የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት (ሰሙነ ሕማማት)
ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ‹‹ሁሉ ተፈጸመ›› አለ፡፡ ያን ጊዜም ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡ አይሁድም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ ብለው ጭን ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ ጭፍሮቹም የሁለቱን ወንበዴዎች ጭናቸውን ሰብረው አወረዷቸው፡፡ ወደ ጌታችንም ሲቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ‹‹ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንቱንም አትስበሩ›› ተብሎ የተነገረው ምሳሌያዊ ትንቢት ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ (ዘፀ.፲፪፥፵፮)