ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል
ከመምህር ተስፋሚካኤል ታደለ
በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እና በመጻሕፍት ውስጥ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል አገልግሎትና አማላጅነት በብዙ ቦታዎች ላይ ተገልጿል። «ዑራኤል» የሚለው ስም ትርጉሙ «ብርሃነ እግዚአብሔር፣ የእግዚአብሔር ብርሃን” ማለት ሲሆን፣ እርሱ በብርሃናት ሁሉ ላይ የተሾመ፣ የፍርሃትና የረዓድ መጽናኛ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ጥበብና ምሥጢር ለወዳጆቹ የሚገልጥ ታላቅ መልአክ ነው።
ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል በሥነ ፍጥረት ሕግጋትና በሰማያዊ ብርሃናት ዑደት ላይ የሠለጠነ መልአክ ነው። በመጽሐፈ ሔኖክ (በተለይም ከምዕራፍ ፳፩ እስከ ፳፭ ባሉት ክፍሎች) እንደተገለጸው፣ ቅዱስ ዑራኤል «በብርሃናት ላይ ሁሉ የተሾመ» (ሄኖክ ፮፥፪) እና የሰማይ አካላት ያለ አንዳች መዛነፍ በፈጣሪ በተሰጣቸው ሥርዓት መሠረት እንዲጓዙ የሚመራ ነው።
ነቢዩ ሄኖክ በመልአኩ ቅዱስ ዑራኤል መሪነት የሰማያትን ሥርዓት፣ የፀሐይንና የጨረቃን ጉዞ፣ የከዋክብት መውጫና መግቢያ መስኮቶችን እንዲሁም በምድር ላይ የሚነፍሱትን ፲፪ የነፋሳት ዓይነቶች ተመልክቷል። የሰማይ ብርሃናት በየሥልጣናቸው፣ በየዘመናቸውና በየመውጫቸው በሚመላለሱበት ጊዜ ሁሉ የመልአኩ ጥበቃና መሪነት አይለያቸውም።
ጨረቃ ብርሃኗን ከፀሐይ እየተቀበለች በየወሩ በመስኮቷ እየወጣችና እየገባች ጊዜያትንና ወራትን እንድትቆጥር፣ ከዋክብትም በየስሞቻቸውና በየክፍላቸው ተመድበው እንዲወጡ ለሔኖክ ያስጎበኘውና ምሥጢሩን ያሳወቀው ቅዱስ ዑራኤል ነው። በተጨማሪም በምድር ላይ ከሚነፍሱት ፲፪ የነፋሳት መስኮቶች መካከል አራቱ የበረከትና የሰላም ነፋሳት ምድርን የሚያለመልሙ ሲሆኑ፣ ስምንቱ የመቅሰፍት ነፋሳት ደግሞ ድርቅንና ጥፋትን የሚያመጡ ተፈጥሮአዊ ሂደቶች ናቸው። (መቅድመ ወንጌል) እነዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ሕግጋት በፈጣሪ ፈቃድና በመልአኩ አስጎብኚነት የሚከናወኑ የሥነ-ፍጥረት ምሥጢራት ናቸው። ቅዱስ ዳዊት «ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» (መዝ. ፲፱፥፩) እንዲል፣ ቅዱስ ዑራኤል የዚህን መለኮታዊ ሥርዓት ታላቅነት ለፍጥረታት የሚገልጥ መልአክ ነው።
ቅዱስ ዑራኤል በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት «ከሣቴ ምሥጢር፤ ምሥጢር ገላጭ በመባል ይታወቃል። የተሰወረውን ምሥጢር መግለጥና በአዲስ ቋንቋ ማናገር የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ለቅዱስ ዑራኤል በወደዱትና እንዲያውቁ በተፈቀደላቸው ሰዎች አእምሮ ላይ ጥበብንና እውቀትን የማፍሰስ ጸጋ ሰጥቶታል። ለዚህም ዋናው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ለዕዝራ ሱቱዔል የተደረገለት ታላቅ ተአምር ነው። «መልአኩ ዑራኤል አፍህን ክፈት፤ እኔም የማጠጣህን ጠጣ አለኝ… ብሎ አእምሮ ለብዎውን ገልጦለታል።» (ዕዝራ ፲፫፥፴፰)
ዕዝራ ለረጅም ወራት እግዚአብሔርን ደጅ ሲጠና፣ እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን ልኮ የጥበብና የዕውቀት ጽዋ አጠጥቶታል፤ በዚህም ምክንያት የሰማዩን ምሥጢር ዐውቋል፣ የነገሩትን የማይረሳ አእምሮም አግኝቷል። በተመሳሳይ መልኩ ለነቢዩ ሔኖክ ምሥጢረ ሰማይንና ዕውቀትን ሁሉ የገለጠለት እርሱ እንደሆነ በመጽሐፈ ሄኖክ የተጻፈ ሲሆን (ሔኖክ ፳፰፣፲፫) ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም ልቡናውን ያበራለትና ድንቅ ድንቅ የድርሰትና የምሥጢር ቃላትን ያደለው ይህ መልአክ እንደሆነ በገድሉ ላይ ተመዝግቧል። አፋቸውን ከፍተው የምስጋና ቃል ለሚናገሩና እግዚአብሔርን ደጅ ለሚጠኑ ሁሉ ቅዱስ ዑራኤል አእምሯቸውን ያበራል፣ ጥበብን ያሳድራል፣ ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስም ይጠብቃቸዋል።
ቅዱስ ዑራኤል በሰው ልጅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ድንቅ አገልግሎት አድርጓል። ነቢዩ ዳዊት «የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል፥ ያድናቸውማል» (መዝ. ፴፫፥፯) እንደተናገረው እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች በጭንቀት ጊዜ በመካከላቸው እየተገኘ ያጽናናቸዋል፣ ረዓድና ፍርሃት ላለባቸውም ታላቅ ረዳታቸው ነው። የመልአኩ ተራዳኢነት አገልግሎት በሚከተሉት ታላላቅ ታሪካዊ ክስተቶች ይገለጻል፦
● የክርስቶስን ደም በጽዋዕ መቀበል፦ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ ደሙን በፈቃዱ ሲያፈስ በዕለተ ዓርብ በሚነበበው ግብረ ሕማም ላይ እንደተጻፈው ቅዱስ ዑራኤል ያንን ክቡር ደም በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በዓለም ሁሉ ላይ የረጨ መልአክ ነው። በእነዚህ ታላላቅ አገልግሎቶቹ ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የመልአኩን መታሰቢያ በዓላት በተለያዩ ወቅቶች ታከብራለች፦
- ሐምሌ ፳፪ ቀን፦ ለዕዝራ ሱቱዔል ዕውቀትንና ጥበብን ያደለበትን እና ተአምራት ያደረገበትን ዕለት በማሰብ የሚከበር ዓመታዊ ንግሥ።
- ጥር ፳፪ ቀን፦ ሊቀ መላእክት ሆኖ የተሾመበትን ታላቅ ክብር በማሰብ የሚከበር በዓል ነው ።
- መጋቢት ፳፯ ቀን፦ በዕለተ ዓርብ ከጌታችን ጎን የፈሰሰውን ክቡር ደም በጽዋዕ የተቀበለበትን ታላቅ ምሥጢር በማሰብ የሚከበር በዓል ነው።
በአጠቃላይ፣ ሊቀ መልአክ ቅዱስ ዑራኤል በሥነ-ፍጥረት ሥርዓት፣ በጥበብና እውቀት መገለጥ፣ እንዲሁም በሰው ልጅ መጽናናትና ድኅነት ውስጥ ታላቅ ሚና ያለው የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ነው። አማላጅነቱና ተራዳኢነቱ አይለየን፤ አሜን!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!