ፊደል
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
ፊደል፤ ፈደለ፤ ጻፈ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን፤ ትርጉሙም የጽሕፈት ሁሉ መጀመሪያ፤ ምልክት፤ የመጽሐፍ ሁሉ መነሻ ማለት ነው፡፡
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ፊደል የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ በቁሙ ልዩ፤ምርጥ ዘር፤ ቀለም፤ ምልክት፤ አምሳል፤ የድምጽና የቃል መልክ ሥዕል፤ መግለጫ፤ ማስታወቂያ፤ ዛቲ ፊደል፤ ሆህያተ ፊደል፤ ወዘተ በማለት ያብራሩታል፡፡
ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህን ጠቅሰው፡-
፩.ፊደል ማለት መጽሔተ አእምሮ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ ፊደል ማንበብም መጻፍም አይቻልምና የአእምሮ መገመቻ፤ የምሥጢር መመልከቻ ማለት ነው፡፡
፪. ፊደል ማለት ነቅዐ ጥበብ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የጥበብ ሁሉ መገኛ ፊደል ናትና፡፡
፫. ፊደል ማለት መራሔ ዕዉር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የሰውን ልጅ ሁሉ ከድንቁርና ጨለማ አውጥቶ ወደ ብርሃን ዕውቀት ይመራልና፡፡
፬. ፊደል ማለት ጸያሔ ፍኖት ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ድንቁርናን ጠርጎ አጽድቶ ከፍጹም ዕውቀት ያደርሳልና፡፡
፭. ፊደል ማለት ርዕሰ መጻሕፍት ማለት ነው ምክንያቱም የመጽሐፍ ሁሉ ራስ ፊደል ነውና፡፡
፮. ፊደል ማለት ጽሑፍ ማለት ነው፣ ፊደል ማለት ፍጡር፣ ወይም መፈጠሪያ ማለት ነው ብለው አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ፊደል ማለት በዚህ መልክ የሚገለጽ ሲሆን፤ እያንዳንዱ ፊደል ሀልዎተ እግዚአብሔርን፤ የሥነ ፍጥረትን ነገር ወዘተ የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡
የግእዝ ፊደል ቅደም ተከተል በአበገደ ወይስ በሀለሐመ የሚለው ሐሳብ ላይ በርካታ ሊቃውንት ጠንከር ያለ ክርክር ያነሳሉ፡፡ ለምሳሌ ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር በሁለቱም ጎራ ካሉት እየጠቀሱ የምሁራኑንም ሐሳብ ካቀረቡ በኋላ የእርሳቸውንም ያቀርባሉ፡፡ የተወሰኑትን እንመልከት፡-
አለቃ ኪዳነ ወልድን፤ ደስታ ተክለ ወልድን፤ መምህር ዘሚካኤል ገብረ ኢየሱስን ጠቅሰው በአበገደ እንደሚጀምር ያስረዳሉ፡፡ እንደነዚህ ሊቃውንት አባባል ሌላው ቀርቶ አብዛኞቹ የፈጣሪ መጠሪያ ስሞች በአልፋው አ ነው የሚጀምሩት ይላሉ፡፡
ለምሳሌ እግዚአብሔር፣ አኽያ (/ያ/ አይጠብቅም)፤ አዶናይ፤ ኤልሻዳይ፤ አብ፤ አውሎግዮስ፤ አማኑኤል፤ ኤሉሄ፤ ወዘተ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም እግዚአብሔርን ባመሰገነበት መዝሙሩ ከአሌፍ እስከ ታው ሲደርስ የተጠቀመው በአበገደ ነው በማለት በአበገደ የሚጀምረው ትክክል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ ቀዳሚውና ትክክለኛው በአበገደ የሚነበብ ሲሆን፤ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአባ ፍሬምናጦስ ከሣቴ ብርሃን ጀምሮ ግን በሀለሐመ ቅደም ተከተል እያገለገለ ይገኛል፡፡
በሁለተኛው ጎራ ደግሞ የመጀመሪያውና ትክክለኛው በሀለሐመ የሚነበበው ነው ይላሉ፡፡ ከጥንት ከጥዋቱ ጀምሮ ፊደላችን የሚጀምረው በሀለሐመ ቅደም ተከተል ነው፡፡ በአበገደ ነበር የሚሉት በልማድ የመጣ ከጽርዕና እብራይስጥ በተውሶ የተገኘ ሐሳብ ነው፡፡ በዚህም ጎራ ካሕሳይ የጠቀሷቸው ዶክተር ፍሥሓ ጽዮን ካሳና አስረስ የኔሰው ግንባር ቀደምቶች ናቸው፡፡ የነሱንም መሟገቻ እንዲህ በማለት ጠቅሰውታል፡፡
‹‹…በመሠረቱ በሕገ ጠባይዕም ከአ ሀ ይቀድማል፤ አንድ ሰው ሀ ካላለ አ ማለት አይችልም፡፡ ሀ ማለት አፍ መክፈት ማለት ነው፡፡ ጥንት በሳባውያን ወይም በአግዓዝያን ቋንቋ ሀ አፍ መክፈት ማለት ሲሆን በትርጓሜም ቢሆን ሀ ትልቅ ምሥጢር ያለው ፊደል ነው፡፡ ሀ ሀገር፤ ሀ ሀብት ከማለት ጋር በግእዙ ግስ “ሀለወ” አለ፤ ኖረ፤ ነበረ ማለት ነው፡፡ ይህ የዶክተር ፍሥሐ ጽዮን ሲሆን፤ የአስረስ የኔሰውም እንዲህ ቀርቧል፡፡
ትክክለኛው የግእዝ ፊደል ቅደም ተከተል ሀለሐመ ለመሆኑ ከዕብራይስጥና ጽርዕ የማይገናኝ ለመሆኑ፡-
፩.የግእዝ ጽሑፍ ከግራ ወደ ቀኝ መሆኑ፤
፪.የዕብራውያን ፊደል ደረጃ አምስት ሲሆን የግእዝ ግን ሰባት መሆኑ፤
፫. የግእዝ ፊደሎች ተራ ቊጥር ፳፮ መሆናቸው ነው፡፡
በአጠቃላይ የፊደላቱ ቅደም ተከተል በሁለቱም ቢሆን እያንዳንዱ ፊደል ትርጉም አለው፡፡ ትርጉሙ ነገረ እግዚአብሔርን ማለትም ዘለዓለማዊነቱን፤ ፈጣሪነቱን በአጠቃላይ ትምህርተ ሃይማኖትን የሚያስረዳ ነው፡፡ በዚህ እትም የምንመለከተው ከሀ እስከ ፐ የፊደላትን ትርጉም ከትምህርተ ሃይማኖት አንጻር ይሆናል፡፡
ሀ፡- ሀልዎቱ ለአብ እምቅድመ ዓለም፤ የአብ አኗኗር ከዓለም በፊት ነው፡፡
ለ፡- ለብሰ ሥጋ እምድንግል፤ አካላዊ ቃል ከድንግል ሥጋን ተዋሐደ፡፡
ሐ፡- ሐመ ወሞተ እግዚእነ፤ ጌታችን መከራን ተቀብሎ ሞተ፡፡
መ፡- መንክር ግብሩ ለእግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፡፡
ሠ፡- ሠረቀ በሥጋ አምላክ፤ አምላክ በሥጋ ተገለጠ
ረ፡- ረግዓት ምድር በቃሉ፤ ምድር በቃሉ ረጋች ፡፡
ሰ፡- ሰብአ ኮነ እግዚእነ፤ ጌታችን ሰው ሆነ፡፡
ቀ፡- ቀዳሚሁ ቃል ውእቱ፤ በመጀመሪያ ቃል ነበረ፡፡
በ፡- በትሕትናሁ ወረደ እምሰማይ፤ ጌታችን በትሕትናው ከሰማይ ወረደ፡፡
ተ፡- ተሰብአ ወተሰገወ፤ ጌታችን ፈጽሞ ሰው ሆነ፡፡
ኀ፡- ኃያል እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ኃያል ነው፡፡
ነ፡- ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ ጌታችን ደዌያችንን ተቀበለ፣ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡
አ፡- አአኵቶ ወእሴብሖ ለእግዚአብሔር፤ እግዚአብሔርን ፈጽሜ አመሰግነዋለሁ፡፡
ከ፡- ከሃሊ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ቻይ ነው፡፡
ወ፡- ወረደ እምሰማይ እግዚእነ፤ ጌታችን ከሰማይ ወረደ፡፡
ዐ፡- ዐርገ ሰማያተ እግዚእነ፤ ጌታችን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡
ዘ፡- ዘኩሎ ይእኅዝ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ሁሉን የሚይዝ ነው፡፡
የ፡- የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኃይለ፤ የእግዚአብሔር ሥልጣን ኃይልን አደረገች፡፡
ደ፡- ደመረ ሥጋነ ምስለ መለኮቱ፤ ሥጋችንን ከመለኮቱ ጋር አንድ አደረገ፡፡
ገ፡- ገብረ ሰማያተ በጥበቡ፤ ጌታ በጥበቡ ሰማያትን ፈጠረ/አዘጋጀ/፡፡
ጠ፡- ጠዐሙ ወታእምሩ ከመኄር እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱና ዕወቁ፡፡
ጰ፡- ጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ፤ የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ ነው፡፡
ጸ፡- ጸጋ ወክብር ተውህበ ለነ፤ ጸጋና ክብር ለእኛ ተሰጠን፡፡
ፀ፡- ፀሐየ ጽድቅ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር የእውነት ፀሐይ ነው፡፡
ፈ፡- ፈጠረ ሰማየ ወምድረ፤ ሰማይና ምድርን ፈጠረ፡፡
ፐ፡- ፓፓኤል ስሙ ለአምላክ፤ ፓፓኤል የአምላክ ስም ነው፡፡
ከሀ እስከ ፐ ያሉት ፊደላት እንዲህ ያለ ትርጉም ሲኖራቸው በአበገደ ቅደም ተከተልም እንዲሁ የየራሳቸው ትርጉም አላቸው፡፡ በአበገደው ቅደም ተከተል መጠሪያም ስላላቸው ያን መሠረት አድርጎ ትርጉማቸውንም መመልከት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ አ አሌፍ የሚል መጠሪያ አለው፡፡ በመሆኑም አሌፍ ማለት አብ ፈጣሬ ኵሉ ዓለም፤ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ አብ ነው ማለት ነው፡፡ ሌሎቹም በዚህ መልክ የየራሳቸው ትርጉም ያላቸው ሲሆን፤ በዋናነት መመልከት የፈለግነው የግእዝ ፊደላት እያንዳንዳቸው ትርጉም ያላቸውና ነገረ እግዚአብሔርን መግለጽ የሚችሉ መሆናቸውን ነው፡፡
ፊደላት ነገረ እግዚአብሔርን የሚገልጹ እንደመሆናቸው ሁሉ የመጻሕፍት ራስ ናቸው፡፡ መንፈሳውያን መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ናቸውና፡፡ እግዚአብሔር ለአበው ቃል በቃል፤ በራእይ እና በምሳሌ እየተገለጠ መልእክቱን እንዳስተላለፈ ሁሉ በመጽሐፍም ተናግሯል፡፡ «እስመ ይነግሮሙ ለሕዝቡ በመጽሐፍ፤ ለሕዝቡ በመጽሐፍ ይነግራቸዋልና» በማለት ልበ አምላክ ዳዊት እንደተናገረው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለሕዝቡ መልእክቱን የሚናገርባቸው መጻሕፍት የሚጀምሩት ከፊደል ነው፡፡ በመሆኑም ፊደል የመጻሕፍት ሁሉ ራስም እግርም ናት፡፡ ከላይ ቢሉ ከግርጌ የምትገኝ እርሷ ናትና፡፡
እንግዲህ በዚህ እትም የሀለሐመ ፊደላትን ትርጉም ተመልክተናል በሚቀጥለው ደግሞ የአበገደን ፊደላት ትርጉም እንመለከታለን፡፡
ይቆየን
ምንጭ፤ ሐመር መጽሔት ፳፮ኛ ዓመት ቊጥር ፱