‹‹እግዚአብሔር መልካም ነው፤ በመከራ ቀን መሸሸጊያ ነው›› (ናሆም ፩፥፯)

እግዚአብሔር አምላክ የሰዎችን ደኅነትን የሚሻ መልካም አባት በመሆኑ ልጆቹን ከመከራ ይሸሽጋል፡፡ በዘመነ ኦሪት እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ሲኖሩ ከመከራ ሠውሯቸዋል፤ ነፃ ሊያወጣቸውም ፈቅዶ ነቢዩ ሙሴን እንዲህ አለው፤ ‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያንም ተገዥነት አወጣችኋለሁ፥ ከባርነታችውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ፤ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፡፡›› (ዘፀ. ፮፥፮-፯)

መፃጒዕ

በዘመነ ሥጋዌ በኢየሩሳሌም ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በተለያየ ሕመም ይሠቃዩ የነበሩ ሰዎች ለመፈወስ የሚሰበሰቡባት ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፡፡ አምስትም መመላለሻ ነበራት፡፡  በዚያም ብዙ ድውያን ይተኛሉ፤ ከእነርሱም ውስጥ የታወሩ፣ አንካሾች፣ የሰለሉ፣ ልምሹ የሆኑ፣ በየእርከን እርከኖች ላይ ይተኙ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም ውኃውን ለመቀደስ በሚወርድ ጊዜ ድምፁ እስኪያስተጋባ ድረስ ውኃው ይናወጣል፡፡ ድውያኑም በዚያ ሥፍራ ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቃሉ፡፡ ምክንያቱም በዕለተ ሰንበት (ቀዳሚት) ውኃው ሲናወጥ ቀድሞ ወደ ውኃው የገባ አንድ ሰው ከደዌው ይፈወስ ነበርና፡፡…

የሻጮችና የለዋጮች ወንበር የሞላው ቤተ መቅደስ

ጥንቱን ለልማዱ የቤተ መቅደስ መሠራት ምክንያቱ ሰዎችን ለመቀደስ፣ ሕያዊት ነፍስ የተሰጠቸው ሥጋዊ ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ጸሎቱን አድርሶ መሥዋዕቱን አቅርቦ ከእግዚአብሔር ምሕረት ሊቀበልበት አልነበረምን? ‹‹ለዘለዓለም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይኖራሉ›› ብሎ የመረጠው የነገሥታት ንጉሥ የእግዚአብሔር ልዩ ሥፍራ ነው ቤተ መቅደስ፡፡ መቅረዙና ጠረጴዛው የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበረበት፤ የወርቁ ማዕጠንት፣ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ጽላት፣ በውስጧም መናን የተሸከመችው መሶበ ወርቅና ክህነት የጸናባት የአሮን በትር እንዲኖሩ ታዝዞ ነበር፡፡  በምድራውያን ሰዎች መካከል እንደ ምሰሶ የሚቆመው ካህን ገብቶ የሚያጥንበት ይህ ቤተ መቅደስ ምንኛ የከበረ ነው? ለሰዎች ሁሉ ራዕይን አይቶ የሚነግራቸው ባለ ራዕይ ነቢይ የማይታጣበት፣ ሊቀ ካህናቱ የሚደገፈው ያቁም፣ ንጉሡ የሚደገፈው በለዝ የሚባሉት ምሰሶዎች የሚገኙበትም ነው፡፡ ያዕቆብ እንዳለው ይህ ቤተ መቅደስ የሰማይ ደጅ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ (፩ ነገ. ፱÷፫፣ ዕብ. ፱÷፪፣ ዘፍ. ፳፰÷፲፯)

‹‹የሚራሩ ብፁዓን ናቸው›› (ማቴ.፭፥፯)

መራራት ማለት ምሕረት ማድረግ፣ ቸርነት፣ ለተጨነቀ ወይም ለተቸገረ ማዘንና ርዳታን መስጠት፣ ይቅር ማለት፣ ማዘን፣ ወዘተ ሲሆን ምሕረት ሥጋዊና ምሕረት መንፈሳዊ ተብሎ በሁለት ሊከፈል ይችላል።

‹‹አንተ ሰይጣን፤ ከአጠገቤ ሂድ!›› (ማቴ.፬፥፱)

መቈጣት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ሊቃውንቱ እንዲህ ዓይነቱን ቊጣ ‹‹መዓት ዘበርትዕ›› ይሉታል፤ የሚገባ ቊጣ ማለታቸው ነው፡፡ ቊጣና ተግሣጽ ከሚያስፈልጋቸው ፍጥረታት አንዱ ሰይጣን ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ይገባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተቈጥቶ የሚያውቀው በአይሁድና በአጋንንት ላይ ነው፡፡ ሰይጣንን ተቈጥቶ ካስወገደበት ቀን አንዱ ይህ ዛሬ የምናነሣው ነው፡፡ ሰይጣን አፍሮ ከኛ የሚርቅባት ቀን ምንኛ የተባረከች ቀን ናት? ጌታ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ገዳመ ቆሮንቶስ ገባ፡፡ ካመኑ ከተጠመቁ በኋላ ወደ መንፈሳዊው ዓለም መጓዝ ይገባል ማለቱ ነው፡፡ ገዳም ገብቶ አርባ ቀንና አርባ መዓልት ጾመ ጸለየ፡፡ ሲጠመቅ በመጠመቁ ዋጋ የሚያገኝበት ሆኖ አይደለም፡፡ ውኆችን ለማክበር በጥምቀት ምእመናን እንዲወለዱ ጥምቀትን የጸጋ ምንጭ ሊያደርጋት ተጠምቋል እንዳልን በመጾሙና በመጸለዩም እንደ ኤልያስ ወደ ሰማይ ያረገ፣ እንደ ዳንኤል የአንበሳን አፍ የዘጋ፣ እንደ ሙሴም ሕግን የተቀበለበት አይደለም፡፡ ጾምና ጸሎት ዋጋ ማሰጠታቸውን አውቀው ከእሱ በኋላ የተነሡ ምእመናን እንዲይዙት ለማስተማር ነው፡፡ በዚያውም ላይ ጥንቱንም የጎዳን መብልና መጠጥ ነው፤ አሁንም ነፍሳችን የምትታደሰው በጾምና በጸሎት ስለሆነ ነው፡፡

የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን ተቃጠለ

የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን መንሥኤው ባልታወቀ እሳት መቃጠሉን የገዳሙ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ በመጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም የጀመረውን እሳት ለማጥፋት ርብርብ ቢደረገም ከሰው ዐቅም በላይ በመሆኑ ማጥፋት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ የገዳሙ መነኰሳት፣ ከሐረር፣ ድሬዳዋና አሰበ ተፈሪ የተሰባሰቡ ምእመናን እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ቃጠሎውን ለማስቆም ቢሞክሩም ጥረታቸው ባለመሳካቱ ደኑ በመቃጠል ላይ ይገኛል፡፡ አካባቢውም ንፋሳማ በመሆኑ በተለይም ምሽት ላይ የሚነፍሰው ኃይለኛ ንፋስ ቃጠሎውን በማባባሱ እሳቱ ደኑን ጨርሶ ወደ ገዳሙ በመድረስ እንዳያቃጥለውም ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያም አስታውቀዋል፡፡

‹‹እግዚአብሔርም የፈጠረው ሁሉ እጅግ ያማረ እንደሆነ ተመለከተ›› (ዘፍ.፩፥፴፩)

በባሕርዩ ክቡር የሆነው እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ ክቡር ነው። ይሁን እንጂ አበው በብሂላቸው ‹‹ከጣትም ጣት ይበልጣል›› እንዲሉ እጅግ የከበሩ ፍጥረታትም አሉ። ከእነዚህ እጅግ የከበሩ ፍጥረታት ከሚባሉት መካከል በቀዳሚነት የሚገኘው የሰው ልጅ ነው። ስለዚህ የሥነ ፍጥረትን ታሪክ የጻፈልን ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሁሉንም ፍጥረታት ከፈጠረ በኋላ ‹‹መልካም እንደሆነ አየ›› እያለን ይመጣና ሰው ላይ ሲደርስ ግን ‹‹እጅግ መልካም እንደሆነ አየ›› በማለት ይደመድማል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ‹‹ሰንበት ተዐቢ እምኵሉ ዕለት ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት፤ ከዕለታት ሰንበት ትበልጣለች፤ ከፍጥረታትም ሁሉ ሰው ይበልጣል›› በማለት እንደነገረን የሰውን ልጅ እጅግ ክቡር ፍጥረት መሆኑን ያስረዳናል። የሰው ልጅ ክቡርነት በተመለከተ መጻሕፍት አምልተውና አስፍተው ይናገራሉ። (ዘፍ.፩፥፴፩)

‹‹የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ›› (ዮሐ.፪፥፲፮

በኢየሩሳሌም፤ ምኵራብ ተብሎ በተሰየመው የዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት ዕለተ እሑድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ አይሁድ ንጉሥ ናቡከደነፆር ቤተ መቅደስን ካፈረሰባቸው በኋላ ሕገ ኦሪትን መማሪያ እና መጸለያ ስፍራ በማጣታቸው የሠሩት አዳራሽ ምኵራብ ነበርና፡፡ በዚያም ጌታችን በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው ባገኘ ጊዜ ያየውን ባለመውደዱ የገመድ ጅራፍ ካዘጋጀ በኋላ በጎችንና በሮዎችን እንዲሁም ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የሻጮቹንም ገንዘብ በተነባቸው፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ይሸጡ የነበሩትን ደግሞ፤ ‹‹ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮)

ቅድስት

ቅድስት የሚለው ቃል ትርጉሙ ‹‹የተለየች፣ የተመረጠች፣ የከበረች›› ማለት ነው። ሥርወ ቃሉም ‹‹ተቀደሰ›› ሲሆን ፍቺው ደግም ‹‹ክቡር፣ ምስጉን፣ ምርጥ›› ማለት ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ሁለተኛው እሑድ በአዘጋጀው ምስጋና አማካኝነት ዕለቱ ‹‹ቅድስት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ገጽ ፯፻፹፬)

‹‹ኢየሱስን በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው ይህ ነው›› (ራእ. ፲፬፥፲፪)

በዮሐንስ ራእይ ላይ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ኢየሱስን በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው ይህ ነው›› በማለት የተናገረው ኃይለ ቃል የመጨረሻውን ዘመን አስጨናቂ እና ፈታኝ መሆን እንዲሁም ክርስቲያኖች ይህን ተረድተው በትዕግሥት መጽናት እንደሚገባቸው ለማስረዳት ነው፡፡ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር ፲፩ ላይ ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ፣ የስሙንም ምልክት የሚጽፉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት እንደሌላቸው፣ ሕዝብንና አሕዛብን ስለሚፈትነው፣ በመጨረሻ ዘመን ስለሚነሣው አውሬ እና በእርሱም ምክንያት ብዙዎች ወደ ዘለዓለማዊ እሳት እንደሚጣሉም ይገልጻል፡፡ (ራእ. ፲፬፥፲፪)