ዐቢይ ጾም

በሊቀ ጉባኤ ቀለመወርቅ ውብነህ

የካቲት ፳፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጾም ማለት መተው መከልከል ማለት ነው፡፡ ጾም በእግዚአብሐር የተቀደሰ ተግባር ስለኾነ ወደ ቅድስና ጎዳና የሚመራ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ጾመን ከአምላካችን ጋር ኅብረት እንዲኖረን፤ መንፈሳዊ ኃይል እንድናገኝ ታደርጋለች፡፡ በጾም ወራት ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይኾን ዐይን ክፉ ከማየት፣ አንደበት ክፉ ከመናገር፣ ጆሮ ክፉ ከመስማት መቆጠብ እንደሚገባው በቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎአል፡፡ ‹‹ይጹም ዐይን ይጹም ልሳን እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ኀሡም በተፋቅሮ›› እንዲል ቅዱስ ያሬድ /ጾመ ድጓ/፡፡ በጾም ወራት ላምሮት፣ ለቅንጦት የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የኾኑ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ፣ ሥጋንና የሚያሰክሩ መጠጦችን /ዳን.፲፥፪-፫/፣ ቅቤና ወተትን ከመጠቀም መታቀብ እንደሚገባ ታዟል /መዝ.፻፰፥፳፬፣ ፩ቆሮ.፯፥፭፤ ፪ቆሮ.፮፥፮/፡፡

በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ ነበረው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር በሚገናኙበት ወራት እህልና ውኃ በአፋቸው አይገባም ነበር /ዘፀ.፴፬፥፳፰/፡፡ አስቴር አስቀድማ ሦስት ቀን ጾማ ጸልያ በእስራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች /አስቴር ፬፥፲፭-፲፮/፡፡ በዘመኑ በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰውም ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር  /ዮናስ ፪፥፯-፲/፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይኾን ራሱ ክርስቶስ የሠራው ሕግ ነው /ማቴ.፬፥፪፤ ሉቃ.፬፥፪/፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም በየጊዜው ከመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾም በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር /ሐዋ.፲፫፥፪/፡፡ ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስትም የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነው /ሐዋ.፲፫፥፫፤ ፲፬፥፳፫/፡፡ እንደ ቆርነሌዎስ ያሉ ምእመናን ያላሰቡትን ክብር ያዩና ያገኙ የነበረውም በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን በመማጸን ነው /ሐዋ.፲፥፴/፡፡

ዐቢይ ጾም ጌታችን ከተጠመቀ በኋላ ዐርባ ቀን የጾመው፤ እኛም እንድንጾማቸው በቤተ ክርስቲያናችን ከታዘዝናቸው ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ ነው፡፡ ምእመናን ጌታችን ያደረገውን ምሳሌ ተከትለን ጾሙን በየዓመቱ እንጾመዋለን፡፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት (፶፭ ቀኖች) አሉት፡፡ በውስጡ ስምንት ቅዳሜዎች፣ ሰባት እሑዶች ይገኛሉ፡፡ ይኸውም ዐሥራ አምስት ቀን ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቀናት ከጥሉላት እንጂ ከእኽል ውኃ ስለማይጦሙ የጦሙ ወራት ዐርባ ቀን ብቻ ይኾናል፡፡

ጾሙ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፤ አንደኛ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው በመኾኑ፣ እንደዚሁም ‹‹ዐቢይ እግዚአብሔር ወዐቢይ ኀይሉ ዐቢይ እግዚአብሔር ወብዙኅ አኰቴቱ›› /መዝ.፵፯፥፩፤ መዝ.፻፵፮፥፭/ የተባለ ጌታችን የጾመው ጾም ስለኾነ ‹‹ዐቢይ ጾም›› ይባላል፡፡ ሁለተኛ ‹‹ሁዳዴ ጾም›› ይባላል፡፡ ይህም የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥራ ሁዳድ ስለሚባል ሲኾን፣ ዐቢይ ጾምም ከአጽዋማት ዅሉ ብዙ ቀናት ስለሚጾምና ኃያሉ አምላካችን ስለጾመው ነው /አሞ.፯፥፩/፡፡ ሦስተኛ ‹‹በአተ ጾም›› ይባላል፡፡ የጾም መግቢያ፣ መባቻ ማለት ነው፡፡ አራተኛ ‹‹ጾመ ዐርባ›› ይባላል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ፵ ቀን ስለኾነ /ማቴ.፬፥፩/፡፡ አምስተኛ ‹‹ጾመ ኢየሱስ›› ይባላል፡፡ ጌታችን እርሱ ጾሞ፣ ጹሙ ብሎ ስላዘዘን፡፡ ስድስተኛ ‹‹ጾመ ሙሴ›› ይባላል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ጾመ ድጓው ‹‹ከመዝ ይቤ ሙሴ እስመ ለዓለም ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት›› እያለ ስለዘመረ /የሰኞ ዕዝል/፡፡

ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ዘወረደ (ዘመነ አዳም)›› ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም አምላካችን አዳምንና ልጆቹን ከሞት ለማዳን ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መኾኑንና የፈጸመውን የማዳን ሥራ ያመለክታል፡፡ ‹‹ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም›› ካለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሣት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘየሐዩ በቃሉ›› በማለት በጾመ ድጓው መጀመሪያ ላይ ይህን ዕለት ገልጾታል፡፡ ትርጕሙም ‹‹አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አምላክ አይሁድ ሰቀሉት፤ የሰማይ ሥልጣን ያለው የዅሉ ጌታ እንደኾነም ምንም አላወቁም›› ማለት ነው፡፡ ይህም ድርሰት በቤተ ክርስቲያናችን የጾም መጀመሪያ የኾነው ዕለተ ሰንበት ዋዜማ፣ መግቢያ (መሐትው) ኾኖ ከዋዜማ በፊት ምንጊዜም በየዓመቱ ይቆማል፤ ይዘመራል፤ ይመሰገናል፡፡

በዚህ ሳምንት በተለይም እሑድና ሰኞ የሚነገሩት ውዳሴያት ከመጻሕፍተ ኦሪትና ነቢያት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሁለተኛም ሳምንቱ ‹‹ሙሴኒ›› በመባል ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ለማዳን ከሰማይ መውረዱንና በመስቀል መሰቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ጾመ ሕርቃል›› ይባላል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊየስ) የቤዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው፣ የጌታችንን መስቀል ማርከው ወስደውት ነበር፡፡ እርሱ ወደ ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡

ሕርቃል ከፋርሶች ጋር ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ‹‹ነፍስ የገደለ ሰው እስከ ዕድሜ ልኩ ይጹም›› ብለው ሥርዓት ሠርተዋልና ጾሙን ፈርቶ ስለነበር በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን አሳቡን ደግፈው ‹‹አንተ ጠላታችንን አጥፋልን፤ መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ ሰው ዕድሜ ቢበዛ ሰባ፣ ሰማንያ ዓመት ነው፡፡ ጾሙን አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እኛ እንጾምልሃለን›› ብለው ጾመውለታል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጾመውታል ብለው ሥርዓት አድርገው በዓመት በዐቢይ ጾም መጀመሪያ ላይ ጾመ ሕርቃል እያሉ የሚጾሙት ኾነዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ሥርዓት መሠረት በማድረግ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስም ሰይማ እንዲጾም አድርጋለች (የመጋቢት ፲ ቀን ስንክሳርን ይመልከቱ)፡፡

በቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ ዘወረደ እየተባለ የሚታወቀው፣ በጾመ ዐርባው ወቅት በተለይም በመጀመሪያው ሳምንት የሚገኘው ድርሰት በነግህ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንደዚሁም ቅዳሜና እሑድ በሌሊት የሚዘመር ነው፡፡ በውስጡም የያዘው ፍሬ ሐሳብ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና የፍቅርን ጠቃሚነት አጕልቶ የሚያስተምር ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ጾመ ድጓው ‹‹አዘዞ እግዚአብሔር ለሙሴ ወይቤሎ ሰብእከ ወላህምከ ወኵሉ ቤትከ ያዕርፉ በሰንበት፤ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝብህ የከብትህ መንጋህ ቤተሰብህ ዅሉ በሰንበት ቀን ከድካማቸው ይረፉ በማለት አዘዘው፤›› በማለት ሰንበት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይኾን፣ ሕይወት ላለው ነገር ዅሉ ጸጥታና ሰላም የሰፈነባት የዕረፍት ቀን ስለመኾኗ ተናግሯል /ዘፀ.፳፥፲፤ ፳፫፥፲፪/፡፡ በዚህም ወቅቱ ‹‹ዘመነ ጾም›› ወይም ‹‹ጾመ ሙሴ›› ይባላል፡፡

በአጠቃላይ ጾምን መጾም የፈቃድ ብቻ ሳይኾን የትእዛዝም ነው፡፡ ነቢዩ ኢዩኤል ‹‹ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምሕላ …፤ ጾምን ያዙአጽኑ፡፡ ምሕላንም ዐውጁ፡፡ ሸማግሌዎቹን ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ኾናችሁ ወደ እግዚአብሔር ጩኹ (ለምኑ)፤›› ብሏል /ኢዩ.፩፥፲፩፤ ፪፥፲፪፤ ፲፪፥፲፭-፲፮/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ወኩኑ ላእካነ ለእግዚአብሔር በጾም ወበንጽሕ፤ በጾም፣ በንጽሕና ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤›› ብሏል /፪ቆሮ.፮፥፬-፮/፡፡ ጾም ባያስፈልግ ኖሮ ጌታችን ‹‹በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትኹኑ … ስለ ጽድቅ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን ክብራን ናቸው፤›› ባላለም ነበር /ማቴ.፭፥፮-፲፮/፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ‹‹ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅባት በማጣት ከሳ፤›› /መዝ.፻፰፥፳፬/ ማለቱ የጾምን አስፈላጊነት ያስረዳል /ዳን. ፱፥፫-፬፤ ፲፬፥፭/፡፡ በቁራኝነት አብሮ የሚኖር መንፈስ ርኩስ (ሰይጣን) እንኳን በጾም የሚወገድ መኾኑን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሮአል /ማቴ.፲፯፥፳፩፤ ማር.፱፥፪/፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ሙሽራውን ከእነሱ ለይተው የሚወስዱበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ያን ጊዜ ይጾማሉ፤›› ያለውን የጌታን ቃል መሠረት በማድረግ ጌታችን ሞቶ ከተነሣ እና ካረገ በኋላ ጾመዋል፤ የጾምንም ሕግ ሠርተዋል /ሐዋ.፲፫፥፫/፡፡ ሠለስቱ ምዕትም ‹‹ሐዋርያት የጾሙትንና እንዲጾም የወሰኑትን መጾም ይገባል›› ብለው አጽዋማትን እንድንጾም መወሰናቸው ይህን የጌታችንን ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠራዔ ሕግ እንደመኾኑ ዐርባ ቀን ዐርባ ሌሊት ጾሞ እንጂ ዝም ብሎ ጾሙ አላለንም፡፡ ስለዚህ ጾም ትእዛዝ (ሕግ) መኾኑን ተገንዝበን ዅላችንም መጾም አለብን፡፡ ጾመን ለማበርከት ያብቃን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ይቅርታ ልትጠየቅ እንደሚገባ ተገለጸ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዐድዋ ጦርነት ጊዜ በአገሩ ላይ የደረሰውን ሽንፈት ለመበቀል ሲል የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ላይ ላደረሰው ቃጠሎ፤ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአባቶች ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና መነኮሳት እንደዚሁም በምእመናን ላይ በግፍ ለፈጸመው ጭፍጨፋ የጣልያን መንግሥት እና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን (ቫቲካን) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እና ኢትዮጵያን ይቅርታ መጠየቅ፤ የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት ከየገዳማቱና አድባራቱ የዘረፋቸውን ንዋያተ ቅድሳት፣ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን እና አገራዊ ቅርሶቻችንንም መመለስ እንደሚገባቸው ተገለጸ፡፡

img_0725

በስተቀኝ እና በስተግራ አቅጣጫ፡- ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎቹ ቀሲስ ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል እና ቀሲስ ኃይለ ኢየሱስ አለባቸው፤ ከመካከል፡- የጥናቶቹ አወያይ አቶ መስፍን መሰለ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ባህሎች እና ቋንቋዎች አካዳሚ ተመራማሪና የፎክሎር መምህር)

ይህ ሐሳብ የተገለጸው በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል አዘጋጅነት የማኅበሩ አባላት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተማሪዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በአጠቃላይ በርከት ያሉ ምእመናንና ምእመናት በታደሙበት በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አዳራሽ የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በተካሔደው የጥናት መርሐ ግብር ላይ ሲኾን ፣ በዕለቱ ‹‹በኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ እና የሮሙ ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ አቋም›› እና ‹‹ቅኔ ዘዝክረ ዐድዋ›› በሚሉ አርእስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፤ በጥናቶቹ ዙሪያ ከታዳሚዎች ለተነሡ ጥያቄዎችም በጥናት አቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

img_0723

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ አባቶች እና ወንድሞች በከፊል

‹‹በኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ እና የሮሙ ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ አቋም›› የሚለው ርእሰ ጉዳይ አቅራቢ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ፋሽስት ኢጣልያ አገራችን ኢትዮጵያን በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም በወረረበት ወቅት የጊዜው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ወረራውን እና በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን ግፍ በዝምታ መመልከታቸው ተገቢ አለመኾኑን አስታውሰው ፖፑ ወረራውን ሊያወግዙ ያልቻሉበት ምክንያትም፡- በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በኢጣልያ መንግሥት መካከል ጥላቻ እንዳይፈጠር በመስጋታቸው፤ በዘመኑ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በካህናቱ መካከል ከባድ ተቃውሞ ስለነበር በመካከላቸው ግጭት እንዳይፈጠር በማሰባቸው እንደኾነና ዋነኛው ምክንያት ግን የኢጣልያ ኢትዮጵያን መውረር የካቶሊክ ሃይማኖትን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት መልካም ዕድል ይፈጥራል ብለው በማመናቸው እንደኾነ በጥናታቸው አትተዋል፡፡

img_0729

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል (በቤተ ክርስቲያናችን በምርምር ሥራ እና በልዩ ልዩ ሓላፊነት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ሲሰጡ የኖሩ፣ አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙ አባት)

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ አያይዘውም ፖፑ የወቅቱ የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት ‹‹በእግዚአብሔር ፈቃድ የተነሣ፣ በሊበራሊዝም አስተሳሰብ ያልተሞኘ መንግሥት ነው›› ብለው ያምኑ እንደነበር፤ በወቅቱ ስለወረራው ሲጠየቁ ለሚድያዎች የሰጡት ምላሽም ፖፑ ለጦርነቱ የነበራቸውን ጥሩ አቋም እንደሚያመለክት፣ ለአብነትም በአንድ ወቅት ‹‹ራስን የመከላከል ጦርነት ነው›› ሲሉ ስለ ወረራው አስፈላጊነት እንደተናገሩ፤ የአገሪቱ መንግሥት ኢትዮጵያን ሊወርር ሲዘጋጅ ሙሶሎኒ በሮም ከተማ ንግግር በሚያደርግበት ጊዜ መላው የሮም ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ደወሎች ለረጅም ሰዓት ሲደወሉ እንደነበር፤ ይህም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያ በኢጣልያ እንድትወረር የነበራትን ፍላጎት እንደሚያመለክት ባለጥናቱ ጠቁመዋል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ወረራውን በገንዘብ ደግፋለች ተብላ ቤተ ክርስቲያኗ ተከሳ እንደነበር ያወሱት ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ፣ ፋሽስት ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላም ‹‹እጅግ የሚያስደስት ድል›› በማለት ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ ጦርነቱን ማድነቃቸው ፖፑ የፋሽስት መንግሥት እና የወረራው ደጋፊ እንደነበሩ አንዱ ማሳያ መኾኑን ልዩ ልዩ ምንጮችን ዋቢ አድርገው የፖፑን አቋም ለጉባኤው አስረድተዋል፡፡

img_0724

የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ እናቶች እና እኅቶች በከፊል

የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለፋሽስቱ ሠራዊት በስውር የሞራል ድጋፍ ከማድረጓ ባሻገር የኢጣልያ ፋሽስት መንግሥት በየጊዜው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አድባራትና ገዳማት ላይ ቃጠሎና የቅርስ ዘረፋ ሲያካሒድ፤ እንደዚሁም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን እና ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን በግፍ ሲረሽን፤ በአባቶች ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ምእመናን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈጽም በዝምታ መመልከቷ (ድርጊቱን አለማውገዟ) የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የወረራው ደጋፊ እንደነበረች የሚያስገነዝብ ሌላኛው ነጥብ መኾኑን በመጥቀስ ለዚህ ዅሉ በደልም የጣልያን መንግሥት እና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን (ቫቲካን) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ፤ ለጥፋታቸውም ተመጣጣኝ ካሣ መክፈል፤ ከየገዳማቱና አድባራቱ የተዘረፉ ንዋያተ ቅድሳትን፣ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትን እና አገራዊ ቅርሶቻችንንም ለአገራችን መመለስ እንደሚገባቸው ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ሐሳብ መሳካትም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያደርጉ በማሳሰብ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አጠቃለዋል፡፡

img_0735

ቀሲስ ኃይለ ኢየሱስ አለባቸው (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ፫ኛ ዓመት የፒ ኤች ዲ ተማሪ)

‹‹ቅኔ ዘዝክረ ዐድዋ›› የሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ቀሲስ ኃይለ ኢየሱስ አለባቸው ደግሞ ከአድዋ ጦርነት በፊት፣ በጦርነቱ ወቅት እና ከድሉ በኋላ የተደረጉ አንዳንድ ጥንታውያን የግእዝ ቅኔያትን ትርጕምና ምሥጢር ከታሪክ መጻሕፍት ጋር አነጻጽረው በማቅረብ በቅኔአቸው ንጉሡንና ሠራዊቱን በማበረታታት ለአገራችን ድል ማግኘት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋጽዖ በጥናታቸው አተተዋል፡፡

አባቶቻችን በዐድዋው ጦርነት ኢጣልያን ድል ማድረግ የተቻላቸው በወታደር እና በጦር መሣሪያ ብዛት ሳይኾን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳዒነት መኾኑን ያስታወሱት ቀሲስ ኃይለ ኢየሱስ ‹‹አዲስ ቅኔ መቀኘት ባንችልም እንኳን አባቶቻችን የፈጸሙትን የዐርበኝነትና የድል አድራጊነት ታሪክ እያነበብን የመወያያ አጀንዳችን ልናደርገው ይገባል›› ሲሉ ትውልዱ የአባቶቹን ውለታ መርሳት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም በጥናታዊ ጽሑፎቹ ላይ ውይይት ከተደረገ እና ከመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች ለተነሡ ጥያቄዎች በጥናት አቅራቢዎቹ ምላሽ ከተሰጠ በኋላ መርሐ ግብሩ በአባቶች ጸሎት ተፈጽሟል፡፡

የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ልዩ ዐውደ ጥናት አካሔደ

te

በደመላሽ ኃይለማርያም

የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት የምሥረታ ታሪክ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚነሣው አንጋፋው የ‹‹ተምሮ ማስተማር›› ሰንበት ትምህርት ቤት በሚያዝያ ወር ፳፻፱ ዓ.ም የሚከበረውን ስድሳኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የሰንበት ትምህርት ቤቱ አዳራሽ የካቲት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ልዩ ዐውደ ጥናት አካሔደ፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፤ መጋቤ ኅሩያን አባ ኤልያስ በልሁ የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ጥሪ የተደረገላቸው ምሁራንና እንግዶች፤ የልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች፤ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች፤ ቀደምት የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባላት እና በርካታ ምእመናን ታድመዋል፡፡ በዐውደ ጥናቱም ‹‹የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አመሠራረትና አገልግሎት›› እና ‹‹የአማርኛ መዝሙራት ታሪካዊ ዕድገትና ተግዳሮቶች›› በሚሉ አርእስት የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በጥናቶቹ ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችም በአቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

02

የሰንበት ትምህርቱ መስማት የተሳናቸው መዘምራን በምልክት ቋንቋ መዝሙር ሲያቀርቡ

‹‹የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አመሠራረትና አገልግሎት›› የሚለው ጥናት አቅራቢ ኢንጂነር ከፈለኝ ኃይሉ የተምሮ ማስተማርን የአመሠራረት ታሪክ እና አገልግሎት በተለይ ከ፲፱፻፴፱ — ፲፱፻፵፱ ዓ.ም የነበረውን የሰንበት ት/ቤቱን እንቅስቃሴ በጥናታቸው ዳሰዋል፡፡ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በተፈሪ መኮንን የወንዶች ትምህርት ቤት ተማሪዎች በመነጨ ‹‹ሰዎችን ለማስታረቅ›› የሚል በጎ ሐሳብ የ‹‹ተምሮ ማስተማር›› ሰንበት ት/ቤት እንደተመሠረተ ኢንጂነር ከፈለኝ ገልጸው ለምሥረታውም ዐሥራ ሁለት ወንድሞች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪ በቀድሞ ስማቸው አባ መዓዛ ይባሉ የነበሩት በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ድርሻ የላቀ እንደነበርም ኢንጂነሩ በጥናታቸው አብራርተዋል፡፡

03

ዲ/ን ዘውዱ በላይ (አወያይ) እና ኢንጂነር ከፈለኝ ኃይሉ (ጥናት አቅራቢ)

ከዅሉም በተለየ በንጉሡ ዘመን በቤተ ክርስቲያንና በማኅበራዊ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩትና በ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ያለ በቂ ምክንያት በደርግ ባለሥልጣናት በግፍ የተገደሉት አቶ አበበ ከበደ ለሰንበት ት/ቤቱ መመሥረትና መጽናት ግንባር ቀደሙን ቦታ እንደሚወስዱ ጥናት አቅራቢው አስገንዝበዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ በ፲፱፻፵፱ ዓ.ም ገብረ ጊዮርጊስ አጋሼ በተባሉ አባት የተሰጠው ‹‹የተምሮ ማስተማር ማኅበር›› የሚለው ስያሜ በ፲፱፻፶ ዓ.ም በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደጸደቀና ከጊዜ በኋላም ‹‹የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት›› የሚለው ስሙ በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና እንዳገኘ ያስታወሱት የጥናቱ አቅራቢ የሰንበት ት/ቤቱ መመሥረት ወጣቶች ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በር ከመክፈቱ ባሻገር ሰባክያነ ወንጌል እንዲበራከቱና ምእመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ በጥናታቸው ማጠቃለያም ሰንበት ት/ቤቱ እንዲመሠረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱትን እንደ አቶ አበበ ከበደ ያሉ ባለውለታዎችን በጸሎት መዘከርና በስማቸው መታሰቢያዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ኢንጂነር ከፈለኝ አሳስበዋል፡፡

01

ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ

‹‹የአማርኛ መዝሙራት ታሪካዊ ዕድገትና ተግዳሮቶች›› የሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ በበኩላቸው የ‹‹ተምሮ ማስተማር›› ሰንበት ት/ቤት የምሥረታ እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ፲፱፻፴፭ ዓ.ም አንሥቶ ለሰባ ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠቱን በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡ የአማርኛ መዝሙራት መዘጋጀት የጀመሩት ሰንበት ት/ቤቱ በተመሠረተበት ወቅት አካባቢ መኾኑን ያስታወሱት ጥናት አቅራቢው በወቅቱ መዝሙራቱ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ በቀጥታ ተተርጕመው ዜማቸውም ሳይቀየር ይቀርቡ እንደነበር እና ይህም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የኾኑ መዝሙራት እንዲበራከቱ በር መክፈቱን በጥናታቸው አመላክተዋል፡፡

ያሬዳዊ ይዘታቸውን የጠበቁ የአማርኛ መዝሙራት እንደ ተምሮ ማስተማር ባሉ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በየዘመናቱ በጥራዝ መልክ እየታተሙ ለዛሬው ትውልድ መድረሳችውንም አስገንዝበዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የሚዘመሩ ጥቂት የማይባሉ መዝሙራት በሥርዓት ስለማይዘጋጁ ካሉባቸው የዘይቤ፣ የቃላት አጠቃቀም፣ የቀለም እና ሐረግ ምጣኔ ጉድለቶች ባሻገር ምሥጢርን እና ይዘትን፣ እንደዚሁም ያሬዳዊ ዜማን ከመጠበቅ አኳያም ብዙ መሥፈርቶችን እንደማያሟሉ የገለጹት ቀሲስ ሰሎሞን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የሚቀርቡ መዝሙራት ዅሉ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተመዝነውና ተገምግመው በተገቢው ዅኔታና በትክክለኛው መሥፈርት ሊዘጋጁ ይገባል በማለት ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አጠቃለዋል፡፡

በዚህ ዐውደ ጥናት ሊስተናገዱ መርሐ ግብር ከተያዘላቸው ጥናታዊ ጽሑፎች መካከል በሰዓት እጥረት ምክንያት ያልቀረበው ‹‹መገናኛ ብዙኃንና የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት›› የሚለው የዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ (በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጥንታውያት መዛግብት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር) ጥናት በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ መርሐ ግብር እንደሚቀርብ የሰንበት ት/ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዲ/ን ዘውዱ በላይ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ቃል ገብተዋል፡፡

temro

ከዚህ መርሐ ግብር በተጨማሪም ከሚያዝያ ፲፭ — ፳፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በዐውደ ርዕይ እና በልዩ ልዩ መንፈሳውያን መርሐ ግብራት የሰንበት ት/ቤቱ ስድሳኛ ዓመት ምሥረታ በዓል እንደሚዘከር ከሰንበት ት/ቤቱ ጽ/ቤት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ለብዙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ለማኅበረ ቅዱሳንና ጽርሐ ጽዮን የአንድነት ኑሮ ማኅበር መመሥረት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው ይህ አንጋፋ ሰንበት ትምህርት ቤት በስልሳ ዓመት የአገልግሎት ጉዞው ውስጥ ያበረከተውን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያሳዩ ተጨማሪ የዳሰሳ ጥናቶች መደረግ እንደሚገባቸው በዐውደ ጥናቱ የተገኙ አባቶችና ምሁራን ጠቁመዋል፡፡ በመጨረሻም በአባቶች ጸሎት ጠዋት የተከፈተው ይህ የዐውደ ጥናት መርሐ ግብር በአባቶች ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ አመሻሽ ላይ ተፈጽሟል፡፡