የእንጅባራ ማእከል ላለፉት 4 ዓመታት ሲያስተምራቸው የቆዩ 200 ተማሪዎችን አስመረቀ
በማኅበረ ቅዱሳን የእንጅባራ ማእከል የግቢ ጉባኤ ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ለአራት ተከታታይ ዓመታት በሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን በመደበኛ እና በኤክስቴንሽን መርሐ ግብር ሲያስተምራቸው የነበሩ 200 የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን አስመርቋል።
ከተመራቂ ተመሪዎች መካከል አንድ የዋንጫ፣ 11 የሜዳልያ እና 12 የማዕረግ ሰርተፍኬት ተሸላሚዎች የሚገኙበት ሲሆን የዋንጫ እና የሁለት ሜዳልያ ተሸላሚው ዲ/ን አላምራው ዋጋው ከወሰደው 55 ኮርሶች መካከል 46ቱን A+ እና 9ኙን A ውጤት በማምጣት ጠቅላላ 4 ውጤት አስመዝግቧል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ትምህርተ ወንጌል፣ ወረብ እና የበገና መዝሙር በተመራቂ ተማሪዎች የቀረበ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳን የእንጅባራ ማእከል ሰብሳቢ አቶ ይበልጣል አበጀ እንኳን አደረሳችሁ በማለት የማኅበሩን መልእክት አስተለላልፈዋል።
ሰብሳቢው በመልእክታቸውም ብዙ ውጣ ውረድ አልፋችሁ ለዚህ ደርሳችኋል እና እንኳን ደስ አላችሁ በማለት የእስካሁኑ ሕይወታችሁ ላይ ቤተ ክርስቲያን: ቤተሰቦቻችሁ: መምህራነ ወንጌል እና ጓደኞቻችሁ ነበሩበት አሁን ደግሞ እነዚ አካላት ከእናንተ የሚጠብቁት ብዙ ነገር ስላለ እናንተ በርትታችሁ ቤተ ክርስቲያንን ሳትረሱ ከጎኗ እንድትሆኑ እና ክርስትና ጉዞ ስለሆነ ይህንን ሕይወት አስቀጥላችሁ በክርስትና ሕይወት እንዲሁም በአገልግሎት እንድትጽኑ በማለት አደራ ብለዋል።
በመጨረሻም በአባቶች ቡራኬ እና ጸሎት ተደርጎ ለሁሉም ተመራቂዎች የአደራ መስቀል ተስጥቶ መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።
