እግዚአብሔር ዝም ይላልን?

ክፍል አንድ

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው

                                    ሰኔ ፳፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

በዓለም ስንኖር መከራና ደስታ፣ ውድቀትና ስኬት፣ ድካምና ብርታት ልዩ ልዩ ነገሮች ይፈራረቁብናል። በርግጥ ይህ አዲሳችን አይደለም። “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ” ተብለናልና! እንኳን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ያለንና መንፈሳዊ ጠላት ያለብን ሰዎች ማንኛውም ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ውጣ ውረድ ያጋጥመዋል። (ዮሐ.፲፮፥፴፫) እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ ሰው ሁሉ ከሚፈተነው በተለየ መንፈሳዊውን ዓለም እያሰብን ስለምንኖር የበለጠ እንፈተናለን። ቤተ ክርስቲያን ከመከራ ተለይታ አታውቅም። ገና ከዓለመ መላእክት ጀምሮ መከራዎች ይለዋወጡባታል።

በግል ሕይወታችንም ሆነ እንደ ቤተ ክርስቲያን በሚገጥሙን ፈተናዎች በተለያየ መንገድ መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት ማድረግ ለእኛ ለክርስቲያኖች የተለመደ ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅም ነው። እንደየፈተናው ሁኔታ የምንሰጠው ምላሽ የተለያየ ይሁን እንጂ በአቅማችን የድርሻችንን ለመወጣት ጥረት እናደርጋለን። ሆኖም አንዳንዴ እኛ የሚጠበቅብንን እያደረግን እግዚአብሔር የዘገየ ወይም ዝም ያለን ሲመስለን “ለምን?” ልንል እንችላለን። ተስፋ ወደ መቁረጥ የምንሔድም አንጠፋም። ለመሆኑ በፈተና ስንናጥ፣ ግራ ስንጋባ፣ ስንጨነቅ እግዚአብሔር እያየን እንደማያይ እየሰማን እንደማይሰማ ዝም የሚለን ለምን ይሆን?

በርግጥ እግዚአብሔር ቸር መሆኑን በእርግጠኝነት የሚያምን ሰው በእንደዚህ ዓይነት ጥያቄ አይፈተንም። የሚያደርገው ነገር ሁሉ መልካም መሆኑን ያውቃልና። “ሲርበኝም ስጠግብም፣ ሲጠማኝም፣ ስረካም፣ ሲከፋኝም፣ ስደሰትም፣ ስደኸይም ሀብት ሳገኝም እግዚአብሔር ትክክል ነው” ማለት መቻል ታላቅ የእምነት ልዕልና ነውና። “ለምን እንዲህ ሆነ?” እያልን በሆነ ባልሆነው እግዚአብሔርን ማማረር መልካም አይደለም። እግዚአብሔር ለምን ይህን አደረገ? ብለን ብንጠይቅ እንኳ የእርሱን ሐሳብ መርምረን ልንደርስበት የማንችል መሆኑን መጀመሪያ ማመን አለብን።

እግዚአብሔር በኛ የጊዜ ስሌት ብቻ መልስ እንዲሰጥ መጠበቅ፣ ያ ሳይሆን ሲቀር እግዚአብሔር ዝም አለኝ ብሎ ማማረርም ተገቢ አይደለም። በኛ ስሌት የዘገየ ቢመስለንም እርሱ የሚሠራበት ጊዜ አለው። ዝም ሲለንም ለበጎ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በቅዱሳንም ሕይወት እንደምናነበው በግል ሕይወታችንም ይሁን በቤተ ክርስቲያን መከራ ሲገጥመን ዝም ያለን እስኪመስለን ድረስ እግዚአብሔር በተለያየ ምክንያት ሊዘገይ ይችላል።

                               በግል ሕይወታችን

ፈተና ሲደራረብብን ወይም ችግሮች ሲገጥሙን አለበለዚያም አንድን ነገር ከፍ ባለ መሻት ስንፈልገው ለችግሮቻችን መፍትሔ እንዲሰጠን፣ የፈለግነውን እንዲያሳካልን ወደ እግዚአብሔር እንጮኻለን። በዚህ ጊዜ ቶሎ መልስ ባናገኝ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው ብለን ማመንና በትዕግሥት መጠበቅ አለብን። በአባቶቻችን ሕይወት እንደምናየው እግዚአብሔር የፈለግነውን ነገር ወይም የችግራችንን መፍትሔ ቶሎ ላይሰጠን የሚችልበት ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

እግዚአብሔር ታጋሽ አምላክ ነውና እኛንም ትዕግሥት ሊያስተምረን ፈልጎ ለጸሎታችን ቶሎ መልስ ላይሰጠን ይችላል። ብዙ ጊዜ የፈለግነውን ነገር ቶሎ ካገኘን ዋጋውን የማሳነስ ዝንባሌ አለብን። በዚህ ምክንያት የተሰጠንን ነገር አቅልለን እንዳናየው ስለሚፈልግ ከብዙ ደጅ ጥናት በኋላ ሊሰጠን ይፈቅዳል። ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ የሆነው ትዕግሥትንም በሕይወታችን እንለማመዳለን።

ሌላው እግዚአብሔር ለጸሎታችን መልስ ከመስጠት ሲዘገይብን ወይም ዝም ሲለንና ሲከለክለን ማሰብ የሚገባን ከለመንነው የተሻለ ነገር አዘጋጅቶልን ሊሆን እንደሚችል ነው። ለዚህ ሐሳብ ሁለት ማሳያዎችን ልንወስድ እንችላለን። በቅዱሳን ታሪክ እንደምናነበው ከመካን ወላጆች የተገኙ ብዙ ጻድቃን አሉ። አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም” በማለት የመሰከረለት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የተወለደው መካን ከነበሩት ከቅድስት ኤልሳቤጥና ከካህኑ ዘካርያስ ነው። (ማቴ.፲፩፥፲፩) እነዚህ ቅዱሳን እግዚአብሔር ልጅ እንዲሰጣቸው ብዙ ዘመናት ሲለምኑ ኖረዋል። በኋላ ግን ልጅ የመውለድ ዘመናቸው ሲያልፍ ተስፋ ቆርጠው ነበር። እግዚአብሔር ግን በእርጅና ጊዜያቸው መንገዱን የሚጠርግና እርሱን ለማጥመቅ የሚያስችል ቅድስና ያለው ልጅ ቅዱስ ዮሐንስን ሰጣቸው።

በመጽሐፈ ስንክሳር ታሪኩ ተጽፎ የሚገኝ ታናሹ ቴወዶስዮስ ደግሞ ለብዙ ዘመን መንግሥቱን የሚወርስ ልጅ እንዲሰጠው ከእግዚአብሔር ይለምን እንደነበር ነገር ግን ልጅ እንደተከለከለ ተጽፏል። እግዚአብሔር ይህን ያደረገበት ምክንያት ነበረው፤ ከዚያ ዘመን በኋላ የሚነሣው ትውልድ እግዚአብሔርን የሚክድ ስለነበር ቴወዶስዮስ ልጅ ቢኖረው ከዚያ ትውልድ ጋር ስለሚኖር “የአንተ ልጅ እኔን ሲክድ ማየት አልፈልግም” ብሎ ነበር እግዚአብሔር ልጅ የከለከለው፣ ይህንንም በወዳጆቹ በመነኮሳት በኩል ገልጾለታል።

የማይጠቅመንን እየለመንን/እየፈለግን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ፦ መቼም ሰዎች ነንና ዕውቀት ይጎድለናል፤ የሚጠቅመንና የሚጎዳንን ሁሉ ለይተን እናውቃለን አንልም። ለዚህ ሐሳብ ማሳያ ይሆነን ዘንድ በቅዱስ ወንጌል የተጻፈ የዮሐንስና የያዕቆብን እናት ልመናና የጌታን መልስ ማስታወስ በቂ ነው። ልጆቿ ግራዝማችና ቀኝ አዝማች እንዲሆኑላት የለመንሁ መስሏት ሞት እየለመነችላቸው ነበር። ጌታ ለዚህ ጸሎቷ የሰጠው ምላሽ “ኢየሱስ ግን መልሶ፦ የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ያለውን መጠጣት ትችላላችሁን?” (ማቴ.፳፥፳-፳፫) እኛም ዛሬ የምንለምነውን ስለማናውቅ እግዚአብሔር ዝም ያለን ይመስላል።

በዝምታው ለበጎ ሊሆን እንደሚችል ማሰብም ይኖርብናል። ከላይ እንደተገለጸው ትዕግሥት እንድንለማመድ እግዚአብሔር ለጸሎታችን ቶሎ ምላሽ ላይሰጠን ይችላል። ያለንበት ሁኔታ ራሱ የሚጠቅመንና መንፈሳዊ ሕይወታችንን የሚያሳድግ ሲሆንም በግልጽ ይከለክለናል። መከራ እንዲርቅለት ጸልዮ እንደተመኘው መከራው ያልራቀለት ቅዱስ ጳውሎስ በኋላ ላይ ያ መከራ ራሱን የሚጠቅመው እንደሆነ ተረድቶ እንዲህ ተጽፎ እናነባለን፦ “ስለዚህም በመገለጥ ታላቅነት እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፥ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ፤ ይኸውም እንዳልታበይ ነው። ስለዚህ ነገር ከእኔ እንዲለይ ሦስት ጊዜ ጌታን ለመንሁ። እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና።” (፪ቆሮ፲፪፥፯-፲)

ተወዳጆች ሆይ እንግዲያውስ እግዚአብሔር መልስ ሲሰጠን የምንደሰተውን ያህል ዝም ያለን ሲመስለንም ለበጎ ነው ብለን መደሰት አለብን፤ የእርሱ ዝምታውም መልስ ነውና።

ይቆየን!