ጌታችን ጾመ፤ በዲያብሎስም ተፈተነ (ማቴ.፬)

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው

የካቲት ፲፯፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ከሁሉ አስቀድመን እግዚአብሔርን እንዲህ እያልን እናመስግነው።  “ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ንሴብሕ ወንዜምር ለዘወሀበነ ጾመ ለንስሓ።” ጾምን ለንስሓ ለሰጠን ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ፣ ምስጋና ይገባል።

እንኳን ለዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት (ቅድስት) በሰላም አደረሳችሁ!

ይህን ሳምንት ቤተ ክርስቲያናችን “ቅድስት” ብላ ትጠራዋለች። በዚህም ስለ እግዚአብሔር የባሕርይ ቅድስና፣ ስለ መላእክት ቅድስና፣ ስለ ሰው ልጅ የጸጋ ቅድስና፣ ስለሰንበት ቅድስና፣ ስለ ንዋያተ ቅድሳት ቅድስና፣ በአጠቃላይ በባሕርይው ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር የቀደሳቸው፣ የባረካቸው፣ የለያቸው፣ የመረጣቸው ቅዱሳን የሚዘከሩበት ሳምንት ነው። “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” እንዲል፡፡ (፩ጴጥ.፬፥፲፭) በቅድስና መኖር እንደሚገባን የምንማርበት ሳምንት ነው።

የሰው ልጅ ተፈጥሮ ስንመለከት በእግዚአብሔር አርአያ የተፈጠረ፣ እግዚአብሔርን የሚመስል፣ መላእክት ሊያዩት የሚቻኮሉለት፣ በማየታቸው ደስ የሚሰኙበት፣ የፍጥረታት ንገሥ፣ መክብበ ፍጥረታት፣ በቅድስና ያሸበረቀ፣ የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ነው። ታዲያ እንዲህ በክብር የተፈጠረው፣ በቅድስና ያጌጠው የሰው ልጅ ይህን ክብሩን እንዳያጣ ሕግ ተሰጠው ዕፀ በለስ እንዳትበላ የሚል ነበር። ነገር ግን አትብላ የተባለውን በመብላቱ ሕግ በመተላለፉ በቅድስና ያጌጠው እራቁቱን ሆነ ጉስቁልናና ኃፍረትን ተላበሰ።

ምሕረቱ እጅግ የበዛው አምላካችን ከሰማየ ሰማያት ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ። አዳም በ፴ ዓመቱ አግኝቶት የነበረውን ክብር ሊመልስለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፴ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገባ። በመብል የወደቀውን አዳምም በጾም ጠላቱን ድል ሊያደርግለት ጾመ፤ “ጾመ እግዚእ አርብዓ መዓልተ ወአርብዓ ሌሊተ” እንዲል፤ ፍለጋውን እንድንከተል አርአያውን ይሠጠን ዘንድ ከቆመ ሳይቀመጥ ከዘረጋ ሳያጥፍ ፵ መዓልትና ፵ ሌሊት ጾመ። (ማቴ.፬፥፪)

የጌታችን ጾምና ፈተናዎች

ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ ሲጾም “ወቀርበ ዘያሜክሮ፤ ሰይጣን ሊፈትነው ቀረበ” ይላል፡፡ በመጀመያም እንዲህ አለው፤ “እመሰ ወልደ እግዚአብሔር አንተ በል ከመ እላ አዕባን ኅብስተ ይኩና፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።” (ማቴ. ፬፥፫) ሰይጣን የመጀመርያውን ሰው አዳም በመብል ድል ነሥቶት ስለነበር በለመደበት ክርስቶስን ድል ሊነሣ መጣ። ይኸውም አብ በደመና “የምወደው ልጄ እርሱ ነው” ሲል ሰምቶ ነበርና ይህን ተናግሯል። (ማቴ.፫፥፲፯) ሰይጣን እንዲህ ያለው በትርጓሜ ወንጌል እንደምናገኘው በአንድ እጁ ደንጋይ ይዞ በሌላ እጁ ደግሞ ዳቦ ይዞ በመቅረብ ነበር። ምን ነው ከያዝከው አንበላም ቢለኝ አዳምን ድል እንደነሣሁት እርሱንም ድል እነሣዋለሁ። ቢያደርገው ደንጋዩን ወደ ዳቦ ቢቀይረው ለሰይጣን ታዛዥ ብየ እዳ እልበታለሁ ብሎ ቀረበ። (የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፫ አንድንምታ ትርጓሜ)

ጌታችንም “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጅ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት ድል ነሳው። (ማቴ.፬፥፬) ክርስቲያኖች ዛሬ እኛ በመብል አልወደቅንም? ሥራችን ሁሉ ለመብል የሆነ አይመስላችሁም? ሰይጣን ዛሬ እኛን ሁለት ጊዜ ድል አደረገን፤ አንደኛ ብሉ የተባልነውን ሁሉ ሳንመርጥ እየበላን ስለሆነ ነው። አስታውሱ! እኛ የንጉሡ የክርስቶስ ልጆች ነን። የንግሥ ልጅ ከእልፍኝ አይወጣም፤ ምግቡና መጠጡ የተመረጠ ነው፤ ሲጓዝ እንኳን አጃቢዎቹ ብዙ ናቸው። እኛስ መኖርያችን ክርስቶስ በነገሠባት ቀራንዮ (ቤተ ክርስቲያን) አጃቢዎቻችን ቅዱሳን መላእክት ምግባችን የክርስቶስ ሥጋና ደም ሆኖ ሳለ ለአሳማዎች ከሚጣል ፍርፋሪ ለመብላት ስንደከም አያሳዝንም።

ክርስቲያኖች ብቻችንን እስከ መቼ እንኖራለን? ኃጢአት ማለት ከእግዚአብሔር መለየት ነውና ከኃጢአታችን እንመለስ! ያንጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ስንሆን ጠባቂዎቻችን የንጉሡ ባለሟሎች ከእኛ ጋር ይሆናሉ። ሁለተኛ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆናችሁ “እንዲህ አድርጉ” ሲለን የሰይጣንና የባለሟሎቹን ፈቃድ በመፈጸም ጠፋን፤ አስታውሱ! ሰይጣን ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ ብቻ ሳይሆን “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ከዚህ መር ብለህ ወደ ታች ውረድ” (ማቴ.፬፥፫-፮) ሲለው አልነበር? አምላካችን ግን የሚሠራውን ያውቃልና ዝም አለው። እኛም የንጉሣችን የክርስቶስ ልጆች ነንና የምንሠራውን እንወቅ። ማንም “በዚህ ሂዱ፤ በዚህ ውጡ” ሲለን አንነዳ።

ፈታኙ አሁንም ሁለተኛ ፈተና ሊፈትነው “ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደው፤ በመቅደስ ጫፍም አቆመው፡፡” ልብ በሉ! ሰይጣን የሚያዝዘው ሆኖ ሳይሆን ፈቃዱን አውቆ ስለሄደለት ነው። እንዲህም አለው፤ “መላእክትን ስለ አንተ ያዝልሃል፤ እግርህንም በደንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል፤ በእጃቸው ያነሡሃል” ተብሎ ተጽፎአልና፡፡ (መዝ.፺፥፲፩) “የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ወደ ታች እራስህን ወርውር” አለው። (ማቴ.፬፥፮) በስስት ፈትኖት ድል የተነሣው ሰይጣን በትዕቢት ሊፈትነው እንዲህ አለው። በዘመናችን የምናየው የጥቅስ ብዛት የእግዚአብሔርን ቃል የአለአግባቡ መጥቀስ መምህሩ ዲያብሎስ እንደሆነ ያሳያል። አምላካችንም “ኢታመክሮ ለእግዚአብሔር አምላክከ፤ ጌታ አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ  ተጽፎአል” በማለት ድል ነሳው። (ማቴ.፬፥፯)

ለሦስተኛ ጊዜም ወደ ረጅም ተራራ ወስዶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም  አሳይቶ “ወድቀህ ብተስግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።” (ማቴ ፬፥፱) ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ኦ ትሕትና ዘመጠነዝ ትሕትና ኦ ትግሥት ዘመጠነዝ ትዕግሥት ኦ አርምሞ ዘመጠነዝ አርምሞ፤ ይህን ያህል ትሕትና እንደምን ያለ ትሕትና ነው? ይህን ያህል ትዕግሥት እንደምን ያለ ትዕግሥት ነው? ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው? እንዳለ (ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ ቁጥር ፶፪) እግዚአብሔር ሰይጣንን ምን ያህል እንደታገሠው ተመልከቱ፤ ዝም ቢለውም በመንግሥቱ ገባበት።  ከመጠንም አለፈ፤ በአምላክነቱም ገባና ስገድልኝ አለ። አምላካችንም በአምላክነቱ ቢገቡበት አይወድምና “ሂድ አንተ ሰይጣን! ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና።” በማለት ከእርሱ በኋላ ከሚነሱ ምዕመናን ዘንድ ሁሉ አራቀው። (ማቴ.፬፥፲)

በዘመናችን እየሆነ ያለውን ስናስተውልም የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ ክርስቶስ እስኪመጣ በትዕግሥት፣ በአርምሞ፣ በትሕትና ሆና መምጣቱን ስትጠባበቅ ዛሬም ሰይጣን ከእግሩ በታች ወድቃ እንድትገዛለት ሽቶ ጦሩን ሰበቀ፤ ዝናሩን ታጠቀ፤ ቀስቱን ወረወረ። እናም ክርስቶስ ፈጽሞ ዝም እንዳላለ፣ ፈጽሞም እንዳልተናገረ፣ የሚጠቅመውን ግን እንደተናገረ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን “ከበኋላየ ሂድልኝ” የምትልበት ሰዓት ደርሷልና ሰይጣን ሆይ ከቤተ ክርስቲያን ዘወር በል ልንለው ይገባል። ይህ የሚሆነው ደግሞ በጾም ነውና ከፊቱ ይልቅ እንበርታ!

የክርስቶስ ቤተሰቦች! ዛሬ ሰይጣን እኛን አላንበረከከንምን? ስንቶቻችንስ በገንዘብ ሃይማኖታችንን አሳልፈን ሰጠናት? በሚጠፋ ገንዘብ ሥልጣን ሽቶ ማተቡን የበጠሰውን ማሰብ ልብ ይከፍላል። አባቶቻችን ገንዘባቸው፣ ክብራቸው፣ ዝናቸው፣ ሥልጣናቸው እግዚአብሔርን ለማገልገል ነበር። ዛሬ ግን ሥልጣን፣ ክብር፣ ዝና፣ ሃብት ሲያገኙ ማተብ መበጠስ፣ ሃይማኖትን መካድ፣ ለሰይጣንና ግብረ አበሮቹ መስገድ፣ የተለመደ ተግባር ሆኗል። ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ርቀን ከቤተ ክርስቲያን ተለይተን ከምናገኘው ዝና፣ ክብር፣ ሃብት፣ ሥልጣን ይልቅ በእግዚአብሔር ቤት ችግረኛ ሆነን መኖር ይሻላልና እንደ ቅዱስ ዳዊት እንዲህ እያልን እንለምነው እንጅ በጥቅማጥቅም ከቤቱ አንውጣ፤ “አሐተ ሰዓልክዎ ለእግዚአብሔር ወኪያሃ አኃሥሥ ከመ እኅድር ቤቶ ለእግዚአብሔር በኵሉ መዋዕለ ሕይወትየ፤ “እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።” (መዝ.፳፯፥፬)

   ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን ጾመ? ለምንስ ተፈተነ?

ጾምን ሊባርክልን፦ ጌታችን የጾመው ለእኛ አርአያ ሊሆነን ፈቃዳችንን ለእርሱ እንድናስገዛ ሊያስተምረን ነው እንጅ። መብል የሥጋ ፍላጎትን የሚጨምር፣ በሰውነታችን ውስጥ ያሉ ሕዋሳቶቻችን ፈሳሾችን ቶሎ ቶሎ እንዲያመነጩ የሚያደርግ ነው። ይህ ፈሳሽም የደም ሥሮቻችንን በመሙላት ግፊት ይፈጥራል። በዚህም ለዝሙት ትልቅ ፍላጎት ያሳድራል፤ አንድ አባባል እናንሳ፤ “እየበሉና እየጠጡ የሥጋ ፍላጎትን ዝሙትን አጠፋለሁ ማለት የሚነድን እሳት ለማጥፋት ቤንዚን እንደመጨመር ነው።” መጣላት ከእኔ በላይ ሰው የለም ማለት ያመጣል፤ ይህን ነገር ተቆጣጥሮ ሥጋን ለነፍስ ለማስገዛት ጾም አስፈላጊ ነውና አምላካችን ጾምን ሠራልን።

አምላካችን ጾምን ቀድሶ ሰጠን፤ ጹመን እንቀደስ ዘንድ የሳምንቱም ስያሜ ቅድስት ተባለ፤ ቅዱሰ ባሕርይ አምላካችንን በቅድስና እንመስለው ዘንድ የምንማርበት ነውና። ክርስቲያኖች ታዋቂ ግለሰቦችን ለመምሰል ያደረጉትን ለማድረግ በምንደክምበት ዓለም ንጉሣችን ክርስቶስ ያደረገውን የጾመውን ለመጾም መሽቀዳደም አይገባምን? እንግዲያውስ ጾምን በመቀደስ አምላካችንን እንምሰለው።

በመጽሐፍ እንደተጻፈ ፈተናውን ድል ነሥቶ እንዲህ አለን፤ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐ.፲፮፥፴፫) በዚህም አባቶቻችን በፈተና አምላካቸውን የሚመስሉበት በመሆኑ እጅግ ደስ እያላቸው ይፈተናሉ። ቅዱስ ያዕቆብም በመልእክቱ “ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት”  በማለት ፈተናችን ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት እንደሆነ ነገረን። (ያዕ.፩፥፪)

ይቆየን!

ወስበሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!!!