ፊደል፣ ጥንቱ እድገቱና ተግዳሮቱ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀረቡ

ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ጉባኤ ፊደል የተሰኘና በፊደል ላይ ያተኮረ ፊደል፤ ጥንቱ እድገቱና ተግዳሮቱ በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ሰብእ፣ ቋንቋዎች ጥናት፣ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት ኮሌጅ አዘጋጅነት በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች በዘርፉ ምሁራን ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም በእሸቱ ጮሌ ሕንፃ መሰብሰቢያ አዳራሽ ቀርበዋል፡፡

ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተጋበዙ ምሁራን በግእዝ ፊደል ዙሪያ ለበርካታ ዘመናት እንደ ችግር የሚነሡ በተለይም â€Â¹Ã¢€Â¹ሞክሼ ፊደላትâ€ÂºÃ¢€Âº መቀነስ ይገባል፤ አይገባም በሚል ክርክር እያስነሳ ቆይቷል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በመረጃ ላይ የተደገፈ ጥናት ማድረግ እንደሚገባ ምሁራኑ በጥናቶቻቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡ የግእዝ እያንዳንዱ ፊደል የራሱ የሆነ ትርጉም፤ ፊደሉም ሆነ ድምጹ አንዱ ከአንዱ ፊደል እንደሚለይ ነገር ግን አማርኛ የግእዝ ፊደላትን እንዳሉ መቀበሉን በጥናቶቻቸው አመላክተዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው ጉባኤም፡-

ዶ/ር አየለ በከሪ፡- የግእዝ ፊደል አመጣጥ ከታሪክ አኳያ

ዶ/ር ደርብ አዶ፡- የአማርኛ ሞክሼ ፊደላት በፍጥነት መለየት፣ የሥነ አእምሯዊ ሥነ ልሣናዊ ጥናት

ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ፡- አንዳንድ ነጥቦች ስለ መጽሐፈ ፊደል /ወ/ጊዮርጊስ በተባሉ የኢ/ኦ/ተ/ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ በብራና የጻፉት መጽሐፍ ላይ ተመሥርተው ያቀረቡት/

አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ፡- ሄዋን፣ ሔዋን፣ ፊደልና ትርጓሜ /በየኔታ አስረስ የኔሰው ጽሑፍ ላይ ተመስርተው ያቀረቡት/

ፕሮፌሰር ባዬ ይማም፡- ፊደል /ፊደልና ሥርዓተ ጽሕፈት፣ የሥርዓተ ጽሕፈት ዓይነት፣ ሥርዓተ ጽሕፈት ለማን. . /

አቶ ታደሰ እሱባለው፡- ተናባቢና አናባቢ ፊደሎች በእንዚራ ስብሐት መጽሐፍ /አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የጻፉት መጽሐፍ ላይ በመነሣት ያቀረቡት/

ዶ/ር ሙሉ ሰው አስራቴ፡- ለውጥና የለውጥ ሙከራ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ጽሕፈት

መ/ር ካሕሳይ ገ/እግዚአብሔር፡- ሞክሼ ቃላትና ዲቃላ ፊደላት በግእዝና በአማርኛ ቋንቋዎች ያላቸው ጠቀሜታ

ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም፡- የኢትዮጵያ ፊደል ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች

በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ጥናቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በቀረቡት ጥናቶች መሠረት ከታሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች በጥናት አቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም ምሁራን ከጥናቶቹ በመነሣት ሰፊ ግንዛቤ መጨበጣቸውንና በዩኒቨርስቲው ወደፊት ሊሠሩ የሚገባቸውንና በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት በጥናት ላይ የተመረኮዘ ሥራዎችን በማዘጋጀትና በማቅረብ በፊደል ላይ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው ላይ ከአዲስ አበባ የኒቨርስቲ፤ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ፤ ከባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፤ እንዲሁም ከሌሎቹም ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ምሁራን ጥናቶችን በማቅረብ፤ እንዲሁም ሐሳቦችን በማቅረብ ተሳትፈዋል፡፡

ልዩ የምክክር ጉባኤ

ግንቦት 27ቀን 2007ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእክል ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ አባላት ከአባለቱ ጋር ግንቦት 29ቀን 2007ዓ.ም ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ የምክክር ጉባኤ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ማእከል አባላት በምክክር ጉባኤው እንድትገኙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የአዲስ አበባ ማእከል፡፡

የጎንደር ከተማ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

ግንቦት 25ቀን 2007 ዓ.ም

ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ ከጎንደር ማእከል

ከግንቦት 22-23 ቀን 2007 ዓ.ም በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በደብረ ጽጌ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንት ቤተክርስቲያን 3ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድ በጉባኤው ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤት ምክትል ኃላፊ መልአከ በረሃ ገብረ ሥላሴ አድማሱ ናቸው፡፡ በአንድነት መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በአፈጻጸማቸው ከ1-3 ለወጡት ለደብረ ምሕረት አቡን ቤት ቅዳሴ ለገብርኤል ሰንበት ት/ቤት፤ ለልደታ ለማርያም ሰንበት ት/ቤትና ለወልደነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ሰንበት ት/ቤት በቅደም ተከተል ተሸልመዋል፡፡ ልምዳቸውንም አካፍለዋል፡፡ በሰንበት ት/ቤቶች በአገልግሎት ዘመን ቆይታ ያላቸው ወንድሞች የሕይወት ልምዳቸውንና ምክራቸውን ለጉባኤው ተሳታፊዎች አካፍለዋል፡፡

የጎንደር ከተማ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በሥሩ በ፬ት ክፍለ ከተማ የተከፈለ መዋቅር አለው (ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ተብለው የሚጠሩ) በሥራቸው 5 ወይም 6 ሰንበት ት/ቤቶች ይገኛሉ፡፡

በየክፍለ ከተማው የሚገኙ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች መንፈሳዊ ጉባኤ በኅብረት ያካሂዳሉ በየ6 ወሩ ደግሞ በየክፈለ ከተማው ያሉት 24ቱም ሰ/ትቤቶች የጋራ ጉባኤ ያካሂዳሉ፡፡

በ2008 ዓ.ም የአራተኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ የምዕራብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ት/ቤት እንደሆነ በዕለቱ ተገልጿል፡፡

በጉባኤው ከ800 በላይ የሰንበት ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በአንድነት መርሐ ግብሩ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

1. የሰ/ትቤት የአለበት በቁጥር መቀነስ
2. ከሰበካ ጉባኤና ከማኅበረ ካህናት ሰ/ትቤቱ ድጋፍ ያለመኖር
3. የሰንበት ት/ቤት የአዳራሽ እጥረት
4. የሰ/ትቤቶችና የሰበካ ጉባኤያት የፋይናንስ መዋቅር ግንኙነት የተስተካከለ አለመሆን
5. የመምህራን እጥረት
6. የገቢ ምንጭ አለመኖር የተወሰኑት ነበሩ

የሰንበት ተማሪዎች የወደፊቱ የቤተክርስቲያኒቱ ተተኪዎች በመሆናቸው ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ለሰንበት ት/ቤቶች መጠናከር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ƒƒ

የጅማ ማእከል የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አካሄደ

ግንቦት 25 ቀን 2007 ዓ.ም.

ጅማ ማእከል

በማኅበረ ቅዱሳን የጅማ ማእከል ያዘጋጀው ሁለተኛው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በኮሳ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተካሄደ፡፡

የጉዞውን መነሻ በጅማ ሀገረ ስብከት ሁለገብ( አቡነ እስጢፋኖስ) ሕንፃ በማድረግ ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ከ800 በላይ ምእመናንን በማሳተፍ በሊሙ ኮሳ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥር ወደምትገኘው ኮሳ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አድርጓል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ከ2000 በላይ የሚሆኑ የአጥቢያው ምእመናን፣የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ስለሺ አስፋው፣የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህን ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ መሰረት፣ ሌሎች የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎች፣ በጅማ ከተማ የሚገኙ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፣ የአጎራባች ወረዳ ማእከላትና የግንኙነት ጣቢያ አባላት፣ የጅማ ማእከል አባላት፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ ማኅበራት እና በጎ አድራጊ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ክፍል አንድ ትምህርት ወንጌል በመጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግስቱ አማረ፤ የጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ቤተክርስቲያን የ200 መቶ ዓመት ታሪክ በሰበካ ጉባኤ ተወካይ ፡ እንዲሁም የማኀበረ ቅዱሳን የአገልግሎት እንቅስቃሴና መልእክት በአቶ ቡሩክ ወልደ ሚካኤል ቀርበዋል፡፡

ከምእመናን ለቀረቡ ጥያቄዎች ምክረ አበው መርሐ ግብር በሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ እና በመጋቤ ሐዲስ ቀሲስ መንግስቱ አማረ ማብራርያ ተሰጥቷል፡፡በመቀጠል ክፍል ሁለት የወንጌል ትምህርት በሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ተሰጥቷል፡፡

የትምህርት መርሐ ግብሩ እንደተጠናቀቀ ቤተክርስቲያኗን በአዲስ መልክ ለመሥራት የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የተካሄደ ሲሆን ከ130,000(አንድ መቶ ሰላሳ ሺህ )በላይ በጥሬ እና በቁሳቁስ ለማሰባሰብ ተችሏል፡፡

በመጨረሻም የሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ስለሺ ስለነበረው መርሐ ግብር እና አስፈላጊነት ሰፊ ማብራርያና ግንዛቤ ለምዕመናን የሰጡ ሲሆን ይህንን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ያዘጋጀውን የጅማ ማዕከልን አመስግነዋል፡፡በማስከተልም ማኀበረ ቅዱሳን የቤተክርስቲያንን አገልግሎት ለማገዝ እየፈጸመ ያለውን አገልግሎት አድንቀው ምእመናንም ይህንን የማኀበሩን አገልግሎት ከጎን በመሆን ማገዝና መረዳት እንደሚገባ በማስገንዘብ መርሐግብሩ በጸሎት ተዘግቷል፡፡

ከመርሐግብሩ መጠናቀቅ በኃላ የምእመናንን አስተያየት የተሰበሰበ ሲሆን በመርሐግብሩ መደሰታቸውንና ለወደፊቱም እንደዚህ አይነት መርሐግብር በአመት ሁለት እና ሦስት ጊዜ መዘጋጀት እንዳለበት ገልጸው፤ ስለቤተክርስቲያን ወቅታዊ ሁኔታና የማኀበሩን አገልግሎት ለማወቅ እንደረዳቸው ገልጸዋል ፡፡

01desie

የደሴ ማእከል የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ሊያካሂድ ነው

ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም

ከደሴ ማእከል

01desieበማኅበረ ቅዱሳን ደሴ ማእከል የአካባቢውን ማኅበረ ምእመናን በማሳተፍ ወደ ታሪካዊው ደብር ቦሩ ደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ያካሂዳል፡፡

መርሐ ግብሩ የተዘጋጀበት ዓላማ ምእመናን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወታቸውን ለማነጽ፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ መንፈሳዊ ጉዞ ምን መምሰል እንዳለበት ግንዛቤ ለመፍጠር፤ እንዲሁም ወደ ገዳማትና አድባራት በመሄድ በረከት እንዲያገኙ እንደሆነ የማእከሉ ጸሐፊ ዲ/ን ሰሎሞን ወልዴ ገልጸዋል፡፡

በመርሐ ግብሩም የአባቶች ቡራኬ፣ ትምህርተ ወንጌል፣ ያሬዳዊ መዝሙር፣ ምክረ አበው፣ ቅኔ፣ ጉብኝት፣ የፕሮጀክት ምረቃ እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡

የጉዞው መነሻ ቦታ የደሴ ማእከል ጽ/ቤት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ከጠዋቱ 12፡00 ስዓት ሲሆን፤ የጉዞው ሙሉ ወጪ (ቁርስና ምሳን ጨምሮ) 60 ብር እንደሆነ ዲ/ን ሰሎሞን ገልጸዋል፡፡

ምእመናን የጉዞ ትኬቱን በማእከሉ ጽ/ቤት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ፣ በማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ቤት፣ በደብረ ቤቴል ቅድስት ሥላሴና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ቤት (ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር)፣ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ቤትና ተድባበ መዝሙር ቤት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ማግኘት እንደሚችሉ የደሴ ማእከል ጸሐፊ አስታውቀዋል፡፡

ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት የሚያግዝ ስልጠና ተሰጠ

ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከደሴ ማእከል

በማኅበረ ቅዱሳን ደሴ ማእከልና ደሴ ወረዳ ማእከል አስተባባሪነት ከሚያዚያ 18 – 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ከዘጠኝ ወረዳዎች ለተውጣጡ ዐሥራ ስምንት የአብነት መምህራንና ተማሪዎች ለሐዋርያዊ አገልግሎት የሚያበቃ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ለተከታታይ ለሰባት ቀናት በተሰጠው ስልጠናም ትምህርተ ሃይማኖት፤ ሐዋርያዊ ተልእኮ፤ ትምህርተ ኖሎት እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡

በስልጠናው ላይ የተሳተፉት መምህራንና ተማሪዎቹ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን፤ የተሰጣቸው ስልጠና ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት በንቃት እንድንሳተፍ ያደርገናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሥልጠናው ማብቂያ ላይ በማእከሉ የሕክምና ቡድን ለሁሉም ሠልጣኖች የተሟላ የጤና ምርመራ በማድረግ የመድኃኒት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡

ለካህናት የዐቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ

ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከደሴ ማእከል

በደሴ ከተማ ቤተ ክህነት፤ በማኅረ ቅዱሳን ደሴ ማእከልና ደሴ ወረዳ ማእከል አስተባባሪነት ሚያዚያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ደሴ ከተማ ለሚገኙ ከሰባ በላይ ለሚደርሱ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የአንድ ቀን ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናው የተዘጋጀበትን ዓላማ የደሴ ከተማ ቤተ ከህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ቆሞስ አባ ለይኩን ወንድይፍራው ሲገልጹ በከተማው ከዐሥር በላይ አብያተ ክርስቲያናት እና በርካታ ካህናት ስለሚገኙ በዞን ከተማነቱም ለምዕራብ ወሎ እና ለሌሎችም አጎራባች አካባቢዎች መጋቢ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የካህናትን አቅም በሥልጠና ማገዝ እያጋጠሙን ባሉት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ መወያየት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መርሐ ግብሩ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው ሥልጠና ትምህርተ ኖሎት፤ የካህናት ሚና ከቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች እና ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር በሚል ርእስ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ እና ከውስጥ እያገጠሟት ባሉ ፈተናዎች እና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም የካህናት ድርሻ ምን መሆን አለበት በሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በንስሓ ልጆች አያያዝ ዙሪያ እያጋጠሟቸው ስላሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው፣ ዐሥራት አለመክፈል በቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት፣ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ አሁን ያለበት ደረጃ፣ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች እያጋጠማቸው ስላሉ ፈተናዎች እና ሌሎችም ቤተ ክርስቲያንን ከውጭና ከውስጥ እያጋጠሟት ስላሉ ፈተናዎች እና መፍትሔዎቻቸው በማንሳት የጉባኤው ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

ለአብነት ተማሪዎች የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ

ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከደሴ ማእከል

በማኅበረ ቅዱሳን ደሴ ማእከል የቅዱሳት መካናት ማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል አስተባባሪነት በሰሜን ወሎ ደላንታ እና መሀል ሳይንት ለሚገኙ የአብነት ተማሪዎች የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡

በነዚህ ወረዳዎች ብዛት ያላቸው የአብነት ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ የሆነውን የአልባሳት ችግር ለመቅረፍ ከማእከሉ አባላት፣ ከግቢ ጉባኤያት እና ከምእመናን አልባሳትን በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉን ማእከሉ ገልጿል፡፡

ማእከሉ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ጊዜያዊ እና ቋሚ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ ትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ እና በአልባሳት ከሚደረጉ ድጋፎች በተጨማሪ ለዘጠኝ (9) የአብነት መምህራን ለእያንዳንዳቸው ብር 200.00 ወርሃዊ ድጎማ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለአንድ የአብነት ት/ቤትም ቋሚ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ቀርጾ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ማእከሉ ገልጿል፡፡

 

በሊቢያ ለተሠዉ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የመታሰቢያ ጉባኤ ተካሄደ

ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ(ከጎንደር ማእከል)

በሊቢያ ለተሠዉ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በጎንደር ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ለ3 ቀናት የቆየ የመታሰቢያ ጉባኤ ተካሄደ፡፡

ጉባኤውን ያዘጋጁት የጎንደር ከተማ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ በማኅበረ ቅዱሳን የጎንደር ማእከል እና የጎንደር ከተማ የጥምር መንፈሳዊ ማኅበራት በጋራ በመተባበር ሲሆን፤ ከሚያዚያ 24 – 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉባኤው ተካሂዷል፡፡

ጉባኤው የተጀመረው ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ከ7፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን፤ ለሦሰት ቀናት በቆየው ጉባኤ በሰባኪያነ ወንጌል ትምህርት፤ ሰማዕታቱን የሚዘክሩ መነባንብ፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔ፤ ከምእመናን ለቀረቡ ጥያቄዎች በሊቃውንተ ቤተ ክረስቲያን መልስ፤ መዝሙር በጎንደር ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት እና በተጋባዥ መዘምራን፤ የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በተያያዘ ዜና የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በሊቢያ ለተሠዉት 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የከተማው ምእመናን በተገኙበት ሚያዚያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በርዕሰ አድባራት አደባባይ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎላቸዋል፡፡ በዕለቱም 30 ሻማዎች በርተዋል፡፡

001sinoddd

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

001sinoddd

ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በጸሎት የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲካሔድ ቆይቶ ዛሬ ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ተጠናቅቆ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል፡፡

ከሁለቱ አንዱ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ የሚውለው የርክበ ካህናት ጉባኤ ነው፡፡

በመሆኑም የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሚያዝያ 27 ቀን ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተከፍቶአል፡፡

በመቀጠልም ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባን በጸሎትና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ ሰንብቶአል፡፡ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችንም አስተላልፎአል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለዐራት ቀናት ያህል ባካሄደው ቀኖናዊ ጉባኤ፡-

-ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚጠቅሙትን፣

-ለልማትና ለሰላም የሚበጁትን፣

-ከሀገር ውጭ ለሚገኙና በሀገር ውስጥ ላይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁለንተናዊ ሕይወት መጠበቅ የሚያስችሉትን ርእሰ ጉዳዮች በማንሣት በስፋትና በጥልቀት አይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1.ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጉባኤ መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ የሀገራችን ዕድገትንና የሰላም አስፈላጊነት በስፋት የገለጸ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡

2.ምልአተ ጉባኤው በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ዓመታዊ የሥራ መግለጫ ሪፖርት አዳምጦ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡

3.ምንም ጥፋትና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሽባሪዎች ቡድን በግፍና በሚዘገንን ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉ ተስማምቶ ወስኗል፡፡

4.እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም በሊቢያ የተሠውት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በሊቢያ የተሠውት 21 የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖች በሁሉቱም አብያተ ክርስቲያኖች ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለሆነ፣ የሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡

5.በልዩ ልዩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሀገራቸው ወጥተው በባዕድ ሀገር የሚገኙትንና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከልና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርግ፣ ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንም እርዳታ ሰጪዎችን በማስተባበር ኃላፊነቱን ወስዶ በንቃትና በትጋት እንዲሠራ ጉባኤው ወስኖአል፡፡

6.ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አምስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኗን ቅዱስ ሲኖዶስ አውስቶ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎት እንድትተጋ ጉባኤው መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

7.ኢትዮጵያ ሀገራችን ለብዙ ዘመናት ተጭኖአት ከቆየ የድህነት አረንቋ በተጨማሪ የእርስ በእርስ ግጭት ጥሎባት ባለፈ ጠባሳ ክፉኛ የተጎዳች ብትሆንም በተገኘው ሰላም ምክንያት ባሳለፍናቸው ዓመታት እየታዩ ያሉ የልማትና የዕድገት፣ የእኩልነትና የአንድነት እመርታዎች የሰላምን ጠቃሚነት ከምንም ጊዜ በላይ መገንዘብ የተቻለበት ስለሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም በላይ ሰላሙንና አንድነቱን አጽነቶ በመያዝ ሀገሩን ከአሸባሪዎችና ከጽንፈኞች ጥቃት ነቅቶ እንዲጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል፤

8.ሀገራችን ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የካፒታል እጥረት እንደዚሁም በሀገር ውስጥ ሠርቶ የመበልፀግ ግንዛቤ ማነስ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በማናቸውም መመዘኛ ከሌላው የተሻለች እንደሆነች የታወቀ ስለሆነ፤ ወጣቶች ልጆቻችን ወደ ሰው ሀገር እየኮበለሉ ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ በሀገራቸው ሠርተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ኅብረተሰቡም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በሰፊው እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን አስተላልፏል፤

9.ለሀገራችንና ለሕዝቦቻችን ችግሮች ቁልፍ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ልማትን በማጠናከርና ዕድገትን በማረጋገጥ ድህነትን ማስወገድ ስለሆነ ሕዝባችን ይህን ከልብ ተቀብሎ በየአቅጣጫው የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች በመደገፍ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች እኩል ለማሰለፍ የሚደረገውን ሀገራዊ ርብርቦሽ ለማሳካት በርትቶ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤

10.በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያ ክርስቲያናት በየቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ሁሉ የአረንጓዴ ልማትና የራስ አገዝ ልማት በማካሄድ ልማትን እንዲያፋጥኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፎአል፡፡

11.በውጭ ሀገር ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የእርቀ ሰላም ድርድር ለሀገራችን ልማትና ለሕዝባችን አንድነት የሚሰጠው ጥቅም የማይናቅ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያናችን በር ለሰላምና ለእርቅ ክፍት መሆኑን ምልዓተ ጉባኤው ገልጿል፡፡

12.ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለፁትና በሌሎችም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቆአል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፤

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ