በሕይወት ሳልለው
«መፃጒዕ» ለ፴፰ ዓመት የአልጋ ቁራኛ የነበረና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሰንበት የፈወሰው ሰው ነው፡፡ ጌታችንም ያን ሰው በአልጋ ተኝቶ ባየው ጊዜ መዳን እንደሚፈልግ አውቆ ጠየቀው፤ «ልትድን ትወዳለህን?» መፃጒዕም «አዎን ጌታዬ ሆይ፤ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፤ አለው»፤ ጌታም «ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ባለው ጊዜ፤ ወዲያውኑም ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፤ዮሐ.፭፥፮-፱
በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁድ ግን ጌታችን ያደረገለትን ተአምር ባለማመን፤ በሰንበት ቀን አልጋ ተሸክሞ መሄድ ዕለቱን ማርከስ እንደሆነ መፃጒዕን ለማሳመን ሞከሩ፤ ዕለተ ሰንበት ከዐሥርቱ ትእዛዛት አራተኛው «የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ፤»ይላልና ዘፀአት ፳፥፰-፲፡፡
እርሱ ግን ለ፴፰ ዓመት ከአልጋ ላይ መነሳት እንኳን ባልቻለበት ሁኔታ ያ ያዳነው ሰው አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ ባዘዘው ጊዜ ያለ ምንም ጥርጣሬ፤ በእምነት ተፈውሶና ተነሥቶ መሸከም እንደቻለ ነገራቸው፡፡ እነርሱም በመጓጓት ያዳነውን ሰው ማንነት ቢጠይቁትም ሊነግራቸው አልቻለም ፤ጌታችን ከእነርሱ ተሰውሮባቸው ነበርና፡፡
በዚህች የተቀደሰች ሰንበት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎች ድውያንን እየፈወሰ፤ ጎባጣዎችን እያቀና ፣ ዕውራንን እያበራ፣ አንካሶችን እያዳነ፤ ለምፃሞችንም በመለኮታዊ ኃይሉ እያነጻ፤ልምሾዎችን እያዳነና አጋንንትን እያወጣ የዋለበት ዕለትም ነበር።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምስት ገበያ ሕዝብ ይከተለው እንደ ነበር በቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ተገልጾም እናገኛለን፡፡ «አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና ለደቀ መዛሙርቱ በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው፤» (ሉቃ.፱፤፲፬) እንዲል፡፡ ሕዝቡም ጌታችንን የተከተሉበት የተለያየ ዓላማና ምክንያት ነበራቸው፡፡ በትምህርቱ ተማርከው፣ ተአምራቱን ሰምተው፣ ከተያዙበት የአጋንንት ቁራኝነት ለመፈወስ፣ ረሀባቸውንና ጥማቸውን ለማስታገስ፣ መልኩን ለማየት፣ ጎዶሏቸውን ይሞላላቸው ዘንድ ይከተሉት ነበር፤እንደ መሻታቸውም ተፈጽሞላቸዋል፡፡
በዕለተ ሰንበትም ቤተ ክርስቲያን መሄድ ተገቢ ስለሆነ መፃጒዕ ከበሽታው በመዳኑና መራመድ በመቻሉ ወደዚያው አቀና፡፡ ጌታችንንም በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያስተምር አገኘው፤ ጌታም እንዲህ አለው «እነሆ ድነሃል፤ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ተጠንቀቅ»፤ዮሐ.፭፥፲፬፡፡ እርሱም የተባለውን በፀጋ ሰምቶ አይሁድ ካሉበት ስፍራ ሔደ፤ ባገኛቸውም ጊዜ ያዳነው ሰው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ነገራቸው፡፡
አይሁድ ግን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በምቀኝነት ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ አንዱ ክሳቸው ሰንበትን ይሽራል የሚልም ስለነበር መፃጒዕ “በሰንበት የፈወሰኝ እሱ ነው” በማለት ቢመስክርም ለ፴፰ ዓመት ከተያዘበት ሥቃይ የገላገለውን አምላኩን በመካድ በጥፊ እስከ መምታት ደረሰ፡፡
ጻድቁ ኢዮብ «መንገዴን ፈጽሞ ዐወቀ፣ እንደ ወርቅም ፈተነኝ፣ እንደ ትእዛዙ እወጣለሁ፣ መንገዱንም ጠብቄያለሁ፣ ፈቀቅም አላልሁም» በማለት በመከራው ዘመን ለአምላኩ የነበረውን ፍጹም እምነት መሰክሯል፤ ኢዮ.፳፫፣፲፩፡፡
አምላካችን ያደረገለትን ድኅነትና ተአምር ምስክር መሆኑ ተገቢ ቢሆንም፤መፃጒዕ ግን ምላሹን በክሕደት ገለጸ፡፡ ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፭፥፴፪ ላይ «ነገር ግን ለእኔ የሚመሰክር ሌላ ነው፤ ስለ እኔ የሚመሰክረው ምስክርነቱ እውነት እንደሆነ አውቃለሁ»፤ብሏል፡፡
ምርጥ ዕቃ የተሰኘው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስንም ከክሕደት፣ አምላኩንም ከማሳደድ መልሶ የወንጌል ገበሬ ስላደረገው «የጽደቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» እንዲል (፪ኛ ጢሞ.፬፤፰)፤ እስከ ሞት ድረስ ታመነ፤ አንገቱንም ለሰይፍ አሳልፎ እስከ መስጠት አደረሰው፡፡ መፃጒዕ ግን ለክሕደት ራሱን አሳልፎ ሰጠ፣ ክሕደቱንም በጥፊ በመማታት ገለጸ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ሁሉንም በሥርዓት የምታከናውን ስንዱ እመቤት ናትና በዐቢይ ጾም ከሚገኙት ሰንበታት ውስጥ ዐራተኛውን ሳምንት መፃጒዕ ብላ ሰይማዋለች፡፡ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብንወድቅ እንደሚያነሣን፣ ብንታመም እንደሚፈውሰን ለማስተማር እንዲሁም ደግሞ ከመፃጒዕ ሕይወት እንማር ዘንድ መታሰቢያውን አደረገች፡፡
«ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ» ዮሐ.፭፤፲፬፤ እንዳለ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ እንሸጋገር ዘንድ፣ የአምላካችንን ቃል መፈጸም እንደሚገባን፣ እሰከ ሞትም መታመን እንዳለብን ያስተምረናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅፍርናሆም በገባ ጊዜ አንድ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ መጥቶ «አቤቱ ልጄ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተጨነቀ በቤት ተኝቷል፤» ብሎ ለመነው፤ ጌታችንም «እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ» አለው፡፡ የመቶ አለቃውም «አቤቱ አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፡፡ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ ልጄም ይድናል»፤ አለ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መቶ አለቃውን እጅግ አደነቀ፤ «እውነት እላችኋለሁ፣ በእስራኤል ሁሉ እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም» ብሎ መሰከረለት፤ በመቶ አለቃውም እምነት ተደነቀ፡፡ «እንደ እምነትህ ይሁን» አለው፤ ከዚያም ሰዓት ጀምሮ ልጁ ዳነ፤ ማቴ.፰፤፭-፲፫፡፡
ይህ በእምነት ጽናት የተገለጸ ሕይወት ነው፡፡ መፃጒዕ ግን ያዳነውን አምላኩን በዓይኑ አይቶ፣ በእጁ ዳስሶ፣ ለ፴፰ ዓመታት የተኛበትንና የተሸከመውን አልጋ እንደገና እሱ ተሸክሞት እንዲሄድ ዕድሉን የሰጠውን አምላኩን ካደ፡፡ በእምነት የጸኑ፣ እንደ ቃሉም የተጓዙ፣ እስከ ሞትም የታመኑት ሲድኑ «ኑ የአባቴ ቡሩካን» ሲባሉ፤ በክህደት ያጠናቀቁትን ደግሞ «አላውቃችሁም» ተብለው ጥርስ ማፋጨት፣ እሳቱ ማያንቀላፋበት ጥልቅ እንዲወረወሩ ሁሉ፤ መፃጒዕ ዕድሉን አበላሸ፡፡ ጽድቅ በፊቱ ቀርቦለት መርገምን መረጠ፣ ከዘለዓለማዊ ሕይወት ይልቅ ዘለዓለማዊ ሞትን ምርጫው አደረገ፡፡
ምርጫችን የቱ ይሆን? በዐቢይ ጾም ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ሰንበታቱን ስያሜ ሰጥታ ስናከብር እንማርባቸው ዘንድ ነው፡፡ ጽድቅን በመሻት ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንድናደርግ፣ መንገዱንም እንከተል ዘንድ ነው፤ «ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው»፤ መዝ.፻፲፰፤፻፭ ላይ ተብሎ እንደተጻፈው፡፡
የክርስትና ሕይወት ፈተና የተሞላባት ናትና፤ በኑራችን ውስጥ የሚገጥመንን መሳናክልና ውጣ ውረድ ለመቋቋም ሁሌም በእምነትና በሃይማኖት መኖር ብቸኛ መፈትሔ ነው፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ ሳምንት ተአምራትን ከማድረጉ በላይ ለሕይወታችን ስንቅ የሚሆነን የወንጌል ቃል አስተምሮበታል፡፡ «ቃሉም የላችሁም፤በእናንተ ዘንድም አይኖርም፤እርሱ የላከውን አላመናችሁምና፤ መጻሕፍትን መርምሩ፤ በእነርሱም የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ ይመስላችኋልና፤እነርሱም የእኔ ምስክር ናቸው»፤ ብሏል፤የሐ.፭፥፴፰፥፴፱፡፡
“እግዚአብሔርን የሚፈልግ ልብ ደስ ይበለው” እንደተባለው አምላካችን የጎደለንን እንዲሞላልን በጾም፣ በጸሎት፣ በፍጹም ትሕትና እና እምነት ልንተጋ ያስፈልጋል፤ መዝ.፻፭፣፫፤ ፩ኛ ዜና.፲፮፤፲፡፡ «ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ»፤ እንደተባለውም መፃጒዕ የአምላካችንን ቃል ዘንግተን፣ የተደረገልንን መልካም ነገር ሁሉ በክፉ እንዳንለውጥ መጠንቀቅ ከእኛ ኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡ የአምላካችንን ቃል በሕይወታችን ዘመን ሁሉ በመፈጸም፣ እስከ መጨረሻው እንድንጸና አምላካችን ይርዳን፤ አሜን!