የምድርን መከራ፣ ችግርና ሥቃይ አልፎ በእምነት ጽናትና በመልካም ምግባር ለሚኖር ሰው የቅድስና ሕይወት እጅግ ጣፋጭ ናት፡፡ በጠቧቧ መንገድ በእውነት በመጓዝ ፍቅር፣ ሰላምንና የመንፈስ እርካታን በማጣጣም ጥዑመ ነፍሰ ምግብን እየተመገበ የመንፈስን ፍሬ ለመብላት በሚያበቃው በክርስትና ሕይወትም ይኖራል፡፡ መስቀልን የጦር መሣሪያ ወንጌልን ጋሻ መከታ አድርጎ ጠላት ዲያብሎስን ድል የነሣ እንደ እነ አቡነ ተክለሃይማኖት ዓይነት ጻድቅ ደግሞ በቅድስና ማዕረግ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይጓዛል፡፡
በርግጥም በቅድስና ሕይወት ሁሉም ተመሳሳይ ችሎታና ትጋት ሊኖረው አይችልም፤ እግዚአብሔር በሰጠው መክሊት ግን አትርፎ በከበረ ሞት ወደ ፈጣሪው መሄድ ይቻለው ዘንድ የአምላካች ቅዱስ ፈቃድ ነው፡፡ ሰው በመንፈሳዊ ብርታት ፈታናውን ሁሉ ማለፍ ከቻለ ለተለያዩ ክብር እንደሚበቃ ቅዱሳት መጻሕፍት ምሥክሮች ናቸው፡፡ ቅዱሳን በገድልና በትሩፋት ብዛት የሚያገኟቸው ዐሥር ማዕረጋት አሉ፡፡ ‹ጽማዌ፣ ልባዌ፣ ጣዕመ ዝማሬ፣ አንብዕ (አንብዐ ንስሓ)፣ ኩነኔ፣ ፍቅር፣ ሑሰት፣ ንጻሬ መላእክት፣ ተሰጥሞ እና ከዊነ እሳት› የሚል ስያሜም አላቸው፡፡ የንጽሐ ሥጋ፣ የንጽሐ ነፍስና የንጽሐ ልቡና ማዕረጋት በመባል ደግሞ በሦስት ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡