በግዮን ሆቴል ሊካሔድ የነበረው የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ እንዳይካሔድ ተከለከለ
የካቲት 7 ቀን 2006 ዓ.ም.
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት በየሦስት ዓመቱ የሚካሔደው የአብነት መምህራን የምክክር ጉባኤ ከቅዱስ ፓትርያርኩ በተሰጠ መመሪያ መሠረት እንዳይካሔድ ተደርጓል፡፡
የጉባኤውን መከልከል አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ እና የማኅበሩ ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት በጋራ እንደገለጹት “ማኅበሩ በየሦስት ዓመቱ ይህንን ጉባኤ ያካሒዳል፤ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ዓላማውም የአብነት መምህራንን የቀለብ፣ የአልባሳት፣ የፍልሰት ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲሁም መምህራኑ በቂ ደመወዝ ስለማይከፈላቸው ድጋፍ ለማድረግና የአቅም ማጐልበቻ ውይይትና ሥልጠና ለማድረግ የታቀደ ነበር፡፡

ዐሥራ ሦስት የመመሪያ ረቂቅ ሰነዶችን ከ12/11/2005 ዓ.ም ጀምሮ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሲያጠናና ሲያወያይ የነበረው 18 አባላት ያሉት አጥኚ ኮሚቴ ዛሬ የካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተደረገው የመረካከቢያ መርሐ ግብር ረቂቅ ሰነዶችን ለብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ረዳትና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አስረከቡ፡፡