መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት አንደበት – የመጀመሪያ ክፍል
“ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፡፡ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድወደ ሲኦል ወረደች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተናገረው ቃል ዐፅም ሥጋ ወደ መኾን ፈጽሞ እንደ ተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጕድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፡፡ ይህስ እውነት ከኾነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፡፡ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበሥር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፡፡ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትኾን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋው ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደ ተናገረ፡፡ አባቶቻችን ‹ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣው ሥጋ ነው እንጂ› ብለው አስተማሩን፡፡ ይህን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም በእርሱ አየ፤” (ዝኒ ከማሁ፣ ፴፥፴፩-፴)፡፡
የትንሣኤው ብሥራት
“ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል!” የሚለውን የምሥራች ከቤተ ክርስቲያን ለመስማት በናፍቆት ይጠባበቃሉ፡፡ የትንሣኤውን ብሥራት ሰከሙ በኋላም “ጌታ በእውነት ተነሥቷል!” እያሉ ትንሣኤዉን ይመሰክራሉ፡፡ የጌታችን ትንሣኤ፣ የድኅነታችን ብሥራት በመኾኑ ለአምሳ ቀናት ያህል በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ፣ በሌሎችም ቅዱሳት መጻሕፍት በልዩ ሥርዓት ይዘከራል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያኑ “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን አሠሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሰላም” እየተባለ ሞት መደምሰሱ፣ ነጻነት መታወጁ ይበሠራል፡፡
ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – ካለፈው የቀጠለ
በአንድ ጥቅስ መመርኮዝ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ አይደለም፡፡ በዚህ መልክ ድምዳሜ ላይ መድረስም ኦርቶዶክሳዊ መንገድ አይደለም፡፡ አንድ ጥቅስ አንሥቶ የኾነ ዐሳብ መሰንዘር የሚፈልግ ሰው ቢያጋጥም ጥቅሱ የቱንም ያህል ግልጽ መልእክት ያለው ቢኾን እንኳን “እንዲህ ለማለት ነው” ተብሎ ለመደምደም አያስችልም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የኾነ ሰውም በተነሣው ርእሰ ጉዳይ ላይ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን እንደሚሉ ለማወቅ ይጥራል፡፡ ዐሳቡን የተሟላ የሚያደርጉት በጉዳዩ ላይ ሌሎች የቅዱደሳት መጻሕፍት ክፍሎች ተሟልተው ሲቀርቡ ነው፡፡ ሌሎች ጥቅሶች አንዱን ጥቅስ ግልጽና የማያሻማ እንደዚሁም የተሟላ ያደርጉታል፡፡
ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – የመጀመሪያ ክፍል
ታዲያ በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመሥርተን “መዳን ሕጉን በመተግበር ብቻ የሚገኝ ነው” ልንል እንችላለን? አንልም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም የሐዋርያውን ጥቅሶች ሳንነጣጥል በአንድነት እንወስዳቸዋለን፡፡ ሐዋርያው በሁለቱም ቦታዎች በሮሜ. ፪፥፲፫ እና ፭፥፩ ላይ የጻፈልንን ለድኅነታችን አስፈላጊ የኾኑትን ተግባራት እንማራለን፡፡ በዚህ መሠረት ለመዳናችን ማመናችን የሚኖረውን ዋጋ መልካም ሥራ አይተካውም፤ እንደዚሁም መልካም ሥራ ለመዳናችን አስፈላጊ መኾኑ የእምነትን አስፈላጊነት አይሽረውም፡፡ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?” (ያዕ. ፪፥፳፬-፳፭) ተብሎ እንደ ተጻፈው ለመዳን ሁለቱንም እምነትንና ሥራን አዋሕደን መያዝ እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡
ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በኾነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ሲል አምላካችን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለ ጣለው ‹‹ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ?›› ተብሎ ተዘመረ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት በክርስቶስ ሞት ድል ተደርጓልና (ኢሳ. ፳፭፥፰፤ ሆሴ. ፲፫፥፲፬፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፬-፶፭)፡፡
ቀዳም ሥዑር
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለ ኾነ ዕለተ ቅዳሜ ‹ለምለም ቅዳሜ› ተብላም ትጠራለች፡፡ በቀዳም ሥዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል (ቃለ ዓዋዲ) እየመቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ›› የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደ ሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደ ገለጠልን በማብሠር፤ ቄጠማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብሥራት ነው፡፡
ቀዳሚት ሥዑር
ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አርፎ የዋለባት ዕለት በመኾኗ ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትሰኛለች፡፡ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡ የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡
የእመቤታችን ኀዘን ስለ ጌታችን መከራ
ዛሬ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ባየሁህ ጊዜ ላልቅስን? ከሌቦች፣ ከወንበዴዎች፣ ዓለሙን ዂሉ ካስለቀሱት ጋር በመስቀል በሰቀሉህ፣ በቸነከሩህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በሙሴና በኤልያስ መካከል የመንግሥትህ ግርማ በታወቀ፤ የመለኮትህ ብርሃን ባንጸባረቀ ጊዜ ልደሰት? በቀራንዮ መስቀልን በተሸከምህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ መጻጕዕን ‹‹ኀጢአትህ ተሰረየልህ፤ ተነሥና አልጋህን ተሸከም፤ ሔደህም ወደ ቤት ግባ፤›› (ዮሐ. ፭፥፰) በማለትህ ልደሰት? ሐና እና ቀያፋ ‹‹ደሙ በእኛና በልጆቻችን ይኹን›› ባሉህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችዉን ሴት በልብስህ ጫፍ በማዳንህ ልደሰት? በይሁዳ አማካይነት በሠላሳ ብር በመሸጥህ ላልቅስን? ወይስ ከዓሣ ሆድ ዲናር ያወጣ ዘንድ፣ በአንተ እንዳያጕረመርሙም ለቄሣር ግብር ይሰጥ ዘንድ ጴጥሮስን ባዘዝኸው ጊዜ ልደሰት?
የጌታችን መከራ በሊቃውንት አንደበት
‹‹ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡ ሲኦል ተነዋወጠች፤ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፡፡ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ ክብርት ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት በእርሷ ያለውንም ዂሉ ጠበቀ፡፡ ስለ ፍጥረት ዂሉ ሥጋውን በመስቀል እንደ ተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፡፡ ፍጥረትንም ዂሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፤›› (የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ)፡፡
በጸሎተ ሐሙስ የሚፈጸም ሥርዓት
ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡