ፅንሰተ ማርያም ድንግል

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ነሐሴ ሰባት ቀን ከሚዘከሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፅንሰት አንደኛው ነው፡፡ በዓሉን ለመዘከር ያህልም የእመቤታችንን የመፀነስ ታሪክ በአጭሩ እናስታውሳችሁ፤

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ አያቶች ቴክታ እና በጥሪቃ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለ ጠጎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መካኖች ነበሩ፡፡ ዘራቸውን ባለመተካታቸውና ሀብታቸውን የሚወርስ ልጅ ባለማግኘታቸውም ያዝኑ፣ ይተክዙ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በጥሪቃ ሚስቱ ቴክታን ጠርቶ ‹‹አንቺ መካን፤ እኔ መካን፡፡ ይህ ገንዘብ ለማን ይኾናል?›› አላት፡፡ ቴክታም ‹‹እግዚአብሔር ከእኔ ልጅ ባይሰጥህ ከሌላ ይሰጥህ ይኾናል፡፡ ሌላ ሚስት አግብተህ ልጅ አትወልድምን?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል›› አላት፡፡ በዚህ አኳኋን እያዘኑ ሲኖሩ አንድ ቀን ነጭ እንቦሳ (ጥጃ) ከበረታቸው ስትወጣ፤ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ልጅ ስትደርስና ስድስተኛዪቱ እንቦሳም ጨረቃን፣ ጨረቃም ፀሐይን ስትወልድ ራእይ አዩ፡፡

ራእያቸውን ለሕልም ተርጓሚ ሲነግሩም ‹‹የጨረቃዪቱ ትርጕም ከፍጡራን በላይ የምትኾን ልጅ እንደምታገኙ የሚያመለክት ነው፡፡ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጠልኝም፡፡ እንደ ነቢይ፣ እንደ ንጉሥ ያለ ይኾናል፤›› አላቸው፡፡ እነርሱም ይህን ሲሰሙ ‹‹ጊዜ ይተርጕመው ብለው›› ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ለዘር ሊያበቃቸው ፈቅዷልና መካኗ ቴክታ ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ‹ሄኤሜን› አለቻት፡፡ ትርጕሙም ‹ስእለቴን (ምኞቴን) አገኘሁ› ማለት ነው፡፡ ሄኤሜንም ለዓቅመ ሔዋን ስትደርስ ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፤ ቶና ሲካርን፤ ሲካር ሄርሜላን፤ ሄርሜላ ሐናን ወለዱ፡፡ ለሐናም ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ እነርሱም እንደ በጥሪቃና ቴክታ መካኖች ኾኑ፡፡

በእስራኤላውያን ባህል መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይቈጠር ነበርና ሐና እና ኢያቄም ብዙ ዘለፋና ሽሙጥ ይደርስባቸው ነበር፡፡ በአንድ ወቅት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ቤተ መቅደስ ሔዱ፡፡ የዘመኑ ሊቀ ካህናት ሮቤል መካን መኾናቸውን ያውቅ ነበርና ‹‹እናንተማብዙ ተባዙብሎ እግዚአብሔር ለአዳም የነገረውን ቃል ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? እግዚአብሔር ቢጠላችሁ እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን?›› ብሎ መሥዋዕታቸውን ሳይቀበላቸው ቀረ፡፡ አንድም ከአዕሩገ እስራኤል (ከአረጋውያን እስራኤላውያን) የተወለዱ ሰዎች የሚመገቡትን ተረፈ መሥዋዕት እንዳይመገቡ ከለከላቸው፡፡ በዚህ እያዘኑ ሲመለሱ ከመንገድ ላይ ከልጆቻቸው ጋር የሚጫወቱ ርግቦችንና አብበው ያፈሩ ዕፀዋትን ሐና ተመለከተች፡፡ እርሷም ‹‹ርግቦችን በባሕርያቸው መራባት እንዲችሉ፤ ዕፀዋትንአብበው እንዲያፈሩ የምታደርግ ጌታ እኔን ለምን ልጅ ነሳኸኝ?›› ብላ አዘነች፡፡

ከቤታቸው ሲደርሱም ‹‹እግዚአብሔር ልጅ ቢሰጠን ወንድ ከኾነ ለቤተ እግዚአብሔር ምንጣፍ አንጣፊ፣ መጋረጃ ጋራጅ ኾኖ ሲያገለግል ይኑር፤ ሴት ብትኾንም መሶበ ወርቅ ሰፍታ፣ መጋረጃ ፈትላ ስታገለግል ትኑር›› ብለው ተሳሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ሐምሌ ፴ ቀን ኹለቱም ራእይ አዩ፡፡ ሐና ‹‹በሕልሜ ፀምር (መጋረጃ) ሲያስታጥቁህ፤ በትርህ አፍርታ ፍጥረት ሲመገባት አየሁ›› ብላ ያየቸውን ራእይ ለኢያቄም ነገረችው፡፡ ኢያቄምም ‹‹ጸዓዳ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፣ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ›› ብሎ ያየውን ራእይ ለሐና ነገራት፡፡ ወደ ሕልም ተርጓሚ ሔደው ትርጕሙን ሲጠይቁም ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አንተ አልፈታኸውም፤ ጊዜ ይፍታው›› ብለው ተመለሱ፡፡ በሌላ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ‹‹ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ›› ብሎ የሕልሙን ትርጕም ትክክለኛነት ነግሯቸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ብሉይ ኪዳን (ዓመተ ዓለም፣ ዓመተ ፍዳ) ተፈጽሞ የሐዲስ ኪዳን መግባት ሊበሠር፤ ጌታችንም ሊፀነስ ፲፬ ያህል ዓመታት ሲቀሩ በፈቃደ እግዚአብሔር ነሐሴ ፯ ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተፀንሳለች፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናቷ በቅድስት ሐና ማኅፀን ሳለች ካደረገቻቸው ተአምራት መካከልም በርሴባ የምትባል ሴትን ዓይን ማብራቷ አንደኛው ነው፡፡ ይህቺ አንድ ዓይና ሴት (በርሴባ) ‹‹እግዚአብሔር በረድኤት ጐበኘሽ መሰለኝ፤ ጡቶችሽ ጠቁረዋል፤ ከንፈሮችሽ አረዋል›› ብላ የሐናን ማኅፀን በዳሰሰችበት እጇ ብታሻሸው ዓይኗ በርቶላታል፡፡

ይህንን አብነት አድርገውም እንደ እርሷ የሐናን ማኅፀን በመዳሰስ ብዙ ሕሙማን ከደዌያቸው ተፈውሰዋል፡፡ እንደዚሁም ሳምናስ የሚባል ልጅ በሞተ ጊዜ ሐና የአልጋውን ሸንኮር ይዛ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት ከሞት ተነሥቶ ‹‹ሰላም ለኪ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ፤ ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ አያቱ ሐና ሆይ! ሰላም ላንቺ ይኹን! ሰላምታ ይገባሻል!›› በማለት ሕልም ተርጓሚ ያልፈታውን ራእይ በመተርጐም ከቅድስት ሐና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፤ ከእመቤታችን ደግሞ እውነተኛው ፀሐይ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንሚወለድ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል ልዑል እግዚአብሔር ማደሪያውን መረጠ፤ አከበረ፤ ለየ፤ ቀደሰ …፤›› (መዝ. ፵፭፥፬) በማለት ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንደ ተናገረው፣ አምላክን ለመውለድ የተመረጠችው ማኅደረ ማለኮት፤ የዓለሙን ቤዛ በመውለዷ ‹‹ቤዛዊተ ዓለም›› እየተባለች የምትጠራው፤ በአምላክ ሕሊና ታስባ ትኖር የነበረችው፤ የድኅነታችን ምክንያት የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማኅፀን የተቋጠረችው (የተፀነሰችው) ነሐሴ ፯ ቀን ነው፡፡ ፅንሰቷም እግዚአብሔር በባረከውና ባከበረው ቅዱስ ጋብቻ በተወሰኑት ወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ሥርዓት ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ‹‹ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ፤ ድንግል ሆይ በሥጋዊ ፈቃድ የተፀንሽ አይደለሽም፤ ሕጋዊ በኾነ ሥርዓት ከሐና እና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ፤›› እንዳሉ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡

ስለዚህም ‹‹ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዓብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ! እውነተኛውን ምግብ፣ እውነተኛውን መጠጥ አስገኝተሽልናልና እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፤›› በማለት አባ ሕርያቆስ እንዳመሰገኗት፣ ዘለዓለማዊ ሕይወት የሚሰጠውን፤ ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማዳን የሚቻለውን፤ እውነተኛውን ምግበ ሥጋ ወነፍስ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ወለደችልን ‹‹እናታችን፣ እመቤታችን፣ አማላጃችን፣ የድኅነታችን ምክንያት፣ ወዘተ›› እያልን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናከብራታለን፤ እናገናታለን፤ እናመሰግናታለን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት አይለየን፡፡ እናቱን በአማላጅነት፤ ራሱን በቤዛነት ለሰጠን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር፣ ምስጋና ይድረሰው፡፡

ምንጭ፡ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፣ ፭፥፴፰፡፡

ተስእሎተ ቂሣርያ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፱ .

በየዓመቱ ነሐሴ ፯ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ከሚከበሩ የጌታችን በዓላት መካከል የተስእሎተ ቂሣርያ በዓል አንደኛው ነው፡፡ ‹ተስእሎተ ቂሣርያ›፣ የቃሉ (ሐረጉ) ትርጕም ‹በቂሣርያ አገር የቀረበ ጥያቄ› ማለት ሲኾን፣ ይኸውም ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል?›› ብሎ ደቀ መዛሙርቱን መጠየቁን ያስረዳል፡፡ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈው ጌታችን በቂሣርያ አውራጃ ሐዋርያቱን ሰብስቦ ‹‹ሰዎች የሰውን ልጅ (ኢየሱስ ክርስቶስን) ማን ይሉታል?›› ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም ‹‹ዮሐንስ፣ ኤልያስ፣ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ›› የሚል ምላሽ ሰጥተውታል፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ ባቀረበላቸው ጊዜ የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹አንተ ውእቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፤ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ›› ብሎ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያስረዳ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽም ሰዎች ስለ ክርስቶስ ማንነት ከሚሰጡት ግምትና ከሐዋርያት ዕውቀት በላይ በመኾኑ ጌታችን ‹‹የእኔን አምላክነት ሰማያዊ አባቴ ገለጸልህ እንጂ ሥጋዊ ደማዊ አእምሮ አልገለጸልህም›› በማለት በአንክሮ ተቀብሎታል፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ስለ እርሱ የሚናገሩትንም፣ የሚያስቡትንም የሚያውቅ አምላክ ሲኾን በቂሣርያ ሐዋርያቱን ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል›› ብሎ መጠየቁ በአንድ በኩል አላዋቂ ሥጋን መልበሱን ለማጠየቅ፤ በሌላ ምሥጢር ደግሞ አምላክነቱን ለመግለጥ፣ እንደዚሁም መዓርገ ክህነትን ለሐዋርያትና ለተከታዮቻቸው (ለጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ለመስጠት ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ጴጥሮስ ምላሽና ጌታችን በሰጠው ሥልጣን ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ልጅነትና የባሕርይ አምላክነት ከመሰከረ በኋላ ጌታችን፣ ‹‹አንተ ዓለት (መሠረት) ነህ፤ በአንተ መሠረትነት ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ፡፡ የገሃነም ደጆች (አጋንንት) አይችሏትም፡፡ የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ እሰጥሃለሁ፡፡ በምድር ያሠርኸው በሰማይም የታሠረ፤ በምድር የፈታኸው በሰማይም የተፈታ ይኾናል›› በማለት ለአብያተ ክርስቲያናት መስፋፋት፣ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎትና ለምእመናን ድኅነት ምክንያት የኾነውን መዓርገ ክህነት ሰጥቶታል (ማቴ. ፲፮፥፲፫-፲፱)፡፡

ይህ ሥልጣነ ክህነት በቅዱስ ጴጥሮስ አንጻር ከሐዋርያት ጀምሮ ለሚነሡ አባቶች ካህናት የተሰጠ ሰማያዊ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ምእመናን በኃጢአት ስንወድቅ ከካህናት ፊት ቀርበን የምንናዘዘውና ንስሐ የምንቀበለው፤ በመስቀሉ እየተባረክን ‹‹ይፍቱን›› የምንለው ጌታችን ለሐዋርያት የሰጣቸውን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አባቶች ካህናትም ‹‹ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይቀድስ …›› እያሉ በመናዘዝ ‹‹እግዚአብሔር ይፍታ›› የሚሉን ከባለቤቱ የማሠርና የመፍታት ሥልጣን ስለ ተሰጣቸው ነው፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በትርጓሜያቸው እንደሚያስረዱት ጌታችን ሐዋርያቱን ‹‹እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?›› ብሎ ከጠየቃቸው በኋላ ምላሻቸውን ተከትሎ ሥልጣነ ክህነትን መስጠቱ በብሉይ ኪዳን (እግዚአብሔር አምላክ በሥጋ ከመገለጡ በፊት) አዳም የት እንዳለ እያወቀ ‹‹አዳም ሆይ ወዴት ነህ?›› (ዘፍ. ፫፥፲) ብሎ ከጠየቀውና ያለበትን እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል የድኅንት ቃል ኪዳን መግባቱን ያስታውሰናል፡፡ እግዚአብሔር በሦስትነቱ ከአብርሃም ቤት በገባ ጊዜ ሣራ ያለችበትን ቦታ እያወቀ ‹‹ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?›› ሲል አብርሃምን ያለችበትን ቦታ እንዲናገር ካደረገው በኋላ ‹‹ሣራ ልጅን ታገኛለች›› የሚል ቃል መናገሩም ከዚህ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ቃሉም በአንድ በኩል የይስሐቅን መወለድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት የሚያጠይቅ ነው (ዘፍ. ፲፰፥፱-፲፭)፡፡

በሐዲስ ኪዳንም አልዓዛር በሞተ ጊዜ ጌታችን የተቀበረበትን ቦታ እያወቀ ‹‹አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት›› ብሎ መካነ መቃብሩን ከጠየቀ በኋላ በሥልጣኑ ከሞት እንዲነሣ ማድረጉም ከተስእሎተ ቂሣርያ እና ከላይ ከጠቀስናቸው ምሳሌዎች ጋር የሚወራረስ ምሥጢር አለው (ዮሐ. ፲፩፥፴፯)፡፡ ይኼ ዅሉ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ሐሳባቸውን ያላወቀ መስሎ እየጠየቀ ሰዎች ስሜታቸውን እንዲገልጡ እንደሚያደርግ፤ የልባቸውን መሻትና እምነት መሠረት አድርጎም ሥልጣንን፣ በረከትን፣ ጸጋንና ፈውስን እንደሚያድላቸው የሚያስረዳ ትምህርት ነው፡፡ ለዚህም ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው በአካለ ሥጋ ሲመላለስ መዳን እንደሚፈልጉ እያወቀ ‹‹ልትድን ትወዳለህን? ልትድኚ ትወጃለሽን? ልትድኑ ትወዳላችሁን?›› ብሎ እየጠየቀ የልባቸውን መሻት እንዲናገሩ ካደረገ በኋላ የእምነታቸውን ጽናት አይቶ በአምላካዊ ቃሉ ‹‹ፈቀድኩ ንጻሕ፤ ፈቀድኩ ንጽሒ፤ ፈቀድኩ ንጽሑ = ፈቅጃለሁ ተፈወስ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወሺ፤ ፈቅጃለሁ ተፈወሱ፤›› እያለ ለሕሙማነ ሥጋ ወነፍስ ፈውስን ማደሉ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

ትምህርቱን ወደ እኛ ሕይወት ስናመጣው ዛሬ ዓለም ክርስቶስን ማን ትለዋች? እኛስ ማን ብለን እንጠራዋለን? ምላሹ እንደየሰዉ የመረዳት ዓቅም ሊለያይ ይችላል፡፡ እውነታው ግን አንድ ብቻ ነው፤ በእርግጥ እግዚአብሔር አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ሕዝቡን እንዳዳነ ያልገባት ዓለም ክርስቶስን ከፍጡራን ተርታ ትመድበዋለች፡፡ የእርሷ የፍልስፍና ሐሳብ አራማጆች መናፍቃንም አምላክነቱን ክደው ‹‹አማላጅ ነው›› ይሉታል (ሎቱ ስብሐት)፡፡ ሌሎችም እንደየዓቅማቸው ለክብሩ በማይመጥን ልዩ ልዩ ስም ይጠሩታል፡፡ በሐሰተኛ ትምህርታቸውም ብዙ የዋሃንን አሰናክለዋል፡፡ እርሱ ባወቀ ወደ ቤቱ ይመልሳቸው እንጂ፡፡ እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን እርሱ ባለቤቱ፣ ቅዱሳን ሐዋርያትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ አካላት አንዱ፤ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር (አምላክ ወልደ አምላክ)፤ በቈረሰው ሥጋ፣ ባፈሰሰው ደሙ ከዘለዓለማዊ ሞት ያዳነን የዅላችን ቤዛ እንደ ኾነ እናምናለን፤ እንታመናለን፡፡ ይህን ሃይማኖታችንንም ለዓለም በግልጽ እንመሰክራለን፡፡ እርሱም በምድር እንደየእምነታችን መጠን መንፈሳዊ ጸጋን፣ በረከትን፣ ፈውስን ያድለናል፡፡ በሰማይም እንደየሥራችን ዋጋ ይከፍለናል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን እንደ እኛ ድክመት ሳይኾን እንደ ቸርነቱ ብዛት ስሙን ለመቀደስ፤ መንግሥቱንም ለመውረስ ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል ሦስት (የመጨረሻ ክፍል)

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ነሐሴ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ሱባዔ በዘመነ ሐዲስ

በዘመነ ሐዲስ በሰፊው የሚወሳው ሱባዔ ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ ፩ – ፲፬ ቀን ድረስ የገቡት ሱባዔ ነው፡፡ ይህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ጋር፣ ዐሥራ አምስት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩  ቀን ዐርፋለች፡፡ በሐዋርያት ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ ፲፬ ቀን ከተቀበረች በኋላ ነሐሴ ፲፮ ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ ‹‹ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች፤›› በማለት ወደ ሰማይ ማረጓንና በክብር መቀመጧን ተናግሯል፡፡ ከሺሕ ዓመት በፊትም አባቷ ዳዊት ‹‹በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› ሲል የተናገረው ትንቢት ይህንኑ የእመቤታችንን ክብር የሚመለከት ነው (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡

‹ፍልሰት› የሚለው ቃል የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፣ በኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው (ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ፣ ገጽ 68)፡፡ ለሐዋርያት የእመቤታችን የዕረፍትና የዕርገት ምሥጢር የተገለጠላቸው በሱባዔ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታ ወይም የሐዋርያት ሱባዔ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቤተ ክርስቲያን ይታሰባል፡፡ ምእመናን የተቻላቸው ከሰው ርቀው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ያልተቻላቸው ደግሞ በአጥቢያቸው የውዳሴዋና የቅዳሴዋን ትርጕም ይሰማሉ፤ በሰዓታቱና በቅዳሴው ሥርዓት ይሳተፋሉ፡፡ በእመቤታችን አማላጅነት፣ በልጇ ቸርነት በምድር ሳሉ በሃይማኖት ጸንተው ለመኖር፤ በኋላም ለመንግሥቱ እንዲያበቃቸው እግዚአብሔርን ደጅ ይጠናሉ፡፡

የሱባዔ ዓይነቶች

፩. የግል ሱባዔ (ዝግ ሱባዔ)

የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ኾኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በዓቱን ዘግቶ በሰቂለ ሕሊና ኾኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየውና እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው (ማቴ. ፮፥፭-፲፫)፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በዓቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም (መዝ. ፻፩፥፮-፯)፡፡

፪. የማኅበር ሱባዔ

የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድነት ኾነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በኾኑ ቦታዎች ዅሉ ተሰባስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር ቤት በመሔድ ይጸልዩ ነበር (፩ኛ ሳሙ. ፩፥፩፤ መዝ. ፻፳፩፥፩፤ ሉቃ. ፲፰፥፲-፲፬)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፤ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባዔ ይይዛሉ፡፡

፫. የዐዋጅ ሱባዔ

የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲከሠት፤ እንደዚሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የኾነ መቅሠፍት ሲመጣ፤ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖሩ የነበሩ እስራኤላውያን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድረስ ለሦስት ቀናት ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለያቸው እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶላቸዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖሩ የነበሩ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ አርጤክስስ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማጽነዋል (አስቴር ፬፥፲፮-፳፰)፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ‹‹ጉልበት ያለህ በጉልበትህ፣ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ›› በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፡፡ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ባስደነቀ መልኩ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሡ የሚያስችል ፋና ወጊ የኾነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ታሪክ ነው፡፡

የሱባዔ ቅድመ ዝግጅት

ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ (ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ)፣ ጊዜ ሱባዔ (በሱባዔ ጊዜ) እና ድኅረ ሱባዔ (ከሱባዔ በኋላ) ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

ቅድመ ሱባዔ (ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ)

በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይኾን ሱባዔ ቢገባ ከሱባዔው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ድካሙ ዋጋ ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባዔ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ ክርስቲያናዊ ግዴታ ነውና፡፡ ከዚህም ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርጉልናል፡፡ ስለኾነም ቅድመ ሱባዔ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ነው፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት ልዩ ልዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንደዚሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር ከአንድ ምእመን ይጠበቃል፡፡ ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ ዓቅማችንና እንደ ችሎታችን መጠን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው በዋሻ እዘጋለሁ ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻሉ ሱባዔውን ሊያቋርጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዓቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡

ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የኾነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መኾን አለመኾኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ላይ ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም ለማለት አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ ይችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መኾናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ሕሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ሕሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ቢኾኑ ተመራጭ ነው፡፡

ጊዜ ሱባዔ (በሱባዔ ጊዜ)

በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ፣ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንደዚሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ፣ ወደ ግራ፣ ወደ ቀኝ አለመዟዟር፤ በሰፊሐ እድ፣ በሰቂለ ሕሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል (መዝ. ፭፥፫)፤ መዝ. ፻፴፫፥፪፤ ዮሐ. ፲፩፥፵፩)፡፡ በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡

ድኅረ ሱባዔ (ከሱባዔ በኋላ)

ለቀረበ ተማኅጽኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት፣ እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የሕሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህም ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መጽናትና መማጸን ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል ሁለት

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ነሐሴ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

፫. የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን

በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብጹን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል (ዘፍ. ፵፩፥፲፬-፴፮፤ ዳን. ፬፥፱፣ ፭፥፬)፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ኾነ በአጠቃላይ ለሕዝቡ ትምህርት በሚኾን መልኩ ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው እንዲህ ይኾናል የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማጸኑ ነበር፡፡

ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጠው ያስረዱ ነበር (ዳን. ፭፥፳፰)፡፡ እንደዚሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጕም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ኾነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል (መዝ. ፰፥፩)፡፡ ከዚህ ቀጥለን የቀደምት አበውን ሱባዔና ያስገኘላቸውን ጥቅም በአጭር በአጭሩ እንመለከታለን፤

ሱባዔ አዳም

አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቍጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለ ምንም ትካዜና ጕስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል (ዘፍ. ፫፥፳፬)፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነትን ከሚቈራርጥ ባሕር ውስጥ በመግባት ለሠላሳ አምስት ቀን (አምስት ሱባዔ) ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ መሐሪው እግዚአብሔርም የአዳምን ፍጹም መጸጸት ተመልክቶ ‹‹በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ፤ በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ብሎ የድኅነት ተስፋ ሰጠው፡፡

አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቈጥር፣ አዳምም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለ ነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቈጠረ ‹‹የተናገረውን የማያስቀር፣ የማያደርገውን የማይናገር ጌታዬ፤ እነሆ ‹አድንሃለሁ› ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤›› እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸሩ አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ‹‹ተንሥኡ ለጸሎት፤ ለጸሎት ተነሡ፡፡ ሰላም ለኵልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይኹንን!›› በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡

ሱባዔ ሔኖክ

ጻድቁ ሔኖክ የያሬድ ልጅ ሲኾን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመኾኑም በብሉይ ኪዳንም ኾነ በሐዲስ ኪዳን የመልካም ግብር ባለቤት መኾኑ ተመስክሮለታል፡፡ ‹‹ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፍ. ፭፥፳፪)፡፡ ይህም በመኾኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቈጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ (ዑደት) የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል (ዘፍ. ፭፥፳፩-፳፬፤ ሔኖክ ፩፥፱፤ ይሁዳ፣ ቍ. ፲፬)፡፡

ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመሥፈርት የቈጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መሥፈርቱ (ማባዣ ቍጥሩ) 35 ሲኾን 35 በ19 ሲበዛ ውጤቱ 685 ዓመት ይኾናል፡፡ 685ን በ12 ስናባዛው ደግሞ 7980 ይኾናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለ ክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ 7509 ይኾናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 2009 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቈጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይኾናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቍጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን (7509) ስንቀንስ 471 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊኾን 471 ዓመት ይቀረዋል ማለት ነው፡፡

ሱባዔ ነቢያት

እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መኾንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፤ ሱባዔም ቈጥረዋል (መዝ. ፵፱፥፫፤ ኢሳ. ፯፥፲፬፤ ዘካ. ፲፫፥፮፣ ፲፬፥፩)፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባዔ በአነጋገርና በአቈጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ይለያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር፣ ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመኾኑ ነው፡፡ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤›› እንዲል (ዕብ. ፩፥፩)፡፡ የአቈጣጠር ስልታቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡

ሱባዔ ዳንኤል

ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ ከትንቢቶቹ መካከልም፡- ‹‹ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መኾኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንደዚሁም ‹‹እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነጽ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነጻለች፤ በኋላም ትፈርሳለች፤›› በማለት የብሉይ ኪዳንን ማለፍና የሐዲስ ኪዳንን መመሥረት ተናግሯል፡፡ የዳንኤል የሱባዔ አቈጣጠር ስልቱም በዓመት ሲኾን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቍጠር ነው፡፡ ይህም ‹ሱባዔ ሰንበት› ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቈጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ተወለደበት ድረስ 490 ዓመት ይኾናል፡፡ መሥፈርቱ (ማባዣው) ሰባት ስለኾነ ሰባትን በሰባ ብናባዛው 490ን እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቈጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ ክርስቶስ መወለዱን ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሔዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የኾነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀውን የማቅረብ፣ የረቀቀውን የማጉላት ጸጋን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መኾኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ሱባዔ ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ዅሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011 – 971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መኾኑ ብዙ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቈጥሯል፡፡ ይኸውም ‹ቀመረ ዳዊት› በመባል ይታወቃል፡፡ ‹‹እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኀለፈት፤ ሺሕ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን ናት፤›› (መዝ. ፹፱፥፬) የሚለውን ኃይለ ቃል መምህራን ሲቈጥሩት 1140 ዓመት ይኾናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደ ኾነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቍጠሪያ (መሥፈሪያ) ኾኖ አገልግሏል፡፡ 1140 በ7 ሲባዛ 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

ይቆየን

ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ነሐሴ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

አሁን ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ጾመ ፍልሰታን የሚጾሙበት፣ ሱባዔ የሚገቡበት ጊዜ ነውና ወቅቱን የሚመለከት ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

ሱባዔ ምንድን ነው?

‹ሱባዔ› በሰዋስዋዊ ትርጕሙ ‹ሰባት› ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጐም አንድ ሰው ‹‹ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ ጋር እገናኛለሁ›› ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቍጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቍጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቍጥርን ፍጹምነት ያመለክታል (ዘፍ. ፪፥፪፤ መዝ. ፻፲፰፥፷፬)፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም አንድ ሱባዔ ጾመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም ደግሞ ሁለት ሱባዔ ጾመ እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ሱባዔ መቼ ተጀመረ?

ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መላእክት ለአዳም የጊዜያትን ስሌት አስተምረውት ነበር (ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ)፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል (መጽሐፈ ቀሌምጦስ፣ አንቀጽ አራት)፡፡

ሱባዔ ለምን?

የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ሕሊናው ይወቅሰዋል፤ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሕሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ጉዳይ፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡ ‹‹ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ? ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ሮሜ. ፯፥፳፪፥፳፭)፡፡ ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ የትካዜ ሸክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንድ ሰው በትካዜ ሸክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይኾንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ (ሱባዔ) ይገባል፡፡ ሱባዔ የሚገባውም ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት መሠረታዊ ጉዳዮች ነው፤

፩. እግዚአብሔርን ለመማጸን

ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማጸን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅጽኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው (የምንማጸነው) ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ጥቅም የለም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ አገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና፣ ወዘተ. ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች ፈጣሪውን በጸሎት ይማጸናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ኾነ በአገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፡፡ መልሱ ሊዘገይም ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት ይጠበቃል፡፡ ‹‹ለምን ላቀረብኹት ጥያቄ ቶሎ ምላሽ አልተሰጠኝም?›› በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማጸነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለውና፡፡

ከዚህ ላይ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይን ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ አኃው (ወንድሞች) ለተልእኮ በወጡበት ወቅት አንዱን ድቀት አግኝቶት ያድሯል፡፡ በነጋታው ‹‹ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ዓለሙን መስዬ እኖራለሁ›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን›› ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው አንድ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ ‹‹ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከ፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ›› የሚል ድምፅ አሰምቶታል (ዜና አበው)፡፡

ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ (ሰባት ቀን) እንደ ጨረሱም የወደቀው አገልጋይ ‹‹ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ›› የሚል ፈጣን ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ በግል ሕይወትም ኾነ በጓደኛችን ሕይወት ዙርያ ሱባዔ ስንገባ እግዚአብሔር ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡

፪. ከቅዱሳን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶች እና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ ‹‹ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ፤›› (ኢሳ. ፶፮፥፮) በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት ከበረከታቸው መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት ከጥንት ጀምሮ የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡

ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የልዩ ልዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል (ለመሳተፍ) የቅዱሳን ዐፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ፪፥፱ ላይ እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በኤልሳዕ ላይ እጥፍ ኾኖ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት (ዅሉንም ነገር በመተው) የሚኖሩ መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኾኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ ሰዎች መኖራቸውንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ይቆየን

ጾመ ማርያም ለቤተ ክርስቲያን ሰላም

በዝግጅት ክፍሉ

ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት፣ የቈጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ አየሁ፤» (ዕንባ. ፫፥፯) በማለት ነቢዩ ዕንባቆም የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መኾኑንም ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ ዐሥራት አድርጐ በመስጠቱ፣ ከዅሉም በላይ ክርስቶስ ከእርሷ በለበሰው ሥጋ አማካይነት የመዳናችን ምሥጢር በመከናወኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ ፍቅር አለን፡፡

የአብነት ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደ ሌላ አገር እየተዘዋወሩ የአብነት ትምህርት ሲማሩ ‹‹በእንተ ስማ ለማርያም›› (ስለ ማርያም ስም) እያሉ ነው፡፡ ተማሪዎቹ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ኾኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ የልጇ ግማደ መስቀል ወደ ከተመበት ግሼን ደብረ ከርቤ አምባ የሚጓዙ ምእመናንም ‹‹አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ›› እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማጸኗታል፡፡ እርሷም ከልጇ ዘንድ ባገኘችው የአማላጅነት ጸጋ ምልጃቸውን በመቀበል ጸሎታችውን በማሳረግ የእናትነት ሥራዋን ስትፈጽምላቸው ኖራለች፡፡ ዛሬም እየሠራች ነው፤ ወደፊትም አማላጅነቷ አይቋጥም፡፡ እመቤታችን ከልጇ ያገኘችውን (የተቀበለችውን) ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ በአራቱ ማዕዘን ‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኝልን›› የማይላት ክርስቲያን የለም፡፡

በፍቅሯ ተደስተው በአማላጅነቷ ተማምነው ‹‹የእመቤቴ ፍቅሯ እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ምድር አሸዋ በዝቶልኝ፣ እንደ ልብስ ለብሼው፣ እንደ ምግብ ተመግቤው›› እያሉ ተማጽነው ልመናቸው ሠምሮ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው፣ ቅዱስ ያሬድ ዘኢትዮጵያና አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ አባ ጽጌ ድንግል ያዘጋጁላትን፤ የደረሱላትን የምስጋና መጻሕፍት በመድገም እመቤታችንን ዘወትር መማጸን የቀደምቱም ኾነ የዛሬዎቹ ገዳማውያንና ምእመናን ዕለታዊ ተግባር ነው፡፡ ጌታችን ለቀደሙት ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችን አማላጅ እና እናት እንድትኾናቸው በገቢርም በነቢብም ከአደራ ቃል ጋር እናቱን አስረክቧቸዋል፡፡ በገቢር በቃና ዘገሊላ የሰውን ችግር ፈጥና የምትረዳ ርኅርኅት እናት አማላጅ መኾኗን አሳይቷል፡፡ ለዚሁም ‹‹የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል›› ብላ ያቀረበችው ቃለ ምልጃ ማስረጃ ነው፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ከእግረ መስቀሉ ሥር የነበረውን ቅዱስ ዮሐንስን ጠርቶ ‹‹እነኋት እናትህ፤›› ድንግል ማርያምን ደግሞ ‹‹እነሆ ልጅሽ፤›› በማለት ለቅዱሳን ሐዋርያትም ለእኛ ለምእመናንም እመቤታችንን በእናትነት ሰጥቶናል (ዮሐ. ፲፱፥፳፮)፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በእናትነት ከተረከቧት ጊዜ ጀምረው ልጇ በዕርገት በአካለ ሥጋ ሲለይ በቤታቸው አኑረው እንደ ልጅ አገልግለዋታል፡፡ እርሷም የእናትነት ሥራዋን ሠርታላቸዋለች፡፡ በምድር የነበራት ቆይታ ሲፈጸምም ልጇ በአዳምና በልጆቹ ኃጢአት ምክንያት የፈረደውን፣ ለራሱም ያላስቀረውን ሥጋዊ ሞት እናቱ እንድትቀምስ አደረገ፡፡ በእናትነት የተረከቧት ቅዱሳን ሐዋርያትም መካነ ዕረፍት ለይተው በንጹሕ በፍታ ከፍነው በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ የእመቤታችን ሥጋዊ ዕረፍቷና የትንሣኤዋ ምሥጢር ከመ ትንሣኤ ወልዳ (እንደ ልጇ ትንሣኤ) ነውና ሙስና መቃብር ሳያገኛት ከሦስት ቀናት ሥጋዊ ዕረፍት በኋላ ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ስታርግ በዕለተ ቀብሯ ያልተገኘው ቅዱስ  ቶማስ ደመና ጠቅሶ በደመና ሠረገላ ሲመጣ ዕርገቷን ይረዳል፡፡ ለማስረጃነትም የተከፈነችበትን በፍታ (ጨርቅ) ይቀበላታል፡፡ ለቅዱስ ቶማስ የተገለጠው የዕረፍቷ ምሥጢር ለእነርሱም እንዲገለጥላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት ቢማጸኑ እመቤታችን ዳግም ተገልጻላቸው ትንሣኤዋን ለማየት በቅተዋል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በሁለት ሱባዔ ማግኘታቸውን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን የፍልሰታን ጾም እንድንጾም በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ተወስኗል፡፡ ይህ እመቤታችንን የምንማጸንበት ጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያናችን መፍትሔ የምትፈልግባቸውን ጉዳዮች ለእመቤታችን የምታቀርብበት የጸሎት ወቅት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለሚገጥማት ችግር መፍትሔው ከእመቤታችን እጅ ላይ አለ ብለን እናምናለን፡፡ አባቶች ሱባዔ ገብተው እመቤታችንን እንደሚያገኟ ዅሉ፣ እርሷ የፍቅር እናት ናትና ፍቅርን አንድነትን እንድትሰጠን፤ የዶኪማስን ጓዳ እንደሞላች የጐደለውን ሕይወታችንን እንድትሞላልን ውዳሴዋን እየደገምን ድንግል ማርያምን መማጸን ያስፈልጋል፡፡

በውዳሴ ማርያም፣ በጸሎተ ማርያም የሚመካ በጕልበቱ አይመካም፡፡ ጊዜ ረዳኝ ብሎ በወገኖቹ ላይ ግፍን አይፈጽምም፡፡ ስለዚህ በእነዚህ የጾም ሳምንታት የእመቤታችን አማላጅቷ እና ጸጋዋ በአገራችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እንዲያድር በሱባዔ እንማጸናት፡፡ የሁለቱ ሳምንታት ሱባዔ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ዘወትር እየተገኘን ምሕላ የምናደርስበት፣ የተጣላነውን ይቅር ለእግዚአብሔር የምንልበት፣ የበደልነውን የምንክስበት፣ ሥጋውንና ደሙን የምንቀበልበት ወቅት መኾን አለበት፡፡ ነገር ግን ቀናቱን እየቈጠርን እስከተወሰነው ሰዓት ብቻ መጾም ብቻ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ሌላው ቁም ነገር በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ሱባዔ ገብተን ውዳሴ ማርያም በደገምንበት አፋችን ሰው የምናማ፣ በሰው ሕይወት ገብተን የምንፈተፍት ከኾነ እመቤታችንን አናውቃትም፤ እርሷም አታውቀንም፡፡ እናም ‹‹መክፈልት ሲሹ መቅሠፍት›› እንደሚባለው በረከት ማግኘት ሲገባን መቅሠፍት እንዳይደርስብን ዅሉንም በሥርዓቱና በአግባቡ ልናከናውን ያስፈልጋል፡፡

በጾመ ፍልሰታም ኾነ በሌላ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን የሚደረሰው ውዳሴ ማርያሙ፣ ሰዓታቱ፣ ቅዳሴው ከጠላት ሰይጣን ተንኮል የሚያድን፣ ከጥፋት የሚጠብቅ መንፈሳዊ የሰላም መሣርያ ነውና በጸሎቱ እንጠቀምበት፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚተጉ አባቶች እና ምእመናን በዚህ የእመቤታችንን ጾም ወቅት ለተሰደዱ፣ ለተራቡ፣ በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ይጸልያሉ፤ ይማጸናሉ፡፡ እኛም ለእነርሱና ለሌችም ነዳያን ጸበል ጸሪቅ በማቅመስ ከበረከታቸው እንካፈል፡፡ በአጠቃላይ መንፈሳዊነት፣ እውነት፣ ቅድስና፣ ሕጋዊ አሠራር በቤተ ክርስቲያን እንዲሰፍን ዅላችንም በዚህ በጾመ ፍልሰታ ሱባዔ ተግተን ልንጸልይ ይገባል፡፡

                                                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጾመ ፍልሰታ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ .

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ ዓ.ም በ፷፬ ዓመቷ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድና ድካም ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴሴማኒ ይዘዋት ሔዱ፡፡ በዚህ ጊዜ አይሁድ ‹‹እንደ ልጇተነሣች፤ ዐረገች› እያሉ እንዳያውኩን በእሳት እናቃጥላት›› ብለው ሥጋዋን ሊያጠፉ በዓመፃ ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም አጎበሩን ይዞ ሊያወርዳት ሲል የእግዚአብሔር መልአክ ሁለት እጆቹን ቀጣው፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስን ጨምሮ እመቤታችንን በደመና ነጥቆ ወደ ገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጣት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም እመቤታችን ያለችበት ቦታ እንዲገለጥላቸው ባረፈች በስምንተኛው ወር ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ገብተው እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ጀመሩ፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹ስምንት ወር ሙሉ ምን ይዘው ቆይተው ነሐሴ ላይ ሱባዔ ገቡ?›› የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ በመሠረቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ከስብከተ ወንጌል፣ ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከገቢረ ተአምራት ተለይተው እንደማያውቁ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ምስክር ነው፡፡ በመኾኑም እመቤታችን ካረፈችበት ቀን ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ነሐሴ ድረስ ጥያቄያቸውንና ጸሎታቸውን ባያቋርጡም ከሰው ተለይተው ሱባዔ ገብተው ጾም ጸሎት የጀመሩት ግን ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ነው፡፡ ቀድሞስ የክብር ባለቤት የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ኾነው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ተሰውራባቸው እንዴት ዝም ብለው ይቀመጣሉ? ቅዱሳን ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ (ዐሥራ አራት ቀናት) ካደረሱ በኋላም የነገሩትን የማይረሳ፣ የለመኑትን የማይነሳ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታቸውን ሰምቶ ነሐሴ ፲፭ ቀን የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው በክብር ገንዘው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀንም እንደ ልጇ እንደ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታለች፡፡ ትንሣኤዋን ‹‹ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጇ ትንሣኤ›› ያሰኘውም ይህ ምሥጢር ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ሲሰብክ ቆይቶ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ወደ ሰማይ ስታርግ ጠፈር ላይ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?›› ብሎ ትንሣኤዋን ባለማየቱ ኀዘን ስለ ተሰማው ከደመናው ይወድቅ ዘንድ ወደደ፡፡ ‹‹ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ›› እንዲል፡፡ እመቤታችንም ‹‹አይዞህ! አትዘን፤ ባልንጀሮችህ ሐዋርያት ያላዩትን ትንሣኤዬን አንተ አይተሃልና ደስ ይበልህ!›› ብላ ከሙታን ተለይታ መነሣቷንና ማረጓን ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛ የያዘቸውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚያም እርሷ ወደ ሰማይ ዐረገች፤ እርሱም ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ቅዱስ ቶማስ ትእዛዟን ተቀብሎ በክብር ከተሰናበታት በኋላ ወደ ሐዋርያት ሔዶ እንዳልሰማ እንዳላየ መስሎ ‹‹የእመቤታችን ነገር እንደምን ኾነ?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አግኝተን ቀበርናት›› ሲሉት ‹‹ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይኾናል?›› አላቸው፡፡

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ በፊት የክርስቶስን ትንሣኤ መጠራጠሩን ጠቅሶ እየገሠፀ መከራከሩንና መጠራጠሩን ትቶ ስለ እመቤታችን መቀበር እነርሱ የሚነግሩትን ዅሉ አምኖ መቀበል እንደሚገባው ለቅዱስ ቶማስ አስረዳው፡፡ ቅዱስ ቶማስም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ሲሰማው ቆየ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ተቈጥቶ የእመቤታችንን ክቡር ሥጋ ለቅዱስ ቶማስ ለማሳየት ሔዶ መቃብሯን ቢከፍት የእመቤታችንን ሥጋ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ቆመ፡፡ ቅዱስ ቶማስም ‹‹ወንድሞቼ! አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ከሙታን ተለይታ ተነሥታ ስታርግ አግኝቻታለሁ›› ብሎ እመቤታን የሰጠችውን ሰበን ለሐዋርያት ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት እየተደሰቱ ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን በቅዳሴ ጊዜ ሠራዒ ዲያቆኑ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚታሠረው መቀነት መሰል ልብስ፤ እንደዚሁም አባቶች ካህናት በመስቀላቸው ላይ የሚያደርጉት ቀጭን ልብስና በራሳቸው ላይ የሚጠመጥሙት ነጭ ሻሽ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡

በዓመቱ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ቶማስ የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን?›› ብለው ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰባስበው ሥጋዋን ይሰጣቸው (ያሳያቸው) ዘንድ ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምረው ሱባዔ ይዘው ጌታችንን ጠየቁት፡፡ እርሱም ልመናቸውን ተቀብሎ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችንን መንበር፤ ጴጥሮስን ተራዳኢ ካህን፤ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ እመቤታችንንም ሐዋርያትንም አቍርቧቸዋል፡፡ እነርሱም እመቤታችንን በዓይናቸው ከማየት ባሻገር አብረው ሥጋውን ደሙን ተቀብለዋል (ነገረ ማርያም፤ ትርጓሜ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም)፡፡

ይህንን ትምህርት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፭ ቀን ያለው ሁለት ሱባዔ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ኾኖ በምእመናን ዘንድ መጾም እንደሚገባው ሥርዓት ሠርተውልናል (ፍት.ነገ.አን.፲፭)፡፡ ይህ ጾምም ‹‹ጾመ ማርያም (የማርያም ጾም)›› ወይም ‹‹ጾመ ፍልሰታ ለማርያም (የማርያም የፍልሰቷ ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ‹ፍልሰት› የሚለው ቃል ‹‹ፈለሰ ሔደ፤ ተሰደደ›› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መሔድን ያመለክታል፡፡ ‹ፍልሰታ ለማርያም› ሲልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካረፈች በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መወሰዷን (ማረጓን) የሚያስረዳ መልእክት አለው፡፡

በጾመ ፍልሰታ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱና በቅዳሴው በሚደርሰው ቃለ እግዚአብሔር ነገረ ማርያም ማለትም የእመቤታችን ከመፀነሷ ጀምሮ እስከ ዕርገቷ ድረስ ያለው ታሪኳ፣ ለአምላክ ማደሪያነት መመረጧ፣ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ክብሯ፣ ርኅርራኄዋ፣ ደግነቷ፣ አማላጅነቷ፣ ሰውን ወዳድነቷ በስፋት ይነገራል፡፡ እመቤታችንን ከሚያወድሱ ድርሳናት መካከልም በተለይ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌንና ነገረ ድኅነትን ከነገረ ማርያም ጋር በማዛመድ የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም፤ እንደዚሁም ነገረ ድኅነትን ከምሥጢረ ሥጋዌ (ከነገረ ክርስቶስ) እና ከነገረ ማርያም ጋር በማመሣጠር የሚያትተው ውዳሴ ማርያምም በስፋት ይጸለያል፤ ይቀደሳል፤ ይተረጐማል፡፡ በሰንበታት የሚዘመሩ መዝሙራት፤ በየዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ለተዋሕዶ መመረጧን፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ ክብሯን፣ ቅድስናዋን፣ ንጽሕናዋን የሚያወሱ ናቸው፡፡

በጾመ ፍልሰታ ባሕታውያን ብቻ ሳይኾኑ ዓለማውያንም በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት የሰይጣንን ፈተና ድል ለማድረግ እንዲቻላቸው ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በየገዳማቱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ በዓት አዘጋጅተው፣ ሱባዔ ገብተው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ፡፡ እንደዚሁም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ይህ ጾም ለእመቤታችን ያለንን ፍቅርም የምንገልጽበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን ሕፃናት በአብዛኛው ትምህርተ ወንጌል የሚማሩት፤ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የሚቀበሉት በዚህ በጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ጌታችን በስሙ ሁለትም ሦስትም ኾነን ለጸሎትና ለመልካም ሥራ ብንሰባሰብ እርሱ በመካከላችን እንደሚገኝ የገባልንን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ (ማቴ. ፲፰፥፳)፣ ዅላችንም በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት በጌታችን፣ በእመቤታችንና በቅዱሳን ሐዋርያት ስም በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበን ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመማር ባሻገር ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ብናስቀድስ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ደሙን ብንቀበል በበረከት ላይ በረከትን፤ በጸጋ ላይ ጸጋን እናገኛለን፡፡ በኋላም ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንችላለን፡፡

ስለኾነም የእመቤታችንን ዕረፍትና ትንሣኤ በማሰብ ከልጇ ከወዳጇ የሚገኘውን ጸጋና በረከት ተስፋ በማድረግ የአባቶቻችንንና የእናቶቻችንን ፈለግ ተከትለን በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታን እንጾማለን፤ የምንችል ደግሞ ንስሐ ገብተን አስቀድሰን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን በሕግ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ በዚህ ወቅትም ኾነ በሌላ ጊዜ ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉ ወጣቶች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህም አረጋውያንና ሕፃናት ብቻ ሳይኾኑ ወጣቶችም ጭምር የመቍረብና የመዳን ክርስቲያናዊ መብት እንዳለን በመረዳት ራሳችንን ገዝተን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ አምላካችን በማይታበል ቃሉ ‹‹ሥጋዬን የሚበላ፤ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው›› በማለት ተናግሯልና (ዮሐ. ፮፥፶፬)፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት ጸጋና በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ካለፈው የቀጠለ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በቀሲስ ስንታየሁ አባተ አባባል የፍልሰታ ጾም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ለእመቤታችን ያላቸው ፍቅር የተለየ ነው፡፡ ይህም ከእመቤታችን ጋር ያለንን የጠበቀ ትስስር የሚያመላክት ሲኾን ከዚህም ሌላ አገራችን ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዐሥራት አገር ናት፡፡ እመቤታችን ልጇ ወዳጇ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን ይዛ በተሰደደችበት ወቅት በግብጽ ብቻ ሳይኾን በኢትዮጵያ ምድርም መጥታ ዐርፋለች፡፡ በዚህ ጊዜ አራቱንም የአገሪቱን መዓዝን ባርካለች፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚያስተምሩት ነቢዩ ዕንባቆም ‹‹የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ አየሁ›› በማለት የተናገረው ትንቢትም እመቤታችን ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቷን ያጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሥርዓት አድርገን ፍልሰታን በልዩ ኹኔታ እንጾማለን፡፡

ድርሳነ ዑራኤልም ‹‹እመቤታችን ድንግል ማርያም በስደቷ ወራት ልጇ ሕፃኑ ኢየሱስን ይዛ ከምድረ እስራኤል ወደ ምድረ ግብጽ፣ ከዚያም ወደ ብሔረ ኢትዮጵያ መጥታ በቅዱስ ዑራኤል መሪነት በደብረ ዳሞበትግራይ፣ በጎንደር፣ በአክሱም፣ በደብር ዐባይ፣ በጐጃምና በጣና በአደረገችው የስደት ጉዞ ሕፃኑ ኢየሱስ ለድንግል እናቱኢትዮጵያን ዐሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ››› በማለት በሸዋና በወሎ፣ በሐረርጌና በአርሲ፣ በሲዳማና በባሌ፣ በከፋና በኢሉባቦር፣ በወለጋና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍላተ አህጉር በብሩህ ደመና ተጭነው በአየር እየተዘዋወሩ ተራራውንና ወንዙን (አፍላጋቱን) እንደ ጐበኙ ይናገራል፡፡ ይህም የቀሲስ ስንታየሁን ሐሳብ ያጠናክራል፡፡

በጾመ ፍልሰታ ወቅት የምእመናን ቅድመ ዝግጅት

በጾመ ፍልሰታ ወቅት ምእመናን ምን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው? ሱባዔ ከገቡ በኋላስ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? የሚለውም ሌላው ጥያቄአችን ነበር፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም እንዲህ ይመልሳሉ፤

‹‹ምእመናን ጾም (ሱባዔ) ከመጀመራቸው በፊት የሥጋን ኮተት ዅሉ ማስወገድ አለባቸው፡፡ ሐሳባቸው ዅሉ ወደተለያየ አቅጣጫ ሳይከፋፈል ልቡናቸውን ሰብስበው ለአንድ እምነት መቆም፣ ከሱባዔ የሚያቋርጣቸውን ጉዳይም አስቀድሞ ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከገቡ በኋላሥጋቸውን ማድከም፣ በጾም በጸሎት መጠመድ አለባቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ተሰጣቸው ጸጋ መጠን ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ይገባቸዋል፡፡ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ አቅሙ የደከመን መርዳት የማይችል ደግሞ ምክርና ሐሳብ በመስጠት ክርስቲያናዊ ድርሻውን ይወጣ፡፡ ብዙ ከመብላት ጥቂት በመመገብ፣ ብዙ የሚያሰክር መጠጥ ጠጥቶ ከመንገዳገድ ውኃን ብቻ በመጎንጨት ለቁመተ ሥጋ የሚያበቃቸውን ያህል እያደረጉ ፈጣሪያቸውን ይጠይቁ፡፡ አለባበስን በተመለከተም ሥርዓት ያለው አለባበስ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሌላው የተለየና የሌሎችን ቀልብ የሚስብ  ልብስ መኾን የለበትም፡፡››

ቀሲስ ስንታየሁ የተናገሩትም ከሊቀ ማእምራን ደጉ ትምህርት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ እንዲህ ይላሉ ቀሲስ፤ ‹‹ጾም ማለት ለእግዚአብሔር ማመልከቻ ማስገባት ማለት ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች ሦስት ቀን ጾሙ፤ በሦስት ቀናት ውስጥ አገራቸው ከመከራ ዳነች፡፡ የፍልሰታ ጾምም የወገኖቻችንን፣ በአጠቃላይ የሰውን ልጅ ጥፋት አታሳየን› ብለን ቦታና ጊዜ ወስነን ሱባዔ የምንይዝበት ጾም ነው፡፡ እኛ ምእመናን ከሁለት መቶ ኀምሳ ቀናት በላይ እንጾማለን፡፡ ነገር ግን ስንጾም ማየት የሚገባን ነገር አለ፡፡ ፍቅር እንደ ሸማ ያላብስህ እንደሚባለው ስንጾም ፍቅር ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾም ያለ ፍቅር፣ ፍቅርም ያለ ጾም ዋጋ የለውም፡፡ ቁም ነገሩ እኛ በጾም ደርቆ መዋል ሳይኾን ፍቅርና ሰላም መታከል አለበት፡፡ የተጣላ መታረቅ አለበት፡፡ በቅዳሴ ሰዓት ቦታ ላጡ ቦታ መስጠት፣ አቅመ ደካሞችን መርዳት፣ በተለይ አረጋውያንንና ሕፃናትን መደገፍ የወጣቶች ድርሻ ነው፡፡ በቅዳሴ ሰዓት የበረታው ለደከመው ቦታ መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሐሜትናሁካታቂም በቀል ያዘለ ንግግር ቦታ ሊኖረው አይገባም፡፡››

እንደ ቀሲስ ስንታየሁ ገለጻ ጾም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ከኾነ ለምንድን ነው በጾማችን፣ በጸሎታችን ኅብረተሰባችን ከጉስቁልና ያልወጣው? ብለን ብንጠይቅ ሳይጾም ሳይጸለይ ቀርቶ ሳይኾን ፍቅር ስለሌለው ነው እንጂ እግዚአብሔር ጸሎቱን ሳይሰማ ቀርቶ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ፊትም አሁንም ኾነ ወደፊት የሕዝቡን ልመና ይሰማል፡፡

ሱባዔ የገቡ ዅሉ ራእይ ያያሉን?

ለሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም እና ለቀሲስ ስንታየሁ አባተ በመጨረሻ ያነሣንላቸው ጥያቄ ራእይ ከማየትና አለማየት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲታመሙ ከሕመማቸው ለመፈወስ ወይም በምድራዊ ሕይወት ለሚያነሧቸው ጥያቄዎች መፍትሔ ለማግኘት ሱባዔ በመግባት ራእይ ማየት አለብን ይላሉ፡፡ ራእይ ካላዩ ደግሞ ተስፋ ይቈርጣሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ለሕዝበ ክርስቲያኑ የምታስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ መምህራኑ ምላሽ አላቸው፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ፡- ‹‹ምንም እንኳን ወሩ ከሌላው በተለየ የሱባዔና የራእይ ወቅት ኾኖ ቢገለጽም በፍልሰታ ጾም ራእይ ማየት አለማየት የሚለው የብቃት መለኪያ (ማረጋገጫ) መኾን የለበትም፡፡ ቦታ ቀይረውና ከሰው ተለይተው እግዚአብሔርን በጾም በጸሎት መጠየቅ በቅዱሳት መጻሕፍት ታዝዟል፡፡ ምእመናን ወደ ውሳኔ ከመድረሳቸው በፊት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንወቅ ብለው እርሱን ይጠይቃሉ፡፡ ካልተሳካላቸው በተለያየ ጊዜ በሱባዔው ይቀጥላሉ እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም›› ሲሉ ምእመናንን መክረዋል፡፡

ቀሲስ ስንታየሁም፡- ‹‹አንድ ሰው የሚጾመው ራእይ ልይ ብሎ አይደለም፡፡ ይህ እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ የሚታይ ነገር ነው፡፡ አባቶቻችን ሲጾሙ፣ ሲጸልዩ ኃጢአታቸው እንዲገለጽላቸው እንጂ እግዚአብሔር እንዲገልጽላቸው አይደለም፡፡ ኃጢአታን ከተገለጸልንና ንስሐ ከገባን እግዚአብሔርን እናየዋለን፡፡ አንድ ሰው በኃጢአት ተሞልቶ እግዚአብሔርን ልይ ቢል ሊኾን አይችልም፡፡ እኛንና እግዚአብሔርን የሚለያየን ኃጢአትና በደል ነው፡፡ ስለዚህ የሚያራርቀንን ነገር ለማስወገድ መጾም አለብን፡፡ ምእመናን በሕይወታቸው ውስጥ ስላለው ችግር፣ ለሰው ልጅና ለአገር የሚበጅ ነገር አምጣልን ብለው ሱባዔ በመያዝ መጾም መጸለይ ይገባቸዋል እንጂ ራእይ እንዲገለጥላቸው መጓጓት፣ ራእይ አላየንም ብለውም ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አይደለም፤›› በማለት መንፈሳዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ጽሑፋችንን ለማጠቃለል ያህል በሕይወተ ሥጋ ሳለን ካልጾምንና ካልጸለይን ነፍሳችን ልትለመልም አትችልም፡፡ በጾም በጸሎት ዲያብሎስን፣ ዓለምንና ፍትወታት እኩያትን ድል መንሣት፤ እንደዚሁም መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ ምእመናን በምንጾምበት ወቅት የተራቡትንና የታረዙትን በማሰብ ካለን ከፍለን ለተራቡና ለታረዙ ማብላት፣ ማልበስ ይገባል፡፡ ይህን የምናደርገውም በፍልሰታ ወይም በሌሎችም አጽዋማት ጊዜ ብቻ ሳይኾን በማንኛውም ጊዜ ነው፡፡ የተቸገሩትን መርዳት ወይም እርስበርስ መረዳዳት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ግዴታ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ባህልም ነውና፡፡ ይህ ጾም ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን የምናሰፍንት፤ መንፈሳዊ ዕድገትን የምናመጣበት ይኾንልን ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት አይለየን፡፡

                                                              ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጾመ ፍልሰታና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በዚህ ዝግጅታችን ጾም ምንድን ነው? እንዴትና ለምን እንጾማለን? መጾም ምን ጥቅም ያስገኛል? ባንጾምስ ምን ጉዳት አለው? የሚሉ ጥያቄዎች በቤተ ክርስቲያን መምህራን ምላሽ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነው የፍልሰታ ጾም በደመቀና በተለየ ኹኔታ የሚጾምበት ምክንያት ምን እንደ ኾነና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ይዘን ቀርበናል፡፡ ከምላሾቹ በኋላም ጾመ ፍልሰታን እንዴት ማክበር እንደሚገባን ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ መልካም ንባብ!

የጾም ትርጕም

‹‹ጾም›› ማለት ‹‹ጾመ –  ተወ፤ ታቀበ፤ ታረመ፤›› ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲኾን የቃሉ ትርጕም ደግሞ ምግብ መተው፣ መከልከልና መጠበቅ ማለት ነው ሲሉ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ባዘጋጁት ‹‹ጾምና ምጽዋት›› በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ ፰ ላይ ገልጸውታል፡፡ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላትም የሚያትተውም ይህንኑ ሐሳብ ነው፡፡ ጾም ጥሉላትን፣ መባልዕትን ፈጽሞ መተው፣ ሰውነትን ከመብልና ከመጠጥ እንደዚሁም ከሌላውም ክፉ ነገር ዅሉ መጠበቅ፣ መግዛት፣ መቈጣጠር፣ በንስሐ ታጥቦ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መቅረብና እርሱንም ደጅ መጥናት ማለት ነው፡፡ ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ እና ቀሲስ ስንታየሁ አባተ የሚሰጡት ማብራርያም ይህንኑ ትርጕም የሚያጠናክር ነው፡፡

የጾም ሥርዓቱና ጥቅሙ 

‹‹መላው ሕዋሳታችን ካልጾሙ የምግብና መጠጥ ጾም ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ መጽሐፉም የሚለው ወደ አፍ የሚገባ ሰውን አያረክስም፤ ከአፍ የሚወጣ እንጂ› ነው፡፡ ስለዚህ ዐይን፣ ጆሮ፣ እግርና እጅ የመሳሰሉት የስሜት ሕዋሳታችን መጾም አለባቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ ይልቅ የሚበልጡት እነዚህ ናቸው፡፡ ከምግብና መጠጥ የምንቆጠበው በራሱ ኃጢአት ስለ ኾነ ሳይኾን ምግብና መጠጥ ሥጋን አጥግቦ በገደል ስለሚጥል ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ስለሚጎትት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ ስንጾምከሐሜት፣ ከአሉባልታ፣ ከዝሙትና በሐሰት ከመመስከርወዘተ. መቆጠብ አለብን›› ሲሉ ሊቀ ማእምራን ደጉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹የጾም መሠረቱ ሃይማኖት ነው፡፡ በሃይማኖት የተነሣ ለተወሰኑ ጊዜያት ከምግብና ከመጠጥ የምንከለከልበት ኹኔታ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጾም ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለት ዓይነት መስመር አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአጽዋማት ወቅት ከምግበ ሥጋና ከኃጢአት ትከለክላለች፡፡ ከኃጢአት ዅልጊዜም እንከላከላለን፡፡ ከምግብ የምንከለከለው ምግብ ኃጢአት ስለኾነ ሳይኾን ከሃይማኖት የተነሣ ነው፡፡ ምግብ በልተን ፈቃደ ሥጋችንን ከምናደልብ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋችንን ጎስመን ያለ ምግብና ያለ መጠጥ እግዚአብሔርን እያመሰገንን የምንኖርበትን ሰማያዊና ዘለዓለማዊ ሕይወት የምናስብብት መንገድ ነው›› የሚሉት ደግሞ ቀሲስ ስንታየሁ አባተ ናቸው፡፡

የጾም ዓይነቶች

ጾም የግል እና የዐዋጅ (የሕግ) ጾም በመባል በሁለት ይከፈላል፡፡ የግል ጾም ደግሞ የንስሐና የፈቃድ ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የዐዋጅ (የሕግ) አጽዋማት ሰባት ናቸው፡፡ እነዚህም ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት (የሰኔ ጾም)፣ ጾመ ነቢያት (የገና ጾም)፣ ጾመ ገሃድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ድኅነት (ረቡዕ እና ዓርብ) እና ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ መነሻም ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነው ጾመ ፍልሰታ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ወቅቱ የፍልሰታ ጾም ስለኾነ፡፡

የፍልሰታ ጾም 

ከዚህ በመቀጠል ጾመ ፍልሰታን ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምን እንደ ኾነ እንመለከታለን፡፡ የፍልሰታን ጾም ሕፃን አዋቂው ሳይቀር በልዩ ሥነ ሥርዓትና በደመቀ ኹኔታ ይጾማል፡፡ አብዛኞቹ ምእመናን የዕረፍት ጊዜ በመውሰድ በገዳማትና በየአብያተ ክርስቲያናት ሱባዔ በመግባት ከነሐሴ አንድ ጀምሮ እስከ አሥራ አምስት ቀን ድረስ ጾም፣ ጸሎት በማድረግ ይቆያሉ፡፡ ጾም ጸሎት ሲያደርጉ ደግሞ በድሎት ሳይኾን በየዋሻው፣ በየመቃብር ቤቱና አብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ እንጨት ረብርበውና ሳር ጎዝጉዘው ጥሬ እየበሉ ነው፡፡

ፍልሰታ ምን ማለት ነው?

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ለዚህ ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፤ ‹‹ፍልሰታ ማለትፈለሰ – ተሰደደ› ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ፍልሰትማለት ደግሞ የተለያየ ትርጕም ቢሰጠውምፍልሰታ ለማርያም› ተብሎ ሲገለጽ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሚያልፈው ወደ ማያልፈው ዓለም ከመቃብር የወጣችበት (የተነሣችበት) ቀን ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሥጋዊው ዓለም ወደ መንፈሳዊው ዓለም የተሸጋገረችበት ማለት ነው፡፡››

ቀሲስ ስንታየሁ አባተም በተመሳሳይ መልኩ ስለ ፍልሰታ እንዲህ በማለት ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹‹ፍልሰታ ለማርያም› የሚለው የግእዝ ቃል ሲኾንፍልሰታ› ማለት ደግሞፈለሰ› ከሚል ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ፍልሰት› ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መሔድን (መፍለስን) ያመለክታል፡፡ እመቤታችን ካረፈች በኋላ የሥጋዋን መፍለስ አስመልክቶ ሐዋርያት የእመቤታችን ሥጋ የት እንደ ተቀበረ አላወቁም ነበርና እግዚአብሔር የእመቤታችንን ሥጋ እንዲገልጥላቸው የጾሙት ጾም ነው፡፡ ሐዋርያት ሁለት ሱባዔ ጾመው የእመቤታችንን ሥጋዋን ሰጥቷቸው ትንሣኤዋንና ዕርገቷን በማየት በረከት ያገኙበት ጾም ነው፡፡ ስለኾነም ምእመናን ፍልሰታ ለማርያምን ከልጅ እስከ አዋቂው በጾም በጸሎትና በመቍረብ በጋራ በፍቅር፣ በሰላም ያሳልፉታል፡፡›› 

ሊቀ ማእምራን ደጉ ዓለም ካሣ እንዳብራሩት ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችንን እንዲጠብቃት ከተደረገ በኋላ ሐዋርያት ‹‹የእመቤታችን ነገር እንዴት ነው?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ‹‹እመቤታችንማ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ናት››  ብሎ ነገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሐዋርያት እመቤታችን ከመቃብር መነሣቷንና ማረጓን ማየት አለብን፤ እንዴት ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ እንቀራለን ብለው በመንፈሳዊ ቅናት በመነሣሣት ነሐሴ አንድ ቀን በዕለተ ሰኞ ሁለት ሰባት ሱባዔ ያዙ፡፡ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ አንሥቶ ሰጣቸውና በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ እመቤታችን በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋ ነሐሴ ፲፬ ቀን ተቀብራለች፡፡

ይኹንና ሐዋርያት ቢቀብሯትም ትንሣኤዋንና ዕርገቷን አላዩም ነበር፡፡ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ያየው ሲቀብሯት ያላየው ሐዋርያው ቶማስ ነው፡፡ ቶማስ እንዲያስተምር ሕንድ አገር ዕጣ ደርሶት አስተምሮ በደመና ሲመለስ ነሐሴ ፲፮ ቀን እመቤታችን ስታርግ ሕዋ ላይ ተገናኙ በማለት ሊቀ ማእምራን ደጉ ያስረዳሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽ ምእመናን ጾመ ፍልሰታ የእመቤታችን ዕረፍት፣ ትንሣኤና ዕርገቷ የሚዘከርበት ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የኾነ ጾም ነው፡፡ በየዓመቱ ሕፃን አዋቂው ሳይቀር የእመቤታችን ፍቅር አድሮባቸው ጾሙን ይጾማሉ፣ ያስቀድሳሉ፤ ይቈርባሉ፡፡

የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የፍልሰታን ጾም ከሌሎቹ አጽዋማት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሊቀ ማእምራን ደጉ ምላሽ ሲሰጡም ‹‹ኢትዮጵያ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዐሥራት አገር በመኾኗ እና ሕዝበ ክርስቲያኑ ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር ስላላቸው መሬት ላይ እየተኙ፣ ጥሬ እየበሉ በሰላም በፍቅር ይጾሙታል፡፡ ምእመናን ፍልሰታን ከሌሎች አጽዋማት በተለየ መልኩ መሬት ላይ እየተኙ ይጾሙታል፡፡ ይህ ደግሞ የእመቤታችን ፍቅር ስለሳባቸው ነው፤›› በማለት ያብራራሉ፡፡

ይቆየን

የቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ ተጋድሎ

በዝግጅት ክፍሉ

ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፱ .

በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በድርሳነ ገብርኤል እና በገድለ ቂርቆስ ወኢየሉጣ እንደ ተመዘገበው ሐምሌ ፲፱ ቀን ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበት፤ ስማቸውን የሚጠሩ፣ ዝክራቸውንም የሚዘክሩ ምእመናን ይቅርታን፣ ምሕረትን እንደሚያገኙ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእነዚህ ቅዱሳን ቃል ኪዳን የሰጠበት ቀን ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ የተራዳቸውም በዚሁ ዕለት ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን ገድል በአጭሩ እናስታውሳችኋለን፤

ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ናት፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልኾኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡

በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲኾን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡

ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውኀ ያድነናል›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውኀም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ‹‹ሞት ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን፣ መላእክትም ቢኾኑ፣ ግዛትም ቢኾን፣ ያለውም ቢኾን፣ የሚመጣውም ቢኾን፣ ኃይላትም ቢኾኑ፣ ከፍታም ቢኾን፣ ዝቅታም ቢኾን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢኾን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፤›› (ሮሜ. ፰፥፴፰-፴፱) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይኾኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት መልአኩ የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡

እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ዅሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል ‹‹አይዞህ! አይዞሽአትፍራ! አትፍሪ›› በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይኾን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን ‹‹በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወሌሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን›› እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙርያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፴፬፥፯)፡፡ ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር