ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት አንደበት – ካለፈው የቀጠለ

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

“ሕማምን፣ ሞትን ገንዘብ አደረገ፤ በሥጋው የሞተው ሞትም የእኛን ባሕርይ በመዋሐዱ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፤ ሞት ሰው የመኾን ሥራ ነውና፡፡ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመኾን ሥራ ነውና፤ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን /ሞትንና ትንሣኤን/ እናውቃለን፤” (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፴፭)፡፡

“በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደ ኾነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፡፡ ይህ ለመለኮት አይነገርም፤ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፤” (ዝኒ ከማሁ ፸፱፥፱)፡፡

“የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን (ኃጢአትን) ሻረ፡፡ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ (ፍዳ መርገምን አጠፋ)፡፡ ሲኦልን በዘበዘ፡፡ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፡፡ የምሕረትን በር ከፈተ፤ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለዂሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚኾን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፤” (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፫፥፮)፡፡

“ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ እንደ ተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደ ኾነ፤ መድኀኒታችን በሚኾን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደ ሰጠን እናምናለን፡፡ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ዂሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ዂሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከኾነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ትንሣኤም ሐሰት ከኾነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፡፡ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደ መኾኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደ መኾኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከሰው መካከል ባልተደመሰሰም ነበር፤” (ቅዱስ ሳዊሮስ፣ ሃይ. አበ. ፹፬፥፲፰-፳)፡፡

“ፈጣሪያችን ክርስቶስ ለጌትነቱ እንደሚገባ ሥጋ መለወጥ የሌለበት እስኪኾን ድረስ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤ ሙስና መቃብርን አጥፍቷልና፡፡ በሥጋ በተቀበላቸው በሚያድኑ በእነዚህ ሕማማት ከጽኑ ሞት፣ ከዲያብሎስም ሥልጣን ያድነን ዘንድ ወደ ቀደመ ቦታችንም ያገባን ዘንድ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ፣ ሃይ. አበ. ፺፥፴፬)፡፡

“ይታመም ዘንድ በተገባው በሥጋው፣ ነውር የሌለበትን ሕማም በፈቃዱ በእውነት ተቀበለ እንጂ በምትሐት እንዳልታመመ እናገራለሁ፡፡ እንደ ሕማሙ ሞትንም በመስቀል ላይ ተቀበለ፡፡ ለአምላክነቱ በሚገባ፣ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤውም የጌትነቱን ሥልጣን ገለጠ፡፡ ሥጋውንም የማይሞት አደረገ፡፡ ከኃጢአት በራቀ በንጹሕ ማኅፀን በተዋሐደው ጊዜ ለመለኮት ገንዘብ ስለኾነ በሥራው ዂሉ አይለወጥም፤” (ቅዱስ ቴዎዶስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፪፥፲፭)፡፡

“ሕማም የማይስማማው እርሱ በሥጋ ሞትን ታገሠ፤ ብረት ወደ እሳት በገባ ጊዜ ዂለንተናው እሳት እንደ ኾነ እስኪታሰብ ድረስ በእሳት ዋዕይ እንዲግል፤ በመዶሻ በተመታ ጊዜ በመስፍሕ (መቀጥቀጫ) ላይ እንዲሳብ (እንዲቀጠቀጥ)፤ እሳትም ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሳለ ፈጽሞ እርሱ እንዳይመታ፤ ከብረቱም እንዳይለይ ግን የመዶሻ ኃይል ሳያገኘው እንዲመታ፤ ለመዶሻ እንዲሰጥ፤ የሚያድን የጌታ ሕማም እንዲህ እንደ ኾነ ዕወቅ፡፡

በዚህ ትንሽ ምሳሌ በእሳትና በብረት ተዋሕዶ ምልክትነት ፍጹም ተዋሕዶን እንወቅ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ይህ መከራና ሕማምን የሚቀበል ሥጋን ተዋሕዶ በሞተ ጊዜም ከሦስት ቀን በኋላ አምላክነቱ በተገለጠበት ትንሣኤው ሞትን አጠፋው፡፡ ሥጋው በመቃብር በመቀበሩም በመቃብር ውስጥ የነበረ መፍረስን መበስበስን አጠፋልን፤ ከሥሩም ነቀለው፡፡ ይህንም የሚያስረዳ ከቅዱሳን ወገን ብዙ ሰዎች ተነሡ፤” (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፮፥፶-፶፪)፡፡

“ዳግመኛ እርሱ እንደ ሞተ፣ በሦስተኛውም ቀን እንደ ተነሣ፣ ስለ ተነሣም ሥጋው የማይፈርስ የማይበሰብስ፣ የማይታመም፣ የማይሞት እንደ ኾነ እናምናለን፡፡ ሥጋውም ከእርሱ ጋር አንድ ኾኖ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአርያም በልዑል ዙፋኑ ተቀመጠ፡፡ ዳግመኛም በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ዂሉ አንድ ኾኖ በሚነሣበት ጊዜ እርሱ በጌትነት ይመጣል፤ ለዂሉም እንደ ሥራው ይከፍለዋል፡፡ እኛ በእነዚህ ቃላት ሳናወላውል ጸንተን እንኖራለን፤” (ቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ ሃይ. አበ. ፺፱፥፴፪)፡፡

“በፈቃዱ በሥጋው የእኛን ሕማም ታመመ፤ በእውነት የእኛን ሞት ሞተ፡፡ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፡፡ በፈቃዱ በተለየ አካሉ ሞትን ገንዘብ አደረገ፡፡ በሦስተኛውም ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱ ዕሪና ተቀመጠ፡፡ በኋለኛይቱ ቀንም በሙታን በሕያዋን ሊፈርድ ይመጣል፤” (ቅዱስ ፊላታዎስ፣ ሃይ. አበ. ፻፭፥፲፬)፡፡

“በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፤ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱም ሲኦልን በዘበዘ፡፡ ለዂሉም ትንሣኤን ገለጠ፡፡ ፈጽሞ አልተለወጠም፡፡ ለዂሉ አምላክነቱን አስረዳ፡፡ ሙስና መቃብርን ከእኛ አጠፋ፡፡ በቀደመ ሰው በአባታችን በአዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ሠልጥኖብን ለነበረ ኃጢአት ከመገዛት አዳነን፤” (ቅዱስ ዲዮናስዮስ፣ ፻፲፩፥፲፫)፡፡

“እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱን ከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፡፡ እርሱ ራሱ ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ፣ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ› እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም ‹አትንኪኝ› አላት፡፡ ‹ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና›፤ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን፤” (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ)፡፡

“ሞትን በሥጋ በቀመሰ ጊዜ መለኮቱ በመቃብር ውስጥ ያለ ነፍሱ ከበድኑ ጋር ነበር፡፡ በሲኦልም ውስጥ ያለ ሥጋው ከነፍሱ ጋር ህልው ነበር፡፡ በአባቱም ቀኝ ያለ ነፍስና ያለ ሥጋ ህልው ነበር፡፡ በትንሣኤውም ጊዜ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስቀድሞ ለአይሁድ ‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ› ብሎ እንደ ተናገረ፡፡ አይሁድም ‹ይህ ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ያለቀው በዐርባ ሰባት ዓመት ነው፤ አንተ ግን ‹በሦስት ቀን እሠራዋለሁ› ትላለህ› አሉት፤ ይህንም የተናገረው ስለ ራሱ ሰውነት ነው፡፡

በተነሣም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደ ተናገረ አሰቡ፡፡ በመጽሐፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የተናገራቸውን ቃል አመኑ፡፡ ሁለተኛም ‹ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ልለያት መልሼም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህንንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ› ብሏል፡፡ ዳዊትም ‹አቤቱ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ይላል፡፡ ነቢዩ ‹አቤቱ አንተ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ› ለምን አለ? የመቅደሱ ታቦት ከኾነችው ከዳዊት ዘር ከነሣው ሥጋ ጋር በመለኮታዊ ኃይሉ ከሞት እንቅልፍ ከመንቃት በስተቀር የእግዚአብሔር መነሣት ምንድነው?” (አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽ. ምሥጢር ዘትንሣኤ)፡፡

“ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው ከመስቀል አውርደው፣ በድርብ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው፤” (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ፣ ፩፥፱-፴፩)፡፡

“ሰውን ስለ መውደድህ ይህን ሁሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ ‹መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ› ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ፤” (ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ፣ ፩፥፳፬)፡፡

“በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን ‹መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ› ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፡፡ የተወጋውን ጎኑን፣ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የኾነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ፤” (ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት፣ ፬፥፳፭)፡፡

“ሰማያት (ሰማያውያን መላእክት) የደስታ በዓልን ያደርጋሉ፤ ደመናት (ቅዱሳን) የደስታን በዓል ያደርጋሉ፡፡ ምድር (ምድራውያን ሰዎችም) በክርስቶስ ደም ታጥባ (ታጥበው) የፋሲካን በዓል ታደርጋለች (ያደርጋሉ)፡፡ ያከብራሉ (ታከብራለች)፡፡ ዛሬ በሰማያት (በመላእክት ዘንድ) ታላቅ ደስታ ኾነ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን የነጻነት በዓል ታደርጋለች፡፡ የትንሣኤያችን በኵር ክርስቶስ ከሙታን ሰዎች ዂሉ ተለይቶ ቀድሞ ተነሣ፤” (ድጓ ዘፋሲካ)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ትንሣኤ ክርስቶስ በሊቃውንት አንደበት – የመጀመሪያ ክፍል

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በየጊዜያቱና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጠውን ትምህርትና ምስክርነት ሰጥተዋል፤

“ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ‹አባት ሆይ አመሰግንሃለሁ፥› ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ፤” (እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት ፭፥፩)፡፡

“እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፤ ሙታንንም አስነሣ፡፡ እንደ ተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ዘበቱበት፣ እንደ ሰደቡት እንዲሁ በሰማይ ያሉ ዂሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፡፡ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፤” (ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ሃይ. አበ. ፯፥፳፰-፴፩)፡፡

“እንዲህ ሰው ኾኖም ሰውን ፈጽሞ ያድን ዘንድ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፡፡ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤” (ዘሠለስቱ ምዕት ፲፱፥፳፬)፡፡

“ሞትን ያጠፋው፤ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፡፡ ሰው የኾነ፤ በሰው ባሕርይ የተገለጠ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፡፡ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ፡፡ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል፤” (ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ሃይ. አበ. ፳፭፥፵)፡፡

“ሥጋው በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡ በዚያም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ፤ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ፡፡ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ (ሊቃነ አጋንንት፣ ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሡ)፡፡ የብረት ቍልፎቿም ተቀጠቀጡ (ፍዳ መርገም ጠፋ)፡፡ ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃን ነፍሳትን ፈታች፤” (ዝኒ ከማሁ፣ ፳፮፥፳-፳፩)፡፡

“ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፡፡ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድወደ ሲኦል ወረደች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ ተናገረው ቃል ዐፅም ሥጋ ወደ መኾን ፈጽሞ እንደ ተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጕድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፡፡ ይህስ እውነት ከኾነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፡፡ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበሥር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፡፡ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትኾን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋው ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደ ተናገረ፡፡ አባቶቻችን ‹ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣው ሥጋ ነው እንጂ› ብለው አስተማሩን፡፡ ይህን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም በእርሱ አየ፤” (ዝኒ ከማሁ፣ ፴፥፴፩-፴)፡፡

“አሁን እግዚአብሔር ‹ሞተ› ሲል ብትሰማ አትፍራ፤ ‹የማይሞተውን ሞተ ሊሉ አይገባም› ከሚሉ ዕውቀት ከሌላቸው፤ ሕማሙን፣ ሞቱን ከሚክዱ መናፍቃን የተነሣ አትደንግጥ፡፡ እኛ ግን በመለኮቱ ሞት እንደሌለበት፤ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ሥልጣን እንደ ተነሣ እናውቃለን፡፡ ሞት የሌለበት ባይኾንስ ኖሮ በሥጋ በሞተ ጊዜ ሥጋውን ባላስነሣም ነበር፤ ሥጋው እስከ ዓለም ፍጻሜ በመቃብር በኖረ ነበር እንጂ፤” (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ሃይ. አበ. ፴፬፥፲፯-፲፰)፡፡

“ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፡፡ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣው በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፤” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣፴፮፥፴)፡፡

“በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፡፡ ፍሬውንም (ሥጋውን፣ ደሙን) ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወዳልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደ ነበረው መዓርግ ደረስን፡፡ ክፉዉንና በጎዉን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን፤” (ዝኒ ከማሁ ፴፮፥፴፰-፴፱)፡፡

“የሕይወታችን መገኛ የሚኾን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደ ለወጠ እናምናለን፡፡ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ እንደ ተጻፈ፣ ከሰው ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፡፡ ዳዊት ‹በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው?› ብሎ እንደ ተናገረ፤” (ቅዱስ አቡሊዲስ፣ ሃይ. አበ. ፵፪፥፮-፯)፡፡

“በመለኮትህ ሕማም፣ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ በሥጋ መከራ የተቀበልህ አንተ ነህ፤ ከአብ ጋር አንድ እንደ መኾንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ ከእኛም ጋር አንድ እንደ መኾንህ በፈቃድህ የሞትህ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፤ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፡፡ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡ ከሙታን ጋር የተቈጠርህ አንተ ነህ፤ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፤ ሦስት መዓልት፣ ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በዘመኑ ዂሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፤ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ እግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፤” (ቅዱስ ኤራቅሊስ፣ ፵፰፥፲፪-፲፫)፡፡

“እኛስ ኃጢአታችንን ለማስተስረይ በሥጋ እንደ ታመመ፤ እንደ ሞተ፤ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ፤ ከሙታንም ተለይቶ በእውነት እንደ ተነሣ፤ ከተነሣም በኋላ በእውነት ወደ ሰማይም እንደ ዐረገ እናምናለን፡፡ ኋላም እርሱ በሚመጣው ዓለም በሕያዋን፣ በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል፡፡ የሰውን ወገኖች ዂሉ በሞቱበት፤ በተቀበሩበት ሥጋ ከሞት ያስነሣቸዋል፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ ያለ መለወጥ ዂል ጊዜ ይኖራል፡፡ እርሱ በዚህ በሞተበት፤ በተገነዘበት ሥጋ ከሙታን አስቀድሞ እንደ ተነሣ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም፣ ሃይ. አበ. ፶፪፥፲፩-፲፪)፡፡

“የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩ ኃይል እንጂ፡፡ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በኾነ ጊዜ ሞትን አጠፋ፤ ከሞትም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፤” (ቅዱስ ቴዎዶጦስ፣ ሃይ. አበ. ፶፫፥፳፯)፡፡

“መለኮት በሥጋ አካል በመቃብር ሳለ መለኮት የሥጋ ሕይወት በምትኾን በነፍስ አካል ወደ ሲኦል ወረደ፡፡ እንደዚህ ባለ ተዋሕዶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ከትንሣኤ በኋላ አይያዝም፤ አይዳሰስም፤ በዝግ ቤት ገብቷልና፡፡ ነገር ግን ምትሐት እንዳይሉት ቶማስ ዳሠሠው፤ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ቶማስ አመነበት፤” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ሃይ. አበ. ፶፮፥፴፯-፴፰)፡፡

“ክርስቶስ የሙታን በኵር እንደ ምን ተባለ? እነሆ በናይን ያለች የደሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዓዛርን በሞተ በአራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፤ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታንን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፤ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ኾነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኵር ነው፡፡ እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፡፡ ‹ዳግመኛም ሞት አያገኘውም› ተብሎ እንደ ተጻፈ፤” (ቅዱስ ኤጲፋንዮስ፣ ፶፯፥፫-፮)፡፡

“ቃል ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ በሲኦልም ካለች ከነፍሱ አልተለየም፡፡ ከነፍስ ከሥጋ በአንድነት ነበረ እንጂ፤ ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው፤” (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ሃይ. አበ. ፷፥፳፱)፡፡

“ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በትንሣኤ ‹ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ› ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጐመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፤ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞት ነው፤ አይለወጥም፡፡ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የኾነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት (እትራት) አላጠፋምና፡፡ 

በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፤ አምላክ የሆነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፤ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደሆነ ሥራውን አስረዳ፤ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት /እትራት/ አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በዐራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው ብለው አስረዱ፤” (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሃይ. አበ. ፷፮፥፯-፲፪)፡፡

“በእርሱ ሞት ከብረናል፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢሆን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፤ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ወደ ሕይወት ሥጋ ደፍሮ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ /በክርስቶስ/ እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፤” (ቅዱስ ቄርሎስ፣ ሃይ. አበ. ፸፪፥፲፪)፡፡

ይቆየን

የትንሣኤው ብሥራት

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አሳሳችነት አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላላፋቸው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሣ የተፈረደባቸውን ሞት በሞቱ ሊደመስስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ (ዮሐ. ፩፥፩)፡፡ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ እንደ ተጠመቀም ልዋል ልደር ሳይል ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሔደ፡፡ በዚያም ጾመ፤ ጸለየ፡፡ በዲያቢሎስም ተፈተነ፡፡

ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ የአዳምና የሔዋንን ዕዳ ደምስሶ ነጻ ሊያደርጋቸው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መከራ ተቀበለ፡፡ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቆመ፤ ምራቅ ተተፋበት፤ ተገረፈ፤ በገመድ ታሥሮ ተጎተተ፤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ በሞቱ ሞትን ድል አድርጎ የአዳምን፣ የሔዋንንና የልጆቻቸውን ዕዳ በደል ደመሰሰ (ማቴ. ፳፯፥፳፰)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤” በማለት እንደ ገለጸው (ሮሜ. ፮፥፭)፣ ሞቱ ሞታችን፤ ትንሣኤው ትንሣኤያችን ነውና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ ጌታ የጾመውን ጾም በመጾም፣ በሰሙነ ሕማማት ደግሞ መከራውንና ስቃዩን በማሰብ የክርስቶስን ቤዛነት እንዘክራለን፤ የነጻነትና የድል በዓላችንንም እናከብራለን፡፡

“በጥንተ ጠላታችን ምክንያት አይሁድ ክብርህን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢያዋርዱህ፣ ቢገርፉህ፣ ርቃንህን ቢሰቅሉህና ቢገድለህ እኛ ግን ‹ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም – ኃይሌ፣ መከታዬና ረዳቴ ለኾንኸው ለአንተ ለአምላኬ ለአማኑኤል ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ጽናትም ለዘለዓለሙ ይገባሃል›፤” እያልን አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ፫፥፲ ላይ “እርሱንና የትነሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራወም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢኾንልኝ በሞቱ እንደመስለው እመኛለሁ፤” በማለት እንደ ተናገረው ምእመናን እንደ አቅማቸው እያዘኑ፣ እያለቀሱ፣ ከምግብ እየተከለከሉ፣ ጸጉራቸውን እየተላጩ የአምላካንን መከራ ያስባሉ፡፡

“ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል!” የሚለውን የምሥራች ከቤተ ክርስቲያን ለመስማት በናፍቆት ይጠባበቃሉ፡፡ የትንሣኤውን ብሥራት ሰከሙ በኋላም “ጌታ በእውነት ተነሥቷል!” እያሉ ትንሣኤዉን ይመሰክራሉ፡፡ የጌታችን ትንሣኤ፣ የድኅነታችን ብሥራት በመኾኑ ለአምሳ ቀናት ያህል በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ፣ በሌሎችም ቅዱሳት መጻሕፍት በልዩ ሥርዓት ይዘከራል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያኑ “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን አሠሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሰላም” እየተባለ ሞት መደምሰሱ፣ ነጻነት መታወጁ ይበሠራል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – ካለፈው የቀጠለ

በዳዊት አብርሃም

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ከዚህ ቀጥለን ደግሞ የጴጥሮስን እና የይሁዳን መልእክት እንመልከታለን፤

  • “ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን ዐመድ እስኪኾኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው ጻድቅ ሎጥም በመካከላቸው ሲኖር እያየና እየሰማ ዕለት ዕለት በዓመፀኛ ሥራቸው ጻድቅ ነፍሱን አስጨንቆ ነበርና በዓመፀኞች ሴሰኛ ኑሮ የተገፋውን ያን ጻድቅ ካዳነ፥ ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” (፪ኛ ጴጥ. ፪፥፮)፡፡
  • “ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ የሆነ ሄኖክ፦ እነሆ፥ ጌታ በዂሉ ላይ እንዲፈርድ፥ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ዂሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ዂሉ ‹ኃጢአተኞችን ዂሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል› ብሎ ለእነዚህ ደግሞ ትንቢት ተናገረ” (ይሁዳ፣ ቍጥር ፲፬-፲፭)፡፡

እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅሶች በብዛት አሉ፡፡ ይህን ዂሉ ከተመለከትን በኋላ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አንዲት ቦታ ላይ የጻፋትን አንዲት ጥቅስ ብቻ መዝዘን በመውሰድ ኃጢአትን “የሚያደርጉ ይጸድቃሉ” ወደሚል ስሕተት ከመውደቅ እንጠበቃለን፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል አስተምሯልና፤ “ወይስ ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢኾኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝራዎች ወይም ቀራጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌባዎች ወይም ገንዘብ የሚመኙ ሰካራሞች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” (፩ኛ ቆሮ. ፮፥፱-፲)፡፡

በአንድ ጥቅስ መመርኮዝ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ አይደለም፡፡ በዚህ መልክ ድምዳሜ ላይ መድረስም ኦርቶዶክሳዊ መንገድ አይደለም፡፡ አንድ ጥቅስ አንሥቶ የኾነ ዐሳብ መሰንዘር የሚፈልግ ሰው ቢያጋጥም ጥቅሱ የቱንም ያህል ግልጽ መልእክት ያለው ቢኾን እንኳን “እንዲህ ለማለት ነው” ተብሎ ለመደምደም አያስችልም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ የኾነ ሰውም በተነሣው ርእሰ ጉዳይ ላይ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ምን እንደሚሉ ለማወቅ ይጥራል፡፡ ዐሳቡን የተሟላ የሚያደርጉት በጉዳዩ ላይ ሌሎች የቅዱደሳት መጻሕፍት ክፍሎች ተሟልተው ሲቀርቡ ነው፡፡ ሌሎች ጥቅሶች አንዱን ጥቅስ ግልጽና የማያሻማ እንደዚሁም የተሟላ ያደርጉታል፡፡

ይህንም በሚቀጥሉት ስለ ነገረ ድኅነት ከተጻፉት ጥቅሶች አንጻር እንመልከት፤ “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” (ኤፌ. ፪፥፰-፱)፡፡ ይህ ኃይለ ቃል መልእክት “ሥራ አያስፈልግም፤ እምነትና ጸጋ ብቻቸውን ለመዳን በቂ ናቸው” የሚል ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሳንቸኩል አንድ ቍጥር ወረድ ብለን ንባባችንን ብንቀጥል እንደዚህ የሚል መልእክት እገኛለን፤ “እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” (ኤፌ. ፪፥፲)፡፡

ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት፤ “በጸጋ ከኾነ ግን ከሥራ መኾኑ ቀርቶአል፤ ጸጋ ያለዚያ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል” (ሮሜ. ፲፩፥፮)፡፡ አሁንም በዚህ ጥቅስ ሳንወሰን በዚያው ምዕራፍ ወረድ ብለን ንባባችንን እንቀጥል፤ “መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ፤ አንተም ከእምነት የተነሣ ቆመሃል፡፡ ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ፡፡ እግዚአብሔር እንደ ተፈጠሩት ለነበሩት ቅርንጫፎች የራራላቸው ካልኾነ ለአንተ ደግሞ አይራራልህምና፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፥ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ” (ሮሜ. ፲፩፥፳-፳፪)፡፡

ይህ ማለት ምን ማለት ነው? በክርስቶስ ደም ዂላችንም መዳንን አግኝተናል (ድነናል)፡፡ ኾኖም ከእርሱ ጋር ካልተጣበቅን ማለትም እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር የሚያደርገንን የጽድቅ ሥራ መሥራት ካልቻልን የመቆረጥ ቅጣት ይደርስብናል፡፡ ከግንዱ ተቆርጦ ዕጣው መድረቅና መጠውለግ እንደ ኾነበት ቅርንጫፍ እንኾናለን፡፡

አሁንም ሦስተኛ ምሳሌ እንጨምር፤ “ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል፡፡ በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቈጥራለንና” (ሮሜ. ፫፥፳፯-፳፰)፡፡ ይህን ጥቅስ ስናነብ “ለመዳን ሥራ አያስፈልግም” ከሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንዳንቸኩል ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ሌላ ቦታ መሔድ ሳያስፈልገን ጥቂት ብቻ ዝቅ ብለን እናንብበው፤ “እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ” (ሮሜ. ፫፥፴፩)፡፡

አራተኛ ምሳሌ “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚኾነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም” (ቲቶ ፫፥፬-፮)፡፡ ይህ ጥቅስ መዳን የሚገኘው በጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ መኾኑን እንደሚገልጥ ልብ እንበል፡፡

ይህም መዳን “በእምነት ብቻ” የሚለውን ኑፋቄ የሚቃወም ዐሳብ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ሐዋርያው የሥራን አስፈላጊነት ሲገልጥ እንዲህ ይላል፤ “ቃሉ የታመነ ነው፤ እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥ እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ፡፡ ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው” (ቲቶ ፫፥፰)፡፡

አንድን ጥቅስ አንሥተን ስንናገር ያን ማድረጋችን ለጥቅማችን እንኳን ቢኾን በዚያ በአንዱ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረት አይገባንም፡፡ ለምሳሌ “ጻድቅ እንደ ኾነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ዂሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ዕወቁ” (፩ኛ ዮሐ. ፪፥፳፱) በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ ጽድቅን ማድረግ አስፈላጊ መኾኑ ተገልጧልና “ለመዳን ጽድቅ ማድረግ በቂ ስለ ኾነ እምነት፣ ጥምቀትና ሌሎች ምሥጢራት አያስፈልጉም” ወደሚል ጽንፈኛ አቋም ልንወድቅ አይገባም፡፡

ሐዋርያው በሌላ ቦታ ደግሞ ፍቅር ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልሰን መኾኑን ያስተምራል፡፡ “እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ኾንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል” (፩ኛ ዮሐ. ፫፥፲፬)፡፡ በዚህ ጥቅስ ላይ ተመሥርተን ደግሞ “ለመዳን ወንድሞችን መውደድ በቂ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ብንደርስ አሁንም ልክ አይደለንም፡፡

ሐዋርያው ስለ ፍቅር ታላቅነት ደጋግሞ ሲያስተምር “እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፤ እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል” በማለት አስተምሯል (፩ኛ ዮሐ. ፬፥፲፮)፡፡ ስለ ፍቅር ለማስተማር ብለን እንኳን ቢኾን በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ልንመሠረትና ሌላውን ችላ ልንል  አይገባንም፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ፍቅር ሲያስተምር “ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ዂሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ፍቅር ከእምነት እንደሚበልጥ ተናግሯል (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፪)፡፡

በተመሳሳይ መልኩ “እንዲህም ከኾነ፥ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” በማለት የፍቅርን ታላቅነት አስረድቷል (፩ኛ ቆሮ. ፲፫፥፲፫)፡፡ ስለዚህ “መዳን በእምነት ብቻ” የሚል ሰው እነዚህን ጥቅሶች ምን ሊያደርጋቸው ይችላል? በአንጻሩ በአንድ ጥቅስ ተወስኖ መደምደም የለመደ ሰው የፍቅርን ታላቅነት የሚያወሳውን ጥቅስ በመምዘዝ “መዳን በፍቅር ነው” ብሎ እንዳይስት መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡

ጌታችን ለወጣቱ ባለ ጸጋ “ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” (ማቴ. ፲፱፥፲፯) ባለው ላይ ብቻ ተመሥርተን “ለመዳን መንገዱ ይሔ ብቻ ነው” ማለት ትልቅ ስሕተት ነው፡፡ ያለ እምነት የሚፈጸም መልካም ሥራ ብቻውን እንደማያድን አውቀን፣ “ለመዳን ሕግጋትን መጠበቅ ይበቃል” ከሚል ስሕተት ወጥተን፣ እንደዚሁም ስለ እምነትና በጸጋው ስለ መዳን በሚናገሩ አንዳንድ ጥቅሶች ላይ ብቻ ማተኮሩን ትተን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር በትዕግሥትና በጥንቃቄ ማጥናት እንዳንሳሳት ይረዳናል፡፡

ከዚሁ ዂሉ ጋርም “እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይኾን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንኾን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና፤ መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል” የሚለውን የሐዋርያውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል (፪ኛ ቆሮ. ፫፥፮)፡፡

የመዳንን ትምህርት ለመረዳት በፊደል ሳይኾን በመንፈስ ኾነን፣ በአንድ ጥቅስ ላይ ብቻ ሳንወሰን ወይም ጉዳዩን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ ሳንመለከት በስፋትና በጥልቀት የኾነውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በማወቅ መጽናት፣ ለሚጠይቁንም ምላሽ መስጠት ያስፈልገናል፡፡ በአንድ ጥቅስ ላይ ተመሥርቶ ነገረ ድኅነትን ለማወቅ መሞከር ከባድ ስሕተት ውስጥ እንደሚጥለን ለማወቅ አንድ ምሳሌ ተመልክተን ጽሑፋችንን እናጠቃልላለን፤

መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ቦታ “የጌታን ስም የሚጠራ ዂሉ ይድናል” ይላል (ሮሜ. ፲፥፲፮)፡፡ ይህን ጥቅስ መሠረት አድርገን “የጌታን ስም ስለ ጠራን ብቻ እንድናለን” ብለን ብናስብ ከሚከተለው ጥቅስ ጋር እንጋጫለን፤ “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ዂሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” (ማቴ. ፯፥፳፩)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ነገረ ድኅነት በመጽሐፍ ቅዱስ – የመጀመሪያ ክፍል

በዳዊት አብርሃም

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ስለ ነገረ ድኅነትም ኾነ ስለማናቸውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ ስናጠና አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ብቻ መመርኮዝ የለብንም፡፡ አንዲቷን ጥቅስ ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳብ ለይተንና ከሌሎች ጥቅሶች ነጥለን መመልከት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡ ኦርቶዶክሳዊውን የነገረ ድኅነት አስተምህሮ የሚቃወሙና በተቃራኒውም ስሕተት የኾነ ትምህርት በማስተማር የሚከራከሩ ወገኖች በዚህ ዓይነቱ ስሕተት ሊጠመዱ የቻሉበት አንዱ ምክንያት በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ ሙጥኝ ብለው ሌሎቹን ግን ችላ ማለት ስለሚቀናቸው ነው፡፡ ደካማ ሰው አንድን ጥቅስ ብቻ ነጥሎ በማንጠልጠል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ብልህ፣ ጠቢብና ዕውቀት ፈላጊ ሰው ግን አንዱን ከአንዱ ጋር እያነጻጸረ በማጥናት፣ በመታገሥ ምርምሩን ይቀጥላል፡፡ በዚህም ትክክለኛ ዕውቀት ላይ ይደርሳል፤ እውነትን ወደ ማወቅም ይመጣል፡፡

ከነገረ ድኅነት አስተምህሮ አንጻር ይህን ነገር በምሳሌ እንመልከት፤ “እነርሱም ‹በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ› አሉት” (ሐዋ. ፲፮፥፲፫)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ በመምዘዝ “ለመዳን ማመን ብቻ በቂ ነው” ይላሉ፡፡ ይህን ንግግር ቅዱስ ጳውሎስ እና ቅዱስ ሲላስ በፊልጵስዩስ የእስር ቤት ጠባቂ ለነበረው ሰው የተናገሩት ኀይለ ቃል ነው፡፡ “ጥቅሱ የተነገረው ለማን ነው? ለምን ተነገረ? ከዚያስ ወረድ ብሎ ምን ይላል? ከሌሎች ጥቅሶች ጋር ያለው ተዛምዶ ምን ይመስላል?” ብለው ሳይጠይቁ ለውሳኔ መቻኮል ትክክል አይደለም፡፡ እስኪ ጥቅሱን በእርጋታ እንመርምረው፤

፩ኛ. ይህ ቃል የተነገረው ከአሕዛብ ወገን ለኾነ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው እምነት የለሽ ነው፡፡ ስለዚህም ምንም ዓይነት በጎ ሥራ ቢሠራ ዋጋ አያገኝም፡፡ ለመዳን አስቀድሞ ማመን አለበትና፡፡ ሳያምን ወደ ሌላ በጎ ሥራ ቢጓዝ መዳንን አያገኝምና፡፡ ስለዚህም ጳውሎስ እና ሲላስ አስቀድመው የመዳን በር የኾነውን ቃል ነገሩት፤ ‹‹እመን›› አሉት፡፡ እምነት ለመዳን የመጀመሪያው ደረጃ ነው፤ ሌሎች ለመዳን ከሰው የሚጠበቁት ዂሉ ከማመን በኋላ የሚመጡ ናቸው፡፡

፪ኛ. መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ተግባርን የሒደቱን አጠቃላይ ኹኔታ የሚያሳይ አድርጎ ያቀርበዋል፡፡ ለዚህም ዓይነተኛው ምሳሌ ስምዖን አረጋዊ ነው፡፡ ስምዖን አረጋዊ “ዓይኖቼ በሰዎች ዂሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋል” (ሉቃ. ፪፥፴-፴፩) በማለት የተናገረው ጌታ ተሰቅሎ፣ ሞቶ የሚፈጽመውን ማዳን አይቶ አይደለም፡፡ እርሱ ለማየት የቻለው የጌታን መወለድ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የጌታችን መወለድ የማዳን ሥራው አካል መኾኑን ስለተረዳ “እንግዲህ ባርያህን አሰናብተው” አለ፡፡ የጳውሎስ እና የሲላስ ዐሳብም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለእስር ቤቱ ጠባቂ “አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችኁ” ሲሉ የእርሱና የቤተሰቡ መዳን በእርሱ ማመን ብቻ ፍጻሜ ያገኛል ብለው አይደለም፡፡ ነገር ግን በምግባር፣ በተጋድሎ፣ ምሥጢራትን በመፈጸምና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ፍጻሜ የሚያገኘውን የመዳን ጉዞ በእምነት እንደሚጀምር መናገራቸው ነው፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘኬዎስ የተናገረው ኃይለ ቃልም ተመሳሳይ መልእክት ያለው ነው፤ “እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤” (ሉቃ. ፲፱፥፱)፡፡ ይህ ማለት የዘኬዎስ የመዳን ጉዞ ዛሬ ተጀመረ ማለት እንጂ ዘኬዎስ ጌታን በመኖሪያ ቤቱ ተቀብሎ ስላስተናገደው ብቻ መዳንን ወርሷል ወይም ድኗል ማለት አይደለም፡፡

፫ኛ. ጳውሎስና ሲላስም ይህን ሲሉ አሁን ባመንክበት ቅጽበት ትድናለህ ማለታቸው ሳይኾን የመዳኑን መንገድ ይዘኸዋል ማለታቸው መኾኑን የሚያረጋግጥ አንዱ አባባል “ትድናለህ” ብለው በትንቢት አንቀጽ መናገራቸው ነው፡፡

፬ኛ. ሌላው የእርሱ እምነት ለመዳኑ የመጀመሪያ ርምጃ መኾኑን የምናውቀው “ቤተሰቦችህ ይድናሉ” በሚለው የሐዋርት ንግግር ነው፡፡ “እርሱ ባመነው ቤተሰቦቹ እንዴት ይድናሉ?” የሚል ጥያቄ ብናነሣ ሐዋርያት የተናገሩት አሁን በዚያ ቅጽበት ለሚኾነው ሳይኾን ከዚያ ቅጽበት ለሚጀመረውና ወደፊት ለሚጠናቀቀው መዳን መኾኑን እንረዳለን፡፡ እርሱ ካመነ በኋላ ቤተሰቦቹን ሲያሳምን ደግሞ እነርሱም ልክ እንደ እርሱ የመዳንን ጉዞ አንድ ብለው ይጀምራሉ፡፡ ይህም ማመን ለመላው ቤተሰብ የመዳን ጉዞ የመጀመሪያ ምዕራፍ መኾኑን ይገልጣል፡፡

፭ኛ. ኃይለ ቃሉን ዝቅ ብለን ስናነብም ይህን የሚያጠናክር ማስረጃ እናገኛለን፤ “ለእርሱና በቤቱም ላሉት ዂሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሯቸው። በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፤ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተሰዎቹ ዂሉ ጋር ተጠመቀ፤” (ሐዋ. ፲፮፥፴፪-፴፫)፡፡

“እመን፤ ትድናለህ” የሚለውን ኃይለ ቃል ብቻ መዝዘን በማውጣት “ለመዳን የሚያስፈልገው ማመን ብቻ ነው” ከሚል ድምዳሜ ከደረስን በተጠቀሱት ስሕተቶች ላይ እንወድቃለን፡፡ ይህም የበለጠ ግልጽ እንዲኾንልን ሌላ ምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንመልከት፤

አንድ ወጣት ወደ ጌታችን ቀርቦ “መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ?” ሲል ጠየቀው (ማቴ. ፲፱፥፲፮)፡፡ ጌታችን ሲመልስለትም “እመንና ትድናለህ” አላለውም፡፡ ነገር ግን “ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ” ነው ያለው (ማቴ. ፲፱፥፲፯)፡፡ ታዲያ ከዚህ የወንጌል ጥቅስ ተነሥተን “ትእዛዞችን መጠበቅ (ሕግጋቱን መጠበቅ) ብቻውን ለመዳን በቂ ነው” ብሎ መደምደም ይቻላል? በፍጹም አንችልም፡፡ አንድ ጥቅስ ብቻ አንጠልጥሎ ለመደምደም መቸኮል ግን ይህን ከመሰለው ስሕተት ላይ ሊጥለን እንደሚችል ልብ እንበል፡፡

በዚሁ ጥቅስ ላይ ንባባችንን ስንቀጥል ጥያቄውን ያቀረበው ወጣት “እነዚህን ዂሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄያቸዋለሁ” ብሎ መለኮታዊውን ትእዛዝ መጠበቁን ሲያረጋግጥ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ አስቀድሞ ጌታችን “ለመዳን መሥፈርቱ ትእዛዛትን መጠበቅ ነው” ብሎ የተናገረውን ይዘን አሁን ወጣቱ “‹ፈጽሜያቸዋለሁ› በሚል ምላሹ ምክንያት ድኗል” ብለን ልንደመድም አንችልም፡፡ ጌታችን ለወጣቱ “ፍጹም ልትኾን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከተለኝ” በማለት ለመዳን ማድረግ የሚገባውን ዂሉ እንደ ነገረው መዘንጋት የለብንም (ማቴ. ፲፱፥፳፮)፡፡

ከዚህ ላይ ለመዳን እምነት ወይም ጸጋው አልተጠቀሰም፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት ሕግጋትን መፈጸም ወይም በጎ መሥራት እንኳን ቢኾን በቂ አይደለም፡፡ ከዚያ ያለፈ ተግባር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አንድ ጥቅስ ላይ ብቻ መመሥረትን የመረጠ ሰው “ያለውን ዂሉ ሸጦ ለችግረኞች አከፋፍሎ ጌታን ካልተከተሉ በቀር መዳን አይቻልም” ብሎ ለመደምደም ይገደዳል ማለት ነው፡፡

አንዳንድ ስሑታን ስለ ነገረ ድኅነት ሲከራከሩ የሚያነሡት ሌላው ጥቅስ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” የሚለው ኃይለ ቃል ነው (ሮሜ. ፭፥፩)፡፡ አንዳንዶች ይህን ጥቅስ እያነሡ “ከዚህ በላይ ማስረጃ ምን ትፈልጋለህ? በእምነት ብቻ እንደሚጸደቅ በግልጥ ተጽፏል፤ ይህን ጥቅስ ምን ታደርገዋለህ? ወይስ እንዴት ልትክደው ትችላለህ?” በሚል ዐሳብ ይከራከራሉ፡፡

የእኛ ምላሽም እንዲህ ነው፤ ይህንን ትምህርት አንክድም፤ አናስተባብልምም፡፡ ነገር ግን ለብቻው ነጥለን አንመለከተውም፡፡ እዚያው ከአጠገቡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈው ሌላ ትምህርት አለና እርሱን አምጥተን አብረን እናጠናዋለን፡፡ ትምህርቱም እንዲህ የሚል ነው፤ “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይደለም” (ሮሜ. ፪፥፲፫)፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሐዋርያው ጽድቅ (መዳን) የሚገኘው ሕግን በማድረግ መኾኑን ያስተምረናል፡፡

ታዲያ በዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመሥርተን “መዳን ሕጉን በመተግበር ብቻ የሚገኝ ነው” ልንል እንችላለን? አንልም፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም የሐዋርያውን ጥቅሶች ሳንነጣጥል በአንድነት እንወስዳቸዋለን፡፡ ሐዋርያው በሁለቱም ቦታዎች በሮሜ. ፪፥፲፫ እና ፭፥፩ ላይ የጻፈልንን ለድኅነታችን አስፈላጊ የኾኑትን ተግባራት እንማራለን፡፡ በዚህ መሠረት ለመዳናችን ማመናችን የሚኖረውን ዋጋ መልካም ሥራ አይተካውም፤ እንደዚሁም መልካም ሥራ ለመዳናችን አስፈላጊ መኾኑ የእምነትን አስፈላጊነት አይሽረውም፡፡ “ሰው በእምነት ብቻ ሳይኾን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ፡፡ እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን?” (ያዕ. ፪፥፳፬-፳፭) ተብሎ እንደ ተጻፈው ለመዳን ሁለቱንም እምነትንና ሥራን አዋሕደን መያዝ እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

ሌላ ኃይለ ቃል ደግሞ እንመልከት፤ “ነገር ግን ለማይሠራ፥ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን ሰው እምነቱ ጽድቅ ኾኖ ይቈጠርለታል” (ሮሜ. ፬፥፭) በዚህ ኃይለ ቃል መነሻነት ሌሎቹን የትምህርት ዓይነቶች ወይም ኃይለ ቃሉን በምልዓት ለመረዳት ስንሞክር አንድ ሰው ኃጢአተኛ ኾኖ ሳለ፣ ኃጢአት መሥራቱንም ሳያይተው ወይም ንስሐ ሳይገባ “ይጸድቃል” ብለን መደምደም እንችላለን? ይህንን ኃይለ ቃል በትክክል ለመረዳት ጥቅሱን ግልጽ ሊያደርጉ የሚችሉ ሌሎች ነጥቦችን መረዳት ይኖርብናል፡፡

ለምሳሌ ከዚያው ከሮሜ መልእክት አንድ ሌላ ጥቅስ እንመልከት፤

  • “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ዂሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል” (ሮሜ. ፩፥፲፰)፡፡
  • “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለ ጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ” (ሮሜ. ፪፥፭)፡፡

ይቆየን

ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ‹ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል› ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመኾኑ እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፤

፩. ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)

‹ተኰርዖት› የሚለው ቃል ‹ኰርዐ – መታ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ርእስ› ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ. ፳፯፥፳፬፤ ማር. ፲፭፥፲፭፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፭፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፱)፡፡

አይሁድ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በጌታችን ራስ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር. ፲፭፥፲፱)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾኽ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የኾነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡

፪. ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)

‹ተፀፍዖ› የሚለው ቃል ‹ፀፍዐ – በጥፊ መታ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን፣ ‹መጥፊ መመታት› ማለት ነው፡፡ ‹መልታሕት› ደግሞ ‹ፊት፣ ጉንጭ› ማለት ነው፡፡ ይኸውም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቈጥሮበት አይሁድ ጌታችን መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው ‹‹ክርስቶስ ሆይ! በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን!›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡

በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ መድኀኒታችን ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ.  ፳፯፥፳፯)፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይኹን!›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል (ዮሐ. ፲፱፥፪)፡፡ አላወቁትም እንጂ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት የዘለዓለም አምላክ ነው፡፡

፫. ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)

‹ወሪቅ› የሚለው ቃል ‹ወረቀ – እንትፍ አለ፤ ተፋ› ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ‹እንትፍ ማለት፣ መትፋት› ማለት ነው፡፡ ‹ምራቅ› በቁሙ ‹ምራቅ› ማለት ነው፡፡ ወሪቀ ምራቅ፣ አይሁድ በብርሃናዊው በክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ኹኔታ ምራቃቸውን እንደ ተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ በትንቢት ኢሳይያስ ፶፥፮ ላይ ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደ ተነገረ፣ አይሁድ እየዘበቱ በአምላካችን ላይ ምራቃቸውን ተፍተውበታል (ማቴ. ፳፯፥፳፱-፴፤ ማር. ፲፭፥፲፱)፡፡

በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ምራቅ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡ እንኳን በአምላክ ፊት በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ያስነውራል፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የኾነውን ምራቅ በትዕግሥት ተቀበለ፡፡

፬. ሰትየ ሐሞት (አሞት መጠጣት)

‹ሰትየ› ማለት በግእስ ቋንቋ ‹ጠጣ› ማለት ሲኾን፣ ‹ሰትይ› ደግሞ ‹መጠጣት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ‹ሐሞት› የሚለው የግእዝ ቃልም ‹አሞት› ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ቃላቱ በአንድ ላይ ‹ሰትየ ሐሞት› ተብለው ሲናበቡ ‹አሞት መጠጣት› የሚል ትርጕም ይሰጣሉ፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ መራራ አሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡

‹‹ለመብሌ አሞት ሰጡኝ፤ ለጥማቴም ኾምጣጤ አጠጡኝ›› ብሎ ነቢዩ ዳዊትን በመዝሙረ ዳዊት መዝሙር ፷፰፥፳፩ ላይ ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ ኾምጣጤ በሰፍነግ ሞልተው ወደ አፉ አቀረቡለት፡፡ ውኃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ. ፳፯፥፴፬)፡፡ ጌታችንም ኾምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን በፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ (ማቴ.፳፯፥፵፰፤ ማር. ፲፭፥፴፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፴፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፳፱)፡፡

ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃን የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም (ኢሳ. ፶፭፥፩)፡፡ ዐርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ሲጓዙ ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከዐለት ላይ ውኃ አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ አይሁድ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት (ዘዳ. ፲፮፥፩-፳፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፥፫)፡፡ የዝናማት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ዂሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፤ ኾምጣጣውንም ጠጣ፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ የመረረውን መጠጥ ተቀበለ፡፡

፭. ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)

‹ተቀሥፎ› የሚለው ቃል ‹ቀሠፈ – ገረፈ› ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን፣ ‹መገረፍ› ማለት ነው፡፡ ‹ዘባን› ደግሞ ‹ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ› የሚል ትርጕም አለው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባው እስኪላጥ ድረስ ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ ከላይ እንደ ተጠቀሰው በዘመኑ የቅጣት ሕግ መሠረት የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ቅጣቱን ለማቅለል ዐስቦ ጲላጦስ ኢየሱስ ክርስቶስን ቢያስገርፈውም አይሁድ ግን በግፍ ሰቅለውታል፡፡ ጲላጦስ ‹‹ከደሙ ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችንን ለአይሁድ አሳልፎ በመስጠት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንዲሉ የታጠበ እጁን መልሶ አቆሸሸው (ማቴ. ፳፯፥፳፰፤ ማር. ፲፭፥፲፭፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› ተብሎ እንደ ተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡ በመንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጌታችን ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቈጠር ድረስም ተገረፈ፡፡ አይሁድ አገረ ገዥያቸው ጲላጦስ ላቀረበላቸው ምርጫ ይፈታላቸው ዘንድ ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን ክርስቶስን ሳይኾን ራሱን እንኳን ከምድራዊ ወኅኒ ማውጣት ያልቻለውን ወንበዴውን በርባንን መረጡ፡፡ መገረፍ ይገባው የነበረ በርባን ተለቀቀ፡፡ ይህ ዂሉ የኾነውም የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውንና የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው፡፡ በእርግጥ ክርስቶስ ካልሞተ ዓለም አይድንምና ሳያውቁም ቢኾን መድኃኒታቸውን መርጠዋል፡፡

፮. ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)

‹ተዐርቆተ› ማለት በግእዝ ቋንቋ ‹መታረዝ፣ መራቆት› ማለት ነው፡፡ ይኸውም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ለእኛ ሲል ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ለዓለም ድኅነት ሲል ራቁቱን ለፍርድ ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የዓለሙ ዂሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡ የሲኦል ወታደሮች አጋንንት የሰውን ልጅ ጸጋ ገፍፈውት ነበርና ይህን ጸጋ ለማስመለስ ሲል ጌታችን በአይሁድ ወታደሮች ልብሱን ተገፈፈ፡፡

፯. ርግዘተ ገቦ (ጎንን በጦር መወጋት)

‹ርግዘት› የሚለው ቃል ‹ረገዘ – ወጋ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን ‹በጦር መወጋት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ‹ገቦ› ማለት ‹ጎን›፤ ‹ርግዘተ ገቦ› ደግሞ ‹ጎንን በጦር መወጋት› ማለት ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር ተወግቷል፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፡፡ በዚህ ጊዜ ድኅተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ የሚሰጥ ደምና ውኃ ከጎኑ ፈሰሰ (ዮሐ. ፲፱፥፴፫)፡፡ መላእክትም ደሙን ተቀብለው በዓለም ረጭተውታል፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በኾነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ሲል አምላካችን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለ ጣለው ‹‹ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ?›› ተብሎ ተዘመረ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት በክርስቶስ ሞት ድል ተደርጓልና (ኢሳ. ፳፭፥፰፤ ሆሴ. ፲፫፥፲፬፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፬-፶፭)፡፡

ከተወጋው ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደምና ውኃም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘለዓለምን ሕይወት አጥቶ የነበረው ሰው ልጅነቱና ሕይወቱ እንደ ተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን ማግኘት ይቻላልና (ዮሐ. ፫፥፭፤ ፮፥፶፬)፡፡

፰. ተአሥሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)

‹ተአሥሮት› የሚለው ቃል ‹አሠረ (ሲነበብ ይላላል) – አሠረ› ወይም ‹ተአሥረ – ታሠረ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ‹መታሠር› ማለት ነው፡፡ ‹ድኅሪት› የሚለው ቃል ደግሞ ‹ተድኅረ – ወደ ኋላ አለ› ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት በአንድ ላይ (ተአሥሮተ ድኅሪት) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደ ኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ትርጕም ይሰጣሉ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል (ዮሐ. ፲፰፥፲፪)፡፡ በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ለመፍታት ሲል መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡

ከ ፱ – ፲፫ ያሉት የሕማማተ መስቀል ክፍሎች ደግሞ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል ናቸው፡፡

በስምንቱ ሕማማት ላይ ሲደመሩ ዐሥራ ሦስት ይኾናል፡፡ ‹ቅንዋት› የሚለው ቃል ‹ቀነወ – ቸነከረ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹መስቀል› ማለት ደግሞ የተመሳቀለ ዕንጨት ማለት ነው፡፡ ‹ቅንዋተ መስቀል› – መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸውን አምስቱን ጠንካራ የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ነው፡፡ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል፡- ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፤ ሮዳስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መኾናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቀዳም ሥዑር

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.

የሰሙነ ሕማማቷ ቅዳሜ ‹ቀዳም ሥዑር› ወይም ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትባላለች፡፡ ትርጕሙም ‹የተሻረች ቅዳሜ› ማለት ነው፡፡ የማትጾመዋ ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል ‹የተሻረችው ቅዳሜ› ተብላ ተጠርታለች፡፡ ነገር ግን ቃሉ ጾምን እንጂ በዓል መሻርን አያመለክትም፡፡ በቀዳም ሥዑር  ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ፣ እየተመረገደ፣ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጠዋት አቡን፣ መዋሥዕት፣ ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ‹‹ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ›› በሚለው ሰላም ሥርዓተ ማኅሌቱ ይጠናቀቃል፡፡

ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለ ኾነ ዕለተ ቅዳሜ ‹ለምለም ቅዳሜ› ተብላም ትጠራለች፡፡ በቀዳም ሥዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል (ቃለ ዓዋዲ) እየመቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ›› የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደ ሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደ ገለጠልን በማብሠር፤ ቄጠማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብሥራት ነው፡፡

ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት ድረስ በራሳቸው ላይ አሥረውት ይቆያሉ፡፡ ይህም አይሁድ በጌታችን ራስ ላይ የእሾኽ አክሊል ማሠራቸውን የሚያስታውስ ነው፡፡ የቀጤማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ (በጥፋት ውኃ) በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ‹‹የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ፤ ታወጀ፤›› በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡

ዕለተ ቅዳሜ ‹ቅዱስ ቅዳሜ› እየተባለችም ትጠራለች፡፡ ቅዱስ መባሏም ቅዱስ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ዅሉ ስላረፈባት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ዅሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፤ በነፍሱ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለ ኾነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየች ዕለት መኾኗን ለማመላከት ‹ቅዱስ› (ቅድስት) ተብላለች፡፡

ምእመናን ሆይ! በአጠቃላይ የጌታችንን የመከራ ሳምንት ‹ሰሙነ ሕማማት› ብለው ሰይመው፣ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ያቆዩልንን ትውፊት ልንጠብቀውም፣ ልንጠቀምበትም ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና ስያሜ ከማወቅና ከመረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡ ስምዐ ተዋሕዶ፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ከሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፬ .ም፣ አዲስ አበባ፡፡

ቀዳሚት ሥዑር

በመምህር ቸርነት አበበ

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር አምላካችን የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን፣ በክንፍ የሚበሩትን እና በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን፣ በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ነች፡፡ የመጀመሪያዋ ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ፍጥረታትን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ስላረፈባት ‹ሰንበት ዐባይ› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ይህቺን ዕለት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ እግዚአብሔር ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንዳደረገባት ዅሉ፣ የፍጥረት ርእስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አምላካችን ክርስቶስ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አርፎ የዋለባት ዕለት በመኾኗ ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትሰኛለች፡፡ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡ የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

እመቤታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት ዅሉ የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው በማክፈል (በመጾም) እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ለሁለት ቀናት ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸምም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ›› እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምእመናን የምሥራች ቄጠማ ያድላሉ፡፡

ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ ዅሉ፣ አሁንም ‹‹በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዅሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ጥንተ ማኅደራቸው ገነት መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የእመቤታችን ኀዘን ስለ ጌታችን መከራ

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

… ለእኔስ በተሰቀለው ላይ ልቅሶ አለኝ፤ ‹‹በመስቀል ላይ ሞትህን?›› እላለሁ፡፡ የመስቀልህ ጥላ ሙታንን ሲያስነሣም ዐውቃለሁ፤ በመስቀል ላይ ዘንበል ማለትህን አደንቃለሁ፡፡ የሲኦልን መታወክ፣ በውስጧ ያሉ ሰባት መቶ የብረት በሮች እንደ ተሰበሩ አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ ታስረው የነበሩትንም ከአባታቸው ከአዳም ጋር አወጣሃቸው፡፡ በዚያች ዕለትም ወደ ርስታቸው ወደ ገነት አስገባሃቸው፡፡ ነፍስህ ከሥጋህ በተለየች ጊዜም አለቅስሁ፡፡ በቀኝ ተሰቅሎ ለነበረው ወንበዴ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ሠላሳ ሦስት ዘመን ተዘግታ የኖረች ገነትን በከፈትህ ጊዜም ተደሰትሁ፡፡

በዕንጨት መስቀል በሰቀሉህ ጊዜ ላልቅስ? ወይስ ፀሐይ በጨለመ ጊዜ ልደንግጥ? በመስቀል ላይ ራቁትህን ኾነህ በተመለከትሁህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ቀኑ ሌሊት በኾነ ጊዜ ልደነቅ? ‹‹ክርስቶስ ሆይ! ማን መታህ? ንገረን!›› እያሉ በመቱህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት፤ በመስቀል የተሰቀለ›› እያሉ ለማመስገን እልፍ አእላፍ ፍጥረታት ሲወድቁልህ ልደሰት? መጣጣዉን ከሐሞት ጋር ቀላቅለው ባጠጡህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ አምላካዊ የኾነች ደም፣ ከመስቀሉ ታችም ንጹሕ ውኃ በፈሰሰ ጊዜ?

የመለኮት ደም ዐለቱን ሰንጥቆ የአባታችን የአዳምን መቃብር አልፎ በአዳም አፍ ስለ መግባቱ ስለ ማዳኑም አደንቃለሁ፡፡ ስለዚህም ወንጌላዊው ‹‹ዐለቱ ተሰነጠቀ፤ የጻድቃን በድኖች ተነሡ፤›› አለ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡ በፊትህ ምራቅ በተፉብህ ጊዜ ላልቅስ? ወይስ ዕውር ኾኖ የተወለደዉን በማዳንህ ልደሰት? በአንገትህ ሐብል ባደረጉብህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ሰይጣን ያሰራቸዉን ስትፈታቸው ላመስግንህ? ታስረህ በጲላጦስ ፊት ሲያቆሙህ ላልቅስን? ወይስ በባሕሩ እንደ የብስ ሔደህ ነፋሳትን እንደ ሎሌ በመገሠፅህ ላድንቅ? ወይስ ነቢያት አንተን ለማየት በመመኘታቸው ልደሰት?

ዛሬ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ባየሁህ ጊዜ ላልቅስን? ከሌቦች፣ ከወንበዴዎች፣ ዓለሙን ዂሉ ካስለቀሱት ጋር በመስቀል በሰቀሉህ፣ በቸነከሩህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በሙሴና በኤልያስ መካከል የመንግሥትህ ግርማ በታወቀ፤ የመለኮትህ ብርሃን ባንጸባረቀ ጊዜ ልደሰት? በቀራንዮ መስቀልን በተሸከምህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ መጻጕዕን ‹‹ኀጢአትህ ተሰረየልህ፤ ተነሥና አልጋህን ተሸከም፤ ሔደህም ወደ ቤት ግባ፤›› (ዮሐ. ፭፥፰) በማለትህ ልደሰት? ሐና እና ቀያፋ ‹‹ደሙ በእኛና በልጆቻችን ይኹን›› ባሉህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችዉን ሴት በልብስህ ጫፍ በማዳንህ ልደሰት? በይሁዳ አማካይነት በሠላሳ ብር በመሸጥህ ላልቅስን? ወይስ ከዓሣ ሆድ ዲናር ያወጣ ዘንድ፣ በአንተ እንዳያጕረመርሙም ለቄሣር ግብር ይሰጥ ዘንድ ጴጥሮስን ባዘዝኸው ጊዜ ልደሰት?

በመስቀል ላይ ሳለህ ‹‹ተጠማሁ›› (ዮሐ. ፲፱፥፳፰) ስትል ላልቅስን? ወይስ በቃና ዘገሊላ ውኃዉን ወይን በማድረግህ ልደሰት? እናትህ እኔ በጉባኤው መካከል የፊቴን መሸፈኛ ገልጬ ስመለከት፣ ዮሐንስ ‹‹ልጅሽ ሞተ›› ባለኝ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ገብርኤል ‹‹ከአንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤›› (ሉቃ. ፩፥፴-፴፫) እያለ በነገረኝ ጊዜ ልደሰት? ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሥጋህን ለመገነዝ ሽቱ ሲገዙ ባየኋቸው ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ምድራዊ ሳሙና እንደዚያ አድርጎ ማጽዳት የማይቻለው ፀዓዳ የኾነ የመንግሥት ልብስህን ባየሁ ጊዜ ልደሰት?

ሥጋህን ለመቅበር አዲስ መቃብር በፈለጉ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ከአራት ቀናት በኋላ አልዓዛርን ከመቃብር ባስነሣኸው ጊዜ (ዮሐ. ፲፩፥፵፫-፵፬) ልደሰት? በአፍህ መራራ ሐሞትን በጨመሩብህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ከሴቶችና ከሕፃናቱ ሌላ በአምስት እንጀራ ለአምስት ሺሕ ሕዝብ በማጥግብህ፣ ተርፎም ዐሥራ ሁለት ቅርጫት በመነሣቱ (ማቴ. ፲፭፥፲፯-፳፩) ልደሰት? በመቃብርህ ላይ ድንጋይ በገጠሙበት ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በአህያና ላም ባሟሟቁህ ጊዜ ላድንቅ? በሙታን መካከል በተኛህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በጦር የወጋህን ሰው የታወረ ዓይኑን በመዳሰስ ባዳንኸው ጊዜ ልደሰት?

በመስቀል በምትጨነቅበት ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ወንበዴዉን ‹‹ዛሬ እውነት እልሃለሁ፤ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ፡፡ ፈጽመህ እመን፤›› (ሉቃ. ፳፫፥፵፫) ባልኸው ጊዜ ልደሰት? የተረገሙ አይሁድን ምን እንላቸዋለን? በዮርዳኖስ ውኃ ዓለሙን የሸፈነዉን ራቀቱን ሰቅለውታልና፡፡ ዓለምን ከኀጢአት ሞት ያዳነ እርሱን ገድለውታልና፡፡

ምንጭ፡- ርቱዐ ሃይማኖት፣ መ/ር ተስፋ ሚካኤል ታከለ፤ ፳፻፬ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ 211-214)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የጌታችን መከራ በሊቃውንት አንደበት

መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም 

‹‹ታመመ፤ ሞትን ከተቀበለበት ከሥጋ ተዋሕዶ በመስቀል ላይ በፈቃዱ ለሥጋውያን ሞተ፣ ባሕርየ መለኮት ሥጋን ተዋሕዶ በማኅፀን ካደረ ጀምሮ ሥጋ ገንዘቡ እንደመሆኑ በሥጋ ይኸንን ሥርዓት ፈጸመ፡፡ ለማይመረመር ለመለኮቱ ባሕርይ እንደሚገባ ደግሞ እርሱ ኅብስት አበርክቶ ዂሉን ያጠግባል፡፡ አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም፤ አያንቀላፋም፤ አይታመምም፤ አይሞትም፤ ሕይወትን ለዂሉ ይሰጣል፡፡ ዳግመኛ በዚያ በሲኦል ተገዝተው ያሉ ነፍሳትን ያድን ዘንድ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወረደ፤ በመለኮቱም ሲኦልን በዘበዘ፤›› (የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቄርሎስ)፡፡

‹‹እጆቹን፤ እግሮቹን በተቸነከረባቸው ችንካሮች መወጋቱንም እናምናለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስእርሱ ደዌያችንን ወሰደሕማማችንንም ተሸከመ፤ እኛን ለማዳን ኃጢአታችንንም ለማስተስረይ መከራ ተቀበለእንዳለ፤ በባሕርዩ ሕማም የሌለበት ሲኾን በሥጋ የታመመ ነው፡፡ በእርሱ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ድነናል፡፡ በተገረፈና በተቸነከረም ጊዜ በመከራው መለኮትን ሕማም ተሰማው የሚል ሰው ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይሁን፤›› (ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስ)፡፡

‹‹እርሱ መቼም መች ከመለኮቱ ሳይለይ የሰውነትን ሥራ ገንዘቡ አደረገ፡፡ ይኸውም መራብ፣ መጠማት፣ መንገድ በመሔድ መድከም፣ በመስቀል ላይ መሰቀል፣ በብረት ችንካር መቸንከር ነው፡፡ በሰውነቱ መቸም መች ሰው ነው፤ በአምላክነቱም ሰውን የፈጠረ ነው፡፡ ነገር ግን ከማይከፈል ተዋሕዶ በኋላ መከፈል የለበትም፡፡ ሰው እንደ መኾኑ ስለ እኛ የታመመው፣ የሞተው እርሱ ነው፡፡ በመለኮቱ ግን መቸም መች አይታመምም፤ አይሞትም፡፡ ሕማምንና ሞትንም አይቀበልም፡፡ በሞቱ ሞትን ያጠፋው እርሱ ነው፡፡ ሲኦልንም የበዘበዘው እርሱ ነው፤›› (የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ዲዮናስዮስ)፡፡

‹‹ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ያን ጊዜ በሲኦል ፈጥኖ ብርሃን ታየ፡፡ ጌታችን በአካለ ሥጋ ያይደለ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ሔደ፡፡ ሲኦል ተነዋወጠች፤ መሠረቶቿም እፈርስ እፈርስ አሉ፡፡ ምድርን ያለ ጊዜዋ እንዳታልፍ ክብርት ደሙን በምድር ላይ አፈሰሰ፡፡ ከኅልፈት ጠበቃት በእርሷ ያለውንም ዂሉ ጠበቀ፡፡ ስለ ፍጥረት ሥጋውን በመስቀል እንደ ተሰቀለ ተወው፡፡ ነፍሱ ግን ወደ ሲኦል ወረደች ከዚያ ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን አዳነች፤ ሲኦልንም በዘበዘች፡፡ ፍጥረትንም ዂሉ ገንዘብ አደረገች፡፡ ሥጋውም በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፤›› (የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ)፡፡

‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፣ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፣ በባሕርዩ ከአባቱ ጋር አንድ የሚኾን፡፡ ዂሉ የተፈጠረበት፤ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የተፈጠረ የሌለ፤ በሰማይ በምድር ያለውም ቢኾን፡፡ እኛን ስለ ማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ኾነ፡፡ የሠላሳ ዘመንልማሳ ኾኖ በጲላጦስ የሹመት ዘመን ስለ እኛ ተሰቀለ፤ ስለ እኛም ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤›› (ሠለስቱ ምእት)፡፡

‹‹ምትሐት ያይደለ በእውነት ተራበ፤ ተጠማ፡፡ ዳግመኛም ከኃጥአን፣ ከመጸብሐን ጋር በላ፤ ጠጣ፡፡ ያቀረቡለትንም በላ፡፡ ራሱን አሳልፎ ለመስቀል ሰጠ፡፡ እጁን፣ እግሩን ተቸነከረ፤ ጐኑን በጦር ተወጋ፡፡ ከእርሱም ቅዱስ ምሥጢር የተገለጠበት ደምና ውኃ ፈሰሰ (ወጣ)›› (ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ)፡፡

‹‹የሚሠዋ በግ እርሱ ነው፤ የሚሠዋ ካህን እርሱ ነው፡፡ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋርም መሥዋዕት የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ በፈቃዱ መከራን በሥጋው የተቀበለ መከራንም የታገሠ እርሱ ነው፡፡ እንደ በግ ሊሠዋ መጣ፤ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደማይናገር አልተናገረም፡፡ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፤›› (ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ)፡፡

‹‹በሥጋ መወለድ፣ በመስቀል መከራ መቀበል፣ መሞት፣ መነሣት፣ ገንዘቡ የኾነ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ በመስቀል ላይ ሳለ ከጥንት ጀምሮ በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤›› (ሰማዕቱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ፊልክስ)፡፡

‹‹ሙሴም ሞትን ያጠፋ ዘንድ አልቻለም፤ እርሱንም ይዞ ገዛው እንጂ፡፡ ከእርሱም በኋላ የተነሡ ነቢያትንም ሞት ገዛቸው እንጂ፡፡ ክርስቶስ ግን በቸርነቱ ለዂሉ ሕይወትን ሰጠ፤›› (የሮማ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ አቡሊዲስ)፡፡

‹‹በመስቀል በሥጋ ተሰቅሎ ሳለ ለመለኮት ከሥጋ መለየት የለበትም፡፡ አንዲት ሰዓትም ቢሆን የዐይን ጥቅሻ ያህል ስንኳ ቢሆንም መለኮት ከትስብእት አልተለየም፣ በመቃብር ውስጥ በሰላም መለኮት ከትስብእት አልተለየም (የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አዮክንድዮስ)፡፡

‹‹ከአብ ጋር አንድ እንደ መኾንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፡፡ ከእኛ ጋር አንድ እንደ መኾንህ በፈቃድህ የሞትህ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፡፡ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፡፡ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፡፡ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፡፡ ከሙታን ጋር የተቈጠርህ አንተ ነህ፡፡ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፡፡ በዘመኑ ዂሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፡፡ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምህ አካላዊ የእግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፤›› (የኪስኪስ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤራቅሊስ)፡፡

‹‹ኃጢአታችንን ለማሥተስረይ በሥጋ እንዲህ ታመመ፤ እንደ ሞተ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደ ገነዙ እናምናለን፤›› (የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ)፡፡

‹‹ነቢይ ዳዊትነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም› አለ፡፡ ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፡፡ የቀና ልቡና ዕውቀት በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ፡፡ ዳዊት እንደ ተናገረው እውነት ኾነ፤ ነፍስ መለኮትን ተዋሕዳ ወደ ሲኦል ወርዳለችና፡፡ ሥጋም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር ሳለ መለኮት ከሥጋ አልተለየም፤ አምላክ ሰው የመኾኑን እውነት ያስረዳ ዘንድ፡፡ መለኮት ነፍስን ተዋሕዶ በአካለ ነፍስ የሲኦል ምሥጢርን ገልጦ ፈጽሟልና በሲኦልም በቁራኝነት አልተያዘምና፤›› (የቆጵሮስ ደሴት ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ)፡፡ 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፣ ሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፯ .ም፡፡