የሰናፍጭ ቅንጣትማቴ 13÷31

 ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም.

 

ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መላክ
በምዕ/ጎጃም ሀገረ ስብከት
የ፬ቱ ጉባኤያት መምህር

 

 

ታላቅነትን በታናሽነት ሰውራ የያዘች እንከን የለሽ፤ዙሪያዋን ቢመለከቷት ነቅ የማይገኝባት አስደናቂ ፍጥረት ናት፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት፡፡ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስወንጌልን በምሳሌ ካስተማረባቸው መንገዶች አንዱ ሰናፍጭ ነው፡፡ ስትዘራ ታናሽነቷ ስትበቅል ግን ታላቅነቷ የገዘፈ ምሥጢር ያለው በመሆኑ ለዚህ ተመርጣለች በመጽሐፍ እንደተባለ ሰናፍጭ ስትዘራ እጅግ ታናሽናት ስትበቅል ግን ባለብዙ ቅርንጫፍ እስከመሆን ደርሳ ታላቅ ትሆናለች ከታላቅነቷ የተነሳ እጅግ ብዙ አእዋፍ መጥተው መጠጊያ እንደሚያደርጓትም አብሮ ተገልጿል አሁን ታናሽነቷን በታላቅነት መሰወር ችላለችና ብዙዎችን ልታስገርም ትችላለች፡፡

ይህ ምሳሌ ታላቅነትን በታናሽነት ሰውራ ይዛ የኖረችውን የክርስቶስ ቤተ ክርሰቲያን ነው እንጅ ሌላ ምንን ያመለክታል? የሰናፍጭ ቅንጣት ብሎ የጠራት አካሉ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ሰናፍጭ ሁሉ ሲዘራት ትንሽ ነበረች፡፡ በመቶ ሃያ ቤተሰብ ብቻ የተዘራች ዘር ናት፡፡የእግዚአብሔርን ምሥጢር ልብ አድርጉ ኦሪትን ሲመሰርት እንዲህ ነበርን? በሙሴ ምክንያት በስድስት መቶ ሺህ ህዝብ መካከል የሰራት አይደለምን? ወንጌልን ግን እንዲህ አይደለም ከመቶ ሃያ በማይበልጡ ሰዎች መካከል ሰራት እንጅ ፡፡ወደሕይወት የሚወስደው መንገድ የጥቂቶች ብቻ መሆኑን ሲያሳየን ይህን አደረገ፡፡

ሰናፍጭ ካደገች በኋላ ለብዙዎች መጠጊያ እስኪሆን ድረስ ብዙ ቅርንጫፍ እንድታወጣ ቤተ ክርስቲያንም የዓለም መጠጊያ የሰው ልጆች መጠለያ ናት፡፡ ኦሪት በብዙዎች መካከል የተሰበከች ብትሆንም ቅሉ ቅርንጫፏ ከቤተ እስራኤል ወጥቶ ለሞዓብና ለአሞን ስንኳን መጠጊያ ሊሆን አልቻለም፡፡ ቤተክርስቲያን ግን ቅርንጫፏ ከምድር እስከ ሰማይ ደርሶ ሰማያውያኑንና መሬታውያኑን ባንድ ማስጠለል ይችላል ሙታን ሳይቀር መጠለያቸው ቤተክርስቲያን ናት እንጅ ሌላ ምን አላቸው፡፡ከዚህም የተነሳ‹‹ ሰናይ ለብዕሲ መቅበርቱ ውስተ ርስቱ፤ለሰው በርስቱ ቦታ መቀበሩ መልካም ነው ››እያሉ ሥጋቸውን በቤተክርስቲያን ነፍሳቸውን በገነት እንዲያኖርላቸው ይማጸናሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን እንደ ሰናፍጭ ካልቀመሷት በቀር ጣዕሟ የማይታወቅ ታናሽ የምትመስል የሰናፍጭ ቅንጣት ናት ለቀመሷት ሁሉ ደግሞ ጣዕሟ በአፍ ሳይሆን በልብ የሚመላለስ ከደዌ የሚፈውስ ነውና ቀርባችሁ ጣዕመ ስብከቷን ፣ጣዕመ ዜማዋን ፤ጣዕመ ቅዳሴዋን እንድትቀምሱ አደራ እላችኋለሁ፡፡ከዚሁሉ ጋራ ርስታችሁ ናትና ከአባቶቻችሁ በጥንቃቄ እንደ ተረከባችሁ ለቀጣዩ ትውልድ እስክታስረክቡ ድረስ የተጋችሁ እንድትሆኑና የጀመራችሁን መንፈሳዊ ተጋድሎ በትጋት እንድትፈጽሙ መንፈስ ቅዱስን ዳኛ አድርጌ አሳስባችኋለሁ፡፡

ኃያሉ አምላክ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሀገራችን ኢትዮጵያን አንድነት የኦርቶዶክስ ተዋህዶቤተ ክርስቲያናችንን ዕድገት ለዘለዓለሙ ይባርክ፡፡