የቱን ታስታውሳላችሁ?
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፳፰፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ ለሆነው ጾመ ፍልሰታ አደረሳችሁ፡፡ ልጆች! በየዓመቱ በጉጉት የምንጠብቃት ጾመ ፍልሰታን እንደ አቅማችን በመጾምና በመጸለይ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከቤዛዊተ ዓለም በረከትን መቀበል ይገባናል፤ ልጆች! በጾመ ፍልሰታ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ፣ ትምህርት በመማር፣ በማስቀደስ፣ መልካም ምግባራትን በመፈጸም መሳተፍ አለብን፡፡
ልጆች! በዛሬ “የቱን ታስታውሳላችሁ?” መርሐ ግብራችን ባሳለፍነው ዓመት ስንማራቸው ከነበሩ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራት መካከል የተወሰነ ጥያቄን አዘጋጅተንላችኋል፡፡ ከዚህ ቀደም የአስተማርናችሁን ትምህርት በደንብ ከልሷቸው፤ ከዚያም ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ በድረ ገጽ አድራሻችን “website.amharic@eotcmk.org” እና “https://t.me/Hiwot122716” ትልኩልናላችሁ! እንደተለመደው ጥሩ ውጤት ለሚያመጡ ልጆች ሽማቶችን አዘጋጅተናል፡፡
፩. ውድ ልጆች! እርሱን የያዘ ሰው ድሀ ሀብታም፣ ኃጥእ፣ ጻድቅ ሳይል ሁሉን እኩል ይወዳል፤ በፍጹም ልቡ እርሱን የያዘ ጻድቅ ነው ብሎ አይወድም፤ ኃጥእ ብሎ አይጠላም፤ እኩል ይወዳል፤ በሰዎች ክፉ አያደርግም፤ ክፉ አያደርግበትም፤ ወንድሙ ሲያጠፋ ቢያየው እንኳን ይመክረዋል፤ ገበናውን ይሸፍንለታል፤ አሳልፎ አይሰጠውም፤ ለራሱ ብቻ ጥፋቱን ይነግረዋል፡፡ ታዲያ እርሱ ማን ነው? —————————————-
፪.አባቱ ያዕቆብ ለወንድሞቹ ስንቅ አድርስ ብሎ ላከው፤ መንገዱ ሩቅ ስለነበር በጣም ደከመው፤ በዚያም ላይ ራበው፤ የያዘውን ምግብ እንዳይበላ ደግሞ የወንድሞቹ ነው፤ የሚበላ ይዞ ተራበ፤ ለአባቱ በመታመን ለወንድሞቹ አድርስ የተባለውን ቢርበውም አልበላውም፤ በዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና በተአምራት ድንጋዩን ዳቦ አድርጎለት በላ፤ እርሱ ማን ነው? ——————————-፡፡
፫. ከንጉሣቸው ታዘው ሊይዙት የመጡትን የሶርያ ንጉሥ ወታደሮችን በእግዚአብሔር ቸርነት ማርኮ ከእስራኤሉ ንጉሥ ዘንድ ወሰዳቸው፤ ምንም እንኳን እነርሱ ሊገድሉት ቢመጡም እርሱ ግን ይቅርታን በማድረግ እንጀራ በልተው በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አደረገ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ማን ነው? —————————————
፬. እምነቱ፣ ታጋሽነቱ ይለካ (ይታይ) ዘንድ ንብረቱ ወደመበት፤ እንደገናም ልጆቹ ሞቱበት፤ ይህም ብቻ አይደለም፤ እርሱ ራሱ በጣም ለብዙ ዘመን ታመመ፤ እግዚአብሔር እየረዳው ሁሉን በትዕግሥት አሳለፈ፤ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ እግዚአብሔር አዳነው፤ ሀብት ንብረቱንም ሰጠው፤ ለትዕግሥት (ለመታገስ) ምሳሌ አድርገው ይጠሩታል! እርሱ ማን ነው? —————————————-
፭. ስለ መታዘዝ በተማራችሁት መሠረት በአጭሩ ግለጹ! ———————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————————-፡፡
፮. የእስራኤል ንጉሥ በነበረበት ጊዜ ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ መጠጣት ፈለገ፤ “ከቤተልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ” ሲልም ተመኘ፤ በዚህ ጊዜ የጭፍሮቹ አለቆች አዲኖን፣ ኢያቡስቴ እና ኤልያና ለእርሱ ካላቸው ፍቅር የተነሣ ወደ ጠላቶቻቸው ጦር ሄደው፣ ውኃውን ቀድተው አመጡለት፤ ለእርሱም ፍቅር ብለው ደማቸውን ለማፍሰስ መድፈራቸውን ተገንዝቦ ወንድሞቹ ያመጡለትን ውኃ አልጠጣም ብሎ ውኃውንም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በማድረግ አፈሰሰው፤ እርሱ ማን ነው? —————————————–
፯.ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር የተባለው ሰው እኅቶች መልካም ምግባር የነበራቸው ጌታችንም ይወዳቸው የነበሩ ——————————-እና ———————– ይባላሉ፡፡
፰. ባላጠፋችው በሐሰት (በውሸት) ተከሳ ለፍርድ ቀረበች! ምስክሮቹ በውሸት መሰከሩባት፤ ያለ ጥፋቷም ሊትቀጣ ስትል እግዚአብሔር ነቢዩ ዳንኤልን ልኮ የሐሰተኛ ምስክሮችንና ክፉ ሥራቸውን አጋለጠ፤ እርሷም ከመቀጣት ዳነች፤ ሐሰተኞቹ ግን ተቀጡ፡፡ ውድ ልጆች መዋሸት ጥሩ አይደለም እሺ! እግዚአብሔር ከሐሰተኛ ምስክሮች የጠበቃት እርሷ ማን ናት? ——————————፡፡
፱. እግዚአብሔር በልጅነቱ ንጉሥ አድርጎ ሾመው፤ ንጉሥ ሳኦል የተባለው በእርሱ ቀንቶ ብዙ ጊዜ ሊገድለው ሞከረ፤ እግዚአብሔር ግን አዳነው፤ ሁለት ጊዜ ሊገድሉት የመጣውን ንጉሥ ሳኦልን አግኝቶ ምንም ሳያደርገው በይቅርታ አለፈው፤ ውድ ልጆች! እግዚአብሔር እንደልቤ በማለት የሚጠራው የእስራኤል ንጉሥ የነበረው እርሱ ማን ነው? ———————
፲. አባ ባይሞን ታዛዥነቱን ለማየት የደረቀ እንጨት ተክሎ ውኃ እንዲያጠጣ አዘዘው፤ እርሱም የመምህሩን ትእዛዝ በመቀበል ለሁለት ዓመታት ያንን ደረቅ እንጨት ውኃ አጠጣው፤ በሦስተኛውም ዓመት እግዚአብሔር ታዛዥነቱን ተመልክቶ የደረቀው እንጨት ፍሬ እንዲያፈራ አደረገለት፤ ውድ ልጆች! እናንተም ታዛዦች ሁኑ! ግን ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? ——————————
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ትማሩት ከነበረው ትምህርት “የቱን ታስታውሳላቸሁ?” በሚል ጥቂቱን ብቻ ጠየቅናችሁ፤ ምላሻችሁን እንጠብቃለን፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ልዩ ነው! ውለታውን ሳንረሳ ትእዛዙን በመጠበቅ እኛ ደግሞ ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጽ፡፡ ወላጆቻችን ለእኛ ብዙ ነገር እያደረጉልን በትምህርታችን ጎበዝ ስንሆን፣ በሥነ ምገባር ስንታነጽ ደስ እንደሚላቸው እኛም ፈጣሪ እግዚአብሔር ያዘዘንን ትእዛዝ በመፈጸም ለእርሱ ያለንን ፍቅር እንግለጥ፡፡
ቸር ይግጠመን !!!
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!