መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም.
ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ አገልግሎቱን ለማፋጠን ባቋቋማቸው 44 ማእከላት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሂድ ተገለጸ፡፡
የሀገር ውስጥ ማእከላትና የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ሓላፊና ምክትል ዋና ጸሓፊ ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል እንደገለጹት ማእከላት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ከጥቅምት 15 እስከ ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ወቅት እንዲደረግ ምክንያቱ የማኅበሩ ቀጣይ የ4 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ በማኅበሩ 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማጽደቅ ስለነበረበት መሆኑን ገልጸው ማእከላቱም የቀጣይ 4 ዓመት ዕቅዳቸው በስልታዊ ዕቅድ መሠረት የሚያዘጋጁ ሲሆን የ2005 ዕቅዳቸውም በጉባኤው የሚጸድቅ በመሆኑ ነው፡፡
ከጥቅምት አጋማሽ እስከ ኅዳር መባቻ ድረስ በሚደረገው ጉባኤም በየማእከላቱ ከዋናው ማእከል ተወካይ ልዑክ የሚገኝ ሲሆን በጉባኤውም የ2004 ዓ.ም. የዕቅድ አፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ይገመገማል የተለያየ አጀንዳም ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን ጉባኤውም የ2005 ዓ.ም. ዕቅድ በማጽደቅና የአገልግሎት ጊዜያቸውን የፈጸሙ የማእከላት የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ምርጫ ይካሄዳል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤውም የማእከላቱ አባላት፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች፣ የምእመናን ተወካዮች፣ የወረዳ ማእከላትና የግንኙነት ጣቢያዎች ተወካዮች ይሳተፋሉ፡፡
በዚህ የማእከላት ጠቅላላ ጉባኤ እያንዳንዱ ማእከል ለ2 ቀናት የሚቆይ ጉባኤ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ዲ/ን አንዱ አምላክ ይበልጣል ከማእከላቱ ጠቅላላ ጉባኤ በመቀጠልም በማእከላቱ ስር የሚገኙ ወረዳ ማእከላት ጠቅላላ ጉባኤያቸው የሚያከናውኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በአሁኑ ወቅት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በሀገር ውስጥ ብቻ 44 ማእከላት፣ 333 ወረዳ ማእከላት 183 ግንኙነት ጣቢያዎችና 325 የግቢ ጉባኤያትን ያዋቀረ መሆኑ ይታወቃል፡፡