ምልአተ ባሕር

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

የበአተ ክረምት ሁለተኛው ክፍል ምልአተ ባሕር ይባላል፡፡ ይህም ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ድረስ ያለው ወቅት ሲሆን ዝናም ምድርን የሚያለመልምበት፤ የተዘራው የሚበቅልበት፤ በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ከሐምሌ ፲፱ እስከ ሐምሌ ፳፱ መባርቅት የሚበርቁበት፤ ባሕርና አፍላጋት የሚሞሉበት ወቅት ነው፡፡

መብረቅና ነጎድጓድ

መብረቅ ማለት የእሳት ሰይፍ፤ የእሳት ፍላፃ፤ በዝናም ጊዜ ከደመና አፍ የሚመዘዝ የሚወረወር ነው፡፡ (ራእ ፬፥፭፤ ኤር ፲፥፲፫፤ ኢዮ. ፴፯፥፬) የመብረቅ ተፈጥሮ ውሃው በደመና አይበት ተቋጥሮ ሲመጣ በነፋስ ወደል ጋዝ ተጭኖ ፤ ደመናና ደመና በተጋጨ ጊዜ የሚፈጠር ነው፡፡ ወተት ሲገፋ ቅቤ እንደሚወጣው አይነት ማለት ነው፡፡

ነጎድጓድ ማለት ታላቅ ግሩም ድምፅ፤ የሚያስፈራ፤ የሚያስደነግጥና የሚያንቀጠቅጥ ሲሆን (መዝ. ፸፮፥፲፰፤ ኢዮ. ፵፥፬)፤ መብረቅ ከወረደ በኋላ የሚሰማ ድምፅም ነው፡፡ (ኢዮ. ፴፯፥፪-፭፤ መዝ. ፳፰፥፫) ነገር ግን ለማስደንገጥ ወይም ለመዓት ብቻ የተፈጠረ አይደልም፤ ማኅፀነ ምድርን በመክፈት ውኃው ሠርፆ እንዲገባና አዝርዕትና አትክልት እንዲበቅሉ፤ እንዲያብቡና እንዲያፈሩ የሚያደርግ ጭምር ነው፡፡(ሄኖ.፮፥፩)

የክረምትን ኃይልና ብርታት ጥግ አድርገው የሚከሠቱ የተፈጥሮ ኃይላት ዑደትም ይጸናበታል፡፡ መብረቅ፤ ነጎድጓድ፤ ባሕርና አፍላጋት (ወንዞች) ይሠለጥናሉ፡፡ጥልቅ የሆኑ ቦታዎች መጠናቸው ያድጋል፤ ምንጮች ይመነጫሉ፤  የወንዞች ሙላት ይጨምራል፡፡

በቅድስት ቤተክርስቲያን በዚህ ክፍለ ክረምትና ንኡስ ክፍል ዘርዕን፤ ደመናን፤ ዝናምን የሚያዘክሩ እና የመብረቅን፤ የነጎድጓድን፤ የባሕርን፤ የአፍላጋትን፤ የጠልን ጠባይዓት የሚያመለክቱ መዝሙራት ይዘመራሉ፤ ምንባባት ይነበባሉ፤ ስብከት ይሰበካል፡፡

ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድም ይህን ወቅት አስመልክቶ በድጓው ላይ በገለጸው መሠረት ‹‹ደምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌሥሑ ነዳያን፤ ይጸግቡ ርኁባን ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናብም በዘነመ ጊዜ ድሆች ደስ ይሰኛሉ፤ ረኃብተኞችም ይጠግባሉ፤ ምድር አየችው፤ አመሰገነችውም፤ ባሕርም ሰገደችለት›› የሚለው ዜማ ይዜማል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፡፡ ‹‹ሰማይን በደመና የሚሸፍን፤ ለምድርም ዝናምን የሚያዘጋጅ፣ ሣርን በተራሮች ላይ ልምላሜውንም ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል›› (መዝ.፻፵፮፥፰፤መዝ.፻፴፬፥፮፤መዝ.፸፮፥፲፰፤ መዝ.፷፬፥፱) ሲል ዘምሯል፡፡

እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ፤ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑን፤ የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡ ምንባባትም ከቅዱስ ወንጌልና ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት እንዲሁም ከሐዋርያት ሥራ ክረምቱን በተመለከተ የተዘጋጁት ይነበባሉ፡፡

 

ቃል

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

ቃል የፊደላት ስብስብ ሆኖ ልናስተላልፈው የፈለግነውን ሐሳብ የሚሸከም የሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው፡፡ ቃል የማይታይ፣ የማይዳሰስ፣ በጆሮ ብቻ የሚደመጥ ሲሆን ቋንቋ ትዕምርታዊ በመሆኑ እና ቃል ደግሞ የቋንቋ አንድ መዋቅር በመሆኑ በፊደላት አማካኝነት ይታያል፡፡ ይህ ጸሐፊ ብዕር ቀርጾ፣ ብራና ዳምጦ፣ ቀለም በጥብጦ በልቡናው ያለውን ሐሳብ ሲጽፈው ረቂቁ ይገዝፋል፤ የሚታይ፣ የሚዳሰስም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነው ቃል የፊደላት ስብስብ ሆኖ በልቡናችን ላለና ልናስተላልፈው ለፈለግነው ሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው የተባለው፡፡

ቃል ከምልክትነት ወይም ከቋንቋ መዋቅር ብቻ ሳይሆን ከትርጉም ሰጭ መዋቅርነት አንጻር የነገር ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ባየ ይማም በመጀመሪያም ቃል ነበረ የሚለውን በዮሐንስ ወንጌል ዮሐ.፩፥፩ መሠረት አድርገው የቋንቋ ፍች ወይም ትርጉማዊነት መነሻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ትርጉማዊ መዋቅር ከመመሥረት አንጻር ቃልን የሚቀድመው መዋቅር የለም፡፡ ፊደል ብንል ብቻውን ትርጉም ሊሰጠን አይችልም፡፡ ምዕላድ ብንልም ትርጉም አዘል እንላለን እንጂ ሙሉ ትርጉም ሊሰጠን አይችልም፡፡ ሙሉ ትርጉም ሊሰጠን የሚችል መዋቅር ቃል ስለሆነ የትርጉማዊ መዋቅር መነሻ እንለዋለን፡፡

የቃልን ምንነት ፕሮፌሰር ባየ ይማም የአማርኛ ሰዋስው በሚባል መጽሐፋቸው ከቃል የሚያንሰውን የቋንቋ ቅንጣት (ምዕላድን) ከአስረዱ በኋላ ቃልንም እንዲህ ይገልጹታል፡፡

-ትርጉም አዘል አሐድ ነው፡፡

-ራሱን ችሎ መቆም የሚችል ነው፡፡

-በውስጡ ብዙ ጥገኛ ምዕላዶችን ሊይዝ ይችላል፡፡

-ከቃላት ክፍሎች ውስጥ ባንዱ ሊመደብ ይችላል፡፡ ባየ (፳፻፱፥፸፭)

ከላይ የተገለጸው የቃል ብያኔ እንደ ማንኛውም ቋንቋ ነው፡፡ ግእዝም የራሱ የሆነ መለያ ባሕርይ ቢኖረውም እንደማንኛውም ቋንቋ የጋራ የሆኑትን የቋንቋ ባሕርይን፣ ብያኔንና መዋቅርን ይጋራልና የቃል ብያኔ በግእዝ ቋንቋም ከላይ የተገለጸውን እንጠቀማለን፡፡ በራሱ ሥርዓትና አገባብ ለመግለጽ አንድ ምንባብ እንጥቀስና በምሳሌ እናስረዳ፡፡

አቡነ ዘበሰማያት ይትቀደስ ስምከ ትምጻእ መንግሥትከ ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር ሲሳየነ ዘለለእለትነ ሀበነ ዮም ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንሕነኒ ንሕድግ ለዘአበሰ ለነ ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት አላ አድኅነነ ወባልሀነ እምኵሉ እኵይ እስመ ዚአከ ይእቲ መንግሥት ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ዕለት ዕለት እንድናመሰግነው ባዘዘንና ዘወትር በምንጸልየው ጸሎት (አቡነ ዘበሰማያት) በርካታ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ሐሳብ በቃል ይገለጻል ብለናልና ሐሳባችንን ለመግለጽ ቃላትን ተጠቅመናል፡፡ ቃላቱ በሥርዓት ተዋቅረው ሙሉ መልዕክት እንድናስተላልፍ አድርገውናል፡፡ ቃላቱን በተወሰነ መልኩ ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡

አቡነ፣ ሰማያት፣ ይትቀደስ፣ ስምከ፣ ትምጻእ፣ መንግሥትከ፣ ይኩን፣ ፈቃድከ፣ ሰማይ፣ ምድር፣ሲሳየነ፣ ዕለት፣ ሀበነ፣ ዮም፣ ኅድግ፣ ለነ፣ አበሳነ፣ ጌጋየነ፣ ንሕነ፣አበሰ፣ ኢታብአነ፣ እግዚኦ፣ ውስተ፣ መንሱት……..ወዘተ እነዚህ ሁሉ ከላይ ፕሮፌሰር ባየ ይማም በገለጹት መንገድ ቃል ለመባል የሚያስችለውን መስፈርት የሚያሟሉ የሐሳባችን ወካዮች ናቸው፡፡

ለምሳሌ አቡነ የሚለው ቃል መልእክት አለው አባታችን የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ማለትም ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል፡፡ ይህ ማለት በዐሥሩ መራሕያን መርባት ይችላል፡፡ በዐሥሩ መራሕያን ሲረባ ጾታን፣ መደብን፣ ቁጥርን፣ ወዘተ ያመለክታል፡፡  ስለዚህ ዋና ቃሉ አብ የሚለው ሲሆን “ነ” የሚለውን ዘርፍ አመልካች ምዕላድ አስጠግቷል፤ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ስም በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡

“ይትቀደስ” የሚለውንም ቃል ብንወስድ መልእክት አለው ይመስገን የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ ሌላ ፊደል ወይም ምዕላድ ሳይፈልግ ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል፡፡ ይህም ዋና ቃሉ ቀደሰ የሚለው ሲሆን በግስ እርባታ ሥርዓት “ይት” የሚለውን የሣልሣይ (የትእዛዝ) አመልካች ምዕላድ አስጠግቷል፤ በዐሥሩ መራሕያን መርባት ይችላል፡፡ በዐሥሩ መራሕያን ሲረባ ጾታን፣ መደብን፣ ቁጥርን፣ ጊዜን ወዘተ ያመለክታል፡፡ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ግስ በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡

ሐሳቡ ግልጽ እንዲሆን አንድ ተጨማሪ ምሳሌ እንጥቀስ፡፡ “እኩይ” የሚለው ቃል መልእክት አለው “ክፉ” የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ ሌላ ፊደል ወይም ምዕላድ ሳይፈልግ ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል ይህም “እምኵሉ” ከሚለው ቃል ኵሉ “እኩይ” ላይ ተቀፅሎ “እም” የሚለው አገባብ (ምዕላድ) የሚያርፈው እርሱ ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በራሱ የአረባብ ሥርዓት እየረባ መደብን፣ ቁጥርን፣ ጾታን ወዘተ መግለጽ ይችላል፡፡ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ቅፅል በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡

የቃል ክፍሎች

በማንኛውም ቋንቋ ቃላት ምድብ ( ክፍል) አላቸው፡፡ የቃላት አከፋፈል እንደየቋንቋው የተለያየ ነው፡፡  በግእዝ ቋንቋ ውስጥ የሚገኙት ቃላት በአምስት ይከፈላሉ እነሱም፡- ስም፣ ቅፅል፣ ግስ፣ ተውሳከ ግስ፣ አገባብ ናቸው፡፡ በእያንዳንዳቸው የቃል ክፍሎች በርካታ ክፍሎች አሉ፡፡ የቃል ክፍሎችን በተናጠል ስናይ የምንመለከታቸው ይሆናል፡፡ ከላይ በጠቀስነው ምንባብ ውስጥ የዘረዘርናቸውን ቃላት በቃላት ክፍል እየዘረዘርን እንመልከታቸው፡፡

ስም፡- አቡነ፣መንግሥትከ፣ ሰማይ፣ ምድር፣ ሲሣይ፣ አበሳ፣ ጌጋይ፣ ወዘተ

ቅፅል፡- እኩይ፣ መንሱት፣ ይእቲ፣ ኵሉ፣ ወዘተ

ግስ፡- ይትቀደስ፣ ትምጻእ፣ ይኩን፣ ሀበነ፣ ኅድግ፣ ንኅድግ፣ ኢታብአነ፣ ወዘተ

ተውሳከ ግስ፡- ዮም፣ ዓለም፣ ኵሉ

አገባብ፡- እስመ፣ ዘ፣ ወ፣ በ፣ ከመ፣ ከማሁ፣ አላ፣ እም፣ ለ፣ ወዘተ

በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አቡነ ዘበሰማያት አምስት መሠታዊ ጉዳዮችን ይይዛል፡፡ እነሱም ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ተአምኖ ሐጣውዕ (ትሕትና) እና ጸሎት(ልመና) ናቸው፡፡ ይህን ጥልቅና ዘርፈ ብዙ ጽንሰ ሐሳብ ማስተላለፍ የቻልነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር የበቃነው በቃል አማካኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ለመግባባት የተዋቀሩ ቃላት፣ የሰዋስው ሥርዓት፣ የቋንቋ ጉዳይ ያስፈልገዋል ማለት አይደለም፡፡ እንደኛ ግን እርስ በእርስ ሰዎች እንድንግባባ ቋንቋ ያስፈልገናል፡፡ ከሰዎች ጋር በመናደርገው ተግባቦት ቋንቋ እንዳስፈለገን ሁሉ በመዋዕለ ስብከቱም እንደኛ ሰው በሆነበት ጊዜ በቋንቋ ከሰው ጋር ተግባብቷል፡፡ ዛሬም በዚህ አንጻር ሐሳባችንን በቃላት አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር እናቀርባለን፡፡ ስለዚህ እርስ በእርሳችን ለመግባባት፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ታዛዥነት፣ አምልኮታችንን ወዘተ ለሰዎች ለመግለጽ ቋንቋ መሠረት ነው፡፡የቋንቋ መሠረት ደግሞ ቃል ነውና ቃል ማለት ልናስተላልፈው የፈለግነውን ሐሳብ የሚወክልልን የሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው በሚል እናጠቃልላለን፡፡

የቃልን ምንነትና የቃላት ክፍሎችን በአጭሩ እንዲህ ከተመለከትን በእያንድዳንዱ የቃላት ክፍሎች ውስጥ የሚኖረውን ክፍፍል (ዓይነት)፣ የቃላቱን ሙያ፣ መዋቅራዊ ሥርዓት ወይም የአገባብ ሥርዓታቸውን በሰፊው በዝርዝር የምንመለከት ይሆናል እስከዚያው ቸር እንሰንብት፤ አሜን፡፡

በአተ ክረምት

 ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ስሌት መሠረት ወቅቶች በአራት ይከፈላሉ፡፡ እነዚህም፡- ዘመነ መጸው (መከር)፣ ዘመነ ሐጋይ (በጋ)፣ ዘመነ ጸደይ (በልግ) እና ዘመነ ክረምት ይባላሉ፡፡ ከአራቱ ወቅቶች መካከልም ከሰኔ ፳፮ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ (አሁን የምንገኝበት ወቅት) ዘመነ ክረምት ተብሎ ይጠራል፡፡ ቃሉን ለማብራራት ያኽል፣ ‹ክረምት› የሚለው ቃል ‹ከረመ – ከረመ› ካለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም የዝናም፣ የአዝርዕት፣ የአረም ጊዜ፣ እንደዚሁም ዕፀዋት፣ አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው የሚያድጉበት፣ ምድር በአረንጓዴ ዕፀዋትና በልምላሜ የምታሸበርቅበት ወቅት ማለት ነው፡፡ ‹ዘመነ ክረምት› ማለትም ይኼንኑ ወቅት የሚያስገነዝብ ትርጉም አለው፡፡

በአተ ክረምት (ዘርዕ፣ ደመና)

ከሰኔ ፳፮ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው የመጀመሪያው የክረምት ክፍለ ጊዜ ‹በአተ ክረምት› ወይም ‹ዘርዕ፣ ደመና› ይባላል፡፡ ‹በአተ ክረምት› ማለት ‹የክረምት መግቢያ፣ መጀመሪያ› ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ስለ ክረምት መግባት፣ ስለ ዘርዕ፣ ስለ ደመና እና ስለ ዝናም የሚያዘክሩ መዝሙራትና ምንባባት ይዘመራሉ፣ ይነበባሉ፡፡ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፣ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ ነውና፡፡

ዘርዕ

ምድር ከሰማይ ዝናምን፣ ከምድርም ዘርን በምታገኝበት ወቅት ዘሩን አብቅላ ለፍሬ እንዲበቃ ታደርጋለች፡፡ በምድር የምንመሰል የሰው ልጆችም ከእግዚአብሔር ባገኘነው ጸጋ ተጠቅመን፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት እና ከመምህራነ ቤተ ክርስቲያን የምናገኘውን ቃለ እግዚአብሔር በተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባን ከምድር እንማራለን፡፡ ይህን ካደረግን ዋጋችን እጅግ የበዛ ይኾናል፣ ከዚህም አልፎ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንበቃለን፡፡ የተዘራብንን ዘር ለማብቀል ማለትም ቃሉን በተግባር ለማዋል ካልተጋን ግን በምድርም በሰማይም ይፈረድብናል፡፡ ‹‹ምድርም በእርስዋ የሚወርደውን ዝናብ ከጠጣች፣ ያን ጊዜ ስለ እርሱ ያረሱላትን መልካም ቡቃያ ታበቅላለች፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድም በረከትን ታገኛለች፡፡ እሾኽንና ኵርንችትን ብታወጣ ግን የተጣለች ናት፡፡ ለመርገምም የቀረበች ናት ፍጻሜዋም ለመቃጠል ይኾናል፣›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ገለጸው (ዕብ. ፮፥፯-፰)፡፡

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ፲፫፥፩-፳፫ እንደ ተገለጸው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስትና ሕይወትን ከዘርና ፍሬ ጋር በማመሳሰል አስተምሯል፡፡ ይኸውም አንድ ገበሬ ዘር ሲዘራ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ከመብቀሉ በፊት በወፎች እንደ ተበላ፣ በጭንጫ ላይ የተጣለውም ወዲያውኑ ቢበቅልም ነገር ግን ሥር መስድድ አልቻለምና፡፡ በፀሐይ ብርሃን እንደ ጠወለገ፤ በእሾኽ መካከል የወደቀው ደግሞ ሲበቅል በእሾኽ እንደ ታነቀ፣ ከሁሉም በተለየ መልኩ በመልካም መሬት ላይ የተጣለው ዘር ግን አድጎ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ ፍሬ እንደ ሰጠ የሚያስረዳ ነው፡፡

ይህም ምሳሌ አለው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተረጐመው በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ የማያስተውል (ልብ የማይል) ክርስቲያን ምሳሌ ነው፣ እንደዚህ ዓይነቱ ምእመን ሙሉ እምነት ስለማይኖረው በመከራው ጊዜ አጋንንት ድል ያደርጉታል፡፡ በጭንጫ ላይ የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበል፣ ነገር ግን ተግባራዊ የማያደርግ (የማይተገብር) የክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ ይህ ምእመንም በጠንካራ እምነት ላይ የጸና አይደለምና በሃይማኖቱ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ፈጥኖ ይክዳል፡፡ በእሾኽ መካከል የተዘራውም ቃሉን የሚሰማ ቢሰማም ግን በዚህ ዓለም ዐሳብና ባለ ጠግነት ተታሎ ቃሉን የማይተገብር ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡

በመልካም መሬት የተዘራው ደግሞ ቃሉን ሰምቶ ተግባር ላይ የሚያውል ክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምእመን በተማረው ትምህርት ጸንቶ ይኖራል፣ መልካም ሥራም ይሠራል፡፡ በመልካም መሬት የተዘራው ዘር ስለ አንዱ ፋንታ መቶ፣ ስድሳ፣ ሠላሳ እንደሚያፈራ ሁሉ በክርስቲያናዊ ግብር ጸንቶ የሚኖር ምእመንም ሥራውን በሦስት መንገድ ማለትም በወጣትነት፣ በማእከላዊነትና በፍጹምነት ደረጃ እንደሚፈጽም፣ ዋጋውንም በሥራው መጠን እንደሚያገኝ የሚያስረዳ ነው፡፡ በሌላ በኩል ባለ መቶ ፍሬ የሰማዕታት፣ ባለ ስድሳ የመነኮሳት፣ ባለ ሠላሳ በሕግ ተወስነው በዓለም የሚኖሩ ምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ በተመሳሳይ ምሥጢር ሁሉም የፍሬ መጠን በሁሉም ጾታ ምእመናን ሕይወት ውስጥ እንደሚገኝ የትርጓሜ ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ስለዚህም በሰማዕትነትም፣ በምንኵስናም፣ በዓለማዊ ሕይወትም ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን መልካም ግብራቸው እጅግ የበዛ ከሆነ በባለ መቶ ፍሬ፣ መካከለኛ ከሆነ በባለ ስድሳ፣ ከዚህ ዝቅ ያለ ከሆነ ደግሞ በባለ ሠላሳ ፍሬ ይመሰላል፡፡ (ትርጓሜ ወንጌለ ማቴዎስ፣ ማቴ. ፲፫፥፩-፳፫)፡፡

ደመና

እግዚአብሔር አምላካችን የውቅያኖስ እና የሐኖስ ድንበር ይሆን ዘንድ በውኃ መካከል ጠፈርን ፈጥሮ ከጠፈር በታች (በዚህ ዓለም) ያለው ውኃ በአንድ ቦታ እንዲወሰን አድርጎታል፡፡ ከዚያም ከምድር እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ የነበረውን ውኃ ከሦስት ከፍሎ ሢሶውን አርግቶ ጠፈር ብሎ ሰይሞታል፡፡ ከጠፈር በላይ ያለውን ሢሶውን የውኃ ክፍል ሐኖስ ብሎታል፡፡ ሢሶውንም ይህንን ዓለም ከሰባት ከፍሎ ሰባተኛውን ዕጣ አጐድጕዶ በዚያ ወስኖ ስሙን ውቅያኖስ ብሎ ጠርቶታል፡፡ የብሱን ክፍል ደግሞ ምድር ብሎ ሰይሞታል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከደረቅ ምድር ደረቅ ጢስን፣ ከርጥብ ባሕር ርጥብ ጢስን አስወጥቶ እንደ ጉበት በለመለመች ምድር ላይ ደመናን አስገኝቷል (ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት፣ መዝ. ፻፴፬፥፯)፡፡

ደመና፣ ዝናምን የሚሸከም የማይጨበጥ፣ የማይዳሰስ ጢስ መሰል ፍጥረት ነው፡፡ በትነት አማካይነት፣ በደመና ተሸካሚነት ከውቅያኖሶች እና ከወንዞች እየተቀዳ ወደ ሰማይ ተወስዶ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ምድር የሚጥለው ውኃ ዝናም ይባላል፡፡ ይኸውም በእግዚአብሔር ጥበብ በደመና ወንፊትነት ተጣርቶ ለፍጡራን በሚመችና በሚጠቅም መጠን በሥርዓት ይወርዳል፡፡ ‹‹ያጸንዖ በፍኖተ በድው ከመ ይዝንም ብሔረ ኀበ አልቦ ሰብእ ወኢይነብሮ ዕጓለ እመሕያ፣ ዝናሙን ሰው በሌለበት በምድረ በዳ ያዘንመዋል፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በቅዳሴው፡፡ ይህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር በረዶውን በምድረ በዳ አፍስሶ የጠራውን ውኃ ሰው ወዳለበት እንዲዘንም ማድረጉን የሚያስረዳ መልእክት የያዘ ሲሆን፣ ምሥጢሩም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንበለ ዘርዐ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) በልዩ ጥበቡ ተፀንሶ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱንና በተዋሐደው ሥጋ በምድር ተመላልሶ ወንጌልን ማስተማሩን፣እንደዚሁም ‹‹ሑሩ ወመሀሩ፤ ሒዱና አስተምሩ›› ብሎ ቅዱሳን ሐዋርያትን በመላው ዓለም ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ማሰማራቱን ያመለክታል (ትርጓሜ ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ ፪፥፭-፮)፡፡

ዘመነ ክረምት ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት፤ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን (ምግብን) ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይ እና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት የውኃ ባሕርይ ይሠለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን ውኃ በብሩህነቱ ከእሳት፣ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህን ምሥጢር ከሕይወታችን ጋር አያይዘን ስንመለከተው ዘመነ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፡፡ በክረምት ወቅት ገበሬው ብርዱንና ዝናሙን ሳይሳቀቅ ለሥራ ይሰማራል፣ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሣል፡፡ ይህም ምእመናን በሰማያዊው ዓለም የምናገኘውን ተድላና ደስታ በማሰብ በምድር ቆይታችን ወቅት የሚደርስብንን ልዩ ልዩ መከራ በትዕግሥት ማሳለፍ እንደሚገባን ያስገነዝባል፡፡

በዘመነ ክረምት አዝርዕቱ በስብሰው ከበቀሉ፣ ካበቡና ካፈሩ በኋላ የሚጠቅሙት በሪቅ፣ በጎተራ እንደሚሰበሰቡ፣ እንክርዳዶቹ ደግሞ በእሳት እንደሚቃጠሉ ሁሉ እኛም ተወልደን፣ ተጠምቀን፤አድገን፣ ዘራችንን ተክተን እንደምንኖር፣ ዕድሜያችን ሲያበቃም እንደምንሞት፣ ሞተንም እንደምንነሣና መልካም ሥራ ከሠራን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደምንገባ፣ በኀጢአት ከኖርን ደግሞ በገሃነመ እሳት እንደምንጣል የምንማርበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ሰይጣን በሚያዘንበው የኀጢአት ማዕበል እንዳንወሰድና በኋላም በጥልቁ የእሳት ባሕር እንዳንጣል ዅላችንም ቅዱሳት መጻሕፍትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጁልንን የቃለ እግዚአብሔር ዘር በእርሻ ልቡናችን በመዝራት (በመጻፍ) እንደየዓቅማችን አብበን፣ ያማረ ፍሬ አፍርተን መንግሥቱን ለመውረስ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወላጆች ልጆቻችንን በመንፈሳዊ መንገድ እንዴት እናስተምር?

ዲያቆን ዮሴፍ ከተማ

ወላጆች ለወለድናቸው ልጆች ትልቅ አምላካዊ አደራ አለብን፡፡እግዚአብሔርም ልጅን ያህል ትልቅና የደስታ ምንጭ የሆነ ስጦታ ሲሰጠን ደግሞ ከትልቅ ኃላፊነት ጋር ነው፡፡ ከኃላፊነታችን  ትልቁ ለልጅ፡- ሃይማኖትን፤ ምግባርና ትሩፋትን በማስተማር ለእግዚአብሔር መንግሥት እንዲበቃ አድርጎ በፈሪሀ እግዚአብሔር ማሳደግ ነው፡፡ «ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፤ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም» እንዲል ምሳ. ፳፪፥፮፡፡

በዘመናችን መንፈሳዊ እሴቶች ተሸርሽረው በአብዛኞቹ ወላጆች «ወልጄ አሳድጌ፤ ወግ ማዕረግ አሳይቼ» የሚሉት የሥጋዊውን ፍላጎት ብቻ በመያዝ ነው፡፡ ዋናው የልጆችም ጥቅም፤ የወላጆችም ኃላፊነት ልጆቻችንን ለክብረ መንግሥተ ሰማያት ማብቃት ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ወላጅ «ልጄን ለሲኦል ነው ለመንግሥተ ሰማያት ነው የማሳድገው?» ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡

ማንም ለልጁ ክፉን አይመኝምና ሁሉም ሰው እርሱም ልጆቹም ለክብረ መንግሥቱ እንዲበቁ ይሻል፤ ስለዚህ ልጆች ዛሬ በጥሩ መሠረት ላይ መታነጽ ይኖርባቸዋል፡፡ ልጆች በልጅነታቸው ያልተዘራባቸውን በሕይወታቸው አያፈሩም፡፡አንዳንድ ወላጆች ለዓለማዊ ትምህርት ብቻ ቅድሚያ በመስጠት፤ መንፈሳዊውን ወደ ጎን ይተዋሉ፡፡ መንፈሳዊው ሕይወት ካደጉ በኋላ የሚደርስ ይመስላቸዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ወላጆች እኛ ራሳችን የመንፈሳዊ ሕይወት ግንዛቤ ስለሌለን አስፈላጊነቱም እምብዛም አይታየንም ወይንም በሰንበት ቀን ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እንገድበዋለን፤ ሁሌ የሚኖሩት ሕይወት መሆኑን አናውቅም፡፡ ይህ ግን ለዚህ ዘመን የልጅ አስተዳደግ አስቸጋሪ ነው፡፡ይህ ዘመን ልጆቻችንን ወስዶ ብኩን የሚያድርጋቸው ብዙ የሕይወት ወጥመድ የሞላበት ነው፡፡ ካደጉ በኋላ በልጅነት የሌላቸውን ለማምጣት ይቸግራል፡፡ «ተስፋ ገና ሳለች ልጅህን ገሥጽ፤ መሞቱንም አትሻ» ምሳ. ፲፱፥፲፰

ስለዚህ የልጆቻችን ዕድገት ሁለንተናዊ እንዲሆን ከዓለማዊ ትምህታቸው ባልተናነሰ ወይንም በበለጠ ለመንፈሳዊው ትምህርትና ሕይወታቸው ከፍተኛ ትኩረትና ጥረት ልንሰጥ ይገባል፡፡ «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል?» ማር. ፰፥፴፮፤ ልጆቻችን በአስኳላ (በሳይንስ) ትምህርት ውስጥ ብቻ ቢያልፉ ምዕራባዊ ይሆናሉ፡፡

ምን ማለት ነው?

ዓለማችን በፈጣን ለውጦች ውስጥ እየተጓዘች ነው፡፡ብዙዎች የነሱ ሐሳብ፤እምነት፤ባህልና ሥርዓት በዓለም ላይ እንዲንሰራፋና የዓለም ሕዝብ የነሱ ተከታይ እንዲሆን እየተጉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የምዕራቡ ዓለም በዚህ ረገድ ፊታውራሪ ነው፡፡ሉላዊነት ወይንም ግሎባላይዜሽን በመባል የሚታወቀው የዘመናችን ገዢ ርእዮት ምዕራባዊ ባህልን፤የአኗኗር ዘይቤን በዓለም ላይ ለማሥረጽ የተቀረጸ ነው፡፡የሀገራችን ሥርዓተ ትምህርት ከምዕራባውያን ሥልጣኔ የተቀዳ ነው፡፡

ለመሆኑ ምዕራባዊነት መገለጫውና ግቡ ምድነው?

ምዕራባዊነት በተለይ ልጆችና ታዳጊዎች በሰፊው ተደራሽ በሚሆኑባቸው ፊልም፤ዘፈን፤ የትምህርት ሥዓታችን ወዘተ. በሰፊው የሚሰብክ ሲሆን

፩. ከመንፈሳዊነት ይልቅ ቁሳዊነትን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ

፪. ቋሚ የሕይወት ዕሴት የሌለው እንደ ጊዜው የሚለዋወጥ ሰብእና፤ ዓለማዊነትን፤ ግብረ-ሰዶማዊነትን፤ ጾታ መቀየርን፤ የኮንትራት (በውል በተገደበ ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ) ትዳርን ወዘተ

፫. ሃይማኖት የለሽነትን ወይንም ፕሮቴስታንትነትን ግብ አድርጎ የሚሰራ ነው፡፡

ነገር ግን ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ይኸው ሕይወት ከፍ ያለና የሚያስቀና አስመስሎ በቁሳቁስ አጅቦ በማቅረብ የብዙ ወጣቶችን እና ታዳጊዎችን ቀልብ የሚማርክ ሆኗል፡፡ በዚህም አብዛኛው በተለይ የከተማው ወጣት ልቡ መማረኩ በአለባበሱ፤ በምኞቱና በአኗኗሩ ሁሉ የሚታይ ነው፡፡

ምዕራባውያኑ ይህን ዓይነቱን ሁኔታ ለመፍጠር የሚተጉት ለምንድነው?

ልብ በሉ! አንድ ማኅበረሰብ የእኛን አኗኗር የሚከተል ከሆነ ሌላው ሁሉ ቀርቶ ቢያንስ በዘላቂነት የእኛን ምርቶች ይጠቀማል፤ በየጊዜው የምናመጣውን አዳዲስ ነገር ይገዛል፡፡ ስለዚህ ዘላቂ የሆነ የገበያ ዕድል ባህላችንን በመሸጥ ብቻ እናገኛለን ማለት ነው፡፡ ይህ የምዕራባውያኑ አንዱ ግብ ሲሆን፤ በፖለቲካ፤ በሃይማኖትና በሌላም መስኮች የዓለም ቁንጮ ሆኖ የመምራትንና ለፈጠራዎቻቸው ሁሉ ተቀባይነትን ያስገኝላቸዋል ማለት ነው፡፡

ምን እናድርግ?

በመሠረቱ ልጆቻችን ላይ የተሠጠንን ኃላፊነት መወጣት የሚገባን ከምዕራባዊነት ልንታደጋቸው ብቻ አይደለም፡፡ ማንነታቸውን በትክክል አውቀው፤ በምድርም በሰማይም ተስፋ ያላቸው፤ ሥጋዊም መንፈሳዊም ዕድገትና ስኬት ያላቸው መሆን ይችሉ ዘንድ ነው፡፡

ክረምት

በተለይ ይህ ወቅት ሕፃናትና ታዳጊ ልጆች ብሎም ወጣቶቻች ከመደበኛው ትምህርት በአንጻሩም  ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በታች ይህን ጊዜያቸውን ሊያውሉበት ይገባል ብለን ያቀረብናቸው ምክረ-ሐሳቦችም በእርግጥ በክረምቱ ጊዜ የበለጠ ቢተገበሩም በበጋውም ቢሆን መዘንጋት የሌለባቸው ነገሮች ናቸው፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ልጆች በዚህ ክረምት የበለጠ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ማጎልበት ላይ በማተኮር፤ እግረ መንገዱን ደግሞ ለዘላቂው የክርስትና ሕይወታቸው ስንቅ የሚሆኑ እውቀትና ክህሎቶችን የሚያስጨብጧቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ እንደ ምሳሌም

፩. የአብነት ትምህርቶችን ቢከታተሉ

በየደብሩ የአብነትን ትምህርት ከጠቃሚ የአባቶች የሕይወት ምክሮችና ግብረ-ገብ ጋር ጨምረው የሚያስተምሩ ካህናት አሉ፡፡ ልጆች እነዚህን መማራቸው ለጸሎትና አጠቃላይ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ከመጥቀሙም ባሻገር በነገዋ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአገልግሎት ዕድል ፈንታ ይሰጣቸዋል፤ ይህም ቤተ ክርስቲያናችን ለምትመኘው በሁለት በኩል የተሳለ አገልጋይ ትልቅ መሠረት ነው፡፡ በአገልግሎት ውስጥ መኖር ደግሞ ለሌሎች ከመትረፍም ባሻገር ለራስ መጠበቅ የበለጠ ጠቃሚ ነው፡፡

፪. በሰንበት ትምህርት ቤቶች መርሐ ግብሮች ላይ ቢሳተፉ

እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ልጅ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል፡፡  በጋውንም ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤት ቤተ ክርስቲያን ሕፃናትን የምትታደግበት አንዱ መዋቅር ነው፡፡ በክረምት ደግሞ በርካታ በአማራጭ የተዘጋጁ መርሐ-ግብሮች ስላሉ ሕፃናት ብዙ ያተርፉባቸዋል፡፡

፫. መንፈሳዊ የዜማ መሣርያዎችን ቢማሩ

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት ቤቶችና በአንዳንድ ሰንበት ትምህት ቤቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዜማ መሣርያዎች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህም በገና፤ መሰንቆ፤ ከበሮና ዋሽንት ናቸው፡፡ ልጆች እነዚህን በዚህ ክረምት ቢማሩ እያደጉ በሄዱ ጊዜ ደግሞ የበለጠ ልምድ ስለሚሆናቸው ባለሙያ ይሆናሉ፡፡ይህም ለአገልግሎት ሕይወትም በር ይከፍትላቸዋል፡፡

፬. መንፈሳዊ ፊልሞችን፤መንፈሳዊ ታሪክና ትምህርት የያዙ የልጆች መጻሕፍትን፤ የሕፃናት መዝሙራትን ወዘተ. መመልከትና ማንበብ ቢችሉ የበለጠ ጠቃሚ ይሆንላቸዋል፡፡ በዚያውም እነዚህን ነገሮች ልምድ እንዲያደርጉ ስለሚረዳቸው ወላጆች ልጆቻቸው በእነዚህ መንገዶች ራሳቸውን በራሳቸው ስለሚያስተምሩ ብዙ ይረዳቸዋል፡፡

እነዚህን ቢያደርጉና በዘላቂነትም ገንዘብ ማድረግ ቢችሉ ለአጠቃላይ ሕይወታቸው ትልቅ ትርጉም ያለው ከመሆኑም ባሻገር ወላጆችም እግዚአብሔር የሚወዳቸውን በጎ ሥራዎች በማድረጋቸው ዋጋ ያገኙበታል፡፡

በመጨረሻም መዘንጋት የሌለበት ልጆች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጥሩ ሲሆኑ፤ በአስኳላ ትምህርታቸውም የበለጠ ብርቱዎች እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በታችኞቹ ደረጃዎች ሳይወሰን ዛሬ በየዩኒቨርሲቲው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማቶቻቸውን ለቤተ ክርስቲያን ሥጦታ የሚያበረክቱ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን መመልከት በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

 

ወጣትነትና ፈተናዎቹ

የወጣትነትን የዕድሜ ክልል በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምሮ መሠረት ከሃያ እስከ ዓርባ ዓመት ያለው ዕድሜ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ማለትም ከነፋስ፤ ከእሳት፤ ከውሃና፤ ከመሬት ሲሆን አምስተኛ ነፍስን ጨመሮ እነዚህ በአንድ ሰው የሕይወት ዘመን ላይ ሲንጸባረቁ ይኖራሉ፡፡ የሰው ልጅ በሚሞትበት ጊዜ አራቱ ባሕርያት ወደነበሩበት ጥንተ ህላዌ ይመለሳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሥጋ ይበሰብሳል ይፈርሳል፡፡ በትንሣኤ ዘጉባኤ ደግሞ አራቱም ባሕርያት ከነፍስ ጋር እንደገና  ተዋሕደው ይነሣሉ፡፡ አራቱን ባሕርያተ ሥጋ ረቂቃን ግዙፋን (ክቡዳን ቀሊላን) ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ የሚገርመው ክቡዳኑን ከላይ ቀሊላኑን ከታች አድርጎ ነው ያስቀመጣቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው ተጠባብቀው እንዲኖሩ አደረጋቸው ምክንያቱም ክቡዳኑ ከላይ ሆነው እንዲጠብቋቸው ነው ቀሊላኑ ግን ከላይ ቢሆኑ ኖሮ ሽቅብ ይሄዱ ነበር ክቡዳኑም ከታች ቢሆኑ ኖሮ ቁልቁል ሲሔዱ በኖሩ ነበር፡፡ ተሸካክመው የሚኖሩት ምሳሌነቱም አራቱ ባሕርያተ ሥጋ ተቻችለው እንደሚኖሩ እኛም ከኛ በላይ ያሉ እንዳሉ በማወቅ ተቻችለን እንድንኖር ነው፡፡ የመሬት መሠረቷ ጽናቷ ነፋስ ነው፡፡ የእኛም ከላይ ሥጋችን መሬት ነው፡፡ መሬትም በውኃ ላይ ናት ይህም ውሃው ደማችን ነው፡፡ የእኛም ሥጋችን በደማችን ነውና የሚጸናው የውሃዎች ሕይወት ነፋስ ነው ውሃው ንጹሕ አየር ከሌለው ይበከላል፡፡ አበው ከአፋፍ ላይ ነፋስ ከአፍ ላይ እስትንፋስ እንዲሉ የሰው ልጅም ሁሉ በዘመኑ ሲተነፍስ ይኖራልና፡፡ የሰው ልጅ የሰውነት ሙቀት ባሕርየ እሳት ለመኖሩም በቂ ማስረጃ ነው፡፡

ከሃያ እስከ አርባ ያለው የዕድሜ ክልል የእሳት ባሕርይ ጎልቶ የሚታይበት ነው፡፡ ይህም ዘመነ እሳት ወይም ምግበ እሳት ይባላል፡፡ ይህም ሰውን ወጣት የሚያሰኘው ዘመን ነው፡፡

በዚህ የወጣትነት ዘመናችን ጥሩና ታላቅ መሆን ካልቻልን የምናጣው ክብርን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ኃላፊነት ጭምር እናጣለን፡፡ እንደ ኤሳው ስንሆን እንደ ያዕቆብ ያለ ታናሽ ወንድምህ ብኵርናህን ይወስድና አንተ የእሱን እጅ ስታይ ትኖራለህ፡፡ እንዲሁም ታናናሾችህን የመቅጣትና የመገሠጽ መብት አይኖርህም፡፡ አላዋቂ ጎልማሳ ወጣቶችን መገሠጽ እንደማያምርበት ሁሉ አንተ ሕገ ወጥ ወጣት ሆነህ ታናናሾቼን ልቅጣ ልምከር ብትል ማንም አይሰማህም፡፡ ምክንያቱም (ማቴ. ፯፥፭) ላይ አንተ ግብዝ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፡፡ ከዚያ በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ ስለተባልን ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰው ልጅ ከልጅነት ወደ ወጣትነት በሚሸጋገርባቸው ወራትና ዓመታት አካላችን እንደሚደራጅና አእምሮአችን እንደሚዳብር ሁሉ ምኞታችንም በዓይነትና በመጠን እየሰፋና እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህ የወጣቶች ምኞት በአመዛኙ ከመንፈሳዊነት ጋር የሚቃረን ይሆናል፡፡ እንዲሁም በጎልማሶች ላይ የሚከሰተውን ምኞት አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ (በ፪ኛ ጢሞ. ፪፥፳፪) ላይ ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ ብሎናል፡፡ በእርግጥም በወጣትነት ዘመን የሚገኝ ምኞት እጅግ ክፉ ነው ወጣትነት የሚሠራበት ዘመን እንጂ ክፉ ምኞት የሚመኙበት ዘመን አይደለም፡፡

ወጣቶችና ጾሮቻቸው (ፈተናዎቻቸው)

ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ፩፥፲፬ ላይ «ሰው ራሱ በገዛ ምኞቱ ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል» በማለት እዳስተማረን፤ በወጣትነት ዘመን የሚገኝ ምኞት ከመጠን በላይ ወደ ጥፋት የሚስብ የሚጎትትና የሚያታልል ነው፡፡ በተለይ ሰው በገዛ ምኞቱ ሲሳብ በወጣትነት ዘመን ምንም አእምሮው የበሰለ ቢሆንም እንኳ ራሱን መግዛት ካልቻለ በብዙ ነገር ይፈተናል በዚህም ወጣቶች ከሚፈተኑባቸው መንገዶች መካከል ዝሙትና ትውዝፍት (የምዝር ጌጥ) መውደድ ነው፡፡ እንዲሁም የወጣቶች ልዩ ልዩ ጾር (ፈተና) ቢኖሩም እነዚህ ዐበይት ጾሮች የኃጢአት መንገድ ጠራጊ ይሆናሉ፡፡

መፍትሔዎች

  • ራስን መግዛት

ይህ ማለት ፍቃደ ሥጋን ለፍቃደ ነፍስ ስናስገዛ፤ በዚህም ሕገ እግዚአብሔርን ስንጠብቅ፤ ራሳችንን ሆነን በተማርነው መኖር ስንጀምር፤ ልማድ የሆነብንን ድርጊት አስወግደን በተቀመጠልን ትእዛዝ ስንኖር እና ሁለንተናችንን ለእግዚአብሔር ስናስገዛ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት (በመዝ. ፪፥፩) ላይ በፍርሀት በመንቀጥቀጥ ተገዙ ስላለን በመገዛት ውስጥም የማያቋርጥ ዘለዓለማዊ ደስታ እንዳለ አውቀን ራሳችንን መስለን መኖር እንችላለን፡፡ ስለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ (፩ኛ ጢ. ፫፥፭) ላይ ቤቱን ማስተዳደር የማይችል የእግዚአብሔርን ቤት ሊመራ እንደማይችል ሁሉ ሌሎችን ማስተዳደር የምንችለው ራሳችንን ስንገዛ፤ ስንገራና ስንቆጣጠር እንደሆነ ነግሮናል፡፡ እንዲሁም ኖኅን ስንመለከት (ዘፍ. ፮፥፩) ላይ ከነቤተሰቡ ራሱን ገዝቷል፡፡ ሌሎችን ለመናገርና ለመውቀስ መርከቧን በመሥራት፤ አራዊትን፤ እንስሳትንና አዕዋፍን ሁሉ መግዛት ችሏል፡፡ ራስን መግዛት ማለት ቤተ ክርስቲያን ገብተን እስክንወጣ፤ ትዳር እስክናገኝ፤ ሥራ እስክንይዝና እና የፈለግነው ነገር ሁሉ እስኪሳካልን ድረስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ራስን መግዛት ማለት መፍረድ ሲቻል አለመፍረድ፤ ማድረግ ሲቻል አለማድረግ ልክ እንደ ዮሴፍ (ዘፍ. ፴፱፥፩) ጀምሮ ሁሉ ሲቻል መተው እንዲሁም ልክ ይሁን አይሁን በነገሮቻችን ሁሉ ራሳችንን ስንገዛ በአጠቃላይ ከአላስፈላጊ የሥጋ ጠባይዓት ሁሉ መራቅ ስንችል ራሳችንን ገዝተናል ማለት እንችላለን፡፡

  • ራስን ማወቅ

ለራሳችን ያለንን አመለካከትና ጠባይ በአጠቃላይ ከሌሎች ሰዎች የሚለየንንና የሚያመሳስለንን ማንነት በመረዳት በዓላማ መኖር ስንችል ራሳችን ማወቅ ቻልን ማለት ነው፡፡ ይህም ሰው ጠንካራና ደካማ ጎኑን ማወቅ ከቻለ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ሕይወት አዎንታዊ አስተዋጽዖ ለማበርከትና ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ የሚያስችለውን እውቀት ያገኛል፡፡ ሙሴ (በዘፀ. ፬፥፲) ላይ ጌታ ሆይ እኔ አፌ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የኮነ ሰው ነኝ ብሎ ነው የተናገረው፡፡ ሆኖም ሙሴ በውስጡ ያለውን ጠንካራ ጎን አልተመለከተም፡፡ ራሱን የሚያውቅ ሰው ለራሱ ሕይወት ኃፊነት ይወስዳል ሌላ ሰው እንዲንከባከበው አይጠይቅም፡፡ በጉብዝናው ወራት ገደል አለ ከተባለ ይሰማል፤ ገደሉ እንደሚጎዳው ስለሚያውቅ፤ ሕይወቱን ለአደጋ አያጋልጥም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ (፪ኛ ጴጥ. ፩፥፭-፮) ላይ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፤ በበጎነትም እውቀትን፤በእውቀትም ራስን መግዛት፤ ራስን በመግዛትም መጽናትን በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰልን ነግሮናልና፡፡ ስለዚህ ይህን በማድረግ ለሕይወታችን ኃላፊነትን እንወስዳለን፡፡

ራሱን የሚያውቅ ሰው ሰብእናውን ያከብራል፤ ለምን ዓላማ እንደተፈጠረ በመረዳት ሰብእናውን ጠብቆ በደስታ ይኖራል፤ በራሱም ይተማመናል፡፡ የሚያውቀውን በአግባቡ ይናገራል፤የማያውቀውን ይጠይቃል፤ ድክመቱን ሲነግሩት በአዎንታዊ መንገድ ይቀበላል፤ ማንነቱን በቦታና በጊዜ ራሱን አይለዋውጥም የጸና ግንብ ነው፤ በዐለት ላይ ተመሥርቷልና፡፡ ከሐሜት ይርቃል፤ በግልጽ መወያትን ያዘወትራል፤ ለውድቀቱም ራሱን ተጠያቂ ያደርጋል፤ ሌሎቹን ተጠያቂ አያደርግም፤ ለውድቀት በቀላሉ እጁን አይሰጥም የሚጓዝበትን ያውቃልና፡፡ ካለፈው የወጣትነት ሕይወቱ ልምድ በመውሰድ አሁን ያለበትን ሁኔታ በመረዳት ሥጋዊና መንፈሳዊ ሕይወቱ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል አስቀድሞ ይዘጋጃል፡፡ ይህም የዛሬ ማንነቱ ለነገ ዘለዓለማዊ ሕይወቱ መሠረት መሆኑን በመረዳት ጠንክሮ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ይተጋል፡፡ በመጨረሻም ራሱን የሚያውቅ ወጣት ለመንፈሳዊ ሕይወቱ መሳካት አስፈላጊውን መሥዋዕትነት ይከፍላል፡፡ ራሱን ያላወቀና ያልገዛ ወጣት ዓላማውን ይስታል፤ ለራሱም ለሌሎችም መሆን አይችልም፡፡

ስለዚህ በወጣትነት ዘመናችን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያቀርበንን እንጂ የሚያርቀንን ነገር እንድንሠራ አይጠበቅብንም፡፡ እኛ ራሳችንን አድነን ሌሎችን በማዳን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት ይጠበቅብናል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከሰኔ ፩-፲፭ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም

ክርስቲያናዊ ሕይወት

ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ

በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ መልካም ሥራ ሁልጊዜ ይኖራል፤መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ   በትምህርተ ወንጌል እንዳስተማረን  ድኅነትን የምናገኝው በሕገ እግዚአብሔር ጸንተን ስንኖር እንደሆነ ነግሮናል። የሰው ሕይወቱ የጸጋ ነው፤ በፈቃዱ በሁለት ሞት ነፍሱን/ሕይወቱን/ ይነጠቃል፡፡ የመጀመሪያው ሞት የማይቀር ሲሆን የሁለተኛው ሞት ግን በሕገ እግዚአብሔር ለልደተ ነፍሳት የተሰጠ ነው፤ ራዕ. (፪፥፲፩)፤ ሕያው የሆነ ሰው እንጂ ሕይወት የሆነ ሰው የለምና፡፡

ስለሆነም ለዘለዓለም በሕይወት ለመኖር ይቻለን ዘንድ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በቆየበት ጊዜ ያደረገውን ተአምር፤ ያስተማረውን ወንጌልና  ለእኛ የገለጸልንን ፍቅር መሠረት አድርገን መመራት ይጠበቅብናል። ይህንንም በተግባር ለመፈጸም የሚከተሉትን ምግባሮች ማከናወን አለብን፡፡

፩.አገልግሎት

ከሁሉም አስቀድሞ የሰው ልጅ ዕለት ዕለት ፈጣሪውን ሊያመሰግን ይገባል፤ ይህም መጸለይ፤መጾም፤ማስቀደስና መዘመር ይገባዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ነዳያንን ማብላትና ማጠጣት በጉልበትና በሙያ አድባራትን ማሰራት ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ ሲሆን አሁን አሁን ግን የምንመለከተው እንደዚህ አይደለም፡፡ የዛሬ ፲ ዓመት ሰንበት ተማሪ የነበረው ልጅ ከዓመት በኋላ የመድረክ ዘፋኝ ይሆናል፤ የዛሬ ፭ ዓመት ሰንበት ትምህርት ቤት ድራማ ይሰራ የነበረው ሰው በኋላ ተለውጦ ሌላ ታሪክ ውስጥ ይገባል፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት ሰብሳቢ፤ ጸሓፊና አባል የነበረው፤ ሚስት ሲያገባ ያንን ሁሉ እርግፍ አድርጎ ይተወዋል፤ ትዳር እኮ የአገልግሎት ጡረታ አይደለም፤ አንዴ ካገቡ አይመለሱም፡፡

ሰንበት ተማሪ ሆኖ ቤተክርስቲያንን እያገለገለ እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ዘማሪ፤ ካህን፤ ዲያቆን ወይም ሰባኪ ሆኖ ገዳማትን እያሰራ፤ ነዳያንን እያበላ፤ ጉባኤ እያዘጋጀ፤ ጽዋ ማኅበራትን እየመራና ወዲህ ወዲያ ሳይል፤ ታመምኩ፤ ተቸገርኩ፤ ምስጋና ቢስ ነኝ፤ እጄን በቆረጠው ሳይል የሚኖር ማን ነው? አንዳንዶች ደከምን ብለው አገልግሎትን  የሚተው አሉ፡፡ ታማን ብለን የምንተውም አለን፤ ይህቺን ካልታገስን ታዲያ ስለ ዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ለምን እናወራለን? እስከ መጨረሻው የትኛው ሰው ነው የሚጸናው? በክርስቲያናዊ ሕይወት እስከ መጨረሻዋ ዕለት መጽናት ያስፍልጋል፡፡

.ጊዜን ማክበር

ጊዜ ከእግዚአብሔር የተሰጠን ስጦታ ነው፤ እናም በአግባቡ ልንጠቀምበት ያስፈልጋል፡፡ ጉባኤ ላይ በመገኘት፤ ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ በማገልገል፤ ድሆችን በመጎብኘት፤ ሕመምተኞችን በመጠየቅ፤ ገዳማትንና አድባራትን ለማሰራት በመድከም፤ መምህራኑ ሲያስተምሩና መዘምራኑ ሲዘምሩ በማገልገል ጊዜን ማክበር ያስፈልጋል፡፡ በማቴዎስ ወንጌል  (፳፭፥፴፬-፴፮) ላይ እንደተገለጸው «እናንተ የአባቴ ቡሩካን፤ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ኑ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ተጠምቼም አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳም ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፡፡ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜም ጎብኝታችሁኛልና፤ ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ  ጠይቃችሁኛልና» ይለናል።

መጠቀም ያለብን ትርፍ ጊዜያችንን አይደለም፤ ያለንን ጊዜ መስጠትና ሙሉ ጊዜን መስጠት ይለያያሉ፤ በወንጌል እንደተጠቀሰው አንድ ሰው ከሞላው ከኪሱ አፈሰና ሰጠ፤ አንዲት  ምስኪን መበለት ደግሞ ሁለት ሳንቲም ነበራትና እሱን ሰጠች፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነዚህ ሰዎች ሁሉ ይህቺ ጸደቀች አለ፡፡ በሉቃስ ወንጌል (፳፩፥፫-፬) ላይ እንደተናገረው «እውነት እላችኋለሁ፥ይህቺ ደሃ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብዝታ ለእግዚአብሔር መባ አገባች፡፡ እነዚህ ሁሉ ከተረፋቸው ለእግዚአብሔር መባ አግብተዋና፤ ይህች ግን ከድህነቷ ያላትን ጥሪቷን ሁሉ አገባች»፡፡ካለን እንድንሰጥ ነው እንጂ ሲተርፈን፤ ሥራ ሠርተን፤ በልተን፤ ጠጥተን፤ተዝናንተን ስንጨርስ መጨረሻ ላይ የት ልሂድ ብለን ቤተክርስቲያን የምንሄድ ከሆነ ይህ ለጊዜ ዋጋ መስጠት አይደለም፡፡ በጊዜያችን ተጨማሪ ልንሰራበት የምንችለውንና ገንዘብ የምናገኝበትን፤ ሰው ቤት ሄደን ጥዑም ምግብ ተመግበን የምንጠጣበትን ጊዜ ሰውተን፤ እንደ አስፈላጊነቱ ስንሰጥ ለጊዜ መሥዋዕት አደረግን ይባላል፤ሲተርፍ መስጠት ዋጋው ትንሽ መሆኑን ወንጌልም ነግሮናልና፡፡

፫. በሃይማኖት መጽናት

በዮሐንስ ራእይ ፲፪፥፲፮-፷ እንደተጠቀሰው ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስ ምስክር ያላቸውን ከዘሯ የቀሩትን ሊወጋ ሄደ ይላል፡፡ ከዘሯ የቀረነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት ያለንን ሊዋጋ ከተነሣው ዘንዶ ጋር ታግሎ ሃይማኖትን መጠበቅ ተገቢ ነው፤ በዚህ ዘመን ሃይማኖት ጸንቶ ሃይማኖትን መጠበቅና ከመናፍቃን ጋር መዋጋት የክርስቲያን ኃላፊነት ነው፤ ይሁዳ (፩፥፫) «ለቅዱሳን የተሰጠችውንም ሃይማኖት ትጋደሉላት ዘንድ አማልዳችኋለሁ» ይላል።

ስለ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መጋደል ክርስቲያናዊ ምግባር ነው፤ ብዙዎቹ ዛሬ በገንዘብና ከንቱ በሆነ ነገር ይታለላሉ፤ ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው «ለዚህ ዓለም ስሕተት፥ በክርስቶስ ሕግ ያይደለ፥ በሰው ሠራሽ ሥራዐት ለከንቱ የሚያታልሉ ሰዎች በነገር ማራቀቅ እንዳያታልሉአችሁ፥ተጠንቀቁ» (ቈላ. ፪፥፰)፡፡ በሰይጣን በመታለል ሃይማኖታቸውን የሚለውጡ አሉ፤ ጌታችን በማቴ. (፳፬፥፲፫) ላይ «እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል» ብሏል፡፡

፬.እራሳችንን ከፍትወት መጠበቅ

 ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በዚህ ዘመን ራሳችን ከዚህ ዓለም ፍትወት መጠበቅ  እንዳለብን አሳስበለዋል፡፡ አሁንኮ እስከ ጋብቻ ድረስ በድንግልና መጽናት ከባድ ሆኖብናል፤ የ «መ» ሕጎች እየተባለ በትምህርት ቤቱ ሁሉ መከራ የሚበላው ይህን ሕግ እየረሳን ነው፡፡ ልክ የዚህን ዓለም ፍትወት መቻል በእሳት ውስጥ ማለፍ እንደሆነ፤ ፍትወት ራሱን የቻለ እሳት ነው፤ እሳት እንኳን የቀረበውን የራቀውን ይጠራል፡፡ አባቶቻችን «እሳት ይጠራል»  ይላሉ፤ እኛ የምንኖረው በዓለም ነው፡፡ ስለዚህ ለምን በኅሊናችን የፍትወት ስሜት መጣ? ለምን በዙሪያችን ኃጢአት ኖረ? ማለት አንችልም፤ ግን ወንዙን አቋርጠን ማለፍ እንችላለን፤  ራስን በንጽሕና መጠበቅም አለብን፡፡ ወንድና ሴት ራሳቸውን ከዝሙት ስሜት ጠብቀው ሲኖሩ፤ በቤተክርስቲያን በተክሊል ሲጋቡ አክሊል ይጫንላቸዋል፤ ቤተ ክርስቲያን አክሊል ላደረገችለት ሰው ደግሞ እግዚአብሔር እጥፍ ዋጋን እንደሚከፍል ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ተጽፏል፡፡ እነዚህ ሰዎች እድል ወይም ምድራዊ ጥቅም ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም፤ ነገር ግን ምድራዊ ፍላጎታቸውን በመግታት ከራሳቸው፤ ከጓደኞቻቸውና ከአካባቢያቸው ጋር በመታገል ለነፍሳቸው መሥዋዕት ለመክፈል ስለሚሹ ነው፡፡

፭. በትዳር መጽናት

 በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ አንድ ወንድ በአንዲት ሴት፤ አንዲት ሴት በአንድ ወንድ ጸንተው ይኖራሉ፡፡ ባልና ሚስት በመቻቻል በሰላም መኖር ከቻሉ፤ ሰው የራሱን፤ የአጋሩንና የልጆቹን ጠባይ ችሎ በትዕግሥት ከኖረ፤ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎም፤ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን  እግዚአብሔርን የሚያገለግል ከሆነ ክርስቲያን ይባላል፡፡ በምንኩስና ሳይወሰኑ ወይም በትዳር አንድ ሳይሆኑ እንዲሁ የሚኖሩ ሰዎች ክርስቲያናዊ ሕይወትን የማይሹ ሰዎች ናቸው፤ ልክ በዘመነ ሰማዕታት ጊዜ እንደነበሩ ለጊዜው ክደናል እንደሚሉት አይነት ናቸው፡፡ ፶ እና ፷ ዓመት በትዳር እየኖሩ የብር፤ የወርቅ፤ የአልማዝና ኢዩቤልዩ የሚያከብሩ ሰዎች ተመችቷቸው እንዳይመስለን፤ ብዙ የችግር ጊዜን አሳልፈው ሊሆን ይችላል፤ እግሬን በሰበረው፤ ምላሴን በቆረጠው፤ አይኔን በሰወረው፤ ብር ብዬ በጠፋው ያሉበት ጊዜም ይኖራል፤ ግን ያን ሁሉ አልፎ መጽናት ያስፈልጋል፡፡

በትዳር ያላችሁ እስከመጨረሻው እንድትጸኑ፤ንጽሕናችሁን ጠብቃችሁ በመዘምርነት የምታገለግሉ፤ በስብከት፤ ለአድባራትና ገዳማት ያላችሁን እየመጸወታችሁ ከቁርሳችሁ ቀንሳችሁ፤ ሁለት ጫማ ካላችሁ አንድ ጫማ፤ ሁለት ልብስ ካላችሁ አንዱን እየለበሳችሁ፤ እኛ ይቅርብን፤ አባቶቻችን ተርበው ከተማ ለከተማ ሲንከራተቱ አንይ ብላችሁ የምታገለግሉ፤ የምታስታርቁ አባቶች፤ የጠፉትን ፈልጋችሁ የምታመጡ፤ መናፍቃንን ተከራክራችሁ የምታሳምኑ፤ አሕዛብን ወደ ጥምቀት የምታመጡ ሰዎች ሁሉ እስከ መጨረሻው ጸንታችሁ፤ ጸንተን፤ ኑ «የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን ርስት ውረሱ» እንድንባል የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፤አሜን፡፡