ሃያ አራቱ አለቆች (መጽሐፈ ስንክሳር)

ኅዳር ፳፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ምስጋና ለሥሉስ ቅዱስ ይድረስና ሁልጊዜ በየዓመቱ በኅዳር ፳፬ ቀን እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን የካህናተ ሰማይ (ሱራፌ) በዓልን እንድናከብር አባቶች ሥርዓትን ሠርተውልናል፡፡

ቅዱሳን መላእክት ሱራፌል እግዚአብሔር ለመላእክት መኖሪያነት ከፈጠራቸው ከሦስቱ ሰማዮች መካከል በኢዮር በሦስተኛው ከተማ የሚኖሩ መላእክት ናቸው፡፡ ሱራፌል የነገደ መላእክቱ የብዙ ቁጥራቸው መጠሪያ ሲሆን በነጠላ ስማቸው ሱራፊ (የአንዱ መልአክ መጠሪያ) ይባላሉ፡፡

ስያሜ

ሱራፊ የሚለው ቃል ‹‹የሚያነድ፣ የሚያጤስ፣ የሚያጥን፣ ዐጣኝ›› የሚል ትርጉም ሲኖረው ይኸውም አገልግሎታቸውን ይገልጻል፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፰፻፹፮)  ቅዱሳን መላእክት ሱራፌል ሃያ አራቱ ካህናት፣ ሃያ አራቱ ሊቃናት (አለቆች)፣ አንዳንዴም ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ተብለው የሚጠሩ ሥጋ የሌላቸው ረቂቃን የእውነት ካህናት የሆኑ ከቅዱሳን ሁሉ በላይ የሆኑና ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ ከፍ ከፍ ያሉ መላእክት ናቸው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በራእዩ  ‹‹በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፤ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው፣ በራሳቸውም የወርቅ አክሊል፣ ደፍተው ሃያ አራት ሊቃናት ተቀምጠው ነበር›› በማለት ስለ እነርሱ ጽፏል፡፡ (ራእይ ፬፥፲፬)

ቁጥራቸው ሃያ አራት መሆኑ

መጽሐፍት እና የቤተ ክርስቲያን መምህራን ካህናተ ሰማይ ቁጥራቸው ሃያ አራት የሆነበትን ምክንያት ሲያስተምሩ ሱራፌል በሃያ አራቱ ሰዓት ያለሟቋረጥ ለአምላክ ምስጋናና ጸሎት በማቅረብ ራሳቸውንም ፍጥረትንም ጠብቀው ዋጋቸውን ተቀብለው የሚኖሩ በመሆናቸው አምላካችን እግዚአብሔር ሃያ አራት አድርጓቸዋል በማለት ይናገራሉ፡፡  በተጨማሪ ደግሞ በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ዘሥጋ መነሻ የሆኑት ዐሥራ ሁለቱን አበውና በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የእስራኤል ዘነፍስ መሠረት የሆኑትን የቅዱሳን ሐዋርያትን ድምር ስለያዙ ቁጥራቸው ሃያ አራት ሆኗል፡፡  ለቤተ እስራኤል ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ምንጮች እንደሆኑ ለቤተ ክርስቲያንም ቅዱሳን ሐዋርያት ምንጭ (ነቅዕ) ናቸውና፡፡ (መዝ.፲፯፥፲፭)

አገልግሎታቸው

ሱራፌል  ‹‹ዐጠንተ መንበሩ ለልዑል›› በመባል ይጠራሉ፡፡ የካህን ሥራው መንበር ማጠን እንደሆነ  እነርሱም ማዕጠንተ-ወርቃቸውን ይዘው፣ አክሊላቸውን ተቀዳጅተው፣ ስለሚያመሰግኑ ካህናተ-ሰማይ ተብለው ይጠራሉ፡፡ አእላፍ መላእክት ሲላላኩ፣ ኪሩቤል መንበሩን ተሸክመው ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› ሲሉ፣ ሠራዊተ-መላእክት ከፊቱ ቆመው ሲሰግዱ፣ ትጉሃን ሲያመሰግኑ፣ ሱራፌልም ማዕጠንተ ወርቃቸውን ይዘው መንበሩን እየዞሩ ያጥናሉ፡፡ ሥራቸውን በመንፈስ ቅዱስ የተመለከተው ቅዱስ ያሬድም  ‹‹ፍቁራኒሁ ለአብ ኄራን መተንብላን እለ ይሥእሉ ምሕረተ ለውሉደ ሰብእ›› ይለናል (ኄራን መላእክት ለሰው ልጆች ምሕረትና ይቅርታን ይለምናሉ) ማለት ነው፡፡

በማዕጠንታቸውም ዘወትር ወደ አምላካችን የጻድቃንን ጸሎት፣ ምድራውያን ካህናት የሚሠውትን መሥዋዕት እና የሚያጥኑትን ዕጣን የሚያሳርጉም ቅዱሳን መላእክት ሱራፌል  ናቸው፡፡ በቅዱሳን መላእክት ሱራፌል አገልግሎት ውስጥ ስድስቱ ክንፎቻቸው ሦስት ትእምርቶችን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህም ትእምርተ ፍርሃት፣ ትእምርተ ተልእኮ እና ትእምርተ መስቀል ናቸው፡፡

ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ የእነርሱን ሁኔታ ሲገልጥ ‹‹ሱራፌል በዙሪያው ቆመው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ስድስት ክንፍ ነበረው፤ በሁለት ክንፍ ፊቱን ይሸፍን ነበር፤ በሁለት ክንፍ እግሮቹን ይሸፍን ነበር፤ በሁለት ክንፍ ይበርር ነበር፡፡ አንዱም ላንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር›› ብሏል፡፡ (ኢሳ.፮፥፪-፫)

በሁለቱ ክንፋቸው ፊታቸውን መሸፈናቸው፣ በሁለቱ ክንፋቸው እግራቸውን መጋረዳቸው የመለኮቱ እሳትነት (ዋዕየ መለኮት) እንዳያቃጥላቸው ነው፤ ያስ ቢሆን አካላቸው አይደለም ቢሉ ትእምርተ ፍርሀት ነው፤ አሁን ሰው ሾተል በመዘዙበት፣ ጦር በነጠቁበት ጊዜ እጁን እንደሚጋርድ ነው፡፡

ሁለት ክንፋቸውን ወዲያ እና ወዲህ ማድረጋቸው ትእምርተ ተልእኮ፣ ተልእኮ አለብን ማለታቸውን ይገልጻል፡፡ በሁለቱ ክንፋቸው ፊታቸውን በሁለቱ ክንፋቸው እግራቸውን ሲሸፍኑ በሁለቱ ክንፋቸው ጽንፍ እስከ ጽንፍ ሲበሩ በአንድነት ትእምርተ መስቀል ይሆናል፡፡

ቅዱሳን መላእክት ሱራፌል (ካህናተ ሰማይ) ዛሬ የእኛ ሕይወት ፍቅር በማጣት፣ በኃጢአት ከርፍቷልና በወርቅ ማዕጠንታቸው የፍቅርን ዕጣን አጥነውን፣ ከኃጢአታችንም ነጽተንና ሥራችን ሁሉ በጎ መዓዛ ኖሮት በሰላምና በመተሳሰብ ለመኖር ይርዱን፤ አሜን!

ምንጭ፡-  መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትንቢተ ኢሳይያስ ንባቡና ትርጓሜው (በአንድምታ)፣  መጽሐፈ ስንክሳር ፣ መጽሐፈ አሚን ወሥርዓት  በመምህር ዶ/ር ዘበነ ለማ ፣ምሥጢረ ሰማይ ( መምህር ማዕበል ፈጠነ)፣ የአንቀጸ ብርሃን አንድምታ ትርጓሜ (መምህር ኃይለማርያም ዘውዱ)