በጅማ ማእከል የጽ/ቤት ግንባታ ለማካሔድ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

የማኅበረ ቅዱሳን በጅማ ማዕከል ለሚያስገነባው ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ የመሠረት ድንጋይ ታህሳስ 24 ቀን 2008 ዓ.ም ተቀመጠ፡፡የጅማ፣ ኢሊባቦር እና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የመሠረት ድንጋዩን ካስቀመጡ በኋላ በሰጡት ትምህርት “€œበመከከላችን መደማመጡ፣ መተባበሩ፣ ሲኖር እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናልና ፤የሀገረ ስብከቱን ሁለገብ ሕንፃ ከእለት ጉርሳችሁ ቀንሳችሁ እንደገነባችሁ ይህንንም ሕንፃ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አድባራት እና መላው ምእመናን ጥረት በማድረግ የቤተ-ክርስቲያኒቷን አገልግሎት እንድታፋጥኑ” በማለት መልእክትና መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

የጅማ ማዕከል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ማሞ መኮንን ባደረጉት ንግግር ቤዝመንቱን ጨምሮ ስድስት ወለል ያለው ሕንፃ እንደሚገነባ ገልጸው፤ “€œሕንፃው ሲጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወንባቸው የአገልግሎት ክፍሎች ፣የስብሰባና የስልጠና ይኖሩታል” ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ማሞ ገለጻ ሕንፃው ከ12 ሺህ በላይ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ከሚማሩበት የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት መገንባቱ ማኅበሩ በከፍተኛ ተቋም ውስጥ የሚማሩ ኦርቶደክሳዊያን ወጣቶች ከዘመናዊ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የቤተክርስቲያናቸውን ትምህርተ ሃይማኖት፣ታሪክ፣ሥርዓትና ትውፊት ተምረው የቤተ-ክርስቲያኒቷ ተረካቢ እንዲሆኑ ለማስቻል ማኅበሩ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚያግዘው አስረድተዋል፡፡
ሕንፃውን ለማጠናቀቅ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ የተናገሩት አቶ ማሞ ለግንባታው መጠናቀቅ መላው የቤተ-ክርስቲያኒቱ አባላት ሁሉ “€œየድርሻችንን እንወጣ”€ በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሕንፃ ግንባታውን ሥራ በገንዘብ ለማገዝ የምትፈልጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለE.0.T.C MAHIBERE KIDUSAN TS/BET BUILIDING. ሒሳብ አካውንት ቁጥር 1000143436989 ብሎ መላክ እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

የጂንካ ማእከል የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት ጉዞ ወደ ስብከት ኬላ አደረገ

ጂንካ ማእከል

በጂንካ ማእከል በማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል የመጀመሪያውን የሐዊረ ሕይወት ጉዞውን በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት፣ በበና ጸማይ ወረዳ፣ ጫሊ ቅድስት ሥላሴ ስብከት ኬላ ታኅሣሥ 17 ቀን 2008 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ ተካሄደ፡፡በጉዞው ላይ የደቡብ ኦሞ ሀ/ስብከት የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የጂንካ ከተማ ገዳም፣ አስተዳደርና የአቢያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ የመጡ ተጋባዥ እንግዶች፣ ሰባኬ ወንጌልና ዘማሪያን በአጠቃላይ 1000 ምእመናን ተሳትፈዋል፡፡

ጉዞው ቤተ ክርስቲያን ባልታነፀበት የስብከት ኬላ እና ሁልጊዜም “አጥምቁን እና ቤተ ክርስቲያን ሥሩልን” ወደሚሉት አርብቶ አደር ወገኖቻችን ጋር መደረጉ ከሌሎች ማእከላት ልዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

ጉዞው ታኅሣሥ 17 ቀን 2008 ዓ.ም ጠዋት 12፡30 ላይ በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በተገኙበት በአንቀጸ ብፁዓን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አበምኔት ቆሞስ መ/ር አባ ኤፍሬም ፈቃዴ በጸሎት የተከፈተ ሲሆን በአስተባባሪዎች አማካኝነት ሁሉም ምእመናን ወደተዘጋጀላቸው መኪና ከገቡ በኋላ ጉዞው ተጀመረ፡፡ በጉዞው ላይ በአስተባባሪዎች አማካኝነት በክርስትና ሕይወት ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መዝሙር እየተዘመረ እና ከተጓዦች ጥያቄ እየተሰበሰበ የጉዞው ቦታ ላይ ተደርሷል፡፡ በቦታውም ያሉ አርብቶ አደር ምእመናን “ሁሌም አጥምቁን ቤተ ክርስቲያን ሥሩልን” የሚሉን በርካታ ምእመናን በቋንቋቸው በዝማሬ ተጓዦችን ተቀብለዋል፡፡

የጧዋቱ መርሐ ግብር በካህናት ጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን ትምህርትም በመምህራን ወንጌል ተሰጥቷል ፡፡ከሰዓት በኋላ ከጂንካ አጥቢያ በተገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቆሞስ መ/ር አባ ኤፍሬም ፈቃዴ የአንቀጸ ብፁዓን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አበምኔት ከሕዝብ የተነሳውን ጥያቄዎችን፣ ሊቀ ብርሃናት ኤልያስ ዘውዴ በቤተ ክርስቲያን የምእመናን ድርሻ ምንድነው? መሪጌታ ዘመልአክ የበዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የልጆች አስተዳደግ ምን መምሰል አለበት? በሚል ርእስ ለምእመናን በቂ መልስ የሰጡ ሲሆን፣ በጉባኤው ላይ የተገኙት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም ደግሞ ስለ ቅዱስ ጋብቻ እና የንስሐ ሕይወት ዙሪያ ከአባታዊ ምክር ና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ስለ ጫሊ ስብከት ኬላ አመሠራረትና አሁን ስላለው የአገልግሎት እንቅስቃሴ እና ስለ ቀጣዩ ዕቅዳቸው በጥያቄና መልስ የተብራራ ሲሆን፤ ስብከት ኬላውም ጳጉሜ 3 በ1999 ዓ/ም በአቡነ ዕንባቆም እንደተባረከ ተገልጧል፡፡

በመጨረሻም የጂንካ ማዕከል ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጌታቸው አጠቃላይ መልእክት፣ ማሳሰቢያና ለስብከት ኬላው ገቢ በማሰባሰብ እና በጉዞው አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና በማቅረብ በጂንካ ደብረ ቀራኒዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አማካኝነት በጸሎት ተዘግቶ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡ ከተጓዦች መካከል እንግዶች በሰጡት አስተያየት ጉዞው ቢደገምና ሌሎችም እንዲህ ዓይነቱን ዝግጅት ቢካፈሉ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበሩም የአገልግሎት ማኅበር መሆኑን ተገንዝበናል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

alt

የአርባ ምንጭ ማዕከል ሐዊረ ሕይወት አካሄደ

alt

በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አርባ ምንጭ ማዕከል የተዘጋጀው ልዩ መንፈሳዊ የጉዞ መርሐ-ግብር “ሐዊረ ሕይወት” የሕይወት ጉዞ ታህሳስ 24/2008 ዓ/ም ወደ ምዕራብ አባያ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተደረገ፡፡


“በዚህ ዓመት ለ2ኛ ጊዜ የተደረገ የሕይወት ጉዞ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ እና አካባቢዋ የሚኖሩ ከ900 በላይ ማኅበረ ምእመናን ተሳትፈውበታል፡፡ ይህ ታላቅ መንፈሳዊ የሕይወት ጉዞ በወርኃ-ታኅሣሥ ጾመ ነቢያት ወቅት መደረጉ ምእመናን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲበረቱና በገጠር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን ሁለንተናዊ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲደግፉ ለማድረግ ነው” በማለት የጉዞው አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሥራት ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡ alt
መርሐ-ግብሩ በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ተወካይ በጸሎት ተከፍቷል፡፡ በጠዋቱ ምዕራፍ የወንጌል ትምህርትን አስከትሎ ምዕመናን በታላቅ ናፍቆት የሚጠብቁት ምክረ-አበው ክፍል አንድ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድሃኔ ዓለም ጉባኤ ቤት መምህር የሆኑት መምህር በጽሐ ዓለሙ እና ከደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በተጋበዙ መምህር ኃይለማርያም ዘውዱ አማካኝነት ምእመኑ ማብራሪያ በሚሻባቸው ርእሶች ዙሪያ ጥልቅ የነገረ ሃይማኖት ትንተና አድርገዋል፡፡ መምህራኑ በዋናነት ለቅዱሳን፣ ጻድቃን እና ሰማዕታት የምንሰጠው ክብርና አማላጅነታቸውን፤ ስለ ጾም፣ ጸሎትና ስግደት ከቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አንጻር ቅዱሳት መጻህፍትን አጣቅሰው አመስጥረው አስተምረዋል፡፡ በምዕራፍ ሁለት የከሰዓቱ መርሐ-ግብር ደግሞ መምህራኑ በወቅታዊ የቤተክርስቲያን ፈተናዎች፣ የተሐድሶ አራማጆች ግራ በሚያጋቧቸው የኑፋቄ አስተምህሮዎች ዙሪያ፣ የጸበል ሥርዓትን በተመለከተ እና በጋብቻ ላይ ለምእመኑ የሕይወት ስንቅ ይሆን ዘንድ በስፋት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ሥርዓት መክረዋል፤ አስተምረዋል፡፡alt በሌላ መልኩ የአርባ ምንጭ ማዕከል የበገና ተማሪዎች ነፍስን በሚያለመልም ዝማሬ እግዚአብሔርን ያመሰገኑ ሲሆን፤ በ2007 ዓ/ም በጋሞ ጎፋ ሀ/ስብከት፣ በኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነትና በማኅበረ ቅዱሳን ትብብር ተጠምቀው የመንፈስ ቅዱስን ልጅነት ያገኙት የጉኛራና ኮልሜ አዳዲስ ተጠማቂያን በተጋባዥ እንግዳነት መርሐ-ግብሩን ተሳትፈዋል፡፡ እንግዶቹም ከተቋቋመ አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላው የሰንበት ት/ቤት በኮንስኛና በአማርኛ መዝሙር በማቅረብ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ በተያያዢነት ተጓዡ ምዕመን የደብሩን አጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት የመናፍቃን ጫና እና የዐቅም ውስንነት ለመቅረፍ ከ7000 ብር በላይ ሰብስቦ በዕለቱ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም ምእመኑ ይህ መሰሉ የሕይወት ጉዞ በተደጋጋሚ ወደተለያዩ ቅዱሳት መካናት መዘጋጀት እንዳለበትና ምአመኑም በሚችለው ሁሉ ከማኅበሩ ጋር አብሮ ለመሥራት ተነሳሽነቱን አሳይቷል፡፡ በመሆኑም 3ኛው ሐዊረ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በዚሁ ዓመት ወርኃ ሚያዝያ ውስጥ ወደ ዶርዜ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንደሚደረግ የጉዞ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ታህሳስ 25/2008 ዓ/ም

6

የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣቢያ ሐዊረ ሕይወት አካሄደ !

6

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን የሩቅ ምስራቅ ግንኙነት ጣቢያ ከዐስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ወደ አስተማረበት ደቡባዊ ሕንድ ኬረላ ግዛት ከታህሣሥ 17 እስከ 25 ቀን 2008 ዓ.ም የሐዊረ ሕይወት ጉዞ አካሂዷል፡፡

በዚህ መንፈሳዊ ጉዞ በሕንድ የተለያዩ ግዛቶች ከኒው ደሊህ፣ሮርኪ፣ ፐንጃቢ፣ ፑኔ ፣ ሙምባይ ፣አንድራ እና ባንግሎር የሚማሩ እና የሚኖሩ ምእመናን በባቡር ከ 10 እስከ 48 ሰዓት ተጉዘው ተሳታፊ ሆነዋል ፡፡በጉዞው ላይ ኤርትራውያንም ተሳትፈዋል።

የሐዊረ ሕይወት ተሳታፊዎችም ቅዱስ ቶማስ በመጀመርያ መቶ ክፍለ ዘመን የሥራቸዉን አብያተክርስቲያናት የአጽሙ ክፍል ያለበትን ቤተክርስቲያን ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የልብሷ ክፋይ ያለበትን ቤተክርስቲያን ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጽሙ ክፋይ ያለበት ቤተክርስቲያንን ፣ ቅዱሳን አባቶች እና እናቶች የጸለዩባቸዉን ገዳማትና አድባራት፣ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከላትን፣ በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ ሰዎች ማገገሚያ ማዕከልን፣ 200 ዓመት ያስቆጠረዉን ሴሚናሪ(Seminary) መንፈሳዊ ኮሌጅ እና የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክን ƒƒƒ‚በመጎብኘት የበረከቱ ተሳታፊ መሆናቸውን የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣቢያ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}../ruqemeseraqe{/gallery}

በሐዊረ ሕይወት ጉዞም የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የማር ጎርጎርዮስ የተማሪዎች ማኅበር ፕረዘዳንት እና የቦምቤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ አባ ቄርሎስ (His Grace Geevarghese Mar Coorilos Metropolitan of Bombay Diocese and Presedant of Mar Gregorios Orthodox Christian Student Movement) ከመጀመሪያ አንስቶ ጉዞው እንዲሳካ በመጸለይና በሀሳብ በመርዳት በመጨረሻም ሀገረ ስብከታቸው ከሚገኝበት ማራሽትራ ግዛት ከሙምባይ ከተማ ተነስተው 1600 ኪ.ሜ በመጓዝ መንበረ ፕትርክናው ከሚገኝበት ኬረላ ግዛት ኮታይም ከተማ ከታህሣሥ 19 እስከ 22 2008 ዓ.ም ድረስ በቦታው በመገኘት ለጉዞው መሳካት ሁኔታዎችን በማመቻቸት እና ከተጓዦች ጋር በየዕለቱ በመገኘት በአባታዊ ምክር እንዲሁም ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት እና የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተሐድሶ መናፍቃን ስለደረሰባት ከፍተኛ ፈተና ገላጻ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በጉባኤው ላይ መዝሙር እና ወረብ በየአብያተክርስቲያናቱ ገዳማት እና መንፈሳው ኮሌጆችተማሪዎች የቀረበ ሲሆን የተጓዦችን ሕይወት የሚያንጹ ትምህርቶች በተለይም ስለመንፈሳዊነት እና ወጣትነት ውይይት ስለቤተክርስቲያን ወቅታዊ ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ገለጻና ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሁለቱ አብያተክርስቲያናት የወጣት ተማሪዎች ኅብረትን ለማጠናከር ሲባል በሊቀ ጳጳስ አባ ቄርሎስ በተደረገ ግብዣ ከታህሣሥ 15 እስከ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ከማኅበረ ቅዱሳን የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣቢያ የተወከሉ አባላት በ107 ኛው የማር ጎርጎርዮስ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ወጣቶች ሀገር አቀፍ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በመጨረሻም የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ባስልዮስ ማርቶማ ጳዉሎስ ዳግማዊ (Baselios Marthoma Paulose II Catholicos of the East and Malankara Metropolitan Malankara Orthodox Syrian Church) ለተጓዦች ባደረጉት ግብዣ በመንበረ ፓትርያርክ በመገኘት ለቅዱስነታቸው የኢትዮጵያዊዉን የዜማ ሊቅ የቅዱስ ያሬድ ሥዕል እና ታሪኩን የያዘ ጥራዝ የተበረከተላቸው ሲሆን ተሳታፊዎች በቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርጎ ስለሕንድ ቤተክርስቲያን ሰፊ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን ቅዱስነታቸውም ስለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እና ስለ ሕንድ ቤተክርስቲያን ገለጻ በማድረግ ለተጓዦች ጸሎትና ቡራኬ በመስጠት የዕለቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡ በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ተሳታፊዎችወደ መጡበት ቦታ ከታህሳስ 23 እስከ ታህሳስ 25 2008 ዓ.ምባሉት ጊዚያት በመኪና፣በባቡር እና በአውሮፕላን በመጓዝ በሠላም ተመልሰዋል፡፡

ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መድረስ እንደሚገባ ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ

የልደት ክርስቶስ በዓል የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነፃነትና የእኩልነት በዓል ሊሆን እንደሚገባ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ታኅሣሥ 26 ቀን 2008 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡

ማንም ይሁን ማን፣ በየትኛውም ደረጃ ወይም አካባቢ ይኑር፣ ከሰላም ወጭ ጥቅሙን ማረጋገጥ የሚችል የለም፤ ሊኖርም አይችልም፤ በሰላም ውስጥ ሆኖ ግን ሁሉንም ማግኘት እንደሚቻል ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት አየታየው ውጤት ምስክር ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችንም ሆነ አገራችን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዋች በቀላሉ ማምለጥ የሚቻለው ከሁሉ በፊት ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ይዘው ሲጓዙ እንደሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ ገልፀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተመልሶ ሰውን ከሞት ያዳነው ማንንም ሳይጎዳ በሰላም ጎዳና ብቻ ተጉዞ ነው፡፡ ጥላቻና ራስ ወዳድነት ሲያፈርሱ ሲያጠፉ እንጅ ሲያለሙ እና ሲገነቡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ታይተውም፤ ተስምተውም፣ በታሪክ ሲደገፍም አይተን አናውቀም ብለዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በልማትና በዕድገት እየገሠገሰች ያለች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነገ ብሩህ ተስፋ ትሆናለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሀገር ነች፡፡ ይህ ተስፋ እግዚአብሔር ባርኮልን በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም ሳንለያይ መላ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን ያስገኘነው የልማት ፍሬ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡ የተገኘው የልማት ፍሬ እየበረከተና እየደለበ ወደፊት እንዲቀጥልና እንዲያድግ እንጂ በማናቸውም ምክንያት ወደ ኋላ እንዲመለስና ህዝባችን መፍቀድ እንደሌለበት አያይዘው አስገንዝበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መላው ህዝባችን በሚገባ ማጤን ያለበት ነገር ቢኖር ምንጊዜም የችግር መፍትሔ ሰላምና ልማት እንጅ ሌላ አማራጭ መፍትሔ የሌለ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም የአገራችን ህዝቦች የገናን የሰላም መዝሙር እየዘመሩ ለጋራ ዕድገትና ለእኩልነት፤ ለህዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ልማት በፅናት መቆም እንደሚገባ ገለጡ፡፡
በመጨረሻም በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት ለምግብ እጦት የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችን የወገንን እጅ በተስፋ እየጠበቁ ይገኛሉ፤ እነዚህ ወገኖች ግማሽ አካላችን መሆናቸውን ተገንዝበንና ጌታችን እኛን ለመፈለግ ወዳለበት የመጣበትን ፍቅር አብነት አድርገን፤ እኛም ወዳለበት በፍቅር በመሔድ በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና አለን ከጎናችሁ ልንላቸው ይገባናል፡፡ አነሰ ሳንል በወቅቱ ፈጥነን እጃችንን ልንዘርጋላቸውና በአጠገባቸው ሆነን ልናበረታታቸው ይገባል፤ እግዚአብሔር ሁላችንን እንደወደደን እኛም ወንድሞቻችንን በመመገብ፤ በማልበስና ችግራቸውን ሁሉ በመጋራት ለእግዚአብሔርና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ዛሬውኑ በተግባር እንድናሳይ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመስቀል ኃይልና ቅርጾች በሚል ርዕስ የነገረ ቤተክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ሊካሔድ ነው

ጥናታዊ ጽሑፉ የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 16 ቀን 2008 ዓ.ም አዲስ አበባ አምስት ኪሎ ቅድስተ ማርያም አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው አዳራሽ ይካሔዳል፡፡

“የመስቀሉ ኃይልና ቅርጾች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የነገረ ቤተ ክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ላይም ቁጥራቸው ከ350-400 የሚደርሱ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ ሲጠበቅ፤ በጉባኤው ላይም ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ ክህነት የመመሪያ ሓላፊዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሑራን እና ከሌሎች ማኅበራት የተወጣጡ በርካታ ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

በጉባኤው ላይ በሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍም የመስቀል ኃይልና ቅርጾችን በተመለከተ ግንዛቤ ከመፍጠርም በተጨማሪ አጠቃላይ ስለ መስቀል ገናናነት በማስረዳት ትውልዱ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በዕለቱ የሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍ ርዕስን አስመልክቶ ውይይት የሚደረግ ሲሆን በጉባኤው ላይ ሁሉም ምዕመናን መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ ታውቋል፡፡

ጉባኤው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡30 ይቆያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የኢቢኤስ የቴሌቪዥን ሥርጭርቱ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ገለጸ

ኅዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም

ዝግጅቱን በኦን ላይን፣ በስልክ እና በአሜሪካ የማኅበረሰብ ቴሌቪዥኖች ማሠራጨቱን ይቀጥላል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት /EBS/ አማካይነት የሚያቀርበው ሳምንታዊ የአንድ ሰዓት መንፈሳዊ የቴሌቪዥን አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የተቋረጠበትም ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጠቀሰው ማሠራጫ ጣቢያ አማካይነት በቤተ ክርስቲያኗ ስም ትምህርት የሚያስተላልፉትን አካላት ማንነትና ዓላማ አጣርቶ መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጥ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የሚሠራጩ መርሐ ግብራት እንዲቆሙ በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ታቅፎ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ያለ በመሆኑ የተጻፈው ደብዳቤ ይመለከተዋል ብሎ ባያምንም፤ አባቶች በጣቢያው አማካይነት የሚተላለፉትን መርሐ ግብራት ይዘትና ዓላማ በአግባቡ አጣርተው መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጡ ሥርጭቱን ማቆሙን መርጧል፡፡

በአስቸኳይ አገልግሎቱን ለመጀመር በሚችልበት ሁኔታም ከቤተ ክርስቲያኗ የበላይ አካላት ጋር እየተወያየ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በሀገር ውስጥና በተለይ በአረብ ሀገራት መርሐ ግብሩን በቀጥታ በኢቢኤስ ማሠራጫ ጣቢያ ሲከታተሉ የነበሩ ምእምናን በትእግስት እንዲጠብቁ ጠይቆ፤ የቴሌቪዥን ሥርጭቱ እስከሚጀምር ድረስ http://onlinetv.eotc.tv/ በስልክ አሜሪካ ለሚገኙ ምእመናን በ605-475-81-72፣ ካናዳ (604)-670-96-98፣ አውሮፓ (ጀርመን 0699-432-98-11፣ እንግሊዝ(ዩኬ) 033-0332-63-60 መከታተል እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

እኛም ሁኔታውን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊጀምር ነው

ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ከኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንደሚጀምር የኅትመትና ኤልክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ም/ክትል ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ ገለጹ፡፡

በNilesat, OBS /Oromiya broadcast Service/ ለሠላሳ ደቂቃ ዘወትር እሑድ ከረፋዱ 4፡30-5፡00 ሰዓት እንዲሁም በድጋሚ ረቡዕ ከጠዋቱ 12፡30-1፡00 ሰዓት የሚሠራጨው መርሐ ግብር የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊትን ጠብቆ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ እምነታቸው እንዲያውቁ እና ጸንተው እንዲኖሩ፣ እንዲሁም ከእምነታቸው ለወጡ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ታስቦ መጀመሩን ምክትል ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሞ ማኅበረሰብን ከቤተ ክርስቲያን ለመነጠል በርካታ መጻሕፍት ታትመው እየወጡ በመሆናቸው የማኅበረ ቅዱሳን የአፋን አሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ይህንን ለመከላከል ምእመናን ለማስተማር፣ እምነታቸውን ጠብቀው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ ፕሮጀክቱ መቀረጹንም ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ ምእመናንን የሚያንጹ በርካታ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን፣ የጸሎት መጻሕፍትንና መጽሔት በማሳተም፣ በኦሮምኛ ድረ ገጽ ጭምር ሲያሠራጭ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡም Dangaa Lubbuu/ የነፍስ ምግብ/ የተሰኘ መጽሔት በማሳተም ለምእመናን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡

በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚተላለፉ መርሐ ግብሮችን በካናዳ ለማዳረስ በስልክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋፋት የሚያስተላልፋቸውን ዝግጅቶች በስልክ አማካይነት በካናዳ ለሚገኙ ምእመናን ማሠራጨት ጀመረ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ምእመናን ስለእምነታቸውና ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲያውቁ፣ በሃይማኖት እንዲጸኑ መረጃ በመስጠትና በማስተማር ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚያሰራጫቸውን መርሐ ግብሮች በሰሜን አሜሪካ፣ በጀርመን እና በእንግሊዝ /UK/ በስልክ አማካይነት በማዳረስ ላይ ነው፡፡

ማኅበሩ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ብቻ ሳይወሰን ቁጥሩን ወደ ዐራት በማሳደግ በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚተላለፉት ዝግጅቶችን በቅርቡ በስልክ አማካይነት በካናዳ ማሠራጨቱን ቀጥሏል፡፡

በካናዳ የሚገኙ ምእመናን የስልክ አገልግሎቱን (604) 670 9698 በመደወል በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉም መረጃው ያመለክታል፡፡

sami.02.07

የጥቅምት 2008 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸሎት ተጀመረ

ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም

sami.02.07በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት ተጀመረ፡፡

ምልዓተ ጉባኤው አስፈላጊና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡