dsc01723

የ2004 የከተራ በዓል አከባበር ከዓድባራቱ እሰከ ጃንሜዳ፡፡

ጥር 11/2004ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ዐበይት በዓላት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ይህንም በዓል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ፤ በማእከለ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከዋዜማው ከጥር 10 ጀምሮ በደመቀ ሁኔታ በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ፤ የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መሠረት በማረድግ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ ታቦታት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በካህናትና ዲያቆናት፤ እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራንና ምእመናን በዝማሬ በመታጀብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ታቦት ማደሪያ በማምራት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሔድ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ማምራቱን ያበሥራሉ፡፡ ‹‹ያን ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ናዝሬት መጣ ዮሐንስም በዮርዳኖሰ ወንዝ አጠመቀው›› እንዲል፡፡/ማቴ.3፡1/

 

dsc01723

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሥራቿን መድኀኔዓለም ክርስቶስን ለዓለም የምትሰብክበት፣ ከእርሱም ያገኘችውን፣ ይህም ዓለም እንደሚሰጠው ያልሆነውን፣ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ትሕትና ለዓለሙ ትሰብክበታለች፡፡ እንዲሁም ለአገራችን በጎ ገጽታን በመፍጠር ረገድ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ተደንቀው የሚያዩትና አንዳንዶች ልባችውን ለእውነት ክፍት ያደረጉ የሚያምኑበት በመስተንግዶው የሚደመሙበት በመሆኑ ሃይማኖታዊ በዓሉን በልዩ ትኩረት ታከብራለች፡፡

 

ለዚህ በዓል አከባበር ቤተ ክርስቲያን ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ታቦታት በሰላም ወጥተው dsc01724በሰላም እንዲመለሱ ጉልህ ሚናዋን ትወጣለች፡፡ በዚህ መሠረት  በየአጥቢያው የሚገኙ ወጣቶች ከክብረ በዓሉ ቀደም ብሎ ለሓላፊነት በመሰብሰብ ቅዱሳት ሥዕላትን በታቦታት ማረፊያዎች በማዘጋጀት፣ በተለያዩ ኅብረ ቀለማት ያሸበረቁ ጨርቆችን /ባነሮችን/፤ የኢትዮጵያ ባንዲራን በየአብያተ ክርስቲያናቱ አደባባዮች በመስቀል፣ የቤተ ክርስቲያናትን ቅጥርና አስፋልት በማጽዳት፤ለታቦት ክብርን በመስጠት ምንጣፎችን በማንጠፍ በዓሉን ያደምቁታል፡፡

 

‹‹ያሰባሰበንና ያነሳሳን እግዚአብሔር ነው፡፡ በራሳችን ያደረግነው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ይህንን ክብረ በዓል ከዐራት ዓመታት ወዲህ ነው በዚህ ሁኔታ በማክበር ላይ የምንገኘው፡፡ በየወሩ ከእያንዳንዱ አባል ዐሥር ዐሥር ብር በማዋጣት፤ ከምእመናን በመጠየቅ፤ እንዲሁም በጎ አድራጊ ምእመናንን በማነጋገር የገንዘብ ድጋፍ  በማድረግ እናሰባስባለን፡፡ ባገኘነው ገንዘብ የኢትዮጵያ ባንዲራን፤ የተለያዩ ኅብረቀለማት ያላቸው ጨርቆችን በchurchesማዘጋጀት፤ ምንጣፎችን በመግዛት  በቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን የበኩላችን እንድንወጣ ከበረከቱ ተሳታፊ እንድንሆን እያገለገልን እንገኛለን›› በማለት ስሜቱን ያካፈለን ከመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስና  የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያናት አጥቢያ፤ የስድስት ኪሎ አካባቢ ወጣቶች መካከል አንዱ ወንድም ነው፡፡ በየአጥቢያው ተዘዋውረን የበዓሉን ቅድመ ዝግጅት ለመቃኘት በሞከርንበት ወቅት ያገኘናቸው ወጣቶች የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ገዳም አጥቢያ ወጣቶች፤ የቅድስት ማርያም ቤዛዊት ዓለም ማኅበር አባላት፤የዐራት ኪሎ አካባቢ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያኒቱንና አደባባዮችን በማስጌጥ ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ስለ ዝግጅቱም የተሰማቸውን ሲገልጹ  ነበር፡፡ በተጨማሪም ‹‹ከፖሊስ አባላት ጋር በመቀናጀት ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግና በመወያየት  አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡›› በማለት የገለጹ ሲሆን ባስተላለፉት መልእክትም ወጣቶች የእነሱን አርአያነት በመከተል ቤተ ክርስቲያን ከእነሱ የምትጠብቀውን አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም እምነታቸውን አጥብቀው እንዲይዙ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

‹‹ኀዲጎ ተስዐ ወተስዐተ ነገደ››
ምእመናን ከየቤታቸው ለበዓሉ በሚገባው ልብስ አሸብረቀው ወጥተዋል፡፡ እናቶቻችን ከየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰሙትን የሊቃውንት አባቶቻችን ወረብ ተከትልው፣ የታቦታቱን መውጣት በመጠባበቅ እልልታቸውን ያሰማሉ፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ዝግጅቶቻቸውን አጠናቅዋል፣ የዝማሬ ልብሳቸውን ለብሰዋል፡፡ የሻይ የእረፍት ሰዓታቸውን በመጠቀም ከየመሥሪያ ቤታቸው በር ላይ የታቦታትን ማለፍ በእነርሱም መባረክን ዐይናቸው ተስፋ እያደረገች ታቦታቱ የሚመጡበትን አቅጣጫ ያማትራሉ፡፡

begena04
የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራንም ለወትሮው በሚታወቁበት፤ እኅቶች በሙሉ ነጭ ልብስ ወንድሞችም በነጭ ልብስና በቀይ ጃኖ ደምቀው የመንግሥተ ሰማያት ሙሽራ መስለዋል፡፡ ዘንድሮ ግን ሁሉንም ያስደመመ ነገር ይዘው ቀርበዋል፡፡ በርካታ ምእምናንን ዐይናቸውን ማመን እንዳልቻሉ ያስታውቃሉ፡፡ ‹‹በውኑ ይሄን ያህል በገና ደርዳሪ አለን?›› የሚሉ ይመስላል፡፡ አንዳንዶቹም በደስታ ፊታቸው እያበራ በተመሰጦ ‹‹እመቤቴ በምልጃሽ መድኀኒቴ ነሽ›› በሚለው መዝሙር ከበገና ደርዳሪዎቹ ጋር ወላዲተ አምላክን ያመሰግናል፤ ይማጸናል፡፡ ቁጥራቸው ወደ 150 የሚጠጋ የቅዱስ ዳዊት የበገና ቤተሰብ አባላት በገናችውን ወድረው ለዝማሬ ማየት በእውነት ልብን በሐሴት ይሞላል፡፡ ዐይንን ሳይነቅሉ ዐሳብን ሣይከፍሉ ለመከታተል ለመዘመርም ያስገድዳል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርትና ሥልጠና ማእከልን በርቱ ቀጥሉበት ያስብላል፡፡

ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር በተለይም በጃንሜዳ ከየአድባራቱ ዐሥራ ሦስት ታቦታት በአንድነት የሚገኙበት በመሆኑ ሕዝቡን ለመባረክ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፤ በመዘምራንና ምእመናን በመታጀብ ጉዞ የተጀመረ ሲሆን አመሻሽ ላይ ጃን ሜዳ ሊደርሱ ችለዋል፡፡ የየሰንበት ት/ቤቶቹ መዘምራን፤ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት ያሬዳዊ ዜማ እየዘመሩ፤ ምእመናን በእልልታና በሸብሸባ ታቦታቱን በማጀብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ ዕለቱን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ‹‹የዛሬው በዓላችን በሃይማኖታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ጸጋና በረከት የምናገኝበት፤ ሁላችንም በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የምንወለድበት፤ ልጅነት የምናገኝበት በዓል ነው፡፡›› በማለት  ገልጸዋል፡፡

በዓሉን በተመለከተ ያነጋገርናቸውና ከፈረንሳይ ሀገር የመጡት ቱሪስት በዓሉን በመገረም እየተከታተሉ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ የራሺያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያውያን በጣም የተለያችሁ ናችሁ ማለት ይቻላል ፡፡ እንደዚህ ዓይነት የበዓል አከባበር ዐይቼ አላውቅም፡፡ በጣም አስደሳችና ታላቅ በዓል ነው፡፡ ሕዝቡ በእልልታና በዝማሬ፣ በሽብሸባና በጭብጨባ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ፍጹም አስደሳች ነው፡፡›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ የኦሃዮ ስቴት ኮሎምበስ ከተማ የደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑት ቀሲስ ያሬድ ገ/መድኅን  dsc05178ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን ከረጅም ጊዜ በኋላ በሀገራቸው ማክበር በመቻላቸው መደሰታቸውን፤ ወጣቶች ለታቦታቱ ምንጣፍ በማንጠፍ የሚያደርጉት ጥረት እንዳስደነቃቸው የገለጹ ሲሆን፤ በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን  የሚያደርጉት ጥረት በተመለከተ ‹‹እኛ እምነታችንን ለዓለም የምናስተዋውቅበት ጊዜ እየደረሰ ነው፡፡ በውጭው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት መተከላቸው፣ በዓላትን በጋራ ማክበራችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ለዓለም ሕዝብ ማስተዋወቅ የጀመርንበት ወቅት እንደሆነ ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ከፈቀደ እነሱም ተጠምቀው የማይመለሱበት፤ የቤተ ክርስቲያን ልጆች የማይሆኑበት ምክንያት አይኖርም ›› በማለት ወደፊት ብዙ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በበዓሉ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ከውጭ ሀገር በዓሉን ለመከታተል የመጡ እንግዶችና ቱሪስቶች የተገኙ ሲሆን  የዓመቱ ተረኛ የሆነው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን ዕለቱን በማስመልከት ያሬዳዊ ዝማሬ ‹‹ተሰአልከ እግዚኦ ምደረከ ሃሌ ሉያ ወረደ ወልድ እም ሰማያት ውስተ ምጥማቃት በፍስሐ ወበሰላም›› በማለት አቅርበዋል፡፡ በብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገሪማ ሰፋ ያለ  ቃለ እግዚአብሔር  ተሰጥቷል፡፡ በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ ታቦታቱ ወደ ተዘጋጀላቸው ማረፊያ ቦታ ገብተዋል፡፡  

ወስብሐት ለእግዚአብሔር