ጸሎተ ሐሙስ

ሚያዝያ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን

ጸሎተ ሐሙስ በብሉይ ኪዳን ለፋሲካ ዝግጅት ተደርጎበታል (ማቴ. ፳፮፥፯-፲፫)፡፡ ‹ፋሲካ› ማለት ማለፍ ማለት ነው፡፡ ይኸውም እስራኤላውያን በግብጽ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፡፡ ሙሴም የታዘዘውን ለሕዝቡ ነገረ፤ ዅሉም እንደ ታዘዙት ፈጸሙ፡፡ በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ መቅሠፍት ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የግብጻውያንን ቤት በሞተ በኵር ሲመታ፤ የበጉ ደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ አልፏል፡፡ ፋሲካ መባሉም ይህን ምሥጢር ለማስታወስ ነው (ዘፀ. ፲፪፥፩-፳)፡፡

በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እስራኤላውያን በመጀመሪያው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች አገር እንደ መኾኗ ይህን ሥርዓት ትፈጽም ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ‹ፋሲካ› ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ጌታችን በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ ምሥዋዕት አድርጎ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስም ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ርቆልናል፡፡ ስለዚህም ክርስቶስን ‹ፋሲካችን› እንለዋን (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፯፤ ፩ኛ ጴጥ. ፩፥፲፰-፲፱)፡፡

የጸሎተ ሐሙስ ስያሜዎች

ጸሎተ ሐሙስ በቤተ ክርስቲያን በርካታ ስያሜዎች አሉት፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መኾኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ቀን ነውና ‹ጸሎተ ሐሙስ› ይባላል (ማቴ. ፳፮፥፴፮-፶፮)፡፡ ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዅሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ የንጽሕና፣ የቅድስና አምላክ መኾኑን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህም ዕለቱ ‹ሕጽበተ ሐሙስ› ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ሊቃነ ጳጳሳትና ቀሳውስት ‹‹በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ፤ እኛም የአንተን አርአያነት ተከትለን የልጆቻችንን እግር እናጥባለን፤›› ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙ ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ ‹የምሥጢር ቀን› ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታችን ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ ‹‹ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ፤ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ፤›› በማለት እርሱ ከእኛ፤ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ የምንኾንበትን ምሥጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመኾኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የኾነ ዅሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

መድኃኒታችን ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመኾኑ ይህ ዕለት ‹የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ› ይባላል (ሉቃ. ፳፪፥፳)፡፡ ‹ኪዳን› ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ዅሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለ ኾነ ሐሙስ ‹የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ› ተባለ፡፡

ይህ ዕለት ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ኾኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለ ኾነ ‹የነጻነት ሐሙስ› ይባላል፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፡፡ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤›› በማለት ከባርነት የወጣንበትን፤ ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመኾኑ ሊቃውንቱ ‹የነጻነት ሐሙስ› አሉት (ዮሐ. ፲፭፥፲፭)፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች ሳይኾን ወዳጆች ተብለን በክርስቶስ ተጠርተናልና፡፡

በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ዅሉ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፲፬፥፲፮ የሚገኘውን ሰፊ ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎችም ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ያካትታሉ፡፡ ጌታችን እነዚህን ትምህርቶች በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳ፣ ለደቀ መዛርቱ ምሥጢሩን በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲቻለው በሰፊ ማብራርያ እንዲረዱት አድርጓል፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ያልገባቸውንም እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቀን መረዳት እንደሚገባን ከዚህ እንማራለን፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ የሰጠውም በዚሁ ዕለት ከምሽቱ በሦስት ሰዓት ነው (ማቴ. ፳፮፥፵፯-፶፰)፡፡

በጸሎተ ሐሙስ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ሥርዓት

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደ ተለመደው ይከናወናሉ፡፡ መንበሩ (ታቦቱ) ጥቁር ልብስ ይለብሳል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፤ ቤተ ክርስቲያኑም በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ ሕጽበተ እግር ይደረጋል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በየቤቱ ደግሞ ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

ሕጽበተ እግር

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ሕጽበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፤

ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ወይራ ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ሕጽበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ሕጽበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡

 ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲኾን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልኡካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡-

ስምዐ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)፣ ከሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ገጽ ፮-፯፣ ፲፫ እና ፳፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ አዲስ አበባ፡፡

ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት

በመምህር ቸሬ አበበ

ሚያዝያ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የእግዚአብሔር ቸርነት 

ከአባታችን አዳም በደል ወይም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሠፍታት፣ ወዘተ. በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የኾነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ፣ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ዅልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የኾነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ፣ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላምን ሊሰጥ፣ ተስፋ ለሌለው ተስፋን ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም፤ ዲያብሎስን ድል አድርጐ እኛም ዲያሎስን ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ኾነን፡፡

ሰሙነ ሕማማት 

ሰሙን ‹ሰመነ – ስምንት አደረገ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲኾን ትርጕሙም ሳምንት፣ ስምንት ማለት ነው፡፡ ‹ሕማማት› ቃሉ ‹ሐመ – ታመመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ብዙ ሕማምን ያመላክታል፡፡ ‹ሰሙነ ሕማማት› ስንልም ‹የሕማም ሳምንት› ማለታችን ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ዅሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ለማውጣት ሲል የተቀበለውን መከራ የምናስብበት ወቅት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት ከዕለተ ሆሣዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኵነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፤ የሚያለቅሱበት፤ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው እግዚአብሔርን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን ለካህን የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ልዩ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልዕት (የምግብ ዓይነቶች) አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ፣ በመጠማት፣ በመውጣት፣ በመውረድ፣ በመስገድ፣ በመጸለይ፣ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ በማሰብ ወቅቱን እናሳልፋለን፡፡ በዚህ ሳምንት አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ቅዱሳት መጻሕፍት በየሰዓቱ ይነበባሉ፡፡ በዚህ ሳምንት መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታህ›› አይሉም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመኾኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የሚያሰሙትን የመለከት ድምፅ፤ በዚያች ሰዓት ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ከሞት እንደሚነሡ ለማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜአቸው

ዕለተ ሰኑይ (ሰኞ)

ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ (የቤተ መቅደስ መንጻት) እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው (ማቴ.፳፩፥፲፰-፳፪፤ ማር. ፲፩፥፲፩፤ ሉቃ. ፲፫፥፲፮)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ፡- ‹‹… ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፤›› በማለት በበለስ ስለ ተመሰለው የሰው ልጅ እና በንስሐ ተመልሶ በሕይወት መኖር እንደሚገባው እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያስረዳል፡፡ በለሷ እንደ ጠወለገችና እንደ ተቈረጠች ዅሉ፣ ንስሐ አልገባም አልመለስም የሚሉም የምግባር ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቈረጡ፤ እንደዚሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል፤ ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባር ነው፡፡ ዅላችንም ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት እና ምግባርን አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንኾን፣ ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል መፈጸም ይጠበቅብናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ (ማክሰኞ)

ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን ‹‹በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ የሚል ነበር (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፳፯)፡፡ ጌታችንም «… እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል፤›› ሲል አስተምሯል (ማቴ. ፳፩፥፳፰)፡፡

ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ ‹የምክር ቀን› በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ መኾኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ዕለቱ ‹ጸሎተ ሐሙስ› በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትናንና ፍቅርን እንደዚሁም የአገልግሎትን ትርጕም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ዕለቱ ‹ሕጽበተ ሐሙስ› በመባልም ይጠራል፡፡ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ባጠበ ጊዜም፡- «… ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?… እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስኾን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፤››  በማለት የእርሱን አርአያነት መከተል እንደሚገባ አስተምሯል (ዮሐ. ፲፫፥፲፪-፳)፡፡

ዕለተ ሐሙስ ጌታችን ‹‹… ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱ ጠጡ፤›› በማለት ምሥጢረ ቍርባንን የመሠረተበት የጀመረበት ቀን በመኾኑ ‹የምሥጢር ቀን› ተብሎም ይጠራል (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱)፡፡ ይኸውም ምእመናን ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን፤ ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ አይሁድ ጌታችንን የያዙበት ቀን ስለ ኾነ በዚህ ዕለት በለኆሣሥ (ብዙ የድምፅ ጩኸት ሳይሰማ) የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ መላው ሕዝበ ክርስቲያን የሕጽበት፣ የምሥጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሐ ታጥበው፣ ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «አውቀውስ ቢኾን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» በማለት እንደ ተናገረው (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰) ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ንጹሕና ጻድቅ የኾነውን ጌታ ያለበደሉና ያለጥፋቱ በሐሰት ወንጅለው የሰቀሉበት፤ ጌታችንም በፈቃዱ በመስቀል የተሰቀለበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ዅሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልዕልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው (ማቴ. ፳፯፥፴፭-፸፭)፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ‹‹ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ›› አለ፡፡ እነርሱ ግን ‹‹እኛስ ምን አግዶን?  አንተው ተጠንቀቅ፤›› አሉ፡፡ ይሁዳም ብሩን በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው ‹‹የደም ዋጋ ነውና ወደ መባዕ ልንጨምረው አልተፈቀደም፤›› አሉ፡፡ ተማክረውም ለእንግዶች መቃብር የሚኾን የሸክላ ሠሪ መሬት ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ ‹የደም መሬት› ተባለ (ማቴ. ፳፯፥፫-፱)፡፡

ዕለተ ዓርብ እኛ የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት (ቁራኝነት) እንኖርበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመባትና ፍጹም ድኅነት ያገኘንባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ዅልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ የክርስቶስን ሕማሙን፣ ስቅለቱንና ሞቱን የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት፤ የሕይወት መቅጫ አርማ ኾኖ ሳለ ለእኛ ግን የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት ዕለቱ ‹መልካሙ ዓርብ› በመባል ይታወቃል፡፡

ቀዳሚት ሥዑር

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር አምላካችን የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን፣ በክንፍ የሚበሩትን እና በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን፣ በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ነች፡፡ የመጀመሪያዋ ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ፍጥረታትን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ስላረፈባት ‹ሰንበት ዐባይ› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ይህቺን ዕለት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ እግዚአብሔር ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንዳደረገባት ዅሉ፣ የፍጥረት ርእስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አምላካችን ክርስቶስ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አርፎ የዋለባት ዕለት በመኾኗ ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትሰኛለች፡፡ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡ የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

እመቤታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት ዅሉ የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው በማክፈል (በመጾም) እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ለሁለት ቀናት ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸምም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምእመናን የምሥራች ቄጠማ ያድላሉ፡፡

ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ ዅሉ፣ አሁንም ‹‹በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዅሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ጥንተ ማኅደራቸው ገነት መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ሰሙነ ሕማማት (ከሰኞ እስከ ረቡዕ)

በመ/ር ኃይለ ማርያም ላቀው

ሚያዝያ ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሰሙነ ሕማማት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ስለ ተገለጠበት፣ የመሥዋዕትነት ሥራ ስለ የተሠራበት፣ የሰው ልጆች ድኅነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኃኔ ዓለም በመስቀል ተሰቅሎ ለእኛ ቤዛ መኾኑ በስፋት ስለሚነገርበት ‹ቅዱስ ሳምንት› ይባላል፡፡ በተጨማሪም ‹የመጨረሻ ሳምንት› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመኾኑ ነው፡፡

በዚህ ልዩ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ይዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ ይከበራል፡፡ ይህም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው፡፡

ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ መኾኑ ይነገራል፡፡ ‹‹ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጠረ፡፡ እርሱ ግን ግፍን አላደረገም፤ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኢሳ. ፶፫፥፬-፲፪)፡፡ ምእመናን ክርስቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መኾኑን በመዘከር፤ ከማንኛውም የሥጋ ሥራ በመታቀብ ዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር ሰሙነ ሕማማትን ልናከብር ይገባል፡፡ ብድራትን የማያስቀረው አምላካችን እግዚአብሔር መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ አድርጎናልና፡፡

ሰሙነ ሕማማት አስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከዐቢይ ጾም ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር፡፡ በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም፣ ሕማማቱም፣ ትንሣኤውም ተከታለው እንዲከበሩ ተደረገ፡፡ ምዕራባውያን ከዐርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል፡፡ የምሥራቃውያን (ኦርየንታል) ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን ዐርባውን ጾም ጨርሰን ከኒቆዲሞስ በኋላ ያለውን ተከታዩን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን፡፡ ከእነዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት (በሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ) ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሰኞ

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሣዕና ማግሥት ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ነገሮችን አከናውኗል፤ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፯፤ ማር. ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፭-፵፮)፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ ‹‹በማግሥቱ ተራበ›› የሚል ቃል እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤›› ይላል (ኢሳ. ፵፮፥፳፭)፡፡ በቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ ቃል እንደ ነበር፤ ያ ቃል ቀዳማዊ እንደ ኾነ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበር፤ ያም ቃል እግዚአብሔር እንደ ኾነ ተጽፏል (ዮሐ. ፩፥፩-፪)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱ ሲያስተምር፡- ‹‹የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፤ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው፤›› ሲል ተናግሯል (ዮሐ. ፬፥፴፬)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ?

ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፣ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ፤ ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ጌታ ‹‹ተራበ›› ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመኾኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረኃብ የድህነት (የማጣት) አይደለም፡፡ የክርስቶስ ረኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይኾን የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባርን ፍሬ የሻ መኾኑን ለማጠየቅ ‹‹ተራበ›› ተባለ፡፡ ‹‹በለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱ›› እንዲል፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹በአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤ በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት›› ብሏል፡፡

እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው፤ አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ያመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመኾን መብቃታቸውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፤ ‹‹አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሶኩሰ ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፤›› ብሎ ተርጕሞታል፡፡ እሾኽ የእርግማን፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ዛሬ ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይኾን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤›› ይለናልና እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እናፍራ (ማቴ. ፫፥፰፤ ገላ. ፭፥፳፪)፡፡ ጌታችን በዳግም ልደት ሲመጣ ከሰው ልጅ ሃይማኖት መገኘቱ አጠራጣሪ እንደ ኾነ ተናግሯል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይኾንን?›› ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ ለፍርድ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን እንዲያገኘንና ዘላለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት እንትጋ፡፡

ማክሰኞ

በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ ማርቆስ ወንጌል ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ በሉቃስ ወንጌል ፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማክሰኞ ዕለት የሚነገሩ ትምህርቶችን ይዘዋል፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ የትምህርት ቀን ይባላል፡፡ ክርስቲያን የኾነ ዅሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲኾኑ፣ ጥያቄውም፡- ‹‹በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን›› ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡

ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?›› ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ኹኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት ‹‹ለምን አላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው›› ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ኾነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ዅሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡

ዛሬም ቢኾን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊኾኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ‹‹ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል?›› በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት ‹‹ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው›› የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

 ረቡዕ

በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፤

  • አንደኛ የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ  ተማክረዋል፤
  • ሁለተኛ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡
  • ሦስተኛ ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ ሲኒሃ ድርየም› ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታን ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር ‹‹ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤›› በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማቷል፡፡

ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት የአስቆሮቱ ይሁዳ ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡

‹‹ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር፤›› በማለት ያቀረበው አሳብ ‹‹አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች›› እንደሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ ይህ ታሪክም በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ምዕራፎች ተመዝግቦ እናገኛዋለን፤ ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ዅሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ‹‹የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ‹‹ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤›› ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ‹‹ይህን ዓለ ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡

ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ኾነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይኾን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ኾነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡

ስምዐ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)፣ ከሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ገጽ ፬-፮፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ አዲስ አበባ፡፡

ሆሣዕና በአርያም

በዲያቆን ሚክያስ አስረስ

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሰውን ከወደቀበት የበደል ጉድጓድ ያወጣው ዘንድ እግዚአብሔር ክንዱን ወደ ዓለም ላከ፡፡ ሰው ኾኖ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክንድ በትሕትና ሁለተኛ አዳም ኾኖ በለበሰው ሥጋ በጉድጓድ ተጥሎ፤ በሥጋ፣ በነፍስ፣ በውስጥ፣ በአፍአ ቈስሎ የነበረ አዳምን ከሞተ ነፍስ አድኖታል፡፡ ከእርሱ አስቀድሞ ሰውን ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከባርነት ወደ ነጻነት የሚያመጣ ባለመኖሩ ዅሉን የፈጠረ፣ ዅሉን የሚያኖር እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ ሞቶ ለሰው ልጅ መድኃኒት ኾነ፡፡ በዚህም ‹‹መድኃኒተ ፈነወ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፤ እግዚአብሔር ለሕዝቡ መድኃኒትን ላከ፤›› ተብሎ በነቢዩ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ (መዝ. ፻፲፥፱)፡፡

ክርስቶስ ባለ መድኃኒት ኾኖ በኃጢአት ለታመሙ ደቂቀ አዳም ዅሉ ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ በምድራዊ ሥርዓት እንደምናየው መድኃኒትና ባለ መድኃኒት እንደሚለያዩት አይደለም፡፡ እርሱ በመምጣቱ (ሰው በመኾኑ) ሁለቱንም ፈጸመ እንጂ፡፡ መድኃኒት አድርጎ ሥጋውን ደሙን የሰጠ እርሱ ነው፡፡ በካህናት አድሮ ሰው በንስሐ ሲመለስ መድኃኒት ወደ ኾነው ወደ ራሱ የሚመራም እርሱ ነው፡፡ በእመቤታችን ማኅፀን የተጀመረው የክርስቶስ መድኃኒትነት እና ፍቅሩ ፍጻሜውን ያገኘው በሕማሙ እና በሞቱ ነው፡፡ መሐሪ ንጉሥ እርሱ መኾኑን ይገልጥ ዘንድም በፈቃዱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ከመግባቱ አስቀድሞ ከኢየሩሳሌም ፲፮ ያህል ምዕራፍ በምትርቀው በቤተ ፋጌ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበር፡፡ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለቱን ማለትም ጴጥሮስን እና ዮሐንስን ‹‹በፊታችሁ ወዳለችው መንደርዱ፤ ወደ እርሷ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበትን ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ፤›› በማለት አዘዛቸው (ማር. ፲፩፥፪)፡፡ ሰው ወዳልገባባት የተዘጋች የምሥራቅ ደጅ ወደ ምትባል ወደ ድንግል መጥቶ ዘጠኝ ወር ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ እንደ ኖረ፤ ማኅየዊት ከምትኾን ሕማሙ በኋላም ሰው ባልተቀበረበት መቃብር እንደ ተቀበረ፤ አሁንም ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ለመግባት ማንም ሰው ያልተቀመጠባቸውን፣ አህያንና ውርንጫን እንዲያመጡ ደቀ መዛሙርቱን አዘዘ፡፡

የፍጥረት ዅሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ እስትንፋሷን የገበረችለትን አህያ አሁን ደግሞ በፈቃዱ ስለ ሰው ዅሉ ሊሞት ሲል ንጉሥነቱን ሊያስመሰክርባት ወደደ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ካለው ፲፮ ምዕራፍ ዐሥራ አራቱን በአህያ ላይ ሳይቀመጥ በእግሩ ተጓዘ፡፡ ከዚያም ሁለቱን ምዕራፍ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ከሔደ በኋላ የኢየሩሳሌምን መቅደስ ሦስት ጊዜ በውርጫዋ ላይ ኾኖ ዞረ፡፡ በዚህም ሕግ በተሰጣቸው አይሁድ እና ሕግ ባልተሰጣቸው አሕዛብ ላይ እኩል ቀንበርን መጫን እንዳይገባ አጠየቀ፡፡

ወደ ኢየሩሳሌም ሲሔድም እርሱን የሚከተሉት ሰዎች ሆሣዕና በአርያም› እያሉ ያመሰግኑት ነበር፡፡ ይኸውም በሰማይ በልዕልና ያለ፤ ከሰማይ የመጣ መድኃኒት› ማለት ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን እና ቅጠሎችን በመንገድ ላይ አነጠፉ፡፡ ‹‹ሆሣዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው›› እያሉም ጌታችንን አመሰገኑ (ማር. ፲፩፥፰-፲)፡፡ ዛሬም እኛ ክርስቲያኖች ‹‹ቡሩክ ስሙ ለእግዚብሔር ወቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ስሙ ምስጉን ነው፡፡እግዚአብሔር ነኝ› ብሎ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ እርሱ ክርስቶስም ምስጉን ነው፤›› በማለት የአብ እና የወልድ መለኮታዊ አንድነትን ገልጸን እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

በክርስቶስ ሕማም እና ሞት የእግዚአብሔር ፍቅሩ እና መሓሪነቱ ተገልጧል፡፡ ክርስቶስ የተቀበለው መከራም የእርሱን አምላክነት እና ንጉሥነት አልሸሸገውም፡፡ እንዳውም ዙፋኑን መስቀል በማድረግ ንጉሥነቱን በመድኃኒትነቱ ገልጿል እንጂ፡፡ በማእከለ ምድር ተሰቅሎ በመድኃኒትነቱ ንጉሥነቱን መግለጡንም ነቢዩ፡- ‹‹እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር፤ እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድር መካከልም መድኃኒትን አደረገ፤›› በማለት የተናገረው ቃል ያመለክታል (መዝ. ፸፫፥፲፪)፡፡ በሌላ የመዝሙር ክፍልም፡- ‹‹አንሰ ተሰየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ በጽዮን በደብረ መቅደሱ፤ እኔ በተቀደሰው ተራራ ላይ ንጉሥ ኾኜ ተሾምኹ፤›› በማለት ነቢዩ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መንገሡን ተናግሯል (መዝ. ፪፥፮)፡፡ ይህንም ‹‹እነርሱ (አይሁድ) ‹ሰቀልነው፤ ገደልነው፤ በኋላ ፈርሶበስብሶ ይቀራል፤› ይሉኛል እንጂ እኔስ ደብረ መቅደስ በሚባል መስቀል ላይ ነግሻለሁ›› ብለው ኦርቶዶክሳውያን አበው ይተረጕሙታል፡፡

የጌታችን ሕማሙ እና ሞቱ ንግሥናው፣ ክብሩ የተገለጠበት ምሥጢር እንጂ ክብሩን የሚሸሽግ ውርደት አይደለም፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ‹‹ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማተ ወልዱ ክብረ ወስብሐተ፤ የልጁን ሕማማት ክብርና ምስጋና አድርጎ የሰየመ እግዚአብሔር ይመስገን!›› ያለውም ስለዚህ ነው፡፡ የክርስቶስ ሕማሙ እኛን ያከበረበት በመኾኑ ክብርና ምስጋና እንደ ተባለ እናስተውል፡፡

ከጌታችን በስተቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴም፡- ‹‹አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ?›› በማለት ንጉሥነቱን መስክሮለታል (ሉቃ. ፳፫፥፵፪)፡፡ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በምስጋና መግባቱ መድኃኒትነቱን እና ንጉሥነቱን ያሳያል ማለታችንም ስለዚህ ነው፡፡ ዳግመኛም ዅሉን የያዘ ጌታ በአህያ ላይ መቀመጡ ትሕትናውን ያስረዳል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፡- ‹‹ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል ዲበ ዕዋለ አድግ ነበረ›› በማለት ሰማያዊው አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በትሕትና በአህያ ጀርባ እንደ ተቀመጠ ተናገረ፡፡

ጌታችን በመድኃኒትነቱ ድንቅ የኾኑ ተአምራትን ለሰዎች አሳየ (ገለጠ)፡፡ ‹‹እምሆሣዕናሁ አርአየ ተአምረ ወመንክረ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በቅዳሴው፡፡ ይህም ክርስቶስ በአህያ ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ አእምሮ፣ ጠባይዕ ያልቀናላቸው ሕፃናት ዕውቀት ተገልጾላቸው ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ ማመስገናቸውን ያጠይቃል፡፡ መናገር የማይችሉ ድንጋዮች እርሱ በከሃሊነቱ ዕውቀት ሰጥቷቸው መናገር ችለው ጌታችንን አመስግነዋልና፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑን፤ ቀድሞ በአዳም በደል ምክንያት ለሰው ከመገዛት ውጪ የነበሩ ፍጥረታት የሰውን ሥጋ ለብሶ በተገለጠው በክርስቶስ አማካይነት ዳግመኛ ለሰው መገዛታቸውን ከዚህ ምሥጢር እንረዳለን፡፡

ዳግመኛም ጌታችን በመድኃኒትነቱ የሥላሴ ልጅነት ማግኘትን እና ተአምራት ማድረግን ገለጠ፡፡ ‹‹እምሆሣዕናሁ አርአየ ጸጋ ወኃይለ›› እንዲል (ቅዳ. ጎርጎ. ዘኑሲስ)፡፡ የእርሱ የማዳን ሥራ ከሰው ተወስዶ የነበረውን የጸጋ ልጅነት እንዲመለስ ከማድረጉ ባሻገር በልጅነት ላይ ተአምራትን ለማድረግ አስችሏል፡፡ ይኸውም እርሱ በረድኤት አድሮባቸው ድንቅ ተአምራትን ለሚያደርጉ ቅዱሳን መሠረት ነው፡፡ በተጨማሪም የበደሉትን ያከብራቸው ዘንድ፤ ኃጥአንን ከኃጢአታቸው ያነጻቸው ዘንድ፤ እንደዚሁም የሳቱትን ይመልሳቸው ዘንድ ለንስሐ የሚኾን ዕንባን ሰጠ፡፡ ‹‹እምሆሣዕናሁ ወሀበ ፈልፈለ አንብዕ ለኃጥአን›› እንዲል (ቅዳ. ጎርጎ. ዘኑሲስ)፡፡

በተመሳሳይ ምሥጢር ጌታችን በመድኃኒትነቱ ለዕውራን ብርሃንን ሰጥቷል፡፡ ይኸውም ለጊዜው በዐይነ ሥጋ የታወሩትን በመፈወስ ዐይናቸውን እንዳበራላቸው፤ ለፍጻሜው ግን ዕውቀትን ከማጣት የተነሣ ታውረው ለነበሩ ዅሉ ዕውቀትን፣ ጥበብን ማለትም አንድነቱን፣ ሦስትነቱን፣ አምላክነቱንና የዓለም መድኃኒት መኾኑን የሚረዱበትን ጥበብ እንደ ገለጠላቸው የሚያመለክት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ሆሣዕና

በመ/ር ኃይለ ማርያም ላቀው

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹ሆሣዕና› የሚለው ቃል ‹ሆሼዕናህ› ከሚለው የዕብራይስጥ  ቃል የተወሰደ ሲኾን፣ ትርጕሙም እባክህ አሁን አድን› ማለት ነው፡፡ ‹‹አቤቱ እባክህ አሁን አድን፤ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፡፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፻፲፯፥፳፭-፳፮)፡፡ የሆሣዕና በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አዕሩግም ሕፃናትም ‹‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡

በሌላ አገላለጽ ይህ በዓል ‹የጸበርት እሑድ› (Palm Sunday) ይባላል፡፡ ታሪኩም የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ኾኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ሣራ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ዅሉን ቻይ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብጻውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ፣ እንደዚሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ወደ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት፣ ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አዕሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እግዚአብሔር አመላክቷቸው ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል (ሉቃ. ፳፪፥፲፰)፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ዘንባባ በመያዝ እግዚአብሔርን እንዳመሰገኑ እኛ እስራኤል ዘነፍስም ዘንባባ (ጸበርት) በግንባራችን በማሰር በዓሉን እናከብራለን፡፡ በዕለተ ሆሣዕና አዕሩግና ሕፃናት ‹‹ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል›› እያሉ ዘምረዋል፡፡

ይህ ዅሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲኾን፣ በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታችንን ‹‹ደቀ መዛሙርትህን ገሥፃቸው›› ነበር ያሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ፡- ‹‹እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ›› በማለት ሕያዋን ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ ግዑዛን ፍጥረታትም እርሱን እንደሚያመሰግኑ አስረድቷቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያን የሕዝቡን ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ በማድረጋቸው በዕለተ ሆሣዕና ዘንባባ ይዘው ይዘምሩ የነበሩ ጭምር በዕለተ ዓርብ ‹‹ይሰቀል!›› እያሉ በጌታችን ላይ ጮኸዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ በነቢዩ ዘካርያስ፡- ‹‹እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ኾኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሟል (ዘካ. ፱፥፱፤ ማቴ. ፳፩፥፬፤ ማር. ፲፩፥፩-፲፤ ሉቃ. ፲፱፥፳፰-፵፤ ዮሐ. ፲፪፥፲፭)፡፡ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መኾኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲኾንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መድኃኒታችን ክርስቶስ መላእክት በዕለተ ልደቱ ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል፤ በምድርም ሰላም ለሰዉ ዅሉ ይሁን›› እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው (ሉቃ. ፪፥፲፫)፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ‹‹ሰላሜን እሰጣችኋለሁ›› ብሎ አስተምሮናል (ዮሐ. ፲፬፥፳፯)፡፡ ሰላሙን የሚሰጥበት ዕለት መቃረቡን ለማመልከት ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ መጣ፡፡ በሌላ በኩል በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፤ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ፣ ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ አምላክ መኾኑን አስተምሯል፡፡

ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የኾነው ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደ ተቀመጠ ዅሉ ዛሬም ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት አድሮ የሕሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፡፡ እርሱ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅምና (መዝ. ፶፥፲፯፤ ኢሳ. ፷፮፥፪)፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜአችን ሳትጠልቅ በእምነት እግዚአብሔርን እንፈልገው፡፡ ሰላሙን ይሰጠን ዘንድም ንስሐ ገብተን ‹‹ሆሣዕና በአርያም›› እያልን እናመስግነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም፡፡

ኒቆዲሞስ – የክርስቲያኖች ፊደል  

መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፱ .

ጌታችን ወደዚህ ምድር መጥቶ የምሥራቹን ቃል ሲያውጅ እስራኤላውያን የተቀበሉት በተደበላለቀ ስሜት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ለብዙ ዘመናት በባርነት ሲገዙ ስለ ነበር ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ነጻ የሚያወጣቸው መሲሕ ይፈልጋሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለብዙ ዘመናት በባርነት ቀንበር ስለ ደከሙ ተስፋ በመቁረጥ ተዳክመው ነበር፡፡ መሲሕ ቢመጣ እንኳ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት ጦር ይዞ፣ ሠራዊት አስከትሎ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው የክርስቶስን መሲሕነት ያልተቀበሉት፡፡ አብዛኛው እስራኤላዊ የክርስቶስን መሲሕነት ቢጠራጠርና ባይቀበለውም፣ በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው  የተከተሉትም  ነበሩ፡፡ ለዚህም  ትልቅ ማሳያ የሚኾነን ከፈሪሳውያን ወገን የኾነው ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን  ታላቅ ሰው ለማዘከር የዐቢይን ጾም ሰባተኛ እሑድ በስሙ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ ተከታዮቿ ምእመናንም የእርሱን አሠረ ፍኖት እንዲከተሉ ትመክራለች፤ ታስተምራለችም፡፡

ኒቆዲሞስ ማነው?

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው (ዮሐ. ፫፥፩)

የእስራኤላውያን ለብዙ ዘመን በባርነት መኖር የሕዝቡን የአኗኗር ኹኔታ ቀይሮታል፡፡ በግዞት ጊዜ ከአሕዛብ የቀሰሟቸው አጉል ትምህርቶች በእምነትም በአስተሳሰብም እጅግ እንዲለያዩና እንዲራራቁ ምክንያት ኾነዋል፡፡ አይሁዳውያን፣ ሳምራውያን፤ ከአይሁዳውያንም ሰዱቃውያን፣ ጸሐፍት፣ ፈሪሳውያን፣ ወዘተ. ተብለው እንዲከፋፈሉ ከዚህም እጅግ ወርደው ገሊላዊ፣ ናዝራዊ እንዲባባሉ ያበቃቸው ከአሕዛብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ፈር አለማስያዛቸው ነበር፡፡

ከአይሁድ ቡድኖች መካከል ፈሪሳውያን ሕግን በማጥበቅ ሕዝቡን የሚያስመርሩ፤ ቀሚሳቸውን በማስረዘም እነርሱ የማይፈጽሙትን ሕግ በሕዝብ ላይ የሚጭኑ፤ ራሳቸውን ከሌሎች በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ‹‹አባታችን አብርሃም ነው›› እያሉ የሚመጻደቁ፤ የአባታቸው የአብርሃምን ሥራ ግን የማይፈጽሙ የአይሁድ ቡድን ክፍሎች ናቸው (ዮሐ. ፰፥፴፱)፡፡ ኒቆዲሞስም ራሱን ከዚህ ሕዝብ ለይቶ በፍጹም ልቡ ክርስቶስን ፍለጋ የመጣ ፈሪሳዊ ነው፡፡ ቀድሞ አባታችን አብርሃምን ‹‹ከቤተሰብህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሒድ›› ያለው አምላክ ኒቆዲሞስን ከፈሪሳውያን ለይቶ ጠራው (ዘፍ. ፲፪)፡፡

ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ ነው (ዮሐ. ፫፥፩)

ሮማውያን ሕዝቡን የሚያስተዳድሩት ከላይ ያለውን ሥልጣን ተቆናጠው ታች ያለውን ሕዝብ ባህላቸውን በሚያውቅ፣ ቋንቋቸውን በሚጠነቅቅ አይሁዳዊ ምስለኔ ያስገዙ ነበር፡፡ አውሮፓውያንም አፍሪካን ለመቀራመት የተጠቀሙበት ስልት ይህን ዓይነት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ምንም እንኳ ፈሪሳዊ ቢኾን አለቃ እንዲኾን በሮማውያን የተሾመ ባለ ሥልጣን ነው፡፡

ኒቆዲሞስ መምህረ እስራኤል ነው (ዮሐ. ፫፥፭)

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ምሥጢረ ጥምቀትን በገለጸለት ጊዜ ሲደናገር አይቶ «አንተ የእስራኤል መምህር ስትኾን ይህን አታውቅምንብሎታል፡፡ ይህ ጥያቄ የሚጠቁመን ኒቆዲሞስ አለቅነትን ከመምህርነት የያዘ፤ በአይሁዳውያን ዘንድ የታፈረና የተከበረ ሰው እንደ ነበረ ነው፡፡ መምህር ቢኾንም ‹‹የሚቀረኝ ያላወቅሁትያልጠነቀቅሁት ብዙ ነገር አለ›› በማለት የመምህርነቱን ካባ አውልቆ፣ የተማሪነትን ዳባ ለብሶ ከክርስቶስ ሊማር መጣ፡፡

ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው (ዮሐ. ፫፥፯)

አንዳንዴ ሳያውቁ አወቅን ሳይማሩ እናስተምር የሚሉ ደፋር መምህራን አይጠፉም፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ከዚህ በተለየ አለቅነትን ከመምህርነት፣ መምህርነትን ከምሁርነት አስተባብሮ የያዘ፤ ዕውቀትን ከትሕትና፣ ምሁርነትን ከመንፈሳዊነት ጋር አስማምቶ የኖረ ሰው ነበር፡፡ የኦሪት ምሁር መኾኑን የሚጠቁመን ደግሞ ከካህናት አለቆች ጋር ያደረገው ክርክር ነው፡፡

ኒቆዲሞስ ምን አደረገ?

ለምሥጢረ ጥምቀት መገለጥ ምክንያት

የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀኑ እንደ ደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡፡ እንደ ሰውነቱ ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ሕዝቡን ቀንና ሌሊት በትምህርትና በተአምራት ያገለግል ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን የመጣው፡፡ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ» ብሎ የእርሱን አላዋቂነት፣ የክርስቶስን ማእምረ ኅቡዓትነት (የተሰወረን አዋቂነት) መሰከረ፡፡ ጌታችንም አመጣጡ ከልብ መኾኑን አውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ልደትን) ገለጸለት፡፡ ምሥጢሩም የኦሪት ምሁር ለነበረው ኒቆዲሞስ ለጆሮ የከበደ፣ ለመቀበል የሚቸግር ኾነበት፡፡ የከበደውን የሚያቀል፣ የጠበበውን የሚያሰፋ አምላክ ምሥጢሩ ለኒቆዲሞስ  እንደ ከበደው ስላወቀ ቀለል አደረገለት፡፡ ዳግም ልደት ከእናት ማኅፀን ሳይኾን ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ እንደ ኾነ አብራራለት፡፡

 አዋቂ ነን የሚሉትን አሳፈራቸው

ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት፤ ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደ ሙሴም ሕግም ሊያስፈርዱበት የተቻኮሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ጌታችን የሙሴ ፈጣሪ መኾኑን አላወቁምና፡፡ የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩበት ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የኾነ ታላቅ ሰው ነው – ኒቆዲሞስ፡፡

ጌታን ለመገነዝ በቃ (ዮሐ. ፲፱፥፴፰)

ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ከአንተ አንለይህም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ከዮሐንስ በቀር ሲበታተኑ፣ በዘጠኝ ሰዓት ቀራንዮ ላይ የነበረው ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ኾኖ የክርስቶስን  ስጋ ከአለቆች ለምኖ የገነዘው፤ ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር፡፡

ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?

አትሕቶ ርእስ (ራስን ዝቅ ማድረግ)

ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ፣ የዕውቀት እና የሥልጣን ደረጃ ራሳችንን ከፍ ከፍ አድርገን የመማር አቅም ያጣን፤ ቁጭ ብሎ መማር ለደረጃችን የማይመጥን የሚመስለን ስንቶቻችን እንኾን? በአንድ ወቅት አባ መቃርስ ከሕፃናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ፣ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ እያነቡ ወደ በዐታቸው እንደ ተመለሱ እያወቅን እኛ ግን ከአባቶች የመማር አቅም አጣን፡፡ ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃ፣ መምህረ እስራኤል፣ ምሁረ ኦሪት ቢኾንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ሥር ቁጭ አለ፡፡ ሕዝብን ከመምራትና ከማስተማር ይልቅ ቁጭ ብሎ መማር ምንኛ መታደል ነው!

ጌታችንም በትምህርቱ «ማርያምም  መልካም ዕድልን መርጣለችከእርሷም አይወሰድባትም» ያለው ስለዚህ አይደል? (ሉቃ. ፲፥፵፪)፡፡ በቅዱስ ወንጌል ላይ በተደጋጋሚ የምናገኘው የፈሪሳውያንን ግብዝነትና የጌታችንን ተግሣፅ ነው፡፡ ትሑት የሚያሰኘው ሳያውቁ አውቃለሁ ማለት ሳይኾን፣ እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ ማለት ሳይኾን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ ከፈሪሳዊው ይልቅ የቀራጩ ጸሎት ተቀባይነትን ማግኘቱም ለዚህ አንዱ ማስረጃ ነው (ሉቃ. ፲፰፥፲፩-፲፮)፡፡

 ጎደሎን ማወቅ

በአብዛኞቻችን ዘንድ የሚታየውና ክርስትናችንን፣ አገልግሎታችንን እና ቤተ ክርስትያናችንን እየተፈታተነ ያለው ችግር ጎደሎዎቻችንን አለማወቃችንና ምሉዕ እንደ ኾነን ማሰባችን ነው፡፡ ነገር ግን ምንም  እንዳልኾኑ አውቆ ራስን ለክርስቶስ እና ለቤተ ክርስቲያኑ አሳልፎ መስጠት ምንኛ መታደል ነው! ኒቆዲሞስ ያለውን ሳይኾን ያጣውን፤ የሞላለትን ሳይኾን የጎደለውን ፍለጋ ወደ ክርስቶስ መጣ፡፡ ዕውቀት ብቻውን ምሉዕ አያደርግም፡፡ አለቅነትም ቢኾን ገደብ አለው፡፡ ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት እንጅ ምሁረ ሐዲስ አይደለም፤ መምህረ እስራኤል ዘሥጋ እንጅ መምህረ እስራኤል ዘነፍስ አይደለም፡፡ የሕይወቱን ክፍተት ሊሞላ የሚችል አንድ ክርስቶስ ብቻ ነውና ኒቆዲሞስ ጉድለቱን አምኖ ጎደሎውን ሊያስሞላ ወደ ክርስቶስ መጣ፡፡ ‹‹የሚጎድለኝ ምንድን ነው?›› ብሎ እንደ ጠየቀው እንደዚያ ሰው ጎደሎን ማመን ምንኛ ታላቅ ነገር ነው!

አልዕሎ ልቡና (ልቡናንን ከፍ ማድረግ)

ኒቆዲሞስ ይዞ የመጣው ሥጋዊ ሕዋሳቱን ነበር፡፡ ጌታችን ግን አመጣጡ ለመልካም እንደ ኾነ አውቆ ለሥጋዊ ዕውቀት እጅግ የሚከብደውን ምሥጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ መጀመሪያ ይህን ምሥጢር ለመቀበል አልተቻለውም ነበር፡፡ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ምሥጢሩን ፍንትው አድርጎ ሲያብራራለት ግን ልቡናው ምሥጢሩን ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡ ምሥጢራትን ለመቀበል ልቡናን ከፍ ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡ የእምነታች መሠረት በሥጋ ዓይን ማየት፣ በሥጋ ጆሮ መስማት፣ በሥጋ እጅ መዳሰስ ብቻ ከኾነ እምነታችን ልክ እንደ እንቧይ ካብ ኾነ ማለት ነው፡፡ ትቂት የፈተና ነፋስ ሲነፍስበት፣ ጠቂት የመከራ ተፅዕኖ ሲደርስበት መፈራረስ፣ መናድ ይጀምራል፡፡ ኒቆዲሞስም ምሥጢሩ መጀመሪያ ቢከብደውም ቅሉ በኋላ ልቡናውን ወደ ሰማያዊው ምሥጢር ከፍ ስላደረገ ምሥጢሩን በቀላሉ ተረዳ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ሲፈታተኗትና እየተፈታተኗት ያሉ አካላት በሙሉ የስሕተታቸው ምንጭ እንደ ግያዝ ከአካባቢያቸውና ከምናየው አካል (ቁሳዊ ዓለም) ውጭ መመልከት አለመቻል ነው (፪ኛ ነገ. ፮፥፲፯)፡፡ ለዚህም ነው ካህኑ በሥርዓተ ቅዳሴ ጊዜ የቍርባኑ ምሥጢር እንዲገለጽልን «አልዕሉ አልባቢክሙልቦናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ» የሚሉን፡፡

ስምዐ ጽድቅ (የእውነት ምስክር) መኾን

ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ለእውነት እንጅ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልም» በማለት እንደ ተናገረው (፪ኛ ቆሮ. ፲፫፥፰)፣ ቤተ ክርስቲያን በሰማዕትነት የምትዘክራቸው ቅዱሳን በሙሉ ለእውነት ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡትን አባቶች እና እናቶችን ነው፡፡ በፍርኀትና በሐፍረት፣ በይሉኝታና በሐዘኔታ እውነትን አለመመስከር በክርስቶስ ፊት ያስጠይቃል እንጅ አያስመሰግንም፡፡ ኒቆዲሞስ ያለ ፍርኀትና ያለ ሐፍረት በካህናቱ ፊት እውነትን መስክሯል፡፡ ካህናቱን መጽሐፍ ጠቅሶ እውነትን ተናግሮ አሳፍሯቸዋል፡፡ እውነትንና ፀሐይን ፈርቶ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ በመሪዎችና በታላላቅ ባለ ሥልጣናት ፊት እውነትን መመስከር ክርስትናችን የሚያስገድደን ዐቢይ ቁም ነገር ነው (ሉቃ. ፲፪፥፫-፭)፡፡

ትግሃ ሌሊት (በሌሊት ለአገልግሎት መትጋት)

እንደ ሌሊት ለመንፈሳዊ ሕሊና፣ ለተመስጦ የሚመች ጊዜ የለም፡፡ ቀን ለሥጋ ሲራወጥ የነበረ አካልና መንፈስ ሌሊቱን ለነፍስ በመገዛት ሥጋውን ማድከም አለበት፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀኑን በቅዳሴ፤ ሌሊቱን ደግሞ በማኅሌት፣ በሰዓታት፣ በኪዳን እግዚአብሔርን ስታምሰግን  የምታድረው፡፡ ‹‹ሌሊትስ ጌታን ለማመስገን የተፈጠረ ድንቅ ጊዜ ነው›› እንዳለ ቅዱስ ማር ይስሐቅ፡፡ ጌታችንም ሐዋርያቱን ‹‹ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ›› ብሏቸዋል (ማቴ. ፳፮፥፵፩)፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያን እንደ ኒቆዲሞስ ለኪዳን፣ ለማኅሌት፣ ለጸሎት በሌሊት የሚገሰግስ ምእመንን ትፈልጋለች፡፡

እስከ መጨረሻ መጽናት

ክርስትና ለጀመሩት ሳይኾን ለጨረሱት፤ ለወጠኑት ሳይኾን ለፈጸሙት የድል አክሊል የምትሰጥ መንገድ ናት፡፡ ስለዚህም የመሮጫ መሙ ጠበበን፤ ሩጫው ረዘመብን ብለው ከመስመሯ ለሚወጡ ዴማሶች ቦታ የላትም (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፲)፡፡ ጌታችንን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ሺሕ ሕዝብ ቢከተለውም እስከ መስቀሉ አብረውት የነበሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የተወሰነው ሕዝብ ቀድሞም የተከተለው ለምግበ ሥጋ ነበርና ቀራንዮ ላይ አልተገኘም፡፡ ቀራንዮ ላይ ምግበ ነፍስ እንጅ ምግበ ሥጋ የለምና፡፡ ሌሎችም አይሁድን ከመፍራታቸው የተነሣ ከመስቀሉ ሥር አልተገኙም፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ክርስቶስ በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው በለየበት ሰዓት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ኾኖ የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከመስቀል አውርዶ፣ ገነዞ በሐዲስ መቃብር ለመቅበር ታድሏል፡፡

በዚህ የመከራ ሰዓት ከዮሐንስና ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ውጭ ማንም በሥፍራው አልነበረም፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር የተገኙት የቁርጥ ቀን ልጆች ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ናቸው፡፡ ይህም ኒቆዲሞስ ፈተናውን ዅሉ ተቋቁሞ እስከ መጨረሻው ለመጽናቱ ምስክር ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታችን በምቹ ጊዜ የምናገለግል፣ ፈተና ሲመጣ ግን ጨርቃችን (አገልግሎታችንን) ጥለን የምንሮጥ፣ ሰበብ አስባብ ፈልገን የምናፈገፍግ ብዙዎች ነን (ማር. ፲፬፥፲፭)፡፡ ዕውቀት፣ ሀብት እና ጊዜ ጣኦት ኾኖበት ከመሃል መንገድ የቀረውን፤ ሩጫውን ያቋረጠውን፤ ከቤተ ክርስቲያ አገልግሎት የራቀውን ክርስቲያን ቈጥረን አንጨርሰውም፡፡ ጌታችን በትምህርቱ «ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል» (ማቴ.፳፬፥፲፫) በማለት የድኅነት ተስፋ ሰጥቶናልና ዅላችንም እንደ ኒቆዲሞስ እስከ መጨረሻው በሃይማኖታችን ልንጸና ይገባናል፡፡

በአጠቃላይ ከኒቆዲሞስ ሕይወት ብዙ ቁም ነገሮችን እንማራለን፡፡ የኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ መምጣት ለምሥጢረ ጥምቀት ትምህርት መገለጥ ምክንያት እንደ ኾነ ዅሉ፣ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን በቅዳሴው፣ በኪዳኑ፣ በሰዓታቱ፣ በማኅሌቱ ብንሳተፍ ረቂቅ የኾነው ሰማያዊ ምሥጢር ፍንትው ብሎ ይገለጥልናል፡፡ እንደ ኒቆዲሞስ ራሳችንን ዝቅ አድርገን በምሥጢራት በመሳተፍ ለታላቅ ክብር እንበቃ ዘንድ የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም

በአያሌው ዘኢየሱስ

መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፤›› (ዮሐ.፫፥፫)፡፡

ይህ ቃል ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ካስተማረው ትምህርት የተወሰደ ኃይለ ቃል ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ብዙ የተማረ፤ ብዙ ያወቀ የሃይማኖት ሊቅ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ሊቅ፣ ምሁር፣ አለቃ ተብሎ ተጠርቶአል፡፡ በጊዜው ከነበሩ ሰዎች ከፍ ያለና የላቀ ዕውቀት የነበረው ሰው ነበር፡፡ በሌሊት ወደ ጌታ እየመጣ ይማር ነበር፡፡ የማታ ተማሪ ነበር፡፡ ቀን፣ ቀን የምኵራብ አስተማሪ ኾኖ ብዙ ሰዎችን ያስተምር ስለ ነበረና እርሱ የሚያስተምራቸው አይሁድ ጌታችንን ስላልተቀበሉ በቀን ለመማር አመቺ ጊዜ አልነበረውም፡፡

በአይሁድ ሕግ ጌታን የሚከተልና የሚቀበል ሰው ከምኵራብ ይባረር ስለ ነበረ እነርሱን ላላማስቀየም ኒቆዲሞስ ማታ፣ ማታ ነበር የሚማረው፡፡ ኒቆዲሞስ፡- ‹‹ከሰው ችሎታ በላይ የኾኑ ተአምራትን ስለምትሠራ እኛን ለማስተማርና ለመምከር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልከህ የመጣህ ነህ›› ብሎ ለጌታችን መስክሮለታል፡፡ ጌታችንም፡- ‹‹እናንተን ለማስተማር እንደ መጣሁ ከተረዳህ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም›› አለው፡፡

ኒቆዲሞስ ስላልገባው ‹‹እኔ አርጅቼአለሁ፤ እንዴት ነው ወደ እናቴ ማኅፀን ተመልሼ የምገባውና ዳግም የምወለደው?›› ብሎ ኢየሱስ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ጌታችንም፡- ‹‹ሰው ከሰው ከተወለደ ሥጋዊ ነው፤ የሰው ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ለመኾን በመንፈስ መወለድ አለበት፡፡ ከእግዚአብሔር መወለድ ነፋስ ከየት ተነሥቶ ወዴት እንደሚነፍስ እንደማይታወቅ ያለ ረቂቅ ምሥጢር ነው›› አለው፡፡ አሁንም ያ ሊቅ፤ ያ አዋቂ ‹‹አልገባኝም›› አለ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- ‹‹አንተ የእስራኤል መምህር እና ሊቅ ኾነህ እንዴት ይህን አታውቅም?›› አለው፡፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የሚወጣ የለም፤ የምናውቀውንም እንናገራለን ካለው በኋላ ጥያቄውን በዚህ ገታ፡፡

ኒቆዲሞስ  ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ መማሩ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው፡፡ አይሁድ ወገኖቹ ጌታን ሳይከተሉት እርሱ ግን ጌታን መውደዱ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ የሚያመሸው ከጌታ ጋር ነበር፡፡ ባለችው ትርፍ ጊዜው ዅሉ ወደ ፈጣሪው ይሔድ ነበር፡፡ ይህ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ቀን ሲያስተምርና ሲደክም ስለሚውል ማታ፣ ማታ ማረፍ ይገባው ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ቤቴ ገብቼ ልረፍ አላለም፡፡ ባለ ሥልጣንና ባለጠጋ ስለ ነበር ደጅ የሚጠናው ሕዝብና መሰል ባልንጀሮቹ ይፈልጉት ነበር፡፡ ይኹን እንጂ ከእነርሱ ጋር አላመሸም፡፡

ከዚህ አባት ታላቅ ትምህርት ልንማር ያስፈልጋል፡፡ እኛ ዛሬ የምናመሸው የት ነው? የምናመሸውስ ከማን ጋር ነው? ምን ስናደርግ ነው የምናመሸው? ኒቆዲሞስ ቤቱ አልነበረም የሚያመሸው፤  ከእውነተኛው መምህር ጋር እንጂ፡፡ ኒቆዲሞስ ጽድቁንና በረከቱን እየያዘ ነበር ወደ ቤቱ ይገባ የነበረው፡፡ እኛ ወደ ቤታችን የምንገባው እየከበርን ነው ወይ? ጸድቀን ነው የምንገባው ወይስ ጐስቁለን?

የዛሬ ዘመን ሰው እየሰከረ፣ እየጨፈረ፣ እየደማ፣ እየቆሰለ አእምሮውን ስቶ ነው ወደ ቤቱ የሚመለሰው፡፡ የሚሞትም አለ፡፡ በቤት ያሉት ወገኖቹም ‹‹እንቅፋት ያገኘው ይኾን? ይሞት ይኾን?›› እያሉ እየተሳቀቁ ነው የሚያመሹት፡፡ ማምሸት እንደ ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር ነው እንጂ! ኒቆዲሞስ ከጌታ ጋር በማምሸቱ ፈጣሪውን አወቀ፡፡ ጌታን ማወቅ ብቻ ደግሞ አይበቃም፡፡ ማወቅማ አጋንንትም ያውቁታል፡፡ ከመንፈስ መወለድ ያስፈልጋል፡፡

የሰው ልጅ ዕፀ በለስን በበላ ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ተነጥቆ ነበር፡፡ ጌታችን መጥቶ ዳግም ሰው እስከሚያደርገን ድረስ የሰይጣን ልጆች ኾነን ነበር፡፡ ከዚያም በዐርባና በሰማንያ ቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስና ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደናል፡፡ እግዚአብሔርን አባታችን የምንለውም ስለዚህ ነው፡፡ ከእርሱ ከተወለድንና ልጅነትን ካገኘን፣ እንደ ገና ልጅነታችንን እንዳናጣ አክብረን እንያዘው፡፡ መጀመሪያም አላወቅንበትም ነበር፡፡ አዳም ከገነት የሚወጣ አልመሰለውም ነበር፡፡ ሰይጣን አታሎታል፡፡ እኛም እንደ ገና እንዳንታለል ልጅነታችን እንዳይሰረዝ እንጠንቀቅ፡፡

የብዙዎቻችን ልጅነት ዛሬ እየተወሰደ ነው፡፡ ልጅነታችንን እያስነጠቅነው ነው፡፡ እነኤሳው እየነጠቁን ነው፡፡ ብዙዎች እንደ ያዕቆብ ልጅነታችንን ሊወስዱብን አሰፍስፈዋል፡፡ ሰይጣን እንደ አዳም ሊነጥቀን አሰፍስፏል፡፡ ኒቆዲሞስ አርጅቶ ነበር፡፡ በጥምቀትና በንስሐ ግን አዲስ ሕይወትን አግኝቶአል፤ ታድሷል፡፡ ያረጀው ሕይወቱ ለምልሟል፡፡ እኛም ዛሬ በጣም አርጅተናል፡፡ ያረጀው ሰውነታችንን በሥጋውና በደሙ በንስሐ እናድሰው፡፡ ይህ ከኾነ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርሰው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

  • ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ሥልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ በአዲስ አበባ የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ደብር የበላይ ሓላፊ፤ በዚሁ ደብር በአስተዳዳሪነት ባገለገሉባቸው ዓመታት ካስተማሩት ትምህርተ ወንጌል የተወሰደ (መጋቢት ፳፩ ቀን ፲፱፻፹፭ .ም)፡፡

ኒቆዲሞስ

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ፡፡ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ዅሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ፡፡ በጽዮን መለከት ንፉጾምንም ቀድሱ፤›› በማለት የዐዋጅ አጽዋማትን እንድንጾም እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ ኢዩኤል ላይ አድሮ ነግሮናል (ኢዩ. ፩፥፲፬፤ ፪፥፲፭)፡፡ ከእነዚህ አጽዋማት መካከልም ዐቢይ ጾም አንዱ ነው፡፡

ይህ ጾም የጠፋውን የሰውን ልጅ ለመፈለግ፣ የሞተውን አዳምን ለማስነሣት ሰው ኾኖ ወደዚህ ዓለም የመጣው፣ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመብል የተጀመረውን የሞት መንገድ ለማጥፋት ሲል የጾመው ጾም ነው፡፡ እኛም አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሠረት በዐቢይ ጾም ወራት ‹ዘወረደ› ብለን ጀምረን በዓለ ትንሣኤን እስከምናከብርበት ዕለት ድረስ ያሉትን ሰንበታት በልዩ ልዩ ስያሜ በመጥራት የተከፈለልንን ዋጋ እያሰብን ቃለ እግዚአብሔር እንማራለን፤ እንዘምራለን፤ እንጸልያለን፡፡ ከእነዚህ ሰንበታት መካከል በሰባተኛው ሳምንት የሚገኘው ወቅት ‹ኒቆዲሞስ› ይባላል፡፡

ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የነበረው ሰው ነው፡፡ የአይሁድ አለቆች አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ምልክት አሳየን›› እያሉ ይፈታተኑት ነበር፡፡ ጌታችን ስለ ሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ እያስረዳ ቢያስተምራቸውም እነርሱ ግን አልገባቸውም ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ጌታችን በተአምራቱ የታመሙትን ሲፈውስ ‹‹ሕጋችን ተሻረ›› ይሉ ነበር፡፡ በዚህ ዅሉ ተአምራትና ትምህርት የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ወቅት ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኒቆዲሞስ በቀን እንዳያደርገው አይሁድን ቢፈራ፣ አንድም ጊዜ ባያደርሰው እንደ ባልንጀሮቹ ክርስቶስን ሳይቃወም በሌሊት ወደ ጌታችን ዘንድ እየሔደ ወንጌልን ይማር ነበር፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነፍስ የታመሙትን በቃሉ፣ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ ኒቆዲሞስ ሰምቶ፣ ተመልክቶ በመምህርነቱ ሳይኮራ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ በልቦናው የተሳለውን እውነትን የመፈለግ ስሜት አንግቦ ከጌታው፣ ከመምህሩ ከክርስቶስ ዘንድ በሌሊት ይገሰግስ ነበር (ዮሐ. ፫፥፩)፡፡ ምስክርነቱንም እንዲህ ሲል መስጠት ጀመረ፤ ‹‹መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከኾነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና፤›› (ዮሐ. ፱፥፳፬፤ ሐዋ. ፲፥፴፰)፡፡

ይህን ምስክርነቱን በሚሰጥበት ጊዜም ጎዶሎን የሚሞላ፤ አላዋቂነት በአዋቂነት የሚለውጥ፤ ከምድራዊ ዕውቀት ወደ ሰማያዊው ምሥጢር የሚያሸጋግር አምላክ ‹‹ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም፤›› በማለት የአይሁድ መምህር ለኾነው ኒቆዲሞስ ቢያስተምረው ምሥጢሩ አልተገለጠለትም ነበርና ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?›› በማለት ጥያቄ አቅርቧል (ዮሐ. ፫፥፮፤ ፩ኛጴጥ. ፩፥፳፫)፡፡ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፤›› (ኤፌ. ፭፥፳፮) በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ቢያስረዳውም ምሥጢሩ ከአቅሙ በላይ ስለ ኾነበት እንደምን ይቻላል? በማለት ጠይቋል፡፡

አበ ብዙኃን አብርሃም ከአምላኩ ሞገስን አግኝቶ የሰዶምና ገሞራ ጥፋት እንዳይደርስ ለመማለድ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር እንደ ነበረ፤ ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምሥጢር ከአምላኩ በጠየቀ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- ‹‹አንተ የእስራኤል መምህራቸው ኾነህ ሳለ ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራችሁ ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለምሙሴምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡ ያመነበት ዅሉ ለዘለዓለም ሕያው እንዲኖር እንጂ እንዲጠፋ አይደለም ...፤›› እያለ ሰው በመብል ምክንያት የአምላኩን ትእዛዝ አፍርሶ ከእግዚአብሔር ቢለይም የሰው ልጅ ያጣውን ልጅነት ለመመለስ፣ ስመ ክርስትናን፣ ሀብተ ወልድን ለመስጠት ጌታችን መምጣቱን አስረዳው (ዮሐ. ፫፥፲፬)፡፡ ይህን የክርስቶስን የማዳን ሥራና በሥጋ መገለጥም ‹‹ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ አመከርከኒ ወኢተረከ ዐመፃ በላዕሌየ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው፤ ልቤን ፈተንኸው፡፡ በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ፈተንከኝም፡፡ ምንም አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤›› (መዝ. ፲፮፥፫) በማለት ቅዱስ ዳዊት ከኒቆዲሞስ ሕይወት ጋር በማዛመድ አመሥጥሮታል፡፡

በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምሥጢሩ የተገለጸለት ኒቆዲሞስ ቀድሞ በአደባባይ ሔዶ መማርን ይፈራ እንዳልነበረ ምሥጢሩ ሲገለጽለት ግን አይሁድ ጌታችንን በሰቀሉት ዕለት ፍርኃት ርቆለት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበር በቃ፡፡ ‹‹ወአልቦ ፍርኃት ውስተ ተፋቅሮትነ፤ ፍጹም ፍቅር ፍርኃትን አውጥቶ ይጥላል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፯፥፶፰፤ ፩ኛዮሐ. ፬፥፲፰)፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ያመነየተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ፣ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል›› (ማር. ፲፮፥፮) በማለት በሰጠን ቃል ኪዳን መሠረት በአምላክነቱ አምነን የመንግሥቱ ወራሾች እንኾን ዘንድ ለኒቆዲሞስ ምሥጢሩን እንደ ገለጸ ለእኛም ይግለጽልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ክርስቲያናዊ ምግባርን ከገብር ኄር እንማር

በዲያቆን አባተ አሰፋ

መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛው ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ‹ገብር ኄር› የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ትርጕሙም ‹በጎ አገልጋይ› ማለት ሲኾን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ነው (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የኾነው ይህ የወንጌል ክፍል በርካታ መልእክትታን በውስጡ ይዟል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ሓላፊነት ላይ የሚገኙ ሰዎች ትኩረት ሰጡባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ይጠቁማል፡፡ ይህን ለመረዳት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመርያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና ነጥቦችን መመርመር ጠቃሚ ነው፤

በዚህ ምሳሌያዊው ታሪክ አንድ ጌታ አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደ ሰጣቸው ተጠቅሷል፡፡ ከታሪኩ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ እንዲያተርፉበት ገንዘቡን ለአገልጋዮቹ ሰጥቷቸዋል፡፡ ሰውዬው ማትረፍ በመፈለጉ ብቻም ገንዘቡን ያለ አግባብ አልበተነም፡፡ ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ እንደየችሎታቸው መጠን እንዲሠሩበት አከፋፈላቸው እንጂ፡፡

ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደ ኾነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት፣ ሁለት፣ አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡ የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለን ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የባለ መክሊቱን ቅንነት እናስተውላለን፡፡

ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት አገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደ ሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ተመልሷል፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደ ሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የኾነ መክሊትን በመስጠት እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናስተውለው ከአእምሯቸው በላይ ሳይኾን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደ ሰጣቸው ነው፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት፣ እንደዚሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፈው ከጌታቸው ፊት እንደ ቆሙ፤ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታ ቦታ እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው አገልጋይ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት ምድርን ቆፍሮ እንደ ቀበረ፤ ከዚህም አልፎ ‹‹ምን አደረግህባት?›› ተብሎ ሲጠየቅ የዐመፅ ንግግር እንደ ተናገረ፤ በዚህ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው እንረዳለን፡፡ በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችን፣ ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጠል እንመልከታቸው፤

የአገልጋዮቹ ጌታ

ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመኾኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው፡፡ ባለ መታዘዙ ምክንያት በክፉው አገልጋይ ላይ የፈረደበትን ፍርድ (ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት፣ በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት የሚለው) የጌታው ሙሉ ሥልጣን ያሳያል፡፡ ይህ ጌታ ፍርዱ በእውነት ላይ የተመረኮዘ መኾኑንም በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት ሁለቱ አገልጋዮቹ ከሰጣቸውን ክብር መረዳት ይቻላል፡፡

በጎ እና ታማኝ አገልጋዮች

በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በጎ ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ቍጥር ያለው መክሊት በመቀበላቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ብዛት ሳይኾን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡

ክፉና ሰነፍ አገልጋይ

አንድ መክሊት የተቀበለውን አገልጋይ ከሁለቱ አገልጋዮች ያሳነሰውም ከአንድ በላይ መክሊት አለመቀበሉ ሳይኾን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ አገልጋይ ሦስት መሠረታዊ ስሕተት ፈጽሟል፤

የጌታውን ትእዛዝ በቸልተኝነት መመልከቱ የመጀመርያው ስሕተቱ ነው፡፡ ጌታው ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትእዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡

ሁለተኛው ስሕተቱ ጌታው መክሊቱን በተቆጣጠረው ጊዜ የዐመፅ ቃል መናገሩ ነው፡፡ ጌታው ከሔደበት ቦታ ተመልሶ በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ይህን አገልጋይ ሲጠይቀው፡- «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደንህ አውቃለሁ፡፡ ስለ ፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤» ሲል ነበር የመለሰለት፡፡ ይህ ምላሽ ከዐመፃ ባሻገር የሐሰት ቃልም አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢኾን ኖሮ ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደ ነበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡

ሦስተኛው ስሕተቱ ደግሞ ዕድሉን ለሌሎች አለመስጠቱ ሲኾን፣ ይህ አገልጋይ በተሰጠው መክሊት ነግዶ ማትረፍ ቢሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች መስጠት ሲገባው መክሊቱን ቆፍሮ ቀብሮታል፡፡ ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትእዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ እርሱ መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ በውስጡ የተቀረፀው የዐመፅ መንፈስ ለመኾኑ ለጌታው የሰጠው ረብ የሌለው ምላሽ ማስረጃችን ነው፡፡

የአገልጋዮቹ ጌታ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደ ኾነ፤ ሦስቱ አገልጋዮች ደግሞ በተለያየ ደረጃ ያሉ ምእመናንን እንደሚወክሉ የቤተ ክርስቲያን መተርጕማን ያስተምራሉ፡፡ ከተጠቀሰው ታሪክ ከምንማራቸው ቁም ነገሮች መካከልም ሁለቱን እንመልከታለን፤

ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ጸጋ እንዳለ እንረዳበታለን

እግዚአብሔር አምላካችን እያንዳንዳችን በሃይማኖታችን ፍሬ እንድናፈራ ይፈልጋል፡፡ ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይልና ጸጋ ደግሞ እርሱ ይሰጠናል፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቍጥር እጅግ ብዙ ቢኾኑም በዓይነታቸው ግን በሁለት መክፈል እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምሥጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጠን ስጦታ ነው (ዮሐ.፫፥፫)፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደየአቅማችን ለመንፈሳዊ አገልግሎታችን ማስፈጸሚያ ይኾነን ዘንድ የሚሰጠን ስጦታ ነው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር፣ በልዩ ልዩ ልሳናት መናገር፣ አጋንንትን ማስወጣት፣ ወዘተ. የመሳሰሉት ጸጋዎች (ስጦታዎች) ከዚህኛው ዓይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው (፩ኛቆሮ.፲፪፥፬)፡፡

በመጀመሪያውም ይኹን በሁለተኛው ዓይነት ስጦታ በእኛ በተቀባዮች ዘንድ ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ ዳግመኛ በመወለድ ምሥጢር (በጥምቀት የሥላሴን ልጅ መኾን) ስላገኘው የልጅነት ጸጋ የሚያስብና በዚህም የሚደሰት ክርስቲያን ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ለዓመት በዓላት (ለመስቀል ደመራ፣ ለጥምቀት፣ ለፋሲካ፣ ወዘተ) ካልኾነ በስተቀር ክርስትናችን ትዝ የማይለን ክርስቲያኖች ጥቂቶች አይደለንም፡፡ እንደዚሁም ዘመዶቻችን ወይም ራሳችን ከዚህ ዓለም በሞት ስንለይ ካልኾነ በስተቀር በሕይወት ዘመናችን ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ የማንደርስ ብዙዎች ነን፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡

እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውኃ የፈሰሰውም በጦር ከተወጋው ከጌታች ጎን ነው (ዮሐ.፲፱፥፳፬)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይኼንን ዅሉ ምሥጢር ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፤›› በማለት ያደንቃል (፩ኛ ዮሐ.፫፥፩)፡፡ እኛ ልጆቹ እንኾን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅሩ ባሻገር ልጆቹ በመኾናችን መንግሥቱን እንድንወርስ መፍቀዱም ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከኾናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፤›› በማለት የሚነግረንም ይህንኑ ተስፋ ነው (ገላ.፬፥፯)፡፡

ትልቁ ችግር ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢኾን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለ ማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኞቻችን ክርስቲያን የክርስትና እምነት ደጋፊዎች እንጂ ተከታዮች አይደለንም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው ግን በምናሳየው የደጋፊነት (የቲፎዞነት) ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት የሚያስፈልገው በጊዜ እና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለኾነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታና ጊዜ ልንኖርበት የሚገባ ዘለዓለማዊ የሕይወት መስመር ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መኾኑን በሚገባ መረዳት ያስፈልገናል፡፡ በዚህ መክሊታችንም የታዘዝናቸውን ምግባራት ፈጽመን የሚጠበቅብንን ፍሬ ማፍራት አለብን፡፡ ካለዚያ መክሊቱን እንደ ቀበረው ሰው መኾናችን ነው፡፡

እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንገነዘብበታለን

እግዚአብሔር ያለ አንድ ዓላማ በሓላፊነት ለሰዎች ስጦታን አልሰጠም፤ አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለዓላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ መንጋውን እንዲጠብቁለት ልዩ ልዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ (ዮሐ. ፳፩፥፲፭፤ ገላ. ፩፥፲፭-፲፮)፡፡ ኾኖም ግን የተሰጣቸው ሓላፊነት የሚያስጨንቃቸው፤ ከልባቸው በትሕትና የሚተጉ ክርስቲያኖች የመኖራቸውን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን፣ ጸጋቸው የሚያስጠይቃቸው መኾኑን የዘነጉና መንገዳቸውን የሳቱም በርካታ ናቸው፡፡

በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል እንደ ድልድይ ኾነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈጽሙ አገልጋዮች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለ ክብራቸው ተሟጋች እንዲኾን፤ እርስበርስ ጎራ እንዲፈጥርና ‹‹የጳውሎስ ነኝ፤ የአጵሎስ ነኝ›› በሚል ከንቱና የማይጠቅም ሐሳብ እንዲከፋፈል የሚያደርጉ ሰባኪዎችም አይታጡም፡፡ በአጠቃላይ ዅላችንም በተሰጠን መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ ስለሚጠይቀን ከገብር ኄር ታሪክ በጎ አገልጋይነትን ተምረን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን፣ እንደየአቅማችን መልካም ፍሬን ማፍራት ይጠበቅብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

እንደ ገብር ኄር ታማኝ አገልጋዮች እንኹን

በአያሌው ዘኢየሱስ 

መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፱ .

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ ትምህርቱን ቃል በቃል ወይም በሰምና ወርቅ ወይም በምሳሌ አስተምሮአቸዋል፡፡ ሲያስተምርም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ የተለያዩ ምሳሌዎችን በማቅረብና ምሥጢሩን በማስረዳት ነበር፡፡ ስለዚህም ቃሉን ለገበሬዎች በዘርና በእንክርዳድ፤ እንደዚሁም በሰናፍጭ ቅንጣት፤ ለእናቶች በእርሾ፤ ለነጋዴዎች በመዝገብና በዕንቍ፤ ለዓሣ አጥማጆች በመረብ፤ ወዘተ. እየሰመሰለ ያስተምራቸው ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በዐሥሩ ቆነጃጅት፤ በሰርግ ቤት፤ በበግና በፍየል፤ ወዘተ. እየመሰለ ስለ መንግሥቱ በስፋት አስተምሯል፡፡ ጌታ ትምህርቱን በምሳሌ ያስተምር የነበረው አስቀድሞ፡- «አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሌት እናገራለሁ፤» ተብሎ በነቢዩ ዳዊት እንደ ተነገረ (መዝ.፸፯፥፪)፣ ቃሉን የሚሰሙት ዅሉ ትምህርቱ ሳይገባቸው እየተጠራጠሩ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱና ምሥጢሩ ግልጽ እንዲኾንላቸው ለማድረግ ነበር፡፡

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት በቤተ ክርስቲያን የሚቀርበው ንባብ፣ ስብከትና መዝሙር የሚያስረዳን ምሥጢርም ስለ አንድ በጎ እና ታማኝ አገልጋይ በምሳሌ የተነገረውን ትምህርት ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ንባብ ውስጥ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ሰዎች እንደ ሥራቸው መጠን እንደሚዳኙ በምሳሌ አስተምሯል፡፡ በዚህ ምሳሌ አንድ ጌታ ለሦስት አገልጋዮቹ ለአንዱ አምስት፤ ለአንዱ ሁለት እና ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ከሰጣቸው በኋላ ነግዱና አትርፉ በማለት እርሱ ወደ ሌላ አገር መሔዱ ተገልጦአል፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው የመጀመሪያው አገልጋይ በተሰጠው አምስት መክሊት ቆላ ወርዶ፣ ደጋ ወጥቶ ከነገደ በኋላ አምስት ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ ዐሥር መክሊት አኖረ፡፡ ሁለተኛውም በተሰጡት አምስት መክሊቶች ከነገደ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አስቀመጠ፡፡ ሦስተኛው ግን እንደ ሁለቱ አገልጋዮች ሳይወጣና ሳይወርድ፣ ሳይደክምና ሳያተርፍ በአቅሙ መጠን በተሰጠው አንድ መክሊት ሥራ ሳይሠራ መክሊቱን በጉድጓድ ቀበረው፡፡

ይህ ዅሉ ከኾነ በኋላ ለእነዚህ ሦስት ባሪያዎች በመጠን የተለያዩ መክሊቶችን ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር ሔዶ የነበረው ጌታቸው ወደ እነርሱ ተመልሶ መጣ፡፡ ከዚያም እያንዳንዳቸውን በየተራ እየጠራ በተሰጧቸው መክሊቶች ምን እንደ ሠሩ ጠየቃቸው፤ ተቆጣጠራቸው፡፡ በዚህ መሠረት አምስት መክሊቶችን የተቀበለው የመጀመሪያው አገልጋይ በጌታው ፊት ቀርቦ በተሰጡት አምስት መክሊቶች አምስት በማትረፍ ዐሥር መክሊቶችን ለጌታው አስረከበ፡፡ ሁለተኛውም እንዲሁ ሌሎች ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አራት መክሊቶች ለጌታው አስረከበ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነዚህ ሁለት አገልጋዮች ጌታ በእነርሱ ደስ በመሰኘቱ፡- ‹‹አንተ መልካም፣ በጎ እና ታማኝ ባርያ! በጥቂቱ ታምሃልና በብዙ ስለምሾምህ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› በማለት ሁለቱንም ወደ መንግሥቱ አስገባቸው፡፡

የተሰጠውን አንድ መክሊት ምንም ሥራ ሳይሠራና ሳያተርፍበት ጉድጓድ ውስጥ የቀበረው ሦስተኛው አገልጋይ ግን፡- ‹‹ጌታ ሆይ፣ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መኾንህን ስለማውቅና ስለ ፈራሁ መክሊትህን ጉድጓድ ቆፍሬ በመቅበር አቆይቼልሃለሁና እነሆ ተረከበኝ!›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ፡- ‹‹አንተ ክፉና ሐኬተኛ ባርያ! በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰው መኾኔን ካወቅህ ገንዘቤን ለሚነግዱበት ወይም ለሚለውጡ ሰዎች በመስጠት እንዲያተርፉበት ማድረግና ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ ከእነርሱ መቀበል እችል ነበር፡፡ አንተ ይህን ሳታደርግ ጭራሹኑ በድፍረት እነዚህን በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ክፉ ቃላትን ስለ ተናገርህ ቅጣት ይገባሃል!›› ሲል መለሰለት፡፡ ከዚያም፡– ‹‹ያለውን መክሊት ውሰዱና ዐሥር መክሊት ላተረፈው ጨምሩለት፤ላለው ይሰጠዋል፤ ይበዛለትማል፡፡ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ ስለዚህ የማይጠቅመውን ባሪያ ወደ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ውጪ አውጡት!›› ብሎ ለወታደሮቹ አሳልፎ ሰጠው፡፡

በዚህ የወንጌል ቃል «ወደ ሌላ አገር የሚሔድ ሰው» ተብሎ የተጠቀሰው ባለጠጋ ቅን ፈራጅ የኾነው የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት አገልጋዮች የሚወክሉት ምእመናንን ወይም እኛን ነው፡፡ መክሊት የተባለው ደግሞ በጎ የሚያሰኘው መልካም ሥራ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች ምግባርን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረው በያዙ ጻድቃን ይመሰላሉ፤ መክሊቱን ጉድጓድ በመቆፈር የቀበረው ክፉና ሐኬተኛ አገልጋይ ደግሞ ምግባርና ሃይማኖት የሌላቸው ኃጥአን ምሳሌ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመካከላችን ተገኝቶ ወንጌለ መንግሥቱን ከሰበከልን በኋላ ለእያንዳንዳችን አንድ፣ ሁለትና አምስት መክሊቶችን በመስጠት ‹‹ለፍርድ እስከምመጣ ደረስ ነግዳችሁና አትርፋችሁ ጠብቁኝ›› ብሎን በዕርገቱ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ  ሔዷል፡፡ ዅላችንም ከእግዚአብሔር የተለያዩ መክሊቶችን ተቀብለናል፤ እንድንነግድባቸውና እንድናተርፍባቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ቃሉን ባስተማረበት መልእክቱ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ ለአንዱም በዚያው መንፈስ ዕውቀትን መናገር ይሰጠዋል፡፡ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፤ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፤ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፤ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፤ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፤ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል፡፡ ይህን ዅሉ ግን ያ፣ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል፤» (፩ኛ ቆሮ.፲፪፥፰-፲፩)፡፡

እግዚአብሔር ለልጆቹ የሰጣቸው መክሊት ብዙ ነው፤ ለአንዱ የመስበክ፣ ለሌላው የማስተማር፣ ለሌላው የመቀደስ፣ ለሌላው የመዘመርመ ለሌላው የመባረክ፣ ለሌላው የማገልገል፣ ወዘተ. መክሊቶችን ወይም ልዩ ልዩ ጸጋን ሰጥቶአል፡፡ አንድ ሰው የሚሰጠው አንድ መክሊት ብቻ አይደለም፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ መክሊቶች ሊሰጡት ይችላል፡፡ በፍርድ ቀን ዅሉም ሰው የሚፈረድበትም በተሰጠው መክሊት ትርፍ መሠረት ነው፡፡ በተቀበለው መክሊት የሚያተርፍ ሰው በፍርድ ቀን በኢየሱስ ክርስቶስ፡- ‹‹መልካም፤ አንተ በጎ፣ ታማኝም ባርያ! በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙም እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› የሚል ቃል ይሰማል፡፡ መክሊቱን መሬት ቆፍሮ የሚቀብር አገልጋይ ግን በውጪ ባለው ጨለማ ውስጥ ተጥሎ በዚያ በልቅሶና ጥርስ በማፋጨት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ዅሉም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተለያዩ ስጦታዎችን ወይም መክሊቶችን ተቀብሏል፡፡ ይኹን እንጂ ዅሉም መክሊቱን ቆፍሮ ስለ ቀበረ ለእግዚአብሔር ምንም ሊያተርፍ አልቻለም፡፡ በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ክፉና ሐኬተኛ አገልጋይ የተሰጠውን መክሊት ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራበት ወይም ሳይነግድበት ወይም ሳያተርፍበት በመሬት ውስጥ ቆፍሮ በማስቀመጡና ጌታው ሲመጣ ያለ ትርፍ በማስረከቡ በዚህ ዘመን ከምንገኝ ሰዎች እጅጉን ይሻላል፡፡ ምክንያቱም እኛ መክሊቶቻችንን ጠብቀን በማቆየት ለእግዚአብሔር ማስረከብ እንኳ አልቻልንምና፡፡ ዛሬ መክሊት የተቀበለ ዅሉ መክሊቱን ቀብሯል ወይም ጥሏል ለማለት ያስደፍራል፡፡ አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ በተሰጠው የመቀደስ መክሊት መቀደስ ሲገባው የሚዘፍን ከኾነ መክሊቱን ጥሏል፡፡

አንድ የመዘመር መክሊት የተሰጠው አገልጋይ ለእግዚአብሔር መዘመር ሲገባው የሚዘፍን ወይም ሰዎችን የሚያማ ወይም የሚሳደብ ከኾነ መክሊቱን ጥሏል፡፡ ትክክለኛውን የወንጌል ትምህርት እንዲያስተምርና ሰዎችን በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስገባ የማስተማር መክሊት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለ ሰባኬ ወንጌል የኑፋቄ ትምህርት በማስተማር የዋሃንን ወደ ሲኦል የሚመራ ከኾነ መክሊቱን ጥሎታል ወይም አጥፍቶታል እንጂ አልቀበረውም፡፡ በተሰጠው የመባረክ መክሊት ወይም ሥልጣን ምእመናንን መባረክና ኃጢአታቸውን መናዘዝ ሲገባው ለጥንቆላ ሥራ ተቀምጦ እፈርዳለሁ የሚል ከኾነ መክሊት የተባለ ክህነቱን አቃሎአታል፤ አጥፍቷታል እንጂ አልቀበራትም፡፡ በእግዚአብሔር ዐውደ ምሕረት ላይ ወንጌልን መናገር ሲገባው ተራ ወሬ ወይም ፖለቲካ የሚደሰኩር ከኾነ ይህ ሰው መክሊቱን ጥሏል፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ለዚህ ነው በዚህ ዘመን ያለን ሰዎች መክሊቱን ከቀበረው ሰው ያነስን፤ ክፉዎች እና ሐኬተኞች ነን የምንለው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን በወንጌል እንደ ተነገረለት ለጻድቃን ሊፈርድላቸውና በኃጥአን ሊፈርድባቸው ዳግመኛ ወደ ምድር ይመጣል፡፡ ከፍርዱ በፊት ዅላችንንም በሰጠን መክሊቶች መጠን ይቆጣጠረናል፡፡ ስለዚህም አንድ መክሊት የተሰጠን ሁለትና ከዚያ በላይ፤ ሁለት የተሰጠን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ፤ አምስት የተቀበልነውም አምስትና ከዚያም የሚበልጡ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅብናል፡፡ ለመኾኑ በተሰጠን መክሊት እኛ ያተረፍነው ምንድር ነው? በዕርቅ ፋንታ ጠብን የምናባብስ ከኾንን በመክሊታችን ሰዎችን አጉድለናል እንጂ ማትረፍ አልቻልንም፡፡ በመመረቅ ፋንታ የምንራገም ከኾንን መክሊታችንን ጥለናል፡፡ በመጸለይ ፋንታ ለመደባደብ የምንጋበዝ ከኾነም የተሰጠንን መክሊት አጥፍተናል፡፡ የገብር ኄርን ሰንበት ዛሬ ስናከብር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ እያንዳንዳችንን፡- ‹‹ታተርፉበት ዘንድ የሰጠኋችሁን መክሊት እስከነትርፉ አስረክቡኝ!› ቢለን ምንድር ነው የምናስረክበው? ለጥያቄው የምንሰጠውስ ምላሽ ምን የሚል ይኾን?

በወንጌል የተጠቀሰው ያ፣ ሰነፍ አገልጋይ መክሊቱን መቅበሩ ሳያንሰው ለጌታው የሰጠው ክፉ መልስ ለከፍተኛ ቅጣት ዳርጎታል፡፡ ለጌታው፡- «ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መኾንህን አውቃለሁ፤» የሚል ምላሽ ነበር የሰጠው፡፡ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ከዚህ ሰው ጋር የሚመሳሰል ጠባይ አላቸው፤ እነርሱ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምንም ነገር ሳያውቁ የእግዚአብሔርን ጠባይና ዕውቀት በእነርሱ የዕውቀት ሚዛን ለመመዘን ይሞክራሉና፡፡ አንድ ክርስቲያን በጠና ሕመም ሲታመም ወይም ከልጆቹ አንዱ በሞት ሲለይበት ወይም ንብረቱ በእሳት ቃጠሎ ሲወድም ይህን አደጋ ያደረሰበት እግዚአብሔር እንደ ኾነ አድርጎ በማሰብ የማይገቡ ቃላትን በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዝሩ ሰዎች አሉ፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች በእግዚአብሔር ህልውና ላይ በመምጣት «እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ ይህ ሕመም ወይም አደጋ በእኔ ላይ አይደርስም ነበር፤» ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ «እግዚአብሔር እንደዚህ የጨከነብኝ ምን አድርጌው ነው እያሉ እግዚአብሔርን እንደ ሐኬተኛው አገልጋይ ጨካኝ አምላክ የሚያደርጉት ሰዎችም አሉ፡፡

የጻድቁ የኢዮብ ሚስት በእግዚአብሔር ላይ በልቧ ስትሰነዝራቸው የነበሩ ቃላትን ይደግማቸው ዘንድ «እግዚአብሔርን ስደበውና ሙት» በማለት በእርሱ ላይ ልታነሣሣው ሞክራ ነበር፡፡ ነገር ግን «የለም» ወይም «ጨካኝ ነው» ብሎ በድፍረት እግዚአብሔርን መናገር ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨለማ የሚያስገባ ክፉ ቃል መኾኑን እናስተውል፡፡ በመሠረቱ ሊነቀፍ ወይም ሊወገዝ ወይም ሊኮነን የሚገባው ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቸር፣ ርኅሩኅ፣ ታጋሽ፣ ይቅር ባይ፣ መዓቱ የራቀ፤ ምሕረቱ የበዛ አምላክ ነው፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ያልዘራነውን የጽድቅ ፍሬ እንድንዘራና እንድናጭድ፤ ያልበተንነውንም መልካም ዘር በመበተን በፍርድ ቀን ምርቱን እንድንሰበስብ የሚፈልግ ጌታ ነው፡፡ እኛ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ በማፍራት የእነዚህ ፍሬዎችን ምርት በመሰብሰብ ሰማያዊ መንግሥቱን እንድንወርስ ይፈልጋል፡፡ እርሱ ለሚያምኑትና ለሚታመኑት ዅሉ ታማኝ ነው፤ የሚያምኑትን የሚክድ ጨካኝ ፈጣሪ አይደለም፡፡ ካልዘራበት የሚያጭድና ካልበተነበት የሚሰበስብ ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፤ ጨካኝ፣ ከሀዲና የማይታመንም ሰው ነው፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር በጎ እና ታማኝ አገልጋይ አጥቶአል፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታመን አገልጋይ አጥታለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ፡- «ዅሉ ዐመፁ፤ በአንድነትም ረከሱ፡፡ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ፤» (መዝ ፲፫፥፫) ተብሎ የተነገረው ለዚህ ዘመን አገልጋዮች ነው፡፡ የሰው ልጅ ለእግዚአብሔርና ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ አገልጋይ ሊኾን አልቻለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቃሉ የሚገኝ ሰው ለማግኘት ተቸግራለች፡፡ በጥቂቱ ታምኖ በብዙ ላይ ሊሾም የሚችል ሰው ስለ ጠፋ ቤተ ክርስቲያን ‹‹የሰው ያለህ!›› እያለች ነው፡፡ ለምእመናን መዳንና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚተጉ አገልጋዮች ቍጥር እየቀነሰ ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አገልጋዮችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሾማቸውና የሚሾማቸው ግን ራሳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያንንና መንጋውን ከጥፋት እንዲጠብቁ ነበር (ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡ ሕዝቡን ለመጠበቅ ተሹሞ የሚያጠፋ ጠባቂ ዕድል ፈንታውና ዕጣ ተርታው ትሉ በማያንቀላፋበትና እሳቱ በማይጠፋበት ዘላለማዊ ሲኦል ውስጥ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ አገልጋይ ቅጣቱ ዘላለማዊ መኾኑን ከወዲሁ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡

አምላካችን በዳግም ምጽአቱ እስከሚገለጥ ድረስ መንጋውን በመመገብ፣ ውኃ በማጠጣትና በማሳረፍ ፋንታ ለራሱ ብቻ የሚበላና የሚጠግብ፤ የሚጠጣና የሚሰክር፤ የሚያርፍና የሚዝናና ከኾነ እግዚአብሔር ዕድሉን ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ባለበት ጨለማ ውስጥ ያደርግበታል (ማቴ. ፳፬፥፵፭-፶፩)፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በተለያያ መልኩ የሚዘርፍና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን አገልጋይም ኾነ ተገልጋይ ከዚህ ጠባዩ ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡  የቤተ ክርስቲያን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለው ለዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በጥፊ የተመታው፤ ርኩስ ምራቅ የተተፋበት፤ የእሾኽ አክሊል የተቀዳጀው፤ በአጠቃላይ የተንገላታውና የሞተው ለዚህች ቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ነው፡፡ ስለ ኾነም ካህናትም ምእመናንም በጎ እና ታማኝ አገልጋዮች ልንኾን ይገባናል፡፡

የአምላካችን የእግዚአብሔር አብ ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይኹን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡