ግንቦት 11፣2003ዓ.ም
ቅዱስ ሲኖዶስ በ1991 ዓ.ም ባወጣው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስና ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ የሚናገሩ ምዕራፎች እና አንቀጾችን አቅርበናል፡፡
ምዕራፍ ሁለት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
አንቀጽ 5
የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና /የበላይነት/
1. በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት ነው፡፡
2. ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ሁሉ የበላይ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሆነ ሕጐችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማውጣትና የዳኝነት ሥልጣን አለው፡፡
አንቀጽ 5
የቅዱስ ሲኖዶስ ዓላማ
1. ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ አገልግሎቱም የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ፣
2. የሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዳይፋለስ ለመጠበቅና ለማስጠበቅ፣
3. ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለመጠበቅና ለማስፋፋት፣
4. ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋትና ለማጠናከር፣
5. ወጣቶች ከአበው የተቀበሉትን ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው በትምህርትና በሥነ ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ ሰንበት ትምህርት ቤትን ለማጠናከርና ለማስፋፋት፣
6. የሰው ዘር ሁሉ ከርሃብ፣ ከእርዛት፣ ከበሽታና ከድንቁርና ተላቆ በሰላምና በአንድነት በመተሳሰብና በመረዳዳት በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖር ማስተማርና መጸለይ፣
አንቀጽ 7
የቅዱስ ሲኖዶስ ሥልጣንና ተግባር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚከተለው ሥልጣንና ተግባር ይኖረዋል፡፡
1. ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት ይመራል፣ ይጠብቃል፡፡
2. ሕገ ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት ሕጎችን፣ ደንቦችንና ልዩ ልዩ መመሪያዎችን ያወጣል፣ ያሻሽላል፡፡
3. የቤተ ክርስቲያኒቱን አጠቃላይ የምጣኔ ሀብታና የሙዓለ ንዋይ መመሪያዎችን /ፖሊሲዎችን/ ይወስናል፡፡
4. ዓመታዊውን በጀት ያጸድቃል ተግባራዊነቱንም ይቆጣጠራል፡፡
5. የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲሁም የጽሕፈት ቤቶችን ደረጃና ተጠሪነት ይወስናል፡፡
6. የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደርና አገልግሎት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት እንዲመራ ያደርጋል፡፡
7. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት በአገር ውስጥና በዉጭ አገር እንዲስፋፋ ያደርጋል፡፡ ትምህርት ቤቶችንም ያቋቁማል፡፡
8. የክርስቶስን ወንጌለ መንግሥትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ያስተምራል ያስፋፋል፡፡
9. በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር አዲስ የሀገረ ስብከት ጽ/ቤትና መንበረ ጵጵስና እንደ አስፈላጊነቱ ያቋቁማል፡፡
10. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነት ያስፋፋል ያጠናክራል፡፡
11. በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከትና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት የሚመደቡና እንደዚሁም በአገር ውስጥ የሚሰጠውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ተምረው የውጭውን ትምህርት መማር የሚችሉ ካህናትን እየመረጠ እንዲላኩ ያደርጋል፡፡
12. ማንኛውም ሰው ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክሎ ለሥራም ሆነ ለጉብኝት ወደ ውጭ አገር በሚላክበት ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ እየፈቀደ ነው፡፡
13. ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤ እየወሰነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት እንዲመረጡና እንዲሾሙ ያደረጋል፡፡ እንዲሁም ሊቃነ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በየሀገረ ስብከቱና በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ይመድባል በበቂ ምክንያት ያዘዋውራል፡፡
14. በቋሚ ሲኖዶደስ የሚያገለግሉ ጳጳሳትን በየሦስት ወሩ እየመደበ እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡
15. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የሚመደቡትን
ሀ. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ
ለ. የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ
ሐ. የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቱ ም/ሥራ አስኪያጅ
መ. የልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር
ሠ.የውጭ ጉዳይ መምሪያ ሓላፊ
ረ. የልዩ ልዩ ሥራ ዘርፎች ቦርድ አባላት እየመረጡ እንዲሾሙ ያደርጋል፡፡
16. ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች የሚቀርቡትን አጀንዳዎች ያጸድቃል እንደአስፈላጊነቱም ያሻሽላል፡፡
17. ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ ለጥፋተኞችና ለበደለኞችም ምሕረትና ይቅርታ የመስጠት ሥልጣን የቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡
18. በዚህ ሕግ ባልተካተቱ በማናቸውም በቤተ ክርስቲያኒቱ ጉደዮች ላይ ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡
አንቀጽ 8
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
1. በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ፓትርያርክ፣ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት ሆነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከትና በልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች የተሾሙ ሁሉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ናቸው፡፡
2. ከፓትርያርኩ ጀምሮ እያንዳንዱ ሊቀ ጳጳስ፣ ጳጳስና ኤጲስ ቆጶስ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡
3. የቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት ዕድሜ ልክ ይሆናል፡፡
4. አንድ የቅድስ ሲኖዶስ አባል ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚያፋልስ ሆኖ ከተገኘ ከአባልነቱ ይሠረዛል፡፡
5. ይህም የሚሆነው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ነው፡፡
6. በሃይማኖትም ሆነ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተከሰሰ የሲኖዶስ አባል በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቀርቦ ራሱን የመከላከል መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡
7. አንድ የሲኖዶስ አባል ስለራሱ ጉዳይ በሚታይበት ስብሰባ ላይ በአባልነት መገኘት አይችልም፡፡
አንቀጽ 9
የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ
1. የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በፓትርያርኩ ሰብሳቢነት ይመራል፡፡ ፓትርያርኩ በልዩ ልዩ ምክንያት ጉባኤውን መምራት ባይችል ከአባላቱ መካከል እሱ የሹመት ቅድምና ያለውን አባት በመወከል ስብሰባው ሊመራ ይችላል፡፡
2. ከዚህ በታች ከተመዘገቡት በሦስት ምክንያቶች ካልሆነ በቀር ፓትርያርኩ ርዕሰ መንበር ያልሆነበት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ሊካሔድ አይችልም፡፡
ሀ. ፓትርያርኩ በዕርጅናና በጤና ጉድለት ምክንያት ጉባኤውን የሚመራ አባት መወከል ካልቻለ፣
ለ. የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ቀኖና በተመለከተ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንዲደረግ የሲኖዶሱ አባላት ሲጠይቁት ፈቃደኛ ሳይሆን ከቀረ፣
ሐ. ስብሰባው ፓትርያርኩን የሚመለከት ጉዳይ ከሆነ በፍትሕ መንፈሳዊ መሠረት ይፈጽማል፡፡
3. ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ፓትርያርኩ ጉባኤውን መምራት ካልቻለ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በተመረጡ የሹመት ቅድምና ባለው አንድ አባት ስብሰባው ሊካሔድ ይችላል፡፡
አንቀጽ 10
የቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥርዓት
1. ፍትሕ መንፈሳዊ በአምስተኛው አንቀጽ ቁጥር 164 በሚያዝዘው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ ያካሒዳል፡፡ የስብሰባውም ጊዜ፣
ሀ. የመጀመሪያው ጉባኤ በየዓመቱ ጥቅምት 12 ቀን
ለ. የሁለተኛው ጉባኤ ትንሣኤ በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን /በርክበ ካህናት/ የሚካሔደው ነው፡፡
2. አስቸኳይና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም፣
ሀ. ቅዱስ ፓትርያርኩ ወይም ቋሚ ሲኖዶስ በሚያደርጉት ጥሪ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሊካሔድ ይችላል፡፡
ለ. ከጠቅላላው አባላት ከሦስት ሁለት እጁ የሚሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ምልዓተ ጉባኤ እንዲደረግ በጠየቁ ጊዜም ጥሪ ሊደረግና ስብሰባው ሊካሄድ ይችላል፡፡
3. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚባለው ከዓቅም በላይ የሆነ ዕክል ካላጋጠመ በቀር መላው አባላት የተገኙበት ጉባኤ ሲሆን ነው፡፡
4. በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ በሕመምና በልዩ ልዩ ከዓቅም በላይ በሆነ ምክንያት አንዳንድ አባላት ባይገኙ፣
ሀ. ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በሚመለከት ጉዳይ ከጠቅላላው አባላት ከአራት ሦስት እጅ የተገኙ ከሆነ፣
ለ. አስተዳደርን በሚመለከት ጉዳይ ከጠቅላላው አባላት ከሦስት ሁለት እጅ የተገኙ ከሆነ ነው፡፡
5. ቅዱስ ሲኖዶስ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ፣
ሀ. አስተዳደርን የሚመለከት ጉዳይ ከሆነ ከተገኙት አባላት መካከል ከግማሽ በላይ በሆነ ድምጽ የተደገፈው ሐሳብ ያልፋል፡፡
ለ. አንድን ጉዳይ ለመወሰን የአባላቱ ድምፅ እኩል በኩል ከሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያለበት ያልፋል፡፡
ሐ. ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከት ከሆነ በሙሉ ድመፅ ያልፋል፡፡
ምዕራፍ አራት
የኢትዮጵያ ፓትርያርክ
አንቀጽ 13
ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ
1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት ተመርጦ ይሾማል፡፡
2. ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ በሚወስነው ቁጥር መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል፣
3. ለፓትርያርክነት የሚመረጡት ዕጩዎች ከሊቃነ ጳጳሳት ከጳጳሳትና ከኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሲሆን ብዛታቸው ከሦስት ያላነሡ ከአምስት ያልበለጡ ይሆናል፡፡
4. አስመራጭ ኮሚቴው እጩዎችን ጠቁሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀርባል፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ምርጫው እንዲካሔድ ይደረጋል፡፡
5. መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች የአድባራት አስትዳዳሪዎች ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በዕድሜ ከሠላሳ ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምእመናን ተወካዮች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ22 አስከ 30 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤው የሚወከሉት ከአንድ ሀገረ ስብከት አሥራ ሁለት ሆነው በሥጋወደሙ የተወሰኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው፡፡
6. የምርጫው አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይሆናል፡፡
7. የተመረጠው ፓትርያርክ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትንና ቀኖናዋን ሊጠብቅና አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊያስተዳድር ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡
8. ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያወጣል፡፡
አንቀጽ 14
የፓትርያርኩ የማዕረግ ስምና መንበር
1. ፓትርያርኩ ከተሾመበት ቀን ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እገሌ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ይባላል፣ ስሙም በመላዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት ይጠራል፡፡
2. ፓትርያርኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጨ አገር ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን መንፈሳዊ አባት ነው፡፡
3. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበር በአዲስ አበባ ከተማ በቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ነው፡፡
አንቀጽ 15
የፓትርያርኩ ሥልጣንና ተግባር
1. ፓትርያርኩ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሃይማኖትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፣ ያስጠብቃል፡፡
2. በዚህ ሕግ አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶስን ጉባኤ በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡
3. ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 እና በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 13 መሠረት ፓትርያርኩ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር ሆኖ ኤጲስ ቆጶሳትን ይሾማል፣ እንዲሁም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ሲስማማበት ለብፁዓን ጳጳሳት የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ይሰጣል፡፡
4. በዚህ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 15 መሠረት የተመረጡትን የሥራ ሓላፊዎች ይሾማል፤ በቀደምትነትና በታሪክ የታወቁትን የታላላቅ ገዳማት አበምኔቶችና የከፍተኛ አድባራት አስተዳዳሪዎች በየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት እየተመረጡ ሲቀርቡለት የማዕረግ ስም እየሰጠ ይሾማል፡፡
5. ስለ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የመንግሥትን ፈቃድ ማግኘት በሚያስፈልግበት ጊዜ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰነ በተግባር ላይ ያውላል፡፡
6. ቅዱስ ፓትርያርኩ በዓበይት ጉዳዮች ላይ ሁሉ በቅዱስ ሲኖዶስ አያስወሰነ ይሠራል፡፡
7. በቅዱስ ሲኖዶስ የወጡ ሕጐች፣ የተላለፉ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ሁሉ በተግባር ላይ መዋላቸውን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡
8. በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡትን ሕጐችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በፊርማው ያስተላልፋል፡፡
9. ከመንግሥታውያንም ሆነ መንግሥታውያን ካለሆኑ መ/ቤቶች ድርጅቶችና ግለሰቦች የሚቀርቡ ደብደቤዎች ወይም አቤቱታዎችን ደረጃቸውን ጠብቀው በሕግ መሠረት ይፈጸሙ ዘንድ ለጠቅላይ ጽ/ቤት ያስተላልፋል፡፡
10. በውጭ አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አህጉረ ስብከት ለማገልገል ወይም የነፃ ትምህርት ለመማር የሚላኩ ካህናት በዚሁ ሕግ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 11 መሠረት ተመርጠው ሲቀርቡ እንዲላኩ ያደርጋል፡፡
11. ከውጭ የሚመጡትን እንግዶች በውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቅራቢነት እየተቀበለ ያነጋግራል፡፡
12. ፓትርያርኩ በውጭ አገር በሚደረግ በማናቸውም ስብሰባ ላይ ለመገኘትና ጉብኝት ለማካሔድ በሚያስፈልግ ጊዜ ስለተልዕኮው ጉዳይ አስቀድሞ በቅዱስ ሲኖዶስና በቋሚ ሲኖዶስ ያስወስናል፡፡
አንቀጽ 16
የፓትርያርኩ ከማዕረግ መውረድ
1. ፓትርያርኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከተሾመ በኋላ የተቀበለውን ሓላፊነት በመዘንጋት፡-
ሀ. የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ ቤተ ክርስቲያንን የሚያሰነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፣
ለ. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ከቁጥር 172 እስከ 208 በተደነገገው መሠረት በደለኛ መሆኑ ከታመነበት፣
ሐ. በቃሉ የማይገኝና በዚህ ሕግ አንቀጽ 13 ንዑስ አንቀጽ 7 ድንጋጌ መሠረት በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ያልጠበቀ በአጠቃላይ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነትን ያጣ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያስነቅፍ መሆኑ በትክክል ከተረጋገጠ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከሥልጣኑ ይወርዳል፤ በምትኩም ሌላ ፓትርያርክ ተመርጦ ይሾማል፡፡
2. ከዚህ በላይ በተደነገገው መሠረት ከሥልጣኑ የተገለለ ፓትርያርክ በቀኖና ተወስኖ በገዳም ይቀመጣል፡፡
3. ከሥልጣን የተገለለው ፓትርያርክ በገዳም አልቀመጥም በቀኖናም አልወሰንም በማለት እምቢተኛ ከሆነ ተወግዞ ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ይለያል፡፡
4. ፓትርያርኩ መንፈሳዊ ሥራውን በማካሔድ ላይ እያለ እሥራትና ግዞት ቢደርስበት ቤተ ክርስቲያኒቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ትመራለች እንጂ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም፡፡
5. ከዚህ በላይ የተዘረዘረው ሁሉ ፍትሕ መንፈሳዊ በሚያዝዘው መሠረት ይፈጸማል፡፡
አንቀጽ 17
ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ
1. ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ወይም በዚህ ሕግ አንቀጽ 16 መሠረት ከሥልጣኑ ሲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡
2. የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም እንደጊዜውና እንደሥራው ሁኔታ እየታየ ከ40 እስከ 80 ቀን ባለው ጊዜ ይሆናል፡፡
3. የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ተግባር
ሀ. ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ጊዜያዊ ጉደዮችን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር እየመከረ ያከናውናል፡፡
ለ. በፓትርያርኩ ምርጫ ጊዜም የቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ መንበር ሆኖ ምርጫውን ያስፈጽማል፤ እርሱ ግን ከምርጫው አይገባም፡፡
/ምንጭ፦ ሕገ ቤተ ክርስቲያን 1991 ዓ.ም/