የሐዋርያት ጾም
ዲያቆን ዘኪዮስ አደሙ
ሰኔ ፪፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ጾም ማለት፡- “ጾመ” ተወ፣ ታቀበ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ለተወሰነ ሰዓት ከእህልና ከውኃ፣ በተለይም ሥጋዊ ስሜትን ከሚቀሰቅሱ ምግቦችና መጠጦች መከልከልን ያመለክታል፡፡ በሌላ መልኩ ዐይንን ክፉ ከማየት፣ ጆሮን ክፉ ከመስማት፣ አፍንጫን የመጠጥ ሽታና የሲጋራን ጪስ ከማሽተት፣ እጅን ከመስረቅና ከመማታት፣ እግርን መሸታ ቤትና ቃልቻ ቤት ከመሄድ ወዘተ. መከልከል ጾም ይባላል፡፡
የጾም ዓላማ
፩. ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት፡- ይህ ማለት ሰው በሚጾም ጊዜ ከዚህ በፊት ሳይጾም ያደርጋቸው የነበሩ ነገሮችን እያደረገ አይጾምም ማለት ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ለሥጋ ኃይልና ጉልበት ከሚሰጡ ምግቦች ይርቃል፤ ጾም ኀዘን በመሆኑ ምክንያት ለሥጋ ደስታን ከሚፈጥሩ ማንኛቸውም ነገሮች ይታቀባል፣ ከምቹ አልጋው ላይ ይወርድና ምንጣፍ ላይ ይተኛል፤ በፊት ከሚጸልየው ጸሎት በላይ እጅግ አብዝቶና ተግቶ ይጸልያል፤ ምክንያቱም ጾም የጸሎት እናት ናትና፡፡ እንዲህ ባለ መልኩ ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን ካላስገዛን፣ ያለ ገደብ ያገኘነውን ሁሉ ካግበሰበስን ሰውነታችን ይፋፋል፤ ስሜታችን ይግላል፤ ደማችን ይፈላል፤ ፍትወተ ሥጋችንም ያይልብንና ኃጢአት እንሠራለን፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፡- “የጠላትን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፡ የእህሉንም መግቢያ ይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶች ይራባሉ፤ ይጠማሉም፡፡ የነፍስን ጾር ለማሸነፍም በተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኀብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይደክማሉ” ብሏል፡፡ ስለዚህ ይህ ጾም ጠላት ዲያብሎስ በፈቃደ ሥጋችን በኩል ተጠግቶን በፈተና እንዳይጥለን አርቆ ማጠሪያ ሥርዓት መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡
፪. ሥጋውና ደሙን ለመቀበል፡-
ልጆቿ እንደ መሆናችን በዚህ ዓለም ስንኖር እናት ቤተ ክርስቲያን አድርጉ ያለችንን እያደረግንና አታድርጉ ያለችንን በመተው ነው፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም እንደ ሥራችን ዋጋ የምንቀበልበት ከሞት በኋላ ትንሣኤ እንዳለ ስለምናውቅ፡፡ ለንስሐ የተሰጠንን ቀኖና ከፈጸምን በኋላ ለ ፲፰ ሰዓታት ማለትም ሐሙስ ማታ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አንሥቶ ነፍሱን እስከሰጠበት ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ያለውን ጌታችን ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራውን እያሰብን በመጾም ሥጋውና ደሙን እንቀበላለን፡፡ የትውልድ ሁሉ ናፍቆት የሆነችውን ሰማያዊ መንግሥትን ለመውረስ እምነትን ከሥራ በማስተባበር ከጾምን በኋላ ቅዱስ ቊርባንን እንቀበላለን፡፡
በጾም እነ ማን ተጠቅመዋል?
፩. አዳምና ሔዋን፡- አዳምና ሔዋን ትእዛዘ እግዚአብሔርን አፍርሰው አትብሉ የተባሉትን ዕፀ በለስ በመብላታቸው ምክንያት ከጸጋ ተራቁተውና ተረግመው ከገነት ተባረሩ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በአዳም አነሣሽነት ሁለቱም ሱባኤ ይዘው ጾሙ፣ ጸለዩ መሥዋዕትንም አቀረቡ፡፡ ምንም እንኳን ጾማቸውና መሥዋዕታቸው ባያድናቸውም ተስፋ ግን አስገኝቶላቸዋል፡፡ ይህም ከ5500 ዘመን በኋላ እኔ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው የሚል ተስፋ ነው፡፡ ይህ ይታወቅ ዘንድ (ገላ.፬፥፬) ‹‹የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከው›› አለ፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ የተባለው ፶፻፭፻ ዘመን ነው፡፡ እናም አዳምና ሔዋን በመጾማቸው ምክንያት አምላክ ሊያድናቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው፡፡ ቃል ኪዳኑንም ጠብቆ አዳናቸው፡፡ ስለዚህ ጾም ከመከራ መውጫ መንገዳቸው ሆነ ማለት ነው፡፡
፪. ሊቀ ነቢያት ሙሴ፡- አባታችን ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት በጾምና በጸሎት ቢተጋ በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ ሁለት ጽላቶችን ለመቀበል ችሏል፡፡ ይህም በጾም የተገኘ ታላቅ ስጦታ ነው፡፡
፫. የነነዌ ሰዎች፡- ይህስ እንዴት ነው ቢሉ የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን በመርሳት የማይገባ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን ቢበድሉት እርሱም ነቢዩ ዮናስን ልኮ ገሥፃቸው፡፡ እነሱም ተጸጽተው ሦሰት ቀን ሙሉ ከእህል ውኃ ተከልክለው ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም ይቅር አላቸው፡፡ ሊያመጣባቸው የነበረውንም መዓት ከእነርሱ ላይ አራቀ፡፡ በዚህ ታሪክ የታዘዘ መቅሠፍት በጾም እንደሚከሽፍ እንማራለን፡፡
ይህን ያህል ስለ ጾም ምንነትና በጾም ስለተጠቀሙ ሰዎች ካነሣን ቀጥለን ደግሞ ከፊታችን ባለው በዓለ ጰራቅሊጦስ ማግሥት ስለምንጾመው ጾም እናንሣ፡፡
ጾመ ሐዋርያት (የሐዋርያት ጾም)
ቅዱሳን ሐዋርያት ኃይለ መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ማግሥት አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድመው አገልግሎታቸው ፍሬ እንዲያፈራ ጾምን በመጾም ነው የጀመሩት፡፡ ለዚህም መነሻ የሆናቸው በ (ማቴ.፱፥፲፬) ላይ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ‹‹እኛና ፈሪሳውያን ጾምን እንጾማለን፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን አይጾሙም ለምንድን ነው? ብለው ጠየቁት እሱም ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ ብሎ መለሰላቸው፡፡›› ሐዋርያትም ይህንን የጌታ ቃል አብነት አድርገው ሙሽራው ክርስቶስ ከእነሱ በተለየ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸው መንፈስ ቅዱስን በተቀበሉ ማግስት ለአገልግሎታቸው መቃናት ትምህርታቸውን (ስብከታቸውን) በጾም ጀምረውታል፡፡ ይህም ይታወቅ ዘንድ “እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” በሚል ስብከት ዓለምን መማረክ ችለዋል፡፡ በስቅላቱ ያላፈሩበት አምላካቸው ኃይል ጽንዕ ሆኖላቸው ዓለምን መዋጀት ቻሉ፡፡ የተቀበሉት መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ አድሮ ሥራ በመሥራቱ ፈቃደ ሥጋቸው አይሎባቸው በከንቱ ውዳሴ እንዳይወድቁ ሥጋቸውን በጾም እየጎሰሙ የአምላክን ሥራ በመግለጣቸው ይኸው ዛሬ እነርሱ ያቀጣጠሉት የወንጌል ችቦ እኛ ጋር ደርሶ እንማረዋለን፡፡ ዛሬም እኛ ቅዱሳን ሐዋርያትን አብነት አድርገን በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማግስት እነርሱ የጾሙትን ጾም እንጾመዋለን፡፡ የምንጾምበት ምክንያት ደግሞ፡-
፩. ጾሙን የጾሙ ሐዋርያት በረከት እንዲደርሰንና ጾሙን በመጾም ያገኙትን መንፈሣዊ ኃይል እኛም ለማግኘት፡፡
፪. ለ ፶ ቀናት ያህል ከጾምና ከስግደት ተለይተን በመቆየታችን ሥጋችን ባገኘው ድሎት በኃጢአት ተጠልፈን እንዳንወድቅና ራሳችንን መግዛት እንድንችል፡፡
፫. በጾምና ጸሎት ጅማሬውን ያደረገ ማንኛውም ውጥን የሠመረ ስለሚሆን፡፡
፬. የምንሰጠው ማንኛውም ዓይነት አገልግሎት ፍሬ እንዲያፈራ፣ የምንናገረውን በተግባር እንድንኖረው፣ ሰውን ወደ ንስሐ የሚመራ መልእክት እንድናስተላልፍ በዋናነት የሚረዳን ጾም ስለሆነ፡፡
፭. አልሸነፍ፣ አልለቅ ያለ ክፉ አጋንንት ድል የሚነሳውና አፍሮ የሚኮበልለው በጾም ስለሆነ፡፡
ስለዚህ ጾም ይህንንና በዚህ ውስጥ ያላካተትናቸውን ብዙ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ስለሆነ እንጾማን፡፡ ምናልባት የሐዋርያት ጾምን ላለመጾም ሰበብ ደርዳሪዎች እንዲህ ሲሉ ይሰማሉ፤ “እኔ ካህን ገደልኩ እንዴ የሐዋርያትን ጾም የምጾመው? ይህ የካህናት ጾም ነው እነርሱ ይጹሙት” ሲሉ እንሰማለን፡፡ በመሠረቱ የካህናት ተብሎ ለብቻው የተሠራ ጾም የለም፡፡ ሲቀጥል ደግሞ ካህን የገደለ ሰው ፀጉሩ ተላጭቶ ወደ ወይኒ ይወርዳል እንጂ የሐዋርያትን ጾም እንዲጾም ምክንያት አይሆነውም፡፡ ስለዚህ ይህንና መሰል ስሕተት የሆኑ ሐሳቦችን በመደርደር ከጾሙ የሚገኘውን በረከት እንዳናጣ አምላከ ሐዋርያት ይርዳን፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር