«መጽአ ኀበ እግዚእ ኢየሱስ ቀዲሙ ሌሊተ፣ አስቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታ ኢየሱስ መጣ።»

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ቁጥር አንድ (፫፥፩) ላይ ይህንን ሃሳብ እናገኛለን፡፡ በዚህ ርዕስ ማን እንደመጣ፣ ለምን እንደመጣ እንመለከታለን፡፡ የመጣው በምዕራፉ መጀመሪያ ላይ እንደምናገኘው ኒቆዲሞስ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ፡- የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሦስት ገልጠን ስናነብ «ከፈሪሳውያን ወገን የነበረ የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፡፡» እያለ ስሙ እስከነ ወገኑና ሙያው ይነግረናል፣ ወገኑን የመግለጡ ነገር ለምን ይሆን ብለን ከጠየቅን ቀጥሎ   «በሌሊት ወደ ጌታ መጣ።» የሚለው ነውና በምን ዓይነት አኳኋን ወደጌታ መምጣቱ፣ ያለበትን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጫና እንድንረዳ ነው።

ከፈሪሳውያን ወገን መሆኑን ብቻ የነገረን ሳይሆን የእነርሱ አለቃቸው እንደሆነም ጭምር ሲገልጥልን፣ ሊቃውንት ሲበይኑት ምሁረ ኦሪት (ዮሐ. 3፥10) እንዲሁም ባዕለ ጸጋ መሆኑን ያስረዳሉ።

አንድምታ ወንጌል «በሌሊት ወደ ጌታ ኢየሱስ መጣ» የሚለውን«ከመዓልት ከሚመጡት አስቀድሞ»፣ አንድም « ከማመን አስቀድሞ» የሚለውን አስቀድሞ በማለት የኒቆዲሞስ የአመጣጥ ሁኔታውን ይነግረናል።

ኒቆዲሞስ ቀድመን እንዳየነው ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ ሰው ነው፤ የአይሁድ የሸንጎ ዳኛ ነው፤ ስለሆነም ከፈሪሳውያን ወገን እንደመሆኑ ፍርሀት አለበት፤ የአይሁድ የሸንጎ ዳኛ እንደመሆኑ ቀን ቀን የዳኝነት ሥራው በችሎት ሲፈርድ፣ ሕግ ሲያወጣ ሲያረቅ፣ ሲያስፈጽም፣ ሲያስታርቅ… ይውላል፤ ያለው ብቸኛ አማራጭ ደግሞ የሌሊት ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም ነውና ሌሊት ከሰማያዊ ዳኛ፣ ንጉሥ፣ ባእለ ጸጋ ኢየሱስ ዘንድ ሊማር ወስኖ ተነሣ።

«ሀቡ ዘቄሳር ለቄሳር ወዘእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር፤ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ።» እንዳለው ጌታ በወንጌሉ (ማቴ. ፳፪፥፲፯) ለሥራው፣ ለአመራሩ የሚገባ ጊዜ ከሰጠ በኋላ ለመንፈሳዊ ሕይወቱ (ለእግዚአብሔር) መስጠት ያለበትን ጊዜ መስጠቱን እንገነዘባለን፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያንም ኒቆዲሞስን « የማታ ተማሪ፤ Extension» በማለት ይጠሩታል፤ ይህም ማለታቸው ከዘመናችን በማስተያየት ነው። ይህንን ንጽጽር የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ልብ ልትሉት የሚገባ ነጥብ ነው፤ ምክንያቱም ቀን ቀን አመዛኙ ጊዜያችሁን ለአስኳላ ትምህርታችሁ ትሰጣላችሁ፣ የሌሊት ጊዜያችሁ ደግሞ ለመንፈሳዊ ሕይወታችሁ ለሆነው ለቃለ እግዚአብሔርና ለመንፈሳዊ አገልግሎት ትሰጣላችሁና ነው።

በዚህ ልክ ጊዜያችንን ከፋፍለን የማንጠቀም ከሆነ ግን ሙሉ ሰው አንሆንም ማለት ነው። ምክንያቱም ምሉዕነት የሚገኘው ቢያንስ ፈቃደ ሥጋ ከፈቃደ ነፍስ በተዐቅቦ(በመጠባበቅ) መኖር ሲችሉ፣ ቢቻል ግን በፍጹምነት ሥጋ በነፍስ ግዛት ሥር ሆና መኖር ስትችል ነውና፡፡

በሌሊት የሚመሰሉት

አንደኛ ዘመነ ብሉይ ነው፤ ” ከግላ ኦሪት አልተላቀቀም…” እንዲል አንድምታ ወንጌል፣ ሌሊት ማለት የተከደነ የተሸፈነና ጨለማ ማለት አንደሆነ ይታወቃል። “ገለወ/ሸፈነ” እንደሚለውም “ግላ” ማለት የተከደነ የተሸፈነ ማለት ነው፤ መሸፈኑም መከደኑም አልያም ጨለማነቱም ሰው በበደሉ ምክንያት የጨለማ ገዥ በሆነው በዲያብሎስ ግዞት ሥር “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፣ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ፤ አዳም የዲያብሎስ ወንድ ባርያ ሔዋን የዲያብሎስ ሴት ባርያ” በመሆኑና የጨለማ ሥራ እየሠራ ከአምልኮተ እግዚአብሔር መለየቱ ነው። በወቅቱ ኃጢአት በምድር ላይ በምልዐት ሆነ [ኵሉ አረዩ ወኅቡረ አለው…፤ ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም” እንዲል ዳዊት በመዝሙሩ (መዝ. ፲፬፥፫) በፍዳ የተያዝንበት ወቅት ነበረ።

“ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ወጽላሎተ ሞት ብርሀን ዐቢይ ሠረቀ ላዕሌሆሙ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው።” (ኢሳ. ፱፥፪፣ ማቴ. ፪፥፲፬-፲፮) እንደ ተባለው ጨለማ የተባለው ዘመነ ብሉይ ታላቅ ብርሀን በተባለው በዘመነ ሐዲስ ተተካ፣ “በሌሊት ይደምፅ ብካይ ወበጽባሕ ፍሥሐ፤ ልቅሶ ማታ ይመጣል፥ ጠዋት ግን ደስታ ይሆናል።” (መዝ. ፴፥፭)

በብሉይ ልቅሶ ነበር፤ ” ነባይነ ነባይነ ከመ ዘኢነባይነ ኮነ፤ ጮህን ጮህን እንዳልጮህን ሆንን” እንዲል የገዐር የጩኸት ዘመን ነበር።

በሌሊት ትግል አለ። አበው ብሕትውናን ሲገልጹት “ግርማ ሌሊቱን ፀብአ አጋንንቱን ታግሰው” እንዲሉ ትግል፣ ፍርሃት፣ እንግልት፣ ሥቃይ… ያለው በሌሊት ነው። ለዚህ ነው ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ሲታገል እግዚአብሔር “ሊነጋ አቅላልቶአልና ልቀቀኝ።” ያለው (ዘፍ. ፴፪፥፳፮) ሌሊት የተባለው እንደ ጥንቱ ትርጓሜ መጽሐፍ ዘመነ ብሉይን ነው፤ ኒቆዲሞስም ገና በሕገ ኦሪት ሳለ መዓልት ወንጌልን ሳያይ በፈሪሳውያን የጭንቅ ሕግ ቀንበር ላይ እያለ ነው ወደ ጌታ የመጣው።

ሁለተኛ አለማወቅን ነው። ኒቆዲሞስ የሐዲስ ኪዳን ትምህርት ሳይማር ሳይረዳ ለመማር ወደመምህር መጣ። በዚህም የተነሳ የሐዲስ ኪዳን መመስረቻ የሆነውን ምሥጢረ ጥምቀትን ተማረ።

ሦስተኛ ይህንን ዓለም ነው። ምድራዊ ሕይወት የቀቢጸ ተስፋ፤ የተስፋ መቁረጥ ጨለማ የሰፈነበት፣ የፈተና እንቅፋት የተቀመጠበት በመሆኑ በሌሊት ይመሰላል። በሌሊት የሚሄድ ሰው እንደሚሰናከል እንደዚሁ በዚህ ዓለም መሰናክል አለ። ክርስቲያን ደግሞ እነዚያ መሰናክሎችን አልፎ ነው በጌታ፣ በቀንና በብርሀን በተመሰለው በመንግሥተ ሰማይ ከክርስቶስ ጋራ መቆም የሚችሉት።

አራተኛ አለማመንን ነው። አለማመን ጨለማ(ሌሊት) ነው፤ ማመን ደግሞ ብርሀን(ቀን) ነው፤ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም ልጅነት በምታሰጥ ጥምቀት አጠቃላይ በሐዲስ ኪዳን ትምህርት ከማመኑ በፊት በኦሪት እምነት እያለ መጥቷልና።

አምስተኛ መከራ ነው። ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገንና የአይሁድ አለቃ እንደመሆኑ ወደ ጌታ ዘንድ መሄድ ለእርሱ ሕጉ እጅግ ይበረታበታል፤ ማለትም አይሁድ በሸንጓቸው በመካከላቸው ወደጌታ ኢየሱስ ዘንድ የሚሄድ ሰው ቢኖር ከምኩራብ እንዲሰደድ የሚል ድንጋጌ ስለደነገጉ ማለት ነው፤ እርሱ ደግሞ የሸንጎው ዳኛ እንደመሆኑ ሕጉ ይጸናበታልና ነው። በዚህም እኛ የምንማረው በመከራ፣ በኃዘን፣ በችግር ሳለን መፍትሔ ወደሚሰጠን ጌታ ዘንድ መሄድ እነዳለብን ነው

ኢየሱስ: – “ወንጌል ክርስቶስ፣ ክርስቶስ ተስፋ፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት” እንዲል አንድምታ ወንጌል፣ ንጋት የተባለው ወንጌል ያየንበት ሌሊት ብሉይን ያመለጥንበት እርሱ ኢየሱስ “ፀሐየ ጽድቅ” ነው። አካላዊ ቃል፣ መለኮትና ሥጋ በተዋሕዶ ለድኅነተ ዓለም ሰው ሆኖ በተገለጠ ጊዜ ኒቆዲሞስን ሲያገኘው አዲስ ሥርዓት ምሥጢረ ጥምቀትን (ረቂቅ ልደትንና) ሰማያዊ ዕውቀትን አስተማረው።

ይህንን ሰማያዊ ጥበብ እንደሚያስተምረውም አውቆ የአይሁድ መምህር ኒቆዲሞስ ተደብቆ “በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጣ” አለ።

“መጣ” አለ ከልቡ ጽድቅን ሽቶ አእምሮ በሚሰበሰብበት ጊዜ ሌሊት መጥቷልና፤ በፍጹም ትሕትና ሊሰግድለት መጥቷልና፤ ሥጋዊውን ምስፍና አቃሎ ለአገልጋይነት መጥቷልና፤ ለምስክርነት መጥቷልና፤ “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።” እንዲል ወንጌሉ መስክሮለታል (ዮሐ. ፫፥፪) በዚህም ክርስቶስ “እውነተኛ መምህር” እንደሆነ አስረዳን።

“ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ መጣ” ሲል ገንዘብን፣ ሥልጣንን ወይም ሌላ ምድራዊ ጥበብን ፈልጎ ሳይሆን ሰማያዊ ሀብትን ብቻ ፈልጎ ስለመጣ አመጣጡ ልዩ ያደርገዋል። ወደኋላም ባለመመለስ ምድራዊ ሹመትን፣ ሽልማቱን ዝናውን ሁሉ ጥሎ እስከ መስቀል ታምኖ ከዮሴፍ ጋር የጌታችን ቅዱስ ሥጋውን ገንዟል። “…ዮሴፍ ወኒቆዲሞስ ገነዝዎ ለኢየሱስ፤ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ኢየሱስን ገነዙት” እንዲል (ዮሐ ፲፱፥፴፰-፴፱)

“ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና።” 2ኛ ጢሞ. 4፥2 እንዳለው እናንተ የግቢ ተማሪዎች ኒቆዲሞስን አብነት አድርጋችሁ የጥበባት ሁሉ ምንጭ የሆነው ዕውቀት የሰጣችሁ እንዲሁም የሚሰጣችሁ አምላካችንን ፈልጋችሁ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መምጣት ይኖርባችኋል፤ ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ሲሆን ፍጹም ዕውቀት የሚገኘው ከአምላክ እንደሆነ ዐውቆ መጥቷልና። በመምጣቱም ሳይንስ በላቦራቶሪና በምጡቅ ቴክኖሎጂው ፈላስፋዎች ደግሞ በፍልስፍናቸው የማይደርሱበት የዳግም ልደት ምሥጢርን ገለጠለት።

ምሁራን እንደሚያስረዱን የእውቀት ምንጭ /source of knowledge የሚባሉት ሦስት ናቸው። እነዚህም ሳይንስ፣ ፍልስፍና እና ቲኦሎጂ ሲሆኑ ከሁሉ የሚበልጠው ደግሞ የነገረ መለኮት ትምህርት ነው። ምክንያቱም ሳይንስና ፍልሰፍና የሚመረምሩት በአምስቱ የስሜት ሕዋሳቶች ተመርምረው የሚደረስባቸውን ብቻ ነው፤ ማለትም ግዑዙን ዓለም ብቻ ነው፣ ሥጋን እንጂ ነፍስን፣ መንፈስን ፣መልአክንና አምላክን መመረመር አይችልም፤ ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ስለ ምድር እንጂ ስለሰማይ መረዳት አይችልም፤ ስለ ምድራዊውም ቢሆን ያለው መረዳትና ግንዛቤ ተከፍሎ/partiality አለበት፤ ቋሚ መረዳት የለውም፤ ዥዋዥዌ ሆኖ ሁሌ ይዋዥቃል። ጥናቱም ሲሰራ አንዱ በጥናቱ ያገኘውን ግኝት/finding ሌላው አጥኚ እንደገና አጥንቶ ሊያፈርሰው ይችላል። ጥናትን የሚያፈርስ ጥናት/antithesis ይሠራል።

ፊሎሶፊም ቢሆን ከሳይንስ አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ሜታፊዚክስ/metaphysics በሚለው ዘርፍ ውስጥ ከቁስ ወጪ ያሉትን አጠናለሁ ቢልም የሚያጠናበት መሣሪያው በቦታ የሚወሰንና ገደብ ያለበት የሰው አእምሮ በመሆኑ የሚወሰን አካል/finite being ለማይወሰን አካል/ infinite being መመርመር አይችልምና ከሚታየው ዓለም ውጪ አልፎ ረቂቁን መገንዘብ አይችልም።

ነገረ መለኮት ግን የዕውቀቱ መሠረት ራሱ እግዚአብሔር ሆኖ በመገለጥ(revelation) ሥርዓት ስለሆነ ምንም የሚሠወር ነገር አይኖረውም። ግዑዙ ረቂቅን መመርመር ቢያቅተው እንጂ ረቂቁ ግዑዝ አካልን መመርመር አይሳነውምና፤ አምላክ በዕውቀት ተከፍሎ የሌለበት ሁሉን አዋቂ/ omniscient ነውና፤ ሁሉን አዋቂ አምላክ ደግሞ ለሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ ዕውቀትን ሲገልጥ ቆይቷል። ሐዋርያው በዕብራውያን መልእክቱ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤» እንዳለ።

ሁለት ዓይነት መገለጥ መኖሩን የነገረ መለኮት ምሁራን ያስቀምጣሉ የመጀመሪያው ዓቢይ መገለጥ (general revelation) ሲሆን የሁለተኛው ንኡስ መገለጥ (specific revelation) ይባላል። ንኡስ መገለጥ የሚባለው «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ።» ያለውን ሲሆን፤ ዓቢይ መገለጥ የሚባለው ደግሞ «ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤» የሚለው ነው። በዚህ በሁለቱ መገለጥ ሳይንስና ፍልስፍና በእውናቸው ይቅርና በሕልማቸው የማያስቡት ምሥጢር ተገልጧል።

 በመሆኑም ያላችሁን ጊዜ በአግባቡ ተጠቅማችሁ መንፈሳዊ ዕውቀትን ልትቀስሙ ኒቆዲሞስንም አብነት በማድረግ በግቢ ጉባኤ አገልግሎት ሱቱፋን ሆናችሁ መገኘት ይኖርባችኋል።

ወርኃ መጋቢት ፳፻፲፰ ዓ/ም

መ/ር አበበ ፍቅሬ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *