‹‹የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ›› (ዮሐ.፪፥፲፮

በኢየሩሳሌም፤ ምኵራብ ተብሎ በተሰየመው የዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት ዕለተ እሑድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ አይሁድ ንጉሥ ናቡከደነፆር ቤተ መቅደስን ካፈረሰባቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን መማሪያ እና መጸለያ ስፍራ በማጣታቸው የሠሩት አዳራሽ ምኵራብ ነበርና፡፡ በዚያም ጌታችን በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ባገኘ ጊዜ ያየውን ባለመውደዱ የገመድ ጅራፍ ካዘጋጀ በኋላ በጎችንና በሮዎችን እንዲሁም ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የሻጮቹንም ገንዘብ በተነባቸው፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ይሸጡ የነበሩትን ደግሞ፤ ‹‹ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮)

ቅድስት

ቅድስት የሚለው ቃል ትርጉሙ ‹‹የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች›› ማለት ነው። ሥርወ ቃሉም ‹‹ተቀደሰ›› ሲሆን ፍቺው ደግም ‹‹ክቡር፣ ምስጉን፣ ምርጥ›› ማለት ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፹፬)

‹‹ኢየሱስን በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው ይህ ነው›› (ራእ. ፲፬፥፲፪)

በዮሐንስ ራእይ ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ኢየሱስን በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው ይህ ነው›› በማለት የተናገረው ኃይለ ቃል የመጨረሻውን ዘመን አስጨናቂ እና ፈታኝ መሆን እንዲሁም ክርስቲያኖች ይህን ተረድተው በትዕግሥት መጽናት እንደሚገባቸው ለማስረዳት ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር ፲፩ ላይ ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ፣ የስሙንም ምልክት የሚጽፉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት እንደሌላቸው፣ ሕዝብንና አሕዛብን ስለሚፈትነው፣ በመጨረሻ ዘመን ስለሚነሣው አውሬ እና በእርሱም ምክንያት ብዙዎች ወደ ዘለዓለማዊ እሳት እንደሚጣሉም ይገልጻል፡፡ (ራእ. ፲፬፥፲፪)

‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› (ሚል ፫፥፯)

የሰው ልጆችን ጥፋት የማይወደው ፈጣሪያችን እግዚአብሔር በንስሓ እንድንመለስ ይሻል፤ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ›› ብሎም ዘወትር ወደ እርሱ ይጠራናል፡፡ (ሚል ፫፥፯)

‹‹በወንድማማችነትም ፍቅርን ጨምሩ›› (፪ ጴጥ. ፩፥፯)

በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ፍቅር ልባዊ መዋደድ ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ፍቅር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ፍቅር ያስታግሣል፤ ፍቅር ያስተሳዝናል፤ ፍቅር አያቀናናም፤ ፍቅር አያስመካም፤ ፍቅር ልቡናን አያስታብይም፡፡ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም፤ ክፉ ነገርንም አያሳስብም፡፡ ጽድቅን በመሥራት ደስ ያሰኛል እንጂ፥ ግፍን በመሥራት ደስ አያሰኝም፡፡ በሁሉ ያቻችላል፤ በሁሉ ያስተማምናል፤ በሁሉም ተስፋ ያስደርጋል፥ በሁሉም ያስታግሣል፤ ፍቅር ለዘወትር አይጥልም፡፡›› (፩ ቆሮ. ፲፫፥፬-፰)

ስእለት

ስእለት ማለት ልመና፣  ምልጃ፣ ጸሎት፣ ጥየቃ እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት ሐዲስ ገልጸዋል፡፡ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ስእለት ይሳላሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹እግዚአብሔር የልቤን ጭንቀት ቢፈጽምልኝ እንዲህ አደርግለታለሁ፡፡ እመቤቴ ማርያም ስእለቴን ወይንም ልመናዬን ብትሰማኝ ለቤተ ክርስቲያን እንዲውል ጃን ጥላ አስገባለሁ››  ብለው ይሳለሉ፤ ወይንም አቅማቸው የፈቀደውን ነገር እንደሚሰጡ ቃል ይገባሉ፡፡ ስእለታቸውም ሲደርስ ‹‹እመቤታችን እንዲህ አድርጋልኛለች›› ብለው ለክብሯ መገለጫ ድባብ ወይንም የተሳሉትን ነገር ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣሉ፡፡(ገጽ ፰፻፵፪)

‹‹አሁንስ ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?›› (መዝ.፴፰፥፯)

በእግዚአብሔር ተስፋ መኖር በእርሱ ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ እግዚአብሔር ከጎናችን ሲሆንም እያንዳንዳችን ከምናስበው ዳርቻ መድረስ እንችላለን፡፡ ስለዚህ ተስፋችን የሚወሰነው በአምላካችን ላይ ባለን የእምነት ጥንካሬ ነው፡፡ ተስፋ በሕይወታችን ውስጥ ወደፊታችን የምንራመድበት መወጣጫ ድልድይ፣ የኑሮአችን መሠረት እንዲሁም የደስታችን መጀመሪያ ነው፤ በተስፋ ኖረን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት እንሸጋገራለንና፡፡

‹‹ከአነጋገርህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከአነጋገርህ የተነሣ በቃልህ ይፈረድብሃልና›› (ማቴ. ፲፪፥፴፯)

በአንደበታችን የምንናገረው ነገር መልካም ሲሆን ጽድቅ ሆኖ እንደሚቆጠርልን ሁሉ መጥፎ ከሆነ ደግሞ ኃአጢት ይሆንና በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ ያደርገናል፡፡ ኃጢአት በአብዛኛው ከንግግር የሚመነጭ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል እንደተጻፈው ‹‹ከአነጋገርህ የተነሣ ትጸድቃለህ፤ ከአነጋገረህ የተነሣ በቃልህ ይፈረድብሃልና።›› ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከት ውስጥ እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹በወንድሙ ላይ በከንቱ የሚቈጣ ሁሉ እርሱ ይፈረድበታል፤ ወንድሙንም ጨርቅ ለባሽ የሚለው በአደባባይ ይፈረድበታል፡፡›› (ማቴ. ፲፪፥፴፯፣፭፥፳፪)

ጽድቅ

ጽድቅ ማለት እውነት፣ ርግጥ፣ ቅንነት እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ መጽሐፋቸው ውስጥ ገልጸዋል፡፡ በመጽሕፍ ቅዱስ ላይ እንደተጻፈው ደግሞ ሰው በእግዚአብሔር ታምኖ በፊቱም ክብርና ሞገስ የሚያስገኝለት በጎ ሥራ ጽድቅ ይባላል፡፡ ‹‹መጽሐፍ፥ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፤ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጕበኞችን ተቀብላ፥ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው›› እንዲል፤ (ገጽ ፯፻፵፮፣ ያዕ. ፪-፳፬-፳፮)

ልደተ ክርስቶስ

‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፡፡…››