‹‹በበለስ ዛፍ ሥር አየሁህ›› (ዮሐ.፩፥፶፩)

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

ናትናኤል የተባለው እስራኤላዊ በቤተ ሳይዳ ሲኖር የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በጎ ሰው ስለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያነግረናል፡፡ ይህም እንዲህ ነበር፤ በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን  ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ በወደደ ጊዜ ፊልጶስ የተባለውን ሰው አገኘውና ‹‹ተከተለኝ›› አለው፡፡ ፊልጶስም ሀገሩ ቤተ ሳይዳ ስለነበረ ጌታ ተከተለኝ ባለው ጊዜ ብቻውን አልተከተለውም፡፡ ናትናኤል የሚባለው ወዳጁን ሙሴ በኦሪት ነቢያት በትንቢት ስለ እርሱ ያስተማሩለትን መሲሕ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ስላገኘው ወደ እርሱ አብሮት እንዲሄድ ነገረው፡፡ ናትናኤልም ‹‹በውኑ ከናዝሬት ደግ ሰው ሊወጣ ይችላልን?›› ሲል ጠየቀው፡፡ ፊልጶስም ‹‹መጥተህ እይ›› አለው፡፡ ከዚያም ጌታችን ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ ስለአወቀው ‹‹እነሆ፥ በልቡ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ እስራኤላዊ ይህ ነው›› አለ፡፡ ናትናኤልም ‹‹በየት ታውቀኛለህ?›› አለው፡፡ ጌታችንም መልሶ ‹‹ገና ፊልጶስ ሳይጠራህ በበለስ ዛፍ ሥር ሳለህ አይቼሃለሁ›› አለው፡፡ ናትናኤልም መልሶ ‹‹መምህር ሆይ፥ በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ የእስራኤል ንጉሥ አንተ ነህ›› አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ ‹‹በበለስ ሥር አየሁህ ስላልኩህ አመንህን? ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ›› ካለ በኋላ በዚያ ለተሰበሰቡትም ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰማያት ሲከፈቱ፥ የእግዚአብሔርም መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ›› አላቸው፡፡

ጌታችን ናትናኤልን ሐዋርያ እንዲሆን መረጠው፤ ቅዱስ ስምዖን ተባለ፤ ይህም ሐዋርያ ያዕቆብ በአይሁድ ተገሎ ሲሞት ለኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ሆነ፤ በኋላም ወንጌልን በማስተማር ከአይሁድን ብዙዎችን ክርስትናን እንዲቀበሉ ከማድረጉ ባሻገር በሽተኞችንም አድኗል፡፡ በመጨረሻ በሰማዕትነት ባረፈበት ዕለት ጌታችን ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ሰማይ ሲከፈቱ፥ የእግዚአብሔርም መላእክት ወደ ሰው ልጅ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ›› ብሎ እንደተናገረው ሐምሌ ፲ ቀን ቅዱሳን መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ፣ ሰማይ ተከፍቶ ተመልክቷል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረትም ይህን ዕለት ናትናኤል የተባለውን የቅዱስ ስምዖንን በዓል እናከብራለን፡፡ (ዮሐ. ፩፥፵፬-፶፪፣ ስንክሳር ዘወርኃ ሐምሌ ፲)

የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ በብዙ ነገር ይገለጻል፤ ፊልጶስ ናትናኤልን ወደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወስደው ፈጣሪውን ሥራውን አይቶ እንዲያምን ነበር፡፡ ያን ጊዜም በአንድ ጊዜ ሦስት ምስክርነት ሰጠ፡፡ መምህርነቱን፣ የእግዚአብሔር ልጅነቱን፣ የእስራኤል ንጉሥ መሆኑንም መሰከረ፡፡

እኛም ለሰዎች የእግዚአብሔርን ሥራ ሰምተው ያምኑ እንዲሁም ምስክር ይሆኑ ዘንድ ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡ ስለጸበል ፈዋሽነት ከምንነግራቸው በተጨማሪ ‹‹ሂዱና እንጦጦ ጸበልተኞች ሲፈወሱ እዩ፤ ጻድቃኔ ማርያም፣ ሸንኮራ እና ሌሎችም ገዳማትም ያለውን ተአምር ተመልከቱ፤ ራሳችሁ ምስክር ትሆናላችሁና›› እንበላቸው፡፡

በእርግጥ እምነት ጽናትን ይጠይቃልና በአንድ ጀምበር ለድኅነትም ሆነ ምስክርነት መብቃት አይቻልም፡፡ ትላንት ጥሩ ስለነበርን ብቻም ነገ በእግዚአብሔር ታምነናል ማለት አይደለም፡፡  ጽናት፣ ትዕግሥትና እና ብርታት ያስፈልጋል፡፡ ኢየሩሳሌም የዳዊት፣ የንጉሥ ሰሎሞን እና የነቢያት ሁሉ ሀገር ነበረች፡፡ ጌታ የተሰቀለባት፣ የተቀበረባት፣ የተነሣባት፣ ያረገባት ዳግም የሚመጣባትም ጭምር ናት፡፡ ያ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ጠቢቡ ሰሎሞን አርባ ዓመት ሙሉ ቀንና ሌሊት የተጋበት እና ከወርቅ የሠራው ቤተ መቅደስ ያለባት ሀገር ብትሆን እንኳን ሕዝቡ ኃጢአተኛ በመሆኑ ጦርነት ረኃብና ችግር በዝቶባታል፡፡

ድንጋይ መቶ ዓመት ውኃ ውስጥ ቢዘፈዝፉት ውስጡ ውኃ አይገባም፡፡ የአንዳንድ ሰው ልቡና በቅዳሴው፣ በመዝሙሩ፣ በማኅሌቱ፣ በትምህርቱ፣ በተአምራቱ ተከቦ ውስጡ በጭራሽ አይለወጥም፡፡

እግዚአብሔር ሁላችንንም ከበለስ በታች ያውቀናል፡፡ እግዚአብሔር ዝም የሚለው ስለማያውቀን አይደለም፡፡ ናትናኤልን እያወቀው ተንኮል የሌለበት የእስራኤል ሰው እንደሆነ ተናገረ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በገሊላ ባሕር እንዳስተማረው ትምህርት  ሊሰሙ፣ ሊማሩ፣ ሊለወጡ ባለመቻላቸውም ‹‹ኮራዚ ወዮልሽ! ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ቀድሞ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው በተቀመጡ ንስሓም በገቡ ነበር፡፡ ነገር ግን ጢሮስና ሲዶና ከእናንተ ይልቅ በፍርድ ቀን ይቅርታን ያገኛሉ፡፡ አንቺም ቅፍርናሆም እስከ ሰማይ ድረስ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ›› ብሎ ጌታችን ተናገሯል፡፡ (ሉቃ.፲፥፲፫-፲፭)

እነዚህ ከተማዎች እነ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ እንድርያስን፣ ፊሊጶስን የመሰሉ የተመረጡ ሰዎች የኖሩባቸው ነበሩ፡፡ ነገር ግን ምንም ቅዱሳን እዚህ ቦታ ቢወጡ፣ ሐዋርያትም ከዚህ ቦታ የተገኙ ቢሆኑም፣ በአሁን ጊዜ ያሉት ሰዎች ንስሓ መግባት ባለመቻላቸው ከተማዎቹ በኃጢአት ጠፍተዋል፤ የእኛም እጣ ፈንታ እንደዚያ እንዳይሆን መጨነቅ አለብን፡፡

ዐመፅ እና በደል ከመፈጸም ሕዝቡም ካልተመለሰ የኮራዚ፣ የቅፍርናሆምና ቤተ ሳይዳ ዕጣ ፈንታ አይቀርልንም፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች ሰው ስለ ወጣ ወይንም ቅዱሳን ስለተገኙባት ብሎ እግዚአብሔር ድኃ ሲበድል ፍርድ ሲጓደል ዝም ብሎ አይመለከተም፡፡ ጌታችን ብዙ ጊዜ ያስተማረበት ምኩራብ (የቅፍርናሆም ምኩራብ) ሮማዊው መቶ አለቃ ያመነበትና ያሠራው በመሆኑ ዛሬም ምልክቱ አለ፤ ግን ከተማው ጠፍቷል፡፡

ትግላችን መሆን ያለበት የእኛ ዕጣ ፈንታ እንደዚያ እንዳይሆን ነው፡፡ ‹‹ሀገራችን ቅድስት ናት፤ ብዙ ገዳማት አሏት፤ ሃያ አራት ሰዓት ስብሐተ እግዚአብሔር የማይጓደልባት ናት›› እያልን እያመካኘን መቀመጡ ብቻ አያድነንም፡፡ ለንስሓ በቅተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እየተቀበልን በሃይማኖት ልንጸና ይገባናል፡፡