ተዝካሩን አውጥቶ ክርስቶስን የተከተለ ሐዋርያ

ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ

በዲያቆን ዘክርስቶስ ጸጋዬ

ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

አንድ ሰው ከቅፍርናሆም ገበያ ወደ ገሊላ ባሕረ ወደብ በሚወስደው ዐቢይ መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ ነጋዴዎችን ቀረጥ ያስከፍል ነበር፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ሲያስተምር ቀረጥ ከሚሰብስብበት ቦታ ጠርቶ ‹‹ተከተለኝ›› አለው፡፡ እርሱም ሥራውን ርግፍ አድርጎ ትቶ ተከተለው፡፡ ለሐዋርያነት በተጠራ ጊዜ በቤቱ ድግስ አዘጋጅቶ ለጌታችን ግብዣ አቅርቦ፣ ለድሆች መጽውቶ፣ የቁም ተዝካሩን አውጥቶ ክርስቶስን ተከተለው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. ፱፥፲-፲፫)፡፡

ማቴዎስ ማለት ‹የእግዚአብሔር ስጦታ፣ ኅሩይ እመጸብሓን (ከቀራጮች መካከል የተመረጠ)› ማለት ነው፡፡ አባቱ ዲቁ እናቱ ደግሞ ክሩትያስ ይባላሉ፡፡ አባቱ (ዲቁ) በሌላ ስም ‹እልፍዮስ› (Aliphaeus) እየተባለ ይጠራል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ብሔረ ሙላዱ (የተወለደበት አገር) ናዝሬት፤ ነገዱም ከነገደ ይሳኮር ነው፡፡ የቀድሞ ስሙ ‹ሌዊ› ነበር (ማር. ፪፥፲፬)፡፡ በዕብራውያን ዘንድ በሁለት ስሞች መጠራት የተለመደ ሲኾን ሌዊ ከቀድሞ ጀምሮ ይጠራበት የነበረ፤ ማቴዎስ ደግሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከተከተለ በኋላ የተጠራበት ስሙ እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡

የቅዱስ ማቴዎስ ለሐዋርያነት መጠራት

ቅዱስ ማቴዎስ በቅዱሳን ሐዋርያት የስም ዝርዝር ላይ በራሱ ወንጌል በስምንተኛ፤ በማርቆስና በሉቃስ ወንጌል ደግሞ በሰባተኛ ቍጥር ተጠቅሷል (ማቴ. ፲፥፫)፡፡ በቀድሞ ሥራው ቀራጭ (የሮማውያን ግብር ሰብሳቢ) ነበር፡፡ የቀራጭነት ሥራውን ይሠራ የነበረውም በገሊላው ገዥ በሄሮድስ አንቲጳስ ሥር የነበረ ሲኾን ቦታውም በገሊላ ባህር አጠገብ በምትገኘው ደማቋ ከተማ ቅፍርናሆም ነበር፡፡ ዛሬ ይኼ ቦታ በእሾኽ ታጥሮ የጥንቱን የገበያ ምልክት ይዞ ይገኛል፡፡ የእልፍዮስ ልጅ ሌዊ በዚህ የመቅረጫ ቦታ ተቀምጦ የዓሣ እና የሌላም ነገር ንግድን እየተቆጣጠረ የቀራጭነት ሥራውን ይሠራ ነበር፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚቀርጥበት ቦታ ጠጋ ብሎ ‹‹ተከተለኝ›› አለው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ሲጠራ ቤት፣ ንብረት የነበረው ታዋቂ ባለ ሥልጣን ነበር፡፡ ጌታችን ‹‹ተከተለኝ›› ሲለው ድሆችን በነጻ የሚያበላ፣ ድውያንን በነጻ የሚፈውስ አምላክ መኾኑን ተረድቶ ሥራውን ርግፍ አድርጎ ትቶ ተከተለው፡፡ የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር መኾኑን በቤቱ ለጌታችንና ለተከታዮቹ ግብዣ በማድረግ ግልጥ አደረገ (ሉቃ. ፭፥፳፱)፡፡ ለጌታችና ለተከታዮቹ ግብዣ ያቀረበበት ቤቱም በቅፍርናሆም የሚገኝ ሲኾን ዛሬ ላቲኖች ቤተ ክርስቲያን ሠርተውበታል፡፡

የሐዋርያው አገልግሎት

ተዝካሩን ያወጣው ሐዋርያ ከክርስቶስ ጋር በነበረበት ጊዜ ከዋለበት እያዋለ፣ ካደረበት እያደረ፣ እንዲሁም በትንሣኤና በዕርገቱ ጊዜ በበዓለ ኀምሳ ደግሞ ለደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ አብሮ ነበር (ማቴ. ፲፥፩-፭፤ ሉቃ. ፲፰፥፴፩)፡፡ ከዚያም ሰባቱ ዲያቆናት እስከ ተመረጡበትና እስጢፋኖስም እስከ ተገደለበት ቀን ድረስ ከዚያም በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በኢየሩሳሌም ከሐዋርያት ጋር አብሮ ነበር፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ ሲከፋፈሉም ለእርሱ በደረሰው ሀገረ ስብከት በምድረ ፍልስጥኤም ገብቶ ጌታ ከፅንስ ጀምሮ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርት፣ የሠራውን ትሩፋት ቢነግራቸው ብዙዎች ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመለሰው፣ በክርስቶስ አምነው ተጠምቀዋል፡፡

 በካህናት አገር ወንጌልን መስበኩ

ቅዱስ ማቴዎስ በደመና ተጭኖ በጌታችን ትእዛዝ ወደ ሀገረ ካህናት እንደ ተወሰደ በገድለ ሐዋርያት እና በመጽሐፈ ስንክሳር ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ በዚያም ወደ ከተማው መግቢያ ደጅ በደረሰ ጊዜ አንደ ወጣት ብላቴና አገኘ፡፡ ወደ ከተማው ለመግባት እንዴት እንደሚችል ቢጠየቀው ወጣቱ ብላቴናም ‹‹እራስኽንና ጺምኽን ካልተላጨኽ፣ በእጅህም ዘንባባ ካልያዝኽ መግባት እትችልም›› ሲል መለሰለት፡፡ ይህም ነገር ለሐዋርያው ማቴዎስ አስጨንቆት ሲያዝን አስቀድሞ ያነጋገረው ያ ወጣት ብላቴና ዳግም በስሙ ጠራው፡፡ ሐዋርያውም ‹‹ወዴት ታውቀኛለህ?›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እኔ ጌታህ ኢየሱስ ነኝ፤ አሁንም እንደ ነገርኹኽ አድርግ፡፡ እኔም ካንተ ጋር አለሁ፡፡ ካንተም አልርቅም›› አለው፡፡

ከዚያን በኋላ ጌታችን እንዳዘዘው አድርጎ ወደ ካህናት አገር ገባ፡፡ በዚያም ከጣዖቱ ካህናት አለቃ ከአርሚስ ጋር ተገናኘ፡፡ ከእርሱም ጋር ስለ አማልክቶቻቸው ተነጋገረና ‹‹ራሳቸውን ማዳን የልቻሉ ሌላውን እንዴት ያድናሉ?›› ብሎ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ ጣዖቶቻቸውን አቃጠላቸው፡፡ በዚያን ጊዜም ከአርሚስ ጋር ብዙዎች ሰዎች አመኑ፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አጠመቃቸው፡፡ ከሰማይ ምግብ አውርዶም መገባቸው፡፡

የአገሩም ንጉሥ የሐዋርያውን ድንቅ ስራ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ ከአርሚስ ጋር ሐዋርያውን ወደ እሳት በጨመረው ጊዜ ጌታችን ከእሳቱ አዳናቸው፡፡ ከዚያን በኋላ በሚያሰቃያቸው ነገር ሲያስብ ንጉሡ ልጁ መሞቱን ሰማ፡፡ በዚህም እያዘነ ሳለ ሐዋርያው ማቴዎስ ‹‹ልጅህን እንዲያስነሡት ወደ አማልክትህ ለምን አትለምንም?›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹አማልክት የሞተ ማንሣት እንዴት ይችላሉ?›› ብሎ መለሰ፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም ‹‹ብታምንስ የእኛ አምላክ ልጅኽን ከሞት ማስነሣት ይችላል›› አለው፡፡ ንጉሡም ‹‹ልጄ ከሞት ከተነሣ እኔ አምናሁ›› አለው፡፡ በዚያን ጊዜ ሐዋርያው ክብር ይግባውና ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸለየና የንጉሡንም ልጅ ከሞት አስነሣው፡፡ ንጉሡም በጌታችን አመነ፡፡ የአገሩ ሰዎችም ዂሉ አመኑ፡፡ የቀናች ሃይማኖትንም አስተምሮ ክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው፡፡ የጣዖቱ ካህን የነበረው አርሚስንም ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾመላቸው፡፡

የማቴዎስ ወንጌል

ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቀኖና በጠቀሰበት ጽሑፉ ቅዱስ ማቴዎስ ከአይሁድ ወደ ክርስትና ለተመለሱ ዕብራውያን ወንጌሉን እንደ ጻፈው ሲገልጽ ‹‹ማቴዎስ ለዕብራውያን ተአምራተ ኢየሱስን ጻፈ›› በማለት ተናግሯል፡፡ በመቅድመ ወንጌል ትርጓሜ ላይም እንዲህ ይላል፤ ‹‹ምድረ ፍልስጥኤም ለማቴዎስ በዕጣ ደረሰችው፡፡ ከዚያ ገብቶ ጌታ ከፅንስ ጀምሮ ያደረገውን ተአምር፣ ያስተማረውን ትምህርት፣ የሠራውን ትሩፋት ቢነግራቸው እስራኤል ናቸውና ከኦሪት ወደ ወንጌል፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመለሱ፤ አመኑ፤ ተጠመቁ፡፡ ትምህርት ካልደሰበት ለማዳረስ ወጥቶ በሚሔድበት ጊዜም ‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል› ብለውት ጽፎላቸዋል››፡፡

የሐዋርያው አገልግሎት በኢትዮጵያ 

አውሳብዮስ ዘቂሣርያ እና ሩፊኖስ የጻፏቸው ማስረጃዎች እንደሚያስረዱት ቅዱስ ማቴዎስ በእስራኤል፣ በኢትዮጵያ፣ በፋርስ፣ በባቢሎን፣ በዓረቢያ፣ በግሪክ፣ በፍልስጥኤም እና በብሔረ ብፁዓን ወንጌልን አስተምሯል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ቅዱስ ማቴዎስ በአገራችን ኢትዮጵያ በትግራይ አካባቢ ከዓድዋ አውራጃ በስተምዕራብ ልዩ ስሙ ናዕይር በተባለው ቦታ ወንጌልን አስተምሯል፡፡

ሐዋርያው በብሔረ ብፁዓን

ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ብሔረ ብፁዓን በደመና ተጭኖ ሔዶ ማስተማሩን ገድለ ዞሲማስ (ዘሲማስ) ያስረዳል፡፡ ከቅዱስ ማቴዎስ በኋላ በብሔረ ብፁዓን ስለሚኖሩ ወገኖች አኗኗር በጥልቀት በቀሲስ ዞሲማስ የተዘረዘረ ሲኾን ለእነዚህ ወገኖች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱስ ማቴዎስም ወንጌልን እንዳስተማሯቸው በመጽሐፈ ገድሉ ተጠቅሷል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዂልጊዜ በየበዓላቸው ወደ ብሔረ ብፁዓን መሔዱ፣ ቅዱስ ማቴዎስም ከቅዱሳን መላእክት እና ሄሮድስ ካስገደላቸው አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናት ጋር እግዚአብሔርን ማመስገኑ ተገልጿል፡፡

የሐዋርያው ተጋድሎና የምስክርነቱ ፍጻሜ

የቅዱስ ማቴዎስ ተጋድሎውና የምስክርነቱ ፍጻሜ ሲቃረብ ወደ አንዲት ከተማ ገብቶ አስተማረ፡፡ በዚያም ብዙዎችንም አሳመነ፡፡ አገረ ገዢውም ይዞ ከወኅኒ ቤት ጨመረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም አንድ እጅግ የሚያዝን እስረኛ አገኘና ስለ ሐዘኑ ጠየቀው፡፡ እርሱም ብዙ የጌታው ገንዘብ ከባሕር እንደ ሰጠመበት ነገረው፡፡ ሐዋርያው ማቴዎስም እስረኛው የጠፋበትን ገንዘብ የሚያገኝበትን የባሕር ዳርቻ ጠቆመው፡፡ እስረኛውም ሐዋርያው በነገረው መሠረት የጠፋውን ገንዘብ አግኝቶ ለጌታውም ሰጠው፡፡ ጌታውም ከየት እንዳገኘው ቢጠይቀው ከወኅኒ ቤት ባገኘው በሐዋርያው ማቴዎስ ጥቆማ የጠፋውን ገንዘብ ሊያገኘው መቻሉን ነገረው፡፡ ጌታው ግን ሊያምነው አልቻለም ነበር፡፡

ይልቁንም እጅግ ተቆጥቶ ሐዋርያውን ከእስር ቤት አስወጥቶ ወደ ንጉሡ ወሰደው፡፡ ንጉሡም ተዝካሩን አውጥቶ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የተከተለውን ሐዋርያ ቅዱስ ማቴዎስን ወዲያው በሰይፍ ራሱን እንዲቆርጡት፣ ሥጋውንም ለሰማይ ወፎች እንዲጥሉት አዘዘ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም በታዘዙት መሠረት ጥቅምት ፲፪ ቀን በ፷ ዓ.ም የሐዋርያውን አንገት በሰይፍ ቆርጠው ራሱን ለብቻ፣ ሰውነቱን ለብቻ አድርገው አሞሮች እንዲበሉት ጥለውት ሔዱ፡፡ ምእመናንም ራሱንና ቀሪው ሰውነቱን በአንድ አድርገው ካባቶቹ መቃብር እንዲቀበር አደረጉ፡፡ ያ ሐዘንተኛ እስረኛም የቅዱስ ማቴዎስን መገደል ሲሰማ ለሦስት ቀናት እያዘነ አለቀሰ፡፡ ከቅዱስ ማቴዎስ ሞት በኋላ አምስት ቀናት ቆይቶ እርሱም ዐረፈ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን! እኛንም ተዝካሩን አውጥቶ፣ ሥልጣኑንና ሥራውን ትቶ፣ የሚበልጠውን ሰማያዊ መንግሥት ሽቶ ክርስቶስን በተከተለው ሐዋርያ በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- የጥቅምት ፲፪ ቀን ስንክሳር እና ገድለ ሐዋርያት፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌላዊ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

የጌታችን፣ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌልን ለመላው ዓለም በማብሠር መምለክያነ ጣዖትን ወደ አሚነ እግዚአብሔር፣ አሕዛብን ወደ ክርስትና ከመለሱ ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አንደኛው ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ አገሩ ናዝሬት፣ የዘር ሐረጉም ከይሳኮር ነገድ ሲኾን አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡ ለደቀ መዝሙርነት ከመመረጡ በፊት ‹ሌዊ› ይባል ነበረ፤ ከተጠራ በኋላ ግን ‹ማቴዎስ› ተብሏል፡፡ ‹ማቴዎስ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ጸጋ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ስጦታ)› ማለት ሲኾን ስሙን ያወጣለትም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለወንጌል አገልግሎት የተጠራውም በቅፍርናሆም ከተማ ከቀራጭነት ሥራ ላይ ነው (ማቴ. ፱፥፱-፲፫፤ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪)፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ቍጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ሲኾን ከ፬ቱ ወንጌሎች አንደኛውን የጻፈው እርሱ በመኾኑ ‹ወንጌላዊ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወንጌሉን የጻፈውም ጌታችን ባረገ በ፰ኛው ዓመት መጨረሻ በ፵፩ (፵፪) ዓ.ም፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዘመን ነው፡፡ ወንሉን የጻፈበት ቋንቋ ዕብራይስጥ ሲኾን ጽሕፈቱንም በፍልስጥኤም አገር ጀምሮ በህንድ ፈጽሞታል (ማቴ. ፳፰፥፳)፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈበት ምክንያትም በሀገረ ስብከቱ በፍልስጥኤም ጌታችን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርትና የሠራቸውን ትሩፋቶች ሲያስተምራቸው ብዙ አሕዛብ ከኦሪት ወደ ወንጌል፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰዋል፡፡ እነዚህ ምእመናን ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ያስተማርኸንን ጻፍልን›› ብለውት፤ አንድም እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ (አመንጭቶ)፤ አንድም አይሁድ ክርስቲያኖችን ‹‹ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መኾኑን ሠፍራችሁ፣ ቈጥራችሁ አስረዱን›› ቢሏቸው ለማስረዳት የዕውቀት ማነስ ነበረባቸውና እርሱ ጽፎላቸዋል፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንደሚስተምሩት የማቴዎስ ወንጌል በውስጡ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማካተቱ አይሁድን ለማሳመን የተጻፈ ለመኾኑ ማስረጃ ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ከኦሪታዊ ይዘቱ አኳያ በመጀመሪያ ተቀመጠ እንጂ የተጻፈው ግን ከማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ እንደኾነም መምህራኑ ያስረዳሉ፡፡ ወንጌሉን ከጻፈ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ አፓንጌ በሚባል አገር ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በክርስቶስ አሳምኗል፡፡ የማቴዎስን ወንጌል ወንጌላዊው (ሐዋርያው) ዮሐንስ በእልአንሳን፣ በህንድና በኢየሩሳሌም አገሮች እየተረጐመ አስተምሮታል፡፡ የእርሱ ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጠቀሱም መላ ሕይወቱን ለክርስቶስ አገልግሎት የሰጠ ሐዋርያ መኾኑን እንደሚያሳይ መምህራን ይመሰክራሉ፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹‹ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም›› በማለት የክርስቶስን ምድራዊ ልደት (ሰው መኾን) ጽፏልና ከአራቱ የኪሩቤል ገጽ መካከል በአንደኛው በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ የኤፌሶን ወንዝ ፈለገ ሐሊብ ይባላል፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም በዘር የሚወለዱ አበውን ልደት ጽፏልና፤ ዳግመኛም ሄሮድስ ስላስፈጃቸው ሕፃናት ተናግሯልና በኤፌሶን ወንዝ ይመሰላል፡፡

ወንጌልን አስተምሮ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ከመለሰ በኋላ ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድና የካህን ልብስ ለብሶ፣ ፀጉሩንና ጺሙን ተላጭቶ፣ በቀኝ እጁ ዘንባባ ይዞ ወደ አገሩ ቅፅር እንዲገባ ስላዘዘው በደመና ተጭኖ ሔዶ ወደ ቤተ ጣዖታቱ ገብቶ በጸለየ ጊዜ መብረቅ የመሰለ ብርሃን ወረደ፡፡ የአምላክን ከሃሊነት ለመግለጥ በተከሠተው ርዕደ መሬትም የአገሩ ጣዖታት ዂሉ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ አርሚስ የሚባለው የጣዖቱ ካህንም ካየው አምላካዊ ብርሃንና ድንቅ ተአምር የተነሣ በክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ የቅዱስ ማቴዎስ ረድእ ኾኗል፡፡

ይህ ክሥተትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን በክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ያማኞች ቍጥርም ፬ ሺሕ እንደ ነበረ በገድለ ሐዋርያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ በሞተ ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ ከሞት ቢያስነሣው ንጉሡ፣ ቤተሰቦቹና የአገሩ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው አጵሎን የተባለውን ጣዖት በእሳት አቃጥለው ቤተ ጣዖቱን የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ ሥፍራ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አርሚስን ኤጲስ ቆጶስ በማድረግ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሞላቸዋል፡፡

በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ ‹‹አምላካችንን ሰደበብን›› ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ወንጌልን ይሰብክ ነበር፡፡

ቅዱስ ማቴዎስ በ፵ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ወንጌልን እንደ ሰበከና በዘመኑ የነበሩ ኦሪታውያን ነገሥታትን ጨምሮ በርካታ አሕዛብን አስተምሮ በማጥመቅ ወደ ክርስትና ሃይማኖት እንደ መለሰ፤ እንደዚሁም ለምጻሞችን በማንጻት፣ አንካሶችን በማርታት፣ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና በትግራይ ክልል በማኅበረ ጻድቃን ዴጌ ገዳም የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡

ወንጌላዊው በአገልግሎቱ መጨረሻም በትርያ በምትባል አገር ሲያስተምር አገረ ገዥው አሠረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም ጌታው ለንግድ የሰጠውን ገንዘብ ማዕበል ወስዶበት በዕዳ ምክንያት የሚያለቅስ አንድ እሥረኛ አገኘና አጽናንቶ መኰንኑ ገንዘቡን ከሕዝቡ ለምኖ እንዲከፍለው በመሻት ከእሥር እንደሚፈታው፤ ከባሕር ዳርቻም የወደቀ ወርቅ የተሞላ ከረጢት እንደሚያገኝ፤ ያንንም ለጌታው ከሰጠ በኋላ ከዕዳና ከእሥር ነጻ እንደሚኾን አስረዳው፡፡ ሰውየውም ቅዱስ ማቴዎስ የተናገረው ዂሉ ስለ ተፈጸመለት ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ›› እያለ፤ ለቅዱስ ማቴዎስ እየሰገደ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመኑን ተናገረ፤ ደስታውን ገለጸ፡፡

ይህንን ድንቅ ተአምር የሰሙ ብዙ አሕዛብም በጌታችን አምነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አርያኖስ በሚባል ንጉሥ ትእዛዝ ጥቅምት ፲፪ ቀን አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ዐርፏል፤ ምእመናንም ሥጋውን በክብር ቀብረውታል፡፡ ትርጓሜ ወንጌል ደግሞ ብስባራ በምትባል አገር በደንጊያ ተወግሮ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የቂሣርያ ክፍለ ዕጣ በምትኾን በቅርጣግና መቀበሩን ይናገራል፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ይደርብን፡፡

ምንጮች፡

  • መጽሐፈ ስንክሳር፣ ጥቅምት ፲፪ ቀን፤
  • የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤
  • የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፤
  • ገድለ ሐዋርያት፡፡

ዘመነ ጽጌ  

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በአገራችን በኢትዮጵያ የወቅቶች ሥርዓተ ዑደት መሠረት ከመስከረም ፳፮ ቀን ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ፺ ቀናትን የሚያጠቃልለው ጊዜ ‹ዘመነ መጸው› ይባላል፡፡ ‹መጸው› ማለት ‹ወርኀ ነፋስ› (የነፋስ ወቅት) ማለት ሲኾን ይኸውም ‹መጸወ ባጀ፤ መጽለወ ጠወለገ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ዘመነ መጸው ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ የሚብት (የሚገባ) የልምላሜ፣ አበባ፣ የፍሬ ወቅት ነው፡፡ በውስጡም አምስት ንዑሳን ክፍሎችን የሚያካትት ሲኾን እነዚህም፡- ዘመነ ጽጌ፣ ዘመነ አስተምህሮ፣ ዘመነ ስብከት፣ ዘመነ ብርሃን እና ዘመነ ኖላዊ ናቸው (ያሬድና ዜማው፣ ገጽ ፵፰-፵፱)፡፡

ከአምስቱ የዘመነ መጸው ክፍሎች መካከልም የመጀመሪያው ክፍል ‹ዘመነ ጽጌ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ቀን ድረስ ያሉትን ፵ ቀናት ያጠቃልላል፡፡ ‹ጽጌ› ቃሉ ‹ጸገየ አበበ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም አባባ ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ጽጌ› ደግሞ ‹የአበባ ወቅት፣ የአበባ ጊዜ፣ የአበባ ዘመን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ዕፀዋት በአበባ የሚያጌጡበት፣ ምድር በአበቦች ኅብረ ቀለማት የምታሸበርቅበት፣ ወንዞች ንጹሕ የሚኾኑበት፣ ጥሩ አየር የሚነፍስበት፣ አዕዋፍ በዝማሬ የሚደሰቱበት፣ እኛም የሰው ልጆች ‹‹አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት፤ አቤቱ ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት›› እያልን የዘመናት አስገኚ እና ባለቤት የኾነውን ልዑል እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፤ ከዚህም ባሻገር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከተወደደ ልጇ ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ ምድር መሰደዷን የምናስብበት ወቅት ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም በተወለደ ጊዜ የዘመኑ ንጉሥ ሄሮድስ ሥልጣኔን ይቀማኛል በሚል ቅናት ተነሣሥቶ ጌታችንን ለማስገደል አሰበ፡፡ ጌታችንም በተአምራት መዳን ሲቻለው የትዕግሥት፣ የትሕትና አምላክ ነውና በለበሰው ሥጋ በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም ጀርባ ታዝሎ በመልአኩ ተራዳኢነት፣ በአረጋዊው ዮሴፍ ጠባቂነትና በሰሎሜ ድጋፍ ከገሊላ ወደ ግብጽ ተሰዶ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቆይቷል፡፡ ሄሮድስም ጌታን ያገኘሁ መስሎት በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የሚገኙ የሁለት ዓመት ከዚያ በታች የኾኑ አንድ መቶ ዐርባ አራት ሺሕ ሕፃናትን በሰይፍ አስጨርሷል፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን የጌታችን እና የእመቤታችን የስደት ወቅት በወርኀ ግንቦት ነው፡፡ ነገር ግን ዘመነ ጽጌ የአበባ፣ የፍሬ ወቅት በመኾኑ እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የስደቱ ጊዜ ከመስከረም እስከ ኅዳር ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡ ይህ የእመቤታችን አበባነትና የጌታችን ፍሬነትም እንደ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫና አባ ጽጌ ድንግል ባሉ ሊቃውንት ድርሰቶች በስፋት ተገልጧል፡፡ በተለይ በአባ ጽጌ ድንግል ድርሰት በማኅሌተ ጽጌ በጥልቀት ተመሥጥሯል፡፡

በአጠቃላይ በዘመነ ጽጌ በማኅሌትና በቅዳሴ ጊዜ የሚቀርቡ መዝሙራትና የሚሰጡ ትምህርቶችም ይህንኑ ምሥጢር የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሚገኙ ሰንበታት ሊቃውንቱ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እመቤታችን አበባነትና ስለ ጌታችን ፍሬነት የሚያትት ትምህርት የያዙትን ማኅሌተ ጽጌና፣ ሰቆቃወ ድንግልን ከቅዱስ ያሬድ ዚቅ ጋር በማስማማት ሲዘምሩ፣ ሲያሸበሽቡ ያድራሉ፡፡ ቅዳሴውም በአባ ሕርያቆስ የተደረሰውና ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ሥላሴንና ነገረ ማርያምን በጥልቅ ትምህርተ ሃይማኖት የሚያትተው ቅዳሴ ማርያም ነው፡፡ ምንባባቱም ከዚሁ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው፡፡

በተአምረ ማርያም እና በማኅሌተ ጽጌ ተጽፎ እንደሚገኘው ጌታችን በግብጽ ምድር በስደት ሳለ ብዙ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም እናቱን እመቤታችንን የዘለፏትን ትዕማንና ኮቲባ የሚባሉ ሴቶችን ከሰውነት ወደ ውሻነት መቀየሩ፤ ውኃ በጠማቸው ጊዜ ውኃ እያፈለቀ ማጠጣቱና ይህንንም ውኃ ክፉዎች እንዳይጠጡት ማምረሩ፤ ለችግረኞችና ለበሽተኞች ግን ጣፋጭ መጠጥና ፈዋሽ ጠበል ማድረጉ፤ ‹‹የሄሮድስ ጭፍሮች ደርሰው ልጅሽን ሊገድሉብሽ ነው›› ብሎ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ እመቤታችንን በማስደንገጡ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ድንጋይ ኾኖ እንዲቆይ ማዘዙ፤ መንገድ ላይ የተራዳቸው ሽፍታ ሰይፉ በተሰበረች ጊዜ ሰይፉን በተአምራት እንደ ቀድሞው ማደሱ፤ እንደዚሁም የግብጽ ጣዖታትን በአምላክነቱ ቀጥቅጦ ማጥፋቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራ በማስታወስ ዘመነ ጽጌን በፈቃዳቸው የሚጾሙ ካህናትና ምእመናን ብዙዎች ናቸው፡፡ ኾኖም ግን የጽጌ ጾም የፈቃድ ጾም እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት ጋር የሚመደብ ስላልኾነ ጽጌን የማይጾሙ አባቶች ካህናትንና ምእመናንን ልንነቅፋቸው አይገባም፡፡ የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በሄሮድስ እጅ በግፍ የተሠዉ ሕፃናት በረከት አይለየን፡፡ አምላካችን በአበባ የሚመሰለው ሰውነታችን የጽድቅ ፍሬን ሳያፈራ እና ንስሐ ሳንገባ በሞት እንዳንወሰድ መልካም ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ብዙኃን ማርያም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን ከሚዘከሩ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓላት መካከል መስከረም ፳፩ ቀን የሚውለው በዓል ብዙኃን ማርያም በመባል ይታወቃል፡፡ በዓሉ በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ይከበራል፤ የመጀመሪያው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ ውሳኔ ለማዘጋጀት ከሩቅም ከቅርብም የተሰባበሰቡት ቀን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀል በግሸን ደብረ ከርቤ የተቀመጠበት ዕለት መኾኑ ነው፡፡ ሁለቱንም ታሪኮች ከዚህ ቀጥለን እንመለከታቸዋለን፤

በ፫፻፳፭ ዓ.ም አርዮስ የሚባል መናፍቅ የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት አልቀበልም በሚል ክህደት እርሱ ተሰናክሎ ለሌሎችም መሰናክል ኾነ፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት አርዮስ ክህደቱን እንዲተው ቢመክሩትም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ይህ የአርዮስ ክህደትም በሊቃውንቱ መካከል መለያየትን ፈጠረ፡፡ ጊዜው ታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ‹‹አብያተ ጣዖታት ይትአጸዋ አብያተ ክርስቲያናት ይትረኀዋ፤ የጣዖታት ቤቶች ይዘጉ! አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ!›› የሚል ዐዋጅ የነገረበት ወቅት ነበርና ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በአርዮስ ክህደት ምክንያት በኒቅያ የሃይማኖት ጉባኤ እንዲካሔድ በየአገሩ ላሉ ሊቃውንት መልእክት አስተላለፈ፡፡

በዚህም መሠረት ከሚያዝያ ፳፩ ቀን ጀምሮ እስከ መስከረም ፳፩ ቀን ድረስ ፳፫፻፵፰ (ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ዐርባ ስምንት) ሊቃውንት በኒቅያ ተሰበሰቡ፡፡ ኒቅያ ለዚህ ጉባኤ የተመረጠችበት ምክንያትም ጳጳሱን ከማኅበረ ካህናቱ፤ ንጉሡን ከሠራዊቱ ጋር አጠቃላ ለመያዝ የምትችል ሰፊና ምቹ ቦታ ከመኾኗ ባሻገር ለኹሉም አማካይ ሥፍራ ስለነበረች ነው፡፡ በጉባኤው ከተሰበሰቡ ሊቃውንት መካከልም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ሙታንን ያስነሡ፣ ለምጽ ያነጹ፣ አንካሳ ያረቱ፣ የዕውራንን ዓይን ያበሩ ድውያንን የፈወሱ፣ ሌላም ልዩ ልዩ ተአምር ያደረጉ፤ እንደዚሁም ስለ ርትዕት ሃይማኖታቸው በመጋደል ዓይናቸው የፈረጠ፣ እጃቸው የተቈረጠ አበው ይገኙበታል፡፡

ሊቃውንቱ ሱባዔ ይዘው በጸሎት ከቆዩ በኋላ ኅዳር ፱ ቀን በንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ሊቀ መንበርነት፣ በእለእስክንድሮስ አፈ ጉባኤነት ጉባኤው ተጀመረ፡፡ ንጉሡ ሊቃውንቱን ‹‹ስማችሁን፣ አገራችሁንና ሃይማኖታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝ›› ባላቸው ጊዜም ከ፳፫፻፵፰ቱ መካከል ፫፻፲፰ (ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ሃይማኖታቸውን ሲገልጹ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው ‹‹ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ፤ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና አንድ ነው›› ብለው ጽፈው ሰጡት፡፡ ንጉሡም ‹‹ሃይማኖት እንደ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት ይኹን›› ብሎ ዐዋጅ አስነግሯል፡፡

፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በጉባኤው አርዮስን አውግዘው በመለየት ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ፤ በአንድ አምላክ እናምናለን›› የሚለውን የሃይማኖት ጸሎት (የሃይማኖት መሠረት) እና ሌሎችንም የሃይማኖት ውሳኔዎች ደንግገዋል፡፡ ሊቃውንቱ ጉባኤውን ያካሔዱት ኅዳር ፱ ቀን ይኹን እንጂ በአንድነት የተሰባሰቡት መስከረም ፳፩ ቀን ስለ ነበረ ይህ ዕለት ብዙኃን ማርያም እየተባለ ይጠራል፡፡ ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሃይማኖታዊ ጉባኤ የተሳባሰቡበት ዕለት ነውና፡፡ እነዚህ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሱት የአብርሃም ብላቴኖች ምሳሌዎች ናቸው (ዘፍ. ፲፬፥፲፬)፡፡

በሌላ በኩል መስከረም ፳፩ ቀን የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአምባሰል ተራራ በግሸን ደብረ ከርቤ የገባበትና በዓሉ የከበረበት ዕለት ነው፡፡ ታሪኩም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

ዐፄ ዳዊት መንፈሳዊና ደግ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዘመናቸው በኢትዮጵያ ቸነፈር ተከሥቶ ሕዝቡ ስለ ተሰቃየባቸው እጅግ አዘኑ፤ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላኩ ባሕታዊ መጥተው ‹‹የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል አስመጥተህ በአገርህ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተህ ብታስቀምጥ ረሃቡ፣ ቸነፈሩ ኹሉ ይታገሥልሃል›› አሏቸው፡፡ ዐፄ ዳዊትም ከብዙ ገጸ በረከት (ስጦታ) ጋር ‹‹የጌታችንን መስቀል ላኩልኝ›› የሚል መልእክት አስይዘው መልእክተኞችን ወደ ኢየሩሳሌም ሰደዱ፡፡ መልእክተኞቹም በታዘዙት መሠረት መስቀሉን ይዘው መምጣታቸውን ዐፄ ዳዊት ሲሰሙ ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ብለው አሳውጀው መስቀሉን ለመቀበል ጉዞ ጀመሩ፡፡

ዐፄ ዳዊት ስናር (ሱዳን) ደርሰው ከመልእክተኞቹ ጋር ተገናኝተው መስቀሉን በክብር አጅበው ወደ መካከል ኢትዮጵያ ለማስገባት ሲነሡም ከበቅሏቸው ወድቀው ጥቅምት ፱ ቀን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በዚህም ሠራዊታቸው ተደናግጠው የጌታችንን መስቀል እዚያው ትተው የዐፄ ዳዊትን አስከሬን ይዘው ተመለሱ፡፡ መስቀሉ በስናር ከቆየ በኋላ የዐፄ ዳዊት ልጅ ዘርዐ ያዕቆብ ሲነግሡ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አምጥተው ቤተ ክርስቲያን አሠርተው ለማስቀመጥ ቢያስቡም ምቹ ቦታ ግን ሊያገኙ አልቻሉም ነበር፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው ምቹ ቦታ ሲፈልጉ መስቀሉን በኤረር ተራራ፣ በደብረ ብርሃን፣ በመናገሻ ማርያም ዓምባ፣ በእንጦጦ ጋራ ብዙ ጊዜ አስቀምጠውት ቆይተዋል፡፡

መስቀሉ በእንጦጦ ጋራ ሳለ እግዚአብሔር አምላክ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› የሚል ቃል ለንጉሡ በራእይ ነገራቸው፡፡ መስቀሉን ወደወሎ ሀገረ ስብከት እንዲወስዱትም አዘዛቸው፡፡ ንጉሡና ሠራዊታቸው በእግዚአብሔር መሪነት መስቀሉን ይዘው ወሎ ሲደርሱም ጌታችን ወደ አምባሰል እያመለከተ ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ተራራ ላይ አስቀምጥ›› ይላቸው ነበር፡፡ ንጉሡ መስቀሉን ይዘው ወደ ቦታው ሲያመሩ መስቀለኛው የግሸን ተራራን አገኙ፤ በዚያም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው በ፲፬፻፵፮ (1446) ዓ.ም የጌታችንን መስቀል በክብር አስቀምጠውታል፡፡

ከዚህ በኋላ ንጉሡ ‹‹መካከሏ ገነት፤ ዳሯ እሳት ይኹን! የበረረ ወፍ፣ የሠገረ ቆቅ አይታደንባት! በድንገት ሰው የገደለ፣ ቋንጃ የቈረጠ ወንጀለኛ አይያዝባት!›› ብለው ዐዋጅ አስነግረዋል፡፡ የእመቤታችን ጽላትም አብሮ በግሸን ደብረ ከርቤ እንዲቀመጥ አድርገዋል፡፡ ስለዚህም መስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ይከበራል፡፡ ኀጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሐ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ምእመናን ኹሉ እስከሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ጤፉት በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የክርስቶስ የመስቀሉ ኃይል፣ የአባቶቻችን ሊቃውንትና ነገሥታት በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ / አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ .ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ ፫፻፶፬፫፻፶፮፡፡

ተአምረ ማርያም በጼዴንያ

በዝግጅት ክፍሉ

መስከረም ፲ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን ከሚዘከሩ በዓላት መካከል የእመቤታችን በዓል አንደኛው ሲኾን ይኸውም ጼዴንያ በምትባል አገር ከሥዕሏ ተአምር የተደረገበት ዕለት ነው፡፡ በተአምረ ማርያም እና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበው ቅዱስ ሉቃስ ከሣላት ሥጋ የለበሰች ከምትመስል የእመቤታችን የሥዕል ሠሌዳ ቅባት ይንጠፈጠፍ ነበር፡፡ ከዚህች የእመቤታችን ሥዕል የተገለጠው ተአምርና ታሪክም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የምትወድና በሚቻላትም ዂሉ የምታገለግላት፣ ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች አንዲት ማርታ የምትባል ሴት ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባሉ መነኵሴ ከእርሷ ዘንድ በእንግድነት አድረው በማግሥቱ ከቤቷ ሲወጡ ማርታ የሚሔዱበትን አገር በጠየቀቻቸው ጊዜ  እርሳቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ቅዱሳት መካናትን እንደሚሳለሙ ነገሯት፡፡ ማርታም ከእርሷ ገንዘብ ወስደው የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተው ይዘውላት እንዲመጡ ለመነቻቸው፡፡ መነኵሴውም በራሳቸው ገንዘብ ሥዕሉን ገዝተው እንደሚያመጡላት ቃል ገቡላት፡፡ አባ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ከተሳለሙ በኋላ ሥዕሏን ሳይገዙ ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ?›› የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰምተው ወደ ገበያ ተመልሰው መልኳ ያማረና የተወደደ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕል ገዝተው በሐርና በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ይዘው እየተጓዙ ሳሉ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ደረሱ፡፡ በዚያም ወንበዴዎች ተነሡባቸውና ከእነርሱ ሊሸሹ ሲሉ ‹‹መንገድህን ሒድ›› የሚል ቃል ከሥዕሏ ወጣ፤ መነኵሴውም መንገዳቸውን በሰላም ተጓዙ፡፡ ሁለተኛም አንበሳ ሊበላቸው በተነሣባቸው ጊዜ ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረላቸው፡፡

አባ ቴዎድሮስ ይህን ዂሉ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜም ያቺን ሥዕል ለማርታ ከመስጠት ይልቅ ወደ አገራቸው ሊወስዷት ወደዱ፡፡ በመርከብ ተሳፍረው በሌላ አቅጣጫ ሲሔዱም ታላቅ ነፋስ ተነሥቶ ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያ ወሰዳቸው፡፡ ከመርከብም ወርደው ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ደረሱ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን ለማርታ አልገለጡላትም፤ እርሷም አላወቀቻቸውም ነበር፡፡ በማግሥቱም ተሠውረው ወደ አገራቸው ሊሔዱ ሲሉ የቅፅሩ ደጃፍ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ዋሉ፡፡ በመሸባቸው ጊዜም ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ፡፡ ማታ ማታ በሩን ያዩታል፤ ነግቶ መሔድን ሲሹ ግን የበሩ መንገድ ይሠወርባቸዋል፡፡ እንዲህም ኾነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ማርታም ‹‹አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ኾነህ ነው?›› ሰትል ጠየቀቻችው፡፡ እርሳቸውም ከእመቤታችን ሥዕል የተደረገውን ተአምር እና ሥዕሏን ይዘው ለመጥፋት ያደረጉትን ጥረት ዂሉ ነግረው፣ ራሳቸውን ገልጠው ሥዕሏን ሰጧት፡፡ እርሷም የእመቤታችንን ሥዕል ተቀብላ የተጠቀለለችበትን ልብስ በፈታችው ጊዜ ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋ ብዛት የተነሣም የአባ ቴዎድሮስን እጃቸውንና እግራቸውን ሳመች፡፡

ከዚህም በኋላ ያቺን ሥዕል ወደ ጸሎት ቤቷ ወስዳ በታላቅ ክብር አኖረቻት፡፡ ማንም እንዳይዳስሳትም የነሐስ መስኮትን ሠራችላት፡፡ በቀንና በሌሊትም የሚያበሩ መቅረዞችን በፊቷ ሰቀለች፤ ከመቅረዞች ውጭም የሐር መጋረጃን ጋረደች፡፡ ከሥዕሊቱ በታችም እየተንጠፈጠፈ የሚወርደው የወዝ ቅባት የሚጠራቀምበት ከዕብነ በረድ የተሠራ ወጭት አኖረች፡፡ እኒያ መነኰስም እስከሚሞቱበት ቀን ድረስ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ሥዕል እያገለገሉ ኖሩ፡፡ የአገሩ ሊቀ ጳጳስም የእመቤታችን ሥዕል ሥጋ የለበሰች ኹና ባገኙና ተአምሯንም በተመለከቱ ጊዜ ከዚህ አምላካዊ ግብር የተነሣ አደነቁ፡፡ ከሥዕሏ ከሚንጠባጠበው ቅባት ቀድተው ለበረከት ሲካፈሉም ወዲያውኑ በወጭቱ ውስጥ መላ፡፡ ሥዕሊቱን ወደ ሌላ ቦታም ሊወስዷት በፈለጉ ጊዜም ንውጽውጽታ ኾኖ ብዙዎች በድንጋጤ ወደቁ፡፡ ሥዕሊቱም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያች አገር (በጼዴንያ) ትገኛለች፡፡

‹‹እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፷፯፥፴፭) እግዚአብሔር አምላካችን በልዩ ልዩ መንገድ ለሰው ልጅ ተአምራቱን ይገልጣል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ከዓለት ላይ ውኃ እያፈለቀ ሕዝቡን ያጠጣል፡፡ እንደዚሁም ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸውም፣ በልብሳቸውም፣ በጥላቸውም ሙታንን በማስነሣት፤ ሕሙማንን በመፈወስ ተአምራትን ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ በጥላው፤ ቅዱስ ጳውሎስም በልብሱ ቅዳጅ ያደርጓቸው የነበሩ ተአምራትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከግዑዝ ዓለት ውስጥ ውኃ የሚያፈልቅ አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፤ ከነፍሷ ነፍስ ተዋሕዶ ካከበራት ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ወዝ እንዲፈስ ቢያደርግ ምን ይሳነዋል? ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጣቸው ጸጋ በልብሳቸውና በሰውነታቸው ጥላ ተአምራትን ማድረግ እንደ ተቻላቸው ዂሉ አምላክን በማኅፀኗ የተሸከመችው ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያምም በሥዕሏ ወዝ ብዙ ሕሙማንን መፈወስ ይቻላታል፡፡ ከቅዱሳን ልብስና ጥላ የእርሷ ሥዕል ይከብራልና፡፡ ስለዚህም ነው በየዓመቱ መስከረም ፲ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት የሚከበረው፡፡

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የልጇ፣ የወዳጇ የጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር

በዲያቆን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ

መስከረም  ፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የዘመን አቈጣጠር ዓመታትን፣ ወራትን፣ ሳምንታትን፣ ዕለታትን፣ ደቂቃን እና ድቁቅ ሰዓታትን በየሥፍራቸው (በየመጠናቸው) የሚገልጽ፤ የሚተነትን፤ የሚለካ የቤተ ክርስቲያን የቍጥር ትምህርት ነው፡፡ እነዚህ ዅሉ ተመርምረው፣ ተመዝነው፣ ተቈጥረው ሲያበቁ ምድብና ቀመር ተሰጥቷቸው የሚገኙበትን ውሳኔና ድንጋጌ የሚያሳውቅ የዘመን አቈጣጠር – ‹ሐሳበ ዘመን› ይባላል፡፡ ዓመታት፣ ወራት፣ ሳምንታት፣ ዕለታትና ሰዓታት የሚለኩት (የሚሠፈሩት፣ የሚቈጠሩት) በሰባቱ መሥፈሪያና በሰባቱ አዕዋዳት ነው፡፡ ሰባቱ መሥፈርታት የሚባሉትም፡- ሳድሲት፣ ኃምሲት፣ ራብዒት፣ ሣልሲት፣ ካልዒት፣ ኬክሮስ እና ዕለት ሲኾኑ ሰባቱ አዕዋዳት ደግሞ፡- ዐውደ ዕለት፣ ዐውደ ወርኅ፣ ዐውደ ዓመት፣ ዐውደ ፀሐይ፣ ዐውደ አበቅቴ፣ ዐውደ ማኅተም እና ዐውደ ቀመር ናቸው፡፡

  • ዐውደ ዕለት – ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ያሉት ሰባቱ ዕለታት ሲኾኑ፤ አውራኅን (ወራትን) ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
  • ዐውደ ወርኅ – በፀሐይ ፴ ዕለታት፣ በጨረቃ ፳፱ ወይም ፴ ዕለታት ናቸው፤ ዓመታትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
  • ዐውደ ዓመት – በፀሐይ ቀን አቈጣጠር ፫፻፷፭ ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ፤ በጨረቃ አቈጣጠር ፫፻፶፬ ቀን ከ፳፪ ኬክሮስ ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ በዕለት፤ አራቱ ደግሞ በዓመት ይቈጠራሉ፡፡ ዘመናትን ለማስገኘት በዚህ ሲመላለሱ ይኖራሉ፡፡
  • ዐውደ ፀሐይ – ፳፰ ዓመት ነው፤ በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
  • ዐውደ አበቅቴ – ፲፱ ዓመት ነው፤ በዚህ ፀሐይና ጨረቃ ይገናኙበታል፡፡
  • ዐውደ ማኅተም – ፸፮ ዓመት ነው፤ በዚህ አበቅቴና ወንጌላዊ ይገናኙበታል፡፡
  • ዐውደ ቀመር – ፭፻፴፪ ዓመት ነው፤ በዚህ ዕለትና ወንጌላዊ፣ አበቅቴም ይገናኙበታል፡፡

የዘመናት (የጊዜያት) ክፍል እና መጠን

አንድ ዓመት በፀሐይ ፫፻፷፭ ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ፤ በጨረቃ ፫፻፶፬ ቀን ከ፳፪ ኬክሮስ ነው፡፡ አንድ ወር በፀሐይ ፴ ዕለታት አሉት፤ በጨረቃ ፳፱ ወይም ፴ ዕለታት አሉት፡፡ አንድ ዕለት ፳፬ ሰዓት፤ አንድ ቀን ፲፪ ሰዓት፤ አንድ ሰዓት ፷ ደቂቃ ነው፡፡ አንድ ደቂቃ ፷ ካልዒት፤ አንድ ካልዒት ፩ ቅጽበት ነው፡፡ ኬክሮስ ማለት የክፍለ ዕለት ሳምንት (የዕለት ፩/፷ ወይም ፩/፳፬ኛ ሰዓት) ነው፡፡ አንድ ዕለት ፳፬ ሰዓት ወይም ፷ ኬክሮስ ነው፡፡

ክፍላተ ዓመት (የዓመት ክፍሎች)

የዓመት ክፍሎች፡- መጸው፣ በጋ፣ ፀደይ እና ክረምት ናቸው፡፡

  • ከመስከረም ፳፮ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት መጸው ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት ሌሊቱ ረጅም፣ ቀኑ አጭር ነው፡፡
  • ከታኅሣሥ ፳፮ እስከ መጋቢት ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክፍለ ዓመት በጋ ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት እኩል ነው፡፡
  • ከመጋቢት ፳፮ እስከ ሰኔ ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ፀደይ ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት ቀኑ ይረዝማል፤ ሌሊቱ ያጥራል፡፡
  • ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ክረምት ይባላል፡፡ በዚህ ክፍለ ዓመት የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት እኩል ነው፡፡

የዘመናት አከፋፈል በአራቱ ወንጌላውያን እና ዘመን የሚለወጥበት ሰዓት

  • ማቴዎስ ዘመኑን ከምሽቱ ፩ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከሌሊቱ ፮ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
  • ማርቆስ ዘመኑን ከሌሊቱ ፯ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከጠዋቱ ፲፪ ሰዓት ይፈጽማል፡፡
  • ሉቃስ ዘመኑን ከጠዋቱ ፩ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከቀኑ ፮ ሰዓት (በቀትር) ይፈጽማል፡፡
  • ዮሐንስ ዘመኑን ከቀኑ ፯ ሰዓት ጀምሮ በዓመቱ ከቀትር በኋላ ከምሽቱ ፲፪ ሰዓት ይፈጽማል፡፡

የወራት፣ የሌሊትና የቀን ሥፍረ ሰዓት

  • መስከረም – ሌሊቱ ፲፪፤ መዓልቱም (ቀኑ) ፲፪ ሰዓት ነው፡፡
  • ጥቅምት – ሌሊቱ ፲፫፤ መዓልቱ ፲፩ ሰዓት ነው፡፡
  • ኅዳር – ሌሊቱ ፲፬፤ መዓልቱ ፲ ሰዓት ነው፡፡
  • ታኅሣሥ – ሌሊቱ ፲፭፤ መዓልቱ ፱ ሰዓት ነው፡፡
  • ጥር – ሌሊቱ ፲፬፤ መዓልቱ ፲ ሰዓት ነው፡፡
  • የካቲት – ሌሊቱ ፲፫፤ መዓልቱ ፲፩ ሰዓት ነው፡፡
  • መጋቢት – ሌሊቱ ፲፪፤ መዓልቱ ፲፪ ሰዓት ነው፡፡
  • ሚያዝያ – ሌሊቱ ፲፩፤ መዓልቱ ፲፫ ሰዓት ነው፡፡
  • ግንቦት – ሌሊቱ ፲፤ መዓልቱ ፲፬ ሰዓት ነው፡፡
  • ሰኔ – ሌሊቱ ፲፱፤ መዓልቱ ፲፭ ሰዓት ነው፡፡
  • ሐምሌ – ሌሊቱ ፲፤ መዓልቱ ፲፬ ሰዓት ነው፡፡
  • ነሐሴ – ሌሊቱ ፲፩፤ መዓልቱ ፲፫ ሰዓት ነው፡፡

የበዓላት እና አጽዋማት ኢየዐርግ እና ኢይወርድ (ከፍታ እና ዝቅታ)

  • ጾመ ነነዌ ከጥር ፲፯ ቀን በታች፤ ከየካቲት ፳፩ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • ዐቢይ ጾም ከየካቲት ፩ ቀን በታች፤ ከመጋቢት ፭ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • ደብረ ዘይት ከየካቲት ፳፰ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፪ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • በዓለ ሆሣዕና ከመጋቢት ፲፱ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፳፫ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • በዓለ ስቅለት ከመጋቢት ፳፬ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፳፰ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • በዓለ ትንሣኤ ከመጋቢት ፳፮ ቀን በታች፤ ከሚያዝያ ፴ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • ርክበ ካህናት ከሚያዝያ ፳ ቀን በታች፤ ከግንቦት ፳፬ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • በዓለ ዕርገት ከግንቦት ፭ ቀን በታች፤ ከሰኔ ፲፱ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • ጾመ ሐዋርያት ከግንቦት ፲፮ ቀን በታች፤ ከሰኔ ፳ ቀን በላይ አይውልም፡፡
  • ጾመ ድኅነት ከግንቦት ፲፰ ቀን በታች፤ ከሰኔ ፳፪ ቀን በላይ አይውልም፡፡

የተውሳክ አወጣጥ

፩. የዕለት ተውሳክ

የዕለት ተውሳክ በቅዳሜ ይጀምራል፡፡ የቅዳሜ ተውሳክ ፰፤ የእሑድ ተውሳክ ፯፤ የሰኞ ተውሳክ ፮፤ የማክሰኞ ተውሳክ ፭፤ የረቡዕ ተውሳክ ፬፤ የሐሙስ ተውሳክ ፫፤ የዓርብ ተውሳክ ፪ ነው፡፡

፪. የአጽዋማትና የበዓላት ተውሳክ

የነነዌ ተውሳክ አልቦ (ባዶ)፤ የዐቢይ ጾም ተውሳክ ፲፬፤ የደብረ ዘይት ተውሳክ ፩፤ የሆሣዕና ተውሳክ ፪፤ የስቅለት ተውሳክ ፯፤ የትንሣኤ ተውሳክ ፱፤ የርክበ ካህናት ተውሳክ ፫፤ የዕርገት ተውሳክ ፲፰፤ የጰራቅሊጦስ ፳፰፤ የጾመ ሐዋርያት ተውሳክ ፳፱፤ የጾመ ድኅነት ተውሳክ ፩ ነው፡፡

በዓላት እና አጽዋማት የሚውሉባቸው ዕለታት

  • ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም እና ጾመ ሐዋርያት – ሰኞ፡፡
  • ደብረ ዘይት፣ ሆሣዕና፣ ትንሣኤ እና ጰራቅሊጦስ – እሑድ፡፡
  • ስቅለት – ዓርብ፡፡
  • ርክበ ካህናት እና ጾመ ድኅነት – ረቡዕ፡፡
  • ዕርገት – ሐሙስ ቀን ይውላል፡፡

መጥቅዕ እና አበቅቴ

መጥቅዕ እና አበቅቴ ከየት መጣ ቢሉ፣

የመጀመሪያው – የፀሐይና የጨረቃ ቀን አቈጣጠር ልዩነት ነው፡፡ አንድ ዓመት በፀሐይ ፫፻፷፭ ቀን ከ፲፭ ኬክሮስ፤ በጨረቃ ፫፻፶፬ ቀን ከ፳፪ ኬክሮስ ነው፡፡ የሁለቱ ልዩነት (፫፻፷፭ – ፫፻፶፬ = ፲፩) አበቅቴ ይባላል፡፡

ሁለተኛው – የቅዱስ ድሜጥሮስ ሱባዔ ውጤት ነው፡፡ ቅዱስ ድሜጥሮስ በዓላትና አጽዋማት የሚውሉበት ቀን በጥንተ ዕለቱ እንዲውል ለማድረግ ይመኝ ነበርና ከሌሊቱ ፳፫ ሱባዔ፤ ከቀኑ ፯ ሱባዔ ገብቷል፡፡ ፳፫×፯ = ፻፷፩ ይኾናል፡፡ ፻፷፩ ለ፴ ሲካፈል ፭ ይደርስና ፲፩ ይተርፋል፤ ይህን ቀሪ አበቅቴ አለው፡፡ ፯ በሰባት ሲባዛ ፵፱ ይኾናል (፯×፯ = ፵፱)፡፡ ፵፱ ለ፴ ሲካፈል (፵፱÷፴) ፩ ደርሶ ፲፱ ይቀራል፤ ይህን ቀሪ መጥቅዕ አለው፡፡

ዓመተ ዓለምን፣ ወንጌላዊን፣ ዕለትን፣ ወንበርን፣ አበቅቴን፣ መጥቅዕን፣ መባጃ ሐመርን፣ አጽዋማትን እና በዓላትን ለይቶ ለማወቅ ሒሳባዊ ሰሌቱ እንዲሚከተለው ነው፤

ዓመተ ዓለምን ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ኵነኔ ሲደመር ዓመተ ምሕረት ሲኾን፣ ውጤቱ ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡ ለምሳሌ ፶፭፻ + ፳፻፲ = ፸፭፻፲ (5500 + 2010 = 7510)፤ ፸፭፻፲ (7510) ዓመተ ዓለም ይባላል፡፡

ወንጌላዊን ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ዓለምን ለአራት ማካፈል ነው፡፡ ዓመተ ዓለሙ ለአራት ተካፍሎ ፩ ሲቀር ዘመኑ ማቴዎስ፤ ፪ ሲቀር ማርቆስ፤ ፫ ሲቀር ሉቃስ፤ ያለ ቀሪ ሲካፈል ዮሐንስ ይኾናል፡፡

ዕለቱን (ለምሳሌ መስከረም ፩ ቀንን) ለማግኘት ስሌቱ ዓመተ ዓለም ሲደመር መጠነ ራብዒት (ለአንድ ወንጌላዊ የደረሰው) ሲካፈል ለሰባት ነው፡፡ ዓመተ ዓለም እና መጠነ ራብዒት ተደምሮ ለሰባት ተካፍሎ ፩ ሲቀር ማክሰኞ፤ ፪ ሲቀር ረቡዕ፤ ፫ ሲቀር ሐሙስ፤ ፬ ሲቀር ዓርብ፤ ፭ ሲቀር ቅዳሜ፤ ፮ ሲቀር እሑድ፤ ያለ ቀሪ እኩል ሲካፈል ሰኞ ይኾናል፡፡

ተረፈ ዘመኑን (ወንበሩን) ለማግኘት ዓመተ ዓለም ለሰባት ተካፍሎ የሚገኘው ቀሪ ተረፈ ዘመን (ወንበር) ይባላል፡፡ ከቀሪው ላይ ስለ ተጀመረ ተቈጠረ፤ ስላልተፈጸመ ታተተ (ተቀነሰ) ብሎ አንድ መቀነስ ስሌቱ ሲኾን ቀሪው ወንበር ይባላል፡፡

አበቅቴን ለማግኘት ወንበር ሲባዛ በጥንተ አበቅቴ (፲፩) ሲካፈል ለ፴ ኾኖ ቀሪው አበቅቴ ይባላል፡፡ መጥቅዕን ለማግኘት ወንበር ሲባዛ በጥንተ መጥቅዕ (፲፱) ሲካፈል ለ፴ ኾኖ ቀሪው መጥቅዕ ይባላል፡፡

ከዚህ ላይ አዋጁን (መመሪያውን) እንመልከት፤ አዋጁም መጥቅዕ ከ፲፬ በላይ ከኾነ መጥቅዕ በመስከረም ይውላል፤ የመስከረም ማግስት (ሳኒታ) የካቲት ይኾናል፡፡ ፲፬ ራሱ መጥቅዕ መኾን አይችልም፡፡ መጥቅዕ ከ፲፬ በታች ከኾነ በጥቅምት ይውላል፤ የጥቅምት ማግስት (ሳኒታ) ጥር ነው፡፡ መጥቅዕ ሲደመር አበቅቴ ውጤቱ ዅልጊዜ ፴ ነው፡፡ መጥቅዕ አልቦ (ዜሮ) ሲኾን መስከረም ፴ የዋለበት የቀኑ ተውሳክ መባጃ ሐመር ይኾናል፡፡

መባጃ ሐመርን ለማግኘት የዕለት ተውሳክ ሲደመር መጥቅዕ ሲካፈል ለሠላሳ ነው (የዕለት ተውሳክ+መጥቅዕ÷፴ = መባጃ ሐመር)፡፡ ቍጥሩ ለሠላሳ መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል፡፡

የአጽዋማት እና የበዓላት ተውሳክ አወጣጥ

ጾምን ለማግኘት ስሌቱ መባጃ ሐመር ሲደመር የጾም ተውሳክ ሲካፈል ለሠላሳ ነው (መባጃ ሐመር+የጾም ተውሳክ÷፴ = ጾም)፡፡ ቍጥሩ ለሠላሳ መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል፡፡ በዓላትን ለማግኘት ስሌቱ መባጃ ሐመር ሲደመር የበዓል ተውሳክ ሲካፈል ለሠላሳ ነው (መባጃ ሐመር+የበዓል ተውሳክ÷፴ = በዓል)፡፡ ቍጥሩ ለሠላሳ መካፈል ካልቻለ እንዳለ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ሒሳብ መሠረት በየዓመቱ የሚመላለሱ በዓላት እና አጽዋማት የሚዉሉበትን ቀን ማወቅ ይቻላል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዝክረ ዐውደ ዓመት

በዶክተር ታደለ ገድሌ

መስከረም ፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የዓለም ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ደስታ ከሚያከብራቸውና ከሚዘክራቸው በዓላት መኻከል አንዱ የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ዕለታት እየበረሩ፣ ወራት እየተቀመሩ አልፈው አዲስ ዘመን በባተ ቍጥር ሕዝብ ዅሉ ፍሥሐ ያደርጋል፡፡ ሰላምን፣ ብልጽግናን፣ ጤንነትን፣ ፍቅርን፣ … ለወዳጅ ዘመድ ይመኛል፡፡ አዲሱ ዓመት ዘመነ ሰላም፣ ዘመነ ጥጋብ … እንዲኾን መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡ አዲስ የሥራ ዕቅድና ምኞትን በስሜቱ ያሠርፃል፡፡ ወደ ተግባርም ለመተርጐም ሌት ተቀን ይፋጠናል፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በዓል መስከረም ፩ ቀን ይከበራል፡፡ ‹‹ለመኾኑ በኢትዮጵያ መስከረም የአዲስ ዓመት መባቻ ኾኖ የተመረጠው ለምንድን ነው? በአራቱ ወንጌላውያንና በአራቱ እንስሳ (ኪሩቤል) መካከል ያለው የስያሜ ትሥሥርስ ምሥጢሩ ምንድን ነው?›› የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በአእምሯችን ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ለነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ በአንድ ወቅት እነዚህን ጥያቄዎች አቅርበንላቸው (የካቲት መጽሔት፣ 15ኛ ዓመት ቍጥር 1፤ መስከረም 1984 ዓ.ም፣ ገጽ 4 – 7 እና 34)፤ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በመስከረም የሚያከብሩት ከኖኅ በፊትና በኋላ በተዘረጋው ስሌተ ዘመን እንደ ኾነ በማስረዳት የሚከተለውን ትምህርት ሰጥተዋል፤

የኢትዮጵያ ይዞታ መሠረተ ባሕርይ ከጥንት ጀምሮ ሃይማኖት ሲኾን በጽሑፍም በአፈ ታሪክም እየተወራረሰ የመጣ ነገር ነው፡፡ በሰው ፍልስፍና ወይም በመንግሥት ለውጥ ምክንያት የተናወጠ ነገር የለም፡፡ ለውጦች ጦርነቶችና ግጭቶች፣ በተለያዩ የመንግሥት መሪዎች ቢፈራረቁም መሠረተ እምነትን አልነኩም፡፡ የአገሪቱን ባህልና ታሪክ የሚነካ ለውጥ አልደረሰም፡፡ ነገር ግን ባለ ሥልጣናት በሹም ሽር ሲቀያየሩ በምርጫ የመንበረ መንግሥት መቀመጫ ቦታ ልውውጥም ሲደረግ መጥቷል፡፡ አዲስ ዓመት ከጥንት ከአዳም ጀምሮ የነበረ በዓል ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ የመጣውን የቍጥር ዘመን በጽሑፍ ያስተላለፈው ሄኖክ ነው፡፡ ይኸውም ሳምንታት በፍጥረት ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ሰባት፣ የዕለት ሰዓት ሃያ አራት፣ የወር ቀናት ሠላሳ፣ የዓመት ቀናት ሦስት መቶ ስልሳ አራት ሲኾኑ ስልሳ አምስተኛዋ መዛወሪያ ቀን ናት፡፡ ጳጕሜን አምስት ቀን ስትኾን የሚዘለው ስድስተኛው ቀን ሠግር (የወር መባቻ) ይኾናል፡፡

የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር ከጥፋት ውኃ በፊት ሦስት ትውልዶችን አሳልፏል፡፡ እነርሱም ሄኖክ፣ ላሜህና ኖኅ ናቸው፡፡ ኖኅ የሰው ልጆች ዅሉ አባት እንደ ኾነው እንደ አዳም የሚቈጠር ከጥፋት ውኃ በመጨረሻ የተረፈ አባት ነው፡፡ ኖኅ ከአባቶቹ የተቀበለውን ጥበብ ዅሉ ለልጆቹ አስተላለፈ፡፡ ለአብነትም ዛሬ የምንጠቀምበት የኮሶ መድኃኒት የኖኅ ተረፈ ጥበብ ነው፡፡ ኖኅ በሰኔ ወር ከመርከብ በወጣ ጊዜ የበግ መሥዋዕት ሠውቶ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ፡፡ እግዚአብሔርም ያን ጊዜ ከኖኅ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን መሠረተ፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ልቡ ምንም ክፉ ቢኾንና ቅጣትም የማይቀርለት ቢኾን ጨርሶ እንደማያጠፋው ለኖኅ ቃል ገባለት፡፡ ምልክቱንም የቀስቱን ደጋን ወደራሱ፣ ገመዱን ደግሞ ወደ ሰው ልጆች አድርጐ በደመና ላይ ቀስት ስሎ አሳይቶታል፡፡ 

ጌታ ‹‹መዓልትና ሌሊት፣ በጋና ክረምት፣ ብርድና ሙቀት፣ ዘርና መከር ጊዜያቸውን ጠብቀው ሲፈራረቁ ይኖራሉ፡፡ በምድር ላይ ይህ አይቀርም›› በማለት እንደ ተናገረው በቃሉ መሠረት ክረምት ገባ፡፡ ክረምቱ ካለፈ በኋላ የዓመት መሥፈሪያ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት በመኾናቸው መስከረም አንድ ቀን የአዲስ ዓመት መባቻ ኾነ፡፡ አዲስ ዓመት ሥራውን ጨርሶ በሔደ ቍጥር፣ ዕለት ግን በየጊዜው እየታደሰ ይሔዳል፡፡ እስከ አዲስ ኪዳን መጀመሪያ ድረስ አበው በልዩ ልዩ ጊዜያት የተገለጹላቸውን ምልክቶች በመያዝ የየዘመናትን ብተት (መግቢያ) የእግዚአብሔርን ዙፋን ተሸካሚ በኾኑ በኪሩቤል መላእክት እያመሳሰሉ ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም (ላም) ገጸ ንሥር (አሞራ)፣ ገጸ አንበሳ እያሉ ዓመታትን ይመድቡ ነበር፡፡ ከስብከተ ሐዲስ በኋላ ግን ይህ ተሽሮ ወንጌልን በጻፉት አርድእት ስም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ ስም ተሰየመ፡፡ ወንጌላውያኑ ወንጌልን ሲጽፉ ዕለት ተቀደም (በቅደም ተከተል) ነውና ተራቸውን ጠብቀው በየዓመቱ ይመላለሳሉ፡፡ ይህም ማለት ዘመኑ ዘመነ ምሕረት መኾኑን ለማብሠርና ድኅነት (መዳን) የሚሰበክበት ዘመን መምጣቱን ለመግለጽ ነው፡፡

በገጸ ሰብእ የተተካው ማቴዎስ ነው፡፡ ምሥጢሩም ‹‹ጌታ ከሰማይ ወረደ፤ ሰው ኾነ›› ብሎ ማስተማሩን የሚያመለክት ነው፡፡ በገጸ አንበሳ የተተካው ማርቆስ ነው፡፡ ይኸውም አሕዛብ በግብጽ (ምሥር) በላህም (በላም)፣ በጣዕዋ (ጥጃ) አምሳል ጣዖት አሠርተው ያመልኩ ስለ ነበር ያንን አምልኮ አጥፍቶ፣ ሽሮ በክርስቶስ እንዲያምኑ ስላደረገ ነው፡፡ በገጸ እንስሳ (ላህም) የተተካው ሉቃስ ነው፡፡ ምሳሌነቱም የጌታን መሥዋዕትነት ስለሚያስተምር ነው፡፡ በገጸ ንሥር የተተካው ዮሐንስ ነው፡፡ ንሥር ከአዕዋፍ ዅሉ መጥቆ ይሔዳል፡፡ መሬትም ላይ ምንም ኢ ምንት ነገር ብትወድቅ አትሠወረውም፡፡ ዓይኑ ጽሩይ (ብሩህ) ነው፡፡ ይህም ማለት ቅዱስ ዮሐንስ ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቈጠር ወደ ነበረው ኹኔታ በሕሊናው ርቆ በመሔድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቀዳማዊ ቃል መኾኑን፤ እግዚአብሔርም ዓለሙን የፈጠረው በእርሱ ቃል እምነት መኾኑን፤ ያም ቃል ሰው መኾኑን ስለሚያስተምር ነው ገጸ ንሥር የተባለው፡፡ የሦስቱ ወንጌላውያን ትምህርት ታሪክ ጠቀስ ኾኖ ለሰሚዎችና አንባቢዎች ዅሉ በቶሎ ሲረዳ፣ የዮሐንስ አስተምህሮ ግን ጥልቅ የአእምሮ ብስለትና ምርምርን ይጠይቃል፡፡

ዘመን በተለወጠ ቍጥር ከሰው ልጆች ስሜት ጋር አብሮ የሚንቀሳቀስ ተስፋ አለ፡፡ በጥፋት ዘመን ሰማይ በደመና ተሸፍኖ፣ ከላይ ዝናም፣ ከታች የሚፈልቀው ጎርፍ የኖኅ ሰዎችን አስጨንቋቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ምድር ላይ ለውጥ ታየ፡፡ ነፋስ ነፈሰ፡፡ ብርሃን ፈነጠቀ፡፡ አበባ አበበ፡፡ የኖኅ መልእክተኛ የኾነችው ርግብም ‹‹ማየ አይህ ነትገ፤ የጥፋት ውኃ ጐደለ›› እያለች ርጥብ ቄጠማ በአፏ ይዛ መጥታ ስታበሥረው የኖኅ ሰዎች ከመርከቧ ወደ መሬት ሲወርዱ በመጀመሪያ አበባ፣ እንግጫ፣ ቄጠማ፣ የለመለመ ሣር … አገኙ፡፡ እግዚአብሔርንም በአንቃዕድዎ ልቡና አመሰገኑና በዓላቸውን አከበሩ፡፡ በዚህም አምሳል ክረምት አልፎ መሬት በምታሸበርቅበት በምታብበት ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ አዲስ ዓመታችንን እናከብራለን፡፡ ሰውም ከመሬት የተገኘ በመኾኑ እንደ ዕፀዋትና እንደ አበቦች ዅሉ በመስከረም ወር በተስፋ ስሜት ይለመልማል፡፡ ያጣው አገኛለሁ፣ የታመመው እድናለሁ ብሎ በቁርጥኝነት ይነሣሣል፡፡ በዘልማድም እምነቶች ይገለጻሉ፤ ‹‹በዮሐንስ እረስ፣ በማቴዎስ እፈስ … ጳጕሜ ሲወልስ ጎታህን አብስ … ጳጕሜ ሲበራ ስንዴህን ዝራ›› እያሉ ገበሬዎች ይናገራሉ፤ ይተነብያሉ፡፡ ገበሬዎች ገና በግንቦት ወር የክረምቱን አገባብ ለይተው የሚዘሩትን ዘር ደንብተው የሚያውቁ ሜትሮሎጂስቶች (የአየር ጠባይዕ ትንበያ ባለሙያዎች) ናቸው፡፡

አለቃ አያሌው እንዳስተማሩት ዐውደ ዓመት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ መሠረት የሚከበርና መንፈሳዊ ምሥጢር ያለው ሃይማኖታዊም አገራዊም በዓል ነው፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ በዓል በቤተ ክርስቲያን ከሚፈጸመው መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር በአዲሱ ዓመት ዋይዜማ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጎዘጎዛል፡፡ አበባ በሥርዓቱ እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል፡፡ ልጆችና አረጋውያን አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ፡፡ አመሻሽ ላይ ችቦ አቀጣጥለው ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ … ኢዮሃ የበርበሬ ውኃ … በሸዋ በጎንደር፣ በትግራይ በወሎ፣ በሐረርጌ፣ በሲዳሞ … ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ? እንኳን ከዘመን ዘመን ከጨለማ (ሰኔ፣ ሐምሌ፣ ነሐሴ) ወደ ብርሃን (መስከረም) በሰላም አሸጋገራችሁ! … እንጉሮ ገባሽ በያመቱ ያምጣሽ …›› እያሉ ያቀጣጠሉትን ችቦ በአየር ላይ እየወረወሩ ደስታቸውን ሲገልጹ፣ የምሽቱም የችቦ እሳት ርቀት እስከሚወስነው አድማስ ድረስ ከቀዬ ቀዬ፣ ከአድባር እስከ አድባር፣ ከመንደር እስከ መንደር … ሲንቀለቀልና ሲንቦገቦግ መሬት የእሳት ላንቃዋ ተከፍቶ ነበልባል የምትተፋ ትመስላለች፡፡ የአየር ላይ ወጋገኑን ሲመለከቱት ደግሞ እግዚአብሔር ከመንበረ ጸባዖቱ ወርዶ የብርሃን አክሊል ደፍቶ ቀይ መጐናጸፊያ ተጎናጽፎ ጨለማውን እየገፈፈ በጠፈር (በአየር) ላይ እየተንሳፈፈ ወደ መሬት የሚወርድባት የመጨረሻዋን የምጽአትን ቀን ታስታውሳለች – የዕንቍ ጣጣሽ ሌሊት፡፡

አባቶች የችቦ ብርሃን ላሰባሰበው ሕዝብ ቡራኬና ምርቃት ያደርጋሉ፡፡ ‹‹የተዘራውን እኽል እኽለ በረከት፣ የዘነመውን ዝናም ዝናመ ምሕረት፣ ዘመኑን የሰላም ዓመት ያድርግልን፡፡ እኽል ይታፈስ፤ ይርከስ፡፡ ሳቢ በሬውን፣ አራሽ ገበሬውን ይባረክ፣ ቁንጫ፣ ተባይ ተምች፣ አንበጣ … ፀረ ሰብል ዅሉ እንደ ችቦው ተቀጣጥለው ይንደዱ …›› እያሉ ይመርቃሉ፡፡ እናት አባት በልጆቻቸው፣ በወዳጅ ዘመዶቻቸው የተበረከተላቸውን የእንግጫ ጉንጉን በራሳቸው፣ በእንጀራ ማቡኪያና መሶቡ፣ ከቤቱ ምሰሶ ላይ … ያሥራሉ፡፡ ይህ በአበባ የተዘጋጀ የእንግጫ ጉንጉን የመስቀል ደመራ ዕለት ከእሳቱም ከዐመዱም ላይ ይጣላል፡፡ ተምሳሌቱም እንደ ቁንጫ ዅሉ ቁርጥማቱ ራስ ምታቱ፣ ምችጎንፍ ቁርጠቱ፣ ምቀኛ፣ ሸረኛ፣ ሰላቢው፣ ሌባ፣ ቀማኛ ቀጣፊው … እንዲቃጠልና እንዲጠፋ ነው፡፡ በቤቱም (በአባወራው ቤት) በረከትና ሞገስ (አግሟስ) እንዲቀርብም ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መስከረም ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹እነሆሉን አዲስ አደርጋለሁአዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፡፡ ባሕርም ወደ ፊት የለም›› በማለት እንደ ተናገረው (ራእ. ፳፩፥፩-፭) ዘመን እያለፈ አዲስ ዘመን ይተካል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በዕድሜ ላይ ዕድሜን እየጨመረ፣ ዘመናትን እያፈራረቀ በየጊዜያቱ አዲስ ዓመትን ያመጣልናል፡፡ አሁንም በእርሱ ቸርነት ለ፳፻፲ ዓመተ ምሕረት ደርሰናል፡፡ እኛም ዘመን በመጣ ቊጥር ‹‹እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!›› እንባባላለን፡፡ ስለ ትናንትና እንጂ ስለ ነገ ባናውቅም እስከ ዛሬ ድረስ በመቆየታችንም እንደሰታለን፡፡ ነገን በተስፋ ለሚጠባበቅ ሰው በእውነትም ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ በጣም ያስደስታል፡፡ ነገር ግን ያለፈውን ዓመት ስንዋሽ፣ ስንሰርቅ፣ ስንዘሙት፣ ስንጣላ፣ ስንተማማ፣ ስንደባደብ፣ ስንሰክር አሳልፈን ከኾነ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› የሚለው ቃል ርግማን ይኾንብናል፡፡

ስለ ተለወጠው ዘመን ሳይኾን ስላልተቀየረው ሰብእናችን፤ ስላልተለወጠው ማንነታችን፤ ስላልታደሰው ሥጋችን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በኀጢአት እየኖሩ ዐውደ ዓመትን ማክበር ራስን ያለ ለውጥ እንዲቀጥል ማበረታታት ነውና ከምንቀበለው ዘመን ይልቅ መጪውን ዘመን ለንስሐ ለማድረግ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ያሳለፍነውን የኀጢአት ጊዜ እያሰብን እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀንን እግዚአብሔርን እያመሰገንን ሕይወታችንን በጽድቅ ልናድስ ይገባናል፡፡ በንስሐ ባልታደሰ ሕይወታችን በዕድሜ ላይ ዕድሜ ቢጨመርልን ለእኛም ለዘመኑም አይበጅምና፡፡ ‹‹ባረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፡፡ መቀደዱም የባሰ ይኾናል›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል (ማቴ. ፱፥፲፯)፡፡

ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር እየኖርን ዘመንን ብቻ የምንቈጥር ከኾነ ሕይወታችንን ከሰብአዊነት ክብር ብሎም ከክርስቲያናዊ ሕይወት በታች እናደርገዋለን፡፡ ራስን ከጊዜ ጋር ማወዳደር መቻል ክርስቲያናዊ ሓላፊነት ነው፡፡ ይኸውም ጊዜ ሳይቀድመኝ ልቅደመው ብሎ ማሰብ መቻል ነው፡፡ በአሮጌ ሕይወት ውስጥ ኾነን ዓመቱን አዲስ ከማለት ይልቅ ከኀጢአት ወደ ጽድቅ በመሸጋገር ራሳችንን በጽድቅ ሥራ ማደስ ይበልጣል፡፡ ስለዚህም ያለፈውን ዓመት በምን ኹኔታ አሳለፍሁት? በመጭው ዓመትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል? በሚል ጥያቄ መነሻነት በአዲሱ ዓመት መንፈሳዊ ዕቅድ ሊኖረን ይገባል፡፡

በመሠረቱ ዘመን ራሱን እየደገመ ይሔዳል እንጂ አዲስ ዓመት የለም፡፡ ሰዓታትም ዕለታትም እየተመላለሱ በድግግሞሽ ይመጣሉ እንጂ ከዚህ በፊት ያልነበረ ሰዓት ወይም ቀን ወይም ደግሞ ወር አለዚያም ዓመት የለም፡፡ ወርኀ መስከረምም ለብዙ ሺሕ ዓመታት ራሱን እየደገመ በየዓመቱ አዲስ ሲባል ይኖራል እንጂ ሌላ መስከረም የለም፡፡ ‹‹የኾነው ነገር እርሱ የሚኾን ነው፤ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፡፡ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ ማንምእነሆ ይህ ነገር አዲስ ነውይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል›› እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን (መክ. ፩፥፱-፲)፡፡ ዘመን አዲስ የሚባለው እኛ ሰዎች (ክርስቲያኖች) ሕይወታችንን በጽድቅ ስናድስ ነው፡፡ ያለ መልካም ሥራ የሚመጣ ዓመት፤ ከክፉ ግብር ጋር የምንቀበለው ዘመን አዲስ ሊባልም፣ ሊኾንም አይችልም፡፡ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት በመልካም ሥራ ሲዳብር ግን መጭው ዘመን ብቻ ሳይኾን ያለፈው ዘመንም አዲስ ነው፡፡

በዘመናት ዑደት ውስጥ ሕይወታቸውን በሙሉ በጽድቅ የሚያሳልፉ ወይም ኀጢአታቸውን በንስሐ የሚያጸዱ ብዙ ጻድቃን ምእመናን ቢኖሩም ሰውነታችንን ጥለን በክፉ ምግባር እየኖርን  ዕድሜያችንን የምንቈጥር ኃጥኣን ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ስለኾነም በኀጢአት ያሳለፍነውን ዘመን በማሰብ መጭውን ዘመን ለመልካም ሥነ ምግባር ልናውለው፤ አንድም ለንስሐ መግቢያ ልናደርገው ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለ ልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት፣ በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል›› በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ አስተምሮናልና (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፫)፡፡ እናም ለአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት እንደሚያስፈልግ በመረዳት ራሳችንን በንስሐ ሳሙና አሳጥበን በንጽሕና ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ታጠቡ፤ ሰውነታችሁንም አንጹ፡፡ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፡፡ ክፉ ማድረግን ተዉ … ልባችሁን አንጹ፤ ሰውነታችሁንም ንጹሕ አድርጉ›› ተብለን ታዝዘናልና (ኢሳ.፩፥፲፮፤ መጽሐፈ ኪዳን)፡፡

በአጠቃላይ በዚህ አዲስ ዓመት ከክፉ ምግባር ዅሉ ተለይተን፣ ከዚህ በፊት በሠራነው ኀጢአታችን ንስሐ ገብተን፣ ለወደፊቱ በጽድቅ ሥራ ኖረን እግዚአብሔርን ልናስደስት ይገባናል፡፡ ‹‹ይደልወነ ከመ ንግበር በዓለ ዐቢየ በኵሉ ንጽሕና እስመ ይእቲ ዕለት ቅድስት ወቡርክት፡፡ ወንርኀቅ እምኵሉ ምግባራት እኩያት፡፡ ወንወጥን ምግባራተ ሠናያተ ወሐዲሳተ በዘቦቶን ይሠምር እግዚአብሔር፤ አሁንም በፍጹም ንጽሕና ታላቅ በዓልን አድርገን ልናከብር ይገባናል፡፡ ይህቺ ዕለት ከሌሎች ዕለታት ተለይታ የተባረከች ናትና፡፡ ከክፉ ሥራዎችም ተለይተን እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸውን አዳዲስ የኾኑ በጎ ሥራዎችን እንሥራ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መጽሐፈ ስንክሳር፣ መስከረም ፩ ቀን)፡፡

የተወደዳችሁ ምእመናን! ‹‹ዐዘቅቱ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ዅሉ ዝቅ ይበል፡፡ ጠማማውም የቀና መንገድ ይኹን፡፡ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይኹን፡፡ ሥጋም የለበሰ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ›› ተብሎ እንደ ተነገረው (ሉቃ. ፫፥፫-፮) በኑፋቄ የጎደጎደው ሰውነታችንን በቃለ እግዚአብሔር በመሙላት፤ በትዕቢት የደነደነውን ተራራውን ልቡናችንን በትሕትና በማስገዛት፤ በክፋት የተጣመመው አእምሯችንን በቅንነት በማስጓዝ፤ በኀጢአት የሻከረውን ልቡናችንን በንስሐ በማስተካከል አዲሱን ዓመት የመልካም ምግባር ዘመን እናድርገው፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትኾኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ›› በማለት እንዳዘዘን (፩ኛ ቆሮ.፭፥፯)፣ በኀጢአት እርሾ የተበከለውን ሰውነታችንን በጽድቅ ሕይወት እናድሰው፡፡ በአዲሱ ዓመት በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር ከቻልን ከጊዜ ጋር የሚጣጣም አዲስ ሕይወት ይኖረናል ማለት ነው፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም የደስታችን መጠን በልክ መኾን አለበት፡፡ አሁን አሁን የበዓሉን መንፈሳዊነት የሚያጠፉ እንደ ከልክ በላይ መመገብና መመጣት፣ መስከር፣ መጨፈር፣ መጮኽ፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የውጭ ዓለም የባህል ወረራዎች በየከተሞች ተስፋፍተዋል፡፡ እነዚህ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ወጣቱን ትውልድ ለጥፋት የሚጋብዙ የኀጢአት መሣሪያዎች ናቸውና ለራሳችንም ለአገራችንም ህልውና ሲባል አጥብቀን ልንከላከላቸው ይገባል፡፡ አዲሱን ዓመት ለማየት እንደ ጓጉ በልዩ ልዩ ምክንያት ለመድረስ ያልታደሉትን፤ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘው በየጠበሉና በየሆስፒታሉ የሚሰቃዩትን፤ በጦርነት፣ በረሃብ፣ በስደት፣ ወዘተ. በመሳሰሉ ችግሮች የሚጨነቁትን ወገኖቻችንን በማሰብና መንፈሳዊ ትውፊቱን የጠበቀ አከባበርን መሠረት በማድረግ ዓመት በዓሉን ማክበር ይጠበቅብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቅዱስ ሩፋኤል

ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት

በዲያቆን ዮሴፍ ይኵኖአምላክ

ጳጕሜን ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወርኀ ጳጕሜን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ በዚህ የተነሣ ምእመናን በጾምና በጸሎት (በሱባዔ) ያሳልፏታል፡፡ በተለይም በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት (ርኅዎተ ሰማይ) መኾኑን በማመን ምእመናን ጸሎታቸውን ከምንጊዜውም በበለጠ ያቀርባሉ፡፡ ወደ ወንዞች በመሔድና በሚዘንበው ዝናብ ይጠመቃሉ፡፡ ወርኀ ጳጕሜን የጌታችን ምጽአት የሚታሰብባት በመኾኗ የሚዘመረው መዝሙር፣ የሚነበቡ ምንባባትና ቅዱስ ወንጌሉ እንደዚሁም የሚሰበከው ምስባክ ይህንኑ ምሥጢር የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡ እና ከሚከበሩ በዓላት መካከል በየዓመቱ ጳጕሜን ፫ ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ የቅዱስ ሩፋኤል በዓሉ የሚከበርባቸው ምክንያቶችም ሁለት ናቸው፤ እነርሱም አንደኛው በዓለ ሢመቱን ምክንያት በማድረግ ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ቅዳሴ ቤቱ ነው፡፡ ‹ሩፋኤል› የሚለው የስሙ ትርጓሜ ‹ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ› ማለት ነው፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ያለ ማቋረጥ ፈጣሪያቸው ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው፡፡ ‹‹ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ›› እንዲል (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡

የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቍስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ ‹‹በበሽታ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል (ሄኖክ ፲፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ‹‹በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው›› እንዳለ ሄኖክ (ሄኖክ ፮፥፫)፡፡ ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው፤ ላረገዙ ሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም፡፡ ሕፃኑ (ኗ በማኅፀን እያለ (ች) ተሥዕሎተ መልክዕ (በሥላሴ አርአያ መልኩ /ኳ/ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል በጥበቃው አይለያቸውም፡፡ በመውለጃቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀልላቸዋል፡፡

አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል (ጦቢት ፫፥፰-፲፯)፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል ‹‹ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሄኖክ ፫፥፭-፯)፡፡ ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው (ሄኖክ ፪፥፲፰)፡፡ የጦቢትን ልጁ ጦቢያን በሰው አምሳል ተገልጦ ከተራዳው በኋላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ራሱን ሲገልጥ ‹‹የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደ ገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው›› (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡

በቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት ከተደረጉ ተአምራት መካከል በእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ ደሴት በታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ ያደረገው ተአምር አንደኛው ነው፡፡ በመጽሐፈ ስንክሳር እና በድርሳነ ሩፋኤል እንደ ተጻፈው ብዙ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጠች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ዓሣ አንበሪው ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ምእመናኑም ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔር በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮኹ፡፡ ያን ጊዜ ቅዱስ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ ‹‹እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጥ ጸጥ ብለህ ቁም!›› ባለው ጊዜ አንበሪው ጸጥ ብሎ ቆሟል፡፡ በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገልጠዋል፡፡ ለሕሙማንም ፈውስ ኾኗል፡፡ የቅዱስ ሩፋኤል ተራዳዒነት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዘመነ ክረምት – ክፍል ሰባት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጳጕሜን ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች! በክፍል ስድስት ዝግጅታችን አራተኛውን የዘመነ ክረምት ንዑስ ክፍል ማለትም ጎህ፣ ነግህ፣ ጽባሕ፣ ብርሃን እና መዓልትን መነሻ አድርገን ወቅቱን ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ መንፈሳዊ ትምህርት አቅርበን ነበር፡፡ በዚህ ዝግጅት ደግሞ አምስተኛውን የዘመነ ክረምት ንዑስ ክፍል (ቀዱስ ዮሐንስን) የሚመለከት አጭር ትምህርት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ ይኹንላችሁ!

፭. ዮሐንስ

ከመስከረም ፩ – ፰ ቀን (ከዮሐንስ እስከ ዘካርያስ) ያለው አምስተኛው ክፍለ ክረምት ‹ዮሐንስ› በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ክፍለ ጊዜ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማጥመቅ የተመረጠው፣ የዓዋጅ ነጋሪው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ትምህርቱ፣ ጥምቀቱ፣ ምስክርነቱ፣ አገልግሎቱ፣ ክብሩ፣ ቅድስናው፣ ገድልና ዕረፍቱ በአጠቃላይ ዜና ሕይወቱ ከአዲሱ ዓመት ጋር እየተጣጣመ የሚዳሰስበት የብሥራት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የቅዱስ ዮሐንስን አገልግሎት የሚመለከቱ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን በስፋት ይቀርባሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ አዲስ ዓመት በመጣ ቍጥር የቅዱስ ዮሐንስ ክብረ በዓልም አብሮ ይዘከራል፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑም ለአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን ‹‹ለቅዱስ ዮሐንስ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ›› እያሉ መልካም ምኞታቸውን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መግለጻቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት የቅዱስ ዮሐንስ በዓል ከአዲስ ዓመት መባቻ ጋር በአንድነት ሲከበር ለመቆየቱ ማስረጃ ነው፡፡ ይኸውም የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከጳጕሜን ፩ ቀን ጀምሮ በእስር ቤት ከቆየ በኋላ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ቅዱሱ የሐዲስ ኪዳን አብሣሪ ነውና፣ ደግሞም ዕለቱ ቃል ኪዳን የተቀበለበት ቀን ነውና ስሙና ግብሩ ከዘመን መለወጫ ጋር አብሮ ይታወስ ዘንድ በዓሉ መስከረም ፩ ቀን በሥርዓተ ማኅሌት ይከበራል፡፡ ለዚህም ነው – ሊቃውንቱ ‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ›› እያሉ የአዲስ ዓመት መጀመርያ፣ የመጥቅዕ እና አበቅቴ መነሻ መኾኑን በሚገልጽ ኃይለ ቃል ቅዱስ ዮሐንስን የሚያወድሱት፡፡

ታሪኩን ለማስታወስ ያህል ዮሐንስ ማለት ‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው› ማለት ነው፡፡ ትርጓሜ ወንጌልም ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና (ሉቃ. ፩፥፲፬)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ የካህኑ ዘካርያስና የቅድስት ኤልሳቤጥ ልጅ ነው፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ መካን (ካ ይጠብቃል) በመኾኗ እነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር በጸሎት ይማጸኑት ነበር (ሉቃ. ፩፥፭-፯)፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የካህኑ ዘካርያስ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙን ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱ ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾን፤ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንደዚሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት የእግዚአብሔር መልአክ ለዘካርያስ ነገረው (ሉቃ.፩፥፰-፲፯)፡፡ በዚህ ቃለ ብሥራት መሠረት ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን ተወለደ፡፡ ሕፃኑ ዮሐንስም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ (ሉቃ. ፩፥፹)፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ፴ ዓመት ሲሞላውም በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል ‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!›› እያለ እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ዅሉ ወጣ (ሉቃ. ፫፥፫-፮)። የይሁዳ አገር ሰዎች ዅሉ ኀጢአታቸውን እየተናዘዙ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። እርሱም ቃለ ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር (ሉቃ. ፫፥፯-፲፬)፡፡ በመጨረሻም ‹‹ድንበር አታፍርሱ፤ ዋርሳ አትውረሱ›› እያለ ንጉሡ ሄሮድስንና ሄሮድያዳን በመገሠፁ ምክንያት አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ካረፈ በኋላም የራስ ቅሉ ክንፍ አውጥቶ በዓለም እየተዘዋወረ ፲፭ አምስት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? … ነቢይን? አዎን ይህ ከነቢይም ይበልጣል።እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ›› በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ለሕዝቡ ተናግሯል (ማቴ. ፲፩፥፱-፲፩)። እንደዚሁም ቅዱስ ዮሐንስን ከነቢዩ ኤልያስ ጋር በማመሳሰል ስለ አገልግሎቱ አስተምሯል (ማቴ. ፲፩፥፪-፲፱)።

ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ‹‹ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ ዮሐንስ ሆይ! ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ኾነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም›› ብሎ ታላቅነቱን መስክሮለታል (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ)፡፡

በአጠቃላይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከአዲስ ኪዳን አበው አንዱ የኾነ፣ ንጹሓን ነቢያት፣ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፣ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ኾኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፣ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፣ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፣ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱና ትምህርቱ፣ ያደረጋቸው ድንቆችና ተአምራት፣ እንደዚሁም እግዚአብሔር የሰጠው ቃል ኪዳንና አገልግሎቱን በሰማዕትነት መፈጸሙ በመጽሐፈ ስንክሳር፣ በትርጓሜ ወንጌል (ወንጌለ ሉቃስ) እና በገድለ ዮሐንስ መጥምቅ በሰፊው ተጽፏል፡፡

እንግዲህ እኛም እንደ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከኀጢአት ተለይተን፣ ራሳችንን ለጽድቅ ሥራ አስገዝን፣ በንጽሕና ኾነን አዲሱን ዓመት ለመቀበል ከዅሉም በላይ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንዘጋጅ፡፡

ይቆየን