የሐዋርያት ጾም
ሐዋርያት ወንጌለ መንግሥት እንዲስፋፋና በሕዝብም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ አገልግሎታቸው የሠመረ እንዲሆን መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ በበዓለ ሃምሳ ማግሥት ጾም ጀመሩ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ በሰጣቸው ሥልጣን ድውያንን መፈወስና አጋንንትን ማውጣት እንዲሁም የተለያዩ ገቢረ ተአምራትን ይፈጽሙ ዘንድ ጸሎትና ጾም ያስፈልጋቸው ነበርና፡፡ በማቴዎስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን ጋኔን ያለበትን ልጅ ካዳነው በኋላ ሐዋርያቱ ስለምን እነርሱ ጋኔን ከሰው ማውጣት እንዳልቻሉ በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መልሶላቸዋል፤ ‹‹…ይህ ዓይነቱ ግን ያለጾምና ጸሎት አይወጣም፡፡›› (ማቴ.፲፯፥፳፩)