ጾመ ሰብአ ነነዌ

ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ለሦስት ቀን የጾሙት ጾም ነው፡፡ የነነዌ ከተማ በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትሆን መሥራቿም ናምሩድ ነው (ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪)፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የሆነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶ ነበር (ዮናስ ፬፥፲፩)፡፡

በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኃጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢዩ ዮናስን የስሙ ትርጓሜ ርግብ የሆነ ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሓ እንዲገቡ ወደ ነነዌ ከተማ (ሕዝብ) ላከው (ሉቃ. ፲፩፥፴)፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፤ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ በዚያን ጊዜ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢት ተናገረ (፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩)፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል (፩ኛነገ.፲፯፥፲፱)፡፡

እግዚአብሔር አምላክም ሔደህ በነነዌ ላይ ስበክ ባለው ጊዜ ነቢዩ ዮናስ አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ ብሎ የተባለውን ባለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔርም ነቢዩ ዮናስ በመርከብ ሳለ ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ዮናስ ግን በመርከቧ በታችኛው ክፍል እንቅልፉን ተኝቶ ያንኳርፍ ነበር፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ጀመሩ፡፡ የመርከቡም አለቃ ወደ ዮናስ ቀርቦ “ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ” አለው፡፡ (ዮናስ ፩፥፮) ተሳፋሪዎቹም ተጨንቀው ይህ ነገር ያገኘን በማን ምክንያት ነው?  ብለው ዕጣ ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በነቢዩ ዮናስ ላይ ወደቀ፡፡

ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለሆነ ንብረታችሁን ሳይሆን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ” በማለት ተማጸናቸው፡፡ እነርሱም ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይሆንም አሉ፡፡ ነገር ግን ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜ ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን ዋጠው፤ እግዚአብሔርበበዓሣ አንበሪውም ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አድርሶ በየብስ ላይ ተፋው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ሆድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል (ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪)፡፡

የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዮናስ መጣ፡፡ “ተነሥተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ፤ የነገርኩህንም የመጀመሪያውን ስብከት ስበክላት” አለው፡፡ ነቢዩ ዮናስም “በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” እያለ ሰበከ፡፡ (ዮናስ ፫፥፩)፡፡ የነነዌ ሰዎችም እግዚአብሔርን አመኑ፤ ።ጾምም ዐዋጅ ነገሩ፤ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ፡፡ ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጎናጸፊያውን አወለቀ፤ ማቅም ለበሰ፤ በአመድም ላይ ተቀመጠ፤ ሰዎችና እንስሳትም አንዳች እንዳይቀምሱ ውኃም እንዳይጠጡ ዐዋጅም አስነገረ፡፡ (ዮናስ ፫)

ዮናስ ግን ፈጽሞ አዘነ፣ ተከዘም፡፡ ምነው ቢሉ፡- ነቢዩ ዮናስ የእግዚአብሔር መሐሪነት፣ ቸርነቱም የበዛ እንደሆነ አውቋልና ቁጣውን በምሕረት እንደሚለውጥ ስለተረዳ “ሐሰተኛ ነቢይ እባላላሁ” በማለት ተበሳጨ፤ ከከተማይቱም ወጣ፡፡ ከፀሐዩ ግለት ይሸሸግ ዘንድ ጥጉን ያዘ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ቅሉን አዘዘለትና ከዮናስ ራስ ላይ ጥላ ትሆነው ዘንድ ከፍ ከፍ አደረጋት፡፡ ዮናስም ስለቅሊቱ ደስ አለው፡፡ ነገር ግን በነጋ ጊዜ እግዚአብሔር ትልቁን ትል አስነሥቶ ቅሊቱን መታ ቅሊቱም ወዲያው ደረቀች፡፡ ዮናስንም ፀሐዩ መታው፡፡ ተስፋ ቆርጦም “ከሕይወት ሞት ይሻለኛል” አለ፡፡

ቅጠሉ በመድረቁ ዮናስ ባዘነ ጊዜ እግዚአብሔር አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለሆኑ ያሳዝኑኛል” በማለት ነቢዩ ዮናስን ተናገረው፡፡ ውሸታም ላለመባል መኮብለሉም ስሕተት መሆኑን አስረድቶታል፡፡

ነቢዩ ዮናስ ሐሰተኛ እንዳይባልም ከሰማይ የወረደው እሳት እንደ ደመና ሆኖ ከላይ የታላላቅ ዛፎች ቅጠል እስኪጠወልጉ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሓቸው በከንቱ እንዳልቀረም አስረድቷቸዋል (ትንቢተ ዮናስ)፡፡ በሦስት ቀን ሱባኤም በንስሓ ተመልሰዋልና እግዚአብሔር ሊያመጣ ካለው መቅሰፍት አድኗቸዋል፡፡

ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው፡፡ ይኸውም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል፡፡ ዮናስ ለስብከት ፈቃደኛ ባይሆን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ እንዲሔድ አድርጎታል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አይደለም፤ እርሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ የነነዌ ሰዎች የተነሳሕያን ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ሆኑ ያሳዝኑኛል›› ያለው፡፡

ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀልን እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን፣ ጸልየን ከኃጢአታችን እንነጻ ዘንድ ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኃጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለችበት ወቅት እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለ ሆነ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ፤›› ይለናል፡፡

ስለሆነም በነቢዩ ዮናስ ላይ የተደረጉ ተአምራትንና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመሆኑን በማስተዋል፣ ለነነዌ ሰዎች የወረደውን ምሕረት በመገንዘብ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለሃይማኖት አባቶች እና ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል፡፡ ስንጾምም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶ በኃጢአት ለጠፋው ዓለም ይቅርታውን ይልካል፡፡ በመጾማችን ራሳችን ከመዓትና ከመቅሠፍት ከመዳናችን ባሻገር በእኛ በደል ምክንያት አገራችን፣ ዕፀዋቱና እንስሳቱም ሳይቀር ከድርቅና ከቸነፈር ይተርፋሉና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *