሲሆን ነቢይ ወደ ሕዝብ አደባባይ የሚሔደው በአህያ ላይ ተጭኖ ነበር፤ ዘመኑ እራኤላውያንን እግዚአብሔር ቆጥቷቸው የጦርነት በር የሚከፈትባቸው እንደሆነ ግን በፈረስ ላይ ተቀምጠው በግልቢያ ነበር የሚከሰቱት፤ የሰላም አለቃ የተባለው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥቃይ፣ የመከራ፣ የሰቀቀን ፣ የዋየታ በአጠቃላይ የዲያብሎስ ምርኮ የሆነበት የብሉይ ኪዳን ዘመን አከተመ፤ የሰላም፣ የዕረፍት፣ የሐሴትና የነፃነት ዘመን ተወጠነ ሲል በአህያ ላይ ተቀምጦ መጣ።

ለዘመናችን ትምህርት፦ በዚህ በትዕቢትና በፉክክር በተናወጠ ዓለም ውስጥ፣ እውነተኛ ታላቅነት የሚገኘው በትሕትናና ሌሎችን በማገልገል እንደሆነ ያስገነዝበናል።

. የልብን ምንጣፍ ማንጠፍ (እውነተኛ አምልኮ)

በዓለ ሆሣዕና ሕዝቡ ልብሳቸውንና የዘንባባ ዝንጣፊዎችን በመንገዱ ላይ አነጠፉ። ዛሬ ደግሞ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው የውጭ ልብስን ሳይሆን፣ የልባችንን መከፈትና ንስሐን ነው።

 “ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ዝንጣፊዎችን እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር።” (ማቴዎስ ፳፩፥፰)

ለዘመናችን ትምህርት፦ ጌታ ወደ ሕይወታችን እንዲገባ የልባችንን ዙፋን ልንሰጠው ይገባል። በይሉኝታና በዘልማድ ብቻ ሳይሆን፣ ውስጣዊ ማንነታችንን ለእርሱ ማስገዛት ይጠበቅብናል።

. “ሆሣዕና” – የድኅነት ጩኸት

“ሆሣዕና” ማለት “አሁን አድን” ማለት ነው። በወቅቱ የነበሩ ሕዝቦች ጌታን የተቀበሉት እንደ ፖለቲካ ነፃ አውጪ ቢሆንም፣ እርሱ ግን የመጣው ከኃጢአትና ከዘለዓለም ሞት ሊያድነን ነው።

 “የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።” (ማቴዎስ 21፡9)

ለዘመናችን ትምህርት፦ ዓለማችን በጦርነት፣ በበሽታና በጭንቀት በታወከችበት በዚህ ዘመን፣ የእኛም ጩኸት “ሆሣዕና – ጌታ ሆይ አሁን አድነን!” ሊሆን ይገባል። እውነተኛ ሰላም ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር ብቻ እንደሚገኝ ማመን አለብን።

. የማይለወጥ አቋም (ጽናት)

በሆሣዕና ዕለት “ሆሣዕና” ያሉ ብዙዎች፣ ይሁኑ እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሆሣዕና ብለው ባመሰገኑበት አንደበት “ስቀለው!” በማለት ሲጮኹ ታይተዋል። ይህም የሰው ልጅን ጠባይና የዘመናችንን ክዳት ያሳያል።

ለዘመናችን ትምህርት፦ እምነታችን በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ነገሮች ሲመቻቹ የምናመሰግን፣ ሲከፉ ደግሞ የምናማርር መሆን የለብንም። እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል።

ሲጠቃለል ሆሣዕና የሰላም ንጉሥ ወደ ልባችንና ወደ ቤታችን የሚገባበት በዓል ነው። ዛሬም ጌታ በደጃችን ቆሞ ያንኳኳል። እኛም እንደ ኢየሩሳሌም ሕዝብ በደስታ ተቀብለን፣ በሕይወታችን ላይ እንዲነግሥ በመፍቀድ፣ ክርስቶስን መስለን ልንኖር ይገባል።

ወስብሐት ለእግዘአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን

መልካም የሆሣዕና በዓል!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *