ጥቅምት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.
ማኅበረ ቅዱሳን በጉራጌ ሀገረ ስብከት በምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ሲያከናውናቸው የነበሩት የመጠጥ ውኃና የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ተመረቁ፡፡
የምረቃ መርሐ ግብሩ ጸሎተ ወንጌል በማድረስ የተጀመረ ሲሆን 100 ሺህ ሊትር መያዝ የሚችለው የኮንክሪት የውኃ ማጠራቀሚያ በብፁዕነታቸው ተመርቋል፡፡ በተጨማሪም የአብነት ትምህርት ቤቱ በብፁዕነታቸው ተባርኮ የተመረቀ ሲሆን እያንዳንዱን ክፍል በመዘዋወር ጎብኝተዋል፡፡ በግንባታው የተካተቱት 12 የተማሪዎች ማደሪያ ክፍሎችና ሌሎች 4 ለመምህራን የተዘጋጁት ክፍሎች ሲሆኑ በእያንዳንዱ የተማሪዎች ማደሪያ ክፍል ባለ 2 ተደራራቢ አልጋዎች ይገኛሉ፡፡ 4 ለመምህራን የተዘጋጁት ክፍሎች በቅርቡ ሙሉ የመኝታ ቁሳቁስ እንደሚሟላላቸው ተገልጿል፡፡
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በሰጡት ቃለ ምዕዳን “በዚህ ታላቅ ገዳም በቅዱሳን አባቶቻችን በታሪካቸውና በገድላቸው እንዲሁም በቃል ኪዳናቸው አሻራ ላይ ነው ያለነው፡፡ የቅዱሳን በረከት ለኢትዮጵያ ሀገራችን ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ዓለም በመከራ ሲናጥ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን የያዙ ቅዱሳን ጸሎትና አፅማቸው ጠብቋታል፡፡ የጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በተጋድሎ ከፀኑበት ቦታ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ያኔ በዚህ ቦታ ላይ እነሱና መላእክት ብቻ ነበሩ የከተሙት፡፡ ምድራውያን ሰዎች ሰማያውያን መላእክት የሆኑበት ቦታ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ እኛ በዚህ አለም ስንኖር የቅዱሳኑን ፈለግ ተከትለን ለበረከት ነው የመጣነው፡፡ በዚህ ቦታ ተገኝታችሁ ይህንን ቅዱስ ገዳም ለመርዳትና ለመደገፍ የወጣችሁ፤ የወረዳችሁ ሁሉ ዋጋችሁ ታላቅ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም አበምኔት አባ አብርሃም ወልደ ኢየሱስም ማኅበረ ቅዱሳን ስላከናወነው ተግባር ሲገልጹ “ማኅበረ ቅዱሳን እያከናወነ ያለው አገልግሎት ለዓመታት ስንቸገርበት የነበረውን የውኃ ችግር የፈታ ነው፡፡ ለ6 ወራት ከብቶች በ3 ቀናት ልዩነት ነው ውኃ የሚያገኙት፡፡ እኛም የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት በሳምንት በነፍስ ወከፍ 10 ሊትር ውኃ ብቻ ነው የምናገኘው፡፡ ከዚህ በፊት ውኃ ለማምጣት እስከ 40 ደቂቃ ይወስድብን ነበር፡፡ ሄደንም ወረፋ ጠብቀን ነው የምናገኘው፡፡ አንዳንዴም ተሰልፈንም ላይሳካልን ይችላል፡፡ ዛሬ ማኅበረ ቅዱሳን ከ100 ሺህ ሊትር ውኃ የሚይዝ ማጠራቀሚያ ሠርቶልን ችግራችን ተወግዷል፡፡” በማለት በውኃ ችግር ምክንያት ያጋጠማቸውን ሁሉ መፍትሔ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የአብነት ትምህርት ቤቱን በማስመልከት 48 ተማሪዎች ተቀብሎ ማስተማር እንደሚያስችልና የግንባታ ወጪውን ገዳሙ በመሸፈን ማኅበረ ቅዱሳን 150 ቆርቆሮ፤ 24 አልጋ፤ 24 ፍራሽ፤ 48 ብርድ ልብስ፤ 48 አንሶላ፤ 48 ትራስ ወጪውን በመቻል ለምረቃ እንደበቃ ገልጸዋል፡፡
በገዳሙ ውስጥ ከሚታዩ ከፍተኛ ችግሮች መካከል አንዱ የምግብ አቅርቦት እጥረት እንደሆነ የገለጹት የገዳሙ አበምኔት ለተማሪዎቹ የተያዘ በጀት ባለመኖሩ ማኅበረ መነኮሳቱ በየቀኑ ከሚሰጣቸው ዳቤ እየቆረሱ በማካፈል ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በገዳሙ ውስጥ 28 መነኮሳይት፤ 41 መነኮሳትና መናንያን ፤48 የአብነት ተማሪዎች እንደሚገኙና የምግብ ፍጆታቸውንም በየዓመቱ መጋቢት 5 ቀን በሚከበረው የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የእረፍታቸው መታሰቢያ በዓል ቀን ለማክበር ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚመጡ ምእመናንና በጎ አድራጊዎች ከሚለግሱት እንደሆነ አበምኔቱ ይናገራሉ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ግዛቸው ሲሳይ ለምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም ማኅበሩ ስላከናወነው ሥራ ባቀረቡት ሪፖርት “የውኃ ታንከር ሥራው በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም. እንዲጠናቀቅ በማድረግ ውኃ መያዝ እንዲችል ተደርጓል፤፤ ግንባታው የተሠራው ከመሬት በላይ ሲሆን 100 ሺህ ሊትር ውኃ የመያዝ አቅም አለው፡፡ በገዳሙ አካባቢ ምንም የገጸ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር ውኃ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከዝናብ የሚገኘውን ውኃ ከጣሪያ ላይ በመሰብሰብ /Roof Catchment/ ዘዴ በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በመሠራቱ ምክንያት ቢያንስ ለ50 መነኮሳት ለእያንዳንዳቸው በቀን እስከ 7 ሊትር ውኃ ዓመቱን ሙሉ እንዲያገኙ ያስችላል፡፡” በማለት ያብራሩ ሲሆን በውኃ እጦት ምክንያት ይሰደዱ የነበሩት መነኮሳትና መናንያን ቁጥር እንደሚቀንስና ወደ ገዳሙ የሚመጡ መናንያን ቁጥርም ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ለውኃ ፕሮጀክቱም 493፣459.25 ብር እንደሚያስፈልገው በእቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም በ409፣572 ብር ወጪ ሊጠናቀቅ መቻሉንና ወጪውንም ከተለያዩ በጎ አድራጊ ምእመናን ፤ የድሬዳዋ የቀድሞ ተመራቂዎች የቅድስት ድንግል ማርያም ጽዋ ማኅበርና ከባንኮች የሠራተኛ ጉባኤ እንደተገኘ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ፐሮጀክት የአብነት ትምህርት ቤቱ ሲሆን 124፣466.10 ወጪ በማድረግ የቆርቆሮ፤ የአልጋ፤ የፍራሽ፤ የአንሶላና የትራስ ወጪዎችን መሸፈን እንደተቻለ በሪፖርታቸው ያመለከቱ ሲሆን ከፊል ወጪውን በማኅበረ ቅዱሳን የካናዳ ማእከል በኩል እንደተገኘ ማኅበሩ ለአንድ የአብነት መምህር በየወሩ 300 ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ለሁለቱ ፕሮጀክቶች 534፣038.10 ብር ወጪ መሆኑንም በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡
የተጠናቀቁትም ፕሮጀክቶች በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያምና በገዳሙ አበምኔት አባ አብርሃም ወልደ ኢየሱስ መካከል የፕሮጀክት ርክክብ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው ለገዳሙ አበምኔት ለአባ አብርሃም ወልደ ኢየሱስ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያዘጋጀላቸውን ስጦታ ያበረከተ ሲሆን አባ አብርሐምም ለቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍልና ፕሮጀክቱን በተገቢው ሁኔታ በመሥራት ላጠናቀቀው ተቋራጭ ልዩ ስጦታ አበርክተዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ አባላት፤ በጎ አድራጊ ምእመናን የተገኙ ሲሆን በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ትምህርተ ወንጌል፤ በማኅበሩ መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ፤ እንዲሁም የቅኔ ዘረፋ በገዳሙ መምህር ቀርቧል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ፣ ሀድያ፣ ጉራጌና ስልጢ አህጉረ ስብከትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬና ጸሎት ተጠናቋል፡፡