በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በተሐድሶ መናፍቃን መሠረታዊ ስሕተት እና ወቅታዊ እንቅስቃሴያቸው ዙሪያ ያዘጋጀው የምስል ወድምፅ ዝግጅት መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም ተመርቆ ለምእመናን በነጻ ተሠራጨ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ ማስተባበሪያ በተሰናዳው በዚህ የምስል ወድምፅ ዝግጅት፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ መጋቤ ሐዲስ ቀሲስ እሸቱ ዓለማየሁ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር እና ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ትምህርታዊ ማብራሪያ በመስጠት፣ ዲያቆን ምትኩ አበራ ደግሞ በማወያየት ተሳትፈውበታል፡፡
በምስል ወድምፅ ዝግጅቱ የተሳተፉ መምህራነ ወንጌል
የአምስት ሰዓታት ጊዜን የሚወስደው ዝግጅቱ፣ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሚጠሩ መናፍቃን ለሚያነሧቸው የማደናገሪያ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሽ የተሰጠበት ሲኾን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ ራሱንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃን ወረራ ለመጠበቅ ይችል ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ለምእመናን በነጻ እንዲሠራጭ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ዝግጅቱ ለአንድ ዓመት ያህል እንደ ተደከመበት፤ በከፍተኛ ጥራት እንደ ተዘጋጀ እና ብዙ ገንዘብ ወጪ እንደ ተደረገበትም ከማስተባበሪያው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
በዕለቱ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሰቲት ሑመራ፣ የግብጽ እና የሰሜን ሱዳን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት የበላይ ሓላፊ፤ አባቶች ቀሳውስት እና ወንድሞች ዲያቆናት፤ ሰባክያነ ወንጌል እና ዘማርያን፤ የሰንበት ት/ቤት እና የመንፈሳውያን ማኅበራት አባላት በአጠቃላይ ከሁለት ሺሕ አምስት መቶ በላይ ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይም በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቃለ ምዕዳን ተሰጥቷል፡፡ በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ሒደቶችን የሚያስቃኝ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡ በዋና ጸሐፊው አቶ ውብእሸት ኦቶሮ አማካይነት የማኅበረ ቅዱሳን መልእክት ተላልፏል፡፡ በዋናው ማእከል መዘምራን በአማርኛ ቋንቋ፤ ከሰንዳፋ በመጡ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ደግሞ በአፋን ኦሮሞ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ በዕለቱ በሰጡት ቃለ ምዕዳን ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመንፈሳዊ ጉባኤ ላሰባሰበ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ካቀረቡ በኋላ በአዲስ ዓመት አዲስ ሐሳብ በማቅረብ የተሐድሶ ኑፋቄን ትምህርት ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ለምእመናን ያሠራጨውን ማኅበረ ቅዱሳንን፣ በዝግጅቱ የተሳተፉ አባላትን እንደዚሁም በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ ምእመናንን አመስግነዋል፡፡
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ፈተናዎችን እንዳሳለፈች ያወሱት ብፁዕነታቸው ምእመናን ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን አጽንቶ የመጠበቅ ድርሻ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ሃይማኖትን መጠበቅም ለአገር ሰላምና ጸጥታ፣ ለሕዝብ አንድነትና ፍቅር ዘብ መቆም ማለት መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ራሱን ያዘጋጀ ወታደር ጠላቱን በቀላሉ ድል ለማድረግ እንደሚቻለው የጠቀሱት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ‹‹ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና ቃለ እግዚአብሔርን በመማር ለመናፍቃን ምላሽ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ኹኑ›› በማለት ለምእመናን አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ባቀረቡት የፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ሒደቶችን የሚያስቃኝ አጠር ያለ የዳሰሳ ጥናት፣ በተለይ ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ እንቅስቃሴያቸውን በሦስት ክፍለ ጊዜ በመመደብ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሚጠሩ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱትን ጫና ማስረጃዎችን በመጥቀስ አሳይተዋል፡፡
እንደ ዲያቆን ያረጋል ማብራሪያ በ፲፱፻፺ ዓ.ም አራት የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ መነኮሳት በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው መለየታቸው ለፀረ ተሐድሶው ተግባር ምቹ አጋጣሚ ቢኖረውም በአንጻሩ ግን ኦርቶዶክሳውያኑ ተሐድሶ መናፍቃን የሉም ብለን እንድንዘናጋ፤ መናፍቃኑ ደግሞ ውግዘትን በመፍራት የኑፋቄ ትምህርታቸውን በስውር እንዲያስፋፉ ምክንያት ኾኗል፡፡ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቀሰሴም በየጊዜው እየዘመነ በመምጣቱ አሁን ፈታኝ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
አያይዘውም ችግሮች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት የመካላከል ባህላችን ዝቅተኛ መኾን፣ የተሐድሶ ኑፋቄን ጉዳይ ከግለሰቦች ቅራኔ እንደ መነጨ አድርጎ መውሰድና ጉዳዩን በሽምግልና ለመፍታት መሞከር፣ የገንዘብ ዓቅም ማነስ፣ በሚታይ ጊዜያዊ ውጤት መርካት፣ የሰው ኃይል እጥረት፣ መሰላቸትና መዘናጋት ሐዋርያዊ ተልእኮው በሥርዓት እንዳይዳረስና የመናፍቃን ትምህርት በቀላሉ እንዲዛመት የሚያደርጉ ውስንነቶች መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሕዝበ ክርስቲያኑ መናፍቃኑ በሚያነሧቸው ጥያቄዎች አእምሮው እንዲጠመድና መምህራነ ቤተ ክርስቲያንም ለመናፍቃን ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ መደረጋቸው ለሐዋርያዊ ተልእኮው መቀዛቀዝ ምክንያት መኾኑን አመላክተው ምእመናን ከተሐድሶ ኑፋቄ ትምህርት ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያንን ተግተው መጠበቅ እንዳለባቸው ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ አሳስበዋል፡፡
‹‹ምን እናድርግ?›› በሚለው የዳሰሳ ጥናታቸው ማጠቃለያም የተሐድሶ እንቅስቃሴን ለመከላከል በዐቢይነት የትምህርተ ሃይማኖት ዕውቀትን ማሳደግ እንደሚገባ፤ ለዚህም የሥልጠና መርሐ ግብሮችን፣ የሥነ ጽሑፍ ውጤቶችን እና የቪሲዲ ዝግጅቶችን መጠቀም ምቹ መንገድ እንደሚጠርግ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ጠቁመዋል፡፡
በመናፍቃን ተታለው የተወሰዱ ምእመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ እና በሚሊዮን የሚቈጠሩ ወገኖችን በማስተማር የሥላሴ ልጅነትን እንዲያገኙ ማድረግ ማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ ነድፎ ከሚያከናውናቸው ዐበይት ተግባራቱ መካከል መኾናቸውን የጠቀሱት ደግሞ የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ውብእሸት ኦቶሮ ናቸው፡፡
የምስል ወድምፅ ዝግጅቱን ለምእመናን በነጻ ለማዳረስ መወሰኑ ማኅበረ ቅዱሳን ሕዝበ ክርስቲያኑ በሃይማኖቱ ጸንቶ እንዲኖር ለማበረታታት እና የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲፋጠን ለማድረግ የሚተጋ ማኅበር ለመኾኑ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል – ዋና ጸሐፊው፡፡ ከዚህ የበለጠ ብዙ ሥራ ከማኅበሩና ከምእመናን እንደሚጠበቅም አስታውሰዋል፡፡
በሁለት ቋንቋዎች ብቻ የሚግባቡና በቍጥር ከዐሥር ሚሊዮን የማይበልጡ ምእመናን የሚገኙባት የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከስምንት በላይ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዳሏት ያወሱት አቶ ውብእሸት፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎችን የሚጠቀሙና ወደ አምሳ ሚሊዮን የሚደርሱ ምእመናን ባለቤት ለኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ብቻ በቂ አለመኾኑን ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም ይህን ጉዳይ የተገነዘበው ማኅበረ ቅዱሳን፣ የአየር ሰዓት በመከራየት በአሌፍ የቴሌቭዥን ጣቢያ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ በማስታወስ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብሩን አጠናክሮ ለመቀጠል ያመች ዘንድ በገንዘብም፣ በቁሳቁስም፣ በሐሳብም ምእመናን ድጋፍ እንዲያደርጉ ዋና ጸሐፊው ጠይቀል፡፡
ከዚሁ ዂሉ ጋርም ማኅበረ ቅዱሳን ሰባክያነ ወንጌልን በማሠልጠን፣ አዳዲስ አማንያንን በማስጠመቅ፣ በጠረፋማ አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነጽ እና በመሳሉት ዘርፎች ፕሮጀክት ቀርፆ ለስብከተ ወንጌል መዳረስ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በሚችሉት መንገድ ዂሉ በመደገፍ እና ከማኅበሩ ጎን በመቆም ምእመናን የሚጠበቅባቸውን ክርስቲያናዊ ድርሻ እንዲወጡ አቶ ውብእሸት ኦቶሮ በማኅበረ ቅዱሳን ስም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በመልእክታቸው ማጠቃለያም ትምህርተ ወንጌልን በማዳረስ፤ የግንዛቤ ማዳበሪያ መርሐ ግብራትን በማዘጋጀትና ሥልጠና በመስጠት፤ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎትና ለሥልጠና መስጫ የሚውል ገንዘብ በመለገስ፤ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችን በማጋለጥ በአጠቃላይ በልዩ ልዩ መንገድ ሱታፌ በማድረግ ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ እንዲስፋፋ፣ የተሐድሶ ኑፋቄ ትምህርት ደግሞ እንዲዳከም ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰባክያነ ወንጌል እና በጎ አድራጊ ምእመናን በተጨማሪም ማኅበሩ ያስተላለፈውን ጥሪ ተቀብለው በድምፅ ወምስል ዝግጅቱ ምረቃ ላይ ለተገኙ ወገኖች ዅሉ ዋና ጸሐፊው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም የምስል ወድምፅ ዝግጅቱ በብፁዕ አቡነ ሉቃስ ቡራኬ ተመርቆ በቍጥር አንድ ሺሕ በሚኾኑ በባለ ፲፮ ጊጋ ባይት ፍላሽ ዲስኮች ለምእመናን የታደለ ሲኾን፣ በዕለቱ ያልተገኙ ምእመናን ከማኅበሩ ሕንጻ ድረስ በአካል በመምጣት ዝግጅቱን በፍላሽ እንዲወስዱ፤ በጎ አድራጊ ምእመናን ፍላሽ ዲስኮችን ገዝተው በማበርከት ለትምህርቱ መዳረስ ትብብር እንዲያደርጉ፤ ዝግጅቱ የደረሳቸው ወገኖችም እያባዙ ቤተ ክርስቲያንን ለሚወዱም ኾነ ለማይወዱ ወገኖች እንዲያዳርሱ፤ ዝግጅቱ ያልደረሳቸው ደግሞ ትምህርቱ በማኅበሩ ቴሌቭዥን ሲተላለፍ፣ በዩቲዩብ ሲለቀቅና በሲዲ ሲሠራጭ እንዲከታተሉ በማስተባበሪያው በኩል ማሳሰቢያ ከተሰጠ በኋላ በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳን እና ጸሎተ ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡
ከምረቃ መርሐ ግብሩ በኋላ ስለ ዝግጅቱ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው ምእመናን፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ፈተና የኾነውን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ለመከላከል ይቻል ዘንድ ብዙ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ያዘጋጀውን የምስል ወድምፅ ዝግጅት ለምእመናን በነጻ ማዳረሱ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለመደገፍ የሚተጋ የቍርጥ ቀን ልጅ መኾኑን እንደሚያስረዳ መስክረዋል፡፡ ከማኅበሩ ጋር በመኾን የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በሚቻላቸው ዓቅም ዅሉ የማኅበሩን አገልግሎት ለመደገፍም ቃል ገብተዋል፡፡
ከዚህ በተለየ ደግሞ የማኅበሩ አዳራሽ እና በምድር ቤቱ ወለል ላይ የተዘጋጁ ድንኳኖች ሞልተው በርካታ ምእመናን ቆመው መርሐ ግብሩን መከታተላቸውን፤ ከፊሉም መግቢያ አጥተው በመርሐ ግብሩ ለመሳተፍ አለመቻላቸውን ያስተዋሉ አንዳንድ በጎ አድራጊ ምእመናን በመንፈሳዊ ቍጭት ተነሣሥው ‹‹ብዙ ሕዝብ ማስተናገድ የሚችል ሰፊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ መገንባት አለብን›› እየተባባሉ ሲነጋገሩ ተሰምቷል፡፡