‹‹የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ›› (፩ቆሮ.፩፥፴፩)

እግዚአብሔር አምላክ ኃያልና ገናና ነው፤ የሚሳነውም የለምና ሁሉን ነገር በምክንያት ያደርጋል፡፡ ሰዎችም በሥነ ተፈጥሯችን የእርሱን ህልውና በማወቅ ለፈጣሪያችን እንገዛ ዘንድ ይገባል፡፡ ድኃም ሆነ ሀብታም፣ ባለሥልጣንም ሆነ ተራ ሰው በፈጣሪው መመካት ይችል ዘንድም ተገቢ ነው፡፡  በትንቢተ ኤርምያስም እንደተገለጸው ‹‹ጠቢቡ በጥበቡ አይመካ፤ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፤ ባለጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፡- ምሕረትንና ፍርድን፥ ጽድቅን በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኘኝ ይህ ነውና›› ሲል አምላካችን እግዚአብሔር ነግሮናል፡፡ (ኤር. ፱፥፳፫)

ጥበብንም ሆነ ኃይልን የሚሰጥ እግዚአብሔር መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያነበብነው  የንጉሥ ሰሎሞን ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ንጉሥናን ከአባቱ ነቢዩ ዳዊት ከተረከበ በኋላ ጥበብን ያገኝ ዘንድ ፈጣሪውን ‹‹አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫዬንና መግቢያዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ፡፡ ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ፥ ስለ ብዛቱም ይቆጠር ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው፡፡ ስለዚህም ሰምቶ በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ ማን ይችላል?›› በማለት ከሁሉ አስቀድሞ በጸሎት ጠይቆታል፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ተቀብሎ በእርሱ ደስ በመሰኘት እንዲህ አለው፤ ‹‹ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን፥ ባለጠግነትንም፥ የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና፥ እነሆ፥ እኔ እንደ ቃልህ አድርጌልሃለሁ፤ እነሆም፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ፥ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ፡፡….››  (፩ነገ.፫፥፯፲፪)

ጥበብን የተሰጡ ነገሥታት ሕዝባቸውን ይመሩ የነበረው በጥበባቸው ነበርና ግዛታቸውም ሆነ ሥልጣናቸው በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነበር፡፡ በዚያም ዘመን ንጉሡ ሰሎሞን ቅን ፍርድ ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በእርሱ ላይ እንዳለ የእስራኤል ሕዝብም ብቻ ሳይሆን ዓለምም ሁሉ ዐወቀ፤ ግዛቱም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ፍልስጤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ተስፋፍቶ ዝናው በዓለም ሁሉ ተዳርሶ ነበር፤ እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ባለጠጋና ጥበበኛ አድርጎታልና፡፡

ሥልጣን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ከሆነ ለጥፋት ይዳርጋል፡፡ በዓለማችን በየዘመናቱ ከነገሡ መሪዎች ብዙዎች ሕዝባቸውን መምራትም ሆነ ማስተዳደር አቅቷቸው ሀገራት በእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ሲታወኩ እንደኖሩ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ በእግዚአብሔር የተመረጡ ነገሥታት ግን እንደ ጠቢቡ ሰሎሞን ዘወትር ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ ሕዝብን በጥበብና በማስተዋል ይመራሉ፡፡ እግዚአብሔር በውስጣቸው የሌለ መሪዎች ግን ለራሳቸውም ሰላም የላቸውም፡፡

ሕዝባቸውም ሰላምና ደስታን ከማጣቱ የተነሣ ከእግዚአብሔር የራቀ ስለሚሆን በተሳሳተ መንገድ በመሄድ በዓለማዊ ዕውቀቱ መመካት ይጀምራል፡፡ ለሚያጋጥመው ማንኛውም ችግር እንዲሁም ፈውስ ላላገኘለት በሽታም መፍትሔውን ከእግዚአብሔር ከመሻት ይልቅ ከሰው እጅ ይጠብቃል፡፡ ለዘመናት ባካባተው ሀብትም በመመካት የትኛውንም ዓይነት ችግርና መከራ ማለፍ እንደሚችል ያምናል፡፡ በዚህም የራስ ወዳድነት ስሜት ይጠናወተውና ለሌሎች ማሰብ ያቆማል፤ ከዚህም ባሻገር የግል ጥቅምን በማስበለጥ በጎኑ ያሉትን ሌሎች ሰዎች ይበድላል፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ክፋትንና በደልን በእነርሱ ላይ አብዝቶ  ይፈጽማል፡፡ ይህም ጥላቻን በሰዎች ሁሉ መካከል ስለሚፈጠር ለእርስ በርስ ግጭት ይዳርጋል፤ ማኅበራዊ ቀውስ ያመጣል፤ ለሀገር ሰላምም መጥፋት ትልቅ መንሥኤ ይሆናል፡፡

በእርግጥ ሰው በዚህ ምድር እስካለ ድረስ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ጥበብም ከእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ  ከሌላ ስላልሆነ ድኅነተ ሥጋን ከእርሱ መሻት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን የሕክምና ጠበብቶች ተፈላስፈው የደረሱበት ዕውቀታቸው እንኳን መፍትሔ ያላስገኘላቸው ምድራዊ ችግሮች እንዲሁም ፈውስ የሌላቸው በሽታዎች መኖራቸው ሁሉም ሊመሰክር የሚችለው ነገር ነው፡፡ ይህም በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት በመስፋፋት የሰው ልጆችን እየቀጠፈ ያለውን የኮሮና በሽታን ብቻም ሳይሆን ከዚህ በፊት ተሰራጭተው ብዙ ሰዎችን ለሞት የዳረጉ እንደ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ እና ኢቦላ ያሉት ገዳይ በሽታዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

መመራመር በእግዚአብሔር ዘንድ የተፈቀደ በመሆኑ ‹‹ሁሉን መርምሩ፤ መልካም የሆነውንም ያዙ›› ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ይመክራል፡፡ ሆኖም ግን ወደአልተገባ ፍልስፍና ውስጥ መግባት የእግአብሔርን ህልውና እንድናናንቅ ከማድረጉም ባሻገር ፈጣሪነቱን በመካድ ወደ ባዕድ አምልኮ ይመራል፡፡ (፩ኛተሰ.፭፥፳፩)

ሆኖም የሰው ዘር የዕውቀቱን አድማስ እያሰፋ በመሄድ ችሎታው እስከ ፈቀደለት ድረስ የምርምሩ ዒላማ የሆነውን ሥነ ፍጥረትን ከመመራመር አላማቋረጡ መልካም ነው፡፡ ለሁሉም ነገር ምክንያት መንሥኤ እንዳለውም ማመን ተገቢ ነው፡፡ የዓለምን ጥንተ ተፈጥሮ፣ የሕይወትን ዓላማ፣ መነሻና መድረሻ ሌሎችንም ተመሳሳይ ነገሮች ለማወቅ ይገባል፡፡  (የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም)

የዚህ ዓለም አፈጣጠርና አካሄድ በሥነ ሥርዓት ታስቦና ተሰልቶ በረቀቀ ቀመር የተሰናዳና የተዘጋጀ መሆኑን የተረዱ ፈላስፎች ይህን ሁሉ ያደረገ ወይም የፈጠረ ከፍተኛ ማስተዋልና ጥበብ ያለው አንድ ኃይል መኖር እንዳለበት ያምናሉ፡፡ እንደነርሱ አስተያየት የአንድ ነገር መኖር፣ የአንድ ሁኔታ መከሠት፣ የአንድ ድርጊት መፈጸም እንዲሁ ያለ ምክንያት በአጋጣሚ ወይም በዕድል የሚሆን ነገር እንዳልሆነና ለሁሉም ነገር መነሻ ምክንያት ወይም መንሥኤ እንዳለው ያምናሉ፡፡ (የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም)

ከክርስቶስ ልደት በፊትም ሆነ ከዚያም በኋላ ከተነሡት የታወቁ ፈላስፎች ውስጥ ብዙዎቹ ከላይ በጠቀስነው በሌላም ልዩ ልዩ ስልትና በተራቀቀ ምርምር ሄደው የሥራቸውም ውጤትና ፍጻሜ የሚያመራው የእግዚአብሔርን መኖር በማመን እንደሆነ ማወቅ ይቻላል፡፡ የሃይማኖት አባቶች እውነተኛውን ነገር ለማወቅ በልቡና የዋህነትና ቅንነት ሥነ ፍጥረትን ተደርተዋልና፡፡ (የትምህርት ሃይማኖት መቅድም)

ለሁሉም የማይታወቀውና በሥውር የሚገኘው ፍጹሙ ጥበብ ወደ የሃይማኖት መንገድና ዕውቀት ከመድረስ የበለጠውም የእግዚአብሔር ወደ ዓለም የመጣበትና ዓለሙን ሁሉ ያዳነበት ምሥጢራዊ ጥበብ ነው፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዓለም እግዚአብሔርን በጥበቧ እንዳላወቀችው ለሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ሲናገር ፈጣሪ በፍጥረቱ እንደሚታወቀው የተናገረው ይህ ዓለም ስለምን እግዚአብሔርን በጥበቡ አንዳላወቀው፤ የፊተኛው በጥንተ ተፈጥሮ የተፈጠረው ፍጥረት ለሁሉም በግልጥ የሚታይ በመሆኑ የኋለኛው ግን በልበ አምላክ በምሥጢር ተይዞ በሐዲስ ተፈጥሮ በተአምራዊ መንገድ የተገለጠ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ‹‹የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኀይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ መልስ የሚሰጡበትን ምክንያት እንደ እግዚአብሔርነቱ ሲያውቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ አላከበሩትም፤ አላመሰገኑትም፤ ነገር ግን ካዱት፤ በአሳባቸውም ረከሱ፤ ልቡናቸውም ባለማወቅ ጨለመ፡፡ ጥበበኞች ነን ሲሉ አላዋቂዎች ሆኑ›› አለ፡፡ (ሮሜ ፩፥፳-፳፪)

ጥበበኞች ነን ብለው አላዋቂ ናቸው የሚባሉትም በሰይጣን ኃይል የሚመኩ፣ የሰው ልጅ  በሳይንሳዊ ዑደት እንጂ በሥነ ፍጥረት መገኙትን የማያምኑ፤ በዓለማዊ ዕውቀት በሚያገኙት ፍልስፍና የሚመራመሩ ፈጣሪያቸውን የካዱና የረሱ ሰዎች ናቸው፡፡ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነውና›› በጥበባዊ ጉዞአችን ሁሉ አስቀድመን ልናውቀው የሚገባን ነገር የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት መሆኑን መረዳት ነው፡፡ ህልውናውንም ስናስብ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በመፍራትና ስሙን በማክበር ሊሆን ይገባል፤ ጥበብም ሆነ ኃይል ከፈጣሪ ነውና የሰው ልጅ ፈጽሞ ምድራዊ እና ጊዜያዊ በሆነ በባዕድ ኃይል መመካት የለበትም፡፡ የዕውቀት ደረጃችን ምንም ያህል ከፍተኛ ቢሆን ሰዎች አምላካችንን ልናከብር ለእርሱም ልንገዛ ይገባል፡፡  (ምሳ.፩፥፯)

የፈጣሪን መኖር እንዲሁም ሕጉን እያወቁ የሚክዱ እንዳሉ ሁሉ ከምንፍቅና ወይንም ፈጣሪያቸውን ካለማወቅ ሕይወት ተመልሰው ለእርሱ ወደ መገዛት የደረሱ ደጋግ አባቶች እንደነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክሮች ናቸው፡፡ በዓለማዊ ትምህርት ከመመካታቸው የተነሣ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል መረዳት ያቃታቸውም ሰዎች አጋጥመውን ይሆናል፤ አንዳንዶች በተለይም በቅን ልቡናና በየዋህነት ፈጣሪያቸውን ማወቅና መረዳት ለሚፈልጉት እግዚአብሔር አምላክ ምሥጢሩን ይገልጥላቸዋል፤ ሌሎች በትዕቢት እና በትምክሕትኝነት የተሞሉ ሰዎች ግን የፈጣሪን ሥራ ሲያናናንቁ ይስተዋላሉ፡፡

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ይሰብክ እና በነፍስ የታመሙትን በቃሉ፣ በሥጋ የታመሙትን ደግሞ በተአምራቱ ሲፈውስ በነበረበት ጊዜ ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ መምህር ሰምቶና ተመልክቶ በመምህርነቱ ሳይታበይ፤ አለቅነቱንም መመኪያ ሳያደርግ፤ በልቡናው የተሣለውን እውነትን ማግኘት ፈለገ፤ ይህንንም ለማግኘት ከጌታውና ከመምህሩ ከክርስቶስ ዘንድ በሌሊት ይገሠግሥም ነበር፡፡ (ዮሐ. ፫፥፩)

ጌታችንም ካለማወቅ ወደ ፍጹም ዕውቀት  የሚያደርስ፤ ከምድራዊ ዕውቀት ወደ ሰማያዊው ምሥጢር የሚያሸጋግር አምላክ  ነውና ‹‹ዳግመኛ  ያልተወለደ  የእግዚአብሔርን  መንግሥት ለማየት  አይችልም››  በማለት ለኒቆዲሞስ አስተማረው፤ ሆኖም ምሥጢሩ አልተገለጠለትም ነበርና  ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?›› በማለት ለጌታ ጥያቄ ሲያቀርብ ጌታችን ኢየሱስ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና፤›› ብሎ ለኒቆዲሞስ ቢያስረዳውም ምሥጢሩ ሊገለጥለት ግን አልቻለም ነበር፡፡ ‹‹እንደምን ይቻላል?›› በማለትም ጌታን ጠይቋል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፮፣ ፩ኛ ጴጥ.፩፥፳፫፣ ኤፌ. ፭፥፳፮)

ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምሥጢር ከአምላኩ በጠየቀ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ‹‹አንተ የእስራኤል መምህራቸው ሆነህ ሳለ ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራችሁ ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም…ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲጠፋ አይደለም…›› በማለት አስረዳው፡፡ (ዮሐ. ፫፥፲፬፣ መዝ. ፲፮፥፫)

እግዚአብሔር አምላክ ሰዎችን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል እንደተባለው የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ምደር መምጣትና መሢሕ መባል ያልተቀበሉት በርካታ እስራኤላውያን እርሱን እስከመስቀል ቢደርሱም በፍጹም እምነት እስከ መጨረሻው  ከተከተሉት ፈሪሳውያን አንዱ ኒቆዲሞስ ለታላቅ ክብር የበቃ ሰው ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዲመካ፡፡ እናንተም በኢየሱስ ክርስቶስ  በእርሱ ናችሁ፤ በእርሱም ከእግዚአብሔር ጥበብንና ጽድቅን፥ ቅድስናንና ቤዛነትን አገኘን፡፡ መጽሐፍ እንደአለው ይሆን ዘንድ ‹‹የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ›› ብሎ እንደነገረን በፈጣሪያችን አዳኝነት፣ ቤዛነት፣ ፍጹም ኃያልነት በማመን እንመካ፤ እርሱ ከምድራዊውም ሆነ ከዘለዓለማዊው ሥቃይ ይታደገናልና፡፡

 

ምንጭ፤  የትምህርተ ሃይማኖት መቅድምበሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ