ደመራ

መስከረም ፲፬፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

የታላቁ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች፡፡ በደረሰች ጊዜ የጌታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች፡፡

ኪራኮስ የሚባለው አረጋዊ ሰው መስቀሉ የተቀበረበትን በሥቃይና በመከራ አስጨንቃ ስትይዘው እንደነገራት ታሪኩ ያስረዳናል፤ ቁፋሮ ልታደርግበት የምትችለውን አካባቢም ሲጠቁማት ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ተማፀነች፡፡ የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ አመለከታት፡፡ ንግሥቷም በምልክቱ መሠረት ማስቆፈር ጀመረች፡፡ ለማስቆፈር የወሰደባት ጊዜም ከመስከረም ፲፯ እስከ መጋቢት ፲ ነበር፡፡ በቁፋሮውም መጨረሻ ሦስት መስቀሎችን አገኘች፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ መስቀሎች አንዱ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር መስቀል እንደሆነ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ፈያታዊው ዘየማንና ፈያታዊው ዘጸጋ ሁለቱ በጌታ ቀኝና ግራ የተሰቀሉት ወንበዴዎች እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡

ንግሥት እሌኒ ሦስቱን መስቀሎች ካገኘች የጌታችን መስቀል ለይታ ለማወቅ የሞተ ሰው አስከሬን አምጥታ በላያቸው ላይ አደረገቻቸው፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታ የተሰቀለበት መስቀል ሙቱን አስነሣው፡፡ ይህን ጊዜ ለይታ ያወቀችውን መስቀል በክብር ወስዳ የቤተ ክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል አደረገች፤ የደመራ ሥርዓት ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከበር ነው፡፡

ደመራ ማለት “መጨመር፣ መሰብሰብ መከመር” ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም የቃሉን ፍቺ  “ደመረ” ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን የአስተባበረ መሆኑን ይናገራሉ፤ አያይዘውም የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ (ሰዋሰወ ግእዝ ወግስ መዝገበ ቃላት) በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ቅድስት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው፡፡

የበረከት በዓል ያድርግልን፤ አሜን!!!

 

ተአምረኛዋ ሥዕል

መስከረም ፰፤፳፻፲፰ ዓ.ም.

እጅጉን የሚያስደንቀው የአምላክ ሥራ የተገለጠበት፣ ለሰው ልጆች ተስፋ፣ ፈውስ ሥጋ እንዲሁም ፈውስ ነፍስን ሊሰጠን በፈቀደ እርሱ ድንቅ ተአምራትን በምድር አደረገ፤ ጌታ በትስብእቱ በዓለም ተገልጦ ካደገጋቸው ተአምራትም በተጨማሪ እርሱ ካረገ በኋላም በሰዎች አድሮ ላይ አድሮም ይሁን በተለያዩ መንገዶች ዕጹብ ሥራውን አሳይቶናል፡፡

ከዚሀ ሁሉም በበለጠ መልኩ በክብርት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም የተደረገው ምሥጢር እጅግ ይልቃል፤ ነገረ ድኅነቱን የፈጸመባት እመቤታችን ለአዳም ዘር በሙሉ ተስፋ በመሆኗ ጌታ ከእርሷ በለበሰው ሥጋ ተገልጦ ያደረገልንን ለመግለጽ ቃላት ባይኖርም ምስጋና ግን ማቅረብ የሁላችንም ፈንታ ነው፡፡ አልፎ ተርፎም እርሷም እንደ ልጇ ተነሥታ ካረገች በኋላ ድንቅ ተአምርም በእርሷ ተደርጓል፡፡ ቅዱሳት መጽሐፍት በተለያዩ ጊዜ እመቤታችን ያደረገችውን ተአምር ገልጸው ጽፈዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመጽሐፈ ስንክሳር መስከረም ፲ ቀን ተመዝግቦ የምናገኘው አንድ ተአምረኛ ሥዕል እንዳለ ነው፤ ታሪኩም እንዲህም ይነበባል፡፡

አንዲት ማርታ የምትባል ሴት እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምትወድና በሚቻላትም ሁሉ የምታገለግላት፣ ቤቷንም ለእንግዳ ማደሪያ ያደረገች ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አባ ቴዎድሮስ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ መነኰስ ከእርሷ ዘንድ በእንግድነት አድረው በማግሥቱ ከቤቷ ሲወጡ ማርታ የሚሔዱበትን አገር በጠየቀቻቸው ጊዜ እርሳቸውም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደው ቅዱሳት መካናትን እንደሚሳለሙ ነገሯት፡፡ ማርታም ከእርሷ ገንዘብ ወስደው የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተው ይዘውላት እንዲመጡ ለመነቻቸው፡፡ መነኵሴውም በራሳቸው ገንዘብ ሥዕሉን ገዝተው እንደሚያመጡላት ቃል ገቡላት፡፡

አባ ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌም ደርሰው ቅዱሳት መካናትን ከተሳለሙ በኋላ ሥዕሏን ሳይገዙ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጉዞ ጀመሩ፡፡ ያን ጊዜም ‹‹ሥዕል መግዛትን ለምን ረሳህ?›› የሚል የሚያስደነግጥ ቃልን ሰምተው ተመልሰው መልኳ ያማረና የተወደደ የእመቤታችን ማርያምን ሥዕል ገዝተው በሐርና በንጹሕ ልብስ ጠቅልለው ይዘው እየተጓዙ ሳሉ ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ሲደርሱ ወንበዴዎች ተነሱባቸው፡፡ ሊሸሹ ሲሉም ‹‹መንገድህን ሒድ›› የሚል ቃል ከሥዕሏ ወጣ መነኵሴውም መንገዳቸውን በሰላም ተጓዙ፡፡ ሁለተኛም አንበሳ ሊበላቸው በተነሣባቸው ጊዜ ከዚያች ሥዕል የሚያሥፈራ ድምፅ ወጥቶ አንበሳውን አባረረላቸው፡፡

አባ ቴዎድሮስ ይህን ኹሉ ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜም ያቺን ሥዕል ለማርታ ከመስጠት ይልቅ ወደ አገራቸው ሊወስዷት ወደዱ፡፡ በመርከብ ተሳፍረው በሌላ አቅጣጫ ሲሔዱም ታላቅ ነፋስ ተነሥቶ ወደ ማርታ አገር ወደ ጼዴንያ ወሰዳቸው፡፡ ከመርከብም ወርደው ከብዙ እንግዶች ጋር ወደዚያች መበለት ቤት ደረሱ፡፡ ነገር ግን ማንነታቸውን ለማርታ አልገለጡላትም ፤ እርሷም አላወቀቻቸውም ነበር፡፡

በማግሥቱም ተሠውረው ወደ አገራቸው ሊሔዱ ሲሉ የቅፅሩ ደጃፍ ጠፍቶባቸው ሲፈልጉ ዋሉ፤ በመሸባቸው ጊዜም ወደ ማደሪያቸው ተመለሱ፡፡ ማታ ማታ በሩን ያዩታል፤ ነግቶ መሔድን ሲሹ ግን የበሩ መንገድ ይሠወርባቸዋል፡፡ እንዲህም ኾነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ማርታም ‹‹አባቴ ሆይ አእምሮህ ተነክቷልን? ስትቅበዘበዝ አይሃለሁና ምን ሆነህ ነው?›› ስትል ጠየቀቻችው፡፡ እርሳቸውም ከእመቤታችን ሥዕል የተደረገውን ተአምር ሁሉ ነገሯት፤ ራሳቸውንም ገለጡላትና ሥዕሏን ሰጧት፡፡ እርሷም የእመቤታችንን ሥዕል ተቀብላ የተጠቀለለችበትን ልብስ በፈታችው ጊዜ ወዝ ከሥዕሊቱ ሲንጠፈጠፍ አገኘች፡፡ ከደስታዋ ብዛት የተነሣም የአባ ቴዎድሮስን እጃቸውንና እግራቸውን ሳመች፡፡ ሥዕሏም ቅዱስ ሉቃስ የሳላት ነበረች፡፡

 

አንኳን ለበዓለ ጼዴንያ ማርያም አደረሳችሁ!

 

 

ርእሰ ዐውደ ዓመት

በእንተ ዕረፍቱ ለተክለ ሃይማኖት

የስሙ መነሻ ፊደሉ ትእምርተ መስቀል የሆነው፣ የወንጌል ተቀዳሚ ስም ማቴዎስ፣ የቅዱስ ወንጌል ጸሐፊዋና ሰባኪዋ ማርቆስ፣ የነፍስና የሥጋ ሐኪም ሉቃስ፣ ከሁሉ ይልቅ ሥልጣኑ ከፍ ያለ ጴጥሮስ፣ ሰማያዊ አርበኛ ሚናስ፣ አነዋወሩ በብቸኝነትና በንጽሕና የሆነ ኤልያስ፣ የቤተ ክርስቲያን የልጆቿ አባት ባስልዮስ፣ የቤተ ራባው ጸዋሚ ተሐራሚ ዮሐንስ፣ ዐሥረኛው የአርማንያው ጎርጎርዮስ፣ ግሙደ እግር ያዕቆብ ሐዋርያ፣ እንግዳ መቀበል ፍጹም ተግባሩ የሆነ አብርሃም፣ ጸሐፊ ምሥጢራት ወጥበባት ሄኖክ፣ መሥዋዕቱ የሠመረለት አቤል፣ ሕዝብን የሚያስተዳድር ዮሴፍ፣ እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቡና የሚያመሰግን ዳዊት፣ ከሐዲዎችን የሚበቀል ቄርሎስ፣……………..

‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?››

ከነገደ ብንያም የተወለደው ነቢዩ ሚክያስ የስሙ ትርጓሜ ‹‹እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?›› ነው። እንደ ስሙ ትርጕምም የእግዚአብሔር ቸርነት ከየትኛውም ኃጢአትና ከየትኞቹም በቊጥር የበዙ ኃጢአተኞች ይልቅ ታላቅ መሆኑን፣ ይልቁንም እግዚአብሔር ኃጢአትን እንጂ ኃጢአተኞችን የማይጸየፍ እንደሆነ አስተምሯል። በሰባት ምዕራፎች በተጠቃለለ ነገረ ድኅነትንና ንስሐን ማዕከል ያደረገ ትምህርቱና ትንቢቱ መሲሑ የሚወለደበትን ስፍራ ሳይቀር ‘ደረቅ ትንቢት’ በግልጽ እንዲህ ሲል “አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል” ተናግሯል።

በእንተ ስምዐ ለማርያም

ዛሬ በፍልሰታዋ በአዛኝት የጾም ወራት

ልመናዬ አይደለም ፍርፋሪ ኩርማን ዱቄት

በደብረ ታቦሩ በዓል በተገለጸበት ምሥጢር

የዕለት ጉርሴን አልጠይቅም ቆሜ በደጅዎ በር

ልለምን . . . በእንተ ስማ ለማርያም

ስለ ወላዲተ አምላክ . . .

ስማችን!

ሕፃን ሆኖ አባቷ፣ አባት ሲሆን ልጇ

በእምነት ያበረታት ወርዶ ከእቅፍ እጇ

ወደ ሞት እንዳትሄድ ሥቃይን ተሰቅቃ

ለልጄ እንዳትል የመከራ እሳት ሞቃ

ቆሞ መሰከረ ድምጹን አሰምቶ

ከአላዊው ንጉሥ በመንፈስ ተሞልቶ

ጽኑ እምነት

እለእስክንድሮስ የተባለው መፍቀሬ ጣዖት፣ ጸላዬ እግዚአብሔር፣ የዲያቢሎስ ምርኮኛ የሆነው በሰው እጅ ከድንጋይ ተጠርቦ ለተሠራው ጣዖት ሕዝቡን እንዲሰግዱ ሲያስገድድ፣ ስቶ ሲያስት፣ ሲያስፈራራ ኖሯል፡፡ አብዛኛው ለሥጋው ሳስቶ፣ መከራውን ተሰቆ ለጣዖት ሲሰግድ ሕፃን ቂርቆስ ግን እምቢ አለ፤ የቀደሙ አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክ ያውቃልና ልቡን አጸና፤ ለመከራው ተዘጋጀ፤ እናቱ ለልጇ ሳስታ፣ ለጣዖት ልትንበረከክ፣ ልትክድ ሲዳዳት ሕፃኑ ግን ጸና፤ መከራውን ሳይሰቀቅ እለ እስከንድሮስ ላቆመው ጣዖት አልሰግድም አለ፡፡

ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት

በሐምሌ ሰባት ቀን እግዚአብሔር አምላክ በአብርሃም ቤት ተገኝቶ እንደባረከው ቅን ልቡና ያላቸውን፣ ለጋሾች ለሆኑ፣ ምጽዋትን ለሚያቀርቡ፣ እንግዳ መቀበል የዘወትር ልማዳቸው ላደረጉ ሰዎች በቤታቸው ይገባል፡፡ የተዘጋውንም ማኅፀን እንደከፈተ ቤቱንም እንደባረከ አይተናል፡፡ ዛሬም እኛም ለተራቡ በማብላት፣ ለተጠሙ በማጠጣት፣ ለታረዙ በማልበስ፣ በመመጽወትና በመሳሰለው ተግባር መኖር፣ በቀና አስተሳሰብ መጓዝ እንዳለብን መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

ቅድስት አፎምያና ባሕራን

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁልን? በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐዋጅ ታውጀው ከሚጾሙ አጽዋማት አንዱ የሆነው ጾመ ሐዋርያት የሚጾምበት ወቅት ላይ ነንና ይህን ጾም እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? አባቶቻችንን ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ከተቀበሉ በኋላ ወደ አገልግሎት ከመሄዳቸው በፊት ጾምን ጾመዋል፤ ይህን ጾም ምእመናን በየዓመቱ በዓለ ኀምሳ ከተከበረ ማግስት ጀምሮ እስከ ሐምሌ አምስት ቀን ድረስ እንጾመዋለን፤ ልጆች! እንግዲህ እኛም እንደ አቅማችን ይህንን ጾም መጾም ይገባናል፤ በዘመናዊ ትምህርታችሁም ከፈተና በፊት በርትታችሁ በማጥናት ፈተናውን በደንብ መሥራት ይገባችኋል ፤ መልካም! ለዛሬ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት እንማራለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ተልከው እኛን የሚጠብቁን ናቸው፤ መልካም ስንሠራ ችግር በገጠመን ጊዜ በጸሎት ስንማጸናቸው ፈጥነው በመምጣት ከዚያ መከራ ያወጡናል፤ ከእግዚአብሔር አማልደው ምሕረትን ያሰጡናል፡፡ ከቅዱሳን መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሚካኤል ከመከራ ካዳናቸው መካከል ሁለቱን ታሪክ አንሥተን ለዛሬ እንማራለን፡፡