መስቀል

መስቀል የፍቅር ተምሳሌት

የዓለም ሰላምና አንድነት

ጠላት በቀራንዮ የተሸነፈበት

የሰው ልጅ ድኅነት

መስቀል

መስቀል የሰላም መሠረት ነው

መስቀል  የሰላም መሠረት፤ ሰላምም የመስቀል ፍሬ ነው፡፡ በግእዝ ሰላም የሚለው ቃል ትርጉም ‹‹ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ እርቅ፣ ሰላምታ፣ የቡራኬና የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝና ሲለያይ የሚናገረው›› ነው፡፡ መስቀልና ሰላም አንዱ የአንዱ መሠረት አንዱ የአንዱ ፍሬ ሆነው የተሳሰሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት

ክርስትና የሕይወት መንገድ ነው፡፡ መንገዱም ደግሞ ወደ ዘላዓለማዊ ክብር የሚያደርስ የሕይወት የድኅነትና የቅድስና መንገድ ነው፡፡ ክርስቲያን ለመሆን በ፵ እና በ፹ ቀን በመጠመቅ የሥላሴ ልጅነትን ማግኘት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ ማለትም ነው፡፡

ዘመነ ፍሬ

ከመስከረም ፱ እስከ ፲፭ ያሉት ዕለታት ዘመነ ፍሬ ተብለው ይጠራሉ፡፡ በእነዚህ ወቅት የሚዘመረው መዝሙርም ሆነ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር ለምድር ፍሬንና ዘርን የሚሰጥ የዓለም መጋቢ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡

ስምና የስም ዓይነቶች

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

……ካለፈው የቀጠለ

ባለፈው ጽሑፋችን የስም ክፍሎችን አውጥተን እንድንዘረዝር መልመጃ ሠርተን ነበር፡፡ እንዲሁም ያወጣናቸውን ስሞች ዐረፍተ ነገር እያስገባን ሠርተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ መራሕያን(ተውላጠ ስሞች)ን በመደብ፣ በቁጠርና በጾታ ከፋፍለን እንመለከታለን፡፡

መራሕያንን (ተውላጠ ስሞችን) በመደብ፣ በቁጥር እና በጾታ ከፋፍሎ ማጥናት ይቻላል፡፡

  መደብ   ቀዳማይ (ቅሩብ) አነ፣ ንሕነ
ካልዓይ (ቅሩብ) አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ አንትን
ሣልሳይ (ርኁቅ) ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ፣ ውእቶን

ከላይ የሚያመለክተው ሠንጠረዥ መራሕያንን በመደብ  የሚያሳይ ሲሆን ከጥር  አንጻር ደግሞ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

         ቊጥር
ነጠላ ብዙ
አነ ንሕነ
አንተ አንትሙ
አንቲ አንትን
ውእቱ ውእቶሙ
ይእቲ ውእቶን

ከላይ የሚያመለክተው ሠንጠረዥ መራሕያንን በቁጥር የሚያሳይ ሲሆን ከጾታ አንጻር ደግሞ እንደሚመለከተው ይሆናል፡፡

                  ጾታ
ተባዕታይ አንስታይ
አነ አነ
ንሕነ ንሕነ
አንተ አንቲ
አንትሙ አንትን
ውእቱ ይእቲ
ውእቶሙ ውእቶን

እንደማንኛውም የቋንቋ ትምህርት በግእዝ ቋንቋም የመደብ የጾታና የቊጥር ስምምነት አለ፡፡ ለምሳሌ አንተ ብለን ተሴሰየ ልንል አንችልም፡፡ እንዲሁም አንተ ብለን ተሴሰይኪ ልንል አንችልም፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር የመደብ በሁለተኛው ዐረፍተ ነገር ደግሞ የጾታ መፋለስ ያስከትላል፡፡ መራሕያንን በመደብ በጾታና በቊጥር ከፋፍለን ስናጠናም ይህን ሁሉ መገንዘብ እንዲቻል ነው፡፡ በቋንቋ ባለሙያዎችም ሩቅና ቅርብን፣ አንድና ብዙን፣ ሴትና ወንድን ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባ በሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ፡-

አንተ ካልን ተሴሰይከ

ውእቱ ካልን ተሴሰየ

አንቲ ካልን ተሴሰይኪ

ውእቶን ካልን ተሴሰያ

አንትን ካልን ተሴሰይክን ወዘተ እንላለን፡፡ 

የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ጸሐፈ የሚለውን ግስ እናንሳና በዐሥሩም መራሕያን እንመልከተው፡፡

አነ            ጸሐፍኩ                 አንትን     ጸሐፍክን

ንሕነ          ጸሐፍነ                  ውእቱ       ጸሐፈ

አንተ          ጸሐፍከ                 ውእቶሙ     ጸሐፉ 

አንትሙ       ጸሐፍክሙ              ይእቲ        ጸሐፈት

አንቲ          ጸሐፍኪ                ውእቶን       ጸሐፋ

ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ

ርእሰ ዐውደ ዓመት

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት መስከረም አንድ ቀን ይከበራል፡፡ ስያሜው ቅዱስ ዮሐንስ በመባል ሲታወቅ ከመስከረም አንድ እስከ ስምንት ድረስ ያሉት ዕለታትንም ያካትታል፡፡ በዚህ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር ክብረ ቅዱስ ዮሐንስንና ርእሰ ዐውደ ዓመትን የሚያወሳ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ያስተማረውን ትምህርትና ገድሉን የሚያመለክት ስብከት ይሰበካል፤ ትምህርቱም ይሰጣል፡፡ አዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስም የተሰየመበት ምክንያት፡-

፩. የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል መነሻ በመሆኑ

ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ‹‹እነሆ÷ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ድምጽ፤ ዮሐንስም በምድረ በዳ ያጠምቅ ነበር፤ ኃጢአትንም ለማስተስረይ የንስሓ ጥምቀትን ይሰብክ ነበር፡፡ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ሁሉንም ያጠምቃቸው ነበር»  (ማር.፩፥፪-፭) ብሎ ጽፎልናል፡፡ የካህኑ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ›› እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት በምድረ በዳ እያስተማረና የንስሓ ጥምቀት እያጠመቀ በዘመነ ወንጌል መጀመሪያ ምዕራፍ ተገኝቷል፡፡ እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ በነቢያት መጨረሻ በሐዋርያት መጀመሪያ ተገኝቶ ዘመነ ሐዲስን እንደሰበከና ከዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ መሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ስለነበረ ያለፈውን ዘመን የምንሸጋገርበት የዘመን መለወጫ ቀን የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

፪. መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የጻድቃን የሰማዕታት ርእስ ነውና

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ላይ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም›› (ማቴ.፲፩፥፲፩) ብሎ ጌታችን ስለ ዮሐንስ በተነገረለት መሠረት የጻድቃን የሰማዕታት ርእስ እንደመሆኑ አዲስ ዓመትም የበዓላት ሁሉ በኩር ርእስ ነውና በስሙ ተጠርቷል፡፡ እንደዚሁም ጌታ ባረገ በ፻፹ ዘመን በእስክንድርያ ፲፪ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የተሾመው ቅዱስ ድሜጥሮስ  ባሕረ ሐሳብን ሲደርስ ከዮሐንስ ጀምሮ ደርሶታል፤ ሲጨርስም ለኢየሩሳሌም፣ ለሮም፣ ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ ሊቃነ ጳጳሳት ልኳል፡፡ በእስክንድርያ /ግብጽ/ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በዓላት የሚከበሩትና አጽዋማት የሚገቡት ከመስከረም አንድ ተነስቶ በመቁጠር ነው፡፡  በቤተ ክርስቲያናችን የበዓላቱና የአጽዋማቱ መደብ የሚታወቅበትና የዘመናቱ ሂደት ተቀምሮ የሚታወጅበት መስከረም አንድ በመሆኑ ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም የዘመን መለወጫን አዲስ ዓመት በዓል አስመልክቶ እንደነገረን ‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ፤›› የዓመት በዓል ራስ ዮሐንስ መጥቅዕና አበቅቴን የምትወልድ ነህ›› እየተባለ ይዘመርለታል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች፣ በውጭ ወራሪ ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሰዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ  ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው፡፡

Read more

ጾመ ዮዲት

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

በናቡከደነጾር ዘመነ መንግሥት ንጉሡ ሥልጣኑን መከታ በማድረግ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በግድ እያስገደደ እጅ መንሻ ይቀበል ነበር፡፡ የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበለውንም እየገደለ፣  ጭፍሮቹ ኃያልነቱንና ገናናነቱን በዓዋጅ በጦር አዛዦች ጭምር እያሳወጀ፣ በርካታ የጦር ሠራዊቶችን አሰልፎ ከአይሁድ ከተማ ገባ፡፡ በዚያም ነዋሪዎችን በማስፈራራት የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበሉትን ሁሉ እያሳደደ ስላስጨነቃቸው ማቅ ለብሰው፣ አመድ ነስንሰውና ድንጋይ ተንተርሰው ወደ ፈጣሪያቸው በመጮህ መለመን ጀመሩ። በጭካኔ የተሞላው የጦር አበጋዙ ሆሎፎርኒስም ይበልጥ እጅግ እንዲሰቃዩ ውኃ የሚቀዱበትን ስፍራ ተቆጣጠረው፤ በግዴታ ማርኮም እጅ እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው በመጽሐፈ ዮዲት ፪፥፪ ላይ ተጽፏል፡፡ በአካባቢው ይኖር የነበረ ዖዝያን የተባለ አንድ ሰው የአባቶቻቸው አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማቸው ለአምስት ቀናት በትዕግሥት ይጾሙና ይጸልዩ ዘንድ ሕዝቡን መከራቸው፤ እነርሱም በትዕግሥት ሊጠብቁ ተስማሙ፡፡

የእስራኤል ልጆች የናቡከደነጾርን ጦር ብንችል ተዋግተን እንረታለን፤ ካልሆነም እጅ እንሰጣለን በማለት ይመካከሩ ጀመር። በዚያን ጊዜ ባሏ የሞተባትና በንጽሕና ተጠብቃ፣ በጸሎትና በሕገ እግዚአብሔር የምትኖር ዮዲት የተባለች ሴት ነበረች። (ዮዲት ፯፥፲) እግዚአብሔርን የምትፈራ ብቸኛዋ ሴት እርሷ ነበረችና ምክክራቸውን ስትሰማ ለምን «እግዚአብሔር ያድነናል አትሉም» ብላ ገሠጸቻቸው፡፡ ማቅ በመልበስ፣ አመድ በመነስነስና ድንጋይ በመንተራስም ሱባኤ ገባች። በሦስተኛው ቀንም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቧን የምታድንበትን ጥበብ ገለጸላት፤ ዮዲትም እግዚአብሔር የሰጣትን ውበት ተጠቅማ ሕዝቧን ከጥፋት የምትታደግበትን ጥበብ ተረዳች።

የክት ልብሷን ለብሳ፣ ሽቱ ተቀብታና ተውባ የጠላት ሠራዊት ወዳሉበት የጦር ሰፈር በድፍረት አመራች፡፡ ሠራዊቱም ውበቷን አይተው እጅግ በመደነቅ «ይህችስ ለአለቃችን ትገባለች» ተባብለው ከጦር መሪያቸው ዘንድ ወሰዷት። እርሷም ቀድማ ማምለጫ መንገድ አዘጋጅታ ነበርና ወደ አዛዡ ከገባች በኋላ «ክቡር ጌታዬ ሆይ ርስት ተወስዶብኛል፤ እንድትመልስልኝ አስቀድሜ ደጅ ልጠና መጥቻለውና ርዳኝ፤ ትብብርህ አይለየኝ» አለችው፡፡ በስሜት ፈረስ ታውሮ የነበረው የሠራዊቶቹ አዛዥም የጠየቀችውን እንደሚፈጽምላት ቃል ገባላት። ባማረ ድንካን እንዲያስቀምጧት ሎሌዎቹን አዘዘ። ዮዲትም የተሰጣትን ጥበብ ተጠቅማ፣ መውጣት ስትፈልግ የምትወጣበትን እና የምትገባበትን ዕድል በእግዚአብሔር አጋዥነት ዐወቀች፡፡ ከቀናት በኃላ የጦር አበጋዙ ለሠራዊቱ የምሳ ግብዣ አዘጋጅቶ ዮዲትን ከጎኑ አስቀመጣት፤ ከበሉና ከጠጡ በኋላም ሁሉን ሰው አስወጣ፤ እልፍኙን በመዝጋት ከእርሷ ጋር ብቻውን ሆነ፤ ነገር ግን እንቅልፍ ጣለው፡፡ (ዮዲት ፰፥፪) እርሷም ወደ አምላኳ ጸለየች፤ ፈጣሪዋ እንዲረዳትም አጥብቃ ለመነች። በኋላም ከራስጌው ሰይፍ አንስታ አንገቱን ቀላችው፤ በድኑንም ከመሬት ጣለችው። የሆሎፎርኒስን ሞት ሠራዊቱ ሲሰሙ አውራ እንደሌለው ንብ ተበተኑ፤ ከፊሎቹ ሞቱ። እስራኤላውያንም ከሞት ተርፈው በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረጉ፤ በደስታም ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ።

ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ የሚያስረዳን ዮዲት ጠላቶቿን ድል ያደረገችው በጾምና በጸሎት እንደሆነ ነው፡፡ ለእኛም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ምንም እንኳ ወርኃ ጳጉሜን የፈቃድ ጾም ቢሆንም በሀገራችን የተጋረጠውን ችግር እናልፍ ዘንድ በፈቃደኝነት እንጾማለን። እግዚአብሔር አምላካችን ለሁላችንም ጥበብ ሰጥቶናል። ይህም ችግሮችን ሁሉ የምንፈታበት መንገድ ነው። በዚህም የዓመተ መሸጋገሪያና የክረምቱ ወር ማብቂያ በመሆኑ ዕለተ ምጽአት ስለሚታሰብበት በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ከሌሊት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን ጠበል በመጠመቅ፣ በማስቀደስና በመጸለይ እንዲሁም ሥጋ ወደሙን በመቀበል ልናሳልፍ ይገባል። ዕለተ ምጽአትም ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው ዓለም መሸጋገሪያችን ነውና በቀኙ እንቆም ዘንድ እንጾማለን፡፡ የሚመጣውን አዲስ ዘመንም በንጽሕና ለመቀበል ስላለፈው ዓመት ኃጢአታችን ንስሓ የምንገባበት ጾምም ነው።   

ከተጋረጠብን ችግር «እግዚአብሔር ያድነናል» በማለት ልክ እንደ ዮዲት ሱባኤ ገብተን፣ ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰንና ድንጋይ ተንተርሰን አብዝተን ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡ ሊለያየን፣ ሊነጣጥለን፣ ሊበታትነን እና ሊገድለን ካሰበው እንዲሁም ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ሊነፍገን ከቃጣው ጠላትና ሃይማኖታችንን ሊያስተወን ከሚመጣ ፀረ ሃይማኖት እንድናለን። ስለዚህ ከፊታችን ያለችውን ስድስቱን የጳጉሜን ቀን በፍቅር፣ በአንድነትና በሃይማኖት ጸንተን፣ ጾመን፣ ጸልየን ለዘመነ ዮሐንስ እንድንደርስ እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን፤ አሜን።

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ጎሐ፤ ጽባሕ

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

ጎሐ ፤ ጽባሕ ከነሐሴ ፳፱ እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያሉት ቀናት የሚጠሩበት ነው፤ ጎሐ ማለት ነግህ ሲሆን ጽባሕ ደግሞ ብርሃን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው «ዘመናትን የምታፈራርቅ፤ የብርሃንን ወገግታ የምታመጣ አንተ ነህ» እያለ በመግለጽ ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው፣ ከመኖርም ወደ አለመኖር የሚያሳልፍ፣ በጨለማ መካከል ብርሃንን ያደረገ እርሱ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ብርሃን እና ቀን የልደት፣ ሌሊትና ጨለማን የሞት ምሳሌዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ከነሐሴ ፳፱  እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያለው ወቅት የክረምቱ ጨለማ የሚወገድበት፣ የፀሐይ ብርሃን ወለል ብሎ የሚወጣበት፣ ጉምና ደመና በየቦታቸው ተሰብስበው፣ ሰማይ በከዋክብት አሸብርቆ የሚታይበት ነው፡፡

በክረምቱ ውኃ ሙላት ምክንያት ግንኙነት አቋርጠው የነበሩ ወገኖች ሁሉ በዚህ ክፍለ ጊዜ ብርሃን ስለሚያዩ፤ መገናኛ መንገዶችም ስለሚያገኙ፣ ክረምቱን እንደ ሌሊት በመመልከት ይህን ወቅት እንደ ንጋት መታየቱን ለመግለጽ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ጎሐ፤ ጽባሕ›› በሚለው ስያሜ ትጠራዋለች፡፡ በዚህ ወቅት የሚዘመሩ መዝሙራት ‹‹አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለውና በማለዳ ድምፄን ስማ›› (መዝ.፭፥፪)፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ብርሃንን አየ፣ በሞት ጥላ ሥር ለተቀመጡት ብርሃን ወጣላቸው (ማቴ.፬፥፲፮) የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን (ጸሎተ ሃይማኖት)

ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊት ንጽሕትና ቅድስት የክርስቶስ ማደሪያ ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ እናንተን ጰጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለራሳችሁ እና ለመንጋው ሁሉ ተጠንቀቁ» በማለት ያስጠነቅቃል፡፡ በሰው ልጅ ፈቃድና ሐሳብ ያልተሠራች እግዚአብሔር በደሙ የዋጃት ቅድስት ሥፍራ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሰማይና በምድር ያለች፣ ከሰው ልጅ ዕውቀት ፈቃድና ፍላጎት በላይ የሆነች የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት፡፡ እግዚአብሔር የመሠረታት፣ የቀደሳትና የዋጃት፣ ሐዋርያት፣ ነቢያትና ቅዱሳን አበው የሰበኳትና ያጸኗት ቤት ናት፤ ለሰውም በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን ታድላለች፡፡