ምሁራን ለቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ለሙህራን›› በሚል የጥናትና ምርምር ምሁራን የምክክር መርሐ ግብር ይደረጋል

የካቲት 22/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል ከጥናትና ምርምር ማእከል ባለሙያ ምሑራን ጋር የምክክር መድረክ መርሐ ግብር እንደሚያካሔድ አስታወቀ፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ዳሬክተርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂና ቅርስ አስተዳደር መምህር የሆኑት ዲ/ን መንግሥቱ ጎበዜ እንደገለጹት ምሁራን ለቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን፤ ለምሑራን ያላቸውን ተወራራሽ ጠቀሜታ በማጉላት፣ የምሑራንንም ፋይዳ ከቤተ ክርስቲያን ያገኙትንም ለመግለጽ ዐቢይ መርሐ ግብር መሆኑ ገልጸዋል፡፡ ይህ የውይይት መድረክ ለጥናትና ምርምር ማእከሉ አገልግሎቱን አጠናክሮ ለመቀጠል፣ የሌሎች ምሁራንን ድጋፍ ለማግኘትና ምሑራንም የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት እንዲያግዙ ለማነቃቃት ያግዛል፡፡ ምሑራኑም የጥናት ጽሑፎቻቸውን በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እንዲያደርጉ ከማገዝም በላይ ቤተ ክርስቲያንም ትልቅ የመረጃ ምንጭ በመሆን ለጥናታቸው ውጤታማነት ፋይዳዋ ታላቅ መሆኑን የሚረዱበት ይሆናል ብለዋል፡፡

በዚህ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች መርሐ ግብር ላይ የዘርፉ ባለሞያዎች የሚገኙ ሲሆን መርሐ ግብሩም በአዲስ አበባ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም እንደሚካሔድ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የጥናትና ምርምር ማእከሉ የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፣ ሀገርና የሀገር ሉዓላዊነት” በሚል ርዕስ ጥናት እንደሚቀርብ ገልጻôል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለአድዋ ድል መገኘት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ድርሻ በመሆኑ በዓሉን ጥናታዊ ጽሑፍ እየቀረበ በየዓመቱ እንዲከበር በተሳታፊዎች የተሰጠ ጥቆማ ስለነበር የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግና ለሀገር አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ሚና ማጉላት ዓላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቅዳሜ የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በብሔራዊ ሙዚየም የሚቀርበው “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን፣ ሀገርና የሀገር ሉዓላዊነት” ርዕስ በዋናነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገርን ሉዓላዊነት በመጠበቅ አንጻር ምእመኗን አስተባብራ ድል ያስገኘች መሆኗ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከባሕል ወረራ ሀገርን የመከላከል ያላት አስተዋጽኦ ለማስገንዘብ የሚያስችል መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸው በብሔራዊ ሙዚየም በሚደረገው መርሐ ግብር ሁላችሁም ተጋብዛችኋል በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ሰበር ዜና

የካቲት 21/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን አብርሃም አንዳርጌ

የጥንታዊው አሰቦት ገዳም ደን ዳግም የእሳት አደጋ ቃጠሎ ደረሰበት፡፡

asebot

የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ገዳም ደን ትላንት የካቲት 20 ቀን 2004 ዓ.ም. ባልታወቀ ምክንያት በተነሣ እሳት ቃጠሎ ደረሰበት፡፡

ትላንት ከቀኑ 5፡00 ሰዓት የተነሣው እሳት እስከአሁን ድረስ ያልጠፋ መሆኑንን የገለጹት የገዳሙ አገልጋይ አባ ወልዴ እንዳሉት እሳቱ እየተስፋፋ ከደኑ አልፎ ወደ ቅድስት ሥላሴ የአባቶች ገዳም እየተቃረበ መሆኑንን ገልጸዋል፡፡

እሳቱን ለማጥፋት የአካባቢው ገበሬ ማኅበር ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከውኃ እጥረትና ከሰው ኀይል ማነስ የተነሣ ይህ ዜና እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እሳቱ አለመጥፋቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

ዝርዝርሩን እንደደረሰን እናሳውቃለን፡፡

የመባዕ ሳምንት

Derej A5

ብፁዕ አቡነ አብሳዲ አረፉ

የካቲት 13/2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

abune abusadeብፁዕ አቡነ አብሳዲ በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ቅዳሜ የካቲት 10/2004 ዓ.ም. ለእሑድ አጥቢያ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ብፁዕነታቸው በትግራይ ክፍለ ሀገር ሽሬ በ1912 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ በ1926 ዓ.ም ከሽሬ ወደ ኤርትራ በመሔድና ደብረ ማርያም ገዳም በመግባት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመከታተል ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ይስሐቅ፣ ቅስናን ደግሞ ከአቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡ በደብረ ማርያም ገዳም ውስጥ በቆዩባቸው ዐሥር ዓመታት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ዲያቆናትንና ካህናትን በማስተማር አፍርተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ አብሳዲ በ1943 ዓ.ም በሱዳን በኩል ወደ ኢየሩሳሌም በእግራቸው የሔዱ ሲሆን፤ በግብጽ ለሁለት ዓመታት ለመቆየት ችለዋል፡፡ ከ1959 ዓ.ም. ጀምሮ ከ60 ዓመታት በላይ በኢየሩሳሌም የኖሩ ሲሆን ጥር 30 ቀን 1983 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በኤጲስ ቆጶስነት ከተሾሙት ጳጳሳት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በኤጲስ ቆጶስነት እንደተሾሙ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ረዳት ኤጲስ ቆጶስ ሆነው እስከ ዕለተ እረፍታቸው ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ይገኙ ነበር፡፡

በቆይታቸውም በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ የሆኑትን አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትን ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት ያደረጉና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሟገት የተጣለባቸውን ሓላፊነት በመወጣት ሰፊ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ አብሳዲ ዕብራይስጥንና አረብኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው ይናገሩም ነበር፡፡

ከቡኢ ምድረ ከብድ የሚወስደው መንገድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የካቲት 13/2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በጉራጌ ሀገረ ስብከት የሶዶ ወረዳ ዋና ከተማ ከሆነችው ቡኢ ከተማ ጀምሮ ምድረ ከብድ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ድረስ የሚወስደው የ18 ኪ.ሜትር ጥርጊያ መንገድ በፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ሙሉ ትብብር ሥራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገዳሙ አበምኔት አባ አብርሃም ወ/ኢየሱስ ገለጹ፡፡

ከዚህ ቀደም ይኸው መንገድ በአካባቢው ምእመናን አማካይነት በእጅ ቁፋሮ፣ ድንጋይ በመሸከምና ከጉልበት እስከ ገንዘብ አስተዋጽዖ በማድረግ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ብዛት በመበላሸቱ በመኪናም ሆነ በእግር ወደ ገዳሙ ለመሔድ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ገዳሙ ለክብረ በዓላትም ሆነ ለጉብኝት የሚመጡ ምእመናን በመቸገራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ መጥቷል፡፡

 

ሙሉ ወጪውን በመሸፈን መንገዱን በጥሩ ሁኔታ ሠርቶ ያስረከበውን የፌዴራል መንገዶች ባልሥልጣንን በእግዚአብሔር ስም ያመሰገኑት አበምኔቱ በመንገዱ መበላሸት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የምእመናንና የገዳሙን ግንኙነት ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል፡፡

 

ቀደም ሲል ገዳሙ ሰፊ የእርሻ መሬት ርስት የነበረው በመሆኑ በገዳሙ ውስጥ የሚገኙ መነኮሳትና መነኮሳይያት እርሻ በማረስና ሰብሎችን በመዝራት የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ይተዳደሩ እንደነበር የገዳሙ አበምኔት ተናግረው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ገዳሙ በቂ የእርሻ መሬት የሌለው በመሆኑ መተዳደሪያ ያደረገው በዓመት ሁለት ጊዜያት ጥቅምት 5 እና መጋቢት 5 በጻድቁ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ከሚመጡ ምእመናን ከሚለግሱት የገንዘብና መባ አስተዋጽኦ ብቻ እንደሆነ የገዳሙ አበምኔት ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ገዳሙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ለማጠናከርና በውስጡ የሚኖሩት መነኮሳት በችግር ምክንያት እንዳይበተኑ እንዲሁም ጥንታዊነቱንና ታሪካዊነቱን ጠብቆ ለማቆየት ከምእመናን ብዙ እንደሚጠበቅና በክብረ በዓላትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ ገዳሙ ያለበትን ሁኔታ መጥተው በማየት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

 

ገዳሙ በንጉሥ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት  በራሳቸው በጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የተመሠረተ ሲሆን በጾምና ጸሎት የተጋደሉበት እንዲሁም ያረፉበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቅድስት ቤተልሔም የመጻሕፍት ቤትና የጉባኤ ቤት ተመረቀ

የካቲት 12/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን አብርሃም አንዳርጌ

{gallery count=1 width=275 height=225 counter=1 links=0 alignment=right animation=3000}Beteleheme{/gallery}በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ፕሮጀክት የተገነባው በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በታች ጋይንት ወረዳ የምትገኘው የድጓ ማስመስከሪያ ቅድስት ቤተልሔም ቤተ ክርስቲያን የመጻሕፍት ቤትና የጉባኤ ቤት ተመረቀ፡፡

የካቲት 4 ቀን 2004 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ እንድርያስ የተመረቀው ይኸው መጻሕፍት ቤትና ጉባኤ ቤት ሙሉ ወጪውን የላስ ቬጋስ ምእመናን በዋናነት መሸፈናቸው ታውቋል፡፡

 

ኅዳር 26 ቀን 2003 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ በአንድ ዓመት ውስጥ የተጠናቀቀውን ግንባታ አስመልክቶ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ሲናገሩ የአብነት ትምህርት ቤቶች ለቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋጽዖ ቀላል የሚባል አይደለም” በማለት አመስግነዋል፡፡

 

በዕለቱ አጠቃላይ የሥራ ሒደቱን ዝርዝር ሪፖርት ያቀረቡት የድጓ ምስክር መምህር የሆኑት ሊቀምሁራን ይትባረክ ካሳዬ እንዳሉት “በግንባታው ምክንያት በተፈቀደልን ቦታ ላይ ፕሮጀክት ተቀርጾ የደብሩ ማኅበረ ካህናት፣ የድጓ አድራሾቹ ሁላችን ልማት እያለማን እራሳችንን የምንችልበት መንገድ ይፈልግልን፤ እስከ አሁን ለጉባኤ ቤታችን ለተደረገልን ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት የቅስቀሳና ገቢ አሰባሳቢ ክፍል ሓላፊ ዲያቆን ደረጀ ግርማ በበኩሉ ማኅበሩ በቀጣይም ከቅድስት ቤተልሔም የድጓ ማስመስከሪያ ጎን በመሆን በጋራ ችግሮቹን በመፍታት እንደሚሠራ ጠቁሞ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ የላስቬጋስ ምእመናንንና የአካባባውን ማኅበረሰብ ስለቀና ትብብራቸው አመስግኗል፡፡

 

በዕለቱም በድጓ ያስመሰከሩ የተወሰኑ አድራሾችና በግንባታው በጎ እንቅስቃሴ የነበራቸው ምእመናን ከብፁዕ አቡነ እንድርያስ እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡ በቅድስት ቤተልሔም የድጓ ማስመስከሪያ በሀገራችን ብቸኛው ማስመስከሪያ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት 49ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አከበረ፡፡

የካቲት 9/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም የካቲት 4 ቀን 2004ዓ.ም የተመሠረተበት 49ኛ ዓመት በዓል   ለድርጅቱን መሥራች ክብር አቶ መኮንን ዘውዴ  የመታሰቢያ ሐውልት ቦሌ ሩዋንዳ በሚገኘው መሰብሰቢያ አዳራሽ በር ላይ በማቆም ጭምር ተከብሯል፡፡

በ1955 ዓ.ም. ሚያዝያ 3 ቀን ከሠላሳ በማይበልጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እንደተመሠረተ የሚነገረው መታሰቢያ ድርጅቱ በክብር አቶ መኮንን ዘውዴ ጠንሳሽነትና አሰባሳቢነት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በወቅቱ ቅዱሳን መካናትን ለመሳለም ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሔደው የምእመናን ቡድን በዚያ ያለውን ችግርና በገዳማቱ የሚኖሩ አባቶችና እናቶችን በደልና ስቃይ ተመልክቶ የነበረ ሲሆን በተለይ የዴር ሱልጣን ገዳማችን ወደ ጥንቱ ይዞታ ለመመለስ ካልተቻለበት ምክንያቶች አንዱ ከኢትዮጵያ ገዳማውያንን ለመጎብኘት የሚመጣ ሰው የለም የሚል ምክንያት እንደሚሰጥ መረዳታቸው ለድርጅቱ መመሥረት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ክብረ በዓሉን በንግግር የከፈቱት የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ኮሎኔል ተፈራ ይገዙ “የድርጅታችን የተመሠረተበትን 49ኛ ዓመት በምናከብርበትና በተልይም የታሪኩ ባለቤት ለሆኑት ክቡር አቶ መኮንን ዘውዴ የተሠራውን የመታሰቢያ ሐውልት በሚመረቅበት በዚህ ዕለት የተሰማንን ከፍተኛ መንፈሳዊ ደስታ ስንገልጽ ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፡፡ “ሰው ለታሪክ የተፈጠረ እንጂ ታሪክ ለሰው አልተፈጠረም ያሉት ምክትል ሊቀ መንበሩ በ1955 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ገዳማት የሚደርሰው በደል አሳዛኝ ታሪክ መነሻነት በብሔራዊና በመንፈሳዊ ስሜት በመቆርቆር ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ በርካታ አባላትን በማሰበሳብና የገዳማችንን ታሪክ በማስረዳት ለዚህ የቀደሰ ዓላማ ድጋፍ ለመስጠት ቃል የገቡትን ሰዎች ይዘው የኢየሩሳሌምን መታሰቢያ ድረጅትን የመሠረት ድንጋይ ሚያዝያ 16 ቀን 1956 ዓ.ም ያስቀመጡ የመጀመሪያው ታላቅ ሰው ከመሆናቸውም በላይ የድርጅቱን ዓላማ በተግባር በማዋል ከምንም አንስተው አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስና በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅና እንዲያገኝ ያደረጉ ታላቅ አባት ናቸው” ብለዋል፡፡

 

ክቡር አቶ መኮንን ዘውዴ በተለይ የዴርስልጣን ገዳማችንን በተመለከተ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ተቃዋሚ ወገኖች አጋጣሚ እየጠበቁ ሁከትና ውዝግብ በሚፈጥሩበት ወቅት ፈጥኖ በመድረስና በየቀጠሮም ቀን ከገዳም አባቶች ጋር  በእስራኤልአገር ፍርድ ቤት በመገኘትና ከአባቶች ጎን በመቆም ከፍተኛ የሞራልና የገንዘብ እርዳታ በየጊዜው ለገዳሙ እንዲሰጥ በማድረግ የሀገርና የቤተክርስቲያን ባለውለታ መሆናቸው ተወስቷል፡፡

 

 

በመክፈቻው ንግግራቸው ምክትል ሊቀመንበሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ድርጅቱ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት የገለፁ ሲሆን “በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን ለማስተማርና በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደራጀት በቤተ ክርስቲያን የተነደፈውን እቅድ በመደገፍ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ችግር ለማስወገድ መንግሥት በልማት እንዲሳተፉ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የ700,000 ብር ድጋፍ በመንግሥትና በህዝብ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውን የሕዳሴ ግድብ ሥራ የግማሽ ሚሊዮን ብር ቦንድ ያለ ወለድ ግዥ በማድረግ  ድርጅቱ  በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይወሰን በአገር ውስጥም ለታሪክና መንፈሳዊ ሥራዎች ድጋፍ በመስጠት ላይ ነው” ብለው በተለይ በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን አሰባስቦ በረጲ፣ በአለም ከተማ፣ በደብረ ብርሃን የሕፃናትን በማስተማርና በመንከባከብና በአሁኑ ወቅት ዘላቂነት ያለው ሥራ ለመሥራት የ800,000 ብር ፕሮጀክት በመቅረጽ ውጤታማ ተግባር ለማከናወን በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ኘሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሠላም የክብር ኘሬዝዳንት “ክቡር አቶ መኮንን ዘውዴን የማውቃቸው የትምህርት ሚኒስቴር በነበሩበት ወቅት ነው፤ ያስተማሩኝ፣  በአዳሪ ትምህርት ቤትም እንድንማር ያደረጉኝ ታላቅ ሰው ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው ለትውልድ ታሪክንና ክብርን ላቆዩ ስሞች ክብር ይገባቸዋል ለእኝህ አባት መታሰቢያ ሐውልት እንዲያቆምላቸው ድርጅቱ መወሰኑና ታሪክን ለትውልድ እንዲቆይ በማድረጉ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ መልካምነታቸውን ለትውልድ ልናስተላልፍ ይገባናል) ድርጅቱም አገልግሎቱን አጠናክሮ በመላው ዓለም ጽ/ቤት ከፍቶ ሊሠራ ይገባል” ብለዋል፡፡

የክቡር አቶ መኮንን ዘውዴ የመታሰቢያ ሐውልት ምረቃ ላይ ቅዱስ ፓትሪያርኩን ጨምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች፣ የክቡር አቶ መኮንን ባለቤት ከነ ቤተሰቦቻቸው፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የድርጅቱ አባላት ተገኝተዋል፡፡ በበዓሉ ላይም የቅዱስ ኡራኤል ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌምን በማስመልከት ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

የማኅበሩን አገልግሎት ለማገዝ የማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ተመሠረቱ

የካቲት 9/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በማኅበረ ቅዱሳን ለሀገር ውስጥ ማእከላትና የግቢ ጉባኤያት ማ/ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ተጠሪ የሆኑ 6(ስድስት) ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ተቋቋሙ፡፡

ማኅበሩ አገልግሎቱን ይበልጥ አጠናክሮ ለማገልገል የተሰጠውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሓላፊነት ለመወጣት የማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው የተገለጸው፡፡

መቀመጫቸው የሰሜን ማእከላት ማስተባበሪያ በመቀሌ፣ የሰሜን ምዕራብ ማእከላት ማስተባበሪያ በባሕርዳር፣ የምዕራብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በጅማ፣ የደቡብ ማእከላት ማስባበሪያ ጽ/ቤት በአዋሳ የምሥራቅ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በድሬደዋና የመሀል ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አዲስ አበባ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ጥር ፳6 እና ፳7 ቀን ፳፻4 ዓ.ም ማእከላት የማስተባበሪያ ጽ/ቤት ምስረታ ላይ የማስተባበሪያ ጽ/ቤት የሚያካልላቸው ማእከላት በተገኙበት ተመስርተዋል፡፡ በምስረታ መርሐ ግብሩ ላይ የማስተባበሪያ ማእከላቱ ጽ/ቤት ተግባርና ሓላፊነት እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት በማኅበረ ቅዱሳን ምን መምሰል አለበት በሚሉ ርዕሰ ጉዳይ የስልጠናና የውይይት መርሐ ግብር ተካሔዷል፡፡

15 አባላት ያሉት የማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስፈጻሚ አካላት የሀገር ውስጥ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ጨምሮ በዋና ማእከል ከሚገኙ ዋና ክፍሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ለሚከናወኑ ተግባራት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡

ምክረ አበው በሐዊረ ሕይወት

  • “ሐዊረ ሕይወት ከመንፈሳዊ ጉዞዎች ሊጠበቁ የሚገባቸውን ተግባራት የሚያመለክት ነው”

የካቲት 5/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

IMG_0038ማኅበረ ቅዱሳንን ከአባላቱ ውጭ ካሉ ምእመናን ጋር የሚያገኘው መድረክ እንደሆነ ይታመናል ሐዊረ ሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ፡፡ ከ4 ሺሕ ምእመናን በላይ ይሳተፉበታል ተብሎ ለሚጠበቀው የዘንድሮው ጉዞ ከማንኛውም ጊዜ በላይ በተቀናጀና በተደራጃ መንገድ ዝግጁቱን ለማሳካት ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሚያስተባብር አገልጋይም ተመድቧል፡፡ በአገር ቤት ያሉትን ምእመናን ብቻ ሳይሆን ባሕር አቋርጠው ሰማይን ጠቅሰው ለሚመጡ ምእመናን ሁኔታዎች ተደላድለውላቸዋል፡፡ የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት ከወትሮው በምን ይለያል? የሚሉ እና ተያያዥ ጥያቄዎችን እንዲመልሱልን የጉዞውን መርሐ ግብር የሚያስተባብሩትን ዲያቆን ሙሉዓለም ካሳን የመካነ ድራችን እንግዳ አድርገናቸዋል ተከታተሉን፡፡

መካነ ድር፡- እስኪ አጠር አጠር ካሉ ጥያቄዎች ልጀምርና ጉዞው መቼ ይደርጋል? ስንት ቀንስ ይፈጃል?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ጉዞው መጋቢት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ይከናወናል፡፡ መርሐ ግብሩም ደርሶ መልስ ነው፡፡

 

መካነ ድር፡- የዘንድሮው ጉዞ ወደየት ነው የሚደረገው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ጉዞው በደብረ ብርሃን መስመር ወደ በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይደረጋል፡፡

 

መካነ ድር፡– በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም የተመረጠበት ልዩ ምክንያት አለ?

 

ዲ/ን ሙሉ ዓለም፡- ባለፈው ዓመት ከተመለከትነው ልምድ በመነሣት የዚህን ዓመት ጉዞ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ዓመት በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን ይዘን እንጓዛለን፡፡ በመሆኑም እስከ 4000 ምእመናን እንደሚጓዙ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህን በርካታ ቁጥር ሊያስተናግድ /ሊቀበል/ የሚችል የተመቸ መልክዐ ምድር ያስፈልጋል፡፡ በአንጻሩም አቅመ ደካማ ሰዎች በጉዞው መሳተፍ ቢፈልጉ ደርሰው በጊዜ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በተለየ መልኩ ደግሞ በተመረጠው ደብር አካባቢ ካሉት አድባራትና ገዳማት በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በጥንታዊነቷና በታሪካዊነቷ በውስጧ ከያዘቻቸው የአብነት መምህራንና ደቀመዛሙርት ቀዳሚ በመሆኗ መርጠናታል፡፡

 

መካነ ድር፡- ሐዊረ ሕይወት ማለት ምን ማለት ነው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ሐዊረ ሕይወት የሚሉ ሁለቱ ቃላት ከግእዝ ቋንቋ የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሙሉ ትርጉማቸውም የሕይወት ጉዞ ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዓለማችን የሚከናወኑ የተለያዩ የጉዞ ዓይነቶች አሉ አንድ ሰው ለመዝናናትም ይሁን ዘመድ ለመጠየቅ ወይም ደግሞ አገር ለማየት ይጓዛል፡፡ ያ ጉዞ ሥጋዊና ምድራዊ ጉዞ ነው፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ ቀድሞ በብሉያት እንደተፈጸመው በዘመነ ሐዲስም አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዘው እሱን አብነት አድርገን እንጓዛለን፡፡ በዓላትን ለማክበር ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ከቦታውም በረከት ለማግኘት እንሔዳለን፡፡ ይህ ጉዞ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት ጉዞ ስለሆነ ሐዊረ ሕይወት /የሕይወት ጉዞ/ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

መካነ ድር፡- የዘንድሮው ጉዞ ዝግጅትና ዓላማስ ምን ይመስላል?

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ስለ ዝግጅቱ ከመናገሬ በፊት ስለጉዞው ዓላማ ከመናገር ብጀምር ይሻላል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት “ስም ግብርን ይገልጠዋል” ተብሎ እንደተጻፈው ጉዞው ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ዓላማን ይዞ የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው በመሆኑም በሥራ ቦታ በመኖሪያ አካባቢ ባለው ውጣ ውረድ ሁከተ ኅሊና ያጋጥማል፡፡ በተለያየ ምክንያት የተጨነቀና የዛለ አእምሮ በእንደዚህ ዐይነት ጉዞ ይታደሳል፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ሲነገርም በተከተተ ልቡና ማዳመጥ ያመቻል፡፡ በእንደዚህ ዐይነት ቦታና ሁኔታ የሚነገር ቃለ እግዚአብሔር ወደ ውስጥ ዘልቆ ይገባል የንስሐ ፍሬንም ያፈራል፡፡ ከቦታውም በረከት ያስገኛል፡፡ በዚያውም በተለያየ አጋጣሚ የእግዚአብሔር ቃል ይሰበካል፡፡ በተለየ አጋጣሚ  የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ለማጠንከር ለመንፈሳዊ ዓላማ ታስቦ የተዘጋጀ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው፡፡ በተጨማሪም ከመንፈሳዊ ጉዞ ምን ተግባራት እንደሚጠበቁና ጉዞውን ለሚያዘጋጀው ተቋም የሚያስፈልገውን ሥርዐት ለማመልከትም ያግዛል ተጓዦች በአካል በአእምሮ በነፍስ ተዘጋጅተው በቅዱስ ቦታ ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ ያስተምራል፡፡ የጉዞው ዓላማ ሥጋዊ ጥቅምና ቁሳዊ ትርፍ ለማግኘት ታስቦ የተዘጋጀ መርሐ ግብር አይደለም ዋናውና ተቀዳሚ ዓላማችን መንፈሳዊ ትርፍ እንጂ ሥጋዊ ትርፍ አይደለም፡፡

 

ዝግጅቱን በተመለከተ ጉዞው የተሳካ እንዲሆን አባቶች በጸሎት እንዲያስቡን አሳስበናል፡፡ የጉዞውን ትኬት በአካል በስልክ በአጭር የስልክ መልእክትና በኢ-ሜል ለማግኘት መረጃ ለሚጠይቁ ምእመናን ተፈላጊውን መረጃ ለመስጠት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ተመድቧል፡፡ በጉዞው የሚሳተፉት አዲስ አበባ የሚገኙ ምእመናን ብቻ አይደሉም ከክፍለ ሀገርና ከውጭ ሀገር የሚመጡ ተጓዦች ስለሚኖሩ በጉዞው መርሐ ግብር እንዴት መሳተፍ እንደሚችሉ ከወዲሁ ግንዛቤ በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡

መካነ ድር፡– የጉዞ ቲኬቶችን የት ማግኘት ይቻላል?

 

ዲ/ን ሙሉ ዓለም፡- በአዲስ አበባ ያሉ ምእመናን 5 ኪሎ ሸዋ ዳቦ ፊትለፊት በማኅበረ ቅዱሳን ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ማከፋፈያ ሱቅ፣ እሳት አደጋ ፊት ለፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በቂርቆስ የገበያ አዳራሽ ብሎክ A ቁጥር 230፣ ጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ ኮልፌ አጠና ተራ እፎይታ ገበያ ፊት ለፊት ሳሪስ ማከፋፈያ አዲሱ ሰፈር፣ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥር፣ አምስት ኪሎ በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ሥር ንዋየ ቅዱሳት መሸጫ፣ ዓለም ፀሐይ ድልድይ ፊት ለፊት፣ ኪዳነ ምሕረት ከፍተኛ ክሊኒክ፣ መርካቶ ኬኔዲ ሕንፃ 1ኛ ፎቅ እቴነሽ የሕንጻ መሣሪያ ቁጥር 107ና ኮስሪሞ ላንድ አውቶብስ ተራ ትልቁ መናኸሪያ ፊት ለፊት ማግኘት ይቻላል፡፡

 

ከክፍለ ሀገር ለሚመጡ ተጓዦች በየርእሰ ከተማቸው ባለው የማኅበረ ቅዱሳን ማእካላት ጽ/ቤት ቲኬቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከውጭ ሀገር መምጣት ለሚፈልጉ ምእመናንም http://www.hawirehiywet.somee.com መመዝገብ ይችላሉ፡፡ የውጭ ሀገር ተመዝጋቢዎች ስለ ጉዞው ትኬት ክፍያ በተመለከተ በኢ-ሜይል መልእክት መለዋወጥ ይቻላል፡፡

 

መካነ ድር፡- በጉዞው የሚቀርቡ መርሐ ግብሮች ምንድን ናቸው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም እንደደረሰን ጸሎተ ቅዳሴውን እናደርሳለን፡፡ ከቅዳሴ ውጭ በቤተ ክርስቲያኑ ካህናት ሊቃውንትና ደቀ መዛሙርት ጋር በመሆን የጋራ ጸሎት እናደርሳለን በመቀጠል በማኅበርና በግል የተጋበዙ ዘማርያን ያሬዳዊ መዝሙር ያቀርባሉ፡፡ በገና ደርዳሪዎችም የበገና መዝሙር ያሰማሉ ከዚያም በሊቃውንት አባቶቻችን ትምሕርተ ወንጌል ይሰጣል፡፡ በመጨረሻም ትምህርት ያከናወኑ፣ ምሥጢር ያደላደሉ፣ በእድሜ የበሰሉ በመከራ የተፈተኑ አባቶቻችን የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ምክረ አበው በምእመናን በጣም የሚወደድና የሚናፈቅ መርሐ ግብር በመሆኑ ሰፋ ያለ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር የምእመናን ጥያቄ ይመለሳል፡፡ ሕይወታቸውም ይስተካከል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተዘጋጀው የጉዞ ትኬት ላይ እንደተገለጠው ምእመናን ጥያቄያቸውን በስልክ፣ በኢ-ሜይል በአጭር የሞባይል መልእክት በተለይም በአካል በመቅረብ ጥያቄአቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡

 

መካነ ድር፡- ከተጓዦች የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- በጉዞው ሊደረጉ ስለሚገባቸው ዝግጅቶች ከሞላ ጎደል በትኬቶች ላይ ተገልጠዋል፡፡ ሆኖም ለማስታወስና ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስታወስ እንወዳለን፡፡ የመጀመሪያው የጊዜ አጠቃቀማችን ሥርዓታዊ መሆን አለበት፡፡ ከአዲስ አበባ የምንነሣበት ሰዓት ከንጋቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ ነው፡፡ ከዚህ የጊዜ ገደብ ቀድመንም አንነሣም ዘግይተንም አንጓዝም ስለዚህ በተቻለ መጠን ተጓዞች ሰዓት አክብረው እንዲገኙ እናሳስባለን፡፡ ሁለተኛው ማንኛውም ዐይነት ጽሑፍ ያላቸውን ቲሸርቶች ለብሶ መምጣት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተረፈ አለባበሳችን ክርስቲያናዊ መሆን አለበት፡፡ በመጨረሻም አስተባባሪዎች የሚነግሩንን እየሰማን ምንም ዐይነት መጠባበቅ ሳይኖር በተመደብንበት መኪና በተሰጠን ሰዓት መገኘት ከተጓዦቻችን ይጠበቃል፡፡

 

መካነ ድር፡- የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት ካለፈው ዓመት ሐዊረ ሕይወት በምን ይለያል?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት በርካታ አዲስ ነገሮችን ይዟል በእውነት ለመናገር የአሁኑ ሐዊረ ሕይወት የተደራጃና የተጠናከረ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ለመርሐ ግብሩ ስኬት ሲባል ዝግጅቱ ቀደም ተብሎ ተጀምሯል፡፡ ሰፊ የዝግጅት ጊዜ መኖሩ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ያመቻል ሌላም ባለፈው ዓመት ለመርሐ ግብሩ ሲባል ዝግጅቱ ቀደም ተብሎ ተጀምሯል፡፡  ሌላው ባለፈው ዓመት ባደረግነው ጉዞ የተሰጡን አስተየየቶች ነበሩ፡፡ እነዚያ አስተየየቶች በአሁኑ ጉዞ ተስተካክለውና ታርመው አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ለምክረ አበው የሰጠነው ጊዜ ሰፊ መሆኑም በራሱ አንድ አዲስ ነገር ነው ከሁሉም በላይ የምእመናን ቁጥር በ1ሺሕ ጨምሯል፡፡ ባለፈው ዓመት 3000 የሚሆኑ ተጓዦች ነበሩ አሁን ግን የምእመናን ቁጥር በ1000 ልዩነት 4000 ይሆናል፡፡ የምዝገባው አተገባበርም ቢሆን የተሳለጠና የተመቻቸ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከጅማ፣ ከመቀሌ ከአፋርና ከናዝሬት የመጡ ተጓዦች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከእሩቅ ሀገር ለሚመጡ ምእመናን የአዳር መርሐ ግብር አዘጋጅተናል በአጠቃላይ ጉዞው እስኪጠናቀቅ ድረስ ራሱን የቻለ ጽ/ቤት፣ መደበኛ አገልጋይ፣ መኖሩ፡፡ ትምህርቶች በብሉቱዝና በሲዲ ወጪውን የሚሸፍንልን ካገኘን ለማሠራጨት መዘጋጀታቸው አዲስ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች የዚህን ዓመት ሐዊረ ሕይወት ልዩ ያደርጉታል፡፡

 

መካነ ድር፡- የመነሻ ቦታው የት ነው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡– ከአዲስ አበባ ለሚነሡ ምእመናን 5ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ በማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ምእመናን ደግሞ ባሉበት ርእሰ ከተማ በማኅበረ ቅዱሳን ማእከላት ጽ/ቤት መነሻቸውን ያደርጋሉ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ማስታወስ የምፈልገው ጉዳይ ከአዲስ አበባ ዙሪያ የሚመጡ ምእመናን በዋዜማው መጥተው ማደር አይጠበቅባቸውም፡፡ ከቦታው ቅርበት የተነሣ በዕለቱ ቀደም ብለው ቢነሡ መጋቢት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት መድረስ ይችላሉ፡፡ ከጅማ፣ ከመቀሌ፣ ከአፋርና ራቅ ካለ ቦታ የሚመጡ ምእመናን ግን መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለእነዚህ እንግዶቻችንም በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ መኝታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

 

መካነ ድር፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- እግዚአብሔር አምላክ ሥራችንን እንዲያከናውንልን ምእመናን በጸሎታቸው እንዲያስቡን ቀዳሚው መልእክቴ ነው፡፡ ሌላው መልእክት ይህ ጉዞ ለሥጋዊ ጥቅምና ለትርፍ የተዘጋጀ የጉዞ መርሐ ግብር አይደለም፡፡ 4000 ሰዎችን የሚያስጠልል ድንኳን፣ 4000 ወንበርና 4000 ሳህን ጀኔሬተርና ሞንታርቦ ከአዲስ አበባ ጭነን ነው የምንሔደው የሕክምና ቡድኖች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከእኛ ጋር ይጓዛሉ፡፡ ስለዚህ ከትራንስፓርት ውጭ ከ100,000 ብር በላይ ወጭ ይጠይቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ዶግማ የጠበቁ ትምህርቶች በሲዲ ለማሠራጨትም አቅደናል እነዚህን ሁሉ ወጭዎች ለመሸፈን ማስታወቂያ በማሠራትም ይሁን በተለያየ ዘዴ ጉዞውን እንድንደግፍ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

 

መካነ ድር፡– ስለነበረን ቆይታ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- እኔም ተገቢውን መረጃ በተገቢው ሰዓት እንዳደርስ እድሉን ስለሰጣችሁን በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡

የገዳማውያኑ ጸሎትና አንድምታው /በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/!!

በገብረእግዚአብሔር ኪደ

የካቲት 3/2004 ዓ.ም

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ሲመጣ ለሁሉም እንደሥራው ያስረክባል” /ማቴ.16፡27/ ብሎ ሲናገር እኔም ንግግሩን ስሰማ የድል አክሊልን ከሚቀዳጁ ቅዱሳን ወገን ስላልሆንኩኝ ተብረከረክኩ፡፡ ይህን ፍርሐቴንና ጭንቀቴን ሌሎች ሰዎችም እንደሚጋሩኝ አስባለሁ፡፡ ይህን ሁሉ በልቡ እያሰበ የማይደነግጥ ማን ነው? የማይንቀጠቀጠውስ ማን ነው? ከነነዌ ሰዎች በላይ ማቅን የማይለብስና አብዝቶ የማይጾምስ ማን ነው? ምክንያቱም ይኸን ሁሉ  የምናደርገው ስለ አንዲት ከተማ መገለባበጥ ተጨንቀን ሳይሆን ዘለዓለማዊውን ቅጣትና ትሉ የማያንቀላፋ እሳቱም የማይጠፋውን ነበልባል ለማለፍ ነው፡፡

በየበረሀውና በየገዳማቱ የሚኖሩት አበው ወእማት ይኸንን ቃል ከሌላው ሰው በበለጠ አኳኋን ስለ ገባቸው እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለሁ፤ አደንቃቸውማለሁ፡፡ ምክንያቱም እራታቸውን ከቀማመሱ በኋላ፣ እንደውም እራታቸውን ሳይሆን ምሳቸውን ከተመገቡ በኋላ (ምክንያቱም አብዝተው የሚጾሙና የሚያዝኑ ስለሆነ እራት የሚባል ነገር አያውቁም በዜማ አምላካቸውን ያመሰግኑና መዝሙር ይዘምራሉ፡፡ እናንተም መዝሙሩን መስማት ከፈለጋችሁ ላስታውሳችሁ እና ደጋግማችሁ ዘምሩት፡፡ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን፣ ሥጋ ለባሽን ሁሉ የምትመግብ ቡሩክ እግዚአብሔር ሆይ! መልካሙ ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን፡፡ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ይገባኻል! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህም የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተመላን አድርገን፡፡”

ይህ ዝማሬ በተለይም የመጨረሻው ስንኝ አንክሮ የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም መብል በባሕርይው የድካምና የመወፈር ስሜትን የሚያመጣ ቢሆንም በመነኰሳቱ ዘንድ ግን በነፍስ ላይ ሲያበራና ነገረ ምጽአትን ሲያሳስብ እንመለከተዋለን፡፡ እነዚህ ሰዎች እስራኤል ሰማያዊው መና ከተመገቡ በኋላ ምን እንዳገኛቸው ተምረዋል፡፡ እንዲህ እንደተባለ፡- “የተወደደውን ጥጋብ አቀናጣው፤ ሰባ፤ ወፈረ፤ ሰፋ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ” /ዘዳ.32፡15/፡፡ ዳግመኛም ሙሴ፡- “በበላህና በጠገብህም ጊዜ… እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ” እንዲል /ዘዳ.6፡11-12/፡፡

እስኤላውያን የተወደደውን ምግብ ከበሉ በኋላ አሳፋሪ ነገርን ለማድረግ ጀመሩ፡፡

እናንተስ ይኼን የመሰለ ነገር በእናንተ ዘንድ እንዳይሆን ትገነዘባላችሁን? ምንም እንኳን ለድንጋይ፣ ወይም ለወርቅ ምስል በግ ወይም ከብት ባትሠዉም የራሳችሁን ነፍስ ስለሠዋችሁ መዳናችሁን እንዴት እንደምታጥዋት እና እንዴት ያለ ቁጣ እንደሚደርስባችሁ ተመልከቱ፡፡ እነዚህን መነኰሳት ስንመለከት ይኼን የመሰለ ውድቀት በእነርሱ እንዳይደርስ በመፍራት ምግባቸውን ከተመገቡ በኋላና በጊዜ ጾማቸው መካከል ሁሉ ስለዚያች አስፈሪ ቀን እና ስለ አስጨናቂው የፍርድ ወንበር ያስባሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ መነኰሳት እንኳን በጾም ሌሊቱን ሁሉ በመሬት ላይ ተኝተው እንቅልፍን በማጣት በንቃትና ማቅን በመልበስ እልፍ ጊዜ እየደጋገሙ ስለዚያች ቀን በማሰብ የሚተጉ ከሆነ የምግብ ክምር በጠረጴዛችን ላይ ከምረን ስንጀምርም ስንጨርስም የማንጸልይ ትሩፋተ ሥጋ ትሩፋተ ነፍስ የሌለን እኛስ ይኼን የምናደርገው መቼ ይሆን?

ስለዚህ ምግበ ሥጋ ብቻ በምግብ ጠረጴዛች እንዳንከምር ይኼን የመሰለ ጣዕመ ዝማሬ እና ትርጕሙን እንናገር፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቅሙን እየተመለከትን በማዕዳችን ዙርያ እንድናመሰግን እና ለሆድ ብቻ ብለን የምናደርገውን ሩጫ በማስወገድ የመላእክትን ሥርዓት ወደ ቤታችን እናስገባ፡፡ ከመብላታችሁ በኋላ መልካም እንዲሆንላችሁ ይኸን ታደርጉ ዘንድ ይገባችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ብያንስ እንኳን ለምነግራችሁ ቃል ፈቃደኞች ስላልሆናችሁ ይኸንን ጣዕመ ዝማሬ አድምጡና ከዛሬ ጀምራችሁ ከማዕዳችሁ በፊትም ይሁን በኋላ ምስጋናን ተለማመዱ፡፡
“ብሩክ እግዚአብሔር ሆይ!” ነው ያሉት፡፡ እነዚህ መነኰሳት የሐዋርያትን ትእዛዝ ሲፈጽሙ እንመለከታቸዋለን፡፡ ሐዋርያት እንዲህ ብለው ነበርና፡- “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” /ቈላ.3፡17/፡፡

ሲቀጥሉ ደግሞ የእግዚአብሔር መግቦት ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለሁል ጊዜ እንደሆነ ሲናገሩ፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን” ነው ያሉት፡፡ ይኼን ትእዛዝ ደግሞ፡- “እግዚአብሔር ምግባችሁን ይሰጣችኋልና አትጨነቁ” ማለት ነው፡፡ እናንተ ከአንድ ንጉሥ ጋር እየኖራችሁ ንጉሡ ምግባችሁን ሁሉ ከግምጃ ቤት እያወጣ የሚሰጣችሁ ከሆነ በጭራሽ ስለምትበሉት ነገር አታስቡም፤ ምግብ እንደሚሰጣችሁ ተስፋችሁን ሁሉ በንጉሡ ላይ ጥላችሁታልና፡፡ እንግዲያስ ከዝናብም በላይ በእናንተ ላይ እነዚህን ነገሮች ሊያዘንም የሚችለውን እግዚአብሔር በበለጠ አኳኋን ተስፋ እያደረጋችሁ ስለ አንዳች ነገር ልትጨናነቁ አይገባችሁም፡፡ አዎ! እነዚህ መነኰሳት ራሳቸውንና በእግራቸው ለሚተኩት ደቀመዛሙርቶቻቸው ያስተምሩ ዘንድ ይኼን መዝሙር ደጋግመው ይዘምራሉ፡፡

ከዚህ በኋላ እነዚህ መነኰሳት ለራሳቸው ብቻ ያመሰግናሉ እንዳይባል፡- “ሥጋ ለባሽንም ሁሉ የምትመግብ” ይላሉ፡፡ ስለዚህ በዓለም ሕዝብ ፈንታ እነርሱ ያመሰግናሉ፤ እንደ ዓለም ሁሉ አባቶች እግዚአብሔርን ይባርካሉ፤ ጽኑ ፍቅረ ቢጽን /የወንድም ፍቅርን/ ይለማመዳሉ፡፡ ወንድሞቻቸውን እግዚአብሔር ስለመገበላቸው ያመሰግናሉ እንጂ አይጠሉም፡፡

እንግዲህ በቀደሙትና በእነዚህ የምስጋናቸው ቃል እንዴት አመስጋኝነትን፣ እንደገለጹና ዓለማዊ ምቾትን እንዳራቁ ተመለከታችሁን? እግዚአብሔር ሥጋ ለባሹን ሁሉ የሚመግብ አምላክ ከሆነ የሚያመሰግኑትን ደግሞ የበለጠ ይመግባቸዋል፤ በዓለም ኑሮ ለተወጠሩት እንኳን የሚመግብ ከሆነ ከዓለማዊ ምኞት ራሳቸውን ላራቁ ደግሞ ይበልጥ ይመግባቸዋል፡፡

ይኼን ግልጽ ያደርግ ዘንድ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ከብዙ ድንቢጦች እናንተ አትበልጡምን?” /ሉቃ.12፡7/፡፡ በዚህም እምነታችንን በሀብትና በምድር ፍሬ እንዳንጥል አስጠንቅቆናል፡፡ ምክንያቱም ምግባችንን የሚሰጡን እነዚህ ሳይሆኑ እግዚአብሔር ነውና /ዘዳ.8፡3፣ ማቴ.4፡4/፡፡…

ተሐራምያኑ ልመናቸውን ይቀጥሉና አምላካቸውን፡- “ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን” ይሉታል፡፡ ይህን ማለታቸውስ ምን ማለት ነው? በዚህ ዓለም ደስታ ይሆን? በፍጹም! ይኸን የለመኑ ቢሆን ኖሮ ራሳቸውን በየፍርኩታው፣ በየገደሉ፣ በየበረኻው ማቅ ለብሰው ባልተመላለሱ ነበር፡፡ ስለዚህ እየለመኑት ያለው ደስታና ሐሴት ከዚህች ዓለም ደስታ ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት የሌለው ይልቁንም የመላእክትን ሐሴት የሆነውና ሰማያዊውን ደስታ ነው፡፡

አጠያየቃቸውን እንኳን ተመልክተን ከሆነ ቀለል ባለ አገላለጽ “ስጠን” ሳይሆን “ሙላልን”፤ “እኛን” ሳይሆን “ልባችንን” ነው የሚሉት፡፡ የልብ ሐሴት ማለት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆኑት ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም የመሳሰሉ ናቸውና /ገላ.5፡22/፡፡

ስለዚህ ኀጢአት ሐዘንን ስለምታመጣ ያለዚህም ደስታ ስለማይገኝ በዚሁ ደስታ አማካኝነት ጽድቅን እየለመኑ ነው ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው፡- “እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጐ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” ይላል /2ቆሮ.9፡8/፡፡ እነዚህ መነኰሳት በዚህች አጭር ምስጋናቸው “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” የሚለውን የወንጌሉን ቃል እንደ ተገበሩትና እነዚህን ሁሉ ለመንፈስ ፍሬ እንዴት እንደ ፈለጓቸው ተመልከቱ፡፡ ምክንያቱም፡- “በጐው ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ ልብ በሉ! “ሥራችንን እንፈጽም ዘንድ፣ በጐ ምግባርን እንሠራ ዘንድ” ብቻ ሳይሆን “ይበዛልን ዘንድ” ነው እያሉ ያሉት፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ዘንድ ትንሽዋን ፈቃድ ሲፈልግብን እነዚህ መነኰሳት ግን ከዚህም በላይ የሆነ መታዘዝን ነው ያሳያት፡፡ ይህ አባባል የመልካም ባሮች እና ራሳቸውን የሚገዙ የጠንቃቃ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡

በመቀጠል ይኸን መልካም ሥራ የሚሠሩት በራሳቸው አቅም እንዳልሆነ እና ደካማነታቸውን ለመግለጽ፡- “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ገር ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን” ይላሉ፡፡ በምስጋና የጀመሩት ልመናቸው በምስጋና ያሳርጉታል፡፡

ከዚህ በኋላ አዲስ ምስጋና የጀመሩ ቢመስሉም ያንኑ ምስጋናቸውን ተከትሎ የሚመጣ ተጨማሪ ሐሳብ ይቀጥላሉ፡፡ ይኼም ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶቹን ሲጀምር፡- “እንደ አባታችንና እንደ አምላካችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፡፡ ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን አሜን” ገላ.4፥5 ብሎ በምስጋና ጀምሮ ተመልሶ ወደ መጀመርያው ሐሳብ እንደሚመለስ የመሰለ ነው፡፡ በሌላ ቦታም ቅዱስ ጳውሎስ ፡- “በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው አሜን” ሲል ቃሉን ፈሞ ሳይሆን እንደገና እንደጀመረ /ሮሜ.1፡25/፡፡

እንግዲያስ እኛም እነዚህን መነኰሳት ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደገና ጀመሩ ብለን የምንወቅሳቸው አይደለንም፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያቱ በምስጋና ጀምረው በምስጋና ጨርሰው ዳግመኛ መልእክታቸውን እንደሚቀጥሉ ሁሉ እነዚህ መነኰሳትም ይኼን በመሰለ መንገድ ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡

ስለዚህ፡- “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እገዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና” ይላሉ፡፡

ምስጋናን ማቅረብ ያለብን ስለ ትልልቅ ጉዳዮቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ጥቃቅኑም ጭምር መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መነኰሳት የተባሕትዎን ኑሮ የሚንቁትን ሁሉ ያሳፍሩ ዘንድ ስለ ጥቃቅኑም ጭምር ያመሰግናሉ፡፡ እነዚህ መነኰሳት መናፍቃን እንደሚያወሩት  ማለትም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ከመጥላት ወይም ጋብቻን ከማንቋሸሽ አንጻር ሳይሆን ቁጥብነትን፣ ራስን መግዛት ይለማመዱ ዘንድ ይኼን ያደርጋሉ፡፡

ምስጋናቸው ደግሞ እግዚአብሔር ከዚህ አስቀድሞ በሰጣቸው ሁሉ የተገደበ ሳይሆን ፡- “በመንፈስ ቅዱስ ሙላን” እያሉ ወደ ሰማያዊ መሻት እንደሚወጡና ያንን ሕይወት እንደሚናፍቁ ልብ በሉ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔር ካልረዳው በስተቀር ማንም ሰው ታላለቅ ሥራዎችን መሥራት አይችልም፤ ቢሠራ እንኳን ታላላቅ መሆን ያለባቸውን ያህል ታላላቅ አይሆኑም፡፡

ስለዚህ፡-“ በጐ ሥራችን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” እንዳሉ ሁሉ አሁንም “በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በቅዱስ መንፈስህ ሙላን” ይላሉ፡፡

እንግዲህ ስለአሁኑ ዓለም ኑሮዋቸው ጸሎት ሳይሆን ምስጋናን ብቻ እንዳቀረቡና ከመንፈስ ቅዱስ ለሚሆነው ነገር ግን ጸሎትም ምስጋናም እንዳቀረቡ ተገነዘባችሁን? ጌታም ያስተማረው ይኼንኑ ነበር፡- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” እንዲል /ማቴ.6፡33/፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ መነኰሳት ዘንድ ያለውን ከፍተኛ መልካምነት ልብ በሉ፡፡ ምክንያቱም ሲጸልዩ፡- “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ እንዲህ ማለታቸውም ነበር፡- “በብዙዎች ዘንድ የሚደርስብን ማንኛውም የሚያሳፍር ነገር አያስጨንቀንም፤ ሰዎች በእኛ ላይ የወደዱትን ሁሉ ቢናገሩ፣ ቢስቁብን፣ ቢታበይቡን ለእኛ ቁብም አይሰጠንም፡፡ የእኛ ጭንቀትና ናፍቆት በፊትህ የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ ብቻ ነው፡፡” በዚሁ ጸሎታቸውም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ደግሞም መንግሥቱን ለሚያወርሳቸው ያዘጋጀውን መልካሙን ሁሉ እና የእሳቱን ባሕር በሚገባ አስቀምጠውታል፡፡

ሲጸልዩም፡- “እንዳንቀጣ” ሳይሆን “በአንተ ፊት የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ” ነው ያሉት፡፡ ይኸውም እኛ ሁላችን ከገሃነም አስፈሪነት ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት መቆምን እንድንፈራ ሲያስተምሩን ነው፡፡

ታድያ እነዚህ መጻተኞች፣ ስደተኞች፣ የበረሀው ከዚያም በላይ ደግሞ የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች የሆኑት እነዚህ መነኰሳት ምን ያህል እንደጠቀሙን ተመለከታችሁን? እኛ በዚህ ምድር ሐሳብ ስንፏቀቅ እነርሱ ግን በተቃራኒው ከዚህ ዓለም ተቃራኒ በመቆም የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች ሆነዋል፡፡

ዝማሬአቸውን ከጨረሱ በኋላ ስለ ኃጢአታቸው በማዘንና በማያቋርጥ የእንባ ጅረት ካለቀሱ በኋላ ለቀጣዩ ቀን ራሳቸውን እንደ አዲስ ይዘጋጁ ዘንድ ትንሽ ዕረፍት ይወስዳሉ፡፡ እንደገና ተነሥተውም ሲያመሰግኑ ደግሞም መዝሙረ ዳዊታቸውን እየደገሙ ሌሊትን ቀን ያደርጉታል፡፡
የሚደንቀው ነገር ደግሞ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ የተፈጥሮ ደካማነታቸውን በትጋት በማሸነፍ ይኼን ራስን የመካድ ኑሮ የሚፈጽሙት ሴት መነኰሳየያትም ናቸው፡፡

እንግዲያስ እኛም ወንዶች ስንሆን የእነዚህን ሴት መነኰሳይያትን ትጋት እየተመለከትን በራሳችን የምናፍር እንሁን፡፡ እንደ ጥላ ከሚያልፉት፣ እንደ ሕልም ከሚረሱትና እንደ ጢስ ከሚተጉት ከዚህኛው ዓለም ጉዳዮች ጋር እንታሠር፡፡ ብዙዎቻችን በዚሁ ድንዛዜ ተይዘን ዕድሜአችን ያልቃልና፡፡

የአብዛኞቻችን የዕድሜአችን የመጀመርያው አጋማሽ በዚሁ ስንፍና የተሞሉ ናቸው፡፡ ወደ ሁለተኛው የዕድሜአችን አጋማሽ ከገባን በኋላም ትንሽ ደስታን አጣጥመን መልሰን በርኩሰት፣ በድካምና በሌሎች የማይረቡ ነገሮችን እንታነቃለን፡፡

ስለዚህ ሌባ የማይሰርቃቸውንና ዘላለማውያን የሆኑትን /የማያልፉትን/ ሀብታት እንዲሁም ማርጀት (ሽምግልና) የሌለበትን ሕይወት ትሹ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡

አንድ ሰው በከተማ ውስጥ ሆኖም እንደ እነዚህ መነኰሳት ራስን መግዛት መለማመድ ይችላል፡፡ አዎ! ሚስት አግብቶ፣ በቤትና በኑሮ ጉዳዮች የተጠመደ ሰው እንኳን መጸለይ፣ መጾምና ስለ ኃጢአቱ ማልቀስ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ከሐዋርያት የተማሩትም ምንም እንኳ በከተማ ቢኖሩ በበረሃ የሚኖሩትን ሰዎች ንጽሕናና ቅድስና ይዘው ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ብዙ ሠራተኞች የነበሯቸውም እንዲሁ አድርገዋል፡፡

ነቢያቱም እንዲሁ ሚስትና ቤት ነበራቸው እንደ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤልና ሊቀ ነቢያት ሙሴ፡፡ እነርሱ ከበጎ ምግባርና ትሩፋት የተነሣ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡

እንግዲያስ እኛም እነዚህን ሁሉ እየመሰልናቸው እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ እናመስግን፤ በጊዜውም ያለጊዜውም በመዝሙር እንቀኝለት፤ ትዕግሥትንና መልካም ምግባርን ሁሉ ገንዘብ እናድርግ፡፡ በገዳማውያኑ የተለመደውን ራስን የመግዛት የሕይወት ልምምድ ወደ ምንኖርበት የከተማ ሕይወት በማምጣት በእግዚአብሔር ፊት የተገባን ሆነን እንገኝ፡፡ ብርሃናችንም በሰው ፊት ይብራ፡፡ ሊመጣ ያለውን በጎ ስጦታ ሁሉ እንውረስ፡፡

ይህንን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ያድለን፡፡ ምስጋና ክብርና ለእርሱ በእርሱ ለአብ ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!