ዕርገተ ማርያም
አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ወደ ሰማይ ያረገበት መታሰቢያ ነሐሴ ፲፮ ቀን የከበረ በዓል ነው። ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው ። ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድስተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ ።
የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው። የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው። እነርሱም “የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል” አሏት። ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ።