ወርኃ ጽጌ
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ያለው ወቅት ወርኃ ጽጌ (የጽጌ/የአበባ ወር) ይባላል፡፡ በወርኃ ጽጌ አበባዎች ያብባሉ፤ ፍሬም ያፈራሉ፤ በዚህም ወቅት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እንዲጠብቃት ከታዘዘው አረጋዊው ዮሴፍ ጋር ስትኖር መልኳ አንዳንድ ጊዜ እንደ ጽጌረዳ አበባ ቀይ ሁና፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ሮማን አበባ ነጭ ሁና ስትታየው፣ ቀይ የነበረው መልኳ ተለውጦ እንደ ሮማን አበባ ጸዓዳ ነጭ፣ ነጭ የነበረው እንደ ጽጌረዳ ቀይ ሲለወጥ በመደንገጥ እርሷ መሆኗን ለማረጋገጥ ‹‹ማርያም›› ብሎ እየጠራ ያረጋግጥ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ምሥጢር ሲያስረዳ ‹‹መልኳ እንደ ጽጌረዳና እንደ ሮማን አበባ ይለዋወጥበት ስለነበር በአንድ ዓይነት መልክ አላወቃትም›› ብሏል፡፡ በዚህም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር የስደቱ ጊዜ በወርኃ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡