‹‹በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ፤ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል›› (መዝ. ፳፪፥፬)

ዓለም በኃጢአት እና ክፋት ተሞልታ በሰይጣን አገዛዝ ሥር ከሆነች ውላ አድራለች፤ የሰይጣን ሥራ ከዳር እስከዳር ተስፋፍቶ በበዛበት ወቅት ሰዎች የርኩስ መንፈስ ቁራኛ በመሆን የመከራ አረንቋ እየተፈራረቀባቸው ይገኛሉ፡፡ ጦርነት፣ ቸነፈር፣ ረኃብ፣ በሽታና ሥቃይ እንግልትም እየደረሰባቸው ነው፡፡

እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ክብር በዓል አደረሰን!

የዚህን ታላቅ የከበረ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ለማድረግ መታገል ይገባናል፤ እርሱ ከሰይጣን ወጥመድ ያድነን ዘንድ፤ በዘመናችን ሁሉም ይጠብቀን ዘንድ፤ ኃጢአታችንንም ያስተሠርይ ዘንድ፤ መከራችንንም ያርቅ ዘንድ፤ የምድራችንንም ፍሬ ይባርክ ዘንድ፤ ፈቃዱንም ለመሥራት ይረዳን ዘንድ፤ ከእኛ ወገን የሞቱትን ዕረፍተ ነፍስ ይሰጥ ዘንድ፤ ወደ መንገድ የሔዱ አባቶቻችንና ወንድሞቻተንን ወደ ቤቶቻቸው በሰላም በጤና ይመልሳቸው ዘንድ፤ በመካከላችንም ፍቅር ያደርግልን ዘንድ፤ እስከ መጨረሻዪቱም ሕቅታ ድረስ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ፤ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ ይለምናልና፡፡

‹‹በሕማም፣ በመከራና መሥዋዕት በመሆን ፍቅራችን ይፈተናል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ

ፍቅርን የሚያውቅ ሰው ለእግዚአብሔር እና ለሌሎች ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል፡፡ ሰው በመጀመሪያ መሥዋዕት ለማድረግ መልመድ ያለበት ከእርሱ ውጪ በሆኑ ነገሮች ማለትም ገንዘቡን፣ ጊዜውን እና ሀብቱን በመለገስ ነው፤ መስጠት ከመቀበል አንድ ነውና፡፡ ለሰዎች ደስታ እንደራሱ የሚጨነቅ እርሱ ፍቅርን ያውቃል፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ይኖራል፡፡ መሥዋዕትነት መክፈል ካልቻልን ግን ፍቅር አልገባንም ማለት ነው፤ አምላካችን እግዚአብሔርን ማፍቀር ካልቻልን ደግሞ ድኅነተ ሥጋንም ሆነ ድኅነተ ነፍስን ማግኘት አንችልም፡፡

‹‹እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› (ኢያ. ፳፬፥፲፭)

የሰው ልጅ በመላ ዘመኑ በሚያጋጥመው መከራ እና ሥቃይ ሊፈተን፤ ከባድ ችግርም ሊደርስበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ፈተናው ከእግዚአብሔር ሲሆን ለድኅነት እና ለበረከት ከጠላት ዲያብሎስ ሲሆን ደግሞ ለጥፋት የሚመጣ በመሆኑ ፍርሃት ሳይሆን ጥንቃቄና ጽናት ያስፈልጋል፤ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› እንደተባለው በእምነት ሁሉንም ፈተና ማለፍ ይቻላል፡፡ ይህን እውነት አውቀውና ተረድተው ወደ እግዚአብሔር መመለስ የሚፈልጉ ሰዎች ኢያሱ ‹‹እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› ብሎ እንደተናገረው ባዕድ አምልኮን ትተው እግዚአብሔርን ማምለክ ይኖርቸዋል፤ ካልሆነ ግን የዘለዓለም ቅጣት እንደሚጠበቃባቸው እሙን ነው፡፡ (ማር. ፭፥፴፮፤ ኢያ. ፳፬፥፲፭)

‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው›› (መዝ፣ ፻፲፰፥፻፭)

የእግዚአብሔር ሕግ ብርሃን ነው፤ ‹‹ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው›› ብሎ ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረው ከዚህ ከጨለማ እና ከተወሳሰበ ዓለም ከፈተና ያወጣን ዘንድ በትእዛዙ ልንኖር ይገባል፡፡ ማንኛውም ፍጡር የአምላኩን ስም የሚሰማበት ጊዜም ሆነ ሥፍራ  ይኖራልና ፈጣሪያችን እውነት እና ሕይወትም መሆኑን ተረድተን በመንገዱ መጓዝ የእኛ ፈንታ ነው፡፡  (መዝ፣ ፻፲፰፥፻፭)

‹‹ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ›› (ዮሐ. ፲፬፥፲፭)

ሰው አምላኩ እግዚአብሔርን ከወደደ ሁለተናውን ለእርሱ ይሰጣል፤ ከኃጢአት የነጻ ሆኖ ልበ ንጽሕ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ከፈጣሪያችን ስለምንረቅ ለሌላ ባዕድ ነገር ተገዢ እንሆናለን፡፡ ክርስቶስን በሙሉ ልባችን፤ ነፍሳችን፣ ኃይላችን ከወደድነው ግን ፍቅሩን ተረድተን ሁለመናችን ለእርሱ እንሰጣለን፤ እርሱም ደግሞ ከእኛ ጋር ይሆናል።

‹‹ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር›› (ኢሳ. ፩፥፲፰)

ብዙ ጊዜ በሕይወት በሚገጥመን ፈተናና ችግር ምክንያት ራሳችንን በመመርመር እግዚአብሔርን መማጸንን የመሰለ መፍትሔ ወይም የድኅነት መንገድ የለም፡፡ እስራኤል ከእግዚአብሔር ርቀው፤ ወደ ቃሉ መጠጋት በአቃታቸው ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ የመጣባቸው መቅሠፍት የኃጢአታቸው ውጤት ስለነበረ እግዚአብሔር አጥቦ ቅዱሳን ልጆቹ ሊያደርጋቸው የተዘጋጀ አባት በመሆኑ ‹‹ኑ እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር›› አላቸው፡፡ (ኢሳ. ፩፥፲፰)

‹‹ለታመሙት መድኃኒት አንተ ነህ›› (የዐርብ ሊጦን)

መድኃኒት ለሰው ልጅ ፈውስ መሆኑን እንረዳ ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በሥጋ በተገለጠበት ማለትም በዘመነ ሥጋዌው አስተምሯል፡፡ በዚያን ጊዜም ብዙዎች ወደ እርሱ እየቀረቡ ማንነቱን ለማወቅ ይጥሩ እና ትምህርቱንም ይሰሙ ነበር፡፡ እርሱም በመካከላቸው ሆኖ ወንጌልን ይሰበክላቸው፤ የታመሙትንም ይፈውሳቸው፤ የእጆቹን ተአምራት ዓይተውም ሆነ ሰምተው ያመኑትንም ያድናቸው ነበር፡፡ ‹‹ለታመሙት መድኃኒት አንተ ነህ›› እንደተባለው ፈውሰ ሥጋ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነም ተረዱ፡፡ (የዐርብ ሊጦን) 

ጾመ ሐዋርያት እና ጾመ ድኅነት

በዚህ ዓመት ጾመ ሐዋርያት ሰኔ ፩፤ ጾመ ድኅነት ደግሞ ሰኔ ፫ ቀን ይጀመራሉ፡፡ በመሆኑም የምንጠቀመው በራሳችን መልካም ተግባር፤ የምንወቀሰውም በራሳችን ኃጢአት መሆኑን ተረድተን ‹ይሄ የቄሶች፤ ይሄ የመነኰሳት ነው› የሚል ሰበብ ሳንፈጥር ሁላችንም በአንድነት ብንጾማቸው ከእግዚአብሔር ዘንድይቅርታ ጸጋና ምሕረትን እናገኛለንና ራሳችንን ለጾም እናዘጋጅ፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡ (፩ኛ ዮሐ.፩፥፯)

የሰው ልጅ ንስሓ ገብቶ ከኀጢአት ነጽቶ ቅዱስ ቊርባንን የሚቀበል ከሆነ ዳግም ሞት የለበትም፡፡ በፍጻሜ ዘመኑ ከዚህ ዓለም ተለይቶ ወደ ወዲያኛው ዓለም በሚሸጋገርበት ጊዜም ወደ ገነት እንጅ ወደ ሲኦል አይወርድም፡፡ ወደ ሲኦል ቢሄድም እንኳ ልትቀበለው አትችልም፤ ምክንያቱም በሕይወተ ሥጋ ሳለ በደመ ክርስቶስ ታትሟልና፡፡