‹‹ሦስቱ የጥፋት ገመዶች እንዳይጥሏችሁ ተጠበቁ!›› አቡነ ተክለ ሃይማኖት

ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተጋድሏቸው ዘመን በአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለዐሥር ዓመት በነበሩበት ጊዜ አገልጋዮቹ ወደ እርሳቸው መጥተው ይመክሯቸው ዘንድ ለመኗቸው፤ እርሳቸውም ‹‹ትዕግሥትን፣ ትሕትናን እና እግዚአብሔርን መፍራት ገንዘብ አድርጉ፤ እነዚህ ሦስት ነገሮች ሰውን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት ያደርሱታል፡፡ እየጎተቱ ወደደይን ጥልቅነት የሚያወርዱ ሦስቱ የጥፋት ገመዶች እርሳቸውም ቅናት፣ ትዕቢትና ትምክሕት እንዳይጥሏችሁ ደግሞ ተጠበቁ›› ብለው መከሯቸው፡፡ (ገድለ ተክለ ሃይማኖት  ፵፫፥፬-፮)

ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ለእግዚአብሔር አምላክ መገዛትን አልፈቅድ ብሎ ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም ከተባረረ በኋላ አዳም በገነት መኖሩን ሲያውቅ ሊያስተው ወደ እርሱ የሄደው በቅናት ተነሳስቶ ነበር፡፡ በመጽሐፍም ቅዱስ እንደተጠቀሰው እባብ ተንኮለኛ ስለነበር በእርሱ ላይ አድሮ እግዚአብሔር አምላክ የከለከለውን ዕፀ በለስ እንዲበላ በማድረግ ከገነት አስወጥቶታል፡፡ (ዘፍ. ፫፥፬)

ሰይጣንም በትዕቢት ለእግዚአብሔር አምላክ መገዛትን እንዳልፈቀደ ሁሉ፤ ክፉ ሰዎችም በጎ ነገርን በመሥራት ፈጣሪያቸውን ከማገልገል ይልቅ በሌሎች በጎ ምግባርና ጥሩነት በመቅናት  በትዕቢት ክፋት ይሠራሉ፡፡ በዘመናት የሰዎችን በጎነትም ሆነ ደስታን የማይሹ ልበ ክፉዎች በበጎ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ሐዘንን እየጫሩ እና በዕድል ፈንታቸውም ተጠቅመው ተድላ ደስታን ለማግኘት የእነርሱ ምድራዊ ሕይወት ሥቃይ የተሞላበት እንዲሆን ያደረጉ በርካቶች ናቸው፡፡ የሌሎችን ደስታ መሻት ሲገባቸው በውስጣቸው ቅናት ሞልቶ መጥፎ ነገር ያደርጋሉ፡፡ ‹‹የሚያስታርቅ ሰው ልብ ፈዋሽ ነው፤ ቀናተኛ ልብ ግን ለአጥንት ነቀዝ ነው›› እንደተባለውም ፍቅር ባለበት ቤተሰብ፣ በሚዋደዱ ጓደኛሞች እና እጮኞች መካከል የሐሰት ወሬ በማውራት፣ ክርክር እና ጠብ በማስተነሳትም ቅራኔና ጥላቻን በመፍጠር ፍቅራቸውም ቀዝቅዞ እስከ ማለያየት ያደርሳሉ፡፡ ‹‹መቀናናትና መከዳዳት በአሉበት ስፍራ ሁሉ፥ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና›› አንዲል፡፡ (ያዕ.፫፥፲፮፣ ምሳ. ፲፬፥፴) 

ቅናት የተጀመረው በሳጥናኤል ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የቃየልንና የወንድሙን የአቤልን ታሪክ ማንሳትም ይቻላል፤ አቤል በግ   ይጠብቅ  ቃየልም  ምድርን ያርስ ነበረ። ከዚያም ወንድማቾቹ ካላቸው ነገር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ቃየል ክፉ ልብ ነበረውና እግዚአብሔር አይበላው ብሎ ከአመረተው እህል ጥሩውን ሳይሆን መጥፎን የማይረባውን መናኛውን እህል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። አቤል ልቡ ንጹሕ ነበርና እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ንጹሐ ነገር ቢሠውለት ይወዳል ብሎ ከበጎቹ መካከል ቀንዱ ያልከረከረውን ፀጉሩ ያላረረው ጥፍሩ ያልዘረዘረውን የአንድ አመት ጠቦት በግ ለእግዚአብሔር ንጹሕ መሥዋዕት አቀረበ።

እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ። ነገር ግን ወደ ቃየልና ወደ መሥዋዕቱ አልተመለከተም። በዚህም ምክንያት ቃየልም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ። እግዚአብሔርም ቃየልን አለው፤ ‹‹ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ  የሚበራ አይደለምን?  መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት ይሆንብሃል፣ ቅጣትም ይጠብቅሃል›› አለው። ከዚህም በኋላ ቃየል ተንኮል ስላሰበ  ወንድሙን  አቤልንና  ወደ  ሜዳ  እንሂድ ብሎ። በሜዳም  ሳሉ ቃየል ወንድሙን አቤልን በደንጋይ ገደለው። የቅናት መጨረሻ ይህ ነው፤ በሰዎች ላይ ከቀናን የምንፈልገውን ለማግኘት  በጥላቻ መንፈስ እነርሱን እስከመግደል እንደርሳለን፡፡ ምክርንና ተግሣጽንም ከመፍራት ይልቅ በድፍረት የፈጣሪን ትእዛዝ እንተላለፋለን፡፡ (ዘፍ.፬፥፩-፲፭)

የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መተላለፍ የጀመረ ሰው ትዕቢትና ትምክሕተኝነት በልቡናው ያድርበታልና ለኃጢአት የተጋለጠ ነው፤ ለራሱ የሚሰጠው ያልተፈቀደ ክብር እንደመሆኑ ሌሎችን የመናቅና የማንቋሸሽ ስሜት ጠባይን ይለምዳል፤ በትንቢተ ኢሳይያስ  እንደተገለጸው ‹‹በትዕቢትና በልብ ኩራትም ጡቡ ወደቀ፤ ነገር ግን ኑ፥ ድንጋይ እንውቀር፤ ሾላው ነቀዘ፤ ነገር ግን ጽድን እንቊረጥ፤ ለራሳችንም ግንብን እንሥራ ተባባሉ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ በጽዮን ተራራ ላይ እርሱን በመቃወም የሚነሡትን ይበትናቸዋል፡፡››

የትዕቢት መዘዙ ብዙ ቅጣቱም ከባድና አስፈሪ ነው፤ ሰይጣን በትዕቢት ለፈጣሪው እግዚአብሔር አልገዛም በማለቱ ወደ ዘለዓለማዊ እሳት ውስጥ ይጣላል፡፡ ዓለማችን በዚህ ጊዜ በክፉ እና በትዕቢተኛ ሰዎች የተሞላች ሆናለች፡፡ እርስ በርስ የተናናቅንበትና የተጠላላንበት ምክንያትም ሰውን ከመታዘዝና ታላላቅን ከማክበር ይልቅ ስንታዘዝ በትዕቢት እንቢተኝትን ከመግለጽ ባሻገር ወደ ዘለፋና ስድብ እናመራለን፡፡ ሲመክሩንም ሆነ ሲገሥጹን ክብራችንንም የቀነሱብን ይመስል እነርሱን እንደጠላት በመቁጠር ወደ ጥልም ጭምር እናመራለን፡፡

ትዕቢት መጥፎ መንፈስንም ይጠራል፤ የሰይጣን ፈቃድ ለፈጣሪ አለመገዛት በመሆኑ ለአምላኩ ከመገዛት ይልቅ ከፈጠሪው ኃይል ይበልጥ ዘንድ በመመኘት በሥሩ የነበሩትን መላእክት ፈጣሪያችሁ ነኝ እስከማለት ደርሷልና፡፡ ሰዎችንም እንደእርሱ ፈጣሪን እንዲክዱ፣ ባዕድ አምልኮንም እንዲከተሉ እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር ለመተካከል እንዲያስቡም ያደርጋቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ሀብትንና ክብርን በአቋራጭ መንገድ ለማካበት ከመሻታቸው የተነሣ የትኛውንም ዓይነት ኃጢአት ይፈጽማሉ፡፡ በዕለት ተግባራቸውም እግዚአብሔር አምላክን መፍራትና በጸሎት ከመጠየቅ ይልቅ በራሳቸው በመመካት እያንዳንዱን ውሳኔያቸውንም ሆነ እንቅስቃሴያቸውን በኃይላቸውና በችሎታቸው እንደሚያደርጉ ያስባሉ፡፡ ሆኖም ‹‹አሁን እናንተ በሥራችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህች ያለችው ትምክሕትም ኋላ ክፉ ናት›› እንደተባለው ያልተፈቀደልንን ክብር ለማግኘት ስንል በመጥፎው ጎዳና ከተጓዝን ወደማይመለሱበት ጨለማ ዓለም ገብቶ ለዘለዓለም መቀጣት አለና በራሳችን ሥራ መመካት የለብንም፤ ትምክሕት እንደ ቅናትና ትዕቢት የጥፋት ገመድ ናትና ትጥለናለች፡፡ ‹‹እግዚአብሔርን የሚፈራ….ትዕቢትን፥ ክፉ መንገድንም ይጠላል….››  ስለተባለም እግዚአብሔርን ከማሳዘንና በእርሱ ከመጠላት ተጠብቀን  ቅናትን ትዕቢትንና ትምክሕተኝነትን ከእኛ እናርቅ፡፡ (ያዕ.፬፥፲፮፤ ምሳ.፯፥፲፫)