- “ሐዊረ ሕይወት ከመንፈሳዊ ጉዞዎች ሊጠበቁ የሚገባቸውን ተግባራት የሚያመለክት ነው”
የካቲት 5/2004 ዓ.ም
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
ማኅበረ ቅዱሳንን ከአባላቱ ውጭ ካሉ ምእመናን ጋር የሚያገኘው መድረክ እንደሆነ ይታመናል ሐዊረ ሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ፡፡ ከ4 ሺሕ ምእመናን በላይ ይሳተፉበታል ተብሎ ለሚጠበቀው የዘንድሮው ጉዞ ከማንኛውም ጊዜ በላይ በተቀናጀና በተደራጃ መንገድ ዝግጁቱን ለማሳካት ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሚያስተባብር አገልጋይም ተመድቧል፡፡ በአገር ቤት ያሉትን ምእመናን ብቻ ሳይሆን ባሕር አቋርጠው ሰማይን ጠቅሰው ለሚመጡ ምእመናን ሁኔታዎች ተደላድለውላቸዋል፡፡ የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት ከወትሮው በምን ይለያል? የሚሉ እና ተያያዥ ጥያቄዎችን እንዲመልሱልን የጉዞውን መርሐ ግብር የሚያስተባብሩትን ዲያቆን ሙሉዓለም ካሳን የመካነ ድራችን እንግዳ አድርገናቸዋል ተከታተሉን፡፡
መካነ ድር፡- እስኪ አጠር አጠር ካሉ ጥያቄዎች ልጀምርና ጉዞው መቼ ይደርጋል? ስንት ቀንስ ይፈጃል?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ጉዞው መጋቢት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ይከናወናል፡፡ መርሐ ግብሩም ደርሶ መልስ ነው፡፡
መካነ ድር፡- የዘንድሮው ጉዞ ወደየት ነው የሚደረገው?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ጉዞው በደብረ ብርሃን መስመር ወደ በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይደረጋል፡፡
መካነ ድር፡– በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም የተመረጠበት ልዩ ምክንያት አለ?
ዲ/ን ሙሉ ዓለም፡- ባለፈው ዓመት ከተመለከትነው ልምድ በመነሣት የዚህን ዓመት ጉዞ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ዓመት በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን ይዘን እንጓዛለን፡፡ በመሆኑም እስከ 4000 ምእመናን እንደሚጓዙ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህን በርካታ ቁጥር ሊያስተናግድ /ሊቀበል/ የሚችል የተመቸ መልክዐ ምድር ያስፈልጋል፡፡ በአንጻሩም አቅመ ደካማ ሰዎች በጉዞው መሳተፍ ቢፈልጉ ደርሰው በጊዜ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በተለየ መልኩ ደግሞ በተመረጠው ደብር አካባቢ ካሉት አድባራትና ገዳማት በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በጥንታዊነቷና በታሪካዊነቷ በውስጧ ከያዘቻቸው የአብነት መምህራንና ደቀመዛሙርት ቀዳሚ በመሆኗ መርጠናታል፡፡
መካነ ድር፡- ሐዊረ ሕይወት ማለት ምን ማለት ነው?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ሐዊረ ሕይወት የሚሉ ሁለቱ ቃላት ከግእዝ ቋንቋ የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሙሉ ትርጉማቸውም የሕይወት ጉዞ ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዓለማችን የሚከናወኑ የተለያዩ የጉዞ ዓይነቶች አሉ አንድ ሰው ለመዝናናትም ይሁን ዘመድ ለመጠየቅ ወይም ደግሞ አገር ለማየት ይጓዛል፡፡ ያ ጉዞ ሥጋዊና ምድራዊ ጉዞ ነው፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ ቀድሞ በብሉያት እንደተፈጸመው በዘመነ ሐዲስም አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዘው እሱን አብነት አድርገን እንጓዛለን፡፡ በዓላትን ለማክበር ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ከቦታውም በረከት ለማግኘት እንሔዳለን፡፡ ይህ ጉዞ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት ጉዞ ስለሆነ ሐዊረ ሕይወት /የሕይወት ጉዞ/ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
መካነ ድር፡- የዘንድሮው ጉዞ ዝግጅትና ዓላማስ ምን ይመስላል?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ስለ ዝግጅቱ ከመናገሬ በፊት ስለጉዞው ዓላማ ከመናገር ብጀምር ይሻላል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት “ስም ግብርን ይገልጠዋል” ተብሎ እንደተጻፈው ጉዞው ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ዓላማን ይዞ የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው በመሆኑም በሥራ ቦታ በመኖሪያ አካባቢ ባለው ውጣ ውረድ ሁከተ ኅሊና ያጋጥማል፡፡ በተለያየ ምክንያት የተጨነቀና የዛለ አእምሮ በእንደዚህ ዐይነት ጉዞ ይታደሳል፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ሲነገርም በተከተተ ልቡና ማዳመጥ ያመቻል፡፡ በእንደዚህ ዐይነት ቦታና ሁኔታ የሚነገር ቃለ እግዚአብሔር ወደ ውስጥ ዘልቆ ይገባል የንስሐ ፍሬንም ያፈራል፡፡ ከቦታውም በረከት ያስገኛል፡፡ በዚያውም በተለያየ አጋጣሚ የእግዚአብሔር ቃል ይሰበካል፡፡ በተለየ አጋጣሚ የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ለማጠንከር ለመንፈሳዊ ዓላማ ታስቦ የተዘጋጀ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው፡፡ በተጨማሪም ከመንፈሳዊ ጉዞ ምን ተግባራት እንደሚጠበቁና ጉዞውን ለሚያዘጋጀው ተቋም የሚያስፈልገውን ሥርዐት ለማመልከትም ያግዛል ተጓዦች በአካል በአእምሮ በነፍስ ተዘጋጅተው በቅዱስ ቦታ ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ ያስተምራል፡፡ የጉዞው ዓላማ ሥጋዊ ጥቅምና ቁሳዊ ትርፍ ለማግኘት ታስቦ የተዘጋጀ መርሐ ግብር አይደለም ዋናውና ተቀዳሚ ዓላማችን መንፈሳዊ ትርፍ እንጂ ሥጋዊ ትርፍ አይደለም፡፡
ዝግጅቱን በተመለከተ ጉዞው የተሳካ እንዲሆን አባቶች በጸሎት እንዲያስቡን አሳስበናል፡፡ የጉዞውን ትኬት በአካል በስልክ በአጭር የስልክ መልእክትና በኢ-ሜል ለማግኘት መረጃ ለሚጠይቁ ምእመናን ተፈላጊውን መረጃ ለመስጠት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ተመድቧል፡፡ በጉዞው የሚሳተፉት አዲስ አበባ የሚገኙ ምእመናን ብቻ አይደሉም ከክፍለ ሀገርና ከውጭ ሀገር የሚመጡ ተጓዦች ስለሚኖሩ በጉዞው መርሐ ግብር እንዴት መሳተፍ እንደሚችሉ ከወዲሁ ግንዛቤ በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡
መካነ ድር፡– የጉዞ ቲኬቶችን የት ማግኘት ይቻላል?
ዲ/ን ሙሉ ዓለም፡- በአዲስ አበባ ያሉ ምእመናን 5 ኪሎ ሸዋ ዳቦ ፊትለፊት በማኅበረ ቅዱሳን ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ማከፋፈያ ሱቅ፣ እሳት አደጋ ፊት ለፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በቂርቆስ የገበያ አዳራሽ ብሎክ A ቁጥር 230፣ ጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ ኮልፌ አጠና ተራ እፎይታ ገበያ ፊት ለፊት ሳሪስ ማከፋፈያ አዲሱ ሰፈር፣ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥር፣ አምስት ኪሎ በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ሥር ንዋየ ቅዱሳት መሸጫ፣ ዓለም ፀሐይ ድልድይ ፊት ለፊት፣ ኪዳነ ምሕረት ከፍተኛ ክሊኒክ፣ መርካቶ ኬኔዲ ሕንፃ 1ኛ ፎቅ እቴነሽ የሕንጻ መሣሪያ ቁጥር 107ና ኮስሪሞ ላንድ አውቶብስ ተራ ትልቁ መናኸሪያ ፊት ለፊት ማግኘት ይቻላል፡፡
ከክፍለ ሀገር ለሚመጡ ተጓዦች በየርእሰ ከተማቸው ባለው የማኅበረ ቅዱሳን ማእካላት ጽ/ቤት ቲኬቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከውጭ ሀገር መምጣት ለሚፈልጉ ምእመናንም http://www.hawirehiywet.somee.com መመዝገብ ይችላሉ፡፡ የውጭ ሀገር ተመዝጋቢዎች ስለ ጉዞው ትኬት ክፍያ በተመለከተ በኢ-ሜይል መልእክት መለዋወጥ ይቻላል፡፡
መካነ ድር፡- በጉዞው የሚቀርቡ መርሐ ግብሮች ምንድን ናቸው?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም እንደደረሰን ጸሎተ ቅዳሴውን እናደርሳለን፡፡ ከቅዳሴ ውጭ በቤተ ክርስቲያኑ ካህናት ሊቃውንትና ደቀ መዛሙርት ጋር በመሆን የጋራ ጸሎት እናደርሳለን በመቀጠል በማኅበርና በግል የተጋበዙ ዘማርያን ያሬዳዊ መዝሙር ያቀርባሉ፡፡ በገና ደርዳሪዎችም የበገና መዝሙር ያሰማሉ ከዚያም በሊቃውንት አባቶቻችን ትምሕርተ ወንጌል ይሰጣል፡፡ በመጨረሻም ትምህርት ያከናወኑ፣ ምሥጢር ያደላደሉ፣ በእድሜ የበሰሉ በመከራ የተፈተኑ አባቶቻችን የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ምክረ አበው በምእመናን በጣም የሚወደድና የሚናፈቅ መርሐ ግብር በመሆኑ ሰፋ ያለ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር የምእመናን ጥያቄ ይመለሳል፡፡ ሕይወታቸውም ይስተካከል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተዘጋጀው የጉዞ ትኬት ላይ እንደተገለጠው ምእመናን ጥያቄያቸውን በስልክ፣ በኢ-ሜይል በአጭር የሞባይል መልእክት በተለይም በአካል በመቅረብ ጥያቄአቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡
መካነ ድር፡- ከተጓዦች የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- በጉዞው ሊደረጉ ስለሚገባቸው ዝግጅቶች ከሞላ ጎደል በትኬቶች ላይ ተገልጠዋል፡፡ ሆኖም ለማስታወስና ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስታወስ እንወዳለን፡፡ የመጀመሪያው የጊዜ አጠቃቀማችን ሥርዓታዊ መሆን አለበት፡፡ ከአዲስ አበባ የምንነሣበት ሰዓት ከንጋቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ ነው፡፡ ከዚህ የጊዜ ገደብ ቀድመንም አንነሣም ዘግይተንም አንጓዝም ስለዚህ በተቻለ መጠን ተጓዞች ሰዓት አክብረው እንዲገኙ እናሳስባለን፡፡ ሁለተኛው ማንኛውም ዐይነት ጽሑፍ ያላቸውን ቲሸርቶች ለብሶ መምጣት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተረፈ አለባበሳችን ክርስቲያናዊ መሆን አለበት፡፡ በመጨረሻም አስተባባሪዎች የሚነግሩንን እየሰማን ምንም ዐይነት መጠባበቅ ሳይኖር በተመደብንበት መኪና በተሰጠን ሰዓት መገኘት ከተጓዦቻችን ይጠበቃል፡፡
መካነ ድር፡- የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት ካለፈው ዓመት ሐዊረ ሕይወት በምን ይለያል?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት በርካታ አዲስ ነገሮችን ይዟል በእውነት ለመናገር የአሁኑ ሐዊረ ሕይወት የተደራጃና የተጠናከረ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ለመርሐ ግብሩ ስኬት ሲባል ዝግጅቱ ቀደም ተብሎ ተጀምሯል፡፡ ሰፊ የዝግጅት ጊዜ መኖሩ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ያመቻል ሌላም ባለፈው ዓመት ለመርሐ ግብሩ ሲባል ዝግጅቱ ቀደም ተብሎ ተጀምሯል፡፡ ሌላው ባለፈው ዓመት ባደረግነው ጉዞ የተሰጡን አስተየየቶች ነበሩ፡፡ እነዚያ አስተየየቶች በአሁኑ ጉዞ ተስተካክለውና ታርመው አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ለምክረ አበው የሰጠነው ጊዜ ሰፊ መሆኑም በራሱ አንድ አዲስ ነገር ነው ከሁሉም በላይ የምእመናን ቁጥር በ1ሺሕ ጨምሯል፡፡ ባለፈው ዓመት 3000 የሚሆኑ ተጓዦች ነበሩ አሁን ግን የምእመናን ቁጥር በ1000 ልዩነት 4000 ይሆናል፡፡ የምዝገባው አተገባበርም ቢሆን የተሳለጠና የተመቻቸ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከጅማ፣ ከመቀሌ ከአፋርና ከናዝሬት የመጡ ተጓዦች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከእሩቅ ሀገር ለሚመጡ ምእመናን የአዳር መርሐ ግብር አዘጋጅተናል በአጠቃላይ ጉዞው እስኪጠናቀቅ ድረስ ራሱን የቻለ ጽ/ቤት፣ መደበኛ አገልጋይ፣ መኖሩ፡፡ ትምህርቶች በብሉቱዝና በሲዲ ወጪውን የሚሸፍንልን ካገኘን ለማሠራጨት መዘጋጀታቸው አዲስ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች የዚህን ዓመት ሐዊረ ሕይወት ልዩ ያደርጉታል፡፡
መካነ ድር፡- የመነሻ ቦታው የት ነው?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡– ከአዲስ አበባ ለሚነሡ ምእመናን 5ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ በማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ምእመናን ደግሞ ባሉበት ርእሰ ከተማ በማኅበረ ቅዱሳን ማእከላት ጽ/ቤት መነሻቸውን ያደርጋሉ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ማስታወስ የምፈልገው ጉዳይ ከአዲስ አበባ ዙሪያ የሚመጡ ምእመናን በዋዜማው መጥተው ማደር አይጠበቅባቸውም፡፡ ከቦታው ቅርበት የተነሣ በዕለቱ ቀደም ብለው ቢነሡ መጋቢት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት መድረስ ይችላሉ፡፡ ከጅማ፣ ከመቀሌ፣ ከአፋርና ራቅ ካለ ቦታ የሚመጡ ምእመናን ግን መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለእነዚህ እንግዶቻችንም በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ መኝታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡
መካነ ድር፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- እግዚአብሔር አምላክ ሥራችንን እንዲያከናውንልን ምእመናን በጸሎታቸው እንዲያስቡን ቀዳሚው መልእክቴ ነው፡፡ ሌላው መልእክት ይህ ጉዞ ለሥጋዊ ጥቅምና ለትርፍ የተዘጋጀ የጉዞ መርሐ ግብር አይደለም፡፡ 4000 ሰዎችን የሚያስጠልል ድንኳን፣ 4000 ወንበርና 4000 ሳህን ጀኔሬተርና ሞንታርቦ ከአዲስ አበባ ጭነን ነው የምንሔደው የሕክምና ቡድኖች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከእኛ ጋር ይጓዛሉ፡፡ ስለዚህ ከትራንስፓርት ውጭ ከ100,000 ብር በላይ ወጭ ይጠይቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ዶግማ የጠበቁ ትምህርቶች በሲዲ ለማሠራጨትም አቅደናል እነዚህን ሁሉ ወጭዎች ለመሸፈን ማስታወቂያ በማሠራትም ይሁን በተለያየ ዘዴ ጉዞውን እንድንደግፍ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
መካነ ድር፡– ስለነበረን ቆይታ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡
ዲ/ን ሙሉዓለም፡- እኔም ተገቢውን መረጃ በተገቢው ሰዓት እንዳደርስ እድሉን ስለሰጣችሁን በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡