ዲ/ን ታደሰ ወርቁ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰማያዊ ሥርዓት በምድር ያለች ሰማያዊት ተቋም ነች፡፡ በምድር ያለነውን ልጆቿን በሰማያዊው ሥርዓት በምድር አዘጋጅታ በሰማይ የምታኖር ናት፡፡ “አሐቲ” ተብላ የምትጠራ የክርስቲያኖች መገናኛ በመሆኗ ወደሷ ለሚመጣው ሁሉ በረኛ፣ ጥበቃ፣ ከልካይ፣ አሰናካይ የሌለባት ነፃ እልፍኛችን ናት፡፡ እንዲሁም ከበሉ መራብ፤ ከጠጡ መጠማት የሌለበት ሰማያዊውን መና፣ በሰማያዊ ሥርዓት የምታስገኝልን አማናዊ የእናት ጓዳ በመሆኗ መታመኛችንና መመኪያችን ናት፡፡
ከሁሉ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን በማይነዋወጥ ወለድ ዋሕድ በሚለው መሠረተ እምነት፤ ነቢያት፣ ሐዋርያት ሊቃውንት ስለወልድ ዋሕድ በአስተማሩት ትምህርት መሠረት ላይ የታነፀች እውነተኛ የሕግና የትክክለኛ ሥርዓት መገኛ ናት፡፡ በየጊዜው የነበረው ፈተና የውስጥና የውጭ ጠላቶቿ ጥቃት አስተዳደራዊ ጉዞዋን ቅርቃር ውስጥ የከተተው ቢሆንም የዘመኑን ተልእኮዋን ለማሳካት በቂ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን አሐቲ፣ ሐዋርያዊት፣ ኩላዊት ሁና ሳለች በጥቂቶች ከላሽነት የተነሣ የውጭና የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ በሚል ተከፋፍላለች፡፡ ተቋማዊ አስተዳደራዊ ፋይናንሳዊ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡ የዚህ ድምር ውጤትም የምእመናንን ሕሊናም እየከፈለ፣ እያደማም ይገኛል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በአስተምህሮዋ በአስተዳደሯ፣ በፋይናንስ አያያዟና አጠቃቀሟ የከፋና ውስብስብ ጊዜ ጠየቅ ችግሮችና ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፡፡ አንዳንዶቹ ፈተናዎችና ችግሮች ሥር የሰደዱ አዝማናትን ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ዘመንና መስክ ወለድ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ከኅልፈተ ዓለም በፊት ይቆማሉ ተብሎ የሚታሰቡ አይደሉም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን ለዘመንና መስክ ወለድ ችግሮቻችን መፍትሔ ማፈላለግ የዘመናችን የቤተ ክርስቲያኒቱ ላአላይና ታህታይ መዋቅር መሪዎች ተናጥላዊና የወልዮሽ ሓላፊነት ነው፡፡
እናም በፈቃደ እግዚአብሔር፣ በአባቶቻችን የመንፈስ ልዕልናና ጽናት ተጠብቆ የቆየው የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ትውፊት ለመጪው ትውልድ ያለ እንከን መተላለፍ የሚችለው፣ በጉልህ የሚታዩትን አስተምህሯዊ ቅሰጣ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ችግሮችን ማረም፣ ማስተካከል፣ ሥርዓታዊና ሕጋዊ መሠረት ማበጀት ስንችል ብቻ ነው፡፡
ይህ ሆኖ እንድናይ ደግሞ በታሪክ መስታወትነት ወደ ኋላ ሔደን አሁን ያለንበትን ከአለፈው ጋራ በማዛመድ ከየት ተነሥተን ያለንበት ደረስን? ወዴትና በምን ያህል ፍጥነት እየመራን ነው? ምን ዓይነት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በምን ያህል ፍጥነት ብናስቀምጥ የተጋረጠብንን አደጋ እንቀንሳለን? ለሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ተግባራዊና ተጨባጭ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህን ሦስት መሠረታዊ እና የነባራዊው ሁኔታ ነጸብራቅ የሆኑትን ጥያቄዎች ከግንዛቤ በማስገባት ጽሑፉን በሦስት ዓበይት ክፍሎች ለማቅረብ መርጠናል፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘመናት በሚለው ርእስ ሥር ከየት ተነሥተን ያለንበት ደረስን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በሚለው ርእስ ሥር ወዴትና በምን ያህል ፍጥነት እያመራን ነው? የሚለውን ጥያቄ ከምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለማየት እንጥራለን፡፡ በሦስተኛውና የመጨረሻው ክፍል የመፍትሔ አቅጣጫ ጥቁምታ በሚለው ርእስ ሥር በሁለቱ ቀደምት ክፍሎች ትንታኔ ላይ በመመሥረት ምን ዓይነት የመፍትሔ አቅጣጫዎች፣ በምን ያህል ፍጥነት ብናስቀምጥ የተጋረጡብንን አደጋዎች እንቀንሳለን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን
ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረችበት ታሪካዊ ሁኔታ /Historical condition/ ጥርት ባለ እና በተስተካከለ ገጽታ ለመረዳት ተልእኮዋን እንደ አንድ ማንጸሪያ /parameter/ መጠቀሙ አስፈላጊ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምድራዊውን ሰው በሰማያዊ ሥርዓት ወደ ሰማያዊ ኑሮ እንድታሸጋግር ከመሥራቿና ራሷ ከሆነው ክርስቶስ ሦስት መሠረታዊ ተልእኮ ተሰጥቷታል፡፡ በወልድ ዋሕድ መሠረተ እምነት ማጥመቅ፣ ማጽናትና መከታተል ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪካዊ ሁኔታ የምንፈትሸውም አንዱ ከእነዚሁ ተልእኮዎቿ ተነሥተን ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያዊ ጃንደረባና በሶሪያዊው ፍሬምናጦስ ዘመን
ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Religious Life In Ethiopia” በሚል ርእስ እ.ኤ.አ. በ1970 በአቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው ላይ እንዳመለከቱት፣ የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ የገባበት መንገድ ከሌላው ዓለም በእጅጉ ይለያል፡፡ በሌላው ዓለም ክርስትና የተጀመረው ከተርታው ሕዝብ ነው፡፡ በመንግሥት የታወቀና የተረዳ ሃይማኖት አልነበረም፡፡ በእኛ ሀገር ግን የመጀመሪያዎቹ አማኞች ከተርታው ሕዝብ አይደሉም፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ ከነቤተሰቦቻቸው ነበሩ፡፡ ሃይማኖቱም ብሔራዊ ሃይማኖት ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በሌሎች የዓለም ሀገሮች የክርስትና ታሪክ ውስጥ አልሆነም፡፡ በኢትዮጵያ ግን ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ክርስቲያን የሆነውም በዚህ ሁኔታ ነው፡፡
የክርስትና ሃይማኖት አገባብ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱም አደረጃጀት ከሌላው ዓለም እንዴት እንደሚለይ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ በዚሁ የጥናት ወረቀታቸው ሲገልጹ፤ “…. የቤተ ክርስቲያኒቱ አደረጃጀትም ከሌላው የክርስትና ዓለም የተለየ ነበር፡፡ ክርስትናን ያስተዋወቀው የመጀመሪያ ሰው ሶሪያዊው ፍሬምናጦስ ነው፡፡ ይሁንና ከእርሱ በኋላ አስተዳደሩ ይመራ የነበረው በኢትዮጵያውያን አልነበረም፡፡ በግብጻውያን ጳጳሳት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያም በአንድ ጳጳስ ብቻ እንድትመራ በሕግ ደንግገዋል፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዘመን በአንድ ግብጻዊ ጳጳስ ሥር እንዲወሰኑና ተጨማሪ አስተዳደራዊ ነፃነት እንዳይኖራቸው ተደርጓል” በማለት ነበር፡፡
በእርግጥ ክርስትናው የገባበት መንገድና የቤተ ክርስቲያኒቱ የአደረጃጀት መነሻ ከላይ የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ሥርግው እንደአስቀመጡት ቢሆንም ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባውና ወይም ኢትዮጵያና የክርስትና ሃይማኖት የተዋወቁት መጽሐፍ ቅዲስ እንደሚያስረዳው / ሐዋ.8፥26-40/ ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ባጠመቀው ጊዜ ነው፡፡ ይህም የሆነው ከጌታ ልደት በኋላ በ34 ዓ.ም ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተባለው መጽሐፋቸው ከላይ በጠቀስነው አግባብ የኢትዮጵያና የክርስትና ሃይማኖት ትውውቅ ከአሰፈሩ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ የፍሬምናጦስ /አባ ሰላማን/ ሚና ሲገልጹ፤ “ኢትዮጵያዊው /ጃንደረባው/ ተጠምቆ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ አዲሱን ሃይማኖት ለሀገሩ ሕዝብ አስተምሯል፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ ፍሬምናጦስ /አባ ሰላማ/ ሥርዓተ ክርስትናን በትምህርት ያጠናከረው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በመሠረተው ነው፡፡ ፍሬምናጦስ ጵጵስናውን ተቀብሎ ከተመለሰ በኋላ በኢትዮጵያ የክርስትናን ሥርዓት አስፋፈቶ ሰበከ፤ የክህነትና የቁርባንን ሕግ አጠናከረ፡፡ በኢትዮጵያ ግዛት በሙሉ የወንጌልን ትምህርት ለማዳረስ የሚረዱ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመ፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስት፣ ከዕብራይስጥና ከጽርእ ወደ ግእዝ ቋንቋ መለሰ፡፡ በዚህ አኳኋን በ330 ዓ.ም ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆነ” ይላሉ፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የሐዋርያነት ሥራ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አጭር መግቢያ” በሚለው የጥናት ወረቀቱ እንዳመለከተው ኢትዮጵያዊው ጀንደረባ ከአክሱም ቀጥሎ ኑብያን፣ ከኑብያም በኋላ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ በየመንና በፐርሽያ ወንጌልን ሰብኳል፡፡
ከእርሱም በኋላ ደግሞ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ ሊቅ በአምስተኛ መቶ ክፍለ ዘመን በሊቢያ የኢትዮጵያን ሰዎች ማየቱን ገልጧል፡፡ በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዘመንም አባታችን ወደ ኑብያ፣ አኑኖ እና መርዌ አምስት ቆሞሳትን ልከው እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አብርሃና አጽብሐ ክርስትናን ተቀብለው ከተጠመቁ በኋላ በሸዋ፣ በጎጃም ብሎም እስከ ጋሞ ጎፋ ብርብር ማርያም ድረስ ወንጌል ሰባክያን እየተላኩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Establish event of the Ethiopian church” በሚል ርእስ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው ላይ፤ ከላይ በአቡነ ጎርጎርዮስ የተገለጠውን ዘመነ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ክርስትና ውስጥ ያለውን ታሪካዊ ቦታ ሲያብራሩ፤ “የክርስትና ሃይማኖት እንደመንግሥታዊ ሃይማኖት መተዋወቁ በኢትዮጵያ ታሪክ ወሳኝ ነጥብ መሆኑን ያሳያል” ካሉ በኋላ “ክርስትና በሀገሪቱ የሚያካትተው ንጹሕ ሃይማኖታዊ ክስተቶችን ብቻ አይደለም፡፡ በሁሉም ሀገራዊ ኑሮ ላይ ዘርፈ ብዙ ሚና አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳትሆን ለበርካታ ዘመናት የአገሪቱ ሕዝብ የባህል፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ኑሮ ግምጃ ቤት መሆኗን ያሳያል” ይላሉ፡፡
ዘመነ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲየን መንበረ ጵጵስና ታሪክ ውስጥ ያለውን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሪስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው “ከርሱ /ከቅዱስ ፍሬምናጦስ/ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ጋር እኩል ሆነች፡፡” ብለው ሲገልጹ
“የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትናንትናና ዛሬ” በሚል ርእስ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ የተዘጋጀው መጽሐፍ ደግሞ “…. ቅዱስ ፍሬምናጦስ በዚህ ሁሉ ሥራው ከሣቴ ብርሃን ሰላማ የሚል ቅጽል ተሰጠው፡፡ ከእርሱ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ታወቀች” በማለት ነው፡፡
የኢትዮጵያን ዕሥራ ምዕት ምክንያት በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መድበል ይህንኑ ሐሳብ ሲያጠናክር፤ “ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናውን አክሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ” ይልና “በዚሁ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመሆን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል” ይላል፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመለከት የአንድም ሐዋርያ ደም ሳታፈስ፣ የአንድም ሰማዕት አጥንት ሳትከሰክስ ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትን የተቀበለች ሀገር ነች፡፡ ይኼ እንዲሆን ደግሞ ከሕዝባችን ጨዋነት ባሻገር የመንግሥት እና ቤተ ክህነት ግንኙነትም ወሳኝ ታሪካዊ አጋጣሚም ነበር፡፡ ቀደም ብሎ የንግሥተ አዜብ ወደ ሰሎሞን መሔድና የቀዳማዊ ምኒልክ ከሰሎሞን መወለድ ለሥርዓተ ጽዮን አገባብና ለሕገ ኦሪት አመጣጥ ምክንያት ሆነ፡፡ እንዲሁም ደግሞ በሕንደኬ ንግሥት ጊዜ የበጅሮንዷ ወደ ኢሩሳሌም መሔድና ከሐዋርያው ፊልጶስ ጋራ ተገናኝቶ የወንጌልን ዜና ጽድቅ ለማምጣት መሪ ሆነ፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት አማካኝነት ተመርጦ ወደ እስክንድርያ ሔዶ ጵጵስና ተሹሞ መጠቶ እስካሁን ሲያያዝ የመጣውን የወንጌል መክሊት በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ምእመናን አተረፈ፡፡ ይኼ ደግሞ ሌላኛው ቤተ ክርስቲያናችን የተገነባችበት የታሪክ ገጽታችን ነው፡፡
የዚህ ዓይነቱ ታሪካዊ ትስስር በወቅቱ ከነበረው ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረችበትን ታሪክዊ ቦታ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Establishment of the Ethiopian church” በሚለው ጥናታቸው ሲተነትኑ “የክርስትና ሃይማኖት እንደ መንግሥት ሃይማኖት በኢትዮጵያ መግባቱ በተደራጀ በሌላ ሀገር የስብከት ውጤት ሳይሆን የነገሠታቱ /አማኝነት/ ነው” ካሉ በኋላ “ክርስትና በኢትዮጵያ የተዛመተው እንደ ግሪክ ሮማውያን ዓለም ዓይነት የክርስትና ተዛምቶ መንገድ አይደለም፡፡ ክርስትና በእነዚህ ሀገሮች ለሦስት ምእት ዓመታት በታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ቢታቀብም ወዲያው የገዢው መደብ ተቃውሞታል፡፡ በእርግጥ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎች በጣም ጥቂት የሚሆኑ የነገሥታት ቤተሰቦች የክርስትና ሃይማኖትን መቀበል ቢጀምሩም በኢትዮጵያ ግን መቀበሉ ከምር ነበር፡፡ ክርስትናው በመጀመሪያ በቤተ መንግሥቱ ገባ፣ ከዚያ ቀስ በቀስ ወደመላው ሕዝብ ተዛመተ፡፡ በሮማ ግዛት ዐፄ ሕዝቡን በክርስትና ሃይማኖት ለማሳመን ሐዋርያትና የኋላ ዘመን አባቶች ሲሳተፉ፣ በኢትዮጵያ ክርስትና በፈቃደኝነት ገባ” ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ሐዋርያዊ፣ አገልግሎት አልነበረም ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡
ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ትንታኔያቸውን በመቀጠል፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ መንግሥት ሃይማኖት ከርስትናን ስትቀበል ስለነበረው ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ሁኔታም ሲያብራሩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷ እየተጠናከረ በምትቋቋምበት ወቅት የአርዮስ ክህደት ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጦስ በቅዱስ አትናቴዎስ በሚመራው የእስክንድርያ መንበር ሥር ሆኖ በኒቅያ ጉባኤ አርዮስን ከሚቃወሙ የኦርቶዶክሳውያኑ ወገን ነበር፡፡ ይህም የሆነው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በብሔራዊነት ከመመሥረቷ በፊት ነው፡፡ ነገር ግን የጉባኤው ውሳኔ አስገዳጅ ባይሆንም ኢትዮጵያ ከአትናቴዎስ እና ከኒቅያ እምነት ነች ካሉ በኋላ በወቅቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከአርዮሳውያን የገጠማትንም ፈተና ሲገልጹም፤ “የታላቁ ቆስጠንጢኖስ ልጅ ቆንስጣ ወደ አርዮስ ምንፍቅና ለማምጣት ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ለኢዛና እና ሳይዛና ቅዱስ ፍሬምናጦስን ወደ እስክንድርያ እንዲልከውና የእርሱም ሃይማኖት እንዲፈተሽ ደብዳቤ በመላክ ጠይቆ ነበር፡፡ ዓላማውም የኦርቶዶክሳዊነትን ዓለም ተቀፋዊ ተቀባይነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር በኢትዮጵያ ላይ ያደረጉት ተልእኮ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ቅዱስ ፍሬምናጣስም ከአትናቴዎስ የተማረውን ትምህርት እያስተማረ በአክሱም ቀረ፡፡” በማለት ነው፡፡ ይኼ እንግዲህ አንዱ የታሪኳ አካል ነው፡፡
ዘመነ ተሰዓቱ ቅዱሳን
ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “The Expansion and consolidation of Christianity” በሚል ርእስ በአሰፈሩት መጣጥፋቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያነት አገልግሎት ምን እንደሚመስል ያስቃኙናልና፡፡ “እንደ ኢትዮጵያ ጳጳሳት ታሪካዊ ቅደም ተከተል ዝርዝር ከሆነ ቅዲስ ፍሬምናጦስ የተተካው በአቡነ ሚናስ ነው፡፡ መካነ ልደቱም ከግብጽ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት የግብጻውያን ልዩ የሆነው አገዛዝ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተጫነ፡፡ በዚህ ዘመን በግብጻውያን ዘንድ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ለሢመተ ጵጵስና ብቁዎች ተደርገው አይወሰዱም፡፡ ሚናስ ስለራሱ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጥቂት የሥነ ጽሑፍ መረጃ ቢተውም በሐዋርያዊ አገልግሎት በከፍተኛ አስተዋጽኦነቱ የሚጠቀሰው የዘጠኙ ቅዱሳን አገልግሎት ነው” ይላሉ ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ከላይ በጠቀስነው ጽሑፋቸው፡፡
እኚህ የታሪክ ምሁር “The Religious Life in Ethiopia” በተባለው የጥናት ወረቀታቸው ደግሞ እነዚህ ቅዱሳን ሐዋርያነትን መሠረት በአደረገው አስተዳደራዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ቤተ ክርስቲያኒቱን በየትኛው የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንደአስቀመጡ ሲገልጹ “በዘጠኙ ቅዱሳን ቤተ ጣዖትንና የቆዩ ማእከለ ሁሉን አምላኪዎች /Pagan centers/ ወደ ክርስትና ማእከልነት ለወጡ፡፡ በዚህ ሒደት ከሕዝቡ ምንም ተቃውሞ አልገጠማቸውም፤ አንድም ቅዱስ አልተሰዋም” ይላሉ፡፡
ይህ ሒደት በሀገሪቱ የክርስትና ታሪክ ውስጥ አንዱ አስደሳች ክስተት ነው፡፡ በዘጠኙ ቅዱሳን መምጣት ምክንያት የተስፋፋው የክርስትናው ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የአገሪቱም ባህል ክርስቲያናዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም የጥንቱ የክርስትና አገባብ ጠባይ ነው፡፡ የሚሉት ዶክተር ሥግግው ሐብለ ሥላሴ “ይኼ ሃይማኖታዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊ አገልግሎት፣ የኅብረተሰቡ የማኅበራዊ ኑሮ አካል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ማምለኪያ ሥፍራ ብቻ ሳትሆን የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች መፍቻ ቦታ መሆኗም በእነዚህ ቅዱሳን ተግባር ተረጋግጧል፡፡” ይላሉ፡፡ ከዚያም በመቀጠል “በጥቅሉ እነዚህ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱ ወይም ክርስትና እንደ ሃይማኖት ክስተት ሃይማኖታዊ ተቋም እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ደግሞ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ እንድትሆን አድርገዋታል” ይላሉ፡፡
ብፁዕ አበኑ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን ታሪክ” በተባለው መጽሐፋቸው እነዚህ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታችንን እንዴት እንደ አጸኑም ሲገልጹ “… በእነዚህ ዘጠኙ ቅዱሳን የጸናችልን ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትባላለች፡፡” በማለት ነው፡፡ እነዚህ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያኒቱን ያጸኑበትን የአገልግሎት ትሩፋታቸውን “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትናንትናና ዛሬ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው መጽሐፍ ሲዘረዝር “ሥርዓተ ምንኩስናን፣ ገዳማዊ ሕይወትንና ምናኔን ማስተማር፣ ገዳማትን በየቦታው ማቋቋም፣ በቅዱስ ፍሬምናጦስ ጊዜ ያልተተረጎሙ መጻሕፍትን መተርጎም፤ በከሣቴ ብርሃን ሰላማ ጊዜ የተቋቋመችውን ቤተ ክርስቲያን ማጠናከር” በማለት ነው፡፡
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የሐዋርያት ሥራ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አጭር መግቢያ” በሚል ርእስ በጻፈው መጣጥፉ እንደገለጸው፣ ዘጠኙ ቅዱሳን በትግራይና አካባቢዋ ወንጌልን በማስፋፋት ቅዱስት መጻሕፍትን በመተርጎምና ገዳማትን በማስፋፋት ለሐዋርያነት ተልእኮ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህም የመጀመሪያው ዘመን በኤርትራ፣ ትግራይ፣ ወሎ፣ ጎንደር ጎጃምና ሸዋ ሀገረ ስብከት ወንጌልን ማስፋፋት ተችሏል፡፡ በትግራይ የተሰዐቱ ቅዱሳን ገዳማት፣ በወሎ የተድባበ ማርያም ደብር፣ በሸዋ በጥንቱ ዞረሬ በዛሬው ደረሳ ብርቴ ጥረት የተደረገው በዚህ ዘመን ነው፡፡
ከተግባራቸው ተንሥተው የዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አንድምታ ዶክተር ሥርግው “The Expansion and consolidation of Christianity” በተባለው የጥናት መጣጥፋቸው ሲጠቅሱ “…. የዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሕይወት እና በሀገሪቱ የባህል ዕድገት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው” በማለት ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም” የተባለውም መድበል ከላይ የጠቀስነው የዶክተር ሥርግውን ሐሳብ በማጠናከር እንዲህ ይላል፡፡
“ከዘጠኙ ቅዱሳን መምጣት በኋላ የአክሱም ቤተ መንግሥትና መላው የኢትዮጵያ ግዛት በክርስትና ሃይማኖት ትምህርትና ስብከት ተደርሶ ነበር፡፡ ተሰዐቱ ቅዱሳን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ጥንካሬ ከፍተኛ ተልእኮን ፈጽመው ስለዐረፉ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ብላ ታከብራቸዋለች”
በዚሁ መጽሐፍ ብፁዕ አቡነ ገሪማ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሪስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና መንግሥት በየዘመናቱ” በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሑፍ ተሰዓቱ ቅዱሳን በአመራራቸው በሕዝበ ክርስቲያኑ እንደሚወደዱ ገልጸዋል፡፡
እንግዲህ ከነዚህ የመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት ክንዋኔዎች ተነሥተን ቤተ ክርስቲያኒቱ በወቅቱ ተልእኮዋን ለመወጣት የሚያስችላት የወቅቱ አደረጃጀት እንደነበራት መደምደም ይቻላል፡፡ ይኼንም አደረጃጀት ዶክተር ሥርግው ከላይ በጠቀስነው የጥናት ጽሑፋቸው ላይ የጠቀሱት “ከክርስትና መስፋፋት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ አራት አህጉረ ስብከት ነበር፡፡ እያንዳንዱ የሚመራው በጳጳስ ነበር፡፡ የእነዚህም ርእስ የአክሱም ሊቀ ጳጳስ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለነጽነው ሁሉም ጳጳሳት መካነ ልደታቸው ግብጽ ወይም ግብጻውያን ናቸው፡፡ በዶግማም ሆነ በአስተዳደር ከግብጹ ፓትርያርክ ጋራ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስፈጽሙት የግብጽን ፍላጎት ነበር፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ክስተት ነው” በማለት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር የነበረበት ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ከላይ በጠቀስነው መጽሐፍና ርእሰ ጉዳይ ላይ “አራተኛው መቶ ዓመት በቅዱሳን ነገሥተ ኢትዮጵያ አብርሃ ወአጽብሐ ዘመን መንግሥት፤ በቅዱስ ፍሬምናጦስ ዘመን ክህነት ስብከተ ወንጌል የተስፋፋበት የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር አምሮ፣ ሰምሮ፣ የታየበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክረስቲያን ብሔራዊት የሆነችበት ጊዜ ነበር” ይላሉ፡፡
ከዚህም ጋር አያይዘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአራተኛው መቶ ዓመት እስከ ዐሥራ አምስተኛው መቶ ዓመት እስከ ዐሥራ አምስተኛው መቶ ዓመት በነበሩት በዘመናት በመካከሉ በየጊዜው ችግር ቢያጋጥምም ሁለንተናዊ የሆነ አርኪ የቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ አስተዳደር የተፈጸመበት ዘመን መሆኑን አበክረው ይገልጻሉ፡፡
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን በፊት በኢትዮጵያው ጃንደረባ የተሰበከችልን በቅዱስ ፍሬምናጦስ እና በዘጠኙ ቅዱሳን የጸናችልን ነች፡፡ ከዚያም በኋላ የእስልምና መነሳት፣ የዮዲት ጉዲት ጥፋትና የግራኝ አህመድ ውድመት በቤተ ክርስቲያኒቱ በየዘመኑ ቢፈራረቁም በርካታ ወርቃማ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ከአለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ በላይ መሔድ አንችልም፡፡ የት ነበርን የሚለውን ለማሳየት የክርስትና የመጀመሪያዎቹን ዘመናት አይተናል፡፡ ቦታ ኖሮን እያንዳንዱን ዘመን ብናይ አሁን ከአለንበት ጋራ ስናነጻድር እጅግ ያስቆጭ ነበር፡፡ ይሁንና አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማየት ያነሳናቸው ማሳያዎች በቂ ናቸው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ
እንግዲህ ቤተ ክርስቲያኒቱ በየዘመናቱ የተለያዩ ፈተናዎች ቢገጥሟትም አስቀድመን እንደተመለከትነው ተልእኮዋን በአግባቡና ሥርዓታዊ በሆነ መልኩ ትወጣ ነበር፡፡ በዚህ መልኩም ከእኛ ዘመን ደርሳለች፡፡ ይሁንና አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተወሳሰበ ከመምጣቱ የተነሣ ተልእኮዋ ላይ አደጋዎች ተጋርጠዋል፡፡ እነዚህን በሦስት ከፍለን እናቀርባለን፡፡
ሀ. አስተምህሯዊ ቅሰጣ
ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው ወልድ ዋሕድ በሚለው መሠረተ እምነት እና ነቢያት፣ ሐዋርያት ስለ ወልድ ዋሕድ መሠረተ እምነት በአስተማሩት ትምህርት ላይ ነው፡፡ እነዚህን የመሠረተ እምነት ትምህርቶች ከምእመናን ልቡና የማራቅና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት የማስወገድ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ የእርሷ ነን በሚሉ በተግባራቸው ግን ባልሆኑት እየተሠራ ነው፡፡ ይኼም ሥራ እየተሠራ ያለው በተሐድሶ ኑፋቄ አንቀንቃኞች፣ ሰባክያንና የስሕተት ትምህርት ባዘሉ መጻሕፍት ጸሐፊያን ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓተ አምልኮ፣ ትውፊትና ታሪክ የመከለሱና የመበረዙ ሥራ በነዚሁ አካላት ተጧጡፏል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን አደጋ በአግባቡ የተረዳና ተገቢውን የመፈትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የስብከተ ወንጌል ዕቅድና ግብ የላትም፡፡ ለዚሁ ተግባር ማስፈጸሚያ ተገቢ አደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና በጀት አትመድብም፡፡ ይኼ ደግሞ ችግሩ እጅግ አሳሳቢና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በማሳካት ረገድ መጪውን ዘመን ጨለማ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ እንደማሳያ የሚጠቀሰው በ1999-2000 ዓ.ም በተካሔደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤት በግልጽ የታየው እውነታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምእመናንን ቁጥር ከ50.6 በመቶ ወደ 43.5 በመቶ ወርዷል፡፡ በከተማ ቤተ ክርስቲያናችን ያላት የምእመናን ድርሻ እየቀነሰ መጥቶ ወደ 59.1 በመቶ ሲሆን በገጠር ደግሞ 40.5 በመቶ ነው፡፡ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለው ድርሻ ቁልቁል እየወረደ መሆኑን ያሳያል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የ7.1 በመቶ መቀነስ አሳይቷል፡፡ ይኼ ሁኔታ በዚህ መልኩ ከቀጠለ የቤተ ክርስቲያን ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን ለመጠቆም ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ የእርሷን እንጀራ እየበሉ በሌላው ደጅ የሚጠኑ ሰዎቿ ድርሻውን ይወስዳሉ፡፡
ለ. አስተዳደራዊ ችግር
የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ተልእኮዎች የሆኑት ማጥመቅ፣ ማጽናትና መከታተል መሆኑ እየታወቀ ይህን ተልእኮ ማሳካት የሚያስችል የተጠናከረ አስተዳደራዊ አደረጃጀትና የሰው ኃይል የለም፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ አደርጃጀትና አወቃቀር ወቅቱ ከሚጠይቀው፣ አሁን ካሉት ሥራዎች ስፋትና ከልማትና ማኅበራዊ እንቅስቅሴዎች ጋር አብሮ የሚጓዝ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ወቅቱን በመዋጀት ከጊዜው ጋራ እንዳትራመድ አድርጓታል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፖሊሲ በማውጣትና ስትራቴጀ በመንደፍ የመምራት ሓላፊነቱንና አደራውን በብቃት ለመወጣት በሚያስችል ሁኔታ አልተደራጀም፡፡ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች አፈጻጸም የሚከታተልበትና የሚገመግምበት መከታተያና መገምገማያ እንዲሁም የአሠራር ሥርዓት የለውም፡፡
እንደሚታወቀው የአሠራር መዋቅር ተቋማዊ ግብን የማስፈጸም ሥርዓት እና ብቃት እንዲኖረው ተደርጎ ይዘጋጃል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ የአሠራር ሥርዓትን ጠብቆ ጉዳይን በወቅቱ ማስፈጸምም ሆነ መፈጸም አስቸጋሪ ነው፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የቤተ ክህነቱ አሠራር መዋቅሮች የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔዎች የማስፈጸምም ሆነ የመፈጸም ግዴታ ቢኖርባቸውም መዋቅራዊ የአሠራር ሥርዓቱ ልል ከመሆኑ የተነሣ ይህ ሲሆን አይታይም፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን ከአስፈለገ አንድ የአጥቢያ አስተዳዳሪ የሚጥስበት፣ የጠቅላይ ሥራ አስኪያጅን የሥራ መመሪያ አንድ የመምሪያ ሓላፊ ተገቢና ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የማይቀበልበት እና የማያስፈጽምበት ሁኔታ አለ፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚታየው የአስተዳደራዊ አሠራር ክፍተት እንዲህ መሆኑ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ አካላት ምቹ መስፈንጠሪያ ሆኖላቸዋል፡፡ በየትኛውም አግባብ በየትኛውም የአሠራር መዋቅር የሚፈልጉትን ያስወስናሉ፤ ያልፈለጉትን ውሳኔ ያሽራሉ፡፡
ገዳማቱና የአብነት ትምህርት ቤቶቹም የሚገኙበት አስከፊ ገጽታም የአስተዳደራዊ ችግሩ ነጸብራቅ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ በሚፈጠሩ የተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች የተነሣ ገዳማቱ ያላቸውን ጥቂት ገቢ፣ መሬት፣ የሰው ኃይልና ሌሎች ሀብቶችን እንዳይጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ገዳማቱን ወደ ቁሪት ገዳምነት እንዲቀየሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ በገዳማት ሊኖር ይችል የነበረውንም የልማት ተሳትፎ በእጅጉ ጎድቶታል፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶች ለደቀ መዛሙርቱ እና ለመምህራኑ ምግብና መጠለያ ማግኘት ተስኗቸው ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉና እንዳይስፋፉ የሆነውም የአስተዳደራዊው ችግር ውጤት ነው፡፡ በዚህ መልኩ በየገዳማቱና የአብነት ትምህርት ቤቶቹ የሚታየው ችግር በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የነገይቱን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተካ ትውልድ ማግኘትን ከባድ ያደርገዋል፡፡
የአስተዳደሪዊው ችግር ውጤት /Effect/ ያረፈው በገዳማቱና በአብነት ትምህርት ቤቶቹ ብቻ ሳይሆን በካህናቱም ኑሮ ላይ ነው፡፡ ካህናት የሚያገኙት ደመወዝ አሁን ካለው የገበያ ሁኔታ አንጻር ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዳደር በቂ አይደለም፡፡ ተምረው ነገ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ፣ ኑሯችንን ያሻሽላሉ፤ ጧሪ ቀባሪያችን ይሆኑናል የሚሏቸውን ልጆቻቸውን ዘመናዊ ትምህርት ማስተማር እንዳይችሉ ተፅዕኖ አድርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ ሲብስም “እኔ በየአብነት ት/ ቤቱ ብዙ ደክሜ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ተምሬ ምን አገኘሁ” በሚል ልጆቻቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት እንዲያርቁ አድርጓቸዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት /የሰው ኃይል፣ ገንዘብ፣ ንብረት/ አመራር ሠራተኞችን፣ ገንዘብንና ንብረትን በአግባቡና ዘመኑ በሚጠይቀው የአሠራር ዘይቤ በማቀናጀት የቤተ ክረስቲያኒቱ ዋነኛ ተልእኮ ማስፈጸሚያ የሆነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማስፋፋትና ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል ዕውቀትና ልምድ ያለው የሰው ኃይል እና አስተዳደር ሥርዓት የላትም፡፡ ይህ ደግሞ የመጪው ዘመን ቀጣይ አገልግሎቷን በሚፈለገውና ወቅቱ በሚጠይቀው መጠን ውጤታማ አያደርገውም፡፡
በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ ቤትና በየአህጉረ ስብከት የሓላፊዎች ምደባ የትምህርት ዝግጅትን ሙያና ችሎታን ወይም ብቃትን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ ይኼ ደግሞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የሆነ የአመራር እና አስተዳደር ችግር የሀብት ብክነትና ዝርፊያ፣ ውዝግብና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን አንሰራፍቷል፡፡ ይህ ሁኔታ በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለቤተ ክረስቲያኒቱ ተልእኮ ግድ የሌላቸው ሰዎች መጠራቀሚያ ትሆናለች፡፡ ምእመኑም ባለው አመራር ላይ እምነቱን እያጣ ሲሔድ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ማበርከት የሚገባውን በጎ አስተዋጽኦ ከማበርከት ሊታቀብ ይችላል፡፡
ሐ. ዘመናዊ የፋይናንስ አስተዳደር አለመኖር
ቤተ ክርስቲያኒቱ ተልእኮዋን መፈጸም የሚያስችላት በማእከላዊነት የሚተዳደር ዘመናዊ የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት የላትም፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ከምፅዋት ከሚያገኙት ገንዘብ ባሻገር የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሕንፃዎች እየገነቡ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት ቢያደርጉም የፋይናንስ አያያዛቸውና አጠቃቀማቸው ለብክነትና ምዝበራ የተጋለጠ ነው፡፡ በቤተ ክርስሪቲያኒቱ ውስጥ ጠንካራ የፋይናንስና የኦዲት ሥርዓት እንዲሁም ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት በዕቅድና ሪፖርት የታገዘ የአሠራር ሥርዓት የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ለልማት ሊውል የሚችለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አንጡራ ሀብት ሊባክን ከመቻሉም በላይ ጠንካራ ልማት ሊመጣ አልቻለም፡፡
እንዲህ ዓይነቱ የፋይናንስ አያያዟና አጠቃቀሟ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሠረታዊ ተልእኮ ከማደናቀፉም በላይ የራሷን አገልጋዮች በአመዛኙ ከችግር ማሳቀቅ ያልቻለበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱ በሐዋርያዊ ተልእኮዋ አፈጻጸሟ እንድትደክም ከማድረጉም ባሻገር የሙስናው ጽንፍ ቤተ ክርስቲያኒቱን በምእመናን ዘንድ ያላትን አመኔታና ከበሬታ እያሳጣት ነው፡፡
በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ የሆነ የፋይናንስ አስተዳደር ባለመኖሩ አገልጋዮቿ ገጠሩን እየተው ገቢ ይገኝባቸዋል ወደሚሏቸው ከተሞች እንዲጎርፉ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በገጠር የሚገኙትን ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ያለ አገልጋይ በማስቀረቱ እንዲዘጉ ሆነዋል፡፡ እዚህ ላይ ሆነን የነገይቱን የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን ስናስብ ስጋት ላይ ይጥለናል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲሁም በማኅበራዊ አገልግሎትና ልማታዊ ሥራዎች ሊደግፏት የሚችሉት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በምዝበራና ብኩንነት እየተዳከሙና የሚጠበቅባቸውን ያህል ፍሬያማ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሥር እየሰደደና እየጸና ከሔደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለማትወጣው አዘቅት ሊዳርጋት ይተላል፡፡ የጥቂት ግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት እየጨመረ መዋቅራዊ ውሳኔዎችና አፈጻጸሞች እየከሰሙ ከሔዱ የቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ዕጣ ፋንታ በግለሰቦች እጅ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል፡፡ አሁን እየታየ ያለውም በአመዛኙ የዚሁ ተመሳሳይ ነው፡፡
የመፍትሔ አቅጣጫ ጥቁምታ
በአደጋ ቁልቁለት ላይ ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሯዊ ቅሰጣ-አስተዳደራዊ ፋይናንሳዊ ችግሮች ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጧን በአስቸኳይ የምትፈትሽበት መፍትሔና አፋጣኝ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አለባት፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ቤተ ክርስቲያናችን ዋናና ተቀዳሚ ዓላማዋ የሆነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት በማስፋፋት፣ የምእመናንን ክርስቲያናዊ ሕይወት የማጽናትና የማጠናከር እንዲሁም ያላመኑትን በማስተማርና በማሳመን ተልእኮዋን ማሳካት የሚያስችላትን ተገቢውን አደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና በጀት ሥርዓትም እንዲኖር በማድረግ ረገድ ቀዳሚ ሓላፊነት እንዳለበት ይተወቃል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከውስጥ ሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ በማደናቀፍ ከሌሎች የተለየ ዓላማ ካላቸው ጋር ሽርክና መፍጠር ምእመናንን ከበረታቸው እያስኮበለሉ ባሉት ላይም በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት እርምጃ የሚወስድበትን አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ማስቀመጥ አለበት፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በአስቸኳይ ውስጧን በመፈተሽ ጊዜ እና መስክ ወለድ ለሆኑ መሠረታዊ ፈተናዎችና ችግሮች ዘለቄታ ያለው፣ ተጨባጭና ችግር ፈቺ መፍትሔ ማስቀመጥ አለባት፡፡ ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ አደረጃጀት መሠረታዊ ተልእኮዋን ለማስፈጸም፣ ቀልጣፋ አሠራርን፣ ግልጽ፣ ሓላፊነትና ተጠቃቂነት ሊያሰፍን በሚያስችል መልኩ አስተዳደራዊ የመዋቅር ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ሙሉ ሥልጣንና ሓላፊነት ያለው በብፁዓን አበው የሚመራ፣ በሥሩ የተለያዩ ባለሙያ ምሁራንን ያካተተ የአማካሪ ቡድን የሚዋቀርበት አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅራዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚጠቁም አካል እንዲቋቋም ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ የገዳማቱ ሥሪት ገቢያቸውን በራሳቸው እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል በመሆኑና ወደ ሀገረ ስብከቶች ወይም ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገቢ ፈሰስ እንዲያስገቡ የሚጠይቁ ባለመሆናቸው፤ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የልማት ፕሮጀክቶችን በየገዳማቱ በተናጠል የሚሠራበትን አቅጣጫ ማስቀመጥ ለዚህም ሥራ ተስማሚ የሰው ኃይልና በጀት መመደብ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልማት የሚመራው አካል መንፈሳዊውን አገልግሎት ከሚመራና ከሚያከናውነው አካል ተለይቶ የልማት አስተደደሩ በቂ ዕውቀትና ልምድ ባለው የሰው ኃይል የሚመራበትን አስተዳደራዊና መዋቀራዊ ሁኔታዎች ማመቻቸት እና ማጠናከር ይኖርበታል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት ዘመናዊና ወቅታዊ ድርብ የሒሳብ አያያዝን የተከተለ እንዲሁም የበጀት ሥርዐቱም በመደበኛና የካፒታል በጀት ተለይቶ በየዘመኑና በየሥራ ዘርፉ የበጀት ሥርዓት ተግባራዊ የሚሆንበትን፤ በየወቅቱ ሪፖርት እየቀረበበት ግምግማና ክትትል የሚደረግበትን አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ከዚህም ጋር አያይዞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በማእከላዊነት የሚተዳደር የፋይናንስ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖራት ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አሠራር በመሆኑ በተገቢው ሙያዊ ጥናት መሠረት ተግባራዊ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ላእላይ መዋቅር የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ መፍትሔ ይሆናሉ በማለት የተጠቆሙትን ሐሳቦች እንዳላቸው ተጨባጭነትና ተግባራዊነት እንዲጠቀምባቸው አበክረን እንገልጻለን፡፡ ምክንያቱም አደጋው በዚሁ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዐይናችን እያየ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቀሳጮች ተውጣ፣ ታሪካዊና ወቅታዊ ልዕልናዋን አጥታና ሊኖራት የሚገባው ተደማጭነት ተሸርሽሮ አነስተኛ ቁጥር ተከታይ ያላት እንዳትሆን ስለምንሰጋ ነው፡፡ አሁን ያለው ነባራዊ እውነታም የሚያሳየው ይህንኑ ነውና፡፡
እንግዲህ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁን ያለችበት ሁኔታ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ዘመናት ከነበረችበት ደረጃ ምን ያህል በችግር የተተበተበ እንደሆነ ብዙ የሚያከራክር አይመስለንም፡፡ ከዚህም በላይ ግን አሁን በምንንደረደርበት አቅጣጫ ከቀጠልን ከዚህም የከፋ ውስብስብና ዘመን ተሻጋሪ ችግሮችን ለመጪው ትውልድና ለነገይቷ ቤተ ክርስቲያን እንዳናስተላልፍ ያሰጋል፡፡ ይህም እንደትውልድ ከታሪክ፣ ከሕሊናና ከእግዚአብሔር ተጠያቂነት አያድነንም፡፡
ይህ ማለት ግን የተሻሉ ዕድሎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ከላይ ለመጠቆም እንደተሞከረው በቅዱስ ሲኖዶስ የመፍትሔ እርምጃዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ወደፊት ሊገጥሙን የሚችሉ አደጋዎችን በተሻለ ብቃት መሻገር እንችላለን፡፡ ይህ ሆኖ እንድናይ ደግሞ አሁን ያለንበትን አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ድባብ በመሠረታዊነት ሊቀይሩ የሚያስችሉ ምሁራዊ እይታዎችንና ሒሶችን ማስፋትም ይጠበቅብናል፡፡
ውጤቱም የተጋረጡብንን መሠረታዊ ችግሮች መሻገር ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላእላይና ታህታይ የሥልጣን መዋቅር የሚቀመጡ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በብቃታቸው፣ በሥነ ምግባራቸው፣ በመንፈሳዊ ተጋድሎ የታወቁ፣ ቤተ ክርሰቲያኒቱን ካለችበት አሰክፊ ችግር በዘላቂነት ለማውጣት ችሎታ፣ እልሁና ርእይ ያላቸው ይሆናሉ ብለን እናምናለን፡፡ አምላከ ቅዱሳን ይህንኑ ያድለን፡፡
ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ፣ 19ኛ ዓመት ቁጥር 2