‹‹የይቅርታ ልብ ይኑረን››

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

የሰው ልጅ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ይመለስ ዘንድ የይቅርታ ልብ ሊኖረው ይገባል፡፡ አዳም ይቅርታ ባይጠይቅ እና ከእግዚአብሔር ይቅርታን ባያገኝ ኖሮ የዘለዓለም ቅጣት ይፈረድበት ነበር፡፡ ሆኖም ከሚኖርባት ገነት ወደ መሬት በመምጣት ቅጣት ተቀብሏል፡፡ አዳም ዕንባ ሲያልቅበት ደም፣ ደም ሲያልቅበት እዥ እያነባ ‹‹በድያለሁ ይቅር በለኝ›› ብሎ ፈጣሪን ይቅርታ በመጠየቁ ድኅነትን አግኝቷል፡፡ ይቅርታ ሰውን እንደገና ወደጥንት ክብሩ የመለሰ ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ ያለ ይቅርታ ዓለም ለኃጢአት ስርየትም ሆነ ቸርነት የበቃ አይሆንም፡፡

ሰዎች ለሌሎች የምናደርገው ይቅርታ እና እግዚአብሔር ለዓለም ያደረገው ይቅርታ ይለያያል፡፡ እግዚአብሔር ለዓለም ያደረገው ይቅርታ በቃል ኪዳን የታሠረ ነው፡፡ በማንኛውም ጊዜ ‹‹ይቅር በለን›› ብለው የሚለምኑትን ሁሉ እግዚአብሔር ይቅር ይላል፡፡ ይቅርታ የጠየቁትን ሰዎች ሁሉ ይቅር ይል ዘንድ እግዚአብሔር ሁልጊዜም መሓሪ ስለሆነ በቃሉ ይቅርታን ያደርጋል፡፡

የሰው ልጅ በየዕለቱ ሊያጠፋና ኃጢአት ሊሠራ ይችላል፡፡ ‹‹ሰማያት በፊቱ ንጹሓን አይደሉም›› ተብሏልም፡፡ በሰማያት ይኖሩ የነበሩት መላእክት (ሠራዊተ ዲያብሎስ) እንኳን ስተዋልና ነው፡፡ የሰው ልጅም ሌት ከቀን ኃጢአት ይሠራል፡፡ ነገር ግን ሰው በዚህ ሁሉ ጥፋት እያለ  በዚህች ምድር የኖረው እግዚአብሔር ይቅር የሚል አምላክ በመሆኑ ነው፡፡ (ኢዩ.፲፭፥፲፭)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የኃጢአት ደሞዙ ሞት ነው›› እንዳለ ሰው ኃጢአት በሠራ ቁጥር ሞት ይገባዋል እንደማለት ነው፡፡ ለምን እኛ ኃጢአት በሠራን ቁጥር አንሞትም ቢባል እግዚአብሔር የይቅርታ አምላክ ስለሆነ ነው፡፡ ስንለምነውና ስንጠይቀው ይቅር ስለሚልን ነው፡፡ አንድ ሰው ሲያስቀይመን፣ ሲበድለን ወይም በእኛ ላይ ክፉ ሲያደርግ ችላ ብሎ በማለፍ በራሱ ከይቅርታ የሚቆጠር ነው፡፡ ለምናጠፋው ለእያንዳንዱ ጥፋት ዋጋው ሞት ነው፤ ለበደላችን ቅጣት አለብንና በጸጸት እንዲሁም ንስሓ በመግባት ይቅርታ ማግኘት ይገባል፡፡ (ሮሜ.፮፥፲፫)

በሰዎች ዘንድም የይቅርታ ልብ በመኖሩ በምንጋጭበት ጊዜ ከተጣለነው ሰው ጋር በይቅርታ መስማማት አለብን፡፡ ሰው አብሮ ከኖረ በመካከላችን ግጭት፣ ክርክርና ንግግር መኖሩ ምንም የማይቀር ነገር ነው፡፡ ታላቁ አባት ኢትዮጵያዊው አቡነ ሐራ ድንግል ገዳም ገብተው በነበረ ጊዜ ብቻቸውን በተባሕትዎ እያሉ ደቀ መዝሙሮቻቸው ‹‹ውሾች ወደዚህ ሰፈር መጡ›› ብለው በነገሯቸው ጊዜ ‹‹አይ ውሾማ ከመጣ ሰው መጣ፣ ሰው ከመጣ ነገር መጣ ማለት ነው›› ብለው ጥለው ሄዱ ይባላል፡፡ ሰው ከነገር ሁልጊዜ አይቀርም፡፡ በሚዋደዱና በሚፋቀሩ ሰዎች መካከል እንኳን አለመስማማት ይኖራል፡፡ የአባትና የልጅ፣ የወንድምነትና እኅትነት እንዲሁም የትዳር፣ ግንኙነት እንዲዘልቅ ይቅርታ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ (ገድለ አቡነ ሐራ ድንግል)

ሀገራችን ሰፊ በመሆኗ ብዙ ሕዝብ ይኖርባታል፤ በዚህ መሐል ሕዝብን የሚበድሉ ባለሥልጣናትም ይኖራሉ፡፡ የእነዚያን ሰዎች መሻሻልና መስተካከል አይቶ ሕዝብ ይቅር ማለት አለበት፡፡ ቂምና በቀል የሚቋጥር ከሆነ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር ጥላቻ ይኖራል፤ ይህ እንዳይሆን ሕዝባዊ ይቅርታ ያስፈልጋል፡፡

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ይቅርታ የአፍ ብቻ ሳይሆን ከልብ የሚመነጭ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ካስተማረው አንዱ ስለይቅርታ ነው፡፡ ‹‹ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም፡፡›› እንዲል (ማቴ. ፮፥፲፫)

አንድ ሰው ስለ ይቅርታ ስላወቀ ብቻ ይቅር ሊል አይችልም፤ የይቅርታ ልብም ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ይቅር የሚል ልብ ሰው ሲጣላ የሚጀምር አይደለም፤ ወይም ብዙ ሽማግሌዎች ሁለት ሰዎች ተጣልተውባቸው ለማስታረቅ ሂደው ያን ጊዜ እንዲታረቁ ያስሟሟቸዋል፡፡ እነዚህን ሰዎች ማስታረቅ ቀላል የሚሆነው ሰዎቹ የይቅርታ ልብ ካላቸው መጀመሪያውኑ ይቅርታ ለማድረግ የተዘጋጀ ልብ ሲኖራቸው ነው፡፡

በገጠሪቱ የሀገራችን ክፍል ጠላ ሁልጊዜ አይጠመቅም፡፡ ባለሙያ ሴት ሁሉን ነገር አዘጋጅታ ድፍድፉን ታስቀምጠዋለች፤ እንግዳ በመጣባት ጊዜ እርሱን ለወስ ለወስ አድርጋ ወዲያውኑ ታቀርበዋለች፤ ሊጥም እንደዚሁ ነው፡፡ የሊጥ ማብኪያው ባዶውን አይሆንም፡፡ እንግዳ እንጀራ ሳይኖር ቢመጣ ወዲያውኑ ምጣዱን አስምታ ወዲያውኑ ትጋግራለች፡፡ ይህች ሴትዮ ዝግጁ ናት ማለት ነው፡፡ እንግዳ ለመቀበል፣ ለማብላት፣ ለማጠጣት ዝግጁ ናት፡፡ ለይቅርታም እንዲህ ዓይነት ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡ ሰው መጀመሪያውኑ ይቅር ለማለት የሚችል ልብ ካለው ሁሉም ነገር ቀላል ነው፡፡

ሰው ይቅር ማለት ያለበት ሲጠየቅ ብቻ አይደለም፤ ሳይጠየቅም ይቅርታ ማለት አለበት፡፡ ይህ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሰው የይቅርታ ልብ ካለው ሰው ሲበድለው ይቅር ብየሃለሁ ሊል ይገባል፡፡ ተበድለውም የሚረሱ ብዙ ሰዎች አሉ፤ እነዚህ ሰዎች የይቅርታ ልብ ስላላቸው ነው፡፡ የይቅርታ ልብ የሌለውን ሰው አስተምሮ ታረቅ ማለት በጣም ከባድ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዱ ሰዎች ‹‹እናንተ ቤቴ ድረስ ስለመጣችሁልኝ እሺ ልበላችሁ እንጂ እኔ ግን በልቤ ቂሜን አልተውም›› ይላሉ፡፡ በአንደበት ብቻ ይቅርታን ማድረጉን የሚገልጽ ሰው የይቅርታ ልብ የለውም፡፡

በጸሎት፣ በጾም እና በትጋት ይቅርታን ማድረግ ልንለምድ ይገባል፡፡ ይቅር ማለት እየፈለገ ያልቻለ ሰው ‹‹ቂሜን መተው እፈልጋለሁ፤ ግን አላስችል አለኝ፤ የደረሰብኝ በደል ትዝ ይለኛል፤ ሳስበው ያንገሸግሸኛል፤ ግደለው ግደለው የሚል ሐሳብ ይመጣብኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ለመርሳት ሞከርኩ ግን አልቻልኩም›› ይላል፡፡ ይህ ነገር ከባድ ቢሆንም ማስወገድ የሚቻለው በጾም እና በጸሎት በመሆኑ ከልብ ይቅር ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡