ጸሎትና ጥቅሙ

             

ልጆች ትምህርት ጥሩ ነው?ቤተ ክርስቲያን እሑድ እሑድ ትሔዳላችሁ ? በጣም ጥሩ ልጆች ! ዛሬ የምንማማረው ስለ ጸሎት ጥቅም ነው፡፡ ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር የምንገናኝበት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ትልቅ ኃይል ማለት ነው፡፡

በጸሎት የእግዚአብሔርን ሩህሩህነት፣ ቸርነት ኃያልነት እንገልጻለን፡፡ በጸሎት እግዚአብሔር ያደረገልንን ሁሉ አስታውሰን ምስጋና እናቀርባለን፡፡  በጸሎት በደላችንን ለእግዚአብሔር እንናዘዛለን፡፡ ይቅርታውንም እንጠይቃለን፡፡ በጸሎት ከእግዚአብሔር የፈለግነውንና የጐደለንን ለማግኘት እንለምናለን፡፡ ጸሎት ይቅርታ መጠየቂያ በመሆኗ ከቅጣትና ከመከራ የምታድን ናት፡፡ እንግዲህ ልጆች በአጠቃላይ የጸሎት ጥቅም ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ልጆች እናንተስ ጠዋት ከመኝታችሁ ስትነሡ ማታ ስትተኙ ትጸልያላችሁ ?
ወይንስ ዝም ብላችሁ ትተኛላችሁ፡፡ ትነሣላችሁ? ማታ ስትተኙ እግዚአብሔርን አመስግናችሁ ጠዋት ስትነሡ እግዚአብሔርን አመስግናችሁ ጸልያችሁ መዋል አለባችሁ፡፡ ልጆች ምግብም ስትመገቡ ጸሎት አድርሳችሁ መመገብ አለባችሁ፡፡ ልጆች ጸሎት ትምህርታችሁን ይገልጽላችኋል፡፡ ከብዙ ክፉ ነገር እግዚአብሔር ይጠብቃችኋል፡፡
እንግዲህ ልጆች ጸሎት ብዙ ዓይነት ነው፡፡ 1ኛ የግል ጸሎት፣ 2ኛ. የማኅበር ጸሎት 3ኛ. የቤተሰብ ጸሎት አለ፡፡ ስትጸልዩ በጸጥታና ካለወሬ መጸለይ ያስፈልጋችኋል፡፡ በአጠቃላይ የጸሎትን ጥቅም ማወቅ ይገባናል፡፡ እሺ ልጆች! ከብዙ በጥቂቱ የጸሎትን ጥቅም እንዳወቃችሁ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሥነ ፍጥረት

ልጆች የምንነግራችሁ ስለ ሥነ ፍጥረት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚታየውን ዓለም የፈጠረው በስድስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ ይህም በአንድ ቀን ለመፍጠር አቅም አጥቶ አይደለም፡፡ እርሱ ባወቀ ሁሉን በሥርዐትና በአግባቡ ለማድረግ ብሎ ነው እንጂ፡፡ ደግሞም ፈቃዱና ጊዜውም ስለሆነ ፍጥረታትን በስድስት ቀናት ውስጥ አከናወነ፡፡ 

 
የዕለታት መጀመሪያ እሑድ ናት፡፡ እግዚአብሔር በዕለተ እሑድ በመጀመሪያው ቀን አራቱ ባሕርያት የተባሉትን መሬት፣ ውኃ፣ ነፋስ፣ እሳትን ፈጠረ፡፡ በሁለተኛዋ ዕለተ ሰኞ እግዚአብሔር ጠፈርን ፈጠረ፡፡
በሦስተኛው ቀን በዕለተ ማክሰኞ ልዑል እግዚአብሔር ምድርን፣ ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን በምድርም ላይ እንደ ወገኑ ዘር ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን ታብቅል ብሎ በዚያ መሬት፣ አትክልትን፣ አዝርዕትን፣ ዕፅዋትን አስገኘች /ዘፍ. 1፡12/ እነዚህ ከአራቱ ባሕርያት መካከል ከመሬት፣ ከውኃ፣ ከነፋስ ተፈጠሩ፡፡
ዓርብ በመጀመሪያው ሰዓት በመዓልት ልዑል እግዚአብሔር አዳምን ፈጠረው፡፡ ከአዳም በፊት የተፈጠሩት ፍጥረታት በሀልዮና በነቢብ የተፈጠሩ ሲሆን፤ እግዚአብሔር አዳምን የፈጠረው በእጆቹ በማበጃጀት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ለመፍጠር ሰውን በመልካችንና በአርአያችን እንፍጠር አለ /ዘፍ. 1፡26/
በአራተኛው ቀን የረቡዕ ፍጥረት የሆኑት በሰማይ ጠፈር ብርሃን ይሁን ብሎ በቃል በማዘዝ ሦስቱን ፍጥረታት ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጠራቸው፡፡ /ዘፍ.1፡14/ ሐሙስ ማለት አምስተኛ ዕለት ማለት ነው፡፡ በዕለተ ሐሙስ የተፈጠሩት ሦስቱ ፍጥረታት ዘመደ እንስሳ የሚባሉት ዓሣዎች ዘመደ አራዊት የሚባሉት አዞ፣ ጉማሬ፣ እንቁራሪት፣ ዘመደ አዕዋፍ የሚባሉት ዳክዬዎች ዝዬዎች ናቸው፡፡
በዕለተ ዓርብ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ፍጥረታት በልብ የሚሳቡ በእግር የሚራመዱ በክንፍ የሚበሩ ናቸው፡፡ ሁሉንም የፈጠራቸው ሴትና ወንድ አድርጎ ነው፡፡ለምሳሌ የቤት እንስሳት ላም፣ በሬ፣ ፈረስ፣ በቅሎ፣ ፍየል፣ በግ ውሻ እና ድመት ናቸው፡፡
አዕዋፍ ዶሮ፣ ድንቢጥ፣ እርግብ ሌሎችም ናቸው፡፡ እንስሳት ለምሳሌ አጋዘን፣ ፊቆ፣ ሚዳቋ፣ ጎሽ፣ ዝሆን፣ ዋልያ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ቀዳሚት ሰንበት ማለት ቅዳሜ ማለት ነው፡፡ በዚች ዕለት ልዑል እግዚአብሔር ሊፈጥረው የወደደውን ሃያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ አከናውኖ አረፈባት፡፡ /ዘፍ.2፡2/ በመሆኑም እግዚአብሔር ባርኮ  የቀደሳትን ዕለት ማክበር ይገባል፡፡
ልጆች እስኪ ጥያቄ እንጠይቃችሁ
1ኛ. ሀልዮና ነቢብ ማለት ምን ማለት ነው?
2ኛ. ሔዋን እንዴት ተፈጠረች?
ልጆች በመጠኑም ቢሆን ሥነ ፍጥረትን እንዳወቃችሁ ተስፋ እናደር 
ጋለን፡፡ በተረፈ ሰንበት ትምህርት ቤት ሔዳችሁ ተማሩ እሺ ጎበዞች፡፡