‹‹ልባም ሴትን ማን ሊያገኛት ይችላል፤ ዋጋዋ ከቀይ ዕንቊ እጅግ ይበልጣል!›› (ምሳ. ፴፩፥፱)
ዓለማችን የልዩነት መድረክ ናት፡፡ ልዩነቶቹ እንዲህ፣ እንዲያ፤ አንድ እና ሁለት ተብለው የማይወሰኑ ናቸው፡፡ ሴትነትና ወንድነትም የጾታ ልዩነት አንድ መደብ ናቸው፤ የሴት መሆንም የወንድ መሆንም መገናኛው ሰው መሆን ነው፡፡ ጥያቄው ታዲያ ምን ዓይነት ሴት ወይም ምን ዓይነት ወንድ እንሁን፤ ከዚያም ምን ዓይነት የሰው ልጅ ይኑር የሚለው ነው፡፡ ወንድ የሚለው ስም ብቻውን ወደ ሰውነት አያደርስም፤ ሴት ተብሎ መጠራትም ሴት የመሆንን ትክክለኛ መዳረሻ ጥግ አያመጣውም፡፡ ሁሉ በተገቢው ሚዛን ሊመዝነው የሚችለውን ሚዛን መምረጥ አለበት፡፡