ምሩቃኑ ስለ መልካም አስተዳደር እንዲያስተምሩ ፓትርያርኩ መመሪያ ሰጡ፡፡

ሰኔ ፳፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስቱም መንፈሳውያን ኮሌጆች የዘር ወቅት በኾነው በወርኃ ሰኔ ደቀ መዛሙርታቸውን አስመርቀዋል፡፡

ከእነዚህ ኮሌጆች አንዱ በኾነው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በልዩ ልዩ ትምህርት ክፍሎችና መርሐ ግብራት ሲማሩ የቆዩ ደቀ መዛሙርት ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የተመረቁ ሲኾን፣ የምረቃ ሥርዓቱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየመምሪያ ሓላፊዎች፣ የክፍለ ከተሞች ወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የኮሌጁ ሥራ አመራር አባላትና የምሩቃን ቤተሰቦች በተገኙበት በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ተከናውኗል፡፡

የኮሌጁ አካዳሚክ ምክትል ዲን መምህር ግርማ ባቱ እንዳስታወቁት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በካህናት ማሠልጠኛነት ከተፈተበት ከ፲፱፻፴፮ ዓ.ም ጀምሮ በነገረ ሃይማኖት ትምህርት በርካታ መምህራንን እያፈራ የሚገኝ ሲኾን፣ ለወደፊቱም በሦስተኛ ዲግሪና በዶክሬት መርሐ ግብር ለማስተማር ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ከ፲፰፻ (አንድ ሺሕ ስምንት መቶ) በላይ ደቀ መዛሙርትን እያስተማረ የሚገኘው ኮሌጁ በዘንድሮው የምረቃ ሥርዓቱ የግእዝ ቋንቋን ጨምሮ በልዩ ልዩ የትምህርት ክፍሎችና መርሐ ግብራት በድምሩ ፫፳፬ ዕጩ መምህራንን አስመርቋል፡፡

የምረቃ ሥርዓቱ በጸሎተ ወንጌል ከተከፈተ በኋላ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰ/ት/ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬ የቀረበ ሲኾን፣ ምሩቃኑም ልዩ ልዩ መልእክት ያዘሉ ቅኔያትን አበርክተዋል፡፡ በመቀጠልም ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፤ እንደዚሁም ከኹሉም መርሐ ግብራትና ትምህርት ክፍሎች ተመዝነው ከ፩ኛ እስከ ፭ኛ ደረጃ ያገኙ ሴት ምሩቃን ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ከብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ እጅ የምስክር ወረቀትና ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በዕለቱ *መከሩስ ብዙ ነው፤ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ ለምኑት፤* /ማቴ.፱፥፴፯-፴፰/ የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ቃለ ምዕዳን በሰጡበት ወቅት *እኛ መክረን አስተምረን ዐሥራት በኵራት እንዲከፍሉ ባናደርጋቸውም ምእመናን ልጆቻችን ያላቸውን ከመስጠት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በመኾኑም በቤተ ክርስቲያናችን በተለይ በዐበይት ከተሞች የገንዘብ እጥረት የለም፤ ነገር ግን ገንዘብ አያያዛችን በደንብ ያልተደራጀ ስለኾነና ሙስና ስለበዛ በአግባቡ አገልግሎት ላይ እየዋለ አይደለም፡፡ ስለዚህም በምትሰማሩበት ቦታ ኹሉ ሙስና እንዲጠፋ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሐቀኞች እንድንኾን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ንጽሕናና ቅድስና እንዲጠበቅ ልታስተምሩ ይገባል* በማለት ለምሩቃኑ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

*በሦስቱም ኮሌጆቻችን የምትመረቁ ልጆቻችን የቤተ ክርስቲያናችን ብርሃን ናችሁ!* በማለት ምሩቃኑን ያወደሱት ቅዱስነታቸው ስብከተ ወንጌል ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ተግባር መኾኑን ገልጸው *እናንተ ብርሃን ኾናችሁ ጨለማውን ዓለም እንድታበሩ፤ ወደ ሌላ ሃይማኖት የገቡትን አስተምራችሁ እንድትመልሱ፤ እምነታችሁን አጥብቃችሁ ሌሎችንም እንድታጠነክሩ፤ በየቦታው በመናፍቃን የተዘረፉ ምእመናንም እንድታስመልሱና ከዘረፋ እንድትታደጉ፤ ሕይወቱንና ጤንነቱን ይጠብቅ ዘንድ፤ ከሱስ፣ ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከስካርና ከመሳሰሉት እኩያን ምግባራት ይርቅ ዘንድ ወጣቱን እንድታስተምሩ ቤተ ክርስቲያናችን አደራዋን ታስላልፋለች* ብለዋል፡፡

ምሩቃኑም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውን፤ ሐዋርያት ያስተማሩትን ሕገ ወንጌል እንደዚሁም በሦስቱ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤያት የተወሰኑ ቀኖናዎችን እንደሚጠብቁና እንደሚያስጠብቁ፤ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን፣ የመላእክትንና የቅዱሳንን አማላጅነት እንደሚያስተምሩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቷን፣ ቀኖናዋን፣ እምነቷን፣ አስተምህሮዋንና ዶግማዋን እንደሚፈጽሙና እንደሚያስፈጽሙ፤ በተመደቡበት ቦታ ኹሉ በታማኝነት እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል፡፡

በመጨረሻም በቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ቡራኬ የምረቃው ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የከሣቴ ብርሃን ፍሬምናጦስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በልዩ ልዩ ትምህርት ክፍሎችና መርሐ ግብራት ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ማስመረቁ ይታወሳል፡፡