በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
‹ጰራቅሊጦስ› የሚለው ቃል ከሦስቱ አካላት አንዱ የኾነው የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ስም ሲኾን፣ ትርጕሙም በጽርዕ (ግሪክ) ቋንቋ ናዛዚ (የሚናዝዝ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት በወረደበት ዕለት በቤተ ክርስቲያን የሚከበረው ይህ በዓል ‹በዓለ ጰራቅሊጦስ› ወይም ‹በዓለ ጰንጠቆስጤ› በመባል ይታወቃል፡፡ ‹ጰንጠቆስጤ› በግሪክ ቋንቋ በዓለ ኀምሳ፣ የፋሲካ ኀምሳኛ ዕለት፣ በዓለ ሠዊት (የእሸት፣ የመከር በዓል) ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፱፻፮-፱፻፯)፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ አምስት መቶው ባልንጀሮች እና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በኢሩሳሌም ከተማ በአንድነት ኾነው በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ ጌታችን በሚያርግበት ጊዜ ‹‹እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤›› ሲል ለሐዋርያቱ በሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት በዐረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል (ሉቃ. ፳፬፥፵፱)፡፡ ዅሉም በአንድ ቦታ ተሰባስበው ሳሉ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማለዳ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ ወርዶ የነበሩበትን ቤት ሞላው፡፡ ከዚያም የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በዅሉም ላይ አረፉባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ዅላቸውም መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ዅሉ ተናገሩ (ሐዋ.፪፥፩-፬)፡፡
ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን ካህናተ ኦሪት ስለሚቀበሉበት በብሉይ ኪዳን በዓለ ሠዊት ተብሎ ይከበር ነበር፡፡ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉበት በበዓለ ሠዊት ምትክ በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል፡፡ የበዓለ ትንሣኤ መነሻው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ማለትም በግብጽ፣ እስራኤል ከሞት የዳኑበት የመታሰቢያ በዓል እንደ ኾነው ዅሉ፣ ለበዓለ ጰራቅሊጦስም መነሻው ይኸው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ነው፡፡ የአይሁድ ፋሲካ ከተከበረ ከሰባት ሳምንታት በኋላ በኀምሳኛው ቀን የሩቆቹ ከከተሙበት ወጥተው፣ የቅርቦቹ ከተሰባሰቡበት ተገናኝተው ለበዓሉ ፍጻሜ የሚኾነውን በዓለ ሠዊት (የእሸት በዓል) ያከብሩ ነበር፡፡
ከግብጽ እስከ ከነዓን ምድር የደረሰው የእንስሳት መሥዋዕት ሲጠናቀቅ በኀምሳኛው ቀን ይሰባሰብ የነበረው የአይሁድ ጉባኤም መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ዕለት ጀምሮ ተበትኗል፡፡ መሥዋዕተ ኦሪቱ በአማናዊው መሥዋዕት በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንደ ተለወጠ ዅሉ ጉባኤ አይሁድም በኢየሩሳሌም ከተማ በተሰበሰቡ በቅዱሳን ሐዋርያት ጉባኤ ተለውጧል (ተቀይሯል)፡፡ ይህችውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከጉባኤያት ዅሉ ከፍ ከፍ ያለች የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናትና፡፡ ‹‹ከዅሉ በላይ በምትኾን፣ ሐዋርያት በሰበሰቧት፣ በአንዲት፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፤›› እንዳሉ ሠለስቱ ምእት በጸሎተ ሃይማኖት፡፡
ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ተሰባስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዶ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትና ጸጋን አድሏቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላም በአእምሮ ጐልምሰዋል፤ ጥቡዓን (ቈራጦች)፣ ጽኑዓን ኾነዋል፤ ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑበትንና ለሰማዕትነት የሚዘጋጁበትን ልቡና ታድለዋል፡፡ ቀድሞ ይናገሩት ከነበሩት ቋንቋ በተጨማሪ ፸፩ ቋንቋዎች ተገልጠውላቸው ምሥጢራትን በልዩ ልዩ ቋንቋ መተርጐም ጀምረዋል፡፡ ሐዋርያት በየገአሩ ቋንቋ ሲናገሩ የሰሙ በዚያ የነበሩ ሰዎችም በሐዋርያት ተገረሙ፡፡ አንዳንድ የአይሁድ ወገኖች ግን በሐዋርያት ላይ ያዩት ክሥተት አዲስ ነገር ስለኾነባቸው ‹‹ጉሽ ጠጅ ጠጥተው ሰክረው የኾነ ያልኾነውን ይቀባጥራሉ›› እያሉ ሐዋርያትን ያሟቸው ነበር፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም ይህንን ዐሳባቸውን በመንፈስ ቅዱስ አውቆ ‹‹ሰክረዋል የምትሉ እናንተ እንደምትጠራጠሩት አይደለም፡፡ ጊዜው ማለዳ፣ ሰዓቱም ገና ሦስት ሰዓት ነውና፡፡ ዳሩ ግን በነቢዩ ኢዩኤል ‹ከዚህም በኋላ እንዲህ ይኾናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ዅሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ› (ኢዩ.፪፥፳፰) ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ፣ ይህንን ድንቅ ተአምር ያደረገው እናንተ የሰቀላችሁት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤›› በማለት ሰፊ ትምህርተ ወንጌል ሰጥቷቸዋል፡፡
በትምህርቱም ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት፣ ምሳሌ የመሰሉለት አምላክ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን፣ ማረጉንና ዳግም በክብር በምስጋና መጥቶ በሕያዋንና በሙታን ላይ የሚፈረድ መኾኑን ሐዋርያት እንደሚመሰክሩ በአይሁድ ፊት አሰምቶ ተናገረ፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት የተማረኩ አሕዛብም ‹‹ምን እናድርግ?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ ከክፋታቸው ተመልሰው፣ ንስሐ ገብተው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ ነገሯቸዋል፡፡ በዚያችም ሰዓት ሦስት ሺህ ሕዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል (ሐዋ.፪፥፩-፵፩)፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት፡- ‹‹በዚህች ቀን በሦስት ሰዓት ኢየሱስ ክርስቶስ ጰራቅሊጦስን ልኮልናልና በላያችን ኃይልን ሞላ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን እንዳለው በአዲስ ቋንቋ ተናገርን፤›› በማለት በዕለቱ ያዩትንና የተደረገላቸውን፣ እንደዚሁም የበዓሉን ታላቅነት ከመሰከሩ በኋላ ይህንን በዓል ማክበር እንደሚገባ አዝዘዋል፤ በዚህ ወቅት መጾምና ማዘን ተገቢ አለመኾኑንም ተናግረዋል (ዲድስቅልያ ፴፥፴፰-፴፱፤ ፴፩፥፷፱-፸)፡፡
ከዚህ ላይ ማስተዋል የሚገባን ቁም ነገር ‹መንፈስ ቅዱስ ወረደ› ሲባል፣ በሰዉኛ ቋንቋ መንፈስ ቅዱስ ከከፍታ ወደ ዝቅታ፣ ከሩቅ ወደ ቅርብ መምጣቱን ወይም መምጣቱን ለመናገር አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያት ላይ አድሮ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብንና ልዩ ልዩ ጸጋን ማደሉን ለማስረዳት ነው እንጂ፡፡ ይኸውም ሥራዉን በሰው ላይ መግለጡን፣ ጸጋዉንም ማብዛቱን ለማመልከት የሚያገለግል ቋንቋ ነው፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ወረደ የሚለው ትምህርት መንፈስ ቅዱስን በቦታ፣ በጊዜና በወሰን መገደቡን አያመለክትም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በዓለሙ ዅሉ የሞላ ነውና፡፡ በሰው ላይ አድሮ ጥበብን ሲገልጥ ግን ‹ሞላ፤ አደረ፤ ወረደ› ተብሎ ይነገራል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለጊዜው ለሐዋርያት ቢሰጥም፣ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይገደብ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ በምእመናን ላይም አድሮ ይኖራልና፡፡
በዓለ ትንሣኤውን በደስታ እንድናሳልፍ ፈቅዶ እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ጠበቀን፣ አሁን ደግሞ በጾም፣ በጸሎት ኾነን እርሱን የምናመሰግንበትን ወቅት ስላመጣልን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ለዘለዓለሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡
ምንጮች፡–
- መዝገበ ታሪክ፣ ክፍል ፪፤ መ/ር ኅሩይ ኤርምያስ፤ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፹፬-፹፭፡፡
- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፰ ቀን፡፡
- መጽሐፈ ግጻዌ፡፡
- ማኅቶተ ዘመን፣ መ/ር በሙሉ አስፋው፤ ፳፻፩ ዓ.ም፤ ገጽ ፻፺፭-፪፻፬፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡