የዛሬው የቤተ አብርሃም እንግዳችን መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንቴ ይባላሉ፡፡ ከአባታቸው ከቄስ ፈንቴ ታረቀ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ጎንደር በቀለ በ፲፱፻፶፰ ዓ.ም በምዕራብ ጎጃም ሰከላ ወረዳ ልዩ ስሙ ጉሌ ኪዳነ ምሕረት ተብሎ በሚጠራ ቦታ ተወለዱ፡፡ በአብነት ትምህርቱ ቅኔን ጨምሮ ሌሎቹንም ትምህርቶች ተጨልፎ ከማያልቀው ከቤተ ክርስቲያን ማዕድ በአባቶች እግር ሥር ቁጭ ብለው ተምረዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ በመምጣትም በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ የካህናት ማሠልጠኛ ለአራት ዓመት የነገረ መለኮት ትምህርት ተምረዋል፡፡ በትውልድ አካባቢያቸው ለ፲፫ ዓመት የቅኔና የሐዲሳት መምህር ሆነው አገልግለዋል፣ ከዚያም ወደ ከተማ በመምጣት ከ፳፪ ዓመታት በላይ የቅኔ፣ የሐዲሳትና የብሉያት መምህር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በርካታ ተማሪዎችን አስተምረው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ በአጠቃላይ ባሳለፉት የአገልግሎት ዘመን የቅኔና የትርጓሜ መምህር ሆነው በማገልገል ከ፴፱ ዓመት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሃይማኖተ አበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡ ከመጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ቀጸላ ፈንታ ጋር በሕይወት ተሞክሯቸው ዙሪያ ልምዳቸውን፣ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ያጋሩን ዘንድ የቤተ አብርሃም እንግዳችን አድርገናቸዋል፤ መልካም ንባብ፡፡